ፍልስፍና

የጊዜ እሳቤ፣ የዘመን መንፈስ፣ ለውጥና የጋራ ሕልውና

1. መግቢያ

ጊዜ ውስብስብ ፍልስፍናዊ ፅንሰ-ሐሳብ ሲሆን ከጥንት አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሉ አሳቢዎችን ያነጋገረ ርእሰ-ጉዳይ ነው። ሕይወት እና የጋራ ህልውና፣ የታሪክ ንባብና የወደፊት እቅድ በጊዜ እሳቤ ላይ ይመረኮዛሉ። እንዲያውም አንድ ማኅበረሰብ የሕይወት አረዳዱ ለጊዜ ባለው እሳቤ ላይ ይመሰረታል ብለው የሚሞግቱም አሉ። የዘመን መለወጥ፣ በአላፊ ጊዜ ላይ ያለን አረዳድና የታሪክ ሁነቶች ትርጓሜ፣ የጋራ ሕልውና፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርገው ግንኙነትና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ጊዜ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ነው። የጊዜ እሳቤና የዘመን መንፈስ ሐተታ ያላቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ፤ ከሕይወት ትርጉምና ንጽረተ- ዓለም (World View) ጋር ያላቸውን ቁርኝት መረዳት የዚያን ማኅበረሰብ የኅሊና ካርታ ለማንበብ፣ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ኢኮኖሚና የባህል ሽግግር፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ትልቁን ሚና ይጫወታል። እንዲያውም የአንድ ማኅበረሰብ የጊዜና የዘመን አረዳድ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ ጊዜ፣ ቦታ፣ ተፈጥሮ (ግዙፉ ቁሳዊውና መንፈሳዊው)፣ ሰውና ስሪቱ (ቁሳዊ ግንባታውና አስተሳሰባዊ መዋቅሩ)፣ እና ልዕለ-ተፈጥሮ አካል (እግዚአብሔር፣ አላህ፣ ዋቃ፣ …) በእነዚህ መካከል ያለውን መስተዋድድ (ቁርኝት) አለመረዳት ያንን ማሕበረሰብ ማወቅ፣ ማስተዳደር፣ መጥቀም፣ መቆጣጠርም ሆነ መግዛት አይቻልም።

ይህ ጽሑፍ በየዓመቱ የምናከብረውን የዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው። በኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተመዘገበው የዘመን መለወጫ በዓል መስከረም አንድ ነው። ይህ ማለት ግን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫው መስከረም 1 ነው ማለት አይደለም። ጽሑፉ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ላይ አይደለም ትንታኔ የሚሰጠው። አዲስ ዘመን ምንድን ነው? የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ለመን ከሌላው ዓለም በተለየ ለ7 ዓመታት ከ8 ወራት ገደማ ወደኋላ ዘገየ? የሚሉ ጉዳዮች የባኅረ ሐሳብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት ሰዎች፣ የባህል እና የታሪክ አጥኝዎች ትንታኔ እና ማብራሪያ ቢሰጡባቸው ይሻላል። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ፍልስፍናዊ የጊዜ እሳቤ ምንድን ነው? የዘመን መንፈስ ከጊዜ እሳቤ ጋር ያለው ቁርኝት ምን ይመስላል? የኢትዮጵያውያን የጊዜ እሳቤ ምን ይመስላል? የጊዜ እንሳቤ እና የዘመን መንፈስ ከሕይወት ለውጥ እና ቀጣይነት ጋር እንዴት ይያያዛል? በታሪክ ንባብ፣ የዛሬ ኑሮ እና የነገ ዕቅድ ላይ የጊዜ አረዳድ እና የዘመን መንፈስ እሳቤ ማኅበረ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ምንድን ናቸው? የሚሉ ጉዳዮችን በአጭሩ ለንግግር፣ ለውይይት እንዲያመች ተደርጎ ቀርቧል።

