የታዛ እንግዳ

“የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው በምልበት ጊዜ በምኞት አይደለም። በማስረጃ ነው!!”

በታዛ መጽሔት ቁጥር 36 እና 37፣ ከታዋቂው የቋንቋና የሥነጽሑፍ ምሁር ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ያደረገውን ውይይት ማቅረባችን ይታወሳል። የውይይታችን የመጨረሻ ክፍል እነሆ!! መልካም ንባብ!

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች፣ ሥነጽሑፍና ታሪክ ላይ የሚያደርጉትን የጥናትና ምርምር ፈለግ የሚከተል ሰው ይኖራል ብለው ይገምታሉ?

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተምርበት ጊዜ የኢትዮጵያ የጥንቱ ትምህርት ከአሁኑ ትምህርታችን ጋራ የተያያዘ እንዲሆን ብዙዎች ሞክረዋል። ከሚኒስትሮቹ ጀምሮ እነ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ከእርሳቸው በፊትም የነበሩ ሰዎች ዘመናዊውን ትምህርት ከጥንቱ የኢትዮጵያ ትምህርት ጋር ለማያያዝ ብዙ ደክመው አልሆነላቸውም። ምክንያቱም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታየን ምንድነው… እኛ ወደ ኋላ የቀረነው፣ ጣሊያንም ያሸነፈችን በቴክኖሎጂና በዘመኑ ትምህርት ወደኋላ ስለቀረን ነው። ስለዚህ ወደፊት ለመቅደም፣ እንደ እንግሊዞችና እንደ አሜሪካኖች ለመሆን፣ የእንግሊዝን ካሪኩለም መውሰድ አለብን፤ የአሜሪካን ካሪኩለም መውሰድ አለብን ተብሎ የመጡት መማሪያ መጻሕፍት ሁሉ ለእንግሊዝ አገር የተዘጋጁ፣ ለአሜሪካን አገር የተዘጋጁ ነበሩ። ወደ ኋላ ምናልባት ለምሥራቅ አፍሪቃ የተዘጋጁ ጥቂት መጻሕፍት አምጥተውልን ነበር። በዚያ መንገድ የኢትዮጵያው ትምህርት ሊያያዝ አልቻለም ነበር። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከኢትዮጵያ ሊቃውንት ጋራ ለመገናኘት የሚቻልበትን መንገድ ብዙ እፈልግ ነበር። ዶክተር አክሊሉ ሃብቴንም (የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የነበሩ) ደጋግሜ አነጋግሬው በብዙው ሃሳብ ይስማማኝ ነበር። እርግጥ ያ ሁሉ አልሆነም። አሁን በመጨረሻ በቅርብ ጊዜ የፊሎሎጂ ዲፓርትመንት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተቋቁሟል። በእርሱ ላይ ትልቅ ተስፋ አለኝ። እንደ ድህረ-ምረቃ መሆኑ ነው። ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመርቀው የወጡ እዚያ ይገባሉ። ግዕዝ ያውቃሉ፣ በዚሁ ይቀጥላሉ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጆርናል አለ፣ ደግሞ አዲስ ጆርናልም እያቋቋሙ ነው። ይሄ እኛ ውጪ የምናሳትመው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊታተም ይችላል ማለት ነው። ባለፈው በጣም ጥሩ የሆነ የግዕዝ ምንጭ አግኝቼ አጥንቼ አንድ ጽሑፍ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጆርናል ላኩላቸው። በኋላ የሚታተም መሆን አለመሆኑን ለሚያይ አንባቢ ሰጥተነዋል አሉኝ። ጠበቅኩ። አንባቢው የላከው ትርጉምና አስተያየት በጣም ነው ያኮራኝ። እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሰው ነው። እዚህ እዚህ ላይ ለምን እንዲህ አደረግኸው? ብሎ የጻፈውን አይቼ በጣም ነው የኮራሁት። አንዳንዱ ጋ ስህተት መስሎት ነው፣ ግን ስህተት የሚመስል ነው ነገሩ። አንዳንዱ ቦታ ይህንን ለውጥ ያለኝ ደግሞ ትክክል ነው። እንዴ እንደዚህ ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ምንድነው ችግራችን? የዩኒቨርሲቲው የብራና መጻሕፍት ተንከባካቢ አቶ ደመቀ ብርሃኑን ታውቀው እንደሆን ባለፈው እዚህ መጥቶ ነበር። እና አደራ ያልኩት ከነዚህ ሰዎች ጋር ተገናኝ። እነዚህን ሰዎች ሰብስብና አብራችሁ ሥሩ። የነዚህ መጻሕፍት ኃላፊ ነህ አንተ አይደለም? ካታሎግ በምታደርግበት ጊዜ ከእነርሱ ጋራ ተመካከር። ለምንድነው በየጊዜው እየተገናኛችሁ የማትነጋገሩ ብዬ እንዲሁ ከአደራ ጋር ነው የሸኘሁት።

ከትምህርት ክፍሉስ ጋር?

ከፊሎሎጂ ዲፓርትመንቱ አለቃም ጋር ግንኙነት አለን። በጣም ይጽፍልኛል። አንዳንድ ነገር ሲልክ ደስ ይለኛል። እኔም እዚያው እንዲታተም ነው የምፈልገው። አሁን በየቦታው እባክህን አርቲክል ላክልን፣ ምነው ዝም አልክ ይሉኛል። አንተም በየቦታው ሲታተሙ አይቻለሁ አላልክም? እኔ እሱ እንዲቀንስና ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታተም ነው የምፈልገው። ነገር ግን የገንዘብ ችግር አለባቸው። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጆርናል በስንት ጊዜ ቆይቶ ቆይቶ አንዴ ብቅ ይላል። አሁን የምጽፋቸውን ሁሉ ለእሱ ልላክለት ወይስ ለሌላው ልላክ እያልኩ ነው የምጠብቀው። ችግር አለባቸው። ግን ሰዎች አሏቸው። ያለባቸው ችግር አንደኛ የገንዘብ ነው፣ ሁለተኛው የአስተዳደር ነው። የአስተዳደር ድጋፍ ያላቸው አይመስለኝም እንጂ ትምህርቱ ሊቀጥል ይችላል። እርግጥ ነው ሁሉንም ግዕዝ አዋቂ ልናደርገው አንችልም። መጀመሪያ እኮ ግዕዝ የሚያውቁና የኢትዮጵያን ባህል የሚያውቁ ምንድነው የሚሆኑት ነው? አስተማሪ ነው የሚሆኑት አይደለም? አስተማሪ ለማዘጋጀት ነው እንጂ ለእርሻ ሚኒስቴር ወይ ለጦር ሚኒስቴር ግዕዝ አዋቂ ለማፍራት አይደለምና የግድ ሁኔታውም ያስገድዳል። ብንፈልገውም በተወሰነ ደረጃ እንደሚሆን፣ እንደሚጠብብ የታወቀ ነው። እንደ ድሮው ዋሸራ ሄዶ ተመርቆ መምጣት፣ ደብረወርቅ ሄዶ ተመርቆ መምጣት ላያስኬድ ይችላል። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ግን የግዕዝ መጻሕፍት፣ የግዕዝ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን አለበት። እንግሊዝ ወይም ሌላ አገር መሆን የለበትም። ስለዚህ ሊከተሉ የሚችሉ አሉ ማለቴ ነው። የፊሎሎጂ ዲፓርትመንት መቋቋሙ ሰዎችን ሊያፈራ ይችላል።

