የታዛ እንግዳ

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ – አንጋፋ የቋንቋና የሥነጽሑፍ ተመራማሪ

(በታዛ መጽሔት ቁጥር 36፣ ከእውቁ የቋንቋና የሥነጽሑፍ ተመራማሪ ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ያደረገውን ውይይት የመጀመሪያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። ያለፈውን ክፍል የገታነው ተመራማሪው በሴሚቲክ ቋንቋ ጥናት ለመሰማራት የወሰኑበትን አጋጣሚና ወደጀርመን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትን ጉዞ አጠናቀው ወደካይሮ ስለመመለሳቸው በሰጡት ማብራሪያ ነበር። የውይይታችንን ቀጣይ ክፍል እነሆ!! መልካም ንባብ!)

ወደ ካይሮ መጣሁ። ያኔ ገና ትምህርቴን እየቀጠልኩ ነበር። አሁን ወደ ኋላ ሄጄ ነው የማጫውትህ። መጽሐፉን በቃሌ ነበር የማጠናው። እንዴት እንደሚነበብ አላውቅም። እንዲሁ ቃላቱን እያየሁ ላቲን ፊደል ነበር የማነበው። ሲነበብ ግን ቋንቋ በጆሮ ጭምር ነው የሚሰማው። በዐይን ብቻ አይደለም። ስለዚህ ልሰማው ፈለግኩ፣ አነበብኩ። ግን ጀርመንኛው ምንድነው ድምፁ? ያን የሚያነብልኝ ከየት ላምጣ? ከዚያ እኔው ራሴ ለምን አላነበውም አልኩና ወደ ጫካ ሄጄ “ዳስ ኢስ ዳይን ቮህ፣ ጉተን ሞርገን” (“ይህ ያንተ/ያንቺ… ሳምንት ነው”፣ “እንደምን አደርሽ/ አደርክ…?” በቅደም ተከተል) እንደዚህ እያልኩ ጮክ ብዬ አነበው ጀመር። ‘አይ ይሄ ምንም አያዋጣም። ከዚህ የተሻለ መንገድ መፈለግ አለብኝ። ምን ይሻለኛል?’ እያልኩ ደክሞኝ ቁጭ ብያለሁ። እንደ Botanical Garden (የአዝርእትና የአትክልት ጥናት ማዕከል) ያለ መናፈሻ ቦታ ነው። ባጠገቤ መንገድም አለ። መሸትሸት ብሏል። አንድ በጣም ነጭ የሆነ ሰው፣ ፀጉሩ ሁሉ ነጭ የሆነ፣ በጣም የከሳ ሽማግሌ ነው፣ በዚያ ሲያልፍ አየሁ። ‘ይሄ ሰውዬ ጀርመን መሆን አለበት’ አልኩና “ይቅርታ”፣ በአረብኛ ነው፣ “ጀርመን ነህ ወይ?” አልኩት። እብደት ነው መቼም። “አይደለሁም” አለኝ። “አይ ይቅርታ እንደው ጀርመን ብትሆን ኖሮ የጀርመንኛ ቋንቋ እንድታስተምረኝ ለመጠየቅ ነው እንጂ ለክፋት አይደለም” አልኩት። “አይ ጀርመንም ባልሆን በርሊን ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርኩትና ላስተምርህ እችላለሁ” አለኝ። “ጥሩ” አልኩ። “እዚያ ነው ቤቴ ና እንሂድ” አለኝና ተያይዘን ሄድን። ስንሄድ ታች ጫፉ ላይ ነው ቤቱ። ግንቡ ላይ ነው የሚኖረው። የድሆች መኖሪያ ነበር በካይሮ ደረጃ። ድሆች ስል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሚኖሩበት። እዚያ ስገባ አንድ ክፍል ነው ያለው። ቁጭ ብለን ስናወራ፣ “ሻይ ላፍላልህ ወይ?” አለኝ። “አይ ግድ የለም” አልኩት። “ጀርመንኛውን ምን ሊያደርግልህ ነው የምትማረው?” አለኝ። “እንደው ጀርመን አገር ለመሄድ እፈልጋለሁ፣ እና ጀርመንኛ ለማወቅ እፈልጋለሁ” አልኩት። “ከየት ነህ?” አለኝ። “ከኢትዮጵያ” ስለው፣ “ከተፈሪ አገር? ያ ተፈሪ እኮ አባረረኝ ከኢትዮጵያ። እኔኮ የእቴጌ፣ የንግሥት ዘውዲቱ ፈረሰኛ ነበርኩ፣ ኮንት ‘እገሌ’ እባላለሁ” አለኝ፣ ኮንት እንግዲህ ባለ ሹም ማለት ነው አይደለም? አገረ ገዥ እንደ ማለት ነው፣ እንደ መስፍን ነው። “የራሺያ ሪቮሉሽን ሲመጣ ሁላችንም ተበታተንን። ያለቀውም አለቀ፣ የቀረነውም በየቦታው ስንሄድ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ከሄዱት ውስጥ አንዱ ነበርኩ” አለኝ። ከዚያ እንግዲህ ጀርመንኛውን ጀመርን። ገንዘብ እከፍለው ነበር። ከዚያ ከእርሱ ጋራ መገናኘቱን ተውኩት። አሁን ሳስበው አንዳንዴ ስለዘመኑ ሁኔታ የሚነግረኝን ነገር ባዳምጠው ዋጋ ያለው ነበር። ውስጥ አዋቂ ስለሆነ። ነገር ግን ያን ጊዜ የፈለግሁት ሌላ ስለሆነ እሱን ተውኩት። በኋላ ሳስብ ሳስብ የጀርመን ኮሚዩኒቲ አለ።

የት ካይሮ ውስጥ?

