አድባራተ ጥበብ

የንጋት የሰዓሊነት ህልሙን ያሳካው ትጉ

ብዙዎች በስራ ስነምግባሩ መጠንከር ‘እንግሊዙ’ ስለሚሉት ሠዐሊ ሠማሁ። “ወደ ቤቴ የምትመጣው ይህንን ነገሮች ተከትለህ ነው” ባለኝ መሠረት ወደ መኖሪያው ዘለቅኩኝ፣ ደርሻለሁ ልለው ደወልኩ። “ደጅህ ቆሜያለሁ” አልኩት። “ኧረ? መጣሁ” ብሎ ብዙም ሳይቆይ በሩ ተከፈተ። በፈገግታ ተቀብሎኝ “እባክህ ግባ” በሚል ድምፅ ተቀበለኝ። 3 ወለል ያለው ፎቅ ግቢ መኪናም አትክልቶችንም የያዘ ነው። “ያንተ ነው?” የመጀመሪያው ጥያቄዬ ነበር። “በቅርብ የጨረስኩት ቤቴ ነው” አለኝ። ሳሎን ከመግባታችን በፊት እንደአብዛኛው ድህረ- ኮረና ቤት ጥንቃቄ የበዛበት ነበር። ጫማዬን እንዳወልቅና በራፉ ላይ ከተደረደሩት ነጠላ ጫማዎች አንዱን እንዳደርግ ከተደረኩ በኋላ ለእጄ ሳኒታይዘር ተጨመረልኝ። ለጠጥ ብሎ ግድግዳው በተለያዩ ሠዐሊያን ስራ አሸብርቋል። በምቾቱ ብዛት ‘’ይሄማ ከውጭ የመጣ ነው።” ያስባለኝ ሶፋ ላይ አረፍ አልኩኝ። አብረን የተመገብነውን ቁርስ እንዳገባደድን እያንዳንዱ ህንፃ ላይ በፍሬም የተሰቀሉ ውበ ስዕሎችን እያስጎበኘኝ ወዳ አራተኛ ፎቅ አዘገምን። ጕብኝቴ እኔ የMTV ሾው ላይ የCribs (ታዋቂዎች አሜሪካውያን የቤታቸውን የውጭና የውስጥ ዲዛይን ለህዝብ የሚያቀርቡበት ሾው) ጋዜጠኛ እሱ እንግዳ እንመስል ነበር። አራተኛው ፎቅ ወይም ሰገነቱ ላይ እንደወጣን አዲስ አበባን በከፊል ማየት በሚያስችለው እይታ (View) ተደነቅኩ። በረንዳው ላይ የእንግዳዬን እጥረት ከህንፃው እያነፃፀርኩ ፈገግ አልኩ። እዛው ሰገነት እንግዳዬ የገነባውን ስቱዲዮ አሣየኝ። የበዛ የቀለም ብልቃጥ፣ የብዙ ብሩሾች፣ ነፍስን ከስጋ የሚያዋስቡ ስዕሎች፣ የጠረጴዛ ቴኒስ፣ መቀመጫዎች፣ ግዙፍ ቴፕና ስፒከር ታጭቆበታል። አዲሳበባችንን ቁልቁል እያማተርን ወደተዋበችው ኮተቤ ወንድይራድ ት/ቤት የልጅነቱ ትዝታ በሐሳብ ነጎድን።

ደጃዝማች ወንድይራድ ት/ቤት

እስከ 12ኛ ክፍል ተምሬበታለሁ። ተሰጥኦና ባህሪ ተሰናስለው ቅጥ የሚበጅላቸው ት/ቤት ውስጥ እንደመሆኑ የወንድይራድ እኔን ሠዐሊ አድርጎ የመስራት ውለታ አለብኝ። የስዕል ማዕከሉን ቁልፍ ያዥ መሆን ድረስ ነበር። ለዚህ ብዙ ማሳያዎች ቢኖሩም የበለጡትን እናገራለው።