አመሰግናለሁ ጋሽ ጌታቸው። የግዕዝ ቋንቋና ሥነጽሑፍ አሁንም ድረስ ተፅዕኖው አለ። ተዘዋውሬ እንዳየሁት ሰዎቹ አሉ፣ ቅኔ አዋቂዎች፣ የቅኔ መምህራንና ተማሪዎቹም አሉ። ነገር ግን ትምህርት ቤቶቹ ከመንግሥት ድጋፍ ውጪ በመሆናቸው እየተዳከሙ ነው የሚሄዱት። ቀደም ባለው ጊዜ የቅኔ መምህራኑ ደመወዝተኞች ነበሩ። ወደኋላ ግን የትምህርት ፖሊሲው አንድ መምህር ቢያንስ ከመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም የአንድ ዓመት ሥልጠና የተከታተለ መሆን አለበት ስለሚል ግንኙነቱ ተቋርጧል። ግን አሁንም በድሮው ባህል ተማሪዎቹ ቀፍፈው ለምነው ይማራሉ። መምህሮቻቸውን ያገለግላሉ። ያን ባህል፣ ያን የበለፀገ ዕውቀት ጠብቆ ለማስተላለፍና ጥቅም ላይ ለማዋል ምን መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ?

ትምህርታቸውን የጨረሱት የግዕዝ ሊቃውንትና ባለቅኔዎች፣ ትዳራቸውን በምንድነው እንዲያሸንፉ የምናስበው? ይሄ ነው እንግዲህ ዋናው ጥያቄ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ ዲፕሎማ ያገኘ ሰው ከሌላው ሰው የተሻለ ደመወዝ አግኝቶ ለመቀጠር ይችላል። አይደለም? ኢኮኖሚስት ይሆናል፣ የሕግ ጠበቃ ይሆናል፣ ዳኛ ይሆናል፣ መሃንዲስ ይሆናል። መሃንዲስ በመሆን ዘመናዊ ሕይወት ለመኖር ይችላል። እነዚያ ምንድን ነው የሚሆኑት? ለቤተክህነት ነው የሚያገለግሉት አይደል? እኛ ቅኔ ሲሰጥ፣ ሲቀኙልን ስንሰማ ደስ ይለናል። ግን ያንን ደስታ እንዲያቆዩልን ምንድን ናቸው እነሱ? ተዋንያን ናቸው? ኢንተርቴይነርስ ናቸው? ለነሱስ ለግል ህይወታቸው ምንድን ነው የሚደረገው? እሱ ነው ዋናው ችግር። ቤተክህነት ለነዚያ ሁሉ ደመወዝ ልትከፍል አትችልም። ሕብረተሰቡ ሊደግፋቸው ይችላል ወይ? ያ ካልሆነ እርሻውም ላይ እያረሳችሁ ይህንን አድርጉ ቢባል አይቻልም። የዘመኑ ትምህርትና የዘመኑ ባህል ያመጣብን ችግር ይኼ ነው። ምዕራባውያንም እኮ ነበራቸው፣ በላቲን ነበር የሚማሩት። አሁን ከዛ እየራቁ ነው የሚሄዱት። እንደው ምናልባት አንድ ቀናተኛ አስተዳዳሪ ኖሮ ግዕዝ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ቢሰጥ መልካም ነበር። በየትምህርት ቤቱ ሁለተኛ ቋንቋ እንማራለን፣ እንግሊዝኛ እንማራለን። ምዕራባውያንም ቢሆኑ በየተማሪ ቤታቸው ትርፍ ቋንቋ ይማራሉ። ግዕዝንስ ማስተማር አይቻልም ወይ? ማለት ሌላው ቢቀር፣ ባንቀኝ እንኳን ሌሎቹ የተቀኙትን ቅኔ ለማድነቅና ለመረዳት የሚያስችለንን ግዕዝ ልንማር እኮ እንችላለን። በእውነቱ የግዕዝ ቋንቋን ማወቅ ትልቅ ጥረት የሚፈልግ ነገር አይደለም። በተለይ አማርኛና ትግርኛ ለሚያውቅ ሰው ግዕዝ ለመማር ብዙ ችግር አይገጥመውም። ቅኔ ለመቀኘት ባይችልም የግዕዝ መጽሐፍ ለማጣጣም ይችላል። ታዲያ ያን ዕድል ለምን እንከለክለዋለን? አንደኛው ይሄ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በምርጫ፣ ግዕዝን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ አማራጭ ልናስገባለት እንችላለን። ያን ብናደርግ እነዚያን ግዕዝ አዋቂዎች ሁሉ አስተማሪዎች ልናደርጋቸው እንችላለን። ያኔ ደመወዝተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደዚያ ካልሆነ ዝም ብለን የቅኔ አዋቂዎች አሉን እያልን ቁጭ ልንል አንችልም፣ አይቀጥልም።

አመሰግናለሁ፣ ቀጥዬ የምጠይቅዎትን አሁን በከፊል አንስተነዋል፣ እንደ አቶ መንግስቱ ለማ ያሉት የባህል ጠበብት የግዕዝ ቅኔ ሕጉ፣ ደምቡ፣ ሥርዓቱና ምጥንነቱ እንዲሁም ሰምና ወርቁ፣ ዘመናዊውን ሥነጽሑፋችንን ሊያበለጽገው ስለሚችል ይዘቱን እንኳ ባይሆን ቅርጹን ልንጠቀምበት ይገባል ይላሉ። የእርስዎን ሃሳብ ቢያካፍሉን?

