የታዛ እንግዳ

የናዝሬቱ እሸት

የበዓል አከባበር እና የልጅነት ትዝታ

የብዙዎቻችን ህልሞች ልጅነታችን ላይ ተቀብዋል። አልፎ አልፎ ብቻ የማህበረሰባችንን አጥር አልፈን ያለምነውን እንሆናለን። ወደምንፈልገው እና ተስጥኦ በነበረን ሙያ መድመቅ ስንችል ባልተጠራንበት ስፍራ ተገኝተን ስራ እናበላሻለን። ምድር ላይ በትልቁ የተሣካላቸውን አብዛኛዎቹ ሰዎች ስናይ የልጅነት ህልማቸው ተግተው የከወኑ ናቸው። የዛሬው ሀሳባችን የልጅነት ድምቀት የነበራቸውን ከያኒያንና ያልመከነውን ህልማቸውን አብረን እንቃኛለን።

የናዝሬቱ እሸት

ገና ትንሽ ሆኖ ነጠላውን አጣፍቶ ከፒኮክ ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ሲኳትን በልቡ ሰንበት ት/ ቤት ያጠናውን መዝሙር እየደጋገመ ነበር። አዳማ ለዚህ ወጣት ያጨበጨችው ዛሬ በተለያዩ የቴቪ መስኮቶች ላይ ተመልክታው አልነበረም። በበቂ ሁኔታ የንጋት ኮከብነቱን ገና ከማለዳው መስክራለታለች። የተቀጣጠርንበት ካፌ በአጋጣሚ እኩል ተገኘን። ከዚህ ቀደም ትውውቅ አልነበረንም። ሆኖም እሱ እንጂ ፊቴን የማያውቀው እኔ አውቀዋለሁ። ኋላ ኋላ እየተከተልኩ ወንበር ሰበው የተቀመጡበት ጠረጴዛ ላይ እኔም ተቀመጥኩ። “አንተ ነህ ናትናኤል?” ሁለቱም ጠየቁኝ። “አልተሣሣታችሁም” መልሴ ነበር። እንግዳዬን ለማግኘት ስደውል “ማኔጀሩ ነን” ያለኝ ሠው አብሮት አለ። ከልብሳቸው ቀለም ውጪ ተመሣሣይ አለባበስ አላቸው። ዋናው ሠው ጨርቅ ሱሪ በሠማያዊ በሸሚዝ ለብሷል፤ ቴቪ መስኮት ላይ የሚጣደፈውና ችኩሉ ሰው ዛሬ የለም፣ ያለው የቴሌቪዠን ፕሮግራሙ መጨረሻ ላይ ተረጋግቶ ጣፋጭ መልእከት የሚያስተላልፈው እሸቱ ነው። ከፈጣን አንደበቱ ይልቅ ፈጣን አእምሮውን ያየሁበትን ጊዜ አሣለፍን። በማናጀሩ ሸዋንግዛው የለሰለሰ የዘመን ተጋሪነት ወግ ጋር ማዕዳችን ቆረስን። እዚህ ሲደርስ የገጠመውን ተነፈሠልኝ፣ ዳገቱ ፣ ቁልቁለቱን ሸለቆውና የህይወቱን ጥምዝምዞች አጫወተኝ።