4ኛ ክፍል አማርኛ መምህሬ

ጢም ባለ ክፍል ውስጥ መምህሩ እየተንጎራደዱ ወደ ፊትና ወደኋላ በመደዳዎች ውስጥ እየተሽከረከሩ ወደፊት ምን መሆን እንደምንፈልግ ጠየቁን። ሁሉም የተለመዱትን ይጠራል። ፓይለት፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ መሪ የተለመዱ ተማሪዎች አፍ ላይ እየተደጋገሙ የተጠሩ ናቸው። ሁለት ተማሪዎች ግን ተለየንባቸው። እየተንቀሳቀሱ የነበሩት መምህር ቆሙ። በግርምት “መካኒክ መሆን እፈልጋለሁ” ያላቸውን ልጅ “ለምን ፈለግ መካኒክነት ከቤተሰብ የሆነ አለ?” “አባቴ ጋራዥ አለው” ብሎ መለሰላቸው፣ “አሀ ለዛ ነዋ” ብለው ጥቂት እየተንቀሳቀሱ ጠየቁ፣ ሌላ የሚያስቆማቸው መልስ ተመለሰ፣ ሠዐሊ አልኩኝ፣ ‘’ለምን፣ እንዴትና ቤተሰብ ውስጥ ሠዐሊ አለ?” “አይ ሞያውን እወደዋለሁ’’ አልሏቸው ጥቂት አፍጥጠውብኝ “ በርታ’’ ተገለሉ። ያ የትናንት የመሆን መሀላ እንጀራዬን ዛሬ ላይ አበሰለልኝ። የንጋት ህልሙን ሲያድግ ሊኖረው፤ ከጠዋቱ ተመኘው።

ጭብጨባ

ዛሬም ተከትላኛለች። የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ እህቴና እኔ ት/ቤቱ ውስጥ በተደረገ የግጥምና የስዕል ውድድር እርሷ በግጥም እኔ ደግሞ በስዕል መድረክ ላይ ረዥም ጭብጨባ ተደረገልን። ስዕል የመጀመሪያ ክፍያዋን የጀመረችው ያኔ ነው። ወደ ትልቅነት የተንደረደርኩበት መሰላሌ ነበር። መንደርደሪያ ስዕልን ሙያ ለማድረግ መኖር ነበረብኝ፣ ለመኖር ገንዘብ ያሻል። 11ኛ ክፍል ሆኜ ቀን ስራ ጀመርኩ። ብየዳ፣ ረዳት/መካኒክነት፣ ቀለም ቀቢነት ተሠማርቼባቸው ቀለብ ያገኘሁባቸው ዘርፎች ነበሩ። ሆኖም ዋናውን ጉዳይ አልረሣሁም። ስዕልን ስዕል ት/ቤት ገብቶ መማር። ሆኖም የቀን መርሀ ግብር ላይ አለ ፈለገ ሠላም ለመግባት ተፈትኜ ወደቅኩ። ተስፋ መቁረጥን ሳላስብ የማታ ተመዘግቤ መማር ጀመርኩ። አመቱን ተምሬ ጨረስኩ፣ አሁንም የቀን ለዲፕሎማ የቀን ተፈትኜ ለሁለተኛ ጊዜ ወደቅኩ። ኣዘንኩኝ። ግን አንድ ቀን እንደሚሣሳካልኝ ለውስጤ ነግሬው ስለነበር ለሶስተኛ ጊዜ ስፈተን አልፌ የአርት ስኩል ተማሪ ሆንኩ።