አዎ! ቤተክርስቲያን እንዳላቸውም አውቃለሁ። ለምን እዚያ እየሄድኩ አላስቀድስም? ቅዳሴ ሲቀድሱ ሁልጊዜ ወንጌል ይነበባል፣ ስብከት ይሰበካል። ’ባይገባኝም ምን እንደሚል እስቲ ልስማው’ አልኩ። ይሄ ደግሞ ከእኛው ጋር ተጋጨብኝ፣ እሑድ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የጸሎት ፕሮግራም አለ አይደለም? ግን አንድ ጊዜ እንደምንም ብዬ ሄድኩ። እዚያ የሞላው ነጭ ብቻ ነው። ጀርመኖች እንደምታውቀው ነጮች ናቸው፣ ጠጉራቸው ሁሉ ነጭ ነው። እዚያ ውስጥ አንድ ጥቁር ብቻ ቁጭ ብሏል። እኔው ነኝ። መቼም ቄሱም ሳይገርመው አይቀርም። የምዕራባውያን ካህናት በራፍ ላይ ቆመው አስቀድሶ እሚሄደውን ሰው እየጨበጡ ነው የሚያሰናብቱ። በዚያ ሳልፍ ጨበጠኝና ተሰናበትኩ፣ አለፍኩ። በሳምንቱም መጣሁ አሁንም እንዲሁ ሄድኩ። በሶስተኛው ሳምንት ነው እንደዚህ ያዘኝ። “ምንድነህ አንተ? ምንድን ነው የምትፈልገው? የዚህ ኮሚዩኒቲ አባል ነህ? የምንናገረው ይገባሃል? ምን አስፈልጎህ ነው እዚህ እኛ መሐል የምትቀመጠው?” አለኝ። ኋላ ችግሬን ነገርኩት። “እኔ የመንፈሳዊ ተማሪ ነኝ” ስለው፣ “እንግዲያውስ መንፈሳዊ ትምህርትህን እንድትቀጥል ጀርመን አገር ስኮላርሺፕ ላስፈልግልህ?” አለኝ። “እኔ ፍላጎቴ ቋንቋ ነው። ብሉይ ኪዳንና እብራይስጥ ከሆነም እቀበላለሁ’’ አልኩ። አገኘሁ ስኮላርሺፕ። ከዚያ ጀርመን አገር ሄድኩ። የተመደብኩት ጎቲንገን (Göttingen) እሚባል ቦታ ነው። እብራይስጥ እየተማርኩ፣ ሱርስት፣ ሱሪያ ነው የሱርስት ቋንቋ፣ እየተማርኩ አንድ ዓመት እዚያው ቆየሁ። ዋናው ፍላጎቴ ግን ሊትማን ዘንድ ለመሄድ ነው። ሚስተር ሙራድ ካሚል እዚያ አለ ስላለን። የሊትማንን ታሪክ ታውቀዋለህ። ብዙ ነገር የሠራ ነው። ብዙ ስለ ኢትዮጵያ የጻፈ ሰው ነው። ከአምሳሉ አክሊሉም ጋር እንደገና በሌላ መንገድ ተገናኘን።

እዚያው ጀርመን ውስጥ?

አዎ! እሱ እንግዲህ የራሱ ታሪክ ይኖረዋል። እዚያ ተገናኝተን ገና ልንሄድ ስንዘጋጅ ግን ፕሮፌሰር ሊትማን አረፈ። አላየነውም። አይተነው ቢሆንም እንዲሁ ለሰላምታ ያህል ነው እንጂ ደክሞ ነበረ። የእሱ ተማሪዎች ነበሩ የሚያስተምሩት። እነሱ ዘንድ (University of Tübingen) ትምህርታችንን ቀጠልን። ከዚያ ትምህርታችንን ጨርሰን ወደ አዲስ አበባ መጣን። በ1962 (እ.አ.አ) ነው ወደ አዲስ አበባ የተመለስነው። ከዚያ እንደመጣን አምሳሉ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር ሥራ ያዘ፣ እኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገባሁ። በመካከለኛው ምሥራቅ ክፍልም ተመደብኩ። እንደጀመርኩ ዩኒቨርሲቲ ስጠይቅ ጊዜ የአስተማሪ ቦታ የለንም አሉ። ሆኖም የክረምት ትምህርት ፕሮግራም አላቸው፣ አስተማሪዎችን እዚያ እያመጡ ያስተምራሉ። በዚያ የትምህርት ፕሮግራም “ማስተማር ትፈልጋለህ ወይ?“ የሚል ጥያቄ ሲመጣልኝ እሺ ብዬ ገባሁ። በሚቀጥለውም ዓመት “አስተማሪነቱን ትቀጥላለህ?“ ሲሉኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ሥራ ትቼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ያኔ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ማስተማር ጀመርኩ።

የዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ጊዜዎ ምን ይመስል ነበር? እንዴትስ አሳለፉት? በኋላ ታላላቅ የሥነጽሑፍ ምሁራን ለመሆን የበቁት እንደ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ፣ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ያሉት ያኔ ተማሪዎችዎ ነበሩ?

ማስተማር በጣም እወዳለሁ። ማስተማር ስወድ እንዴት ነው፣ አንድ ሰው አልገባኝም ያለ እንደሆን እሱ ነው የሚማርከኝ። ያንን ለማስረዳት መንገድ እፈልጋለሁ። ተማሪ ቤት በነበርኩበት ጊዜ በተለይ ቁጥር እወድ ነበር። የቁጥር ስጦታ ነበረኝ። የቁጥር አስተማሪያችንም ክፍል ውስጥ ተማሪዎቹ አልገባንም ሲሉ “ና በአማርኛ ግለፅላቸው” ይለኝ ነበር። ቅድስት ሥላሴ እያለን። ሁልጊዜ ዘዴ እፈልግ ነበር። እንዴት አልገባ ሊል ይችላል ይሄ ነገር? እንደዚህ ቢሆን ምናለበት? እያልኩ መንገድ እፈልግ ነበር። መጀመሪያም አስተማሪ ለመሆን ነበር የምፈልገው እንጂ ሌላ ምንም አይነት ሥራ አይማርከኝም ነበር። ምናልባት የምጽፋቸውንም ተመልክተህ እንደሆን ደጋግሜ ነው የማነባቸው ከማሳተሜ በፊት። ይሄ ለሰው ግልፅ ይሆናል ወይ? ይሄ አይሆንም፣ ላያስኬድ ይችላል እያልኩ እደጋግማለሁ። አስተማሪነት ከመግለፅ ጋር የተያያዘ ስለሆነ እወደዋለሁ። እዚያ በማስተምርበትም ጊዜ ተማሪዎችን የማበረታታቸው አስተማሪዎች እንዲሆኑና ትምህርታቸው ላይ እንዲበረቱ ነው። ዩኒቨርሲቲ የመጣሁ ጊዜ እንደገባሁ ሁሉም የማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው። እኔ የመጣሁት ከጀርመን አገር ነው። እርግጥ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ በመቆየቴ እንግሊዝኛ ለማወቅ ዕድል አጋጥሞኛል። ከዚያ በፊትም ተማሪ ቤት ተምረናል። ግን በጀርመንኛና በአረብኛ በይበልጥ እንከታተል ስለነበር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በእንግሊዝኛ ለማስተማር ትንሽ አገድም ያደርገኛል። ሁለተኛ ደግሞ አማርኛ በማስተምርበት ጊዜ አማርኛን በእንግሊዝኛ የምገልፅበት ምን ምክንያት አለ? ግዕዝ በማስተምርበት ጊዜ ግዕዝን በእንግሊዝኛ የምገልፅበት ምን ምክንያት አለ? ተማሪዎቼ አማርኛ የሚያውቁ ናቸው፣ ተፈትነው የገቡ ናቸው። ይሄ ራሱን የአማርኛን ደረጃ ዝቅ እንደማድረግ ነው። የራሳችንን ቋንቋ ደረጃ ዝቅ የማድረግ ስሜት ስለሆነ የሚከለክለኝ እስኪመጣ ድረስ በአማርኛ ነው የማስተምረው አልኩ። አስተዳደሩን ምኑን አልጠየቅኩም። ዝም ብዬ ክፍል ገባሁና አስተማሪያችሁ እኔ ነኝ። የማስተምራችሁ የአማርኛ ስዋሰው ነው። ወይም ደግሞ ግዕዝ ነው ብዬ በቀጥታ ማስተማር ጀመርኩ። እዛ በነበርኩበት ጊዜ እነ ዮናስ አሉ፣ እነ ዮሐንስ አድማሱ አሉ፣ ጎበዞች ናቸው፣ ግጥማቸውን እንከታተላለን። አንዳንዴ ግጥም ይማርካቸዋል። ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ የቀረ እንደሆን እንቆጣቸዋለን። እንደዚህ እያደረግን ጥሩ ጊዜ ነበር የምናሳልፈው። ሌላው በማስተምርበት ጊዜ ደግሞ አማርኛና ግዕዝን ብቻ ማስተማር ሳይሆን የሃገራችንን ባህልም ማስተማር አለብን እያልኩ ከትምህርቱ ውጪ ከሰዓት በኋላ ወደማታ በሳምንት አንድ ቀን ነው ሁለት ቀን እየተሰበሰብን እናወራ ነበር። እንዲሁ ቁጭ ብለን እነሱ ይጠይቁኛል የማውቀውን እነግራቸዋለሁ። ታዲያ ይሄ ወሬ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተሰማ። ሲሰማ የሌላ ዲፓርትመንት ልጆች ዝም ብለው አዳምጠው ለመሄድ እዚያ ይመጡ ጀመር። እኔ ብቻ ሳልሆን እማስተምራቸው እማነጋግራቸው ሌሎች መምህራንም ነበሩ። በተለይ አቶ ዓለማየሁ ሞገስን አንድ ጊዜ ስለባህላችን፣ ይሄ በጸሎትና በመድሃኒት ይዳናል ስለሚባለው፣ ስለድግምት ባህል፣ አስማት ስለሚባለው መጥተው እንዲነግሩን ጠየቅኳቸው። ስለቅኔም ሌላ ሰው እየፈለግኩ፣ እንደዚህ እያደረግን ነበር የምንማማረው። ከዚህ የበለጠ እንኳ ያደረግኩት ነገር የለም። ተማሪዎቹ በእውነቱ በጣም ጎበዞች ነበሩ። ማስተማሩም ደስ ይልሃል፣ እስካሁን ብዙዎች በበጎ ስም ሲያስታውሱኝ ደስ ይለኛል።