አንድ ጊዜ ከአቶ ዓለማየሁ ሞገስ ጋር ስንነጋገር “ቅኔ ኢትዮጵያዊ ነው፣ በግዕዝ ነው የተሰጠው። ግዕዝ ያላወቀ ቅኔ አወቅኩ ሊል አይችልም። መሠረቱ ቅኔ ነው“ የሚል ንግግር አድርጎ ሲጨርስ በኋላ ለብቻችን ቁጭ አልንና፣ “አቶ ዓለማየሁ፣ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ግዕዝ ብናስተምር ደስታውን አልችለውም። ግን ያ የማይሆን ከሆነ የግዕዝን የቅኔ አሰካክ በአማርኛ ብናደርገው ምን ይመስልሃል? አብሮ ከሚቀር ያኛውን ብናመጣውስ? በአማርኛ ብናደርገው ምን ይመስልሃል? አለዚያ እኮ ሁለቱም ቀረ” ስለው፣ “እውነትክን እኮ ነው” አለ።

ግዕዙን መማር እንኳ ቢያቅተን ያን የግዕዙን ስልቱን፣ የግዕዝን የጉባኤ ቃና፣ የመወድስ፣ የስላሴና የመሳሰሉትን ስልት አምጥተን በአማርኛ ልንገጥምባቸው እንችላለን። የቅኔ ኃይሉ ግዕዝ ነው ወይስ ቅኔው ነው? ይኼ ነው እንግዲህ ጥያቄው። የቅኔ ኃይሉ ቅኔው ነው። ኃይለ-ቃሉ ነው እንጂ ቃሉ አይደለም። ስለዚህ ያ ቃሉ በማንኛውም ቋንቋ ሊሆን ይችላል። በአማርኛ ልናደርገው እንችላለን፣ እንደውም በኦሮምኛም “ማሎ ማሎ ጎፍታ ኪያ፣ መና ፈርዳ ፉደቴ አህያ” የተባለውን ሰምተህ የለም እንዴ? እንደዛም ሊደረግ ይችላል። ይሄ ነው። ሁለተኛ አማርኛም ደግሞ የራሱ መብት አለው። መብት አለው ስልህ የአማርኛ ቋንቋም የፈጠረው ግጥም መጠበቅ አለበት። መብቱ ነው። ልክ ግዕዝን የምናከብረውን ያህል አማርኛም የሰጠንን ባህል ማክበር አለብን። የኦሮምኛውንም ባህል ማክበር አለብን። ማለቴ የሰጠንን የግጥም አያያዝ ሁሉ ማክበር አለብን። ግዕዝን እንጠቀምበታለን። ነገር ግን ባህላችን ግዕዝ ብቻ ስላይደለ ሁለቱንም አብረን ማስኬድ ይኖርብናል የሚል ነው የእኔ ስሜት።

(ማስታወሻ፣ እላይ በኦሮምኛ በከፊል የተጠቀሰው “ሥላሴ” ቅኔ በአለቃ ዘወልዴ የተሰጠ ሲሆን ትርጉሙም እንደ ቅደም ተከተሉ “ምነው ምነው የእኔ ጌታ! የፈረስን ቤት አህያ ወሰደች” መሆኑ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በ1980 ዓ.ም ባሳተመው “የግዕዝ ቅኔያት-የስነጥበብ ቅርስ፣ ንባቡ ከነትርጓሜው” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ተመልክቷል። ዓለማየሁ)

የኢትዮጵያውያን፣ በተለይ በውጭ ያለነው፣ ጥንካሬዎቻችን ምንድን ናቸው ብለው ያስባሉ?

ጥንካሬዎች ብዙ አሉን። አንደኛ ለትምህርት ዋጋ እንሰጣለን፣ የተማረ ሰው እናከብራለን። እንደሚመስለኝ ገንዘብ ካለው ዕውቀት ላለው ነው ትልቅ ክብር የምንሰጠው። ይሄ ትንሽ ነገር አይደለም። እዚህ አገር ብዙዎቹ ተማሪዎች በኳስ ጨዋታ ስመጥር ከሆነ ተማሪ ቤት ለመማር እንፈልጋለን ነው የሚሉት። በኢትዮጵያውያን ባህል ግን ከኳስ ጨዋታው ይልቅ በቤተሰብ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ትምህርት ነው። ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ አለ። በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማለቴ አይደለም፣ እንደሕዝብ ግን ኢትዮጵያውያን ትምህርት ያከብራሉ። ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን ጥንካሬ የምለው የኢትዮጵያ ባህል ሥልጣኔ አለስልሶናል። ማንንም ኢትዮጵያዊ አይቼ ይገላምጠኛል ወይንም ደግሞ ያቃልለኛል ብዬ አላስብም። ሽማግሌ በሚያይበት ጊዜ የሚያሳየው ትህትና የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች በጣም ‘ሪፋይንድ’ የሆነ እንደሚሉት የረቀቀ ጠባይ አለ። እኔ ሁልጊዜ ምሳሌ የማደርገው ጀርመን አገር ተማሪ እያለን የገጠመኝን ነው። የተማሪዎች ማህበር ነበረን። በመካከለኛው አውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር (Association of Ethiopian Students in Central Europe) ነበር የምንለው። ጀርመንን ጣሊያንን በተለይ ስዊዘርላንድን ያጠቃልላል። በዓመት አንድ ጊዜ ስብሰባ እናደርጋለን። አንድ ጊዜ ስቱትጋርት የምትባል ከተማ አለች – ጀርመን አገር። እዚያ ላይ እናድርግ ተባለ። እንደአጋጣሚ በዚያ ዓመት የተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እኔ ነበርኩ። ሳጠያይቅ ቦታ አጣሁ። የምንሰበሰብበት ማረፊያና መሰብሰቢያ ያለው ቦታ ያስፈልገናል። ከዚያ የቱሪስቱ ጽ/ቤት “አንድ መርከብ አለን፣ ወንዙ ላይ ይቆማል። ብዙ ሰዎች ይሰበሰቡበታል። ክፍል አለው። መኝታ ክፍል ሁሉ አለው። እናንተም ቁጥራችሁን በሰጠኸኝ መሠረት ይበቃችኋል“ አለንና እሺ አልን። መርከቡ ላይ አረፍን፣ ከተማውን እየዞርን አገር እናያለን ፋብሪካ እናያለን። ልዩ ልዩ ተቋማትን እንጎበኝና በቀኑ መጨረሻ መጥተን የምንቀመጠው የምናርፈው መርከቡ ላይ ነው። ታዲያ ሁልጊዜም ጋዜጠኛ ይከታተለናል። ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ተሰብስበው ነበር ብሎ ሪፖርት ለማድረግ። አለ አይደል የከተማ ወሬ ነው። ተማሪዎች እዚህም እዚያም መርከቡ ላይ ቁጭ ብለው ቼዝ ይጫወታሉ። ያወራሉ። በመጨረሻ ጋዜጠኛውን፣ “ሰሞኑን ስትከታተለን ቆየህ። ምንድን ነው የሚሰማህ?” አልኩት።

