ጣዕሞት

አዶኒስን አጥተነዋል

አዳነ ወንድይራድ ወ/ጊዮርጊስ (አዶኒስ)

አብዛኞቻችን አዶኒስ በሚለው ስሙ እናውቀዋለን። እውነተኛው ስሙ አዳነ ወንድይራድ ወ/ጊዮርጊስ ነው። በሚያዝያ 29 ቀን 1956 ዓ.ም. በደብረብርሃን ከተማ ጥድአምባ ሚካኤል በሚባል ስፍራ ከአባቱ ከአቶ ወንድይራድ ወልደጊዮርጊስ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ተወለደ። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ናዝሬት በሚገኘው አፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በአርክቴክቸር ተመርቋል። በአርክቴክቸር ከተመረቀ በኋላም ለጥቂት ጊዜ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ያገለገለ ሲሆን፤ ቀጥሎም እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በጣና በለስ ፕሮጀክት ላይ ተቀጥሮ ሰርቷል። ከአርክቴክቸርነት ይልቅ ለኪነጥበብ ልቡ ያደላው አዶኒስ፤ የተማረበትን ሞያ በመተው የሙሉ ሰዓት ፀሐፊ ለመሆን ችሏል። የዚህ ታላቅ ፀሐፊ የብእር ትሩፋት ከሆኑ ስራዎች መካከል “ሳጥናኤል በዩኒፎርም”፣ “ጣውንቶቹ”፣ “የአና ማስታወሻ”፣ “ክሊዮፓትራ”… ይገኙበታል። “ፕሮፌሰሩ” እና “ኬሳራ ሳራ” አጫጭር ልቦለዶች እና የግጥም ስብስቦችም ነበሩት። ደራሲ አድነው ወንድይራድ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር። የመጀመሪያው ልጁን በራሱ የብዕር ስም አዶኒስ ብሎ ሰይሞታል። በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ላይ የ “ገመና ቁጥር 1” እና የ “መለከት“ ደራሲ በመሆን በዘርፉ የተከበረ ስም ካላቸው አንዱ ለመሆን በቅቷል። የአዶኒስን ቀጣይ ስራዎች ሁላችንም እየጓጓን እንጠብቃቸው የነበሩ ቢሆንም፤ አሁን ግን የእነዚህ ስራዎች ፈጣሪያቸው የሆነውን ራሱን አዶኒስን አጥተነዋል። የታዛ መጽሔት ዝግጅት ክፍል፤ ለአርክቴክት እና ደራሲ አድነው (አዶኒስ) አድናቂዎች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና የቅርብ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top