ጥበብ በታሪክ ገፅ

የጥንቱ መድረክ መሪዎችና አዲስ ዓመት

ከሶስት ዓመት በፊት በዚሁ የታዛ መጽሔት እትም ላይ ስለ ድሮው የአዲስ ዓመት የሙዚቃ ዝግጅት፣ ፉክክርና ተመልካች ሁኔታ የሚያስታውስ አንድ ጽሑፍ ተመልክቼ ነበር። ጽሑፉ ስለ ድምጻውያን፣ ስለ ተመልካቾችና የጋዜጠኞች አስተያየት ጭምር ድንቅ መረጃ የሚሰጥ ነበር። ጸሐፊው (ተስፋዬ ገ/ማርያም) የጥንቱ ዘመን ተጋሪ እንደመሆናቸው፤ ትውስታቸውንና ከዘመን ተጋሪዎቻቸው የሰበሰቡትን ታሪክ ማካፈላቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ሳልጠቅስ አላልፍም። ይሁንና በዘመኑ ብዙ ስለሚነገርላቸው የመድረክ መሪዎች(Announcers) ምንም አለመጠቀሱ የማይታለፍ ክፍተት መስሎ ተሰምቶኝ ነበር። እንሆ ዛሬ ቀኑ ደርሶ፤ ከልዩ ልዩ ምንጮች ያገኘኋቸውን መረጃዎች በመገጣጠም፤ የጎደለውን እንኳ ባልሞላ፤ የጎደለውን ላስታውስ ተመለስኩ።

የትናንቱ ዘመን የአዲስ ዓመት ዝግጅት ኪነ-ጥበቡን (በተለይ ሙዚቃ) በእጅጉ ያነቃቃ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ላይ አይተኬ ሚና የተጫወተ ጭምርም ነበር። ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ 70ዎቹ መጀመርያ ያሉት ተከታታይ ዓመታት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግና በፉክክር ስሜት በርካታ ዘፈኖች እንደ መስከረም አደይ በየመድረኩ የፈነዱበት ዘመን ነው። በወቅቱ የነበሩ የወታደርና የሲቪል የሙዚቃ ጓዶች የሚያደርጉት የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅ አዲስ ዓመትን በእጅጉ ያስናፍቀው ነበር። በተለይ የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦር፣ የፖሊስና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤት (የአሁኑ ብሔራዊ ትያትር) ለዚህ ፉክክር ዋንኛ ተሰላፊ ናቸው።

ለዚህ ታላቅ ፉክክር ሲባል ሙዚቀኞች፣ ድምጻውያን፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች እና ተወዛዋዦች የአዲስ ዓመት ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት ገና በግንቦት ወር ነበር። ሩቅ ይመስላል። ወራቱን በትጋት ለሚታትሩባቸው ከያኒያን ግን እንደነገ ቅርብ ነው። አንዱ ዜማ ሲያወጣ፣ ሌላው ግጥም ሲጽፍ፣ አንዱ ሲያቀናብር፣ ሌላው ሲለማመድ፤ እንደዋዛ መስከረም ይደርሳል። የአንዱ ክፍል የአንዱን ፈጠራ እንዳይቀማም ነቅቶ መጠበቅ ግድ ይላል። ከመስከረም ዋዜማ ጀምሮ በየተራ በሚቀርበው ዝግጅት አሸናፊ ሆኖ፤ የንጉሱን ሽልማት፣ የታዳሚውን የሞቀ አቀባበልና የጋዜጦቹን ሙገሳ ለማግኘት በር ዘግቶ መትጋት የየክፍሉ ሙዚቀኛ ግዴታ ነው። በዚህ መንገድ ሙዚቃም ዛሬ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንደሚባለው ሳይሆን በጥሩ ቅመምና ለዛ ተሞሽራ አድማጭ ጆሮ ትደርሳለች። ዘመኗም በጊዜ የማይሟሽሽ፣ በቦታ የማይጠለሽ ሆኖ፤ ይኸው ዛሬም ሳንታክት የትናንቶቹ ሙሽሮች አላረጁብንም። ላይናችን አልደበዘዙም፤ ለጆሯችንም አልጎረበጡም።