2. የጊዜ እሳቤ

የጊዜ ትርጓሜና ከሕልውና ጋር ያለው ትስስር አከራካሪ ከሚባሉ የፍልስፍና ርእሰጉዳዮች አንዱ ነው። የተለያዩ ባህሎች የተለያየ የጊዜ እሳቤ አላቸው። ጊዜ (Time) ለአንዳንዶች ምንም ትርጉም የሌለው ብዥታ ሲሆን፤ ለሌሎች ደግሞ ሕልውናን ከጊዜ ውጭ ማሰብ አይቻልም ይላሉ። ጊዜ በሕልውና ላይ ምን ዓይነት ጫና እንዳለው በግልጽ ባይታወቅም የጊዜ እሳቤ ግን በግለሰቦች እና በማኅበረሰቦች ሕይወት እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጫና ያሳድራል።

ጌዜ በዝርው የሰዓት ልኬት ተቀንብቦና ጊዜ በረቂቁ ዘመን ተበይኖ መንፈስን ተላብሶ ሊታሰብ ይችላል።

በመጀመሪያው አረዳድ ጊዜ በመለኪያ ቀርቦ ሁሉም በፈቀደው ልክ የሚጨልጠው መቁንን ነው። ለምሳሌ ስንት ሰዓት ነው? ሁለት ሰዓት ላይ እንገናኝ፤ የዚህ መስሪያ ቤት የሥራ ሰዓት 8 ሰዓት ነው፤ በሰዓት 200 ብር ይከፈልሃል፤ በሰዓት ካልደረስክ … በመስከረም 1980 ዓ.ም እንዲህ ተደረገ፤ ጥር 21 የልደት ቀኔ ነው፤ አንድ ዓመት ይህን ይህን ያክል ወራት እና ሳምንታት አሉት፤ በጥቅሉ በዚህ አረዳድ ጊዜ ከቁጥር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ሲኖረው ተለምዷዊውን ሕይወት እና ተግባቦች በመደጎም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በዚህ አረዳድ መፍጠን እና መዘግየት፣ የነገሮች መለዋወጥ፣ የደቂቃዎች እና የሰዓታት ትርጉም እና ዋጋ የሚበየነው አንድ ማኅበረሰብ የጊዜን እና የክዋኔን፣ የአምራችነትን እና የጊዜን አስፈላጊነት በሚመዝንበት ዋጋ ይለካል። ይህም የጊዜ አረዳድ ከቦታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መሰረታዊ ፋይዳ ያለው ነው።

ኸርበርት ጄ ሙሌር የተለያዩ ይትበሃሎችን (traditions, cultures) እሳቤ በሚከተለው መልኩ ጠቅለል አድርጎ አቅርቦልናል፦

በተለምዶ “ጊዜ ይፍታው” እንላለን፤ ነገር ግን ስለጊዜ ያለን እሳቤ የሚያመጣውን ለውጥ አንገነዘብም። ለጥንት ግሪኮችና ለሮማውያን ጊዜ ቀሰስተኛ (አዝጋሚ) ባሕርይ አለው። የሰው ልጆችን የሥራ ውጤት ጥፋት በማቀድ የማይፋታ (የዘላለም) ጠላት ነው። ለሂንዱ ጠቢብ (sage) ጊዜ ግትርና አወናባጅ (static or illusory)፣ ከወራጅ ወንዝ ይልቅ የረጋ ባሕርን ይመስላል። ስለዚህ የታሪክ ሁረት (ጉዞ) የሚፈጥራቸው ቶሎ ታይተው የሚጠፉ ፍትጊያዎች (ንቃቃቶች) ሞኞችን ያጠቃሉ። ለዘመናዊ ምዕራባዊያን ደግሞ ጊዜ እጅጉን አስፈላጊ ውድ ነገር ነው። ይነገርለታል፣ ይጠብቀዋል፣ ይኖረዋል። አሜሪካዊው ደግሞ ይባስ ብሎ ሊሰራው እና ሊንከባከበው፣ ሊቆጥበው (የሚቆጥበው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም) ይችላል። በጊዜ አማካኝነት ታላላቅ ነገሮች እንደሚከሰቱ ተስፋ ይደረጋል። ተስፋ በቆረጠ ጊዜም የባሱ መቅሰፍቶች በጊዜ ሂደት እንደሚከሰቱ ይሰማዋል። ለእሱ በማንኛውም ሁኔታ ነገሮች በሂደት ላይ ናቸው፤ ጊዜም ይከንፋል! (Time will tell, we say; but we may not be aware of the difference that is made by our very conception of time. To the Greeks and Romans time was characteristically a slow but inexorable enemy of man, telling the destruction of all his work. To the Hindu sage it was static or illusory, resembling a deep pool rather than a flow or a river; so the splash of history made ripples that vanished as they spread, distracting only the foolish. To the modern Westerner, on the contrary, time is all-important. He tells it, keeps it, lives by it punctually. In America he has a passion for making it and saving it (though what he saves it for may not be clear). It has been the great hope, in its promise of ever bigger and better things to come. And if he is now much less hopeful he has more vivid sense of the horrors that time may bring. For him, in any event, things always keep moving. Time Marches On! )

