በላ ልበልሃ

የኢትዮጵና የግብጽ ግንኙነት በውሃ መነጽር ሲታይ

የኢትዮጵያና የግብጽ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የተቃኙባቸውን አቅጣጫዎች ለመረዳት በርካታ አንጻሮችን መፈተሽ ያስፈልግ ይሆናል። ፖለቲካዊ መልክዓ-ምድር፣ መንግስታዊና አገራዊ ፍላጎቶች፣ አህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ግንኙነቶች፣ እንዲሁም ሃይማኖት፣ ባህልና ስነ-ልቦና ከመመልከቻ አንጻሮቻችን ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። የሁለቱን አገሮች ግንኙነቶችና የውጭ ፖሊሲዎች በተመለከተ ግን ሁሉንም የማስተሳሰር አቅም ያለው አንድ ቁልፍ ነገር አለ። እሱም ውሃ ነው። ውሃ!!!

ውሃ፣ ተስፋና ሥጋት

በዓለማችን ሁለት መቶ ያህል ሉዓላዊ መንግሥታት ፖለቲካዊ ድንበራቸውን አካለው ቢኖሩም ብዙዎቹ አገሮች ወሰን በማይገድባቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተቆራኝተው ከጋራ ወንዞች እየጠጡ፣ በጋራ ወንዞች እየዋኙ፣ የጋራ ወንዞች እየቀዘፉ ይኖራሉ። ሁለንተናቸውን በውሃና በወንዝ አቆራኝተው ይጓዛሉ። በጋራ ወንዞቻቸው ህልውናቸው፣ ታሪኮቻቸው፣ ስነ-ልቦናቸው፣ ባህሎቻቸውና ሥልጣኔዎቻቸው ተሳስረዋል። ተረቶቻቸው፣ ዜማዎቻቸውና ቅኔዎቻቸው በሚታዩም በማይታዩም ድሮች ተሳስረዋል። ፍቅራቸው፣ ጠባቸው፣ ተስፋዎቻቸውና ስጋቶቻቸው፣ ምርቃቶቻቸውና እርግማኖቻቸው፣ ህልሞቻቸውና ቅዠቶቻቸው፣ ወጎቻቸውና ሙግቶቻቸው ከጋራ ወንዞቻቸው ጋር ተቆራኝተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከውሃ ባህሪ ይመነጫል። ውሃ ህይወት ነው። የህይወት ምንጭ ነው። ውሃ የህይወት፣ የልማትና የሥልጣኔ መሰረት ነው። ውሃ ሁሉም ነገር ነው ማለት ይቻላል። ውሃ ያለው ሁሉም አለው ማለትም እውነት ነው። ነገር ግን ውሃ ለሁሉም የተረፈና የተትረፈረፈ ሃብት አይደለም። በዓለማችን ውሃ ያላቸው አገሮች እንዳሉ ሁሉ የሌላቸውም በርካታ ናቸው። ሁሉም አገሮች እኩል አልታደሉም። ስለሆነም ተፈጥሮ ራሱን በራሱ ሲያስተካክል ውሃን ግድብ የማያቆመው ሁሌ ተጓዥ መንገደኛ አድርጎ ፈጠረው። ከተራራ ላይ መንጭቶ፣ እዚህ ሞልቶ፣ በተዳፋቱ ሁሉ እየተጓዘ በረሃውን እያጠጣ፣ ያልመነጨበትን አገር እያለመለመ፣ ከውቅያኖስ ይቀላቀላል። አልያም እንደ አዋሽ ወንዝ ወደ ከርሰ-ምድር ሰርጎ ይገባል። ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል›› ማለትም የውሃን የቀን ከሌት ጉዞና አገር አቋርጦ መዝለቅ ይጠቁማል። ዘመን በአንድ መስመር (በዓባይ ውሀ) ብልህና ታታሪ ያደረጋቸው የዛሬ ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ማደሪያ ጉባ ላይ ግድብ መስራት ጀመሩ። የአብራካቸውን ክፋይ ልጃቸውን፣ የባንክና የኢንሹራስ ድርጅቶቻቸውን ‹‹አባይ›› ብለው መሰየም የሚቀናቸው ኢትዮጵያውያን፤ አዲሱን ግድባቸውን ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ›› አሉት። የአባይ ጉዳይ ቀድሞውኑ የሁለቱ አገሮች የመተያያ ተረኮች መነሻ ቢሆንም፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የአባይ የውሃ ዲፕሎማሲ ውዝግብ፣ ድርድርና እሰጥ አገባ በተካረረ ደረጃ ቀጥሎ አንድ አስርት ሊሞላው ተቃርቧል። በዚህ ሂደት ውስጥ ‹‹የውሃ ምንጭ ካልሆኑ›› አገሮች አንዷ ግብጽ፤ ምድቧ ውሃ ከሌላቸው አገሮች ተርታ ቢሆንም፤ ያቺ የአባይ መንገድ መቋጫ የሆነችው አገር በቀጭኑ የሜድቲራኒያን ባህር ሰርጥ ዳርቻ በአማካይ በዓመት ከ20 ሚሊ ሜትር (ወይም 0.79 ኢንች) እስከ 200 ሚሊ ሜትር (ወይም 7.87 ኢንች) ካፍያ ታገኛለች። ይህ ካፍያ የግብጽን በረሀ ሊያለማ ይቅርና የላይኛውን አቧራ ሊያርስ አይችልም። ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎችም ከሰማይ የሚወርድ አንድ ጠብታ ውሃ አያገኙም። ስለዚህም ግብጽ ከሰማይዋ ዘንቦ፣ ከከርሰ-ምድሯ መንጭቶ የሚፈስስ አንድም ወንዝ የላትም። ይህ እውነታ ከኢትዮጵያ መንጭቶ ወደ ግብጽ መሬት የሚደርሰውን የውሃ ሀብት የሁለቱ አገሮች ህልምና ቅዠት፣ ተስፋና ስጋት ያደርገዋል፡፡

