የታዛ እንግዳ

የሻሸመኔው ፈርጥ

የመጀመሪያ መድረኩ እሁድ ሊሆን አርብ እና ቅዳሜ ምሽት የሚቀርበውን ማነብነብ ጀመረ። ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስቶ እስከ ማለቂያው የሚያቀርበውን በቃሉ ተለማመደ። ሲናገር፣ በምናቡ ሲጨበጨብለት ሲያስብ፣ ሲቆምና ሲቀመጥ እንዲሁም ወለሉ ላይ ሲንጎራደድ ዓይኑን ጨፍኖ መድረኩን ለመቆጣጠር ሲያስብ ሁለቱም ሌሊቶች ነጉ።

እሁድ ጠዋት ሻሸመኔ ላይ የተመሠረተው “እኛ ለእኛ ኢትዮጵያ” በመባል በመላው ኢትዮጲያ የታወቀው ክበብ ባዘጋጃው መርሀ ግብር ላይ ልምድ ካላት መድረክ መሪ ጋር መድረኩን ተቆጣጠሩት። “አበጀህ” ተባለ። ታላላቅ በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉ የቴቪ ዝግጅት ላይ ዛሬ በብቃት ቃላት ሲሸራርፍ የማናስተውለው ይህ ሠው አንድ ዝግጅት ከመቅረቡ በፊት ሳያንቀላፉ ማደርን የተማረው ገና እዚያ ሻሸመኔ እያለ መኝታ ቤቱና ሳሎኑ ውስጥ እየተመላለሰ ነበር። ደወዬ ስልኩን አነሣው፣ ተቀጣጠርን። አንድ ሆቴል በረንዳ ላይ ተቀምጠን ቡናና ስፕሪስ አዘን ወደ ዋና መንደርደሪያ ከመንጎዳችን በፊት ሌላ መንደርደሪያ አከለልኝ። ጠይም ክብ ፊቱ ላይ አይኑን እያንከባለለ “እኔ ግን እንግዳና አርአያ ለመሆን ይገባኛል?” ብሎ ጠየቀኝ። “አዎ ለማንኛውም አንተ መዝገብህን አስፈትሸኝ እኔ ደግሞ ልመዝግብ። ከፍታህን አፋልገኝ እንጂ ንገረኝ መች አልኩህ?” አልኩት ፣ ከልጅነቱ የማር ወለላ ላይ ጥቂት ቆነጠረልኝ።

አይደለም እናንተን አዳነ አረጋን ያስተማርኩ ነኝ

ልጅነቴ ጉራማይሌ ነው። የእኔና የቤተሰቤ አኗኗርም እንደዚያው….. በት/ቤት ውስጥ አስቸጋሪም ምርጥም የነበርኩላቸው መምህራን ነበሩ። ለተግባቡኝ እንጀራ ነኝ፣ ለጎረበጡኝ አስቸጋሪ፣ ከእነዚህ መካከል ለምሳሌ መlር ዘውዱ 9ኛ ክፍል አማርኛ ሲያስተምሩን እንድናብራራ በተጠየቅነው መሠረት 5 ደቂቃ ማብራሪያ ሠጠሁ። አስጨበበጨቡልኝ ብቻ ሳይሆን በየክፍሉ ይዘውኝ እየዞሩ ቀልድ ያስቀልዱኝ ነበር። ታድያ ከዚያ ት/ቤት ከወጣሁ በኋላ ስለራሴ ከእኚሁ አስተማሪዬ የረሣሁትን የሚያስታውስ ነገር ሠማሁ። ሻሸመኔ ቤተሰቦቼን ልጠይቅ የሄድኩኝ እለት እኔ የተማርኩበት እየተማረች የነበረችው ታናሽ እህቴ አማርኛ መ/ሩ እኛ ስናስቸግራቸው እንዲህ ማለት አበዙ አለችኝ። “አይደለም እናንተን አዳነ አረጋን ቀጥ አድርጌ ያስተማርኩኝ ሰው ነኝ”

