ታሪክ እና ባሕል

የዓለማችን የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች (ካላንደሮች)

“ሁሉንም ድል አድራጊ፣ ታላላቅ ስልጣኔዎችን ያስረሳ፣ ታላላቅ ሰዎችን በሌሎች ታላላቅ ሰዎች የተካ፣ ሁሉም በእርሱ የሆነ፣ ከእሱም ውጪ ምንም የሆነ ነገር የሌለ… ከሁሉም ነገሮች ኃያል፣ አዲስ የተባሉትን አሮጌ ያስባለ… ከከበሩ ነገሮች ሁሉ የከበረ፣ ከውድ እንቁዎች ሁሉ የተወደደ… ከጀግኖች በላይ ጀግና፣ ከአሸናፊዎች በላይ አሸናፊ… ማን ነው?”

የዚህ ጥያቄ መልስ ጊዜ ነው። “ሁሉም በጊዜው ሆነ” እንዲል ጠቢቡ ሰለሞን፤ በህይወት ኖረን በአየናት ዓለም… ሁሉም ነገር በጊዜው ሲሆን አይተናል። የተከፋንበት ጊዜ አለ፣ የተደሰትንበት ጊዜ አለ… የአሸነፍንበት ጊዜ አለ፣ የተሸነፍንበትም ጊዜ አለ… የኮራንበት ጊዜ አለ፣ ያፈርንበት ጊዜም አለ…።

የሰው ልጅ ገና ከጋርዮሽ ዘመን አንስቶ ማህበራዊ ህይወቱ፣ ስራው፣ ጉዞው፣ አደኑ… ሁሉም ተግባራቱ በጊዜ የተቃኙ ነበሩ። ይህ ባህሪ ግን የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የሌሎች እንስሳት እና የእጽዋትም ጭምር ነው። በቀን አንቀላፍተው በምሽት የሚያድኑ እንስሳት አሉ። በምሽት ተኝተው ቀኑን የሚውሉበት እንስሳትም አሉ። እጽዋትን ከተመለከትን ደግሞ፤ እነሱም በጊዜ ጥላ ስር እንዳሉ ለመመልከት እንችላለን። ለምሳሌ የሱፍ አበባ ብንመለከት፤ በምሽት ወደውስጥ ታጥፎ ከአቃፊ ሐረጋማ ግንዱ ጎበጥ ያለው አበባ… ፀሐይቱ ስትወጣ ካቀረቀረበት ተቃንቶ አበባው ይፈካል። ፀሐይቱን እየተከተለም የሱፍ አበባው በቀን ዑደት ውስጥ የፊቱን አቅጣጫ ይለዋውጣል።

የእንስሳት እና የእጽዋት ከጊዜ ዑደት ጋር የተሳሰረ ባህሪ በሰው ልጅ ላይም ይንጸባረቃል። የሰው ልጅ ግን ለጊዜ አቆጣጠር ስርዓት በማበጀቱ ከእነዚህ ሁሉ ይለያል።

በዓለማችን ላይ ብዙ ዓይነት የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች አሉ። እነዚህ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች በዓለም እንዳሉት ህዝቦች ቁጥር፣ ቁጥራቸው ብዙ ነው። በዓለም ያሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች በአብዛኛው በሚከተሉት ዋና ዋና አመዳደቦች ይመደባሉ። እነሱም፡ – የፀሐይ ኡደት የሚከተሉ፣ የጨረቃ ኡደት የሚከተሉ፣ የጨረቃና ፀሐይ ኡደትን ቀላቅለው የሚጠቀሙ፣ የወቅቶችን መለዋወጥ የሚከተሉ እና ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠር…. ይባላሉ።

የሰው ልጅ ጊዜ እና ዘመንን መቁጠር የጀመረው የፀሐይን እን የጨረቃን ኡደት እየተከተለ ነው። ቀን እና ለሊትን በፀሐይ እና በጨረቃ መፈራረቅ የለየ ሲሆን፤ ወራትን እና ሳምንታትን ደግሞ በጨረቃ ኡደት ሊለይ በቅቷል።