ውሀ ያቆመ ትውልድ

አንዴ ስለ ኡማ ወንዝ (የ‹‹ኦሞ›› ወንዝ ትክክለኛ አካባቢያዊ መጠሪያ) ተፋሰስ በመስክ ቃለመጠይቅ ያደረግኩላቸው አንድ አዛውንት የኡማን ግድብ በማየት ተገርመው ሲናገሩ ‹‹በንጉስ ቁም ሲባል እንኳን ሰው ውሀ ይቆማል ሲባል ሰምተን እንዴት ይቻላል? ብለን እንሳለቅ ነበር። ለካስ አባባሉ ትንቢት ኖሯል። አሁን ነው ነገሩ የገባን። ትንቢቱ ግድብ ነው። ግድብ የውሀ ንጉስ ነው፤ ድንበር የማያቆመውን ውሀ የሚያቆም›› ብለዋል። አዛውንቱ በኡማ ወንዝ ላይ የተገነባውን ጊቤ ሶስት ግድብ አይተው እየተገረሙ ወደ ሰማይ አንጋጥጠው ‹‹ሃይ ጠሶ›› አሉ፤ (‹ወይ እግዝአብሔር!!› ማለት ነው) ‹‹የዕድሜ ብዛት የፍልፈል ዥንጉርጉር ያሳያል” አሉ። ዘመን ከትውልድ ጋር ሲያልፍ፣ ማህበረሰባችን የመልማት ፍላጎቱ እየበረታ መጥቶ የተፈጥሮ ስጦታዎቹን መመርመር ሲጀምር፣ ወንዞቹን እየዘፈነ መሸኘቱን ያቆምና ውሃዎቹን ለማቆም ማሰብ ይጀምራል። ‹‹የውሃን ጥቅም ከሁሉም እንስሳት ዘግይቶ ያወቀው አሳ ነው›› እንደሚባለው ኢትዮጵያም ከራስጌዉ የአባይ ውሃ ተጋሪዎቿ አንጻር ለአባይ ውሃ ተግባራዊ ጠቀሜታ ትኩረት የሰጠች የመጨረሻዋ አገር ነች ማለት ይቻላል። ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች በፈጠሯቸው ክስተቶች ሳቢያ አገሪቱ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በወንዞቿ ለመጠቀም መንቀሳቀስ ጀምራለች። ዛሬ አባይ፣ ኡማና ሌሎችም የአገሪቱ ወንዞች እንዲቆሙ የታዘዙ፣ ለዚች አገር ልማት የቆሙ ወንዞች ሆነዋል። ይህም ትውልድ ውሃ ያቆመ ትውልድ ነው፡፡