የጊዜ ቀስት ሁሌም ወደ ፊት ነው የሚጠቁመው

የአፍሪካውያን የጊዜ እሳቤ ላይ ሙግት ካቀረቡ አንዱ ጆን ሚቢቲ “ለአፍሪካውያን ጊዜ የሩቅ አላፊ እና አሁናዊነት (Long past and present) ብቻ እንጅ ነገ የሚባል ነገር የለም” (“time is a two-dimensional phenomenon, with a long past, a present, and virtually no future.”) ይላል። በዚህም የተለመደው ጊዜ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ ያለውን ሦስትዮሽ ቀጥታዊ ትስስር አፍሪካ ውስጥ የለም የሚል ድምዳሜ ይይዛል። ይህም አፍሪካውያን ነገ የሚባል የጊዜ ማዕቀፍ የላቸውም የሚል ከሕይወት ግብ- የለሽነት ጋር የሚያያዝ አከራካሪ ድምዳሜን ይይዛል። አንድ ማኅበረሰብ ነገ የሚባል እሳቤ ከሌለው የሕይወት ግቡን በንጹር ለማስቀመጥ መቸገሩ አይቀርምና የሚቢቲ አስተሳሰብ ይህ አንድምታ አለው። እንደ ኦኬ ሞሰስ ሙግት ይህ ድምዳሜ የራሱ የሆነ የሥነ- እውቀት እና የአስተሳሰባዊ ስንኩልነትን የሚያመላክት ስሁት ድምዳሜ ነው። የሰው ልጅ አሁናዊ ኑሮው በቦታ የተገደበ ስለሆነ ከዛሬ ባሻገር፣ ከቦታ ወሰን ውጭ ከወዲያ ስላለው ዓለም (‘perception-transcending’ or ‘knowledge-transcending’ world) እንደማያስቡ የሚያመላክት አደገኛ ድምዳሜ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉንም አፍሪካውያን ጠቅልሎ አፍሪካውያን ትንቢት፣ ነገ ወይም መጭው ጊዜ የሚባል ነገር የላቸውም የሚለው ድምዳሜ አሳማኝ አይመስልም። ሴጉን ባዴግሲን(Segun Gbadegesin) ይህንን የሚቢቲን ድምዳሜ “ጥልቅ ትንታኔ እና ግምገማ የጎደለው ዘፈቀዳዊ የላይ የላይ ተራ አስተሳሰብ እና መረጃ ላይ የተመሰረተ ጥንቅር (Mbiti’s thesis is merely “a report of a communal world-view without an attempt to evaluate” it)” ብሎታል። ለምሳሌ የኢትዮጵያውያን የጊዜ እሳቢ ከዚህ ድምዳሜ ጋር አይስማማም።