አመሰግናለሁ ፕሮፌሰር፣ እስኪ አሁን ደግሞ ስለስደት ሕይወትዎ ያጫውቱኝ።

ከኢትዮጵያ የወጣሁት መቼም በህክምና ነው። መጀመሪያ ወታደሮቹ በመጡ ጊዜ ከየቦታው አንድ ተፅዕኖ ነበረባቸው። እናንተ ወታደር ሆናችሁ አገሪቷን ለመግዛት ብዙ ነገር ይጎድላችኋል። ሲቪሊያንስ ለምን አታስገቡም? የሚል ግፊት ነበረባቸው። በኋላ የመጣው ሃሳብ ደርግ ካለ የሲቪሊያን ደርግ አይነት ሸንጎ እናቋቁም የሚል ነው። ከዚያ ከየጠቅላይ ግዛቱ፣ ከየመሥሪያ ቤቱና ከየተቋማቱ ሁለትም ሶሥትም የተውጣጡ ሰዎች እንዲገቡበት ተደረገ። ዩኒቨርሲቲ ተሰብስበን ተነጋገርን። ማንን እንላክ? እንዴት ዩኒቨርሲቲ ከወታደር ጋራ ይሠራል? የወታደር አገዛዝ ሌላ ነው፣ የሲቪል አገዛዝ ሌላ ነው፣ በሚል ተቃውሞ ተነሳ። እንደው ቀደም ብሎ ባንዳንድ ነጥብ፣ የተመዘገበ ነገር ላይኖር ይችላል እንጂ፣ በጣም ከተቃዋሚዎቹ አንዱ ዋናውም ነበርኩ ልል እችላለሁ። እኛ አንሄድም እነሱ የፈለጉትን ያድርጉ እንጂ እኛ ከወታደራዊ አገዛዝ ጋር አናብርም አልን። በተለይ በቺሊ እንደዚሁ ያለ ነገር አጋጥሟቸው ነበር። ወታደራዊ መንግሥት ነበር። ከላቲን አሜሪካ የሚመጣው ወሬ ሁሉ ጥሩ አልነበረም። እንደዚህ ባለው ችግር ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ሊሳተፍ አይገባውም ብለን ሰው ሳንልክ ቀረን። በኋላ ቤተክህነት፣ እንግዲህ የእስላሞቹም የቤተክህነትም ሰዎች ይልካሉ፣ ከዚያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ (የወቅቱ ፓትርያርክ)፣ “ቤተክህነትን ወክለህ እዚያ ልትገባ ትችላለህ ወይ?” አሉኝ። “አይ እዚያ እሚገባ እዚሁ ውስጥ ያለ፣ ሲሆን ካህን ደግሞም በከፍተኛ ደረጃ መሆን አለበት እንጂ እኔ አልሆንም” አልኳቸው። አቡነ ሳሙኤልን ላኩ። አቡነ ሳሙኤል የሃይቆችና ቡታጅራ ጳጳስ ነበሩ። በፊትም እዚህ አሜሪካን አገር አገልግለዋል። እንግዲህ ፖለቲካውንም ያውቁታል። በኋላ የጠቅላይ ግዛቶች ምርጫ ደግሞ መጣ። ከዚያ ለሸዋ ሊመርጡኝ ያሰቡ ሰዎች፣ እነማን እንደነበሩ አሁን አላስታውሰውም፣ ስልክ ደወሉና እባክህን ፓርላማ ሸንጎ እንድትገባ ተወዳደርልን አሉኝ። እምቢ አልኩ መጀመሪያ። የወታደሮቹ አመጣጥ አላማረኝም። በጣም በጣም ለመኑኝ። እና እስቲ ለውጥ አመጣ እንደሆነ እሽ አልኩና እዚያው ውድድሩ ውስጥ ገባሁ። በኋላ ንግግር እንደዚህ አደረግን። ላክሁት ወደ ሸንጎውም። እዚያ ላይ የነበረው ጭቅጭቅ ግራ አጋባኝ። ሁሉም የልቡን ይናገር አይናገር አይገባኝም። ብቻ ሁሉም ሪቮሉሽን ሪቮሉሽን እያለ ነበር የሚናገረው። የሆነው ይሁን እንጂ መቼስ ምን አረጋለሁ አንዴ ከመጣሁ። ደግነቱ ክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ እዚያ አሉ። የሳቸው እዚያ መኖር ያፅናናናል። እዚያ ላይ እንግዲህ ወታደሮቹ የምናገረውን አልወደዱትም መሰለኝ። ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ደግሞ እንዴትና ለምን እንደሆነ፣ ወይ ምን እንደሰማ አላውቅም ጠራኝና፣ “ቤተክህነትና ቤተመንግሥት አብረው መሥራታቸው ቤተክህነትን የቤተመንግሥት ጥገኛ፣ የዚያ ተጠቂ አድርጓታልና በገንዘብ በኩል ራሷን ችላ እንድትተዳደር አንድ ዘዴ መፈለግ አለብንና እባክህ አንድ ኮሚቴ እናቋቁምና እዚያ ላይ አገልግልልን” አለኝ። ኮሚቴው ተቋቋመ። እዚያ ገባሁ። ንቡረ-ዕድ ዲሚጢሮስ ነበሩበት። ሊቀመንበራችን ዶክተር ክንፈርግብ ዘለቀ ነበረ። እዚያ ደግሞ የሚገርመው ነገር አብዛኞቹ የደርግ ስሜት ያላቸው፣ በዚያ ላይ ደግሞ ቤተክህነትን ለማገልገል ሳይሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ከሥልጣን ለማውረድ የሚፈልጉ ናቸው። በቃ ጨነቀኝ። አለቃ አያሌው ታምሩ አሉ። እሳቸው ይረዳሉ፣ የተሰማቸውን ይናገራሉ። ግን አንዳንዶቹ፣ አንድ ሁለቱ በተለይ፣ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የሚናገሩት ነገር ሌላ ነው። እዚያ ላይ ጭቅጭቅ ተፈጠረ። በኋላም ስልኬ እንደሚጠለፍ ተሰማኝ። አንድ ቀን ወታደሮች ቤቴ መጡና እነማን እንደሆኑ አላወቅሁም። አትገቡም አልኩ። እንገባለን አሉ ግብግብ ገጠምን። እነሱ አሸነፉ። አሸነፉና በጥይት መቱኝ። ከዚያ በኋላ ፕሮፌሰር አሥራት ነበር የሚያክመኝ። እና “እንግሊዝ አገር ሄደህ ብትታከም ይረዳሃል” አለኝ። እንግዲህ አሁን እንደገባኝ እንግሊዝ አገር ምንም አይነት ለውጥ ላገኝ አልችልም ነበር። አንድ ጊዜ አከርካሪ ከተመታ ምንም ማድረግ አይቻልም። ግን አንድ ትልቅ ሴንተር አለ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ብዙ ወታደሮች እንደዚሁ ተመተው ለእነሱ ህክምና የተቋቋመ አንድ ሃኪም ቤት አለ። የዚሁ ብቻ፣ የስፓይናል ኮርድ ሕመምተኞች ብቻ ሃኪም ቤት ነው። እዚያ ላከኝ። መውጪያ አልተፈቀደም ነበረ። ኢሳያስ የሚባል የአየር ሃይል ሰው ነበር። በኋላ ፀረ አብዮት ብለው የገደሉት። በእርሱ እርዳታ፣ በስንት ድካም ተፈቀደልኝ። በቃ ከኢትዮጵያ ወጣሁ። እንግሊዝ አገር ሄድኩና አንድ ሰባት ወራት እንደታከምኩ በዚያው መቅረቱ ላይ ወሰንኩ። ከዚያ ቦታ ስፈልግ ኮሌጅቢል የእኛ መጻሕፍት ያሉበት ቦታ ደረስኩ። ወደዚህ ወደ አሜሪካን አገር መጣሁ። እዚህም ቢሆን መቼም አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች ስለነበሩ በእነሱ ሥራ አፈላላጊነት ነው ይህን ቦታ ያገኘሁት።