ፉክክሩ በትልቁ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትያትር ቤት ነው። ንጉሱና የልዑላን ቤተሰቦች፣ ባለስልጣናት፣ ታላላቅ መኮንኖች፣ ጋዜጠኞችና አዳራሹን እንደ ንብ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞሉት ታዳሚያን ጆሯቸውን አንቅተው የሚሆነውን ለማየትና ለመስማት በደስታ ነበር የሚጠብቁት። የየክፍሉ ሙዚቀኞች፣ ተወዛዋዦችና ድምጻውያን በበኩላቸው በተጠንቀቅ ቆመው ተራቸውን በታላቅ ጉጉትና መረበሽ የሚያዳምጡት። እንግዲህ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ነው፤ መድረክ መሪዎች ብቅ የሚሉት። ለወራት የተደከመበት ማዕድ ውጥንቅጡ እንዳይወጣ፤ እየበለቱና እያዋዙ አይተኬ ሚናቸውን የሚወጡት። “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንደሚባለው መድረክ መሪዎች የዝግጅቱ ፊታውራሪ ናቸው። ደምቀው ማድመቅ፣ ስቀው ማሳቅ የተፈቀደላቸው። ታዳሚ ዝግጅቱን በታላቅ ጉጉትና ደስታ ይጠብቅ ዘንድ ቁም ነገሩን እያዋዙ፣ የደረቀውን እያለዘቡ ንቁ ታዳሚን ከከያኒው የሚያገናኙ ሀዲዶች። ቅንጣት ክፍተትን በፈጣን ክህሎታቸው እያሻገሩ ከትልቅ ማዕድ የሚያደርሱ ድልድዮች።

የጥንቱ የአዲስ ዓመት የወታደር ኦርኬስትራዎችና የሲቪል ሙዚቀኞች ፉክክር፣ ከሚሰሙት አዳዲስ ዘፈኖች ባሻገር የየክፍሎቹ መድረክ መሪዎች ዝግጅትም በጉጉት የሚጠበቅ ነው። መድረክ መሪዎች አንዱን ክፍል ከሌላው ለማስበለጥና ውድድሩን ለመጋጋል በእጅጉ ይተጋሉ። በዚህ ምክንያት ፉክክሩ በድምጻውያኑ መካከል ብቻ ሳይሆን በመድረክ አስተዋዋቂዎችም ጭምር ይሆናል። “ማን ምን አለ?” የሚለውን ለመስማት ታዳሚውም በላቀ መቁነጥነጥ ጆሮውን እንደ አንቴና ይቀስራል።

በድንቅ የመድረክ መሪነታቸው ታውቀው ለብዙዎች አርአያ እስከመሆን የደረሱ ብዙ አሉ። የክብር ዘበኞቹ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ገዛኸኝ ደስታ፣ ስዩም ባሩዳ፣ የምድር ጦሩ አምሃ ተወዳጅ፣ የፖሊሶቹ ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ፣ ከሳሁን ገርማሞ እና የብሔራዊ ትያትሮቹ ተስፋዬ ሳህሉ፣ ታማኝ በየነ እና ሌሎችም ከዋነኞቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ጥቂቶቹን እስኪ እንተዋወቅ።

ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ

“የምስራች – ምስር ብላ – የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ የምስራች – ምስር ብላ”

ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ

በ1953 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትያትር ቤትና ዝግጅቱን በቀጥታ በሬዲዮ የሚከታተል ህዝብ በድንገት ነበር እነዚህን ቃላት ከመድረክ መሪው ጋር የተለዋወጠው። “ምን ይሆን? ምን ልንሰማ ይሆን?” ያላለ አልነበረም። ወዲያው ግን ታላቁ ዜና ታወቀ። “የክብር ዘበኛ ባልደረባው ወታደር አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ በጣሊያን ሮም አሸነፈ” ተባለ። አስተዋዋቂው ደግሞ የክብር ዘበኛው መድረክ መሪ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ነበር። ይህ ሙዚቃን ከታላቅ ዜና ጋር ያዋሀደው ድንቅ አጋጣሚ ከሻምበሉ የማይረሱ የአዲስ ዓመት የመድረክ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ነው።

ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ የክብር ዘበኛ ሁለተኛ ኦርኬስትራን ከመሰረቱት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው። የክፍሉ የመጀመርያው መድረክ አስተዋዋቂ ከመሆኑም በላይ የዳንስና ኪሮግራፊ መምህር ሆኖም ሰርቷል። ድንቅ የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ያለው ሰውም ነው። በርካታ የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል። የህይወቴ ህይወት፣ አምሳሉ፣ ኡኡታ አያስከፋም፣ ውበትሽ ይደነቃልና… ሌሎችን ለጥላሁን ገሰሰ፣ እንደ አቤት አቤት ፍቅርዬ ተረዳ፣ ደህና ሁንና… ሌሎችን ደግሞ ለአስናቀች ወርቁ፤ ለብዙነሽ በቀለ ደግሞ የፍቅር መጠኑ፣ ወጣት ሳለሁና… ሌሎች አያሌ የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል። የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ የሙዚቃና ትያትር ክፍልን በኃላፊነት በመምራትም ለዓመታት አገልግሏል።

ሃምሳ አለቃ ገዛኸኝ ደስታ

“ሰላም ለእናንተ ለእኛ፤ በጠቅላላው ለሰው ልጅ ዘር። ማዕረጌ ምክትል አስር አለቃ(በኋላ 50 አለቃ ሆኗል) ስሜ ገዛኸኝ የአባቴ ስም ደስታ! ስራዬ የደስታ መትረየስ መተኮስ! በኢትዮጵያ ውስጥ የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ሙዚቃን በተገቢው መንገድ እንዲሄድ ያደረገ የመጀመርያው መስራች ክፍል ነው”

የሃምሳ አለቃ ገዛኸኝ ደስታ በአዲስ ዓመት ዝግጅት ላይ ካደረጋቸው በስሜት የተሞሉ የመድረክ ንግግሮች መካከል የተቀነጨበ ነው። ተናግሮ መደመጥ፣ ቀልዶ ማሳቅ የሚሆንለት ሰው ነበር። መድረክ ላይ ፈጣን ግጥሞችን በማፍለቅም የተመሰከረለት ነው። እንግዲህ ጹሁፍ እንደ አንደበት አይሆንምና የአንደበቱን ግለትና ለዛ፣ የታዳሚውን ፌሽታና ጭብጨባ እዚህ መግለጥ አልተቻለም። ከፈጣን የመድረክ ግጥሞቹ መካከል ከዘካሪያ መሀመድ “ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክና ምስጢር” ከተሰኘ ማለፊያ መጽሀፍ ላይ እንሆ ለቅምሻ።

እንኳንስ ድምጹና ያስደስታል መልኩ፣
ጥላሁን ገሠሠ አይገኝም ልኩ።
በሰዎች ልብ ውስጥ ሙዚቃ እየዘራ፣
የዘፈኖች ቅመም ተባለ ተዘራ።

ገዛኸኝ መድረክ መሪነትን ከሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ነበር የተረከበው። ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በ53ቱ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳትፈዋል በሚል ሰበብ ታስረው ስለነበር፤ ገዛኸኝ አጋጣሚውን በመጠቀም ወደ መድረኩ ወጣ። እሱም እንደቀደመው ታዲያ መድረክ መሪ ብቻ አልነበረም። የተዋጣለት የግጥምና ዜማ ደራሲም ጭምር እንጂ። በወታደራዊ አገልግሎቱ ደግሞ ከኮሪያ ዘማቾች ጋር ዘምቶ በኮርያ ልሳነ- ምድር ነፍጥ ይዞ ተሰልፏል።