ሰንበት ት/ቤትና አፄ ገላውድዮስ ት/ቤት

ቤተ ክርስትያን ጠፍጥፋ ሠርታኛለች። አስታውሳለሁ 9ኛ ክፍል አንድ ልጅ ቤተክርስትያን እንሂድ ብሎ ናዝሬት ገብርኤል ፈለገ ሠላም ሠንበት ት/ቤት አስመዘገበኝ። ብዙ ነገር ተማርኩኝ። የመጀመሪያ የህይወት ፈተናም ቢሆን የቀመስኩት እዚያው ነው። ቤ/ክርስትያኗ ሁለት አመታዊና እጅግ ደማቅ በዓላት ነበሯት። ከእነዚህ መካከል ታህሳስ እና ሀምሌ 18 ማለትም የገብርኤል ዋዜማ በሰንበት ት/ቤቱ የሚቀርብ ዝግጅት አለ። ዝግጅቱ ግጥም፣ ዜማ፣ ድራማና ስነፅሁፍ ይቀርብበታል። መድረክ ላይ የሚወጡት ደግሞ ከህፃናቱ ጀምሮ በጣም የበሰሉ ስራዎችና ከፍተኛ ዝግጅት ነበር። እና የሀምሌው ዝግጅትን ለማቅረብ ለአንድ ገፀ ባህሪ እጩ ተደርጌ ማጥናት ጀመርኩኝ። በርትቼ አጠናሁ፤ ከኔ ጋር እንዲያጠና የተመደበው ልጅ ደግሞ ነባርና በጣም ጎበዝ ነበር። ከኔና ከሱ የተሻለው ሠው ሀምሌ 18 ሌሊት እንደ አሸዋ በተበተነው ምዕመን ፌት ይቀርባል። እልህ አስጨራሽ ፉክክር ውስጥ ተገባ። ተፎካካሪዬን በአምስት ወር ጭንቅ ውስጥ መክተቴ እራሱ አስደስቶኛል። አይደርስ የለምና ቀኑ ቀረበ። ሀምሌ 18 ቀን ከሰዐት በመዝሙር እና ስነ ፅሁፍ ክፍል ተጠርቼ አድናቆት ተሰጠኝ። ፀባዬ ሸጋ መሆኔም ተመሠከረልኝ። ሆኖም ተቀናቃኝህ በልምድ ስለሚበልጥህ ዛሬ ድራማ እንዲያቀርብ እሱን መርጠነዋል አሉኝ። መጀመሪያ ላይ ሲጠሩኝ ለራሴ የነገርኩት እኔ ባልመረጥም ሊከፋኝ እንደማይገባና እዚህ የመጣሁት ከራሴ አስበልጬ ወንድሜን መውደድ እንዳለብኝ ነበር። ሆኖም ሁለቱ ኃላፊዎች እንዳልተመረጥኩ ሲነግሩኝ መርዶ መሠለኝ። ሰዋቹን ከተለየሁ በረ1ላ ንዴቴን መቆጣጠር አቅቶኝ የቤ /ክርስትያኑን ቅጥር ግቢ ጥዬ ወጣሁ። ሆኖም እራሴን ተቆጣጥሬው ተመልሼ ለሊቱን ወዳ አሳደገኝ ባዕት ተመልሼ ዝግጅቱን ታደምኩ። ኸረ እንደውም በሰንበት ት/ቤታችንን የቀረበው ዝግጅት አስደስቶኝ ለሚቀጥለው አመት በሚገርም ብቃት እንደምመጣ ቃል ገባሁ። የሆነውም እንዲያ ነበር። ከዚያ በኋላ ድራማ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን እስከመጻፍም አስተዋፅኦዬ አደገ። ጭራሽ ተፎካክረን ያሸነፈኝንም ስድ-ንባብ ፅፌ ዓለም ሰፊ መሆኗን አብረን ተውነን አሳየን። ይህን ልምድ 11ኛ ክፍል ታሪክ ላይ ተጠቀምኩት፤ መምህራችን የአፄ ቴዎድሮስን፣ አሉላ አባነጋን፣ የአፄ ዮሀንስና የጀግኖቻችንን ታሪክ በድራማ መልክ እንድናቀርብ አዘዘን። የኔ ቡድን ተማሪዎችን የሰንበት ት/ቤት ልምዴን ተጠቅሜ ከጥናት እስከ ገፀ ባህሪይ ምደባ ተሳትፌ የድራማው ቀን ከክፍላችን አንደኛ ወጣን። ሌሎች የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙዎቹ እንዳስጠናቸው ጠይቀውኝ ረድቻቸዋለሁ።

ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 2001ዓ.ም ፕሮፌሰር እንድያስ እሸቴና ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በተገኙበት ጠበቃ የመሆን ሀሳቤ አይሆንም ተባለ። በዚያ ኣዳራሽ የመጀመያዬ የስታንድ አፕ ኮሜዲ ብልጭታ አሣየሁ። ጉዳዩ “የምትጠይቁት አለ ወይ?” ተብለን እድል ሲሰጠን የሆነ ነው። ጥብቅና መማር እንደተከለከልኩ በማንሳት ‘እናቴ ልጄ ጠበቃ ሆኖ መሬቴን ያስመልስልኛል ስትል ጠበቃ ሆኜ ድራማ ስሰራ ልታየኝ ነው ማለት ነው” በማለቴ አዳራሹ አውካካ::

የመጀመሪያዋ A

የመጀመሪያ ቀን የክፍል ውሎዬ ሙልጌታ ጃዋሬ የሚባል መምህራችን እራሳችን የፃፍነውን ድራማ እራሳችን እንድንፅፍና እንድናዘጋጅ አደረገንና ከአንድ ሴትና ወንድ ጋር አቀረብኩ፣ የድራማው ይዘት አንድም ሀዘን አንድም ሳቅ እንዲኖረው ተደርጎ ክሽን ያለ ዕሁፍ ወጣው። ለሳቁም ለለቅሶውም እኩል መልስ ከተመልካች አገኘን። ይሄኔ ነበር መምህሬ ‘አንተ ኤፕላስ ታገኛለህ’ ብሎ ቀኔን ያበራው።

የመኖር ልምምድ

ህይወት በዩኒቨርሲቲ ሸጋ ነበረች። ተሰጥኦዋችንን ፈትሸናል፣ ማህበራዊ ግንኙነት ላይ አብዛኛው ደግነትን መሠረት ያደረገ ነበር። እርግጥ ዩኒቨርሲቲ እራስን መቻል መለማመጃና ማህበራዊ ህይወት መፈተሻ መድረክ ነው። ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስልና ችግሮቻችንን (በተለይ የገንዘብን) በጋራ የምንወጣበት፣ ወጪ የምንካፈልበት፣ አልባሳትን ጭምር እስከመካፈል የሚያደርስ ነው። ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ግን ሳይንሳዊ ሳይሆን ብልጠት የሞላው ትንቅንቅ ይከሰታል። እንደ ዩኒቨርሲቲው ቅን አካሄድ አይኖርም፣ ይልቁን በራስ መንገድ ትንቅንቁን መገዳደር የግድ ነው። የእኔም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ኮሜዲያንነት

ወደእዚህ ሙያ ከመግባቴ በፊት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ ሠርቻለሁ፣ አፍሮ ኤፍ ኤምና ማስታወቂያም ሠርቻለሁ። ለኮሜዲው ስራ ቲያትር ማጥናቴና ዩኒቨርሲቲ እያለሁ በየክልሉ አዲስ አበባ 4ኪሎ ካምፓስን ጨምሮከጓደኞቼ ጋር ያቀረብናቸው ስራዎች መደላድል ሆኖኛል። ኮሜዲ እንደሚታወቀው ተፅፎ በቃል ሸምደዶ ህዝብ ፊት የሚቀርብ ነው። እኔ ደግሞ ፀሀፊም ነኝ አቅራቢም ነኝ። ይህ በጣም ከባድ ሲሆን ህዝብ ፊት ቀርቦ የሚቀርብበት መንገድ ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነው። እኔ ደግሞ ለህዝብ ድምፅ መሆን እፈልጋለሁ። እኔን ለመከታተል የሚመጣ ሠው በቀልድና በቁም ነገር መካከል ሚዛን እንድጠብቅ ይፈልጋል። እዛ ለመድረስ ያለፍኩት ውጣ ውረድ አስቸጋሪ ነበር። ብዙ ወደኋላ የሚጎትቱ ነገሮች ነበሩ፣ ሆኖም አሸንፌያለሁ።