“እኔ የሚሰማኝ ይሄን ያህል ሰው አንድ ቦታ ተቀምጦ ድምጽ አለመሰማቱ ነው። ፀጥ ብላችሁ ነው የምትሠሩትም፣ የምታወሩትም፣ የምትጫወቱትም። እርስ በራሳችሁ ነው የምትሰማሙት እንጂ ከዚያ አልፎ ከፍ ያለ ድምጽ የለም። እንደዚህ አይነት ሰዎች አይቼ አላውቅም። እኛ ብንሆን ይሄኔ እዚህ ቦታ አንዱ ሲናገር አንዱ አይሰማም” አለኝ።

ይሄ ትዝ አለኝ። ፀጥተኞች ነን፣ አንዳንድ ጊዜም ዝምተኛነታችንን፣ ታዛዥነታችንን፣ ጨዋነታችንን እናበዛዋለን። አበበ ቢቂላ በሩጫ አሸንፎ፣ አዲስ አበባ መጥቶ፣ ከፒያሳ በአራት ኪሎ በኩል ነው ወደ ግቢ ታጅቦ የሄደው። ሰዉ ሁሉ ዙሪያውን መንገድ ላይ ይጠብቀዋል። ዝም ብለን ነው የምናየው። ዝም! አንዳንድ ጊዜ እጁን እያነሳ ሰላምታ ሲሰጠን እናጨበጭባለን። ‘አበበ ቢቂላ፣ ጎበዝ፣ የኛ ሰው፣ የምታኮራን’ የሚል ጫጫታ እንኳን የለም። ዝም ነው! ምንም የምንለው ነገር የለም። ይህን ሁሉ ነገር ሳየው ለስልሰናል። ልስላሴ ደግሞ እኮ ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም። ከባህል ጋር የተያያዘ ነው፣ ከቤተሰብ የተወረሰ ነው። ጥንካሬያችን የምላቸው እነዚህ ናቸው። ሌላው ጥንካሬያችን ተስፋ አንቆርጥም። ጨክነን እንሄዳለን። እርግጥ ነው በዚህ በስደቱ ጊዜ ሁሉም በየቦታው ሲሄድ እስኪሞት ድረስ መቼም ይጨክናል። የኛዎቹም እንደዚሁ ናቸው። በጣም ጨክነው እስከመጨረሻው ለመቋቋም በጣም ይጥራሉ። እና እነዚህን ሁሉ ከጥንካሬያችን ነው የምቆጥረው።

ድክመቶቻችንስ?

ድክመትም አለብን። ትምህርት የምንወደውን ያህል፣ ምናልባት የተማረው ክፍል ብቻ ላይሆን ይችላል ወደእዚህ የመጣው፣ ብቻ ብዙዎች እንደመሆናችን መጻሕፍት ብዙ አይሸጡም። አሁን አቶ አምሐ አስፋው፣ ግጥሙን ካሳተመ በኋላ የሚገዛኝ ስላጣሁ ሰጥቼ ነው የጨረስኩት አለ። አሁን ደግሞ ብዙዎቹን ለማውቃቸው ሁሉ ሰጥቼ አዳረስኩና የተረፈውን ለማን ልስጠው? በመንገድ እየዞርኩ አማርኛ ማንበብ ትችላለህ ወይ? እያልኩ የምሰጠው አይደለሁም አይነት ነው አነጋገሩ። ትንሽ እዚያ ላይ ደከም የምንል ይመስለኛል። በዛ ላይ የቋንቋ ሽግግር ላይ ነው ያለነው። ለምሣሌ የእኔ ልጆች ሁሉም አማርኛ አያነቡም። እንግሊዝኛ ነው የሚያነቡት። ይሄ ደግሞ የባህል ችግር ነው ልልህ ነው። ማንኛውንም ስደተኛ የሚያጋጥመው ችግር አለብን።

አመሰግናለሁ፣ አንዳንዴ ደግሞ ወደዚህ ስንመጣ የአገር ቤት ልማዳችንን ይዘን የምንመጣበት ሁኔታ ይታያል። በጎውን ነገር ይዞ መምጣትና ከዚህኛው አገር ህግና ሥርዓት ጋር አስማምቶ መጠቀም መቼም ክፉ አይደለም። ነገር ግን ለመኖር ስንል መለወጥና መሻሻል ያለብንን ያህል አንገፋበትም፣ ለመማር አንደክምም፣ እርስ በርስ አለመግባባት ይታያል፣ እንደሌሎቹ ኮሚኒቲዎች ጠንካራ አይደለንም፣ መደማመጥ ይጎድለናል፣ የዲሞክራሲ ባህል ባለበት ሃገርም ሆነን የተለያዬ ሃሳብን ማስተናገድ ያቅተናል እንባላለን። ይህን ነገር እንዴት ያዩታል?