እንደ መሳይ ከበደ ሐተታ የኢትዮጵያውያን የጊዜ እሳቤ በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው ጊዜ ዙሪያ ጥምጥም ተፈራራቂ (cyclical) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀጥተኛ የወደፊት ግብ ያለው (teleological)። ሁለቱ በመርህ ደረጃ የሚቃረኑ ይመስላሉ እንጂ የየራሳቸው ማኅበራዊ፣ ህልውናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች አሏቸው። በምድራዊ የቀን ተቀን ሕይወት ማሕበረሰቡ ጊዜን ተፈራራቂ ባሕርይ ያለውና ከዕድል ጋር የተገመደ ተለዋዋጭነት አለው። ዛሬ ከፍ ያለው ነገ ዝቅ ይላል። የዛሬው ጌታ ነገ ባሪያ ይሆናል፣ የዛሬ ሃብታም፣ ነገ ይደኽያል… ወ.ዘ.ተ.. ሕይወት በተፈራራቂነት ለሁሉም ትደርሳለች የሚል አስተሳሰብ አለ። ይህም እያንዳንዱ ተራውን ይጠብቃል እንጂ በዚህ ምድር ላይ ቋሚ፣ ዘለዓለማዊ የሆነ ነገር የለም የሚል ነው። ምናልባት ከተፈጥሯዊ ሁነቶች መቀያየር ጋር የሰው ልጅ ማኅበራዊ መንበር (Status) ም እንዲሁ ተፈራራቂ ነው የሚል ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የሰው ልጆች የጋራ እጣ ፈንታ ወደ ሆነው ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የሚመለከተው የጊዜ እሳቤ ነው። ጊዜ ሄዶ ሄዶ ወደ ዘላለማዊነት የሚለወጥ ነገ እንዳለ የሚያትተው የጊዜ እሳቤ ነው። በዋናነት በአብርሃማዊ ሃይማኖቶች የተቃኘው ይህ አስተሳሰብ ስለ ነገ ግልጽ አተያይ አለው። ከጌታ መምጣት በኋላ ስለሚሆነው በራዕይ ወይም በትንቢት የሚያስቀምጡ የሃይማኖት መምህራን ነገን ከዛሬ የተሻለ ወይም የከፋ (ጽድቅና ኩነኔ)፤ ገነት ከምድር የተሻለች፣ ሲኦል ደግሞ ከምድራዊ ሕይወት የከፋ የስቃይ ስፍራ ተደርገው ተስለዋል። በዚህኛው የጊዜ እሳቤ የመጭው ጊዜ ብቻ ሳይሆን የሕይወት አውድማ የሆነውን ቦታንም ጭምር ያዘጋጀ ትርጓሜ ነው። ይህ አስተሳሰብ እንደ መሳይ ትንታኔ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው “ሃገር በመጨረሻው ጊዜ ከፍ ያለ ሥፍራ የተሰጣት የተመረጠች፤ ከሁሉም በላይ የምትሆን” እንደሆነች ማመላከቱ ነው። እንዲያውም ለመሳይ ኢትዮጵያን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ለመታደግ በአውሮፓዊ የጊዜ አስተሳሰብ የተቃኘ አውሮፓን አንጋጦ የሚያይ የዘመናዊነት መስመር በመተው ከራሳችን የጊዜ እሳቤ በሚመነጭ አስተሳሰብ መቃኘት አለበት ይላል። (ይህን ጉዳይ ወደፊት ገፋ አድርገን እናየዋለን)። በዚህ ሚታዊ (አፈታሪካዊ) አስተሳሰብ የተቃኘው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‘ኢትዮጵያ’ የሚለው ዘፈን ላይ ከመሳይ ሐተታ ጋር የሚስማሙ ስንኞችን እናገኛለን:-

“የመጪው ዘመን ፊት ናት መሪ፣ ዛሬ ዓለም ቢላት ኋላ ቀሪ”

