ስርሆተ ገፅ

ትጉው ድምጻዊ በፊያድ

በአሁኑ ጊዜ በሙዚቃው ከፍተኛ ተደማጭነትን ካገኙ ድምጻውያን መካከል አንዱ ነው። ከሰራቸው ብዙ ሙዚቃዎች ውስጥ “አንቀልባ” ሙዚቃው ተወዳጅ ሆናለች። መልካም ባህሪ አለው። ሰዎች ሲቀርቡት የበለጠ እንዲወድዱት የሚያደርግ። ከሙዚቃ ውጪ በሌሎች ሞያዎች ላይም ስኬትን አግኝቷል። በቴኳንዶ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ሻምፕዮናዎች ላይ በመሳተፍ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። በኤሌክትሪሲቲ ውድድር በኢትዮጵያ ደረጃ አንደኛ በመውጣት ሀገሩን ወክሎ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተወዳድሯል። በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርቶ ያውቃል። ጥሩ እግርኳስ ተጫዋችም ነበር። ይህ ሞያ-ብዙ የሆነው አርቲስት በፍቃዱ ያደቴ (በፊያድ) ከታዛ መጽሔት ባልደረባ ጆኒ በሪሁ ጋር ቆይታ አድርጓል። ጭማቂውን እነሆ፡-

ታዛ፡- በቅድሚያ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ!!

እንኳን አብሮ አደረሰን!!

ታዛ፡- እጅህ ከምን?

በቅርቡ ንጋት አልበም ላይ የወጣ “ሄሎ” የተሰኘ ሙዚቃ አለ። የሙዚቃ ክሊፕ በቅርቡ ይወጣል። ከሶስት ወር በፊት ነበር ያለቀው። አሁን እንዲወጣ ተወስኗል። ሌሎች ያሰብኳቸው ክሊፖችም አሉ። በትልቁ ደግሞ በዚህ ዓመት በሙሉ የሙዚቃ አልበም ለመምጣት እየተዘጋጀሁ ነው።

ታዛ፡- የአሁኑ አልበምህ ምን አዲስ ነገር ለአድማጭ ይዞ መጥቷል?

ብዙ ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል። እኔም ብዙ ዝግጅት አድርጌበታለሁ። በተቻለ መጠን ጥሩ ስራ ይዘን ለመቅረብ እየተዘጋጀን ነው።

ታዛ፡- “አንቀልባ” የሚለው ነጠላ ዜማህ በጣም ስኬታማ ነበር፤ ያኔ የነበረውን ታላቅ አድናቆት እና ተወዳጅነት፤ ቀድመህ የጠበቅከው ነበር?

እውነት ለመናገር ብዙ የደከምንበት ስራ ነበር። ከእኔ ጋር ከአንድ ዓመት በላይ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ብዙ ስለለፋሁበት፤ እንደሚወደድ ጠብቄ ነበር። በዚህ ደረጃ ይወደዳል ብዬ ግን አልጠበቅኩም። እንዲያውም በመንገድ ላይ የሚያገኙኝ ሰዎች በስሜ ከመጥራት ይልቅ “አንቀልባ” ብለው ነው የሚጠሩኝ። በዚህ ሙዚቃ ምክንያት ብዙ አድናቆቶች ደርሰውኛል። ስኬታማ ስራ እንደሆነ ነው እኔም የማስበው።

ታዛ፡- ባሳለፍነው ክረምት ከጓደኞችህ ጋር በመተባበር የቤት እድሳት ስታደርጉ ታይታችኋል

አዎ፤ ከ160 በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች የምግብ አስቤዛ አድርሰናል። ከዛም ደግሞ አንድ ዙር የደም ልገሳ ሰጥተናል። በዋናነት ደግሞ የተቸገሩ ወገኖቻችንን ቤት አድሰናል።

ታዛ፡- ለአዲስና ጀማሪ አርቲስቶች የእናንተን ምሳሌ እንዲከተሉ ምን ትመክራለህ?

ጥሩ ጥያቄ ነው። ምን መሠለህ፤ ሰው ሲያውቅህ አንተ ላይ እምነት ያሳድራል። እውቅና የሚሰጥህን ትንሽ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ደግሞ ለመልካም ነገር ማዋል ይቻላል ብዬ አስባለሁ። እውቅናቸውን ተጠቅመው ብዙ ጥሩ ነገር ማድረግ ይችላሉ። ታዋቂ መሆንም አይጠበቅባቸውም፤ በአካባቢያቸው ያሉትን መልካም ሰዎች በማስተባበር በጎ ተግባር ማድረግ ይቻላል። አሁን ለምሳሌ እኛ በጥቂቱ ካደረግነው መካከል፤ በቋሚነት በወር መቶ ብር መዋጮ እናደርጋለን። እንዲያውም ፍላጎት ያለው ሰው ካለ ከእኛ ጋር መሳተፍ ይችላል። መልካም ነገር ለሌላው ብቻ ሳይሆን ለራስም ደስ ይላል።

ታዛ፡- በፊያድ፤ ልጅ እያለህ በአንቀልባ ታዝለሃል?