እስኪ አሁን ደግሞ ከቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስለተገናኙበት ሁኔታና ስላከናወናችኋቸው ተግባራት ይንገሩን?

አየህ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ብዙ ገዳማት፣ ብዙ ቤተመጻሕፍት በቦንብ ስለተመቱ መጻሕፍቱ አብረው ተቃጥለዋል። በተለይ በእጅ የተጻፉት ናቸው ዋና ዋጋ ያላቸው። የታተሙት ሁለት ሦስት ኮፒ አንዱ ቦታ ቢጠፋ ሌላ ቦታ አይጠፋም። በእጅ የተጻፈው ግን አንድ ብቻ ነው። እነዚያ እንዲጠፉ አይፈልጉም። ግን በጦርነቱ ምክንያት ጠፉ። ስለዚህ የጠፉት ጠፍተዋል ደግሞ ጦርነት ቢነሳ፣ ቃጠሎ ቢነሳ ስለሚጠፉ የተረፉትን ለማዳን ሌላው ቢቀር በማይክሮ ፊልም በፎቶ ግራፍ እያነሳን እናስቀምጣቸው ብለው እየዞሩ መጻሕፍቱን ፎቶግራፍ ያነሳሉ። ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ባህል ያላት ሀገር ስለሆነች እዚያም ሄደን እናንሳ በማለት መጡ። ለዚህም ዋና ምክንያት የሆኑት ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው። ኢትዮጵያ መቼም የጥንት መጻሕፍት አገር በመሆን የታወቀች ስለሆነች አንድ አሜሪካዊ የብሉይ ኪዳን መምህር ስለ ኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት፣ ስለብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ለመመራመር ኢትዮጵያ ድረስ ይመጣል። ከዚያ አባታችንን ሄዶ ሲያነጋግራቸው፣ “ከየት ነው የመጣኸው? ምን ትፈልጋለህ?” ይሉታል። “የብሉይ ኪዳን አስተማሪ ነኝ። ለማስተምረው ትምህርት ምስክር የሚሆኑ የጥንት መጻሕፍት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኙ ይሆናል በማለት ነው የመጣሁት” ይላቸዋል። “አይ ገዳማቱን እየዞርክ ለማየት ያስቸግርሃል። ወጣ ገባ ነው፣ ጊዜህም አጭር ነው። ግን ከዚሁ ጋር አያይዤ አንድ ነገር ልጠይቅህ። እባክህ የእኛ መጻሕፍት እየጠፉ ነው። አይጥ ይበላቸዋል፣ ዝናብ ያበላሻቸዋል፣ እሳት ያቃጥላቸዋል፣ ቱሪስቶች ደግሞ ይወስዷቸዋል። እንደው በየገዳማቱ በየአብያተ ክርስቲያኑ ከፍ ያለ ቤተመጻሕፍት እያቋቋሙ መጻሕፍቱን ለመጠበቅ የሚቻል ነገር አይደለም። ስለዚህ ሌላው ቢቀር መጻሕፍቱን በፎቶግራፍ ብናቆያቸው ፎቶ ግራፍ የሚነሱበትን ነገር ብትፈልግልን?” አሉት። ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ዩኔስኮ አንዳንድ ቦታዎች ሄዶ ፎቶ አንስቶ ነበር። ለምን እንደሆነ አላውቅም ያን ጊዜ ግን ሥራው ቆሞ ነበር። ሰውየው ምን ይላቸዋል፣ “ሚኒሶታ ውስጥ ሴይንት ጆን ዩኒቨርሲቲ በየቦታው እየሄደ ፎቶግራፍ የማንሳት ፕሮጀክት አለው። የእናንተንም እንዲጨምር ገንዘብ እንዳለው፣ እናንተም ትፈቅዱለት እንደሆነ ሄጄ ዩኒቨርሲቲውን ላነጋግርላችሁ?” ሲላቸው፣ “እባክህን እንደው አደራ” አሉት። እንደሄደ የብራና መጻሕፍት የማይክሮፊልም ዳይሬክተሩን ሲጠይቀው ጊዜ፣ “ጥሩ ነው እሽ እንሞክራለን፣ ገንዘብ የለንም ነገር ግን ፕሮግራማችን ውስጥ እናስገባዋለን” አለው፣ ከዚያ አስገቡት። በዚህ ጊዜ ገንዘብ ቸገራቸው። የግብጽ ቤተክርስቲያንን መጻሕፍት ማንሳት ጀምረው ነበር። ነገር ግን ግብጾቹ ስላልተስማሙ አባረሯቸው። ሲያባርሯቸው ለናሽናል ኢንዶውመንት ፈንድ ፎር ሂዩማኒቲስ ደብዳቤ ይጽፋሉ።

