አጭር ልብወለድ

ሉኢዘ ሪንዘር (1911 – 2000)

በአጫጭር ልቦለድ ሥራዎቿ የምትታወቀው ሪንዘር ጀርመን ፒትስሊንግ ውስጥ ተወለደች። በመምህርነት ስራ ላይ ተሰማርታ እስከ 1939 .ም ድረስ ሰርታለች። በጋዜጦች ላይ አጫጭር ታሪኮችን መፃፍ የጀመረችው በ1935 .ም ነበር። ‹‹ በድብቅ ቢቢሲ አዳምጣለች፤ ወታደሮች እንዳይዋጉ መክራለች፤ በዚህም የሀገር ክህደት ወንጀል ፈፅማለች›› በሚል ሞት የሚስቀጣ ክስ ተመስርቶባት በእስር ቆይታ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ እያለ ጦርነቱ በማብቃቱ ለጥቂት ተርፋለች። ሪንዘር የእስር ጊዜዋ በህይወቷ ጥሩ ልምድ ያገኘችበት ወቅት እንደነበር ጽፋለች። እንደ ጉንተር ግራስ እና ዚግፍሪድ ሌንስ ሁሉ እሷም በ1971 የጀርመን ምርጫ ዘመቻ ወቅት ከዊሊ ብራንት ጎን ተሰልፋለች። ከ1972 .ም ጀምሮ ወደ ተለያዩ አገሮች የተጓዘች ሲሆን ሰሜን ኮሪያን በተደጋጋሚ ጎብኝታለች። Iራንንም የጎበኘች ሲሆን የ1979ኙን የእስልምና አብዮት ፖለቲካዊ እና መንፈሳዊ መሪ የነበረውን አያቶላ ሩሆላ ቾሚኒን ‹‹ለሶስተኛው ዓለም የሚያበራ ተምሳሌት›› ስትል አሞግሳለች። ሪንዘር በ1984 .ም ግሪን ፓርቲን ወክላ በእጩ ፕሬዝዳንትነት ለምርጫ ቀርባ ነበር። በስራዎቿ ላይ የራሷን ፖለቲካልሞራል አቋም ታነሳለች። ይህም አብዛኛውን ጊዜ ቁጣን ያዘለ ሂስ ያስከትልባት ነበር።

ቀይዋ ድመት

በተደጋጋሚ ስለዚህች ሰይጣን ስለሆነች ቀይ ድመት ማሰብ ይኖርብኛል። የፈፀምኩት ተግባርም ተገቢ እንደነበር አላውቅም። ነገሩ የጀመረው የአትክልት ስፍራችን ውስጥ በቦምብ ፍንዳታ ምክንያት ከተፈጠረ ጉድጓድ አጠገብ ካለ ድንጋይ ክምር ላይ ተቀምጬ እያለ ነው። የድንጋይ ክምሩ የቤታችን ግማሽ በላይ ፍርስራሽ ውጤት ነው። ትንሹ ክፍል ግን አልፈረሰም። እዚህ ውስጥ እኔ፣ እናቴ፣ ታናሽ ወንድሜ ፔተር እና ታናሽ እህቴ ሌኒ እንኖራለን። እንዳልኳችሁ የድንጋይ ክምሩ ላይ ቁጭ ብያለሁ። ሁሉም ቦታ ሳር እና ሳማ እንዲሁም አረንጓዴ ነገሮች በቅለዋል። በእጄ ቁራሽ ዳቦ ይዣለሁ። ዳቦው ክው ብሎ የደረቀ ነው። እናቴ ታዲያ፣ ‹‹ደረቅ ዳቦ ከትኩሱ የበለጠ ለጤና ተስማሚ ነው›› ትላለች። እውነቱም እንደዚያ ነው። ምክንያቱም ደረቅ ዳቦን ረዥም ጊዜ ማኘክ ያስፈልጋል። እናም ትንሽ ተበልቶ ይጠገባል። እኔጋ ግን ይህ አይሠራም። በድንገት ከእጄ ላይ ቁራሽ ዳቦ ወደቀ። ለማንሳት ጎንበስ አልኩኝ። በዚህ ቅፅበት አንድ ቀይ መዳፍ ከሳማው ውስጥ ወጥቶ ዳቦውን ለቀም አደረገው። ልብ ብዬ ሳላይ ወዲያው ተሰወረብኝ። ከዚያ በኋላ ሳማ ውስጥ አንድ ድመት ስትሽሎኮሎክ አየሁ። እንደ ቀበሮ ቀይ ስትሆን፣ ደግሞም በጣም ከሲታ ነች። ‹‹አስጠሊታ አውሬ!