አጭር ልብወለድ

የዶሮ ወጥ ሙሾ

ዶሮ ወጥ ለመብላት እንደዚ ጓጉቼ አላውቅም። ለዶሮ ወጥ ማንም እንደዚህ ጓጉቶ አያውቅም። ሰዎች ከረጅም ዓመታት እስር ለመፈታት ስለሚጓጉ.. በተለይ ጊዜው ሲቃረብ ቀናት ይቆጥራሉ። ጉጉታቸው ግን የኔን የዚህ ዓመት ዶሮ የመብላት ጉጉት ሊያክል አይችልም። እኔ ቀናት ብቻ አይደለም የምቆጥረው.. ሰዓታትም፣ ደቂቃዎችም፣ ሴኮንዶችንም እንጂ.. አንዳንዴ ካልዒት፣ ሳልሲት፣ ሳድሲት ምናምን ሁሉ መቁጠር ያምረኛል። እንደገና ደግሞ መቁጥርም አልፈልግም። ስቆጥር ጊዜው ይርቅብኛል። ሰዓቱ ሁሉ የተንቀራፈፈ ይመስለኛል። ሳልቆጥርም ደግሞ ጊዜ ራሱ መቁጠር ማቆሜን አይቶ የሚንቀራፈፍ.. ተቆጣጣሪ እንደሌለው የአውቶብስ ሹፌር የሚቆም.. ግንባታ እንደተሰጠው መኃንዲስ ዓመታትን የሚሰርቀኝ ስለሚመስለኝ መልሼ መቁጠር ጀምራለሁ። ነገሬ ሁሉ ፍቅሩን ኤርትራ ልኮ መመለሷን እንደሚናፍቅ ምስኪን የዘጠናዎቹ ወጣት ከሆነ ሰነባብቷል።

ምነው ለእህል ይሄን ያህል ምናምን እያሉ የሚዘምሩ ሰዎች እንደሚኖሩ አውቃለሁ። አልፈርድባቸውም። ምንያቱም ይሄ የዶሮ ወጥ ቀጠሮ ለኔ ምን ማለት እንደሆነ ስለማያውቁ ነው። ኢክማ የልቤ እስትንፋስ በረመዳን ሁለተኛ ሳምንት ውስጥ ነበር ለአዲስ ዓመት ዶሮ ወጥ ሰርታ እንደምታበላኝ ቃል የገባችልኝ። በእጆቿ ሰርታ.. የፍቅርን ዶሮ ወጥ.. የስጋና የነፍስ ምግብ። ሰሞኑን ሀሳቤ ሁሉ ስለ ዶሮ ሆኗል.. አለም ሁሉ በዙሪያዬ እየጮኸ ዶሮ ዶሮ የሚል ሁሉ ይመስለኛል። ዶሮ ወጥ። ዶሮው ወንድ ይሁን ሴት አያገባኝም። ምን አገባኝ። ዶሮ ወጥ። ግን የዶሮው ጾታ በመጀመሪያ የምንወልደውን ልጅ ጾታ የሚጠቁም ቢሆን.. ከዚያ ጋር ቢያያዝስ.. ወይም ደግሞ ግንኙነታችን እንደሚዘልቅ እና እንደማይዘልቅ ማሳያ ቢሆንስ.. እረ እንደዛ ሚባል ነገር የለም። ግን ደግሞ ቢኖርስ! እያቃጀኝ ነው መሰለኝ።

ከስንት ሶላት፣ ጸሎት እና መኃላ በኋላ ዛሬ ጷግሜን አምስት ደርሷል። በዚህ ዓመት ጷግሜን ስድስት ባለመሆኑ ብቻ ራሱ ባለፉት ሳምንታት ምን ያህል ጊዜ ፈጣሪዬን እንዳመሰገንኩ.. እሱ ካስታወሰው ነው እንጂ እኔስ አልቆጠርኩትም። ብዙ.. በጣም ብዙ ጊዜ እንደሆነ ብቻ አውቃለሁ። ለነገሩ ልመና እና ምስጋና ሰሞኑን አብዝቼበታለሁ.. ሳላጨናንቀው አልቀርም። በመዓልትና በሌሊት ሁሉ እንዲህ እያልኩ እጸልያልሁ..