አሜሪካ ውስጥ ማለት ነው?

አዎ፣ “ለግብጾቹ የሰጣችሁትን ገንዘብ አልሠራንበትም። ከግብጽ ቤተክርስቲያን ጋር አልተግባባንም። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ዕድል ተገኝቷልና ገንዘቡን እንመልስላችሁ ወይስ ለኢትዮጵያው እናድርገው?” ብለው ይጠይቋቸዋል። አዲስ ፕሮጀክት ካለ እሱን ገቢ ወጪ ከምንል ብለው ነው መሰል ወይንም በፕሮግራሙ ተደስተው እንደሆነ አላውቅም፣ ተጠቀሙበት አሏቸው። ከዚያ ወደኢትዮጵያ መጡና ቢሮ ከፈቱ። ዶክተር ሥርግው ሐብለሥላሴን ዳይሬክተር አደረጉ። ዶክተር ታደሰ ታምራትን አባል አደረጉ። ኮሚቴ ተቋቋመ። ዶክተር ዕጓለ ገብረዮሐንስ፣ አቶ ጌታነህ ቦጋለና በኋላ እኔ ከአሜሪካን ሃገር የሳባቲካል (የጥናትና ምርምር) ቆይታዬ ስመለስ አባታችን አንተም አባል ሆነህ አገልግል አሉኝ። እሽ አልኩ። እዚያው መሥራት ጀመርኩ። መጻሕፍቱ ከየቦታው ወደአዲስ አበባ ይመጣሉ። ዶክተር ሥርግው ቢሮ ከፍቶ መጻሕፍቱን በደንብ እያዘጋጀ፣ ፎቶግራፍ እያነሳ ይመልስላቸዋል። በመጨረሻ የሴይንት ጆን ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር፣ እና ያ ደግሞ መጀመሪያ ምክንያት የሆነን ሰው (ከናሽቪል ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የታወቀ የብሉይ ኪዳን መምህር ነው)፣ ባሉበት አዲስ አበባ ተሰብስበን ስንነጋገር “ጥሩ ነው መጻሕፍቱን ፎቶግራፍ እናነሳለን። አንድ ኮፒ ለእኛ እናስቀራለን፣ አንድ ኮፒ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንሰጣለን፣ አንድ ኮፒ ለቤተ-መጻሕፍት ወመዘክር፣ አንድ ኮፒ ለቤተክህነትና አንድ ኮፒ ለዩኒቨርሲቲው እዚህ ላለው“ አሁን አለጥርጥር መጻሕፍቱ ወደአዲስ አበባ እየመጡ ማይክሮፊልሙ ተከመረ። ዓለም ግን ምን እንዳለን አያውቅም። “ካታሎግ እናድርገው። ማለቴ ካታሎግ አድርገን እየደረደርን፣ እያጠናን፣ ይሄ አለን ይሄ የለንም ለማለት ነው” ሲል፣ ዶክተር ሥርግው፣ “ግድ የለም እኛ እናደርገዋለን። እናንተ ዘንድ አይሆንም” አለ። በኋላ ስንነጋገር ትንሽ ቸገረኝ። “ማነው ካታሎግ የሚያደርገው? ወይ ዶክተር ሥርግው፣ ወይ ዶክተር ታደሰ ታምራት፣ ወይ ዶክተር አምሳሉ ወይ እኔ ነኝ። ካታሎግ ማድረግ ደግሞ ከጠዋት ጀምሮ እስከማታ ድረስ ቁጭ ብሎ ሲሠሩ መዋል ነው። ከኛ ውስጥ ማነው እዚህ ቁጭ ብሎ ይህንን ሲሠራ ለመዋል የሚፈልግ? ሁሉም በየበኩሉ ሥራ አለበት። ይህን ያህል ዘመን በትምህርት አሳልፌ እኔ ጊዜዬን ካታሎግ ሳደርግ አልኖርም። ታዲያ ማን ሊያደርገው ነው? ደግሞም እኔን ቅጠሩኝ ብላችሁ ምን ያህል ነው የምትከፍሉኝ? እነሱ ያድርጉልን ግድየለም እባካችሁ?” ብዬ ተከራከርኩ። በኋላ እውነትም ኮሚቴው በዚያ ተስማማ። ሥርግው ይህን የተናገረው ያው ለሃገሩ ለባህሉ ተቆርቁሮ ነው። ሌላ ሰው አይነካብንም፣ የኛን እራሳችን መሥራት አለብን ነው። ግን ካታሎግ የሚያደርገው ማንም የለም። ሌላም ሰው ቢሆን ያድርገው እንጂ እዚያ ተቀምጦ እስከመቼ ድረስ? ምን እንዳለንስ እንዴት ይታወቃል? መቼም ማይክሮፊልም መደረጉ እኮ መጠበቁ ብቻ ሳይሆን ሰውም እንዲማር ነው። በዚህ ተወሰነ። በኋላ እነኛ ቦታ እሚፈልጉልኝ ያልኩህ ሰዎች “እዚህ ቦታ ካታሎግ የሚያደርግ ሰው ይፈለጋል። ለምን አትመጣም?” አሉኝና ነው ወደእዚህ የመጣሁ። አዲስ አበባም ሆኜ ግዕዝ፣ አማርኛና የግዕዝ ሥነጽሑፍ አስተምር ነበር። ነገርግን መጻሕፍቱን ዋና ዋናዎቹን አውቃቸዋለሁ እንጂ ሁሉንም አልነበረም። አሁን ካታሎግ ሳደርግ መጽሐፉን ከዳር እስከዳር አንብቤ ነው። አገላብጬ፣ በውስጡ ምን እንዳለ በደንብ አጥንቼ ነው ‹ይሄ መጽሐፍ እንዲህ ነው› ብዬ የምናገረው። ያ ለእኔ ኢትዮጵያ የነበረኝን የግዕዝ ሥነጽሑፍ ዕውቀት ምናልባት በእጥፍ አሳድጎታል። ስለዚህ የኢትዮጵያን መጻሕፍት አብዛኞቹን አንብቤያቸዋለሁ ልልህ እችላለሁ። ከየገዳማቱ የመጡት፣ እነዚህ የተሰባሰቡት መጻሕፍት ብዛት ወደ ስምንት ሺህ ደርሷል።

