ቀዳሚ ቃል

ማን ነው ሀገሩን የሚወድ?

“ማን ነው ሃገሩን የሚወድ? እጁን ያውጣ” ቢባል… ሁሉም እጁን ያወጣል። “ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የሚፈልግስ?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ አሁንም ሁሉም የሀገሩን ሰላም እንደሚፈልግ ይናገራል። ነገር ግን “ማን ነው ራሱን የሚወድ?” ብለን ስንጠይቅ፤ የሐበሻ ወግ ሆኖበት ሁሉም “እኔ ራሴን እወዳለሁ” ብሎ ለማውራት ሲፈራ ይስተዋላል።

እስኪ እውነቱን እናውራ። እያደረግናቸው ያሉት ነገሮች፤ በእውነት ከምናወራው ጋር ይስማማሉን? ስንቶቻችን ይሆን “ሀገሬን እወዳለሁ፤ አይደለም አንድ ህይወት ስለሀገሬ ብዬ አስር ነፍስ ቢኖረኝም በሰጠሁ” እያልን በአደባባይ የምናወራው? ድርጊታችን ግን የቃላችንን ፍሬ የረሳ ነው። አዎ፤ ራስን መውደድ ምንም ክፋት የለውም። ሀገርን መውደድም መልካም ነው። እንዲያውም ሁለቱንም መውደድ ነው ሰናይ ዜጋ ሊያስብለን የሚችለው።

አበው “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይሉናል። ይህንን የሚሉን “ቃል” ምን ያህል ከባድ እነደሆነና፤ ከወለዱትም ልጅ በላይ ሊጠብቁት የሚገባ መሆኑን ሲያዝገነዝቡን ነው። “ሀገሬን እወዳለሁ” ስንል፤ ተግባራችንም ይህንኑ ቃላችን የሚያስታውስ ሊሆን ይገባዋል።

ታዛ መጽሔት ዋነኛ ትኩረቷ ኪነጥበብና ባህል እንደመሆኑ፤ ስለሃገራችን ኪነጥበብና ባህል ትታለቃለች። የኪነጥበብ ሰዎች ሀገራቸውን መውደዳቸው በመድረክ ብቻ ሳይሆን፤ በተግባር በእለት ተእለት ኑሯቸው ላይ ሊያሳዩን ይገባል። ኪነጥበባውያን በሚለያዩን እና እርስ በእርስ በሚያቀያይሙን ርእሰ-ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከሚሰሩ፤ አሁን ያለውን በመሃላችን የተገነባውን ግንብ በማፍረስ ላይ ቢተባበሩ የተሻለ ሀገራቸውን እና ወገኖቻቸውን መጥቀም ይችላሉ።

ሚዲያዎቻችንም ቢሆኑ ሌላውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ጭምር ሊጠቅሙ የሚችሉት፤ በትክክለኛው ሞያዊ ስነምግባር እውነታውን ለህዝብ ሲያደርሱ፤ ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ ርእሰጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ ነው። ዳር እና ዳር ተሁኖ አንዱ አንዱን ሲያሳንስ፤ በመጨረሻ ሁሉም ትንሽ ይሆናል። ልባም እና ትልቅ ሚዲያ የሚባለው “ነግ በእኔ” ብሎ ክፉ ድርጊቶችን የሚያጋልጥ፤ ፍቅርን መተባበርን እና ትዕግስትን የሚሰብከው ነው። “የማታ የማታ እውነት ይረታ” ለምን እንደተባለ ሚዲያዎቻችን ይረዱት ዘንድ ግድ ነው። ዛሬ ላይ ለእውነት መቆም ምንም እንኳ አስፈሪ ሆኖ ቢታይም፤ ይሄ ጊዜ ካለፈ በኋላ ወደፊት ባለው ጊዜ ግን የሚያኮራ እና የሚያስመሰግን ነው።

የትላንቱን ባንረሳም ስለነገ ብለን፤ ዛሬ ላይ የወደፊቱ መንገዳችንን እንዴት የተቃና ማድረግ እንደምንችል ማሰብ መጀመር አለብን። “ቀና የሚያስብ ቀና ይገጥመዋል” እንደሚባለው፤ ቀና አስተሳሰብ ንግግራችን እና ድርጊታችን ቀና ያደርገዋል። ቃሎቻችን ላይ ጥንቁቆች መሆን ይገባናል። አዎ “መልካም ምላስ በትር ትሰብራለች” ነውና ሐቁ፤ ልባቸው የሻከረውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመልካም አንደበት እንዲለዝቡ ማድረግ ይገባናል። የራሳችንን ወገን ያላዳንን ማንን ልናድን ነው? ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ወደመልካሙ መንገድ እንመልሳቸው። ከፉብን ብለን አንራቃቸው። ባህሪውን ሊቀይር የማይችል ሰው ስለሌለ፤ እኛ ራሳችንም ጭምር ብንሆን ባህሪያችንን ለመቀየር ልንጣጣር ይገባናል።

የኩርፊያ ቤት፣ የኩርፊያ ሀገር… “አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው” እንደሚባለው ለጠላት እና ለሌባ ምቹ ነው። እስከመቼ ተቀያይመን? እስከመቼ ተጣልተን? እስከመቼ ተኳርፈን?… እንዘልቀዋለን? መቼ ይሆን ይህንን ክፉ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቁም እና ይብቃ የምንለው?

“ዳሩ ሲፈታ መሀሉ ዳር ይሆናል” ነውና እውነቱ… ጠባቂያችን፣ መመኪያችን፣ መከታችን የሆነው ወገናችን ከእኛ የተለየን ቀን፤ ለውጪ ጠላት እና ለሌሎች ክፉ ነገሮች የበለጠ ተጋላጭ እንሆናለን። አሁን የጀመርነውን አዲስ ዓመት መልካም በማሰብ፣ መልካሙን በመስራት፣ በመታገስ፣ በመከባበር እና በመፈቃቀር… ጥሩ ዓመት ልናደርገው ይቻለናል። ኪነጥበበኞችም ብንሆን በመልካሙ ነገር ላይ፣ ሀገርን እና ወገንን ሊጠቅም በሚችለው ርእሰ-ጉዳይ ላይ በማተኮር ብዙ ልናበረክት ይቻለናል።

መልካም አዲስ ዓመት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሁን!! ሰላምና ተስፋ ለሃገራችንን እና ለወገናችን ይሁን!! የወር ሰው ይበለን…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top