ጥላሁን ገሰሰ የተጫወታት “ጃፓኗን ወድጄ” የተሰኘችዋ ዝነኛ ዘፈን የግጥም ደራሲም ነው። ሌሎች በርከት ያሉ ዘፈኖችንም ደርሷል። ከአያሌ የጥላሁን ገሰሰ ድርሰቶቹ መካከል አመልካች ጣት፣ ባለ ጠላ፣ ይቅርታ እለምናለሁ፣ ተማሪ ነኝ፣ ስትሄድ ስከተላት፣ እወድሽ ነበረ፣ ትዝ አለኝ የጥንቱ እና ዓይኔ ይሳሳልሻል… የሚሉትን መጥቀስ ይበቃል።

አምሃ ተወዳጅ

አምሃ ተወዳጅ

ከክብር ዘበኛ እንውጣና ወደ ምድር ጦር ደግሞ እንግባ። በዚህ ክፍል አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በመድረክ ድምቀታቸው ከሚናፈቁ አስተዋዋቂዎች መካከል ዋንኛው ነው-አምሃ ተወዳጅ። አምሃም እንደ ክብር ዘበኛ መድረክ መሪዎች ሁሉ ታዲያ መድረክ መሪ ብቻ አይደለም። የተዋጣለት የግጥምና ዜማ ደራሲም ጭምር እንጂ። ታምራት ሞላ፣ ሐብታሙ ሽፈራው፣ አባይ በለጠ፣ ፀዳለ ገብረ ማርያምና ሌሎችም፤ ግጥምና ዜማ ድርሰቱን ተቋድሰዋል።

አምሃና መድረክ የተዋወቁት እንዲህ ነበር። በ1950ዎቹ መጀመርያ የምድር ጦር ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ኮንጎ ሲዘምት አምሃም አብሮ ተጉዞ ነበር። በኮንጎ ካታንጋ አንድ መድረክ ይዘጋጅና መድረኩን የሚያጋፍር ሰው ይጠፋል። በወቅቱ በኮንጎ የመንግስታቱ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት ታዋቂው የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ መድረክ የሚመራላቸው ሰው ሲፈልጉ ድንገት ወጣቱ አምሃ ዐይናቸው ይገባል። ፈቃዱን ሳይጠይቁ ጎትተው መድረክ ላይ ለቀቁት። ሲፈራ ሲቸር ጀመረው። አልለቀቀውም፤ እንደተወደደ የእድሜ ልክ ደም ስሩ ሆኖ ቀረ።

ካሳሁን ገርማሞ

ካሳሁን ገርማሞ

ሰላም ለኩልክሙ በስመ ዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣
ንኢ እንቁጣጣሽ ዘእንበለ ዳንኪራ ዳንሳዊ፣
ዘይሳኖ ፖሊስ ኦርኬስትራ ዝነኛዊ፣
አቡነ ዘበሳቅ ደስታ አፍላቂ፣
አሀዱ አንተ ካሳሁን አስተዋዋቂ።

የፖሊስ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ክፍል በአዲስ ዓመት መድረክ ከሚናፈቅባቸው እንደነ ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ ካሉ አንጋፋ መድረክ መሪዎች ቀጥሎ እጅግ የገነነ አስተዋዋቂ ቢኖር ካሳሁን ገርማሞ ቀዳሚው ነው። “ካሳሁን ገርማሞ ማን ነው?” ለሚለው የዚህ ዘመን ጥያቄ የዛሬው ዝነኛ ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) አባት ነዋ! ማለት ብዙ ድካም የሚያቀልል ይመስለኛል።

ካሳሁን ከመድረክ መሪነቱ በተጨማሪ በግጥምና ዜማ ደራሲነት ይታወቃል። እንደነ ታደለ በቀለ፣ ሂሩት በቀለ፣ ተስፋዬ በላይ እና በኃይሉ እሸቴን የመሰሉ ታላላቅ ድምፃውያን ድርሰቱን ዘፍነዋል። በጋዜጠኝነት ሙያም በ”ፖሊስና ህብረተሰብ” የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ለዓመታት ሰርቷል።