እንቅፋት አንድ

አንድ ጊዜ ማስታወቂያ የሚያፅፈኝ ባለሀብት እና ኮሜዲነትም ይሰራ የነበረ ሠው በማቀርበው ነገር የማይሆን ነገር አወራ እንደውም “ኮሜዲውን ትተህ የማስታወቂያ ፅሁፍ ስራ” አለኝ። በአፍ አልመለስኩለትም። በተግባር ቀን ከሌሊት በመስራት ስኬቴን አረጋገጥኩለት። ጉዳይ እንዲህ ሆነ። ‹ዘመነ-ፍሰሀ› የሚል ስለሴትና ወንድ እኩልነት ማጠንጠኛ የነበረ ኮሜዲ ሠራሁ። ሌላው ‹የት ነበርን› ነው። ሁለቱም ትልቅ ተቀባይነትን ያስገኘልኝ ቢሆንም እንደ ‹ነግ በእኔ› ተቀባይነት አላገኙም።

ነግ በእኔ

ከLTV ተደውሎልኝ እንደነበርና የበዐል ፕሮግራም እንድሰራላቸው መጠየቃቸውን ማናጀሬ ነገረኝ። ማናጀሬን የበዓል ፕሮግራም ማዳመቂያ መስራት አልፈልግም በላቸው አልኩት። ጥሩ ገንዘብ ሊከፍሉን ይችላሉ እኮ ሲለኝ፤ በቃ መቶ ሺህ ብር ክፈሉን በላቸው አልኩት። ደውሎላቸው በፍጥነት ወደእኔ መጣና ኑ እንነጋገር ብለውናል አለኝ። ሄድንና ተነጋገርን። ስለክፍያውም ባልኩት ተስማሙ። ቁጭ ብዬ ሳስበው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈናቀሉ ሠዎችን ገቢ ለማሠባሠብ እኔና አንዳንድ አርቲስቶችን ጠርቶን ነበር። ከዚያ ለምን የቴቪ ጣቢያውን ቀረፃ እዛ አንሠራውም የሚል ሀሳብ መጣልኝ። ወደ LTV አዘጋጆች ደውለን ቀረፃው ጎንደር ቢሆንስ ብለናቸው ተስማሙ። ሙሉ ሠራተኞችን ይዤ ጎንደር የበዐል ፕሮግራም ሠራን። መግቢያው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁርስ ሆነና ገቢው ለተፈናቃዮች ዋለ። የተቀረፀውን ቴቪው መስከረም አንድ ቀን አየር ላይ አዋለው። በሬቲንግ አንደኛ ሆነ፣ 8 ጊዜ ተደጋገመ፣ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ 156 የስልክ ጥሪ አስተናገድሁ:: በጥረቴና ውስጤ ባለው ያልሞት ባይ ተጋዳይ መንፈስ የህዝብ ፍቅር ተከተለኝ። ኮሮና መጣ እንጂ ራዲሰን ብሉ ሆቴል እሮብ ፣ አምባሳደር ሠው ሞልቶ እየፈሰሰ፣ ብሄራዊ ቲያትር ደግሞ ከመጣው ሞልቶ የተመለሠው ሠዉ በልጦ እንደነበር ጭምር ጎዳና ከተዳዳሪዎች ሠምቻለሁ። እያንዳንዱ የህዝብ ማዕበል ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ ዝግጅቴ ሲጀምርና ሲያልቅ ሲጨበጨብልኝ በአይነ ህሊናዬ “ኮሜዲው ትተህ’’ ያለኝን ሠው አዬዋለሁ። ከካፌ ወጥተን ሁለተኛውን ዙር ለመጨዋወት ሌላ ቀጠሮ አላስፈለገንም፣ ቪትዝ መኪና ውስጥ እሱ እያሾፈረ እኔ ጋቢና ተቀምጬ ወጋችንን ቀጠልን። ከአፍሪካ በግዙፍ ገበያነቱ አንደኛ የሚባለው ሠፈር(መርካቶ) ውስጥ ለውስጥ እየተዘዋወርን አወጋን። እሸቱ ሠላምታ ለሚሠጡት በሙሉ ያክብሮት አፀፌታ እየመለሰ፣ በነገር ለሚሸነቁጡት የማይጎረብጥ መልስ እየሰጠ በመሀል ሠፊውን ህይወቱን እያወጋን ቀጠልን። የአእምሮው ፍጥነት ያስደመመኝ አነዳድም ከወነ። እኔን ያወራል፣ ይነዳል፣ ለብዙ ሠዎች መልስ ይሰጣል።