እንግዲህ ጨዋነት አለ አይደለም? ቅድም ያልኩት ጨዋነት እኮ ሰው የሚናገረውን ሁሉ ይዞ ጭጭ ማለት ነው። ይሄ አዲሱ ባህል መጥቶ ሃሳቡን መግለጽ በሚጀመርበት ጊዜ ሌላውን ይቆረቁረዋል። ‘ዝም ብለህ ሰምተህ በጨዋነት ዝም አትልም ወይ?’ የሚለውም ነገር ሊኖር ይችላል። እርግጥ ነው አለመግባባት አንዳንድ ጊዜ ያስቸግራል። የሚገርምህ … በአንድ ወቅት ቅንጅትን እንደግፋለን በምንለው መሃል ችግር ተፈጥሯልና አስታራቂ ሰው እንፈልግ ተብሎ አንድ ሰው፣ እገሌ ይሁንልን፣ “እንዴት ያለ ጎበዝ ሰው መሰለህ። እባክህ ጠይቀው” ብሎ ስልክ ደወለልኝ። “አይ ጥሩ ነው እጠይቀዋለሁ” አልኩኝ። በኋላ ሌላ ሰው ደግሞ እንደዚሁ ደወለልኝና፣

“ሰዎች መፈለግ አለብን” ሲል፣ “ኧረ ካልክስ እንደው ሌሎችም ሰዎች ጠይቀውኛልና እስኪ ሰው እንፈልጋለን። አንዱ የተጠቆመውም ሰው እገሌ ነው” ስለው ኡኡ አለ።

“እሱማ ያበላሻል እንጂ ምን ችግር ይፈታል?” ከዚያ ሽማግሌ አይሆንም ያለበትን ምክንያቱን ነገረኝ። ያኛውም ሽማግሌ ይሁን ያለበትን ምክንያቱን ነገረኝ። ተውኩት። የትኛውን ልመነው? ሁለቱም የማውቃቸው ሰዎች ናቸው። እስከዚህ ድረስ ሰዎች የፖለቲካ አስተያዬታችን በጣም ተለያይቷል። ባህሉን አልለመድነውም ይመስለኛል። ችግር አለብን አንድነት ለመፍጠር። እኛም እኮ በሕይወታችን ግለሰቦች ነን። ወደ አገርቤት ስትሄድ ቤቶቹ ሁሉ ለየራሳቸው ናቸው። አንደኛው እርሻው ላይ ነው፣ ሌላው ወደዚያ ነው ያለ። የሚገናኙት ገበያ ነው። ገበያ ደግሞ የሚተዋወቅ ሰው የለም። ዝም ብሎ ገበያ ውሎ ነው የሚሄደው። ከቤተክርስቲያን ጸሎትም በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ነው የሚሄደው እንጂ አንዱ ካንዱ አይገናኝም። ካህናቱ ብቻ ናቸው ደጀሰላም ውስጥ ገብተው፣ የቆራቢ ራት በልተው የሚሄዱ እንጂ ያ የሚያስቀድሰው ሰው እኮ የለም። እዚህ አገር የቅድስት ማርያም አስቀዳሾች ከቅዳሴ በኋላ አብረው ምግብ ሲመገቡ አይቼ በጣም ነው ደስ ያለኝ። እንደዚህ ያለ ግንኙነት ባገራችን የለም። ካህናቱና ሕዝቡ እኮ አይተዋወቁም። ደግሞ ያንድ ቤተክርስቲያን ሰዎችም አይደለንም። ዛሬ እዚህ አስቀድሳለሁ በሚቀጥለው ጊዜ ራቅ ብዬ እዚያኛው አስቀድሳለሁ። በማህበር የተያያዝንም አይደለንም። አንዳንድ ሰንበቴ እንደዚህ ካልሆነ በስተቀር። አብረን የምንሠራ ሰዎች አይደለንም።

ፖለቲካነክጽሑፎችንአልፎአልፎሲጽፉተመልክቻለሁ።አንዳንዴበተረት፣በባህላዊየአጻጻፍመንገድያቀርቡታል።ሌሎችምአሉ።ብዙሰዎችያንእየጠቀሱደግፈውበሬዲዮሲናገሩምሰምቻለሁ።እዚህአካባቢቅዳሜናእሑድበኢትዮጵያውያንየሚዘጋጁየሬዲዮፕሮግራሞችአሉ።ተቃውመውየሚጽፉምአሉ።እናየእርስዎንየፖለቲካተሳትፎእንዴትነውየሚመለከቱት? ራስዎንእንደፖለቲከኛያዩታል?

አንድ ጊዜ በካህናቱ በኩል አንድ ተግሳጽ ደርሶኝ ነበር። ‘እንደው ለምን በማይገባ ነገር ይከሱኛል’ ብዬ በስጨትጨት ስል አቶ አሰፋ ጫቦ፣ ታስታውሰዋለህ?

አዎ፣ በደንብ።

ይገርምሃል ያላሰብኩትን ነው ያነሳልኝ። “አንተ እኮ ወደድክም ጠላህ ‘ፐብሊክ ፊገር’ (ታዋቂ ሰው) ሆነሃል” አለኝ። እኔ ያን አላሰብኩትም ነበር፣ በቅናት አንዳንድ ነገር እጽፋለሁ እንጂ። “ስለዚህ እንደዚህ ያሉ ሰዎች እንኳን ከቃል ከኃይልም ይጠበቃል። ማለቴ ለመቃወም ይፈለጋሉ። ‘ፐብሊክ ፊገር’ ከሆንክ ይህን መጠበቅ አለብህ” አለኝ። አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ይናገራሉ፣ እኔም ደሞ ዝም ብዬ አላይም – የምንቀው ካልሆነ። የማልንቀው ከሆነ በተለይ ስሜን የሚያጠፋ ከሆነ እናገራለሁ። ስለዚህ የሚጠበቅ ነው ማለቴ ነው። አቶ አሰፋ ጫቦ እኮ ነገረኝ። ዋናው ነገር ማየት የምችለው ፊት ለፊት ከሚነገሩት ውስጥ ቅድም እንዳልከው የሚያደንቁና የሚቀበሉ እንጂ የሚጣሉ ብዙም ቁጥራቸው አነስ ያለ ይመስለኛል። በዚያ በኩል እጽናናለሁ። አቶ ሠይፉን ታስታውሰዋለህ የንግድ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የነበረ ኢትዮጵያ? በጣም የታወቀ ነው። በቅርብ ጊዜ ነው ያረፈው። አንድ ጊዜ አሜሪካን ሃገር ሊጎበኝ መጥቶ ፈልጎ ስልክ ደወለልኝ። “እንደምን ነህ? ደህና ነህ ወይ?” ብሎ ጠየቀኝ። እግዜር ይስጠው። ከዚያ “የምትጽፋቸውን ጽሑፎች ሁሉ እንከታተላለን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን፣ እንዲያውም አንድ ነገር ልንገርህ” አለኝ። “እስቲ ምንድነው?“ አልኩት። “አንድ ሰው ሃኪም ቤት ተኝቶ ልጠይቀው ሄድኩና ምን ላምጣልህ? ስለው“ ሃኪም ቤት ሲኬድ ምናምን ተይዞ ይኬድ የለም?