የአባይ ውለታና ውልታ

ውሀን ማስቆም ቢቻልም ጨርሶ ማስቆም አይቻልም። የአባይንም ውሀ ጨርሶ ማቆም አይቻልም። አባይ በትውልድ አገሩ በተሰራለት ግድብ ታቅቦ ቢያዝም ከግድቡ ተርፎ ጉዞውን ይቀጥላል። ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች መፍሰሱን ይቀጥላል። ህይወት እየሰጠ ይጓዛል። ሱዳንን ያጠጣል። ህይወት እየሰጠ ይወርዳል። መላ ግብጽን እንደ አክርማ ሰንጥቆ በረሃውን ያለማልማል። አባይ ለግብጾች በእርግጥ ህይወት ነው። ጥንታውያኑ የዚያች አገር ሰዎች ያመልኩታል። ያወድሱታል። በኢትዮጵያ ተራሮች ላይ የሚጥለው ዶፍ አትረፍርፎት እንደፈረሰኛ ለሚጋልበው አባይ መስዋዕት ያቀርቡለታል። ነጭ በሬ ይሰዉለታል። የአባይ ሙላት ገዢ ነው ለሚሉት አምላክ ተማጽኖ ያደርጋሉ። ይለምኑታል። ያመልኩታል። ያሞካሹታል። ቅኔ ያወርዱለታል፡፡ ያሉበት ተፈጥሯዊ ሁኔታ የአባይን ጥቅም ከኢትዮጵያውያን ቀድመው እንዲገነዘቡ ያደረጋቸው ግብጻውያን ከብዙ ዓመታት በፊት በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን ግድባቸውን በአባይ ወንዝ ላይ ገንብተዋል። ግብርናቸውን አዘምነው ምጣኔ ሀብታቸውንና የህዝባቸውን ኑሮ አሻሽለዋል። ለምተዋል። ዛሬ ስለውሃ ድርሻ አጥብቀው የሚሟገቱት ግብጻውያን፤ በአስዋን ግድብ በያዙት የአባይ ውሃ በተትረፈረፈ አባካኝ አጠቃቀም የበረታ ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። ራሳቸው እንዳሻቸው እያባከኑ ኢትዮጵያውያን ከቀዬአቸው ከሚመነጨው አባይ በእፍኝ እንዳይጠልቁ የንፍገት ስጋት ይሰጋሉ። ይህ የእነዚህ ሰዎች ጠባይ ‹‹ወንድም ወንድሙ እርሻ ላይ ዝናብ አይዝነብ›› ይላል የሚለውን የወላይታ ብሂል ያስታውሳል። ከእሱ እኩል እንዳይሆን። ለልመና እሱ ዘንድ እንዲመጣ። የእሱ የበታች፣ ጥገኛና አገልጋይ እንዲሆን። ይህ እንግዲህ ግብጻዊ ብቻ ሳይሆን ከመሰረቱ ቃየላዊ ባህሪ ነው። ግብጽን አልምቶ፤ አልፎ ተርፎም ለሜድትራኒያን ባሕር ስድስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ የሚለግስ አባይ ግብጽን ንፉግ እንጂ አመስጋኝ አላደረጋትም። አንድ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ‹‹እያንዳንዷን ብርጭቆ ውሀ በጠጣሁ ቁጥር ኢትዮጵያን አስባለሁ›› ማለታቸው እውነት ቢሆንም ብዙሃኑ ግብጻውያን ግን የአባይ ምንጭ የት እንደሆነ እንኳ ማስታወስ አይፈልጉም። ከዚህ የአገሪቱ ጠባይ በመነሳት ብዙ የውሀ ዲፕሎማሲ ተመራማሪዎች ግብጽ የመጨረሻዋ የተፋሰሱ አገር ሆና፤ ይህን ዓይነት ግጭትን ያማከለ ዲፕሎማሲ ያራመደች፤ ከእሷ በታች አስራ ሁለተኛና አስራ ሦስተኛ የአባይ ውሀ ተጋሪ አገሮች ኖረው ቢሆን ምን ዓይነት ፖሊሲ ከታችኞቹ ተጋሪዎች ጋር ትከተል ነበር? ሲሉ ይጠይቃሉ። እንዲያ ቢሆን ኢትዮጵያ ብቻዋን ባልነደደች።

