ታዛ ስፖርት

ተደባዳቢው

ሰውዬው ‹‹አራት ኪሎን ጭጭ ያደረግኩኝ ጉልበተኛ ነኝ›› ስለሚሉ ሁሌም ተደባዳቢ ይፈልጋሉ። ጣሊያኖች ጋር ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። ቋንቋውንም፤ ሥራውንም፤ ትንኮሳውንና ሁሉን ነገር ተምረውታል። ጣሊያን ከወጣ በኋላ ስራቸው ውሏቸውም እዚያው አራት ኪሎ ነው። ከሰውዬው ሌላ ደግሞ ይድነቃቸው ተሰማ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ባለው ክልል በኳስ ተጫዋችነቱ የታወቀ፤ በኃይለኛነቱ የተከበረ፤ በጉልበተኛነቱ የተፈራና አካባቢውን ያንቀጠቀጠ ነበር።

ቱፋ ሻይ ገና ወጣት እያሉ አራት ኪሎ አካባቢ በጉልበተኛነታቸው አካባቢውን ማንበርከክ ይፈልጋሉ። ከይድነቃቸው ጋር አይተዋወቁም። በአካባቢው ስለእሱ የሚወራውን አልሰሙም፤ አላዩም። ቱፋ ከ50 ዓመት በላይ በጓደኝነት አብረው ስለዘለቁት ይድነቃቸው እንዲህ ያወራሉ። ‹‹ያኔ ገና ልጅ ጎረምሳ ሆኜ ነው ይድነቃቸውን የተዋወቅኩት። ብታየኝ ኮ ጋንግ ነበርኩ። ብረት ስለማነሳ ደረቴ ሰፊ ነው። (ካቦርታቸው ውስጥ ያለው ደረታቸውን በጣቶቻቸው እያሳዩ) ዱለኛ ስለሆንኩ ሁሉም ይፈራኛል። መደባደብ እወድ ነበር።

አራት ኪሎ ሰፈሬ ነው። እንዲያውም እዚያ አካባቢ የታወቅኩ ተደባዳቢ ነበርኩ። ዱላ የሚችለኝ ሲጠፋ ‹‹ማን ነው ሐይለኛ እስኪ አምጡልኝ!!›› እያልኩ አፈላልግ ነበር። ለአንዳንድ ልጆች ሳንቲም እሰጥና ሐይለኛ ሰው ተብሎ የሚወራለትን አጣርታችሁ አምጡልኝ እላለሁ። ‹‹እከሌ የሚባል ሐይለኛ!!›› አለ ሲባል እሱ ያለበት ቦታ ሄጄ እደባደብ ነበር። ማንነቴንም አሳይቼ እመጣለሁ። አንድ ቀን ግን የእኔን ጉልበተኛነት የሰማ ሰው መጣና ‹‹ቱፋ›› አለኝ።
‹‹አቤት››
‹‹ድብድብ ትፈልጋለህ?››
‹‹ከአንተ ጋር ከሆነ ይቅርብኝ››
‹‹እኔማ የት እችልሃለሁ››
‹‹ታዲያ ከማን ጋር ነው የፈለግከው››
‹‹ሰው ተገኝቶልሃል››
‹‹ማን የሚባል ነው››
‹‹ኳስ ተጫዋች ነው››
‹‹የትኛው››
‹‹የነጋድራስ ተሰማ ልጅ››
‹‹አላውቀውም..
‹‹ይድነቃቸው ነው የሚሉት››
‹‹ድብድብ ይችላል››
‹‹ኧረ!! እንዲያውም ለአንተ ጉዳት ያመጣብሃል››
‹‹እኔ ቱፋ!!!!››