…ረጅም ሳቅ… አዎ ታዝያለሁ። እናቴ እንደታዘልኩ ነግራኛለች

ታዛ፡- የአዲስ አበባ ልጅ ስለሆንክ ምናልባት በአንቀልባ ካልታዘልክ ብዬ ነው ቀደም ባለው ጊዜ በአዲስ አበባም አንቀልባ ይጠቀሙ ነበር። በአብዛኛው የሃገራችን ክፍሎችም ይጠቀሙበት የነበር ይመስለኛል።

ታዛ፡- ከራስህ ዕይታ ተነስተህ ነዋ ያዜምከው?

አዎ። ይገርማል አሁንም ያ አንቀልባ ቤታችን አለ

ታዛ፡- ክሊፑ ላይ ያለው አንቀልባ እሱ ነው?

አይደለም። ለክሊፑ ብለን የገዛነው ነው (…ፈገግ እያለ)

ታዛ፡- ያለንበት ዘመን የኮሮና ወረርሽኝ ያለበት እንደመሆኑ፤ ብዙ በየናይት ክለቡ የሚሰሩ ድምጻውያን የገቢ መቀነስና የመቸገር ሁኔታ እየታዘብን ነው። አንዳንዶች ሲያወሩ እንደሚሰማው፤ በደህና ጊዜ የኮፒራይት መብት ቢከበር፤ በእንዲህ ያለ ጊዜ እነዚህ አርቲስቶች አይቸገሩም ይላሉ

ጥሩ ጥያቄ ነው። ምን መሠለህ፤ ኮሮናው ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮች ሲከሰቱ ኪነጥበቡ ላይ ነው ተጽዕኖ የሚፈጥሩት። ከሮያሊቲ መብት ከሚገኝ ገቢ ብቻ ማንኛውም አርቲስት መኖር ይችላል። ብዙ ሰው አርቲስቶች የሚቸገሩ አይመስለውም። ሙዚቃም ቢሆን ተገቢውን ክብር ብታገኝ ጥሩ ነው። ሁሉም ሰው ሲደሰትም ይሁን ሲያዝን፤ መጽናኛውም መፈንጠዣውም ሙዚቃ ነው። ይገርምሃል ከእኛ ሀገር ያነሰ የህዝብ ቁጥር ባላቸው ሀገሮች ሙዚቀኞች እንዲህ ሲቸገሩ አይታይም። እኛ የምናውቃቸው በክለብ ውስጥ የሚሰሩ ብዙ ሙዚቀኞች ኑሯቸውን ለመግፋት ሲቸገሩ እያየን ነው። እናም የኪነጥበብ ወዳጆች የሆኑ ሰዎች፣ ኪነጥበበኞች እና መንግስት ተባብረው የሮያሊቲን መብት ቢያስከብሩ፤ ሞያተኛውም ሃገሪቱም ይጠቀማሉ ብዬ አስባለሁ።

ታዛ፡- ከድምጻዊነት ባሻገር ሌሎች ሞያዎች እንዳሉህ አውቃለሁ፤ ቴኳንዶ ትሰራ እንደነበርም አውቃለሁ፤ እስኪ ስላሉህ ሌሎች ክህሎቶች እና ሞያዎች ትንሽ ንገረን