በጣም ብዙ ነው ማለት ነው።

በጣም ብዙ ነው። ነገር ግን ብዙዎቹ እንደ ዳዊት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ፣ ግንዘት፣ ግብረ ሕማማት፣ እንደዚህ ያሉ ናቸው። ግን ከዚያ ውጪ የነገሥታቱ ታሪክ፣ የጻድቃኑ ገድላት፣ የሃይማኖት ውይይት እነዚህ ሁሉ አሉ። እና እነዚህን እያጠናሁ ካታሎግ አደርጋለሁ። የኔ ካታሎግ በመጽሐፍ ሲታተም እያነበቡ ሊቃውንቱ ይሄን ላኩልን፣ ይሄን እናጥናው ሲሉ እኔም ማሰብ ጀመርኩ። ለነሱ መንገር ብቻ ሳይሆን እኔም እኮ መጽሐፉን ባሳትመው ምን አለ? ደግሞም ይሄ የኢትዮጵያ ሃብት ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ቢያሳትመው እኮ የበለጠ ነገር ነው የሚል ሃሳብ መጣልኝ። ሁለተኛም አንዳንዶቹን እንዲህ ያለ መጽሐፍ አለን ብዬ በምገልጽበት ጊዜ የሚያሳትማቸው የለም። ታዲያ እነዚህን ማን ነው የሚሠራቸው እያልኩ ቀን ያን ካታሎግ ሳደርግ እውልና ማታ እቤቴ ቸኩዬ መጥቼ እሱን አጠናለሁ። ደግሞ ያን ጊዜ በእጄ ነው የምጽፈው። ኮምፒውተር አልገባም። ከቅዱስ ዮሐንስ ጋራ ያለኝ ግንኙነት ይህን ይመስላል። እዚያ በምሠራበት ጊዜ ኢትዮጵያውያንም እኮ በአማርኛ ቢጻፍላቸው ይፈልጉ ይሆናል በሚል ተነስቼ ያንን ለማስተዋወቅ ያህል የጻፍኳቸው አሉ።

በጣም አመሰግናለሁ። እኔም እጄ ላይ የገቡትንና በመጽሐፍ መልክ የወጡ ሥራዎችዎን ባሕረ ሐሳብ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፣ እና ዲሞክራሲና አንድነት የተሰኙትን ተመልክቼያለሁ። በየጆርናሉ የታተሙት ሥራዎችዎም እጅግ በርካታ መሆናቸውን ከዝርዝሩም ተረድቻለሁ። የተወሰኑትንም አንብቤያቸዋለሁ። “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች…” አዲስ አበባ ውስጥ እንደገና መታተሙን ነግረውኛል። ሌሎች የታተሙ ሥራዎች አሉዎት? በውጥን ያሉና ገና ወደ ህትመት ያልተላኩስ?

አዎ በተለይ አንዱ ቫቲካን ውስጥ የታተመ አለ – ስለቅድስት ማርያም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ስለቅድስት ማርያም ይጻፉ የነበሩትን ተአምራት፣ ታሪኮች፣ እነዚህን ከዚሁ ከምሠራበት ቦታ አፈላልጌ ሰብስቤ፣ አንድነት ጽፌ ይህኛውን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሜዋለሁ። ግዕዙ ባንድ በኩል፣ እንግሊዝኛው ባንድ በኩል ሆኖ The Mariology of Emperor Zar‘a Ya‘aqob of Ethiopia (ኢትዮጵያዊው ዘርአ ያዕቆብ ስለማርያም ያለው ትምህርት) የሚል መጽሐፍ በ1992 ነው እንደዚህ መሰለኝ በባቲካን ታትሟል። ሌላው ደግሞ ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ መጻሕፍት ውስጥ ብዙዎቹ ታትመው አንዱ ጠፍቶ ነበር። እሱንም እዚያው ስሠራ አግኝቼው ግዕዙን ባንድ በኩል፣ እንግሊዝኛውን ባንድ በኩል አርጌ ሉንድ፣ ቤልጂየም ታትሟል። ሌላው የአባ እስጢፋኖስ ገድል፣ ከአሁን በፊት ከእስጢፋኖሳውያን አባቶች የአቡነ አበክረዙንና የአቡነ እዝራ ታትመዋል። ሁለት ያልታተሙ ነበሩ። “ገድለ አበው” የሚባል የራሳቸው የብዙዎቹ እንደ ስንክሳር አይነት እንደንባብ ሆኖ የተዘጋጀ አንድ አለ። ሁለተኛው ራሱ የአቡነ እስጢፋኖስ ገድል፣ ወደ አማርኛ ተርጉሜ ያሳተምኩት አለ። እሱ በምዕራባውያኑ በኩል አልታተመም ነበር። ግዕዙንና እንግሊዝኛውን አድርጌ ነው ያወጣሁት። ከዚያ ውጪ እንግዲህ ያሉት በተለየ በተናጠል የታተሙ ልዩ ልዩ ይኖራሉ። አንድ አዲስ ነገር ባሳተምኩ ቁጥር አዲስ አበባ እልካለሁ። ይህንን በማደርግበት ጊዜ ራሴን የማስተያዬው የኢትዮጵያን ጥናትና ምርምር ከሚከታተሉ መምህራን ጋር ነው። ከኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከምዕራባውያንም ጋር ማለቴ ነው። ከምዕራባውያን ጋር ስወዳደር እኔ አንድ ተራ ሰው ነኝ፤ ግን ከኢትዮጵያውያን መሃል እነሱ ውስጥ ገብቶ ከእነሱ ጋራ በመታገሌና እዚያም ጽሑፎቼን በማድረሴ ደስ ይለኛል። ከኢትዮጵያውያን በኩል እንግዲህ ካሁን በፊት ዶክተር ባይሩ ተፍላ የሚባል አለ። እሱና ደግሞ አንድ አቶ ያዕቆብ በየነ የሚባል ጣሊያን አገር የሚኖር አለ። እነሱ እንግዲህ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያውያን ስለነበሩ አብረን ነን እንላለን። አሁን ደግሞ አቶ ቴዎድሮስ የሚባሉ አሥመራ የሚኖሩ ደግሞ አሉ፣ በጣም ጥሩ ይጽፋሉ። ከኢትዮጵያውያኑ መሐል ማለቴ ነው። በተለየ ግን ብዙውን ምዕራባውያን ናቸው የሠሩት። ምናልባት ቢብሊዮግራፊውን አይተኸው እንደሆነ። ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት አበክረዙንን ያሳተመው አንድ ጣሊያናዊ ነው። የአቡነ እዝራን ያሳተመው ደግሞ አንድ ፈረንሳዊ ነው። የአፄ ዘርአ ያዕቆብን ጽሑፎች ከአሁን በፊት የነበሩትን ያሳተመው አንድ ጣሊያናዊ ነው። አሁን በቅርብ ጊዜ ደግሞ ሲኖዶሱን አንድ ጣሊያናዊ ወጣት ልጅ አሳትሟል። ከእነርሱ ጋራ ሳስተያየው የእኔ ተራ ሥራ ነው። በተለየ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያወቁኝ እነዚህን ሶሥት መጻሕፍት ስላሳተምኩ ነው።