“ምን ላምጣልህ? ወደ ውጪ ልሄድ ነውና እዚህ በመሆንህ ልታገኘው ያልቻልከው ነገር ካለ ንገረኝና ላምጣልህ ብዬ ብጠይቀው፣ “የጌታቸው ጽሑፍ ወጥቷል ሲሉ ሰምቻለሁና እሱን ፈልገህ አምጣልኝ ብሎ ነገረኝ። እና የማያውቅህ ሰው እንደዚህ አለ” ሲለኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ። አንድ ልጅ ደግሞ ”ከኢትዮጵያ ከመጣሁ ስድስት ነው ሰባት ወሬ ነው” አለኝ ኢሜል ልኮ፣ “እኔ የጂንካ የደቡብ ሰው ነኝ። ኑሮዬ እዚያ ነው። አንተ የምትጽፈው ነገር በወጣ ቁጥር የሚልኩልን ሰዎች አሉ። እንደ ማህበር ተሰብስበን፣ የውይይት ርዕስ አድርገን እያነበብን እንተቸዋለን። ስለዚህ በአካል ልተዋወቅህ እፈልጋለሁ” ብሎ ተዋወቀኝ። ታዲያ እንዴት ታገኙት ነበር? ስለው፣

“ይልኩልናል ከዚያ እንሰበሰብና ‹ስለዚህ ጉዳይ ጌታቸው ምን አለ?› እያልን እንወያያለን” ብሎ ሲነግረኝ እንግዲያውስ የምጽፈው የሰው አእምሮ ውስጥ ገብቷል፣ የሰው ህሊና ነክቷል ብዬ በዚያ እጽናናለሁ። ደግሞ ማንም ሰው ቢሆን የሚጽፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ሄዶ ሥልጣን ለመያዝ ነው የሚለኝ የለም። የምጽፋቸው ጽሑፎች ስም ያተርፉልኛል ብዬም አይደለም። ስም ለማትረፍ በአካዳሚክ በምሁራኑ መሐል የማደርገው ጽሑፍ ነው የሚያተርፍልኝ። ያ ደግሞ እግዜር ይመስገን ያተረፈልኝ ይመስለኛል። ሰዎች ደብዳቤ ጽፈው ሲጠይቁኝ፣ ስለ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ምንጭ ፍለጋ ሲጽፉልኝ ‘ምንድን ነው እባክህ ይህንን ፈልግና አስረዳን። አንተ ካላወቅከው ሌላ ሰው ሊያውቀው ይችላል ብለን አንገምትም’ የሚል ደብዳቤ ሲደርሰኝ፣ ተቀባይነት እንዳለኝ አውቃለሁ። ተቀባይነት ብፈልግ እዚያ ነው እንጂ ስለኢትዮጵያ አርቲክል በአማርኛ ጽፌ በዚያ እንድመሰገንበት ወይም ስም እንዳወጣበት አላስበውም። ጨርሶ በአእምሮዬም ውስጥ የለም። የምጽፈው ከፍጹም ፍቅር የተነሳ ነው። የኢትዮጵያ ፍቅር በሽታ አለብኝ። ለባህላችን በጣም ነው የምቀናው። እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሕዝብ እኩል አስተዋፅኦ አድርገናል። የኢትዮጵያ ታሪክ አለ፣ ከሌሎች ባለታሪክ ሃገሮች ጋር እኩል የምንሰለፍ ነን የሚል እምነት አለኝ። እንግዲህ ራሴን ከኢምንት አገር መጣሁ እንዳልባልም ይሆናል የማስበው። ይሄን ያህል ጊዜ ስኖር የአሜሪካን ዜግነት አልወሰድኩም። አሜሪካ ትልቅ አገር ነች፣ የአሜሪካን ፓስፖርት ብይዝ ትልቅ ያደርገኛል። ነገር ግን ያ በአእምሮዬ ውስጥ መጥቶም አያውቅም። ያው ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ነው የምሞተው። በምንም አይነት ከኢትዮጵያ የሚለየኝ ነገር የለም። ከኢትዮጵያ ጋር በቁርባን የተጋባሁ ነው የሚመስለኝ። ሕጻን ከእናት አባቱ እንደማይለይ ያን ያህል ነው። እዚያ ቁጭ ብዬ መጻሕፍቱን ሳነብብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለሁ ነው የሚመስለኝ። ወይ ጎንደር ነኝ፣ ወይ አክሱም ነኝ፣ ወይ ደግሞ ላሊበላ ነኝ። ከዚያ በአጠገቤ ሰዎች እንግሊዝኛ እየተነጋገሩ ሲያልፉ ምንድነው ብዬ እደነግጣለሁ። እውነቴን እኮ ነው የምነግርህ። ከዚያ ለካ ሌላ አገር ነው ያለሁት እላለሁ። ጨርሶ ያለሁት እዚያ ነው። እርግጥ ነው ልጆቼ ያደጉት እዚህ ነው፣ ሥር ሰደዋል። አገራቸው አድርገውታል። እኔም ወዲያና ወዲህ እያልኩ እጠይቃቸዋለሁ፣ ይጠይቁኛልም። ነገር ግን በአካል ነው እንጂ በህሊና እዚህ የለሁም። እዚያው ኢትዮጵያ ነው ያለሁት። የእኔ አስተሳሰብ የሌላቸው ሰዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው በምልበት ጊዜ በምኞት አይደለም በማስረጃ ነው። ከልዩ ልዩ ቋንቋ መጥተን አብረን የሆንን ነን በምልበት ጊዜ ምኞቴ ነው፤ ምኞቴን ደግሞ ማስረጃዬ ስለደገፈልኝ ደስ ይለኛል። አገራችን በሰላም ኖራ፣ ሰውም እያንዳንዱ በልጽጎ፣ እንደልቡ በነፃነቱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ሻሸመኔ፣ አሥመራ፣ ሐረር፣ እየዞረ የፈለገበት ቦታ እንዲኖር የምፈልግ ሰው ነኝ። ያንን ነው ፕሮሞት የማደርገው። ግብጽ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ያነሳሁልህ ነገር አለ። በንዑሳን ኮሚዩኒቲዎች እንደዚህ ‘ማይኖሪቲስ’ (ንዑሳን) በሚባሉትና ‘ማጆሪቲ’ (ብዙኃን) በሚባሉት መካከል ያለው ግንኙነት አእምሮዬን ነክቶታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ንዑሳን እንዲበደሉ አልፈልግም። እንደውም የእነሱ አባል ለመሆን እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ እኔ እዚህ ሆኜ ስለኢትዮጵያ በምጽፍበት ጊዜ ፓርቲ ተቋቋመ ሲባል በመጀመሪያ ‘ሰብስክራይበር’ (ደጋፊ) የነበርኩት ለማን እንደሆነ ታውቃለህ? ለደቡቦቹ፣ ለእነበየነ ጴጥሮስ ፓርቲ ነበር። እነሱ ለኢትዮጵያ አንድነት ይታገላሉ፣ በየነ ጴጥሮስም በጣም ለኢትዮጵያ አንድነት ይታገላል ገንዘብ ግን የላቸውም፣ አባል ግን የላቸውም በሚባልበት ጊዜ እኔ የነሱ አባል ነው የምሆነው ብዬ በወር በወር የምከፍለው ለእነሱ ነበር። በኋላ ሥራቸው የኤትኒሲቲ ሩጫ መሆኑን ሳይ ጊዜ ነው የሸሸሁት እንጂ መጀመሪያ አባል የነበርኩት እዚያ ነው። መአሕድ (AAPO) በተቋቋመ ጊዜ እንደዚሁ አልፎ አልፎ ይጋብዙኝ ነበር ንግግር እንዳደርግላቸው። ግን ከዶክተር አሥራት ጋር በምን ምክንያት ነው ኢትዮጵያዊነትን ትተህ የአማራ ድርጅት የምታቋቁመው እያልኩ በጣም ነበር የምንከራከረው። አባልም ሆኜ አላውቅም እዚያ። ኋላ ግን መላ ኢትዮጵያ በሚባልበትና እነ አቶ ኃይሉ ሻውል በተነሱበት ጊዜ ይኸን ነው የምንፈልገው ብያለሁ። መላ ኢትዮጵያ ሁሉም በፈለገበት የሚተዳደርበት፣ ሁሉም እኩል የሚታይበት ይሁን የሚለው ነው እኔን የሚገፋፋኝ እንጂ ትዳሬም መጥፎ አይደለም፣ ጤንነቴም ይህንን ይዤ በሰላም እኖራለሁ። ሕክምናውም እዚህ ደህና ነው። ልቤ ግን ኢትዮጵያ ነው ያለው። ለዚህ ነው።