›› አልኩና ድንጋይ ወረወርኩባት። ላባርራት እንጂ ልመታት አልፈለኩም ነበር። ግን ሳልመታት አልቀረሁም መሰል አንድ ጊዜ ብቻ እንደ ህፃን ልጅ ጮኸች። አልሸሸችም። ስለወረወርኩና ስለመታኋት አዘንኩኝ። ካለችበት ቦታ አልወጣችም። በፍጥነት ትተነፍስ ጀመር። ከሆዷ በላይ ያለው ቀይ ፀጉሯ እንዴት ወደ ውጭ ወደ ውስጥ ይንቀሳቀስ እንደነበር ይታየኛል። ዝም ብላ በአረንጓዴ አይኗ ትመለከተኛለች። በዚህ ጊዜ፣ ‹‹ለመሆኑ ምንድን ነው የምትፈልጊው?›› ስል ጠየኳት። ለነገሩ የሞኝ ሥራ ነው። እሷ እንደሁ ሊያናግሯት የሚቻል ሰው አይደለች። በእሷ እና በራሴ ሥራ ተናደድኩ። ወደ እሷ መመልከቴን ትቼ በፍጥነት ዳቦዬን በኃይል ገመጥኩት። ከፍ የሚለውን የመጨረሻውን ቁራሽ በንዴት ወረወርኩትና ሄድኩኝ። ፊት ለፊት ያለው የአትክልት ስፍራ ውስጥ ፔተር እና ሌኒ የባቄላ እሸት እየሸመጠጡ አፋቸው ውስጥ ይወጥቃሉ። ሲያኝኩ ይሰማል። ሌኒ በቀስታ ትንሽ ዳቦ እንዳለኝ ጠየቀችኝ። ‹‹አንቺም የኔን ያክል ዳቦ ነው የተሰጠሽ። አንቺ ገና ዘጠኝ ዓመትሽ፣ እኔ ደግሞ አስራ ሶስት ነኝ። ትላልቆች ደግሞ ብዙ ይበላሉ አይደል?›› አልኳት። ‹‹አዎን!›› አለች። ሌላ ምንም አላለችም። በዚህን ጊዜ ፔተር፣ ‹‹ዳቦዋን እኮ ለድመቷ ስለሰጠች ነው›› አለ። ‹‹የምን ድመት?›› ስል ጠየቅኩኝ። ‹‹አይ የሆነች ድመት መጥታ ነበር። ቀይ፣ በጣም ከሲታ፣ ትንሽ፣ ቀበሮ የምትመስል። እናም ዳቦዬን ስበላ ዝም ብላ ትመለከተኝ ነበር›› አለች ሌኒ። ‹‹ለራሳችን የሚበላ ሳይኖረን… ደደብ!›› ስል በቁጣ ተናገርኩኝ። እሷ ግን ትከሻዋን ነቅንቃ በፍጥነት ወደ ፔተር ተመለከተች። ፊቱ ፍም መስሏል። እርግጠኛ ነኝ እሱም ዳቦውን ለድመቷ ሠጥቷታል። በሁኔታው በጣም ተናድጄ ስለነበር በፍጥነት ከዚያ ቦታ መሄድ ነበረብኝ። ዋናው መንገድ ላይ እንደደረስኩ አንድ ትልቅ እና ረዥም የአሜሪካ መኪና ቆሟል። እንደሚመስለኝ መኪናው ቡIክ ነው። ሹፌሩ ማዘጋጃ ቤቱ የት እንደሚገኝ ጠየቀኝ። የጠየቀኝ በእንግሊዝኛ ነው። እኔም ትንሽ ትንሽ እችላለሁ። ‹‹በሚቀጥለው