ታሪክ እና ባሕል

ወርኻ መስከረም እና ልዩ ገጽታው

እንደ መንደርደሪያ

ዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በሚሉት መጽሐፋቸው መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል። መስከረም ‘‘ምስ-ከረም’’ ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው። የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ፣ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚቆጠቆጡበት ነው ይሉታል። እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል። በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ መሬቷን ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ‘ዕንቁጣጣሽ’ ተብላለች። አቧራ፣ ቡላ የነበረው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልሞ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ አበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች የሚል- ለዕንቁጣጣሽ ስያሜ መነሻ ሊሆን እንደሚችል መዛግብት ይጠቁማሉ። “መስከረም በአበባ፤ ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” ይላሉ አበው። አንድም መስከረም ርዕሰ-ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ በመሆኑ ወርኃ አደይ፣ ወርኃ ጽጌ ተብሏል። እናም ኢትዮጵያውያን በርዕሰ-በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርኃ መስከረም፣ ትልቅ የሆነ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ፋይዳን የያዘ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከእነዚህም ውስጥ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሰፊው የሚታወቁት በዓላት መካከልም፤ ተቀጸል ጽጌ፣ ደመራ፣ የመስቀል እና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ይጠቀሳሉ።

‘‘ተቀጸል ጽጌ’’ (አበባን ተቀዳጅ)

ተቀጸል ጽጌ መስከረም አስር ላይ የሚከናወን ልዩ የመዝሙርና የጸሎት ሥርዓት ነው። በዚሁ ዕለት ካህናቱ አሸብርቀውና ደምቀው ተቀጽል ጽጌን ያከብራሉ። ጽጌ – ጸገየ ከሚለው የግዕዝ ግስ የመጣ ሲሆን ትርጓሜው – አበበ- አበባ ነው። ሊቃውንቱ ስለ ጽጌ የተለያየ ትርጓሜ አላቸው። በተቀጸል ጽጌ የሚነበበው ትርጉም እንዲህ ይላል። የተቀጽል ጽጌ ስርዓት ከዐጼ ገብረመስቀል ጀምሮ እስከ አጼ ዳዊት ድረስ በየዓመቱ መስከረም ፳፭ ሲከበር ኖሯል። ዐጼ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ከኢየሩሳሌም አስመጥተውት መስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ከዚያን ግዜ ጀምሮ የዐጼ ገብረመስቀልና ተቀጸል ጽጌ በዓል መስከረም ፲ ቀን ማክበር ተጀመረ። ‘‘ተቀጸል ጽጌ’’ አበባን ተቀዳጅ ማለት ሲሆን፣ በዘመነ አክሱም በስድስተኛው ምዕተ ዓመት በነበሩት ዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን የክረምት መውጫ በሆነው መስከረም ፳፭ ቀን የሚከበር የወቅት ሽግግር በዓል ነበር። ለንጉሠ ነገሥቱ የአበባ አክሊል/ጉንጉን ይበረከትለት ስለነበር ‘‘ተቀጸል ጽጌ፤ ገብረ መስቀል ሐፄጌ’’ (አፄ ገብረ መስቀል አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ ይዘመር ነበር። ከ15ኛው ምዕተ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሽ ክፍሉ (ግማደ መስቀል) መምጣቱን ተከትሎ በዓሉ ወደ መስከረም ፲ ቀን ዞሯል። እስከ መጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ (1923 – 1967) ድረስ በዓሉ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሲከበር ቆይቷል። ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ወዲህ በዓሉ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት የአበባውን በዓል ማክበሩና ለበዓሉ ታዳሚዎችም አበባን ማደሉ ቀጥሏል።