በጣም አመሰግናለሁ። ከሁለት ሰዓት ተኩል በላይ ነው የተወያየነው። እንግዲህ አንድ የማሳረጊያ ጥያቄ ነው የማቀርብልዎ። ይህም ስለባለቤትዎ ስለወይዘሮ ምሥራቅ አማረ ነው። ለማንኛውም ከእርስዎ ጋር ስጨርስ አንዳፍታ ላነጋግራቸው አስባለሁ። ወይዘሮ ምሥራቅ ለርስዎ ትልቅ ድጋፍና ጥንካሬ እንደሆኑ ይነገራል። ዶክተር አክሊሉ ሃብቴም እንዲሁ በበጎ ሲያነሷቸው ሰምቻለሁ። እና “ከእያንዳንዱ ጀግና ወንድ በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች” የሚል አባባል ያለ ይመስለኛልና እርስዎ ወይዘሮ ምሥራቅን እንዴት ነው የሚገልጿቸው?

አዎ ከምሥራቅ ጋር ያገናኘኝ ያባቴ ፀሎት ነው። አባቴን በጣም ስለማከብረውና በጣም ስለሚያስብልኝ በእሱ ጸሎት የተገናኘን ይመስለኛል። ተገናኝተን በቁርባን ከተጋባንበት ጊዜ ጀምሮ አልፎ አልፎ ብንጣላ እንኳ ከእኔ አንተ ትብስ ከእኔ አንቺ ትብሽ በማለት ነው እንጂ፤ ካንቺ እኔ እብሳለሁ በሚል አይደለም። ይሄ ትልቅ ዕድል ይመስለኛል በእኔ በኩል። ይሄን አሁን ያለሁበትን ሁኔታ በእኔ ሁኔታ ያለ ሰው ብቻ ነው የሚያውቀው። ችግሬን ቀጥ አድርጋ ነው የያዘችው። በምበሳጭበት ጊዜ፣ በምናደድበት ጊዜ እንዳልሰማ ሰምታ ነው የምታልፈው። እንዲሁ በሌላው በሌላውም ምክንያት ስበሳጭ እሷ ላይ ነው የምጮህባት። ነገር ግን ቁጭ ብዬ በኋላ ሳየው ለምን እንደጮህኩ እኔ አላውቀውም። እሷም አታውቀውም። ነገም አናነሳውም። እንደዚህ ያለች ሰው ነች። ለስላሳ ነች፣ ጠንካራ ነች ደግሞ። ለስላሳ ስልህ እንደብረት አሎሎ አለ አይደለም? እንደዚያ ነው። ብረት ደግሞ ጠንካራ ነው። እንደዛ ነው የምላት፣ ለስላሳ እንደ ብረት አሎሎ ነው የምላት። በጣም ጠንካራ ነች። ልጆቿን ሁሉ በደንብ አድርጋ ነው ያሳደገች። እኔ ላሳድጋቸውና ልከታተላቸው አልቻልኩም። እሷ በደንብ አድርጋ ነው የተከታተለቻቸው። የምጽፈውን ሁሉ የታተሙትን መጻሕፍት ሁሉ ታይፕ ያደረገችው እሷ ነች። በዚያ ላይ ደግሞ ስሟ እንዲጠራ፣ እንድትታወቅ አትፈልግም።