ስልጡኑ አስተማሪዬ

ጉዳዩ የሆነው 8ኛ ክፍል ሆኜ ነው፤ የProductive technology አስተማሪዬ በትምህርት አሰጣጣቸው፣ በአካሄዳቸው፣እጅ አሰነዛዘራቸው በጣም ይመስጡኝ ነበር። መነፅራቸው፣ ካፖርታቸው፣ የሠውነት ቅጥነታቸውና ረዥም አፍንጫቸው የሆነ የመፅሀፍ ገፀ ባህሪ ያስመስላቸዋል። ብስላቸው ብዬ ተመኘሁ :: ጉዳዩ እንዴትና የት ልሳላቸው የሚለው ነበር። ሳላስበው መምህሩ አስተምረው ሲወጡ “ብላክ ቦርዱ ላይ ሳል” የሚል ድምፅ ተሰማኝ፣ በዳስተር አፅድቼ ነደፍኳቸው፣ ገና ፊታቸው ላይ መነፅራቸውን ስጀምር ክፍሉ ውስጥ ሳቅ ተስተጋባ፣ በተለይ አፍንጫቸውን ስጨርስ ከፍተኛ ሳቅ ተጨመረ፣ ጀምሬ እስከምጨርሳቸው እየተቆራረጠ ቶኑ እየቀነሰና እየጨመረ ሄዶ ስዬ ስጨርስ ክፍሉ ተደበላለቀ፣ እንደውም ተጨበጨበልኝ። ሰሌዳው ላይ የሳልኳቸው መምህር ሳቁን ሠምተው ተመለሡ። መመለሣቸውን ያወኩት በመስኮት በኩል ነበር። ሲቀርቡ ያስታውቃል። በዳስተር ማጥፋት ጀመርኩ። ሳልጨርሰው ደረሱብኝ፣ ደነገጥኩ፣ እንደምመታ እርግጠኛ ነበርኩ፣ ብላክቦርዱን አዩት፣ ከዛ እኔን። “ማንን ነው የሳልከው?” ብለው ጠየቁኝ፣ እያተንቀጠቀጥኩ “እርስዎን “ አልኩኝ፣ አቀረቀርኩ። ታዲያ ለመመታት ዝግጁ የነበርኩትን እኔን ውዱ መምህሬ በዚያ ዘመን ባልተለመደ የመምህርነት ስነ ልቡና “ታደያ ጠይቀኸኝ ብትስለኝ ምናለበት?” ብለው ብቻ ተለዩኝ።