ጨዋታ አዋቂው፣ መድረክን በግጥም ማስተዋወቅን እንደ ዝርው ንግግር የተካነው ካሳሁን ገርማሞ፤ በአዲስ ዓመት መድረክ ካንቆረቆራቸው አያሌ የማስተዋወቂያ ግጥሞቹ አንዱን እንሆ።

ባህላዊ ሙዚቃ በባህል ልብስ አሸብርቆ፣
በዝነኛው የፖሊስ ሰራዊት ሁለተኛው ኦርኬስትራ ተጠናቅቆ፣
ከንፁህ የማር ወለላና ከጣዝማ ማር ተደባልቆ፣
ከመስከረም አየር ጋር ወግና ስርዓቱን ጠብቆ፣
እንሆ ለክቡራትና ክቡራን ይቀርባል ተራውን ጠብቆ።

ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)

ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)

የወታደርም ይሁን የሲቪል የሙዚቃ ጓድ አዲስ ዓመት ደርሶ ዋናው መፋለሚያ ስፍራ ነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትያትር ቤት። የየክፍሉ አስተዋዋቂዎች ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እየተምነሸነሹ፤ የኋላ የፊቱን በውብ ቃላትና ግጥም ከሽነው የሚያቀርቡበት ይህ ቤት ታዲያ፣ የራሱ ተፋላሚ ዝነኛ መድረክ መሪዎች አሉት። ከዝነኛ መድረክ መሪዎቹ አንዱ ደግሞ ተስፋዬ ሳህሉ ነው።

ተስፋዬ ሳህሉን ከሁሉም መድረክ መሪዎች ልዩ የሚያደርገው አንድ ሰው አለመሆኑ ይመስለኛል። አንድ ሰው አለመሆኑ ስል ምን ማለቴ ነው? ላብራራ። ተስፋዬ ሳህሉ እስካሁን እንዳየናቸው አስተዋዋቂዎች የሁለት ወይም የሶስት ሙያ ባለቤት አይደለም። እጅግ የበዙ ሙያዎችን ጠቅልሎ የያዘ የኪነጥበብ ዋርካ እንጂ። ተዋናይ ነው። የውዝዋዜ አሰልጣኝ ነው። የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ነው። ተረት ተናጋሪ ነው። የዜማና ግጥም ደራሲ ነው። ድምጻዊ ነው። የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጨዋች ነው። ስንቱ ይነገራል።

የሴት ተዋንያንን በመድረክ ላይ መመልከት ብርቅ በሆነበት ዘመን ለዓመታት ሴት መስሎ በበርካታ ትያትሮች ላይ በመጫወት ታላቁን ክፍተት የሞላ ሰው ነው። እንደነ ሰላማዊት ገብረስላሴ ያሉ ፈር ቀዳጅ ሴቶች ብቅ ማለት እስኪጀምሩ፤ ተስፋዬ ሳህሉ ሲሻው እንደ ሴት፣ ሲፈልግ ወንድ ሆኖ እየተጫወተ የኢትዮጵያን ትያትር ዳዴ ብለው ካሳደጉ ጥቂት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አይረሴ ተረቶችን ከድንቅ አቀራረብ ጋር እየከወነ በብዙዎቻችን የልጅነት ልብ ላይ ምስሉን ለዘልዓለም ያተመ ጠቢብም ነው።

በ1940ዎቹ የቃኘው ሻለቃ ወደ ኮርያ ልሳነ-ምድር ሲዘምት፤ ተስፋዬ ሳህሉ ካንዴም ሁለቴ ተጉዞ የወታደራዊ ሳይንስ ተዋናይ በመሆን ታላቅ ጀብድ ፈጽሟል። ለዚህም አገልግሎቱ የሃምሳ አለቅነት ማዕረግን አግኝቷል። በጥቅሉ ተስፋዬ ሳህሉን በዚች ጠባብ ገጽ እንዲህ ነው ብለን፣ ሁሉን መግለጥ አንችልም። የዘመን ስንክሳሩን ለሌላ ቀጠሮ እናሻግረውና በድምጹ ከተጫወታቸው ተወዳጅ ዘፈኖቹ አንዱ የሆነችውን “ዓለም እንዴት ሰነበተች”ን እናጣጥም። ተስፋዬ በህይወት ቢኖር ኖሮ የዛሬውን የዓለም ዱብ እዳ እያሰበ በአዲስ ዓመት መድረክ ይህንኑ ጥያቄ ማንሳቱ የሚቀር አይመስለኝም።