በአካዳሚው አካባቢ ያለው ወገን እንኳ ሌሎች ሥራዎችዎንም ከሞላ ጎደል ያውቃል ብዬ እገምታለሁ። ሌላው ግን እንዳሉት በእነዚህ በአማርኛ ቋንቋ ባሳተሟቸው መጻሕፍትና በመጣጥፎችዎ ይመስለኛል በይበልጥ የሚያውቅዎት።

መቼም በአማርኛ እንድጽፍ ከፍ ያለ ድጋፍ የሰጠኝ አቶ አምሃ አስፋው ነው። እዚያ መጽሐፉ መቅድም ውስጥ ጽፌዋለሁ። በአማርኛ እንዲጻፍ ይፈልጋል። ይሄን ሁሉ ፎርማት ውስጥ ያስገባው እሱ ነው። ጽሑፉን በኮምፒውተር የጻፈችልኝ ባለቤቴ ወይዘሮ ምሥራቅ ነች። ሌላውን የሠራው አምሃ ነው። ፎርማቱን ለውጥ ስለው ይለውጣል። እንደገና ደግሞ ሃሳቤን ቀይሬአለሁና እንደዚህ አድርግልኝ ስለው፣ “በፍፁም እንደው ሳትቸገር የምትፈልገውን እያፈረስክ ገንባ በለኝ እሠራልሃለሁ” እያለ ነው የሚያበረታታኝ። እነዚህ ሁሉ የእሱም ውጤቶች ናቸው እንጂ የእኔ ሥራ ብቻ አይደሉም። እውነት ነው አቶ አምሃ በጣም ደግ ሰው ነው። ሥነጽሑፋዊ ሥራዎቹን፣ የተረጎማቸውን ጨምሮ ድረ ገጽ ላይ አስቀምጧቸዋል። በነፃ መስጠት ማለት ነው። ይሄ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሰዎችን ሥራዎችም እንዲሁ ሕዝብ ዘንድ እንዲደርሱ አድርጎላቸዋል። ብዙዎችንም በሙያው ሲረዳ አያለሁ። እና ደግሞ የሚገርመው እሱ ራሱን እሚያነሳሳ ሳይሆን ሌሎችን እሚያነሳሳ ነው። ግጥሞቹ እኮ ደግሞ አምሳያ የላቸውም። በጣም ከፍ ያሉ ናቸው፣ ከስሜት ጋራ የሚሄዱ ናቸው። እኔ መቼም በጣም ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ ነው። አሁን ደግሞ አንድ አሳሳቢ የሚመስለኝን ጉዳይ ላንሳ። በተለያዩ ቦታዎች በሥራ ምክንያት ስዘዋወር የተመለከትኩት ነገር ነው። አሁን ለምሳሌ እንደ ክብራን ገብርኤል ባሉ ገዳማት በግዕዝ የተጻፉ በርካታ መጻሕፍት አሉ። ይህን ሁሉ የዕውቀት ሃብት ማን ነው የሚያካፍለን? ማንስ ነው ወደ ህዝብ የሚያደርሰው? በዚያ ላይ እርስዎም እንደጠቀሱት በየአብያተ-ክርስቲያኑና በየገዳማቱ ካሉን መጻሕፍት መካከል በእሳት፣ በፍሳሽና በአይጥ እየተበላ የሚጠፋው ቀላል አይደለም። ቀደም ሲል በባህል ሚኒስቴር ስር ተቋቁሞ የነበረው የብራና ጽሑፎችና ማይክሮፊልም ድርጅት ያከናውነው የነበረውን ተግባር በዚያው መልክ የተረከበ ድርጅት ያለም አይመስለኝም። አዎ ባህል ሚኒስቴር በጣም ብዙ መሥራት የሚችል ነበረ። እነዚህ መጻሕፍት፣ አሁን ሄጄ አየኋቸው ያልካቸው፣ በፊልም መነሳት ነበረባቸው። በምንም አይነት መንገድ እነሱን ለማዳን ሌላ ዘዴ ለጊዜው አይታይም። ሌላው ቢቀር ይዞታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ እንፈልጋለን። እነዚህ የሚፈለጉበት ምክንያት ሁለት ነው። አንደኛው ከሃገራችን ታሪክ ምን ትምህርት ተምረናል? ምን ትምህርት አለው? እኛም የጻፍነው ከውጪም የተረጎምነው። ሁለተኛው ደግሞ ራሳቸው ምዕራባውያን የክርስትና ታሪክ አንዳንድ ቦታ ላይ ጠፍቶባቸዋል። መጻሕፍቱን ያን ጊዜ በሃይማኖት ክርክሩ ጊዜ ይሄ ለቤተክርስቲያን ይጠቅማል እናቆየው፣ ይሄ ለቤተክርስቲያን አይጠቅምም እናጥፋው እያሉ ብዙ መጻሕፍት አጥፍተዋል። እነዚያ መጻሕፍት ከመጥፋታቸው በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይሆናል የሚል አስተሳሰብ አለ። ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደሆነ ከመጥፋታቸው በፊት እንያቸው ነው። ከሌላ አገር መጥተው፣ እዚያው ከተፈጠሩበት ከተጻፉበት አገር ጠፍተው እኛ አገር የተገኙ አሉ። እነዚህ ከመጥፋታቸው በፊት ብንደርስባቸውና ብናቆያቸው የሚገባ ነው። ደግሞ የሚገርመው ከምዕራቡ ዓለም ወደእኛ አገር ከመጡ በኋላ የጠፉ መጻሕፍት አሉ። መተርጎማቸውን እናውቃለን። ምክንያቱም አንዳንድ ቦታ ተጠቅሰዋል። በየገዳሙ ሄደን እስካሁን በተደረገው ፍለጋ ግን አልተገኙም። እነዚህን ሁሉ ማግኘት አለብን። ምዕራባውያንም ዘንድ ጠፍተዋል፣ እኛም ዘንድ የጠፉ እንደሆነ ምንም ሳናውቅ ልንቀር ነው። ስለዚህ ነው የኢትዮጵያን መጻሕፍት ለማወቅ የምንፈልገው። አንደኛ አባቶቻችን ምን ጽፈውልናል? ምን ተርጉመውልናል? ሁለተኛው ደግሞ ከውጪ የጠፉት እኛ ዘንድ የት አሉ? እንግዲህ በቤተክርስቲያን ታሪክ ያጨቃጭቁ የነበሩት ዋናዎቹ ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ላይ የነበሩ መጻሕፍት