ጦሰኛዋ መኪና

አርት ስኩል የቀን ት/ት ከመጀመሬ በፊት ገንዘብ ነበረኝ። በተለይ የመጀመሪያ ዐመት ቆይታዬ ላይ የአመት በዐል ፖስት ካርድ ዲዛይን አድርጌና አሣትሜ በማገኘው ገንዘብ የምገባው ሚኒባስ ገዛው፣ መኪናዋ ቀን ቀን ስትሰራ ትውልና ሲመሽ ወደ ቤት ይዣት ገባለሁ። አንድ ቀን ይህቺን ጦሰኛ መኪና ይዤ ት/ቤት ስገባ የምወደውና የሚወደኝ (ይመስለኝ ነበር) አስተማሪዬ ጠራኝ፣ ኮስተር ብሎ “አንተ ማነህ?’’ አለኝ “እንዴት” አልኩት “ ነጋዴ ነህ ወይስ ተማሪ ? መኪና ምናምን እም ብራስሌት እጅህ ላይ ታደርጋለህ ለማንኛውም ተጠንቀቅ’’ አለኝ። ገረመኝ። ክፍል ስራ አዞን ከተማሪዎች ሁሉ የኔን መርጦ “እንደሱ ስሩ’’ ያላቸው መምህሬ እንዴት ተቀየረብኝ? ምን በደልኩት? መልሱ አልመጣልህ አለኝ፤ መልሱ የተመለሰልኝ ግሬድ በሚሰጥበት ቀን ሲሆን የሆነው እንዲህ ነበር፦ A እንደማመጣ እርግጠኛ ነበርኩኝ። ይህ በራስ መተማመን የመነጨው “ለክፍላችን ተማሪዎች በሙሉ ስዕሉን እንደሱ ስሩ” በመባሌ ነው። ጓደኞቼ ኤም ቢም ቢያመጡ የኔን ቢያንስ ኤ ወይም ኤ ፕላስ እንደሆነ ተሰማኝ። የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር። ሲ ተሰጥቶሀል አለኝ። “ለምን” የሚል ድምፅ ከውስጤ ወጣ። ሆዴ ተላወሰ። ምን እንዳደረኩት እርግጠኛ ሆንኩ። ተማሪ ሆኜ መኪና መያዝ መቻሌ ብቸኛው ጥፋቴ ነበር። ይህ ልሙጥ ውስጤ ላይ የተሳለ ጥቁር ነቁጥ ነበር። በእልህ ጥቁሯን ነቁጥ ልጠቀምበት እቅድ አወጣሁ። ወደ ስኬት መወጣጫ መሰላሌን ከነቁጥዋ ገጠምኩት። ይህም ቀሪውን አመታት የስዕል ችሎታዬን ለማሻሻል ከምሽቱ 11፡00 እስከ 2፡00 ሠዐት ሞዴል ሴት እያስቆምኩ ሳልኩ። በወቅቱ ት/ ቤቱ ለአንዲት ምዴል ብቻ ነበር ከፍሎ የሚያስለን እኔ ግን ከመኪናዋ ገቢ ለሞዴሎች በየቀኑ እየከፈልኩ እጅግ ብዙ ድሮዊንግ አመረትኩ። ልፋቴና እልሄ B እስኪናፍቀኝ ከፈለኝ። መምህሬን አመሠግነዋለሁ እልህ ጨምሮልኛል። ያ እልህ እስከመጨረሻው ተከትሎኛል። ጥቁሯን ነቁጥ ገጣጥሜ መሠላል አድርጌ ሠራኋት። በራሴ እምነት ነበረኝ። አያሌ ትልሞች ነበሩኝ። ከትልሞቼ መሀከል ብዙ ሠዐሊያን ስራዎቻቸውን አቅርበው ገንዘብና ክብር የሚያገኙበት ቤት መስራት። ማኩሽ ጋለሪ። በወቅቱ ቁጥር አንድ ጋለሪ በነበረው ቤት ለእንደኔ አይነቱ ሠዐሊ ስዕል መስጠት በእግር እንደመቆም ነበር። ጋለሪው ውስጥ ስራቸውን በሚያቀርቡ ወዳጆቼም መንፈሣዊ ቅናት አድሮብኝ ወደ 12 የሚጠጉ ስዕል ከምርጦቹ በጣም ምርጥ፣ ከበጣም ምርጦቹም እጅግ በጣም ምርጡን ይዤ ገሰገስኩ። ግድግዳ ላይ ስቀለው ተብዬ ሰቀልኩት። ባለቤቱ ጋሽ ተስፋዬ ከ30 ደቂቃ በላይ ስዕሉ ላይ ስሜቱ እየተቀያየረ ተመለከተ። ውስጤ ሀሴት ሞላው ምክንያቱም ሠው ለማይፈልገው ስዕል ይህን ያህል ደቂቃ አይፈጅም። ጋሽ ተስፋዬ ስዕሉን ሲገረምም እኔ 3 ነገሮችን እያብሰለሰልኩ ነበር። መርጦ ሊገዛኝ ነው፣ ገንዘብ ሰጥቶ ሌላ ስዕል ጨምር ሊለኝ ነው፣ መርጦ ሊገዛኝና አንዳንዱን ደግሞ “አልፈልግም” ሊለኝ ነው ስል ድንገት ክርር ጥብቅ ያለ ድምፅ ከገዥው ወጣ። የሆነው ከጠበቅኩት ተቃራኒው ነበር። “አልሠራም” አለኝ፤ “ለምን?’’ አልኩት። “ስራህን አልፈለኩትም፣ በቃ አልገባኝም፣ ስለዚህ ካንተ ጋር አልሠራም።” አለኝ። በጣም ተሰበርኩ። እቃዬን ሠብስቤ ወጣሁ። ጥቂት ቀናት እንዳለፉ እሱ ስራዬ ስላልገባው እኔ አልችልም ማለት አይደለም አልኩኝ። ጠንክሬ መስራቴን ቀጠልኩ።