መንገድ፣ ከዚያ ወደ ግራ ከዚያ…›› ብዬ ‹‹ቀጥታ›› የሚለውን ቃል በእንግሊዝኛ ማወቅ ተሳነኝ፤ እናም በእጄ ምልክት ሰጠሁት። እሱም ገባው። ‹‹ከቤተክርስቲያኑ ኋላ ገበያ ቦታው እና ማዘጋጃ ቤቱ ነው›› አልኩት። እንደሚመስለኝ ይህ በጣም ጥሩ አሜሪካንኛ ነው። መኪናው ውስጥ ያለች ሴትዮ በስሱ የተቆረጠ ጥቂት ነጭ ዳቦ ሰጠችኝ። ዳቦው በጣም ነጭ ሲሆን፣ ከፈት ሳደርገው መሃሉ ላይ ወፍራም የአሳማ ስጋ አለበት። ዳቦውን ይዤ በሩጫ ወደ ቤት ሄድኩኝ። ምግብ ቤት ስገባ ሁለቱ ህፃናት በፍጥነት የሆነ ነገር ሶፋው ስር ሲደብቁ ደረስኩኝ። ግን ምን እንደሆነ አይቼ ነበር። ቀይዋ ድመት ነች። መሬቱ ላይ ደግሞ ጥቂት ወተት ተደፍቷል። በዚህም የሆነውን ነገር ሁሉ አወቅኩኝ። ‹‹እኛ በቀን ለአራት ሰው ግማሽ ሊትር አሬራ ነው ያለን። አብዳችኋል እንዴ!›› ስል ጮኽኩኝና ድመቷን ከሶፋው ስር አውጥቼ በመስኮት በኩል ወረወርኳት። ሁለቱ ልጆች አንድም ቃል አልተነፈሱም። ከዚያ በኋላ ነጩን የአሜሪካ ዳቦ አራት ቦታ ቆረስኩትና የእናቴን ድርሻ ፍሪጅ ውስጥ ደበቅኩት። ‹‹ከየት አመጣህ?›› ሲሉ በፍርሃት እያዩ ጠየቁኝ። ‹‹ሰርቄ!›› አልኳቸውና ከሰል የጫነ መኪና ሲያልፍ ሰምቼ ስለነበር ቶሎ ብዬ መንገዱ ላይ የወደቀ ከሰል እንዳለ ለማየት ወጣሁ። አንዳንድ ጊዜ ከመኪኖች ላይ ከሰል ይወድቃል። ፊት ለፊት ካለው የአትክልት ስፍራ ቀይዋ ድመት ቁጭ ብላ ወደ እኔ ትመለከታለች። ‹‹ሂጂ ጥፊ!›› አልኩና ልመታት እግሬን ሰነዘርኩኝ። እሷ ግን በመሄድ ፈንታ ትንሽዬ አፏን ከፍታ ‹‹ሚያው!›› አለች። እንደሌሎቹ ድመቶች አልጮኸችም። ‹‹ሚያው›› ብቻ ነው ያለችው። ይህንን እኔ ልገልፀው አልችልም። ትክ ብላ በአረንጓዴ አይኗ ተመለከተችኝ። በዚህን ጊዜ በጣም ተናድጄ ከአሜሪካኑ ዳቦ ላይ ቁራሽ ወረወርኩላት። በኋላ ግን ፀፀተኝ። መንገዱ ላይ ስደርስ ሁለት ከፍ ከፍ ያሉ ልጆች አየሁ። ከኔ ቀድመው ከሰሉን ለቅመውታል። ዝም ብዬ አልፌ ሄድኩኝ። አንድ ሙሉ ባሊ ለቅመዋል። ከዚያች ድመት ጋር ባልቆይ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ የእኔ ነበር የሚለው ሃሳብ ወዲያውኑ ወደ አእምሮዬ መጣ። ይሄ ሁሉ ከሰል የእኔ ቢሆንለቤተሰቡ ሁሉ የሚበቃ እራት ማብሰል በተቻለ ነበር። በጣም የሚያማምሩ እና የሚያብለጨልጩ ከሰሎች ናቸው። በዚያ ፈንታ ገና ከእርሻ ላይ የተለቀመ ድንች የጫነ ጋሪ አጋጠመኝ እና በትንሹ ክምሩን ነካ አደረኩት። ጥቂት ድንቾች ወደ መሬት ወደቁ። በድጋሚ እንዲሁ አደረኩኝ። የወደቁትን ድንቾች የሱሪዬ ኪሶች ውስጥ ከተትኳቸው። ጋሪ ነጂው አየት ሲያደርገኝ፣ ‹‹ድንችዎ እየወደቀ ነው›› አልኩት። ከዚያ በኋላ በፍጥነት ወደ ቤቴ ሄድኩኝ። እናቴ እቤት ውስጥ ብቻዋን ነበረች። ጭኗ ላይ ቀይዋ ድመት ተቀምጣለች። ‹‹ያንተ ያለህ! ይህች አውሬ ተመልሳ መጣች?›› ስል ተናገርኩ። ‹‹እንዲህ አትበል። ባለቤት የሌላት ድመት እኮ ነች። ለምን ያህል ጊዜ ምግብ እንዳልቀመሰች ማን ያውቃል? እስቲ እንዴት እንደከሳች ተመልከት።›› አለች እናቴ። ‹‹እኛም እኮ ከሲታዎች ነን›› አልኩኝ። ‹‹ካስቀመጥክልኝ ዳቦ ላይ ትንሽ ሰጠኋት›› አለች እና በጎን ተመለከተችኝ። ስለ ዳቧችን፣ ስለወተቱ እና ነጩ ዳቦ አስታወስኩኝ። ግን ምንም አልተናገርኩም። ከዚያ በኋላ ድንቹን ቀቀልን። እናቴ በጣም ተደሰተች። ከየት እንዳመጣሁ አልጠየቀችኝም። ከፈለገች መጠየቅ ትችል ነበር። በመቀጠል እናቴ ቡናዋን ጠጣች። ሁሉም ያቺ ቀይ አውሬ ወተቱን እንዴት ጭልጥ አድርጋ እንደምትጠጣ ተመለከቱ። በመጨረሻም በመስኮት ዘላ ወጣች። ቶሎ ብዬ መስኮቱን ዘጋሁት እና እፎይ አልኩኝ። ጠዋት 12 ሰዓት ላይ አትክልት ለማምጣት ሄድኩኝ። ሁለት ሰዓት ላይ ስመለስ ትናንሾቹ ልጆች ቁርስ እየበሉ ነበር። መካከላቸው ወንበሩ ላይ እንሰሳዋ እየተተራመሰች ከሌኒ ጋር የስኒ ማስቀመጫ ላይ የረሰረሰ ዳቦ ትበላለች። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እናቴ ከጠዋቱ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ ከቆመችበት ስጋ ቤት ተመልሳ መጣች። ድመቷ ወዲያውኑ ወደ እሷ ዘላ ሄደች። እናቴ እንዴት እንደምታስብ ሊገባኝ አልቻለም። ቁራጭ የአሳማ ስጋ ወረወረችላት። በጣም የታወቀ ግራጫማ መልክ ያለው ምርጥ የስጋ አይነት ነበር። እኛ ዳቧችን ላይ ቀብተን መብላት በወደድን፣ እናቴም ይህንኑ ማድረግ በተገባት ነበር። ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ኮፍያዬን ይዤ ወጣሁ። አሮጌውን ብስክሌት ከመጋዘን አወጣሁና ፊት ለፊት ወደ ከተማ ነዳሁ። እዚያ አሳዎች ያሉበት አንድ ኩሬ አለ። አሳ ማጥመጃ የለኝም። ሁለት ሹል ሚስማር የተመታበት አንድ ዱላ ብቻ ነበር ያለኝ። በዚህ አሳዎቹን እወጋቸዋለሁ። ብዙ ጊዜ ጥሩ እድል ገጥሞኛል። አሁንም እንዲሁ። ገና አራት ሰዓት ሳይሞላ ለምሳ የሚበቁ ሁለት ጥሩ ጥሩ አሳዎችን አጠመድኩኝ። በምችለው ፍጥነት ሁሉ ወደ ቤት ነዳሁኝ። እቤት እንደደረስኩ አሶቹን ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥኳቸው። ቶሎ ብዬ ልብስ ታጥብ ለነበረችው እናቴ ሄጄ ነገርኳት። እሷም አብራኝ መጣች። እዚያ ስንደርስ የነበረው ግን አንድ አሳ ብቻ ነበር። ያውም ትንሹ። የመስኮቱ ክፈፍ ላይ ቀይዋ ድመት ቁጭ ብላ የመጨረሻውን ጉርሻ ትጎርሳለች። እጅግ ከመናደዴ የተነሳ አንድ ቁራጭ እንጨት ወረወርኩባት። መታኋትም። እያቃሰተች ከመስኮቱ ደፍ ላይ ወርዳ እንደተጠቀለለ ጆንያ አትክልቱ ውስጥ ዱብ አለች። ‹‹የታባቷ! ይበቃታል›› አልኩኝ። በዚህን ጊዜ እናቴ ድምፁ በሚያስተጋባ ጥፊ አጮለችኝ። እድሜዬ 13 ዓመት ነው። በእርግጠኝነት ከአምስት አመቴ ጀምሮ አንድም ጊዜ ተመትቼ አላውቅም። ‹‹እንሰሳትን የምታሰቃይ!›› ብላ እናቴ ጮኸችና ፊቷ በንዴት አመድ መሰለ። ከመሄድ ውጭ ሌላ ምንም ማድረግ የምችለው ነገር አልነበረኝም። ቢሆንም ግን በምሳ ሰዓት የቀረበው ድንች የበዛበት የአሳ ሰላጣ ነበር። የሆነው ሆኖ ከዚያች ቀይ አውሬ ተገላግለናል። ግን ማንም ይህ የተሻለ እንደሆነ አያምንም። ትናንሾቹ ልጆች በአትክልት ስፍራው እየሮጡ ድመቷን ይጣራሉ። እናቴ ደግሞ በየማታው ወተት የያዘ ሳህን ከበሩ ፊት ለፊት ታስቀምጣለች። እኔንም ማስጠንቀቂያ ባዘለ እይታ ትመለከተኛለች። እኔ ራሴ የሆነ ቦታ ታማ ወይም ሞታ ተጋድማ ይሆናል በማለት አውሬዋን በየማእዘኑ መፈለግ ጀመርኩኝ። ከሶስት ቀን በኋላ ግን ድመቷ ተመልሳ መጣች። ታነክሳለች፤ የፊት እግሯ ላይ ደግሞ ቁስል አለባት። እኔ ያሳረፍኩባት ዱላ ውጤት ነበር። እናቴ ቁስሏን ጠቅልላላት የሚበላ ነገር ሰጠቻት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ መምጣት ጀመረች። ካለ ቀይዋ ‹ከብት› ምሳ ሰዓት የሚባል ነገር የለም። ከመካከላችን ምንም ነገር ከእሷ መደበቅ የማይቻል ሆነ። የሆነ ሰው የሆነ ነገር ከመብላቱ ከየት መጣች ሳይባል ቁጭ ትልና አፍጥጣ ትመለከታለች። እናም ምንም ብናደድ እኔን ጨምሮ ሁላችንም የፈለገችውን እንሰጣታለን። በየጊዜው እየወፈረች መጣች። ለነገሩ ቆንጆ ድመት እንደነበረች አምናለሁ። የ1946 ዓ.ም ክረምት ተገባዶ የ1947 ዓ.ም ክረምት ተጀምሯል። በዚህን ጊዜ፣ ስለ እውነት ምንም የሚበላ ነገር አልነበረንም ማለት ይቻላል። ለጥቂት ሳምንታት እንደ በረዶ የቀዘቀዘ ድንች እንጂ አንድም ግራም ስጋ አልነበረንም። ልብሶቻችንም እላያችን ላይ ሰፍተው ተንጠልጥለዋል። አንድ ጊዜ ሌኒ ርቧት ከዳቦ ጋጋሪ ላይ አንድ ቁራሽ ዳቦ ሰርቃ ነበር። ይህን የማያውቀው ግን እኔ ብቻ ነኝ። የካቲት መጀመሪያ ላይ ለእናቴ ‹‹አሁንስ ከብቷን እናርዳታለን›› አልኳት። ‹‹የምን ከብት?›› ስትል ትኩር ብላ እየተመለከተች ጠየቀችኝ። ‹‹ድመቷን ነዋ!›› አልኩኝ። ምን ሊከሰት እንደሚችል አውቄዋለሁ። ሁሉም ወረዱብኝ። ‹‹ምን? ድመታችንን! አታፍርም!›› ‹‹አላፍርም። ምግብ እየሰጠን አደልበናታል። ደህና ወፍራም ጠቦት መስላለች። በዚያ ላይ ደግሞ ልጅ ነች። ታዲያስ?›› አልኩኝ። ሌኒ መጮህ ጀመረች። ፔተር በጠረጴዛው ስር በእርግጫ መታኝ። እናቴ በሃዘኔታ፣ ‹‹እንዲህ አይነት ክፉ ልብ ይኖርሃል ብዬ ላምን አልቻልኩም›› ስትል ተናገረች። ድመቷ ምድጃው ላይ ተቀምጣ እንቅልፍ ወስዷታል። በእውነት ተድበልብላለች። ከቤት ወጥታ እያደነች መብላት እስከማትችል ድረስ ሰንፋለች። ሚያዚያ ወር ላይ ድንች የሚባል ስለጠፋ ምን መመገብ እንዳለብን ማወቅ አልቻልንም። አንድ ቀን ላብድ ደርሼ በቁጣ ለድመቷ፣ ‹‹ትሰሚኛለሽ! ምንም የሚላስ የሚቀመስ ነገር የለንም። ተመልከች!›› ብዬ ባዶውን የድንች ሳጥንና የዳቦ ማስቀመጫ አሳየኋት። በመቀጠልም፣ ‹‹አሁን ጥፊ ከዚህ! በምን ሁኔታ ላይ እንዳለን አይተሻል›› አልኳት። እሷ ግን አይኖቿን አርገበገበችና ምድጃው ላይ እንዳለች ዞር አለች። በንዴት ጮኽኩና የእቃ ቤት ጠረጴዛውን በቡጢ መታሁት። እሷ ግን ግድም አልሰጣት። ያዝኳትና ክንዴ ስር ወሸቅኳት ውጪው ትንሽ ጨለም ብሏል። ትናንሾቹ ልጆች ከእናቴ ጋር ከባቡር ሃዲዱ ግራና ቀኝ ያለው ጉብታ ስር የወደቀ ከሰል ለመፈለግ ሄደዋል። ቀይዋ ከብት ከስንፍናዋ የተነሳ ዝም ብላ በቀላሉ ተይዛ ሄደች። ወደ ወንዙ አቅጣጫ ሄድኩኝ። አንድ ሰው መንገድ ላይ አገኘኝ እና ድመቷን እሸጣት እንደሆን ጠየቀኝ። በደስታ ተሞልቼ፣ ‹‹አዎን!