የፀሐይ ኡደት የሚከተሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች

የኢትዮጵያ፣ የቻይና፣ የሮማ ጁሊያን ካላንደር፣ የግብጽ ኮፕቲክ፣ የባይዛንታይን፣ የኔፓል፣ የግሪጎርያን ካላንደር፣ የስዊድን… ወ.ዘ.ተ… የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች (ካላንደሮች) የፀሐይ ኡደትን የሚከተሉ ናቸው።

የፀሐይ ኡደትን የሚከተሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች፤ አንድ ቀን የሚሉት የፀሐይን የመግባትና መውጣት አንድ ሙሉ ሂደትን ነው። ይህም በሰዓታት ሲቀመጥ፤ አንድ ቀን ሃያ አራት ሰዓታት ይሆናል ማለት ነው።

አንድ ወር ደግሞ እንደየካላንደሩ ዓይነት የሚለያይ ሲሆን፤ በአብዛኞቹ የፀሐይ ኡደትን በሚከተሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች ላይ አንድ ወር በአማካይ 30 ቀናት ነው። የግሪጎርያን ካላንደር ከ28 እስከ 31 ቀናት ያሏቸው ወራቶች አሉት፤ በአብዛኛው ግን 30 ቀናት ያሏቸው ወራትን ይይዛሉ።

የጨረቃ ኡደት የሚከተሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች

የጥንት እስራኤላውያን፣ የእስልምና፣ የኔፓል ቡድሂስቶች፣ የአሶራውያን፣ የቀደምት የሰሜን አሜሪካውያን… ወ.ዘ.ተ… የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች የጨረቃ ኡደትን የሚከተሉ ናቸው። በአብዛኞቹ የመካከለኛው ምስራቅ የጥንት ስልጣኔዎች፤ የጨረቃ ኡደትን የተከተለ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች አሏቸው።

ከሙሉ ጨረቃ እስከ ሙሉ ጨረቃ ያለው አንድ ኡደት፤ ሙሉ ወር ይባላል። የዚህ ኡደት ሩብ ደግሞ አንድ ሳምንት ይባላል።

የጨረቃና ፀሐይን ኡደት ቀላቅለው የሚጠቀሙ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች

የጥንት ሮማውያን ካላንደር፣ የግሪክ የሄለናውያን ካላንደር፣ የጥንታዊ ፋርስ ካላንደር፣ የጥንታውያን ሴልቲኮች ካላንደር፣ የቤንጋሊ ካላንደር፣ የታይላን ሂንዱ ቡድሂስት ካላንደር… ወ.ዘ.ተ… የጨረቃ እና የፀሐይ ኡደትን በመቀላቀል የሚጠቀሙ የጊዜ አቆጣጠር ስርአቶች ናቸው።

የወቅቶች መለዋወጥን የሚከተሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች

የሰሜን አሜሪካ ኒስጋኣ ጎሳዎች፣ የሰሜን አሜሪካ ኢኑት ጎሳዎች የወቅቶችን መለዋወጥ የሚከተል የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት ይከተላሉ። በዚህም የተነሳ የአየር ንብረት መለዋወጥ ካላንደሮቻቸው ላይም ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህ ምክንያትም የጊዜ ርዝማኔያቸው የተለያዩ ወራት እንዲኖሩ ያደርጋል።

ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠሮች

በዓለም ላይ አሁንም ድረስ ባህላዊ ጊዜ አቆጣጠር የሚከተሉት በአማዞን ጫካ ያሉ ከተቀረው ዓለም ተነጥለው የሚኖሩ ኋላቀር ጎሳዎች ናቸው። እነዚህ ጎሳዎች “ሻማን” የሚሏቸው የጎሳ መሪዎች አሏቸው። ታዲያ የወቅቶችን መቀያየር እና አዲስ ዓመት መምጣቱን የሚያሳውቁት እኚሁ ሻማኖች ናቸው።