ባሳለፍኩት አጭር ዕድሜ ብዙ ነገር ሞክሬያለሁ። ብዙ በመሞከር አምናለሁ። የኖርኩበትን ህይወት አላባከንኩም ብዬ አስባለሁ። በፕሮጀክት እንዲሁም በቦሌ ክፍለከተማ የእግር ኳስ ቡድን ላይ ተጫውቻለሁ። አምበል እስከመሆንም ደርሼ ነበር። ቴኳንዶ ሰርቼም ነበር ወደ አምስት ዓመት ደግሞ ከገነት (ከሳቦሚት) አዲሱ ጋር በመሆን በኢትዮጲስ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሰልጥኛለሁ። በነጠላ ፋይት በ2000 ዓ.ም. ወርቅ ሜዳሊያ፣ በ2001 ዓ.ም. ደግሞ የብር ሜዳሊያ፣ በሩቲን ስፓሪንግ ደግሞ በቡድን 2 ወርቅ በማግኘት በአዲስ አበባ ሻምፒዮናም፣ በኢትዮጵያ ሻምፕዮናም ዋንጫዎች እና ጥሩ ውጤቶችን አግኝቻለሁ። በቴኳንዶ ብዙ መልካም ባህሪ ያላቸውን ተማሪዎች በጥሩ ስነምግባር መቅረጽ ችያለሁ። በትምህርት በኩል በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አካውንቲንግ ተምሬ ተመርቂያለሁ። በኤሌክትሪክሲቲም ተምሪያለሁ። እንዲያውም በኤሌክትሪክሲቲ ተወዳድሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አንደኛ ወጥቼ፤ ሀገሬን ወክዬ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ሩዋንዳ ሄጄ ተወዳድሪያለሁ። ናይሮቢ ኬንያንም ጎብኝተናል። ከዛም በተጨማሪ ብዙ ንግዶችን ሞክሪያለሁ። ጌም እና ፕለይስቴሽን ቤት፣ ፊልም እና ኢንተርኔት ቤት፣ አትክልት ቤት… ሰርቼ ነበር። ባሉኝ ክፍተቶች እና ባገኘኋቸው ጊዜዎች ብዙ ስራዎችን እና ሞያዎችን ሞክሪያለሁ።

ታዛ፡- ብዙ የሞያ ባልደረቦችህ ስላንተ መልካም ሲያወሩ ሰምቻለሁ። መልካምነት ላንተ ምንድን ነው?

እንግዲህ ስለራስህ አታወራም፤ ሰው ነው ስላንተ ሊያወራ የሚችለው። እኔ ጥሩ በመሆን አምናለሁ። የእኛ ሞያ ከብዙ ሰው ጋር ያገናኝሃል። ጥሩ ባህሪ ከሌለህ ራስህን ነው የምትጎዳው። እናም ለራስህ ስትል መልካም ባህሪ ሊኖርህ ይገባል። ፈጠራ ደግሞ ቅንነትን ትፈልጋለች። እናም እኔ በተቻለኝ መጠን ለሞያ አጋሮቼም ለሌሎች ሰዎችም ቅን ለመሆን እሞክራለሁ። ጥፋት ስሰራም ይቅርታ እጠይቃለሁ። እንግዲህ ከእኔ በላይ ሌሎች የበለጠ ስለእኔ ሊያወሩ ስለሚችሉ… ከእነሱ የተሻለ ነገር መስማት የሚቻል ይመስለኛል።

ታዛ፡- የትኞቹን የሙዚቃ መሳሪያዎች ትጫወታለህ?

ማሲንቆ እሞክራለሁ፣ ክራርና ጊታርም እሞክራለሁ። ወደፊት እንግዲህ ትንሽ ቆየት ስል በክራር እና ማሲንቆ ብቻ ሙሉ አልበም ብስራ ደስ ይለኛል። ኢትዮጵያዊ የሆነ አልበም ብሰራ ደስ ይለኛል።

ታዛ፡- ስለግል ህይወትህ ጥቂት በለን እስኪ

(…ሳቅ) ለጊዜው የፍቅር ወዳጅ የለችኝም

ታዛ፡- ሙዚቃዎችህ ላይ በብዙ ቋንቋዎች ስታዜም ትታያለህ፤ እንደው ስንት ቋንቋዎችን ትናገራለህ? ሰዎች ብዙ ቋንቋ የምችል ይመስላቸዋል።

በብዙ ቋንቋ ስላዜምኩ መሠለኝ እንደዛ የሚያስቡት። እኔ ግን ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ስለሆነ አማርኛ ነው የምችለው። ብዙ ቋንቋዎችን ብችል በጣም ደስ ይለኛል። ኦሮምኛም፣ ትግርኛም፣ ስዋሂሊም… ብችል በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ስዋሂሊ ያልኩህ ምክንያት፤ ቅድም እንደነገርኩህ ውድድር ርዋንዳ ስንሄድ፤ ስልጠና ይሰጥ የነበረው በእንግሊዝኛ እና በስዋሂሊ ነበር። ይገርማህል ስዋሂሊ ቋንቋ የምችል ቢሆን ኖሮ ጥሩ አድቫንቴጅ ነበረን በውድድሩ። ከሃገር ውስጥም ቢሆን ኦሮምኛ ትንሽ ትንሽ ስለምሰማ፤ በደንብ ማውራት ብችል ደስ ይለኛል። ልጅ እያለሁ አያቴ በኦሮምኛ ነበር የምታወራኝ። ሌሎች የሃገራችንን ቋንቋዎችንም እንደትግርኛ ያሉትን ባውቅ በጣም ነው ደስ የሚለኝ።

ታዛ፡- መጀመሪያ የተመለከተህ ሰው፤ ልብ የሚለው ረጅሙን ጸጉርህን ነው። ስንት ዓመት ሆነህ ስታሳድገው?

አዎ፤ ስምንት ዓመት ሆኖታል።

ታዛ፡- እንዴት ወሰንክ ለማሳደግ?

እንዲያውም ይህንን ጥያቄ ከዚህ በፊት ተጠይቄው ነበር። ሌላ ቦታ ያላወራሁት ግን እንዴት ማሳደግ እንደጀመርኩኝ ነው። የእናቴ ማስታወሻ ነው። እናቴ ታማብኝ ሐኪም ቤት ነበረችና፤ ያኔ እኔም አብሬያት ስለነበርኩ ጸጉሬን ባለመቆረጤ፤ አደገና ድሬድ ሆነ። ይገርምሃል ድሬድ ለማድረግ ምንም ነገር አላደረግኩም። የተፈጥሮ ድሬድ ነው። ነገር ግን እንደምታየው ረጅም ሆኖልኛል።

ታዛ፡- ዳንስ ጎበዝ እንደሆንክ በሙዚቃ ክሊፖችህ ላይ (በተለይም አንቀልባ ላይ) በምታደርገው እንቅስቃሴ አይቻለሁ፤ አሁን ላይ ትሰራለህ ወይስ ጠቀልለህ ትተህዋል?

ልጅ እያለሁ ዳንስ እወዳለሁ። እኔና ወንድሜ ሙዚቃ ከፍተን እስኪደክመን እንደንሳለን። ክሊፑ ላይ ያየኸው እንቅስቃሴ ግን የቴኳንዶው ውጤት ነው።

ታዛ፡- ከ10 ዓመት በኋላ በፊያድን የት ደርሶ የምታየው ይመስልሃል?

ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። (..ሳቀ)

ታዛ፡- ሶስት አልበም ወይስ ሁለት?

ብችልማ አስር አልበም ብሰራ ደስ ይለኛል። (…እየሳቀ)

ታዛ፡- አዎን… እሱማ ደስ ይላል

ልክ ነህ። ምን መሰለህ፤ ጊዜ ለሙዚቀኛ ትልቅ ዋጋ አለው። በየዓመቱ አልበም ብሰራ ደስ ይለኛል። ለምሳሌ አስቴር 26 አልበም አላት። ጥላሁንም ከ500 በላይ ሙዚቃዎችን ሰርቷል። እነዚህን ስራዎች ስታይ ብዙ እንደሰሩ እና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንደተጠቀሙ ታያለህ። በእርግጥ አሁን ባለንበት ጊዜ ሙዚቃን ለመስራት ብዙ ውጣ ውረዶች አሉት። ብዙ ውጣ ውረድ አልፎ አንድ አልበም እንኳ ለመስራት ትልቅ ጥንካሬን ይጠይቃል። ነገር ግን በእኛ ዕድሜ አንድ አልበም ለመስራት አምሰት እና አስር ዓመት ከዚያም በላይ ሲፈጅ እንመለከታለን። ይሄ ይመስለኛል ጥሩ ናቸው ብለን እንድንወድዳቸው የሚያደርገን። እናም በእኔ እይታ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ሶስት ወይም አራት ጥሩ አልበም ቢሰራ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ላይ ትልቅ አሻራ ለማስቀመጥ የሚያስችል ይመስለኛል። እናም እኔ በትንሹ ሶስት ወይም አራት አልበም ብሰራ ደስ ይለኛል። የወደፊቱን እኔ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው። እናም እንደምኞት ይያዝልኝ…

ታዛ፡- የተወሰኑ በቀጣይ አልበምህ ላይ ያሉ ሙዚቃዎችህን አሰምተህኛል። እናም ስራ ስትቀበል ያየሁብህ አንድ ነገር፤ ግጥም ላይ በጣም እንደምትጠነቀቅ አስተውያለሁ። እስኪ ምን ዓይነት ሙዚቃ ግጥሞችን ነው የምትመርጠው?