እንደዚያ ስላለኝ ብቻ ሰውየውን አንቄ አንጠለጠልኩት። በኋላ ግን ይድነቃቸው የት እንደሚውል የት እንደሚያመሽ አጣርተህ እስከ ነገ ማታ ካልመጣህ አንተን ነው የምገድልህ አልኩት። ልጁ ስለ ይድነቃቸው መረጃ ይዞ መጣ። ሌሎችን ሰዎች ጠየቅኩ። ‹‹ጉልበተኛ ነው ቦክሰኛ ነው፤ ይቅርብህ ይገድልሃል›› ሲሉኝ ‹‹እኔ ቱፋ እስኪ ማንንም አምጡ ልኩን አሳየዋለሁ ይድነቃቸው ነው እኔን ይገድልሃል የምትሉኝ?›› ብዬ እሱ የሚያመሽበት ቤት ሄድኩኝ። በጥቆማ ደጃች ውቤ እሱ የሚውልበትን ቤት አገኘሁት። ቁጭ ብዬ ጠበቅኩት። እሱ ሲገባ ሁሉም ይፈራዋል። የተቀመጠው ሰው ከወንበሩ ብድግ ይላል። ይድነቃቸውን አይቼው አላውቅም። የዚያን ቀን ነው የተያየነው። ዛሬ ጉድ ይታያል ብዬ ተቀመጥኩ። እሱ ገብቶ ሁሉም ከወንበሩ ሲነሳ እኔ ቁጭ አልኩ። የተቀመጠውን ሰው ይማታል ስለሚባል እስኪ ጉዱን አያለሁ ወደ ወንበሬ ይጠጋ አልኩኝ። በኋላ አየኝና ገላምጦኝ ተቀመጠ። ከዚያ በቆረጣ እንተያይ ጀመር። ግን እንዴት ነው ማንነቴን ማሳየት የምችለው? እሱም ዝም አለኝ። እኔም ዝም አልኩ። ግን የሚያጣላን የሆነ ነገር ያስፈልገን ነበር። በምን ልጀምር? አንድ ሰው አጠገቤ ቁጭ ብሎ ዝም ብሎ ይሰድበኝ ነበር። ለእኔ ስለማይመጥን ከእሱ ጋር መጣላት አልፈለግኩም። ይድነቃቸው ዝም ስላለኝ ለምን በእዚህ ሰውዬ አልጀምርም አልኩኝ። ወደሚሰድበኝ ሰውዬ በይድነቃቸው በኩል አለፍኩና ተመልሼ ወደሰውዬው በመምጣት ‹‹ለምንድነው የምትሰድበኝ?›› አልኩት።
‹‹ብሰድብህ ምን ትሆናለህ?››
‹‹ለመሆኑ እኔን ታውቀኛለህ?››
‹‹እንኳን እኔ ማንም አያውቅህም››
‹‹እኔ ማለት ቱፋ ነኝ። አራት ኪሎን አንቀጥቅጬ የምገዛ›› አልኩት። ይህን ያልኩት ድምፄን ከፍ አድርጌ ይድነቃቸው እንዲሰማኝ ነው። ኮቴን አውልቄ በአንድ እጄ ያዝኩት። ደረቴ እንዲታይ ሸሚዜን ከፈትኩት። ፊቴን ያዞርኩት ወደ ይድነቃቸው ነው። ደረቴን በደንብ እንዲያይልኝ ነው። ሰውየው ቁጭ ብሏል። አልመታሁትም። በድንገት ማንቁርቱን አንቄ ብድግ አደረግኩት። ማን ያላቀው?። አረፋ ደፈቀ። ምላሱ ተጎለጎለ። የቤቱ ባለቤት ‹‹ኧረ!! ሰውዬው ሞተ ብላ›› ጮኸች። ለአራት ሊያስለቅቁኝ ቢሞክሩም አልቻሉም። ያለኝ ጉልበት እኮ ማንም ሊያነቃንቀኝ አይችልም። አራት ኪሎን ጭጭ ያደረግኩ ነኝ። ሰውዬውን አንቄ የማየው ይድነቃቸውን ነው። እሱ መጥቶ ሲገላግል ለመጣላት ነው የፈለግኩት። አልተጠጋኝም ፈራኝ መሰለኝ። የሚገላግሉትን ነው የሚያየው። ሰውዬው አረፋ እንደደፈቀ ምላሱን ተጎልጉሎ ነብሱ ልትወጣ ስትል ሳይሞት ለቀቅኩት። በኋላ በር ላይ ወጥቶ ኡ…ኡ… አለ። ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ እንደገና ወደበሩ መጥቶ ከእኔ ሊጣላ ፈለገ። በአንድ ቦክስ ዘረርኩት። ከመሬት አልተነሳም። ሰዎች ከውስጥ ወጥተው ውሃ ደፍተው አነቃቁት። የቡና ቤቱ ባለቤት ምን አይነቱ ሰው መጣብን እያለች ትጮህ ጀመር። ወደ ቡና ቤቱ ተመልሼ በር ላይ ያሉትን ገፈታትሬ ገባሁ። ውስጥ ሆኜ ቱፋ ማለት እኔ ነኝ። ለመሞት ፍቃደኛ የሆነ ሰው ወደ እኔ ይምጣ አልኩ።