ይህ የመጭው ዘመን መቼ ነው? እንዴት ነው መሪ የምትሆነው? ብለን ስንጠይቅ ከዚህ አስተሳሰብ በተቃራኒ ወደ አሉታዊ መስመር የሚያመራን የጊዜ አጠቃቀም እና ለሕይወት ያለን ለዘብተኝነት ከምድራዊውም ከሰማያዊውም መርሆዎች ውጭ ሆኖ እናገኘዋለን። “ይህንን የመሪነት ሚና” የሚያስተባብል፣ ኢትዮጵያውያን ከምንተችበት ጉዳይ አንዱ፣ በጊዜ ላይ ያለን ለዘብተኛ አቋም ነው። “የሐበሻ ቀጠሮ” እንዲሉ በግለሰቦች ግንኙነትም ሆነ በተቋማዊ አሰራር የምናሳየው መጓተት የከልኩ አያልፍም ዓይነት ቸልተኝነት ምንጩ ምን እንደሆነ መጠናት ይኖርበታል። ምናልባትም ለተፈራራቂው የጊዜ እሳቤ ከዘለዓለማዊው ያነሰ ግምት ስለምንሰጥ ይሆን? ለጊዜ ለምሳሌ ሙሌር እንዳለው አሜሪካውያን ያላቸውን ክብር ያክል አለመስጠታችን በዚህ ምድር ላይ ያልተደረገ የለም፤ በጊዜ ውስጥ አዲስ ነገር አይከሰትም የሚል አቋም ያለን ይመስላል። ይህስ በመጭው ዘመን የመሪነት መንበር ላይ ሊያስቀምጠን የሚችል ትብአት አለው? ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ለዘመን መለወጫ የምንሰጠው ሽርጉድ ከዚህ ከጊዜ እሳቤያችን (አጠቃቀማችን) ጋር የሚሄድ አይደለም። ለዚህ ነው የጊዜ እሳቤ በተግባር ካልተደጎመ እየሆነ ባለው እና በቢሆን ዓለሙ መካከል ተቃርኖ የሚፈጥረው። ይህም በግለሰብ ደረጃ የህሊና መቃወስ እንደሚያስከትለው ሁሉ በሀገር ደረጃም ኋላቀርነትን እና ድህነትን ማስከተሉ አይቀርም።

ይህ የመጀመሪያው የጊዜ አስተሳሰብ ዘመን ተቆጥሮ ትንቢት ተነግሮ የሚከሰት የቀጠሮ ጉዳይ ስለሆነ አስተሳሰቡ የጊዜ ዝርው ትርጓሜ ነው። በሕይወት መስመር ላይ ይህን ብታደርግ በዚህ ጊዜና ቦታ እንዲህ ዓይነት ነገር ያጋጥምሃል የሚል እቅጩን የመበየን አዝማሚያው ነው ጊዜ ከቦታ ጋር የተሳሰረ ግዝፍና ያለው እንዲመስል ያደረገው። ስለዚህ በሕይወት ስኬታማ ለመሆን በቁርጠኝነት ከጊዜ ጋር መቀዳደም፣ ጊዜን መቆጣጠርን ይጠይቃል። ይህን የጊዜ ትርጓሜ በሚቀጥሉት ስንኞች እንቋጨው፤

“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ

ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ”