ቴዲ አፍሮ እንጎቻዬን ጋገረልኝ

በ1997 ዓ.ም በሀገራችን ላይ የቦብ ማርሌ መንፈስ ናኘ። በነፃነት አቀንቃኝነቱ የሚታወቀው ድምፃዊ በአዲስ አበባ ዝክር ተደረገለት። ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ ዘፈኑ ተላለፈለት፣ ኮንሰርት ተዘጋጀለት፣ የስዕል ኤግዚቢሽንም በሸራተን ሆቴል እንዲደረግ ተወሠነ። ይህ እየሆነ ወደ አንድ ስቱዲዮ አቀናሁ። ጓደኞቼ በማኩሽ ባለቤት ታዘው ለሸራተኑ ኤግዚብሽን ይዘጋጃሉ፤ በምናባቸው ያለሙትን በሸራቸው ላይ ያሰፍራሉ፣ ቀለም እየተበጠበጠ ይሳላል። ቀጥ ብዬ ወደ ራሴ ስቱዲዮዬ አመራሁ። ሬድዮ ላይ የቴዲ አፍሮ “ቦብ ማርሌ” ይንቆረቆራል። ዘፈኑን እንደሠማሁት ምናብ አመነጨልኝ፤ ሙዚቃው ስሜቴን ፈንቅሎ Flying in the sky፣ Relationship እና Mother and child ብዬ የሰየምኳቸውን ስዕሎች እንድጨርስ አደረገኝ። የደረሰብኝን ትቼና እልሄን ዉጬ “ካንተ ጋር አልሠራም” ወዳለኝ ሠው ወር ሳይሞላው ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል በሚል ግምት ድጋሚ ተመለስኩ። የጋለሪው ስራ አስኪያጅ ባለቤቱ የሚቀመጥበትና ስዕሉን ሊያይበት ወደሚችል ቦታ አስቀመጠው። ጥቂት ቆይቶ ባለቤቱ መጣና ስዕሌን አየ። እንዳየው ከመቀመጫው ተነስቶ በጩኸት “ማን ነው?” “ማን ነው? የዚህ ስዕል ባለቤት?” አለ። ለመናገር አፈርኩ። በጣም ደነገጥኩ። በድጋሚ ሊያሳፍረኝ እንደሆነ ገምቼ ‘’እኔ ነኝ’’ ለማለት ዘገየሁ። ሆኖም ቀስ ብዬ ተናገርኩ። ለምን እስካሁን እርሱ ጋር እንዳልሠራሁ ጠየቀኝ። “ወር አልሞላኝም እኮ መጥቼ ነበር “እንዳልል እድሉ እንዳይወሰድብኝ ዝምታን መረጥኩ። “ወንዳታ፣ ወንዳታ ነህ” ብሎ እንደሚደውልልኝና በስራዬ ደስተኛ መሆኔን ነግሮ አሠናበተች። ማንቸስተርና ቼልሲ እየተጫወቱ በነበረበት ምሽት 4፡45 ላይ የማላውቀው ስልክ ጮኸ። “ተስፋዬ ነኝ የማኩሽ ባለቤት’’ አለኝ። በድንጋጤ “ምነው? በሠላም?” አልኩት፣ በዚያ ምሽት ያለሁበት ቦታ ድረስ ኮተቤ ድረስ መጥቶ የሰጠሁትን ስዕል ጥቂት ብቻ እንዳሻሽል ነግሮኝ ተመለሰ፣ ለሊቴን ኳሱን ትቼ ሠዋሁ። በማግስቱ ማኩሽ አደረስኩት። ስዕሉ ሸራተን የቀረበ እለት በሁለቱ የቦብ ማርሌ ሠዎች መካከል ስዕሌን ለመግዛት ፀብ መፈጠሩን ሠማሁ። ሪታ ማርሌ (ባለቤቱ) እና ሴዲላ ማርሌ (ሴት ልጁ)መካከል በነበረው ጭቅጭቅ ልጁ አሸንፋ ሶስቱንም ከ 66ዐዐ ዶላር በላይ ገዛች። እኔም እስከ ጥቂት ጊዜ ጋለሪው ውስጥ ስዕላቸው በፍጥነት ከሚሸጥላቸው ሠዐሊያን አንዱ ሆንኩ። ቴዲ አቀነቀነና በስዕል እንጎቻዬን ጋገረልኝ።