ስፖርት አስተማሪዬ

አብዮት ጮራ ከፍተኛ ደረጃ ስማር ተግባቢና ሀላፊነት የሚሰጠኝም ተማሪ ነበርኩ። የክፍል አለቃ፣ የቀይ መስቀል ሀላፊ፣ የእግር ኳስ ውድድር አሰልጣኝና የሚኒ ሚድያም ሀላፊ ነበርኩ። ታታሪው የስፖርት መምህር አዲስ በሚያቅዳቸው እቅዶች በሙሉ እሱን አናግር ሲባል “ማን ነው አዳነ?” የሚል ስሜት ሳያድርበት አልቀረም የት/ቤቶች እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር መቅረቡን ተከትሎ እግር ኳስ ለማሠልጠን ጥያቄ ያቀረበው ለት/ቤቱ ር/ መምህር ነበር። እንደተለመደው ት/ቤቱ አሠልጣኝ አለው ተባለ። “ማን?” ጠየቀ። “አዳነ “ ሲሉት ተንደርድሮ ወደምማርበት ክፍል መጣ። አስተማሪውን ይቅርታ ጠይቆ ‘አዳነ አረጋ የታለ?’ አለ እጄን አወጣሁ። አፍጥጦ ‘ቀይ መስቀል አንተ፣ ቻሪቲ አንተ፣ ሚኒሚድያ አንተ፣ እግር ኳስ አሠልጣኝ አንተ አይደብርህም እንዴ?’ በጩኸት አንባረቀብኝ። በሩን የከፈተው መምህር ጨምሮ ክፍሉ በሣቅ ፈረሠ። እርግጥ ከዚያ በኋላ ተግባባን።

ባለመርሁ የእውቀት አባቴ

ግርማ እሸቱ ይባላል። ጎበዝ፣ ምርጥ መምህር የሚሉ ቃላት አይገልፁትም። 11ኛና 12ኛ ክፍል እንግሊዝኛ አስተምሮኛል። ካልገባን ቤቱ ወስዶ ያስጠናናል፣ እኔም ቤቱ እያጠኑ ከሚያድሩ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ። እሱ ጋር አምሽቼ ሳጠና አደርኩ። በማግስቱ ስነቃ መምህሬ የለም። ቁልፍና ምግብ ግን ተቀምጦልኛል። እንደራሴ ቤት ተጣጥቤ ምግቤን በልቼና ቆልፌ ወጣሁ። ወደ ት/ቤት ገሠገስኩ፣ የክፍሌን በር አንኳኳሁ፣ አብሬው ያደርኩት ሠው፣ ለካ የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜዬ የቲቸር ግርማ ነበር። “ ለምን አረፈድክ?’’ ብሎ ጠየቀኝ። ዝም አልኩ። ‘አትገባም’ አለኝ፣ ‘’ምንድነው የትም እያደራችሁ የምትመጡት’ ብሎኝ በሩን ላዬ ላይ ዘጋ።

በዓል እና ቤተሰብ

ዛሬ የከወንኩት በሙሉ ምስጋናውን የምሰጠው ለእናቴ (እትይ) ነው። አንደበተ ርቱዕ፣ አስታራቂና ይቅር ባይ ነች። የሚገርምህ እትይ 20 አመታት የተጣሉ ቤተሰብ አስታርቃለች፣የቤታችን ሁነት የተረቀቀው በእሷ ነው። በዐልን በተመለከተ የእኛ ቤተሠብ ሁለት ሀይማኖት ያከብራል፣ ፋሲካም ረመዳንም እኩል እናከብራለን። ይህ የሆነው የሁለቱም እምነት ተከታይ ስላለን ሲሆን በየበዓላቱ የአንዱ ከአንዱ ሳይበላለጥ ይከበራል። ቋንቋችንም ያው ነው። ሁሉም እህትና ወንድሞቼ ቢያንስ 3 ቋንቋ እንችላለን። እኔ ብትወስደኝ አማርኛና ኦሮምኛ እናገራለሁ፣ ወላይትኛና ጉራጊኛ ደግሞ ቢያንስ እሰማለሁ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በመጀመሪያዋቹ ሠሞን መጀመሪያ ቲያትር ሞልቼ ጋዜጠኝነት ስመደብ ልቀበለው አልቻልኩም ነበር። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ቲያትር ትምህርት ክፍል ሀላፊ የነበረውን ነብዩ ባዬን እባክህ ትያትር እንድንማር ፍቀድልን ብለን ለመንነው። ተከዘና “በመጀመሪያው ሠሞን ከ3 ነጥብ በላይ ካመጣችሁ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቲያትሪካል አርትን ትቀላቀላላችሁ” አለን። ጠንክረን ተምረን አንደኛ ሴሚስተርን በጥሩ ውጤት ነቢዩ እንዳለው ጨረስን። ሆኖም ጋዜጠኝነት ተስማማንና ወደ ቲያትር ክፍል የመዘዋወሩን ሀሳብ ተውነው። ኧረ እንደውም ረሣነው፣ አንድ እለት ዩኒቨርሲቲ ጊቢ እየተዘዋወርን ነቢዩ ባዬን አገኘነው። ጠርቶን “በቃ 3 ነጥብ ማምጣት አቃታችሁ?’’ አለን። . አቅቶን ሳይሆን ከእኛ (ጋዜጠኝነት ዲፓርትመንት) 3 ነጥብ ያመጣ ሳይሆን ወደናንተ መምጣት ያለበት ከናንተ(ቲያትር) 3 ነጥብ ያመጣ ወደኛ መምጣት ያለበት አልነው።

ተመስገን ደሣለኝ

2005 ዓ.ም በመመረቂያ አመት ላይ የሆነው ያስገርመኛል። ትምህርት ክፍላችን ጋዜጠኞችን ልምድ ለተማሪዎች እንዲያስቀስሙ ይጋብዝ ነበር። ታዲያ በእለተ አርብ መንግስትን በብዕሩ በመሸንቆጥና በመቃወም የሚታወቀውን የፍትህ መፅሄት ባለቤት ጋበዝኩት። በቀጠርኩት ዕለት ጊቢ መጣ። 400 እና 500 ተማሪ በተገኘበት ጥያቄ አቀረብኩለት። አዳራሹ ላይ የተጠጋጉ ወንበሮች ላይ ተቀምጠን ለታዳሚው ስለ እንግዳዬ አብራራሁ፣ ተጨበጨበ። የመጀመሪያዋን ጥያቄ ወረወርኩለት። የተማርከው ታሪክ ነው። በየትኛው ልጠይቅህ በታሪክ ባለሙያነት ወይስ በጋዜጠኝነት? ምረጥ አልኩት። “በጋዜጠኝነት ምክንያቱም እየሰራሁበት ስለሆነ “ አለ ። መንግስትን መቃወም ብቻ ነው ጋዜጠኝነት? ስለው እምብዛም አልቆየም “ETV መንግስትን መቶ በመቶ ልክ ነው ማለት እስካላቆመ ድረስ እኛም መንግስትን ሙሉ በሙሉ መተቸት አናቆምም” አለኝ። በሞጋች ጥያቄ የተሞላው የሀሳብ ግብግባችን እንዲህ በሚል የተመስገን አስተያየት ተገባደደ። “ይህ ልጅ ሲጠራኝ ተቅለስልሶ ነበር፤ አሁን እንደምታዩት ነብር ሆነብኝ” አለኝ።

ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን

በ2006 ዓ.ም ለጥቂት ጊዜ (3 ወር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬድዮ ላይ ከሠራሁ በኋላ ፋና ማስታወቂያ አወጣ። ያን ጊዜ ቴሌቪዝን ባይኖረውም የተደራጀ ሬድዮ ነበረው። ዝም ብዬ ተመዘገብኩ። አእምሮዬ ለሁለት ተከፈለ። ፋና ያቀረበው ገንዘብ አጓጊ ባይሆንም ልምዱ ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝቤ ገፋሁበት። አለፍኩኝ። መጀመሪያ ሬድዮ ላይ ነበር የምሰራው ከዛ ከጣቢያው ጋር በአዲስ ሀሳብ ወደ ቴቪ ዝግጅት ተሸጋገርን። ዛሬ እኔም ድርጅቴም ከፍ ብለናል። እኔና መ/ቤቴ ወደ ቴቪ አዘጋጅነት አድገናል። ከፋና ያገኘሁት ግዙፍ ልምድና እውቀት ከእግዜር ፈቃድ ጋር ይኸው እዚህ አድርሶኛል።

ገጠመኝ አስደናቂ ጥምቀት

ቀኑ ጥምቀት ነው። ቦታው ጃንሜዳ። ሁነቱን ለመዘገብ ምዕመኑ ከቦኝ እየተጠባበቅኩ ነበር። ሲሆን የነበረውን በሙሉ በጭንቅላቴ ማህደር እየሰደርኩ ነበር። ፊት ለፊቴ የቆመው ካሜራ ማን መናገር እንድጀምር በእጁ ምልክት ሠጠኝ። የሰበሰብኩትን ጉልበት መልቀቅ ጀመርኩ። እኔም በጃንሜዳ ደስ የሚል ድባብ ታጅቤ ወደ 10 ደቂቃ እንዳወራሁ ካሜራ ማኑ በድጋሚ የጀምር ምልክት ሠጠኝ። በቀጥታ ስርጭት ንግግሬ እየተላለፈ መስሎኝ ነበር ልፋቴ ‘በድጋሚ ጀምር’ ሲለኝ ግን አብሮኝ የነበረው ህዝብ ጭምር ሳቀ። ያ ሁሉ የተናገርኩት ነገር ባከነ። በሌላ ጉልበት ሁለተኛውን ንግግር ብቀጥልም ሁኔታው ገርሞኝ ነበር።