አቤቱ.. ኢክማን ኢክማ፣ ዶሮን ዶሮ አድርገህ የፈጠርህ ፈጣሪ ሆይ
የሽንኩርት እና የቲማቲም፣ የበርበሬ እና የዘይትን ውህደት ጥበብ የገለጥክ
ኢትዮጵያውያንን ለዶሮ ወጥ የማዘጋጀት ማዕረገ ስልጣን የሾምክ
ሰላም ላንተ ይሁን..
ለአዲሱ ዓመት በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር ታደርሰን ዘንድ..
የፍቅርንም አጋፔ ከምንወደው ጋር እንካፈል ዘንድ.. አሜን።

በመስኮቱ አሻግሬ ወደ ውጪ ስመለከት ጊቢ ውስጥ የነበሩ ጥቂት ዶሮዎች ትኩር ብለው ይመለከቱኛል። ‘ለፍቅር መስዋዕት እንደሚሆን ዶሮ እድለኛ አይኖርም’ የሚሉ ይመስለኛል። ‘የዚያን ዶሮ እድል ለኔ ባደረገው’ እያሉ የሚወያዩም ይመስለኛል። ያዩኝ ያዩኝ እና ‘ምናልባት ይሄ ሰውዬ የፍቅር አምላክ ይሆን’ እያሉ የሚብሰለሰሉ ይመስለኛል። ወደ ቤት ገብቼ ሀሳቤን ከዶሮ ምናባዊ የፍቅር ድርሰት ለማላቀቅ ሬዲዮ ስከፍት.. በሬዲዮ ውስጥ ያለው ሙዚቃ..

እንዴት ነው ዘንድሮ
ስንት ገባ ዶሮ
ባስራ ሁለት ብልት
ይለካ ሴትነት

የሚለውን የማናለቦሽ ዲቦ የበዓል ዜማ ይጫወታል። ሴትነት ሲለካ? ምን ማለት ነው? ስል አስባለው። ኢክማዬ የልቤ እስትንፋስ.. የነፍሴ መረቅ.. የሴትነቷን ልክ ልታሳየኝ ነው ማለት ነው ዶሮ ወጥ ሰራልሃለው ያለችኝ። ሴትነት ከሰውነት የተለየ ነገር ነው? ሴትነት ሆነ ወንድነት ሁለቱም ሰውነት በሚለው ውስጥ የሚካተቱ ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም ማለት ነው? እንዴት ሴትነት በወጥ ይለካል? ግን እኮ ቢያንስ ዶሮ ወጥ ነው። ብዙ ብዙ አስባለው።

አዳም ረታ ምን ታይቶት ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እንዳለ አላውቅም.. ግን ከሰማይ ከወረደ.. ፍርፍር ሳይሆን ዶሮ ወጥ መሆን ነበረበት። ጥሩ ጽፎ እርሱ ላይ ግን አበላሽቷል.. ሚስቱ ይሄኔ የሞተችው በዶሮ ወጥ ፋንታ ፍርፍር ስለሰራችለት ይሆናል። ፍርፍር ሀዘንን ይዞ ይመጣል። መለያየትን ከኋላው ያሳጅባል። ዶሮ ወጥ ግን የመገናኘት፣ የመጀመር፣ የመጣመር ምሳሌ ነው። በረከትን ይዞ ይመጣል። ዶሮ ወጥ የፍቅር ጥምቀት ነው። እንጀራ ሲለያይ፣ ሲሰባበር፣ ሲራራቅ ነው ፍርፍር የሚሆነው። ዶሮ ወጥ ግን እንጀራው ከነግርማ ሞገሱ በፍቅር ከዶሮ ወጡ መረቅ ጋር ይዋሃዳል። ይጣበቃል። ላለመለያየት። ዘላለም ተቃቅፎ ለመኖር። ፈረሰኛ አጥንት የዶሮውን አካል ደግፎ እንደኖረ የፍቅራችንም የጀርባ አጥንት ይሆናል።

ኢክማዬ ቤተሰቦቿ በሙሉ ሁሌ እንደሚያደርጉት በዓሉን ከዘመዶቻቸው ጋር ለማሳለፍ ወደ ገጠር ሲሄዱ.. እሷ እንደማትሄድ በስንት መከራ እንዳሳመነቻቸው በስልክ የነገረችኝ ጊዜ አፌ በምራቅ፣ ልቤ በደም፣ ነፍሴ በፍቅሯ ተጨናነቀ። ጩህ ጩህ አለኝ.. ነገር ግን ከትርጉም ይለሽ ሽርፍራፊ ቃላት ያለፈ ምንም ማለት አልቻልኩም። እንደኔና እንደ ኢክማ ሁለመናቸው ለተጣመረ ሰዎች የቃላት አገልግሎት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሳናወራ እንግባባለን። ሳንገናኝ እንተያያለን። ስንገናኝ የፍቅር ዶሮ ወጥ እንበላለን። ልንበላ ነው.. ዶሮ ወጥ። ለአዲስ አመት።