እንቅፋት ሁለት

ቅድም እንዳልኩህ ፈተናዎችን ተገዳድሬያቸዋለሁ። ትንቅንቁን በጥበብ ረትቸዋለሁ። ቢሆንም ሌላም አልቀረልኝም። የ’ቤተሰብ ጨዋታ’ አዘጋጅ ነፃነት ወርቅነህ ፕሮግራሙን መልቀቅ ተከትሎ ኢቢኤስ አነጋገረኝ። በራሱ ፈቃድ መልቀቁን ከነፃነት ባልሰማ ኖሮ የ’ቤተሰብ ጨዋታ’ን አልቀላቀልም ነበር። ማለፌ ከተነገረኝ በኋላ ለአዲስ የህይወት ምዕራፍ ተዘጋጀሁ። የቴቪ ፕሮግራም አዘጋጅቼ ስለማላውቅ ጥቂት መንገራገጭ እንደሚገጥመኝ አላጣሁትም። ሆኖም ተፈተንኩ። ህዝብ ነፃነት ወርቅነህን ይወደው ስለነበርና የኔም አዘጋጅነት አልተወደደም ነበር። አቆማለሁ ሁላ ብዬ ነበር። የዝግጅቱ ፕሮዲውሰር አቶ ሳሙኤልን እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ። ለመልመድ ጥቂት እንደሚፈጅብኝ ነግሮኝ ፕሮግራሙን የራሴ እስካደርገው አግዞኛል። እንደምገምተው ዝግጅቱ ላይ በተለይ የመጀመሪያዋቹ ሠሞን ህዝቡ የነፃነት ፊት ተለምዶአል። ስለዚህ ሌላ ሠው ማየት የማይፈልጉ ብዙዎች ናቸው። ይህንን በማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ በመሠለ መልኩ ስድቦችን አስተናገድኩ። እስኪበቃኝ ተወገዝኩ። አትችልም ይቅርብህ ተባልኩ። እንዲህ ሲሆን አንድ ነገር መደረግ ነበረበት። ወይ ማቆም ወይ እንደምችል ማሣየት። የመጀሪያው አይታሰብም ሁለተኛውን መረጥኩ። ብቻዬን ቁጭ ብዬ መሻሻል ያለብኝን ነገሮች ማሠብ(Meditate) አደረግኩ። ቁዘማው የመፍትሄ ሀሳብ አመነጨና ሠራተኞቼን ሠብስቤ አወያየሁ። ኦሪጅናሉን የቴቪ ፕሮግራም(የስቲቭ ሀርቬይን) ማየት፣ ጀምሮ የአቀራረብ ለውጥ ማድረግን፣ የተለየ መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶችን መጠቀም ፣ ትያትር እና ኮሜዲ ላይ የነበረኝን ልምድ ወደ ዝግጅቱ መጨመርን ተወያየን። ለሶስት ሳምንት ብቸገርም ከ4ተኛው በኋላ የሰደቡኝና ያወገዙኝ አብዛኞቹ ሀሳባቸውን ሲቀይሩ አየሁ።የቤተሰብ ጨዋታ ለፋሁበትና ከፈለኝ። በራሴ መንገድ ተጉዤ የራሴን አድናቆት ጀመትኩበት። የዘራሁትን እንዳጭድ ተደረግሁ። ሌሊት ብቻዬን ለሾው የለፋሁትን ህዝብ ተረዳልኝ። ሁሉንም አመሠግናለሁ።“ አለኝ። ስለ ‘ቤተሰብ ጨዋታ’ የነገረኝን እንዳምን በመርካቶ የሆነው ምስክሬ ነበር፤ ስንለያይ መኪና ውስጥ ‘’አንተ ትለያለህ’’ ፣ ‘’ምርጥ ሠው” ፣ “በህይወቴ እንዳንተ ወድጄው የማቀው ሾው የለም” አይነት ድምፃችን ስለሠማሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top