ሳምንቶች እና የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት

በአብዛኞቹ በዓለማችን ላይ በሚገኙ ሃገራት ላይ ያሉ ካላንደሮች፤ አንድ ሳምንት ከሰባት ቀናት ጋር እኩል ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ከዚህ ይለያል። በጥንት አዝቴኮች የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት መሠረት አንድ ሳምንት 13 ቀናትን ይይዛል። በጥንታውያን ግብጾች ዘንድ ደግሞ አንድ ሳምንት 10 ቀናት አሉት። በጥንታውያን ሮማውያን እና በሴልቲክ ህዝቦች ዘንድ ደግሞ አንድ ሳምንት 8 ቀናት አሉት። የኮሪያውያን ባህላዊው ካላንደር አንድ ሳምንትን በ5 ቀናት ብቻ ይወሰናል። ከሁሉም የሚለየው ግን የባሊ ካላንደር ነው። በባሊ ካላንደር መሠረት በአንድ ሳምንት ውስጥ ያሉ ቀናት ተለዋዋጭ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች

በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዓይነት የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች አሉ። በአብዛኞቻችን ዘንድ ከተለመደው በመስከረም ከሚጀምረው ካላንደር የተለዩ ሌሎች ካላንደሮችም አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የሲዳማ እና የወላይታ ተጠቃሾች ናቸው። እንዲያውም በሲዳማ ካላንደር መሠረት የሚከበረው አዲስ ዓመትን ማብሰሪያው ፍቼ ጫምበላላ በዓል፤ በዩኔስኮ እውቅና የተሠጠው ነው።

የጊዜ አቆጣጠር ስርዓቶች ጥቅም

ካላንደሮች ብዙ ጥቅም አላቸው። ከዋንኛ ጥቅሞቻቸው ውስጥ አንዱ በዓላት የሚከበሩበትን ቀናት ለማወቅ ይገኙበታል። አዲስ ዘመን መጥቷል እንድንል፤ አዲስ ዘመን መምጣቱን የሚያበስር ካላንደር ያስፈልገናል። ሌላው የካላንደሮች ጥቅም ደግሞ እቅድ ለማውጣት የሚሰጡት ጥቅም ነው። ሰዎች የስራም ይሁን የቤተሰብ እቅድ የሚያወጡት ካላንደሮችን በመጠቀም ነው። በግል ጉዳያችንም ሆነ በስራ ጉዳይ የቀጠሮ ጊዜን ለመወሰን ካላንደሮች አስፈላጊዎች ናቸው።

ሌላው የካላንደሮች ጥቅም የሚስተዋልበት ሞያ አካውንቲንግ ነው። የበጀት ዓመት፣ ዓመታዊ ገቢ እና ወጪ የሚሰሩት ካላንደርን በመጠቀም ነው። የወቅቶች መለዋወጥንም ከካላንደር እናውቃለን።

ስለ ካላንደሮች ልዩ ልዩ እውነታዎች

የቻይና ካላንደር ዓመታቶች አሰያየም ከዞዲያክ (ፍካሬ ክዋክብት) እንስሶች የተወሰደ ነው። ዘመኖቻቸውን በእንስሶች ስም ነው የሚሰይሙት። ለምሳሌ፡- የአይጥ ዘመን፣ የጥንቸል ዘመን፣ የነብር ዘመን… ይላሉ። አሁን ያለንበት 2020 እ.አ.አ. በቻይና ካላንደር መሰረት፤ የአይጥ ዘመን ይባላል። ቀጥሎ የሚመጣው 2021 እ.አ.አ. ደግሞ የበሬ ዘመን ይባላል። 2022 እ.አ.አ. ደግሞ የነብር ዘመን ይባላል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው 46 ዓመተ ዓለም፤ ግራ የሚያጋባው ዘመን ተብሎ ይጠራል። በስህተት 80 ቀናት ተጨምረውበት ስለነበር፤ በአጠቃላይ በዓመቱ ውስጥ የነበሩት ቀናት 445 ናቸው።

መሬት በፀሐይ ዙሪያ አንድ ዙር ለመጨረስ የሚወስድባት ጊዜ 364.242181 ቀናት ነው። በተለምዶ ግን በማጠጋጋት 365.25 ተደርጎ ይታሰባል። ይህ የልኬት መዛባት በየዓመቱ የ45 ደቂቃ ስህተተን ይፈጥራል። ከቄሳር ጁልየስ በፊት የዓመቱ ቀናት 365 ተደርገው ነበር የሚታሰቡት።

