ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል – ቁጥር 37

2012 ዓ.ም. በብዙ መልኩ በመልካም ትዝታዎች የምንዘክረው ዓመት አልነበረም። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሃገራችንን እና የመላው ዓለም ህዝብን የመኖር ተስፋ ያጨለመ የአኗኗርና የግንኙነት መርሃችንን እንደገና እንድናጠና ያስገደደ አጋጣሚ ነው። በማህበራዊ ህይወት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ ያስከተለው ቀውስ በቀላሉ ሊጠገን የማይችል ደረጃ ላይ ደርሷል። በተለይም እኛን የዝግጅት ክፍላችን በቅርቡ በሚመለከተን የኪነጥበብ ዘርፍ ያስከተለው ጉዳት ቅስም-ሰባሪ ሆኖ አልፏል። ትያትር ቤቶች፣ ምሽት ክበቦች፣ ፌስቲቫሎች፣ የሙዚቃ ትርኢቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ልዩ ልዩ መድረኮች ተዘግተዋል። ሙያተኞችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችም በእጅጉ ተጎድተዋል። ሞያቸው ትርጉም እንዲያጣም ሆኗል። እንዲያም ሆኖ የኪነጥበብ ባለሞያዎቻችን ቫይረሱን ለመከላከል እና ህብረተሰቡን ለማዝናናት የተቻላቸውን ከማድረግ አልቦዘኑም።

በኪነጥበቡ ዘርፍ ሌላው የገጠመን ፈተና እንቁዎቻችንን ማጣታችን ነው። በልጅነቱ ታላላቆቹን የእድሜ-ጠገብ ሙያተኞችን የሚያስንቅ አያሌ ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ምሶሶ ለመሆን የቻለው ኤልያስ መልካ፤ ለዚህ ዓለም ህይወት እጁን የሰጠበት ዓመት ነበር። የኦሮምኛ ሙዚቃ ተወዳጁ ድምጻዊ፣ ዜማና ግጥም ደራሲ ሃጫሉ ሁንዴሳ በለጋ እድሜው ተቀጥፏል። የትግርኛ ሙዚቃ ድምፀ- መረዋው ሙዚቀኛ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ ሐጎስ ገብረህይወትም በዓመቱ መገባደጃ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ድርሰት ጸሃፊ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚና አርክቴክት አድነው ወንድይራድ (አዶኒስ) ገና ጽፎ ሳይጠግብ፣ እኛ አድናቂዎቹ ቀጣይ ስራዎቹን እንደተራብን… የልባችንን ሳያደርስ በድንገት ተለይቶናል። የሞያ ባልደረባችን የሆነው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ወልዱም ቢሆን በ33 ዓመቱ፤ ብዙ መስራት በሚችልበት እድሜ ይችን ዓለም በቃሽኝ ብሏታል?

በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን በዚሁ መጠን አስደሳች ዓመት አልነበረም። ፖለቲከኞቻችን ከድሮው የመጠላለፍ ባህል አልወጡም። ዘመናዊና የጠረጴዛ ዙርያ ውይይት ርቋቸው፤ መጠፈፋትንና መጠላለፍን እንደ አኩሪ ባህል መለያቸው አድርገውት ዓመቱን አሳልፈዋል። በዚህም ምክንያት ህዝባችን አላስፈላጊ ዋጋ ከፍሏል። ንብረት ወድሟል። ህይወት ጠፍቷል። ህዝብ ተፈናቅሏል። ሃገራችን ሰላም ልማት ፍቅር ርቋት 2012ን ዘልቃለች። በሞያተኛውም ሆነ በህዝባችን ዘንድ የተፈጠረው መጨናነቅና መደናገጥ አሳሳቢ ነበር። የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በጊዜ መፍትሔ አግኝቶ አሁን ባለንበት መንገድ እንዳይቀጥልና እንዳይባባስ፤ በጊዜ ልጓም ቢበጅለት መልካም ነው። እንዲህ ዓይነት በጤናውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ያጋጠመው ችግር በእኛ የትውልድ ዘመን ያላጋጠመን ነገር ካለመሆኑ በስተቀር፤ ከዚህ የባሰም ችግር ዓለም አጋጥሟት ያውቃል። ወደፊትም ሊያጋጥማት ይችላል።

ስለዚህም በዚህ አዲስ ዓመት መደናገጡንና ግራ መጋባቱን አቁመን፤ ችግሩን ለመፍታት ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ልንተጋ ይገባል። ደግሞም እንችላለን። “ላይቻል አይሰጥም” አይደል የሚባለው!? አበው “ሳይጨልም አይነጋም” ይላሉ። ድቅድቁ ጨለማ ከአሮጌው ዓመት ጋር አብሮ እንዲሄድ እንዳይባባስ እንደማህበረሰብ ማድረግ ያለብንን በመከወን ብቻ ችግራችን መፍታት እንችላለን። ችግሩ የራሳችን ነው መፍትሔውም እኛው ጋር ነው። አዲስ የብርሃን የተስፋና የፍቅር ዘመን እንዲሆን እንመኝ። ከምኞት ባለፈ ራሳችንን ለመለወጥም እንሞክር። በሁሉም መስክ ጠንካራ የባህል ለውጥ ማምጣት አለብን።

ወረርሽኝን በዘመናዊ ባህል እጅ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል። ፖለቲከኞቻችን ለህዝባችን እንጂ ህዝቡ ለእነሱ ሲል እንደማይኖር እና እንደማይናቆር ቢያውቁ መልካም ነው። እንዲህ ከሆነ የመኖር ተሰፋችን ይለመልማል። መድረክ የራቃቸውና የናፈቃቸው ሙያተኞችንም ወደሚወዱት መድረካቸው መመለስ ይችላሉ። በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን ዘመናዊ፣ ተራማጅ የሆነ የፖለቲካ ባህል በመገንባት፣ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተን በመፍታት ተራማጅ ባህል በማዳበር በሁሉም መስክ ሃገራችንን ለማሳደግ ልንተጋ ይገባናል። ከዚህ በተጨማሪ የዘመነ የስራ ባህል እና የዘመነ ማህበራዊ ህይወት በመምራት ፈርጀ-ብዙ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን።

እኛ የታዛ መጽሔት የዝግጅት ክፍል አባላትም፤ ኪነጥበባችን እንዲያብብ እና የፖለቲካ ባህላችን ተራማጅ እንዲሆን ጠንክረን በአዲሱ ዓመት ለመስራት ቃል እንገባለን። የታዛ መጽሔት 4ተኛ ዓመቷን በማስቆጠሯ ለእናንተ ለአንባቢዎቻችን ከፍ ያለ ምስጋናችንን ልንቸር እንወዳለን። ቀጣዩ ዓመት የሰላም የፍቅር የስኬት ዓመት ይሁንልን!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top