ቆይታዬ በቤተመንግስት

በ2008 አካባቢ ትዝ ይለኛል፣ በሀገራችን ሁኔታ ተረብሼ ብሩሼን አነሣሁ ወቅቱን ይገልፃል ብዬ ያሠብኩትን ሸራው ላይ አስቀመጥኩ። ብዙ ጊዜ ለፍቼበታለሁ፣ ደክሜበታለሁ። ይህንን ስዕል ለግለሰብ መሸጥ ሊዋጥልኝ አልቻለም። ከስዕሎቼ ሁሉ ለዚህ ስዕል ሰጠ ሁ። በእውነት ተሠዋሁለት። ተመስጦዬን፣ ጭንቀቴንና ህመሜን እንዲሁም መገለጥን ያካተተ ስለሆነ የአንድ ግለሰብ መኖሪያ ማሳመሪያ ወይም በጣት የሚቆጠሩ ሠዎች ሆቴል እራት እየበሉ ወይን የሚተነፍሱበት ሬስቶራንት ማድመቂያ እንዲሆንም አልሻም። የምጥልበት ሳይሆን የማስረክብበት አስጨነቀኝ። ሆዴን ያባባኝ የመጀመሪያዬ ስዕል ሳይሆን ይቀራል? በአይነ ህሊናዬ ወድቄ የተነሣሁባቸውን ቀናት አስቤ ሲጨንቀኝ ዝም አልኩኝ። ኧረ እንደውም ተውኩት። ያጋጣሚ ነገር አንድ ስዕሌን በተደጋጋሚ ይገዙኝ የነበሩ አንድ ባለሀብት ስቱዲዮዬ ውስጥ ከተመለከቷቸው ‘ አይሸጥም’ ያልኩትን ወደዱት። ቀልባቸው ያረፈበትን እንደለመዱት ወደ ቤት ሊወስዱ “ስንት ይሸጣል?” አሉኝ። የመጀመሪያውን እምቢታ ተረዱ። ‘አይቻልም እንዲቀመጥልኝ የምፈልው ሙዚየም ውስጥ ብቻ ነው። ’ አልኳቸው። ተቀየሙኝ። ዘርዝሬ አስረዳኋቸው። ከገለፃዬ በኋላ ግን ተረዱኝና ግድግዳ ፈለጉልኝ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ወር በኋላ ባለሀብቱ ስልክ ደውለውልኝ ‘ዛሬ ከቤተ መንግስት ትጠራለህ።’ አሉኝ። የማደገውን አጣሁ። አንድ ዕለት ጧት “ከቤተመንግስት 9፡00 ላይ ይደወልልሀል” ተብዬ መጠበቅ ጀመርኩ። ስቱዲዮ ላነብ ያነሣሁትን መፅሀፍ መግለጥ አልቻልኩም፣ ብሩሼ አልጨበጥ አለኝ፣ ስቱዲዮዬ ያለበትን ሠፈር ዞርኩኝ፣ ቡና ጠጣሁ ምሳም ብለሁ፣ ይህን ሁሉ ሳደርግ ግን ስልኬን ጨምቅኳት ማለት ይቻላል። የተደወለልኝ ስልክ ግን የለም። እስከ 9፡ 00 ሠዐት ጠብቄ ተስፋ ቆረጥኩ። 15 ደቂቃ እንደጠበቅኩኝ ስልኬ አንቃጨለች፣ ማንነቴን ጠይቀው “10፡15 ላይ ቤ /መንግስት ተገኝ” የሚል የወንድ ድምፅ ትዛዝ በመሠለ ቃና ነገረኝ። ከምኔው ሻወር አድርጌ ሌላ ጊዜ ቢሆን የምጎተትበትን ሱፍ አጥልቄ እንደተነሣሁ አላውቅም። ከነፍኩ። አብሮኝ ስዕል ጭኖ እንዲሄድ አንድን ባለታክሲ አነጋገርለኩ። “ የት ነህ?’’ አለች። “ቤተ መንግስት” ስለው ‘’እኮ ከቤ /መንግስት ወደ የት?” ሲለኝ “በቃ ወደዛ አካባቢ “ አልኩትና እየተለተለኝ ደረስን። ከጎኔ ቆሞ ሁለት አመልካች ጣቱን አንዱን ባንዱ ላይ እያሽከረከረ “ቀጥሎስ “ አለኝ። ወደ ቤተ መንግስቱ ጠቆምኩት። ተርበተበተ። “እዛ አልሄድም” አለኝ። ‘ገንዘብ እጨምርልሀለሁ ደግሞ አትፍራ አይዞሀ ተጋብዤ “ ነው ብዬ ወደ በሩ ተጠጋን። በፍጥነት ደህንነቶች ወደ አለንበት መጥተው” ምን ፈልጋችሁ ነው?” አሉን፣ ነገርኳቸው፣ ወረቀት ጠየቁኝ። አልነበረኝም ግን ለደውሉልኝ ደውዬ እንድገባ ተፈቀደልኝ። በጣም የሚያምር ቢሮ ውስጥ ስዕሌን ሰቀሉልኝ፣ ባለስልጣናት ከበውኝ አብራራሁ። ወደ ማብራሪያዬ መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየመጡ እንደሆነ ተነገረኝ። “ሽንቴ መጣ” አልኩኝ። በሳቅ ፈረሱ። ተፈቅዶልኝ ከመፀዳጃ ቤት ስመለስ ጥቁር ከረቫት፣ ጥቁር ሱፍና ነጭ ሸሚዝ የለበሱ ሠው ቆመዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ። መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ እመርጥ ነበር። ለሰላምታ እጄን ዘረጋሁና ሠላምታ ተለዋወጥን። ስዕሌን ተመልከተ “ወደዚህ እንዴት መጣህ’’ ስባል “እንዴት እንደመጣሁ አላውቅም የማውቀው እንዴት እንደሣልኩት ነው” ብዬ ማብራራት ጀመርኩ። እጄን ወደ ስዕሉ ቀስሬ በሠዎቹና በብርሀኑ መካከል የጠቆረ ዳመና አለ፣ ይህ ሀገራችን ውስጥ ያለውን ምስቅልቅልና የህዝቦች ሁኔታ ያሳያል። አይነት መልእክት አስተላለፍኩ። በፅሞና የሰሙኝ ጠቅላዩ “ ስዕሉን የሚታይ ቦታ ስቀሉት ለጎብኚዎች የሃገራችሁን በሙሉ እርሱ እንደነገራችሁ በሏቸው ነገር ግን ደመናውን ወይ እናተነዋለን ወይ ይዘንባል በሏቸው “ ብለው ለባለስልጣኖቻቸው ትዕዛዝ አስተላለፉ። ስሜቴ ተገማሸረ። ‘የስዕሌ ግጣሙ ግድግዳው እዚህ ነው ማለት ነው? እኔ እንደ ገበታ ሀሴት ውሃን ተክቶ ውስጤ ተንገዋለለ።

የጨዋታችን ማሳረጊያ

ምን ታደርጋዋለህ? አዱኛን አንዳንዶች እንደሚሉት አይታደሉትም ይልቁንም ይታገሉታል እንጂ፣ ይህንን ሀቅ ለማረጋገጥ ከሰ0ሊ ተክሌ በላይ ህያው ምስክር መጥራት አልችልም። ብሩሽ ቁጥር አንድን ተሠናበትኩት፣ ወደል ሀሣቡ ተጭኖኝ እጥረቱን ዘነጋሁት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top