›› አልኩት። ሳቀና መንገዱን ቀጠለ። ወዲያው ወንዙ አጠገብ ደረስኩኝ። ወንዙ ላይ በረዶ ይንሳፈፋል። አየሩን ጉም ሸፍኖታል። ቀዝቃዛ ነበር። ድመቷ እውስጤ ውሽቅ ብላለች። እያሻሸሁ አዋራት ጀመር። ‹‹ይህንን ማየት እንደማልችል ነግሬሽ ነበር። እህትና ወንድሜ እየተራቡ አንቺ እየደለብሽ ስትሄጂ ዝም ብዬ ማየት በፍፁም አልችልም›› አልኳት። ከዚያም በጣም ጮህኩና ያቺን ቀይ ከብት የኋላ እግሮቿን ይዤ ከአንድ የዛፍ ግንድ ጋር አጋጨኋት። ግና ጮኸች እንጂ አልሞተችም። ከዚያም ከአንድ የበረዶ ቋጥኝ ላይ ፈጠፈጥኳት። በዚህን ጊዜ ጭንቅላቷ ተቦደሰና ደም ይፈሳት ጀመር። በረዶው ላይ ሁሉ ጥቁር ነጠብጣብ ሆነ። እንደ ህፃን ልጅ አለቀሰች። ልተዋት ፈለኩ። ነገር ግን ልጨርሳት ግድ ነበር። በተደጋጋሚ የበረዶ ቋጥኙ ላይ ፈጠፈጥኳት። አጥንቶቿ ይሁኑ በረዶው አላውቅም ይንቋቋል። ይሄም ሆኖ ግን ገና አልሞተችም። ሰዎች ድመት ሰባት ነፍስ ነው ያላት ይላሉ። ይህቺ ግን ከዚያ በላይ ነበራት። በእያንዳንዱ ዱላ በጣም ትጮሃለች። እኔም አንድ ጊዜ ጮኽኩኝ። በዚህ ቅዝቃዜ ውስጥ በላብ እርሼያለሁ። መጨረሻ ላይ ግን መሞቷ አልቀረም። ወንዙ ውስጥ ወረወርኳት እና እጆቼን በበረዶው ታጠብኩኝ። እንደገና ወደ ከብቷ ስመለከት በርቀት በበረዶ ቋጥኞች መካከል ትንሳፈፋለች። ከዚያም በጉሙ ውስጥ ገብታ ተሰወረች። በጣም በረደኝ። ወደ ቤት መሄድ ግን አልፈለኩም። ከተማ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስል ቆየሁና በመጨረሻ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ። ‹‹ምን ሆነሃል? ገርጥተሃል፣ ደግሞ የምን ደም ነው ጃኬትህ ላይ ያለው?›› ስትል እናቴ ጠየቀችኝ። ‹‹ነስሮኝ ነው።›› አልኳት። አየች እና ወደ ምድጃው ሄዳ ሻይ አፈላችልኝ። መጥፎ ስሜት ተሰማኝ። ከዚያ አካባቢ ዘወር ማለት ነበረብኝ እና ወደ መኝታዬ ሄድኩኝ። ከዚያ በኋላ እናቴ ቀስ ብላ መጥታ፣ ‹‹ገብቶኛል፤ ሁል ጊዜም ይህንን አስታውስ!›› አለችኝ። ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን ፔተር እና ሌኒ ግማሹን ሌሊት ከብርድ ልብሱ ስር ሆነው ሲያለቅሱ ይሰማኛል። እናም አሁን ቀይዋን አውሬ መግደሌ ትክክል እንደነበር አላውቅም። ለነገሩ እንደዚች ያለ እንሰሳ እኮ በፍጹም ብዙ አይበላም።

ጀርመን ባህል ማዕከል ካሳተመው ከህግ ፊት እና ሌሎችም አጫጭር የጀርመን ታሪኮች ከሚለው መጽሓፍ የተወሰደ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top