የዚህ ግጥም ደራሲ ዛሬ ላይ የታክሲ ፌርማታዎችን ዞርዞር ብሎ ቢጎበኝ በረጃጅም ሰልፎች በጊዜ ላይ ቆሞ ታክሲ የሚጠብቀውን ተሳፋሪ ቢያይ እና በታክሲ እጥረት ምክንያት የሚሽቀዳደመውን ሕዝብ ቢያይ የዘመኑ መንፈስ እንዴት እንደተለወጠ ማየት ይችል ይሆናል። ምናልባት (ልሽቀዳደም ብዬ ጊዜ ላይ ልሳፈር፤ ታክሲ እየጠበቅሁኝ ውያለሁኝ ሰፈር) ሊል ይችላል። ይህ የቢሮክራሲ፣ የአገልግሎት ተዛንፎ፣ የህዝቦች ስለጊዜ ያለን አመለካከት፣ ሳናርም አዲስ ዘመን መለወጫ ላይ ጉሮ ወሸባ ወይም ለወደፊቱ ቃልኪዳን የተገባልን ታላቅ ህዝቦች ነን እያሉ ቢያወሩት የዘመንን መንፈስ፣ የጊዜን ትርጉም ካለመረዳት የመጣ የአስተሳሰብ ዝንፈት ነው። አንዳንዴ ለመምራት ብቻ ሳይሆን በተገቢው ለመመራትም በጊዜ ሰሌዳ የሚጻፈውን መጻፍ፣ በጊዜ ማዕበል የመዋኘትን ሙያ፣ ከአንድ የጊዜ እርካብ ወደ ሌላ የጊዜ እርካብ የሚያሻግር ድልድይ መገንባትን ይጠይቃል። የጊዜ እሳቤ ከሕይወት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነውና፤ ትክክለኛውን የጊዜ አጠቃቀም ማወቅ ወደ አሸናፊነት፣ የጋራ እድገት፣ ወደ መሪነት የሚያበቃ ቁልፍ ነው።

በዚሁ ወደ ሁለተኛው የጊዜ ይዘት እንለፍ። ለጊዜ ያለን ትርጓሜ (ስሜት) ግልጽም ይሁን አይሁን፣ በመረዳት ላይ ይመስረት ወይም ዘፈቀዳዊ፤ ሄዶ ሄዶ የታሪክ ፍልስፍና ጋር ይቆራኛል፤ የሕይወት መዝገብ መሆኑ አይቀርም። (In short our feeling about time – however vague or unconscious – ultimately involves the philosophy of history). ጊዜ ሁነትን/አሁነንትን ብቻ ሳይሆን ትናንትን አዝሎ፣ ዛሬን አንጠልጥሎ ወደ ነገ የሚደረግ ማዝገም ነው ማለት ነው።

በሁለተኛው እና ረቂቁ የጊዜ እሳቤ ጊዜን የምናገኘው በዘመን ተበይኖ ከሕይወት ምሕዋር ጋር ተቀይጦ፣ ከማኅበራዊ ገቢርና ከተፈጥሮ ዑደት ፍሰት ጋር ተዳቅሎ፣ መንፈስንና ቁስን ተሸክሞ ወይም በመንፈስና ቁስ ላይ ተጭኖ፣ በሕይወት ምንጣፍ ላይ ተሰጥቶ ወይም መንበር ላይ ነግሶ ወይም ለሕይወት ጉዞ መደላድል መንበር ሆኖ፣ የሰውን ሕሊና አስተሳሰብን በይኖ አሊያም በአስተሳሰብ ተወስኖ ነው። ‘አይ ያ ጊዜ! እንዲያው የዛሬ ልጆች?! በእኛ ዘመን!…’ እየተባለ ይሞካሻል ወይም ይወቀሳል። ይህም የዘመን መንፈስ (Zeit geist) ይባላል። አንዳንዶች ሕይወትን በበለጠ ለመረዳት የዘመን መንፈስን በደንብ መረዳትና መተንተን ያስፈልጋል ይላሉ። ይህ የዘመን እሳቤ ከላይኛው የጊዜ እሳቤ በምን ይለያል? የዘመን መንፈስ ሲባልስ ምን ማለት ነው? የዘመን መንፈስ የሚለው አስተሳሰብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እንድምታዎች እና ከታሪክ ንባብ ጋር ያለው ቁርኝት ምንድን ነው? በዘመናት መካከል ለሚደረግ መኳረፍ እና መቃቃር፣ በትውልዶች መካከል ለሚደረግ ግጭት የዘመን መንፈስ ትርጓሜ ምን መፍትሔ ይኖረዋል? እነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚቀጥለው እንመለከታቸዋለን። መልካም የአዲስ ዘመን መባቻ እየተመኘን “አሮጌውን ሸኝተን በአዲሱ” (የዘመን አዲስ እና አሮጌ አለው እንዴ? ለመሆኑ ጊዜ ይታደሳል ወይ?) ለመገናኘት የዚያው ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top