የደመራና የመስቀል በዓል

‘ደመራ’ የሚለው ቃል- ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን፤ መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ሕብረትን ያመለክታል። ስሙ እንደሚያመለክተው ማስታወሻነቱ ለተጠራቀመ፣ ለተሰበሰበና ለተጨመረ ነገር ነው። በዓሉ አካትቶ የያዛቸዉ ሥርዓቱ የሚከናወንባቸው ቁሳቁሶች፣ የደመራው እንጨቶች፣ ችቦዎች፣ አሽክቶችና፣ ሌሎችም በበዓሉ ዙሪያ የሚታዩት፣ የሕዝቡን ስሜት አንድ ላይ ሰብስቦ ስለያዘ ደመራ ተባለ። የደመራ በዓል በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች ደማቅና ውብ በሆነ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ክንዋኔዎች የሚከበር በዓል ነው። ደመራ ምንም እንኳ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ፣ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከሃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የህብረተሰብ ክፍሎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ለደመራው በዓል መነሻዋ ንግሥት እሌኒ ብትሆንም እሌኒ ደመራ ብላ አልሰየመችውም። ይህ በዓል ደመራ ተብሎ አሁን በምናከብረው ሁኔታና መንፈስ እጅግ ሰፍቶ ከመከበሩ በፊት ወደ እኛ ተሻግሮ መጥቶ ሲከበርና ሲታወስ ቢኖርም፤ የመስቀል በዓል እንጅ ደመራ እየተባለ አልነበረም። እሌኒ የሠራችውን ታሪክ በማስታወስ ሲከበር የቆየው የመስቀል በዓል በዐጼ ገላውዴዎስ ዘመን ከታሪካችን ጋራ ደምረውና አስፍተው ደመራ ብለው ሰየሙት። የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሥርዓተ-አምልኮ መሠረት ካህኑ የመጀመሪያዋን የደመራ መብራት “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” በሚለው በሊጦኑ ቃለ ቡራኬ ባርኮ፣ ከደመራው እንጨት ጋራ እንዲደምራት ሕዝቡን በአስተዳደር ለሚመራው ሰው ያቀብለውና የደመራውን እንጨት ይለኩሰዋል። ከዚያ በኋላ በተዋረድ ያገር ሽማግሌ ሁሉ ችቦውን እያቀጣጠለ በደመራው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑ ካቃጣላት ችቦ ላይ የአገሪቱ ሥጋዊ መሪ በራሱ ችቦ እሳቱን እንዲለኩስ ይፈቅድለታል። የአገሪቱ መሪም እሳቱን በካህኑ እጅ ላይ ካለው ችቦ- በችቦው ለኩሶ በደመራው ላይ መለኮሱን ይመራል። በተዋረድ የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎች ይቀጥላሉ። ከዚያ ጎረምሳው፣ ኮበሌው ወጣቱ እሳቱን በችቦው እየተቀባበለ ወደ ደመራው እየወረወረ የጀግንነት ምልክቱን ብትር ከፍ አድርጎ ይዞ ሆ! እያለ ደመራውን ይዞራል።