ውሀ መጋራትና ዲፕሎማሲ

የውሀ ዲፕሎማሲ በብዙ መልኩ እልህ አስጨራሽና አድካሚ ነው። ይህ እውነታ ብዙዎቹን በዓለም ላይ የሚገኙ ወደ 276 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችንና በእርሱ ዙርያ ያሉትን ሉዓላዊ አገሮች ይመለከታል። ከዓለም ጠቅላላ ሕዝብ ወደ 40 ከመቶ በላይ የሚሆነው በእነዚህ ወንዞች ተፋሰስ ውስጥ ይኖራል። በአህጉራችን አፍሪካም 57 የሚሆኑ ወንዞች ከሁለትና ከሁለት በላይ ተጋሪ አገሮችን ያስተሳስራሉ። የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀምን በሚመለከት ሁለት አማራጮች አሉ። ተጋሪ አገሮች ሊጋጩ ወይም ሊተባበሩ ይችላሉ። በዓለም ላይ ብዙ ግጭቶች በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ምክንያት ተከስተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከ4ዐዐ0 በላይ የውሃ ስምምነቶች ተደርገዋል። ውሃ የልማት፣ የዕድገትና የሥልጣኔ መሠረት በመሆኑ ከመንግሥት ደህንነትና ከህዝብ ህልውና ጋር ተቆራኝቷል። ስለሆነም ትብብር እንጂ ግጭት ተጋሪዎችን አይጠቅምም፡፡ አንዳንድ የውሃ ተጋሪ አገሮች ለየራሳቸው ፍላጎቶች ብቻ ዋጋ በመስጠት የጋራ ከሆነው ውሀ ‹‹የአንበሳውን ድርሻ›› ለማግኘት ይሻሉ። ‹‹እኔ ብቻ ላግኝ፤ እኔ ብቻ ልልማ›› የሚል ከራስ-ወዳድነት፣ የራስን ጥቅም ብቻ ማዕከል ከሚያደርግና ከኃይል ከሚመነጭ ‹‹የተጨባጭነት›› የውሀ ፖሊሲ የሚመራ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ይከተላሉ። ይህ የዲፕሎማሲ ዝንባሌ ተፋሰሱን የግጭት ቀጠና ከማድረግ በስተቀር ለማንም አይበጅም። ግለኝነት፤ ስግብግብነት፤ ጉልበተኝነትና ለሌላው ተጋሪ ህይወት አለማሰብ በውሃ ፖለቲካዊ ግንኙነት አይሠራም። ህይወት የሆነውን ውሃ በሚመለከት ተጋሪዎች የፍትሀዊነትና ርዕትአዊነት የግንኙነት መርሆችን መከተል ያዋጣቸዋል። ለሌላዉ ህይወት ማሰብ ግድ ነው። ኃያል የሆነ ተጋሪ የሌላውን የውሀ ፍትሀዊና ዲሞክራስያዊ የመጠቀምና የመልማት መብት በተለያዩ ዘዴዎች ካዳፈነ፤ ደካማው ለመብቱ ስለሚታገል የተፋሰስ ሰላም የታወከ ይሆናል። የዓለምና የአገሮች ሁኔታ ባለበት የሚቆም አይደለም። ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ሁሌም ተለዋዋጭ ናቸው። ዛሬ ደካማ የተባለው የላይኛው ተጋሪ ዘላለም ደካማ ሆኖ አይኖርም። በተነጻጻሪ ዛሬ ጠንካራ የሆነው የታችኛው ግርጌ ተጋሪ ለዘለዓለም ጠንካራ አይሆንም። በመርህ ላይ የተመሰረቱ ግንኙነቶችም በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ የዓለም ሁኔታ ውስጥ የሰከነና ፍሬያማ ግንኙነቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ይጠቅማሉ፡፡ ግብጽ የአባይ ወንዝ የመጨረሻ የግርጌ ተጋሪ አገር ሆና ሳለ በመልክዓ- ምድራዊ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ በተሻለ ይዞታ ላይ የሚገኙትን የራስጌ ተጋሪዎችን ውሃ የማልማት መብታቸውን በመርገጥ የአባይን ውሃ ለብቻዋ በመጠቀም በኢኮኖሚ የበለጸገችና፤ በወታደራዊ ኃይል የፈረጠመች ሆናለች። የዚህ ዓይነት የግብጽን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ያማከለ የውሀ አጠቃቀም ፖሊሲ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን የቆየ ግንኙነት በግጭትና በጥርጣሬ የተሞላና የሻከረ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በተጋሪ አገሮች መካከል የሚኖረው ግንኙነት ዘለቄታዊ እንዳይሆን ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ በጋራ ተስማምተው የሚመሰርቱት የውሀ ተቋም ያለመኖር ነው። ተጋሪዎች በመደራደር የትብብር ተቋም ሲያቋቁሙ በመካከላቸው የሚኖረው ግንኙነት ዘለቀታዊና ሰላማዊ ይሆናል። በአባይ ተፋሰስ የዚህን ዓይነት ተቋም ለመፍጠር በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም እስካሁን የተሳካ ተግባር አልተፈጸመም። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በጀመረችው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት በሁለቱ ተጋሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከምንጊዜም በላይ በውጥረት የተሞላ ሆኗል። በውሃ ዲኘሎማሲ ካልተለሳለሰ በስተቀር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል የሚል ግምት አለ። አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሥጋትም አለ። መፍትሄው ከራስ የፍላጎት ማዕቀፍ ወጥቶ በጋራ መንፈስ የሁሉንም ፍላጎት ማየት ነው። መናገር ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መስማት ነው። ወንዙን ከመነሻ ወይም ከአጋማሹ አልያም ከመድረሻው አንጻር ብቻ ከማየት ይልቅ የተፋሰሱን አካባቢ ሁሉ፣ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉትን ህዝብ ህልውናና የወንዙን ጠቅላላ የተፈጥሮ አካባቢ በምልዓት ማሰብን ይጠይቃል፡፡ የተፋሰሱን አገሮች ህዝቦች ማሳወቅና ማስተዋወቅ፣ ፖለቲካውንና ዲፕሎማሲውን ከስሜት ይልቅ በምክንያት እንዲራመድ በማድረግ ውጥረት ማርገብ። ወንዞችን በትብብር በማልማት የተፈጥሮ አካባቢ እንዲያገግም አዎንታዊ ድርሻ መውሰድ ለሁሉም የተፋሰሱ ህዝቦች የስጋት ሳይሆን የዘላቂ ተስፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top