እኔ ውጭ ወጥቼ እስክመለስ ይድነቃቸው የለበሰውን ከነቴራ አውልቆ በጃፖኒ ቁጭ ብሏል። ቅድም ያየሁት ሰው አልመሰለኝም። እጁ ላይ ያለውን ጡንቻና ደረቱን ሳይ ፈራሁት። ግን የፈራሁ መምሰል የለብኝም። አንድ ነገር ቢነሳ ለመገላገል አቅም ያላቸው ሰዎች እንደሌሉ አውቅኩኝ። ግን መፎከር ስላለብኝ ፊቴን ወደ ሌላ ቦታ አዞርኩና ተናግሬ ወጥቼ ሄድኩኝ። ማንነቴን አሳይቻለሁ አልኩኝ። በኋላ አፈላልጎኝ አራት ኪሎ መጣ። ‹‹ባለፈው ተያይተን ነበር›› አለኝ።

‹‹የት?››
‹‹ደጃች ውቤ››
‹‹አላስታውስም››
‹‹እኔ ግን አስታውስሃለሁ››
‹‹ቡና ቤት ውስጥ ነበርክ?››
‹‹አዎን….እንደውም ከሰው ተጣልተህ….››
‹‹እኔ ብዙ ሰው ስለደበደብኩ ትዝ አይለኝም››
‹‹ለማንኛውም እንተዋወቅ››
‹‹መተዋወቁ ጥሩ ነው››
‹‹ስምህ ማን ነው?››
‹‹ይድነቃቸው እባላለሁ››
‹‹ኳስ ይጫወታል የምትባለው አንተ ነህ››
‹‹አዎን››

የእዚያን ቀን በደንብ ተዋወቅን። ያኔ ደጃች ውቤ በጃፓኒ ያየሁት ቀን ሰዎች ጠይቄ እግዚያብሔር አትርፎሃል ነው ያሉኝ። ስለ እሱ በደንብ አጣርቼ ሁሉንም አውቄያለሁ። አሁን አላስታውስም ያልኩት አውቄ ነው። ሊመታኝ የመጣ ስለመሰለኝ እንዳልፈራሁኝ ሸሚዜን እየጠቀለልኩ ነው ያናገርኩት። ከዚያን ቀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ጓደኛ ነበርን። ይላሉ።

ይድነቃቸው ተሰማ ለጊዮርጊስ ክለብ 23 አመት ተጫውቷል። ይሄ አስካሁን ለአንድ ክለብ ረጅም ዓመት በመጫወት ሪከርድ ነው። ይድነቃቸው ኳስ ያቆመበትን ሁኔታ ተፋ እንዲህ ያስታውሳሉ ‹‹….አንድ ቀን ሰዎች መጡና ይድነቃቸው ኳስ ማቆም እንዳለበት ነገሩኝ። ጊዜው በ1950 ዓ.ም ነው። ማን አቁም ይበለው። ሁሉም ፈርቶታል። በቅቶታል አርጅቷል እስከዛሬ ያገለገለው ይበቃዋል በእሱ ቦታ ተተኪ መግባት አለበት እያለ ያጉረመርማል። ግን በቃህ የሚለው ሰው ጠፋ። ‹‹አንተ ስለምትቀርበው ኳስ እንዲያቆም ንገረው›› አሉኝ። እኔም በነገሩ ተስማማሁ። እሱን ከኳስ መለየት ማለት መቆራረጥና ማጣት ማለት ነው። ሰዎች አንተ ንገረው ሲሉኝ ‹‹ልታሰደበድቡኝ ነው እንዴ?›› ብዬ ለጊዜው ዝም አልኩ። ኳስ እኮ ለእሱ ህይወቱ ነው ብዬ ነገርኳቸው። ‹‹ክለቡን የምትወድ ከሆነ በጊዜ እንዲያቆም ንገረው በቅቶታል አርጅቷል›› ብለው አብራርተው ላኩኝ።