የመስቀሉ ፍቺ

በአብዛኞቹ የሕዝበ-ክርስትና ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መሣሪያ መስቀል ተብሎ ይጠራል። “ክሮስ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደው ክሩክስ ከሚለው የላቲን ቃል ነው። ሆኖም የመስቀል አምልኮ ከክርስቶስ ዘመን በፊትም ጀምሮ የነበረ ለመሆኑ በርካታ የጽሑፍና የሥነ- ቁፋሮ ማስረጃዎች አሉ። የተወሰኑትን ከዚህ ቀጥሎ ማየት ይቻላል፡- በብዙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “መስቀል” (“የመከራ እንጨት”) ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ስታዉሮስ ነው። በጥንቱ ገጽ የግሪክኛ ቋንቋ ይህ ቃል ቀጥ ያለ እንጨት ወይም ምሶሶ ያመለክት ነበር። ከጊዜ በኋላ ቃሉ ቀጥ ባለው እንጨት ላይ ወደጎን የሚተላለፍ እንጨት የተደረበበትን የመግደያ እንጨት ለማመልከት ማገልገል ጀመረ። ዘ ኢምፔሪያል ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ በማለት ያረጋግጣል፡- “መስቀል ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል [ስታዉሮስ] ማንኛውም ነገር የሚሰቀልበትን ወይም [ለአጥር የሚሆንን] እንጨት ወይም ቀጥ ያለ ምሰሶ ወይም ግንድ ያመለክታል። … በሮማውያንም ዘንድ ቢሆን ክሩክስ (ክሮስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘበት ቃል) በመጀመሪያ ቀጥ ያለ ምሰሶ ማለት የነበረ ይመስላል። በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ ጥናት “ከክርስትና ዘመን በፊት ጀምሮ በሁሉም የጥንቱ ዓለም ክፍሎች የተለያየ የመስቀል ቅርጽ ያለባቸው የተለያዩ ዕቃዎች ተገኝተዋል። በሕንድ፣ በሶሪያ፣ በፋርስና በግብፅ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መስቀሎች ተገኝተዋል። … ከክርስትና በፊት በነበሩት ጊዜያትና ክርስቲያን ባልሆኑት ሕዝቦች መካከል መስቀልን እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ምልክት አድርጎ መጠቀም በመላው ዓለም ላይ የተለመደ ልማድ ነበር ማለት ይቻላል። ክርስቶስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊትና ከዚያም ወዲህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አገሮች መስቀል ቅዱስ ምልክት ሆኖ ሲሠራበት መቆየቱ የማይታበል ሐቅ ነው። …የግሪክ ባከስ፣ የጢሮስ ተሙዝ፣ የከለዳውያን ቤልና የኖርስ ኦዲን ሁሉም በአማኞቻቸው ዘንድ የመስቀል ቅርጽ ባለው ምልክት ይመሰሉ ነበር። በብዙ ቦታዎች ልዩ ልዩ ቅርጽ ያላቸው የመስቀል ሥዕሎች በግብጽ ሐውልቶችና መቃብሮች ላይም ተገኝተዋል።