የማይነጋ ሌሊት.. የማይልፍ፣ ለብርሃን ቦታውን የማይለቅ ጨለማ.. ትናንት የማይሆን ዛሬ የለምና.. ነጋ። መስከረም አንድ። በዘመናት ታሪክ፣ ጊዜ በሚባል ወንዝ.. ጸሐይ እና ጨረቃ ከተወለዱበት ከመጀመሪያው መጀመሪያ አንስቶ እንደ ትናንቱ አይነት ረረረረረረረ…ጅም ሌሊት ኖሮ አያውቅም። ወደፊትም አይኖርም። ‘የማያልፉት የለም’ ለሚለው አባባል የቁም ምስክር እንደሆንኩ ይሰማኛል። ባለፉት ሳምንታት ምን ያላለፍኩት አለ? ምን ያላሰብኩት? ምን ያላወጣውት? ምን ያላወረድኩት ነገር አለ? አሁን ወደዛ ሃሳብ መመለስ አልፈልግም። ዛሬ የሃሳብ ቀን አይደለም። ዛሬ የድርጊት ቀን ነው። የዶሮ ወጥ ቀን። የፍቅር ማዕድ ቀን። መስከረም አንድ። ሰዓቴን ተመለከትኩ። ገና አስራ ሁለት ሰዓት ራሱ አልሆነም። በሌሊት ተነስቼ እሷጋ ልሂድ.. ወይስ ትንሽ ረፈድ ይበል? እሷ የምትጠብቀኝ ይሄኔ ለምሳ ነው.. ወይኔ ሰውዬው እስከዛ ምን ሆናለሁ? አይሆንም.. አይሆንም.. አይሆንም.. አሁንም መጠበቅ? በፍጹም አይሆንም.. እንዴት ይሆናል? እረ አይሆንም እኮ አይሆንም። ድምጼን ከፍ አድርጌ.. አይሆንም.. ብዬ ጮኽኩና.. የመጣው ይምጣ ብዬ ወደ ኢክማ ልሮጥ በቻልኩት መጠን ፈጥኜ ስነሳ እግሬ ላይ ታስሮ የነበረው ሰንሰለት ጠልፎ ጣለኝ። ሰንሰለት? ቁልፍ? ከዛሬ በፊት አይቼው አላውቅም.. ምን እየተፈጠረ ነው? ምን እየሆነ ነው? ዓለም የተገለባበጠች መሰለኝ። ከወደቅኩበት ቀና ብዬ እግሬን አየሁት። ሰንሰለቱ እግሬን ጎድቶኛል.. እየደማ ነው። እኔ ግን የሚሰማኝ የዶሮ ወጥ ርሃብ ብቻ ነው። የፍቅር ርሃብ። ወዲያው የህክምና ባለሙያ መለያ ልብስ የለበሱ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ተሯሩጠው ወደ ክፍሌ ገቡ። ለሶስት ደግፈው ወደ አልጋዬ መለሱኝ። እየሆነ ካለው ውስጥ አንዱም ነገር ትርጉም እየሰጠኝ አይደለም። ሰዎቹ ባዩት ነገር ምንም የተገረሙ አይመስሉም። ምንም እንዳልተፈጠረ ፊታቸው ላይ ምንም ግራ መጋባት አይታይባቸውም.. በድንገት ከነበርኩብት ዓለም ውስጥ የሆነ ሃይል ነጥቆ እዚህ አምጥቶ የጣለኝ አይነት ነው የሚሰማኝ። ሺህ የሚሆኑ ጥያቄዎች አዕምሮዬ ውስጥ ሲፈጠሩ ይታወቀኛል.. ነገር ግን አንድ ቃል እንኳን መተንፈስ አልቻልኩም። ከሁለቱ ሴቶች አንደኛዋ ግራ ክንዴ ላይ መርፌ ወጋችኝ.. ወዲያው ሰውነቴ ሲደክም.. ወደ ጥልቁ ስዘቅጥ ይሰማኛል.. ራሴን ከመሳቴ በፊት አንድ የሌላዋ ሴት ድምጽ ይመስለኛል.. ደስ የማይል፣ አስቀያሚ ትህትና የሞላው ድምጽ..

“ጋሼ ነስሮ ምን የመሰለ ዶሮ ዶሮ ወጥ እየተዘጋጀ ነው እሺ.. አሁን ይተኙና ከእንቅልፎ ሲነሱ ለምሳ ሰዓት እኔ ራሴ ነኝ የማመጣሎት..” ሌላም.. ሌላም። ትኩስ እንባ አይኔን ሞላው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top