እንዴት አድርገህ እንደምታነጋግራት አላውቅም። እሽ ካለችህ እንደዚህ ያለ ስሜት ነው ያላት። ሕይወቷን ለእኛ ነው የሰጠችው። አንድ ቦታ ልሂድ ባልኳት ቁጥር እዚያ ይዘን የምንሄደውን ነገር ሁሉ አዘጋጅታ መሄድ ነው። ወደ ስብሰባ ወይም የትም ቦታ ብቻዬን መሄድ ስለማልችል እሷ ‘አይ እኔ ቤት እውላለሁ’ አትልም። እኔም አንዳንድ ጊዜ በተጋበዝኩበት ቦታ ሁሉ ለመሄድ የማልፈልገው እንዲያው እንዳይጨንቃትና እንዳልጎትታት፣ ቤቷ አርፋ እንዳትቀመጥ ምክንያት እንዳልሆንባት እያልኩ ነው። እሷ ግን አንድም ቀን እንደው ዛሬስ አልሄድም አትልም። ስብሰባ ላይ ስሄድ ሄዳ፣ ንግግርም ሳደርግ አዳምጣ፣ ሌላም ሰው ንግግር ሲያደርግ አዳምጣ ነው። አጠገቤ ቁጭ ብላ ውላ ነው የምትመጣው። ስለዚህ የራሷ ሕይወት የላትም ልልህ እችላለሁ። ቤታችን ባለንበት ጊዜ እርግጥ ነው እንጫወታለን፣ እንስቃለን፣ እንተርካለን፣ የሰው ስም እናነሳለን፣ መጽሐፍ እናነባለን ሁለታችንም። እናነብና እንተቻቻለን።

ሌላው ይገርምሃል ብዙው ሰው የማያውቀው የምጽፈው በተለይ የፖለቲካ ጽሑፍ አንድም እሷ ያልተስማማችበት የለም። ብዙውን አስቀርታዋለች፣ ካለዚያም አስለውጣኛለች። በደንብ ነው የምታየው። ‘ይሄን ለምንድን ነው እንዲህ የምትለው? ይሄ ሰው ይጎዳል፣ ለምን አታወጣውም?’ ወይም ደግሞ ’ይሄን ለምን እንዲህ አትለውም?’ እንዲህ ስትነግረኝ እሰማለሁ። አንድ ጽሑፍ ደጋግሜ በማወጣበት ጊዜ መጀመሪያውኑ ጽፌ ስሰጣት ‘አሁን በሚቀጥለው ጊዜ እንደምትለውጠው ስለማውቅ አልነግርህም’ ትለኛለች። በኋላ ትጠብቅ ትጠብቅና ‘አሁን ይኸ ብቻ ቀርቶሃል’ ትለኛለች። በመጨረሻ ሄጄ ሳየው እውነትም እንዴት ሳልጽፈው ቀረሁ እላለሁ። የግዕዙን እርግጥ ብዙውን አታውቀውም። የግዕዝ ዕውቀት የላትም። ነገር ግን ታይፕ በምታደርግበት ጊዜ የፊደል ስህተት አታደርግም። ማለቴ አግባቡን ሶስት “ሀ፣ሐ፣ኀ” ሲኖረን፣ ሁለት “አ፣ዐ” ሲኖረን፣ ሁለት “ጸ፣ፀ” ሲኖረን፣ ሁለት “ሠ፣ሰ” ሲኖረን፣ አታሳስተውም። አብረን በመሥራታችንና ይህ በዚህ ነው የሚጻፈው በማለት ብዙ ከመጻፍ የተነሳ እኔም እንኳ ተሳስቼ ብጽፈው ታርመዋለች። እና በጣም እየተግባባን የምንሠራ ሰዎች ነን። ዕድለኛ ነኝ ቅድም እንዳልኩህ። ስለእርሷ አሁን አውርቼም አልጨርስም።

እግዜር ይስጥልኝ ፕሮፌሰር፣ በጣም አመሰግናለሁ።

በጣም ነው የማመሰግነው፣

ወይዘሮ ምሥራቅ!ሲድ (SEED) የተባለው ማህበር ፕሮፌሰር ጌታቸውን ሲሸልማቸው ምን ብሎ ነበር፣ “ፕሮፌሰር ጌታቸው ምሁር፣ አስተማሪ፣ አርበኛ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አፍቃሪና ምሳሌ ወይም አርኣያ የሚሆኑ አባት (ኤግዘምፕላሪ ፋዘር) እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ” ብሎ ገልጿቸዋል። ብዙዎቹን ቀደም ብለን ከፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር ተወያይተንባቸዋል። እሳቸውም ጋ ያነሳሁት ነገር ነበር። “ከእያንዳንዱ ጀግና በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች” የሚል አባባል አለ። እሳቸው የነገሩኝን ነግረውኛል። አሁን ደግሞ እርስዎ የሚያጫውቱኝን ለማድመጥ ዝግጁ ነኝ። የፕሮፌሰር ጌታቸው የትዳር ሕይወት ምን ይመስላል?

አዎ ሲድ እንዳለው እውነትም ደንበኛ አፍቃሪና ለልጆቹ ምሳሌ የሚሆን አባት ነው። በዚህ ባለበትም መከራ ውስጥ አንድ ቀን እንዲህ ሆንኩ፣ ይህን አመመኝ፣ ምን ምን ሳይል፣ ሁልጊዜ ያንን መከራውን ተሸክሞ፣ እኛን ምንም እንዳይሰማን አድርጎ፣ ምንም ሳይለወጥ ገና እንደመጀመሪያው እንደነበር የነበረ ሰው ነው። እውነትም እንደተባለው የሰው መብት ጠባቂ ነው። ሁልጊዜ ቃሉን ጠባቂ ነው። እውነተኛ ሰው ነው። እዚህ የምናየው ነው ሁልጊዜ። ሌላ የተሸፈነ ሰው አይደለም። ይኸው ነው እኔ መናገር አልችልበትም። (ሳቅ)

ፕሮፌሰር እየነገሩኝ ነበር። እሺ ካለችህ ሞክር እያሉኝ ነበር። በጣም አመሰግናለሁ። እኔ የሥነጽሑፍ ተማሪ ነኝ። የእሳቸውን ሥራዎች እከታተላለሁ። አገር ቤት ያላየኋቸውን እዚህ አግኝቼ አንብቤያቸዋለሁ። አድናቂያቸውም ነኝ። መምህሮቼ የእርሳቸው ተማሪዎች ነበሩ። ፕሮፌሰር ብዙ ሥራ ነው ያበረከቱት። የእርስዎ ምክርና ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ምናልባት ይህን ሁሉ ሥራ ሊሠሩ አይችሉም ነበር ይሆናል። ወደፊትም በዚሁ እንደሚቀጥሉበት አምናለሁ። ፈጣሪ ጤናና ረዥም ዕድሜ እንዲሰጣችሁ እመኛለሁ። እግዜር ይስጥልኝ!ሁለታችሁንም ከልብ አመሰግናለሁ።

እኛም በጣም እናመሰግንሃለን። እግዜር ይስጥልን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top