ናቸው። እነሱን ነው ለማወቅ የምንፈልገው። እነሱ ደግሞ ሽግግሩ እንዴት እንደነበረ፣ ጭቅጭቁ ምን እንደነበረ ይነግሩናል። ለዚህ ነው የሚፈለጉት። እግዜር ይስጥልኝ። በአጼ ዘርአ ያዕቆብ ላይ አፅንኦት ይሰጣሉ። ብዙ ሥራዎችዎ ላይ ይህንን አስተውያለሁ። አጼ ዘርአ ያዕቆብ ምን አይነት ሰብዕና ነበረው ብለው ያስባሉ? በአንድ በኩል ክርስቲያን ነው፣ በሌላ በኩል ክርስቲያን ሊፈጽመው የማይገባውን ሥራ ይፈጽማል። ጭካኔውን ማለቴ ነው። በጥናቶችዎ ውስጥ፣ ለምሳሌ ስለቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ባዘጋጁት ጥናት ላይ “ይሄን ያደረገ፣ ይሄን የለወጠ ዘርአ ያዕቆብ መሆን አለበት” ሲሉ ምክንያትዎንም አቅርበው ነበር። እና እንደ ቅርብ ዘመድ ወይም እንደ ወዳጅ በደንብ የሚያውቁት ስለመሰለኝ ነው ይህንን ጥያቄ ያቀረብኩት። መቼም ታላላቅ ጸሐፊዎች የምንላቸው አፄ ዘርአ ያዕቆብ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ ደግሞ ርቱዕ ሃይማኖት የሚባል ስሙን ሊነግረን ያልፈለገ አንድ ሰው አለ። እሱና ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ናቸው ዋናዎቹ። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መልክ የለወጠ፣ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ጽሑፍ ያዳበረ አፄ ዘርአ ያዕቆብ ነው። ይህንን ለማለት የቻልኩት እኔ ስለ አፄ ዘርአ ያዕቆብ ያው ከተዓምረ ማርያሙ ላይ ነበረ ብዙ ጊዜ የማውቀው። ግን መጻሕፍቱን፣ አንዱን አንድ ጣሊያናዊ አሳትሞታል፣ አንደኛውን አንድ ጀርመን አሳትሞታል። እነዚያን መጻሕፍት በማነብበት ጊዜ ሃሳቡን፣ እሱ ጭንቅላት ውስጥ የመግባት ያህል ነው የማውቀው። ታዲያ አንዳንድ ጽሑፎቹን በማይበት ጊዜ ከዚያ ውጪ ይሄ የእሱ ነው የምለው ለዚህ ነው። አሁን ያን ገድሉን የያሬድን በፊት አነበው ነበረ። ያን ለታ የያሬድን በዓል እንድናከብር አንተ ንግግር አድርግልን ሲሉኝ ጊዜ ነው አጥብቄ ማጥናት የጀመርኩት የያሬድን ገድል። እንደዚህ ሳየው የአፄ ዘርአ ያዕቆብን እዚያ ላይ የእሱ መሆን አለበት እላለሁ። አጥንቼዋለሁ እውነት እንዳልከው። ቀናተኛ ነው። ለቤተክርስቲያኑ ቀናተኛ ነው፣ ለሃገሩ ቀናተኛ ነው። ከአዳል ጋርምኮ ከፍ ያለ ጦርነት አካሄዷል። መጥተው ነበር አዳሎች፤ የክርስቲያኖችን ሃገር ለመዝረፍ መጥተው ነበር። ተዋግቶ ወታደሮቹን አቅርቦ ራሱ ጦሩ መሃል ገብቶ ነው የተዋጋው። የቤተክርስቲያንንም ሥርዓት ቢሆን ያስተካከለው እሱ ነው። ሲኖዶሱ ያኔም አለ። ቤተክርስትያኗ ግን በሲኖዶሱ ሥርዓት አትሄድም ነበር። እሱ ነው በሲኖዶሱ ሥርዓት ያስኬደው። እሑድና ቅዳሜም እንደዛሬው Sunday School (የሰንበት ትምህርት) እንደሚባለው ክርስቲያኖቹ እየመጡ መማር አለባቸው ይል ነበር። ግን እንግዲህ ምንድነው ክርስቲያን ከሆንክ የክርስትና እሥረኛ ነህ፣ ያን ግዴታህን መፈጸም አለብህ ነው። ቤተክርስቲያን አልሄድም ያለ ይቀጣ ነበር። እስላሞቹ ቤተክርስቲያን አይሄዱም፣ ግን አይቀጡም። እስላሞች ስለሆኑ። በቤተክርስቲያን ስሙ ሚካኤል ነው። ግን ራሱን ቆስጠንጢኖስ ነበር የሚለው። የመስቀል ጉዳይ ነው፣ በማረሻው ላይ በግንባራቸው ሁሉ እኮ ጽሑፍ እንዲያደርጉ ይጠይቅ ነበር። “አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ይላል። የክርስትናን ሃይማኖት አንድ ለማድረግ በጣም በጣም ነበር ይጥር የነበረው። ደግሞ በውስጥ የውይይት፣ የንግግርና የሃሳብ ልዩነት አይፈቅድም ነበር። ያለው ይሄ ነው፣ በዚህ ቀጥሉ ነው። ሌሎቹ ‘የቤተክርስቲያን ሃይማኖት ትምህርት፣ የክርስትና ትምህርት ይሄ አይደለም። በዚህ ነው መሄድ ያለብህ’ በሚሉት ጊዜ እሽ አይልም ነበር። በዚያ ዘመን የነበሩ ዘሚካኤል የሚባሉ ነበሩ። ፈረንጆቹ ዘሚካኤላይትስ ይሏቸዋል። እኔን የበለጠ የሚማርከኝ ከእርሱ ጋር የሚጋጩት ሰዎች አስተሳሰብ ነው – ከእሱ ይልቅ። በሃይማኖት በኩል፣ በቲዎሎጂ በኩል የማደላው ለእነሱ ነው እንጂ ለዘርአያዕቆብ አይደለም። ግን አደንቀዋለሁ፣ የጻፋቸውን ሁሉ አንብቤያለሁ፣ ከጻፋቸው ውስጥ ቅድም እንደተናገርኩት ብዙ ድርሰቶቹን አሳትሜለታለሁ። ስለዚህ ነው የማውቃቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top