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን

በዓለ-መስቀል በክርስትና ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ማስታወሻ በዓል ሲሆን፤ በምዕራብም ምሥራቅም አብያተ ክርስቲያናት ይሄንን መታሰቢያ መስከረም ፫ ቀን ሲያከብሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በየዓመቱ መስከረም ፲፯ ቀን ታከብራለች። ይኼ ጽሑፍ በመሠረቱ የሚያጤነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በየዓመቱ መስከረም ፲፯ ቀን ተከብሮ የሚውለውን በዓለ መስቀል ታሪካዊ ዳራ ለማስታወስና በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ የአንዳንድ ሊቃውንት አስተያየቶችን መጠቋቆም ነው። ስለመስቀል በዓል አከባበር መነሾ፣ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ለ፫፻ ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ጥለውት ነበር። ይሁንና በ፫፻፳፮ ዓ/ም የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች። ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም ፲፯ ቀን አስጀምራ በመጋቢት ፲ ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ የሊቃውንቱ ምስክርነት አለ። በነገራችን ላይ ስለመስቀል በዓል ስናነሳ፣ ከላይ እንደተገለጸው ሌሎችም አብያተ- ክርስትያናት ቢያከብሩትም በልዩ ክብር እና ደማቅ ሁኔታ ግን የሚከበረው በተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ መሆኑን ማውሳት ያስፈልጋል። ሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ መሞትና በመስቀሉ የማይረሳ ውለታ የሰው ልጅ መዳኑን ቢያምኑም እንደ ኦርቶዶክስና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ-ክርስቲያናት ትውፊትን ስለማይቀበሉ፣ የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊ በዓል አድርገው አይመለከቱትም። ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ፣ ስለመስቀል በዓል በአንዳንድ ሊቃውንት የተለያየ አስተያየት ሲሰነዘር ቆይቷል። ከዚህ ውስጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል እንደፈጀ ቢነገርም በአንዳንድ ሊቃውንት እሳቤ ደግሞ መስቀሉ የተገኘው መስከረም ፲፯ ነው ሲሉ በአጽንዖት ይናገራሉ። ይሁንና አብዛኛው የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ግን “መስቀሉ የተገኘው በመጋቢት ፲ ቀን ነው፣ ይህ ወር ግን የዐቢይ ጾም ወር በመሆኑ በዓሉ በመስከረም ፲፯ ቀን እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውናል” ሲሉ የላይኛውን ሐሳብ ያፈርሳሉ። በኢትዮጵያችን ሌላው የጌታችንን መስቀል ልዩ ሥፍራ እና ክብር የሚሰጠው ጉዳይ ደግሞ በ፲፭ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መቀመጡ ነው። ስለዚህ መስቀል መምጣት የቤተክርስቲያኗ ጸሐፍት በተለያዩ ሠነዶቻቸው የተረኩ ሲሆን፣ ንጉሡ አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸገረ። በመጨረሻ ግን “አንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል። (መስቀሌን በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠው)” የሚል መለኮታዊ ምሪት ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፬፻፵፮ ዓ/ም አሳረፉት። የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ሥፍራ መስቀልያ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በዘመኑ ፍጻሜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተሰቅሎ በመሞት በክቡር ደሙ ዓለምን ለዋጀበትና ለመላው የሰው ዘር ሰላምን ላደረገበት ለመስቀል የምትሰጠው ክብርና ልዕልና ከሌላው ዓለም የላቀና የተለየ ነው። ከቀደሙት የሀገሪቱ መሪዎች እነ ዐፄ ዳዊት ከኢየሩሳሌም የመጣውን ግማደ መስቀሉን ከእስክንድርያ ለማምጣት ስናር ላይ ተሠውተውበታል። የግብጽ ሡልጣኖች በመስቀሉ ፈንታ በ፲፪ እልፍ ወቄት ወርቅ ሊደልሏቸው ቢሞክሩም ለሀገራቸው ሰላም፣ በረከትና ጤንነት ሲሉ መስቀሉን ነበር የመረጡት። በኋላም ልጃቸው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በነገሡ ጊዜ የአባታቸውን ክርስቲያናዊ ፈለግ በመከተል፣ ስናር ላይ የነበረውን ግማደ መስቀል ከአባታቸው ከዐፄ ዳዊት ዐፅም ጋራ ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው፣ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ማለት “መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ” የሚለውን በራእይ የተነገረውን አምላካዊ ቃል በተግባር በመተርጐም በተፈጥሮ አቀማመጧ የመስቀል ቅርፅ ባላት በግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው እንዲሠለስብት፣ እንዲቀደስበት አድርገው አስቀምጠውበታል። ከዚያም ወዲህ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ድረስ የተነሡት የሀገሪቱ መሪዎችና ሕዝቦች ለመስቀሉ የሚሰጡት ክብርና ልዕልና እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነበር። በየዓመቱ መስከረም ፲፮ እና ፲፯ ቀን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በሚገኝበት በመላ ኢትዮጵያ አስደናቂ በኾነ ድምቀት ይከበራል። በተለይ በዐዲስ አበባ፣ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን፣ በቅዱስ ላሊበላ እና በጎንደር የሀገሪቱ መሪዎች፣ የየክልሉ ባለሥልጣናትና ዓለም አቀፍ የሀገር ጎብኚዎች በሚገኙበት፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እጅግ በሚያስገርምና በሚያስደምም ኹኔታ ነው ሲያከብረው የኖረው። በይበልጥም በአዲስ አበባ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል፣ የሀገሪቱ የጦር ኃይልም የኃይሉን መጠን የሚለካበትና የሚያሳይበት ልዩ በዓል ነበር። የሚገርመው፣ የስድስት ኪሎ አንበሶችም ጭምር ሳይቀሩ ከጦር ኃይሉ ጋራ አብረው ያከብሩት ነበር። ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል፣ በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በዓመት ውስጥ ለአምስት ጊዜያት ያኽል በዐደባባይ ትዘክረዋለች፤ ታከብረዋለች። በመስከረም ወር ብቻ ለዐራት ጊዜ ያህል ይከበራል። መስከረም ፲ ቀን፦ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከስናር ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡበት ዕለት ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. በፊት የዐፄ መስቀል በዓል ተብሎ በቤተ መንግሥት በታላቅ ሥነ ሥርዓት ይከበር ነበር። ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ወዲህ ግን በቤተ ክርስቲያን ብቻ ይከበራል። መስከረም ፲፮ ቀን፦ ንግሥት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት አስቈፍራ ከተቀበረበት ያስወጣችበት የመታሰቢያ ዕለት የደመራ በዓል ተብሎ በዐደባባይ ሕዝበ ክርስቲያን በሚገኙበት በመላ ኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በማግስቱ መስከረም ፲፯ ቀንም፣ ቅዳሴ ቤቱ በዝማሬ፣ በማሕሌት፣ በሥርዐተ ንግሥ በቤተ ክርስቲያን ይከበራል። መስከረም ፳፩ ቀን ደግሞ፣ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የገባበት ዕለት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝበ ክርስቲያንና በርካታ ዓለም አቀፍ የሀገር ጐብኚዎች በሚገኙበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ይከበራል። መጋቢት ፲ ቀንም፣ ንግሥት ዕሌኒ በመጀመሪያ መስቀሉን ያገኘችበት ዕለት በውዳሴ፣ በቅዳሴ፣ በሥርዐተ-ንግሥ ደረጃ በቤተ-ክርስቲያን ይከበራል። ስለመስቀል በዓል በአንዳንድ ሊቃውንት የተለያየ አስተያየት ሲሰነዘር ቆይቷል። ከዚህ ውስጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል እንደፈጀ ቢነገርም በአንዳንድ ሊቃውንት ህሳቤ ደግሞ መስቀሉ የተገኘው መስከረም ፲፯ ነው ሲሉ በአጽንዖት ይናገራሉ። ይሁንና አብዛኛው የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ግን “መስቀሉ የተገኘው መጋቢት ፲ ነው፣ ይህ ወር ግን የዐቢይ ጾም ወር በመሆኑ በዓሉ በመስከረም ፲፯ እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውናል” ሲሉ የላይኛውን ሐሳብ ያፈርሳሉ። ስለመስቀሉ ጉዳይ ስናነሳ አንድ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አለ፤ ይኸውም በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ የተሰቀለበት ቀኝ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል የሚባለው ጉዳይ ነው። ስለዚህ መስቀል መምጣት የቤተክርስቲያኗ ጸሐፍት በተለያዩ ሰነዶቻቸው የተረኩ ሲሆን፣ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት ግማደ-መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸጋረ። በመጨረሻ ግን “መስቀሌን በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠው” የሚል መለኮታዊ ምሪት ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼ አምባ በተባለ ሥፍራ እንዳስቀመጡትና ይህም ሥፍራ መስቀልያ መልክዐ-ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለው ይነገራል።