እንግዲህ ዜማ እና ግጥም የየራሳቸው የሆነ መልክ አላቸው። ዜማ ነብስ ቢሆን፤ ግትም ደግሞ ስጋ ነው። አንዱ ከሌለ ሌላው ሊኖር አይችልም። ዜማውን ሰምተህ ስትጨርስ ግጥሙን የምትጠላው ዓይነት ባይሆን ጥሩ ነው። ለአንድ ሙዚቃ የመጀመሪያ ተደማጭነት ዜማ ትልቅ ቦታ አለው። ያንን ሙዚቃ ረጅም ዘመን እንዲደመጥ የሚያደርገው ግን ግጥሙ ነው። እናም ግጥሙ ይዘት ሲኖረው ጥሩ ነው። ነፍስን የሚሸከማት ስጋ ነው፤ ዜማንም የሚሸከመው ግጥም ነው። ስለዚህም ዜማ የሚቀበል ሆኖ ቀለል ያለ ግጥም ሲሆንም ግን አልጠላም።

ታዛ፤- ከእኔ ጋር አብሮ ቢሰሩ የምትላቸው አርቲስት፣ አቀናባሪ፣ የሙዚቃ ግጥም እና ዜማ ደራሲ… እነማን ናቸው?

ከይልምሽ (ይልማ ገብረአብ)፣ ከአለምጸሐይ ወዳጆ፣ ከአበበ ብርሃኔ.. ጋር አብሬ ብሰራ ደስ ይለኛል። እንደ ዕድል ሆኖ ከአበጋዝ ጋር መስራት ችያለው። በጣም ነው የማከብረው። በዚህ አጋጣሚ አክብሮቴን ለመግለጽ እወድዳለሁ። ከልምዱ እና ካለው እውቀት አኳያ ለወጣት ድምጻውያን ትልቅ ምሳሌ ለመሆን የሚችል ነው። እንዲሁም ወጣቱና የሚገርም ልዩ ተሰጥኦ ያለው እጅጉን የማከብረው ወንድሜ ሚካኤል ኃይሉ፣ እዮኤል መሃሪ እና ስሞላክስ ጓደኞቼ… ከእነሱ ጋር በመስራቴ እጅግ በጣም ዕድለኛ ነኝ። እጅግ በጣም ነው የምወድዳቸው የማከብራቸው። ከአለማየሁ ደመቀም ጋር እንዲሁም ከብዙ ባለሞያዎች ጋር የመሥራት ዕድል አጋጥሞኛል። በጣም እጅጉ የሚገርሙ ወጣት ድምጻውያን አሉ፤ ከእነሱም ጋር ብሰራ ደስ ይለኛል። እንደነ አንተነህ ወራሽ ዓይነት ጎበዝ የሆኑ ዜማ ደራሲዎች አሉ፤ ከእነሱ ጋር ብሰራ ደስ ይለኛል።

ታዛ፡- ቀጣዩን አልበምህ እነማን (የትኞቹ የማህበረሰብ ክፍሎች) በደንብ የሚያደምጡልህ ይመስልሃል?

ይህ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። እንዲህ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል። ነገር ግን በሁሉም ዕድሜ ላይ ያሉ ሙዚቃን የሚያዳምጡ እና ሙዚቃን የሚወድዱ፤ ለሙዚቃ ክብር ያላቸው ሁሉ ቢያደምጡልኝ ደስ ይለኛል።

ታዛ፡- አሁን በያዝነው አዲስ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ምኞት ካለህ ደስታውን፣ ፍቅሩን አንድነቱን እንዲሰጠን። አሁን ያለው ወረርሽኝም አልፎ እንድና እመኛለሁ። የሙዚቃ ባለሞያዎች ደግሞ የኮፒራይት መብታቸው ተከብሮ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ፤ ህይወታቸው እንዲሻሻል እመኛለሁ።

ታዛ፡- በመጨረሻም ለአድናቂዎችህ ምን ትላለህ? በተለያየ አጋጣሚ አድናቆታቸውን ለገለፁልኝ አክባሪዎቼ፤ በሚሰጡኝ አክብሮት እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለእኔ ባላቸው ክብር ልቤ በጣም ነው የሚነካው። ተጨማሪ የኃላፊነት ሸክም ነው የሚሰማኝ። አድናቂዎቼን “አከብራችኋለሁ፣ እወድዳችኋለሁ” ለማለት እፈልጋለሁ። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መልካም የሆነ አዲስ ዓመትን እመኛለሁ። ለአንተም ቢሆን በቀጣይ ህይወትህ ስኬታማ እንድትሆን እመኛለሁ።

ስለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን።

እኔም አመሰግናለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top