በ46 ዓመተ ዓለም የተከሰተው ግራ የሚያጋባው ዘመን፤ በጊዜ አቆጣጠር ላይ ብዙ ስህተቶች ይታዩበት ስለነበር፤ ቄሳር ጁልየስ ይህንን ስህተት ለማስተካከል በየ 4 ዓመቱ አንድ ቀን የሚጨመርበትን የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት (ካላንደር) አስተዋወቀ። ጁልየስ ይህን ያደረገበት ምክንያት በዓመቱ ያሉት ቀናት 365.25 ናቸው ብሎ ስላሰበ ነው። ይሄ ማስተካከያ ለትክክለኝነት ቢቀርብም ከፀሐይ ኡደት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የ45 ደቂቃ ስህተት ፈጠረ። በዚህም የተነሳ በየ 128 ዓመት የጊዜ ቆጠራው 1 ቀን ወደኋላ ሊጎተት ቻለ። በ1582 እ.አ.አ ጳጳስ ግሪጎሪ የጊዜ አቆጣጠሩ በ10 ቀን ወደኋላ እንዳለ በማስተዋል፤ 10 ቀናትን በመጨመር ካላንደሩ ላይ ማስተካከያ አደረገ።

በ1752 እ.አ.አ. እንግሊዝ የግሪጎሪያን ካላንደርን ስትቀበል፤ ከመስከረም 2 ቀጥሎ የነበረው ቀን መስከረም 4 ነበር። ምክንያቱም የ11 ቀን ማስተካከያ ስለተደረገ ነው።

በየ 4 ዓመታት የሚጨመረው ቀን፤ በየ400 ዓመታት 3ቴ አይደረግም። እነዚህ ቀን የማይጨመርባቸው ዓመታት ለ400 የማይካፈሉ ምእተ ዓመታት ናቸው። ስለዚህ ለምሳሌ ያህል በ2000 እ.አ.አ. አንድ ቀን ይጨመራል። በ2100 ፣ በ2200፣ እና በ2300 እ.አ.አ. ግን ያ አንድ ቀን የማይጨመር የሚቀር ይሆናል።

ከእውነተኛው የፀሐይ ኡደት የግሪጎርያን ካላንደር በየዓመቱ ለ26 ሰከንድ (ካልኢት) ያህል ያንሳል። ይህም ወደፊት በየ 4909 ዓመታት በአንድ ቀን ቀደም እንዲል ያደርገዋል። ይሄ በየ 4909 ዓመታት የሚከሰት የአንድ ቀን ስህተትን ለማስተካከል ወደፊት ለየት ያለ ቀመር እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ከጁልየስ ቄሳር በፊት የሮማውያን የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት የሚከተለው የጨረቃ ኡደትን ነበር። ጁልየስ ቄሳር የፀሐይ ኡደት የሚከተል የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት እንዲጀመር ያደረገው፤ ግብጽን ከጎበኘ በኋላ እና የግብፃውያን አንድ ዓመት 365 ቀናት ያሉት መሆኑን ካወቀ በኋላ ነበር። በዚህም ምክንያት መላው የሮም ግዛት አንድ ዓይነት የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት መከተል ስላለበት የጁልየስ ካላንደር እውን ሆነ።

በግሪጎርያን ካላንደር ላይ ያሉት ጁላይ እና ኦገስት የተባሉት ወራት፤ በሮማ ቄሳሮች ጁልየስ እና አውጉስተስ የተሰየሙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ካላንደር ከኮፕቲክ ካላንደር ጋር የ276 ዓመታት ልዩነት አለው። ከግሪጎርያን ካላንደር ጋር ደግሞ ከ7 – 8 ዓመታት ልዩነት አለው።

የሰሜን ኮሪያ ካላንደር የሚጀምረው የአሁኑ ፕሬዝዳንት አያት ከሆኑት ከኪም ኢል ሱንግ የልደት ቀን ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top