የኢሬቻ በዓል

ኢሬቻ ከተከበሩትና ከተቀደሱት የኦሮሞ ክብረ በዓሎች አንዱ ሲሆን፣ ከጥንታውያኑ የኦሮሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ይነገራል። ‹‹ኢሬቻ እርጥብ ሣር፣ ቅጠል ቄጠማ አበባ ማለት ነው›› የሚሉት የኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ ኢሬቻው ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት ሥርዓት ነው ይላሉ። ‹‹አምና በሰላም በጤና 13ቱን ወር አስጨርሰኸናል። መጪውን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድታደርሰን ይሁን። ይኸንን ለሰው ልጅ ለሁሉም ፍጥረት ብለህ የፈጠርከውን ንፁህ ውኃ በአንተ ኃይል አጣርተህ ያስቀመጥከውን በሐይቅህ ላይ ምስጋናህን እናቀርባለን። ውኃ ንፁህ ነውና›› ምርቃቱ በየዓመቱ ከመስቀል በዓል በኋላ በሚመጣው እሑድ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ተከትሎ የሚመጣ ነው። ምርቃቱም የሚዥጎደጎደው መራቂው በባህላዊ የኦሮሞ አለባበስ ተውበው የአንበሳ ለምድ አጥልቀው አንፋሮ ደፍተውና ጋሻ ይዘው ነው። ‹‹ኢሬቻ ሣሩን አበባውን እግዚአብሔር ነው ያበቀለው። ይኸንን አበባውን አብቅለህ ለከብቶች ሣር አብቅለህ፣ ለሰው ልጅ ደግሞ ዘር ሰጥተህ፣ ፍሬ አሰጥተህ ስላደረስከን ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን። በክረምቱ መልካው ወንዙ ሞልቶ ዘመድ ከዘመድ ተለያይቶ አሁን ስለተገናኘ እግዚአብሔር ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን። ›› የመመረቂያው ቦታ አድባር ‹‹ድሬ›› ይባላል፤ የተስተካከለ ቦታ ማለት ነው። ከዚህ ካልተመረቀ ወደታች ወደ ሐይቁ አይኬድም። ዱለቻ በሬ ይታረዳል። ከመልካውም ሲኬድ ኮርማ ይታረዳል። ምርቃቱም ‹‹እንኳን በሰላም ከክረምቱ ወደ ብርሃኑ አወጣኸን። ዘመኑን በሰላም ያድርግልን። የእኛን ሕዝብና አገሪቷን ይባርክልን›› ይባልበታል። ሆራ አርሴዲ የክብረ በዓሉ ዋነኛ ስፍራ ነው። ሰፊና ክብ ነው። አካባቢው ዙርያው በዛፎች የተሸፈነ ነው። ለበዓሉ አክባሪዎችና ሥነ ሥርዓቱ ተከታዮች ምቹ ስፍራ ነው። ታዳሚዎቹ ለምለም ቅጠል፣ ቀጤማ፣ እርጥብ ሣር፣ አደይ አበባ… ይዘው ሐይቁ ውስጥ እየነከሩ ይረጫሉ። ወደራሳቸውም ያስነካሉ። ከሐይቁ ዳርቻም ያስቀምጣሉ። ክርስቲያኖችም፣ ሙስሊሞችም፣ የዋቄ ፈታ ተከታዮችም አሉበት። ዝማሬና ምርቃት ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት በሐይቁ ዳርቻ በሚገኘው ዋርካ ሥር ያደርጉታል። ዋርካውን ‹‹ኦዳ›› ይሉታል። ፕ/ር አስመሮም ለገሠ ‘ገዳ’ በሚለው መጽሐፋቸው እንደጻፉት፣ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ልዩ ልዩ ቁሳዊ መገለጫዎች አሉት። በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የቅርሱ ቁሳዊ መገለጫዎች መካከል የኦዳ ዛፍ አንዱ ነው። በኦሮሞ ባህል የኦዳ ዛፍ የእምነትና የፖለቲካ ማዕከል ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ ለብሔሩ አባላት የተለየ ተምሳሌታዊ ፋይዳ አለው። ኦዳ ለጉባዔ ማስኬጃነት የተመረጠው በግርማ ሞገሱና በጥላው ስፋት ብቻ አይደለም። የኦሮሞ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት፣ ኦዳን ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ተመራጭ ያደረገው ከክረምት እስከ በጋ ሳይደርቅ (ቅጠሉን ሳያራገፍ) መቆየት የሚችልና የሕዝቡን ተስፋና የአገሩን ልምላሜ የሚጠቁም ምልክት በመሆኑ ጭምር ነው። ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የመጡ በዓል አክባሪዎች የአካባቢያቸውን ባህል የሚያንፀባርቁ አልባሳት ለብሰው ጫማ ተጫምተው ጌጣጌጥ አጥልቀው የሚታዩበትም ነው ኢሬቻ።

ሰላም!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top