የጨዋታ ቀን ጠዋት ወደ ቢሮው ሄድኩኝ። ብዙ ጊዜ በእንዲህ አይነት ወቅት እሄዳለሁ። አሰላለፍ ሲያወጣ ደረስኩኝ። ስለሚያሰልፋቸው ተጫዋቾች ሁሌም ይነግረኛል። እኔንም አስተያየት ስጥ ይለኛል። ብዙ ጊዜ ‹‹እስኪ ያንተን አሰላለፍ ልየው›› ይለኛል። አሁን ቢሮ እንደደረሰኩኝ አወራንና የዛሬውን አሰላለፍ በአንተ በኩል በኩል ንገረኝ አለኝ። እሱ የሚጫወተው በ8 ቁጥር ቦታ ነው። ከ1 እስከ 11 ስጠራ የእሱ ስም የለም። ‹‹ምነው እኔን ዘለልክ›› ሲለኝ ‹‹ውይ ሞት ይርሳኝ!!›› አልኩት። ከእዚያ እሱ የሆነ ነገር ነቃ። የአንተን አሰላለፍ ልስማ አልኩት። ከ1 እስከ 7 ሲጠራ ዝም አልኩት። 8 ቁጥር የእሱን ስም ሲያስገባ ‹‹አቁም›› አልኩት።
‹‹ምነው?››
‹‹ሌላ ሰው ይግባ››
‹‹እኔስ?››
‹‹አትገባም››
‹‹ለምን?››
‹‹በቃህ››
‹‹በቃህ ማለት ምንድነው?››
‹‹አርጅተሀል››
‹‹እኔ?››

አነጋገሩ የቁጣ በመሆኑ ከወንበሬ ላይ ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ሮጨ ወደ ውጭ ወጣሁ። ከእዚያ በመስኮት በኩል አንገቴን ብቅ አደረግሁና ‹‹ይድነቃቸው ልንገርህ ሰው ሁሉ ፈርቶህ ነው እንጂ አርጅተሃል እያሉ ነው። ይልቅስ ከእኛ ጋር ብትደግፍ ይሻልሃል›› አልኩት። ለካ ጠዋት የእኔ ጓደኞች አግኝቷቸው ‹‹አዲስ ቱታ እኮ ከውጭ መጣልኝ›› ብሎ ሲነግራቸው ‹‹ልታስቀድስበት ካልሆነ ልትጫወትበት እንኳን አይሆንም›› ስላሉት ነገሩ ገባው፤ እኔ የተናገርኩት ተጨምሮ ያን ጊዜ ኳስ አቆመ። ከሰዓት በተደረገው ጨዋታ ሌላ ሰው በእሱ ቦታ ገባ። በሌላ ቀን የመሰናበቻ ጨዋታ ተብሎ ተሰለፈ። ለእሱ የስንብት ግጥሚያ ሲደረግ የተጫወት ነው ከመቻል ጋር ሲሆን ውድድሩ የሸዋ ሻምፒዮና ነው። እኛ ዋንጫውን ለመውሰድ እኩል ይበቃናል። 1ለ0 መራን። በኋላ 1ለ1 ሆንን። ጨዋታው አለቀ። ዳኛው ሌላ ሰዓት ጨመረ። ፊሽካ ሊነፋ ተዘጋጀ። እኛም ከግቢው ወጥተን መጨፈር ጀመርን። ከየትና የት የተሻማ ኳስ ውንድሙ የተባለ የጦር ሰራዊት ተጫዋች አግብቶ እነሱ ዋንጫ ወሰዱ። እሱም በእዚያው ጫማ ሰቀለ›› ይላሉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top