የሐዋሳው ልጅ ነገር

ሐዋሳ አሞራ ገደል ተቀምጬ በቴቪ መስኮት ያየኝ በሙሉ አንዳንዱ ሠላም ይለኛል፣ አንዳንዱ ፈርምልኝ ይልሀል፣ አንዳንዱ ይጠቋቆሙብሀል፣ አንዳንዱ ደግሞ ፎቶ እንነሣ ይልሃል። ብዙ ሠው አድናቂህ ነኝ እያለ ወደኔ ሲመጣ የተመለከተ አንድ ሠው ወደእኔ መጣ። ሠላም ብሎኝ የሚያስቅ እና የሚያሳቅቅ ጥያቄ ጠየቀኝ። “ታዋቂ ነህ ኧ?” “አይ” አልኩት። ወደኔ የሚያዩ ሠዎችን እየጠቆመኝ ይሄው ታዋቂ ባትሆን ሠዎች አያዩህም ብሎኝ ፎቶ እንነሣ ብሎ ጠየቀኝ። ብጠብቀው ብጠብቀው ዝም ብሎኝ አጠገቤ ቆሟል። ግራ ገባኝ። ለካ ፎቶም የምንነሣው በእኔው ስልክ ነው። ተነሣን።

አፍታ ቆይታ ከታላላቅ ባለስልጣናት ጋር

ጋዜጠኝነት ከሚያድልህ ነገር አንዱ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ታላላቆችን ታገኛለህ። ትልልቅ ክስተቶችን ትዘግባለህ። ዶክተር ቴዎድሮሰ አድሀኖም ለህዝብ በነበራቸው ቀረቤታና ትህትና ከበሬታ ነበረኝ። ዛሬ የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ናቸው። በጣም እኮራባቸውም ስለነበር አግኝቻቸው ለጥቂት ጊዜ ስለ ፌስ ቡክ አጠቃቀማቸውን ጠይቄያቸዋለሁ፣ አንድ ጊዜም አቶ ካሣ ተ/ ብርሀንን (በወቅቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ) አግኝቼያቸው ጥያቄ የማላበዛ ከሆነ እንደሚፈቅዱልኝ ነግረውኝ አንድ ጥያቄ ብቻ አልኳቸው፣ እንዳልኩትም አንድ ብቻ ብዬ መልሰውልኝ ቀጣይ ሲጠብቁ ጨርሻለሁ ስላቸው ገርሟቸው “ከየት ነው የመጣኸው?” ብለውኝ አጭርና ግልፅ እንዲሁም ያልተንዛዛ ጥያቄ በማቅረቤ ደስ ተሰኝተውብኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምም በአንድ ኣዳራሽ አግኝተውኝ “ፋናዎች እሠማችኋለሁ የምትሰሩበት አንግል ተመችቶኛል በርቱ” ብለውኛል።

ጋዜጠኝነት እና ፈተናው

ጋዜጠኝነት ፈተናው ግዙፍ ነው። ሙያህ ትልቅ እንደሆነ እየነገሩህ እውነተኛ ጋዜጠኝነት ግን ይሸሹታል። ሹማምንቱም ቢሆኑ ጋዜጠኛ የሚል መታወቂያ ከማበጀት ባሻገር ሙያውን እንድትሆነው አያደርጉህም። አንዳንድ ሠው ለፍላፊ ብቻ ያደርግሀል፣ መንግስትም በማንኪያ ሰጥቶ እኛ እንድናሰፋለት ይሻል። ኢጋድ እንኳ ስብሰባ ኖሮ ትንተናው ከቢቢሲ ወይም አልጀዚራ ይጠበቃል። ሆኖም እንደ ዳርት መጫወቻ ሁሉም ብሶቱን ይወረውርብናል።

ከፍታ

ቻግኒ የድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው ትውልድ ከተማ ነው። እራሱ ቤታቸውን ኢትዮጲያ በለው፣ የታሪክ ደርዝ ተሰናድቶ ታገኘዋለህ፤ የቤተሰቦቿ ቤት የግቢውን ስፋት ፣ ሆቴላቸው እና ወንዙ ሲያፏጭ በምናቤ እየቃኘሁ አከባቢውን በደንብ ቃርሜ ወደ ንግስታችን ልጅነት ጠልቄ ብዕሯ ከአባይ ዘፈኗ ግጥም ጋራ እንዴት እንደገጠመላት ነጥቡን አገኘሁትና ዶክመንተሪ ወለድኩ። የሚገርም የህዝብ አድናቆት አገኘሁበት፣ በጋዜጠኝነት ህይወቴ ፍሬዬ ነበር። ድማሜው ከእህቷ ፍሬያለም ሽባባው በኩል የጂጂዬ ምስጋና ደረሠኝ ። ከፍታህን አሁን አገኘሽው? የመጨረሻ ጥያቄ ነበር። ሙሉ ፈገግታ ረጨብኝና “ካልክ ይሁን ብያለሁ‘’ ብሎኝ የሚያምረውን ጨዋታችንን ደመደምነው። ሁለታችንም ወደየ እንጀራችን ተፈተለክን። እሱ ወደ እንግዶቹ እኔም የሱን ልፅፍለት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top