ዓለም እንዴት ሰነበተች እስኪ እንጠይቃት
ሰላም ጤና ነች ወይ ከፋት ወይ ደስ አላት፣
ማነው ከልጆቿ በጎ ሚመኝላት፣
ከስቃይ እንድትድን ዓለም የሁሉም ናት።

ታማኝ በየነ

ታማኝ በየነ

ከጥንቱ ቀረብ ወዳለው ዘመን ስንመለስ ደግሞ የማዕከላዊ እዙን ስዩም ባሩዳን ጨምሮ፤ ብሔራዊ ትያትር ከሰፊው ህዝብ ያስተዋወቀውን ትንታግ መድረክ መሪ ታማኝ በየነን እናገኛለን። የዛሬው የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ የተዋጣለት የመድረክ መሐንዲስ ነው። ተናግሮ፣ ዘፍኖና ገጥሞ አፍ የሚያስከፍት ድንቅ የመድረክ ከያኒ።

ወጥ እንኳ አይጣፍጥ በርበሬ ካነሰው፣
ክትፎም አይጣፍጥም ሚጥሚጣ ካነሰው፣

እንዴት ለዚህ ኪነት ጭብጨባ ይነሰው – እያለ ነበር በ1975 ዓ.ም በትንሳኤ በዓል ዋዜማ ከብሔራዊ ትያትር ታዳሚ ባሻገር፤ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት አያሌዎች ለመጀመርያ ጊዜ በአድናቆት የተመለከቱት። ታማኝ በየነ ከዛች ዕለት በኋላ የአዲስ ዓመት ዝግጅቶችን ጨምሮ በርካታ መድረኮችን በታላቅ ብቃት በመምራት፤ የታላላቆቹን ፈለግ በልዕልና ያስቀጠለ ባለሙያ ነው።

በደርግ ዘመን በህዝብ ለህዝብ መድረክ ዓለምን ከዞሩ ከያኒያን ጋር አብሮ፤ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያዊ ባህል ካስተዋወቁ ጠቢባን መካከል አንዱ ነው። እንደ መድረክ መሪ፣ እንደ ተወዛዋዥና እንደ ሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋች ጭምር እየሆነ፤ በጎደለው ሁሉ እየሞላ ለጥበብም ለሀገሩም እንደ ስሙ የታመነ- ታማኝ በየነ።

መውጫ

መድረክ መሪነት ዛሬ ዛሬ የእግረ-መንገድ ሥራ ቢመስልም፤ ሙያውን አክብረውና አስከብረው ቢነገር-የማያሳፍር፣ ቢፃፍ- የሚያኮራ ታሪክ ያላቸው አስተዋዋቂዎች ብዙ ናቸው። እዚህ የተነሱት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። የተነሱትም እዚህ ከተገለፀው እጅግ የሚልቅ ህልቆ መሳፍርት የሚነገር፣ የሚፃፍ ታሪክ አላቸው። የጥንቱን አዲስ ዓመት ድባብና የመድረክ መሪዎችን አይተኬ ሚና በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል ስለሆነ፤ የተገለፁት መድረክ መሪዎች ታሪካቸው በዝርዝር አልተወሳም። ጊዜ ሲፈቅድ ሁሉንም አንድ በአንድ ዘርዝረን እንዘምርላቸው ይሆናል። ላሁኑ ግን ስለ መልካም ተግባራቸው ሁሉ አመስግነን እንለያይ። አዲሱ ዓመት ከፍ የምንልበት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የጤና ሰገነት ይሁንልን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top