ታዛ ወግ

አርትስ ቴቪ ቨርቹዋል ባዛር አዘጋጀ

ስለቨርቹዋል ባዛሩ ትንሽ ንገሪን እስኪ?

እሺ። ጤና ይስጥልኝ!! አዜብ ወርቁ እባላለሁ። የአርትስ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ ነኝ። አርትስ ቴሌቪዥን የቨርቹዋል ባዛር አዘጋጅቷል። ቨርቹዋል ባዛሩ የተዘጋጀበት ምክንያት፤ በአሁኑ ጊዜ በኮቪድ19 ምክንያት ባዛሮች እየተዘጋጁ ባለመሆኑ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ አዲስ ዓመትና የተለያዩ በዓላት ሲመጡ ባዛሮች ይዘጋጁ ነበር። የተለያዩ ምርቶችና የንግድ እቃዎች በባዛሮች አማካኝነት ለሸማቹ ህዝብ ይቀርቡ ነበር። ገበያው በባዛሮች አማካኝነት ይደምቅ ነበር፤ የዓመት በዓሉ መዳረሻ አካባቢ የነበሩት ሁለትና ሶሰት ሳምንቶች ራሳቸውን የቻሉ የበዓሉ ድምቀት ነበሩ። የዘመን መለወጫ ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶችና ህዝቦች በጋራ የሚያከብሩት እንደመሆኑ፤ ኃላፊነት እንደሚሰማው አንድ ሚዲያ እኛም የበዓሉ መቀዛቀዝ ያሳስበናል። ስለዚህም አንደኛው የገበያ መቀዛቀዝ፤ ሁለተኛ ደግሞ የህ/ሰቡ የድባቴ መንፈስ አለ፤ ይህንን ለመቀየር አሰብን።

በዚህ ጉዳይ ብዙ ካሰብን በኋላ፤ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብዙ ታዳሚዎች አሏቸው፤ ቦታም አላቸው (ቦታ ያልኩህ የአየር ሰዓቱን ነው) ስለዚህ ለምን የቨርቹዋል ባዛር አናዘጋጅም ብለን ሐሳብ ፈጠርን። ሐሳባችንን ለተለያዩ ለምንቀርባቸው ሰዎች አማከርን፣ ነጋዴዎችንም አናገርን፣ ደግሞም ለዳሽን ባንክ ስናቀርብ በሐሳባችን ተስማሙ። ዳሽን ባንክ ኢ-ኮሜርስ የሚጠቀም ስለሆነ ሰዎች ከውጭ ሃገራትም ጨምር መሸመት ይችላሉ፤ አሞሌን በመጠቀም ከየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው ሊገበያዩ ይችላሉ። ሃገር ውስጥም በውጭ ሃገራትም ያሉ እኩል ሊገበያዩ ይችላሉ። እንዲያውም ውጭ ሃገር ያሉ ሰዎች እዚህ ላሉ ቤተሰቦቻቸው እቃ መግዛት ይችላሉ። ይህም በዛ ያለ የውጭ ምንዛሬ ወደሀገር ለማስገባት ይረዳል። በዛ ላይ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት፣ የአንድነት መንፈሱን እና ያለንን ባህል ልናጎላው እንችላለን።

ስለዚህ በነጋዴው የሚቀርቡ ምርቶችን በቴሌቪዥን ስርጭቶቻችን፣ በሶሻል ሚዲያ ድህረ-ገጾቻችን፣ በዩቲዩብ ይቀርባሉ። ተመልካቾችም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በተለያየ ቦታ ሆነው፤ አንዱ ከአረብ ሃገር፣ አንዱ ከአሜሪካ፣ አንዱ ደግሞ በሃገር ውስጥ ሆነው… እኩል ዕቃዎችን እየመረጡ መግዛት ይችላሉ።

ቨርቹዋል ባዛሩ ትክክለኛውን የባዛር ስሜትን የያዘ ነው። ዕጣዎች አሉ፤ ሽልማት ያላቸው ጥያቄዎች አሉ፤ ኮንሰርቶች አሉ፤ ወቅታዊ መልእክቶችም ይተላለፋሉ። በባዛሩ ማጠናቀቂያ ላይም ትልቅ ሽልማት አለን፤ እሱን አብረን የምናየው ይሆናል። ወቅታዊ መልእክቶች ይተላለፋሉ። ስለ ሰላም፣ ኤችአይቪ ኤድስ፣ ኮቪድ 19፣ በጎ አድራጎት… ህብረተሰቡን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ልዩ ልዩ መልእክቶች አሉን። እንደ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ሰዎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እንዲያስቡ መልእክቶች ይኖሩናል። ከዛም በተጨማሪ ደግሞ ከአዲስ አበባ ትረስት ፈንድ ጋር ተነጋግረን፤ ከባዛሩ ገቢ የተወሰነውን ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ ስለሚችሉ ለአዲስ አበባ ትረስት ፈንድ እንዲውል አድርገናል።

በቤታቸው ሆነው ሰዎች በቴሌቪዥን የሚያይዋቸውን እቃዎች አድራሻ በመመልከት እንዲገዙ ያግዛል። ከዛም በተጨማሪ በንግድ ለተሰማሩ ወገኖቻችን አንድ ተጨማሪ የገበያ ዕድል እንፈጥራለን ማለት ነው። እንዲሁም እኛም እንደ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የንግድ ድርጅት ስለሆንን፤ ተጨማሪ ገቢ የምናገኝበትን አማራጭ ዕድል ፈጠርን ማለት ነው።

የፈጠርነው ምህዳር ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮና ጠብቀው ያሻቸውን ዕቃ እንዲገዙ ትልቅ አጋጣሚ ይሆናል። ሁሉም የሚጠቀምበትና ሁሉንም ለማስተናገድ ምቹ የሆነ ባዛር ነው።

በባዛሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ?

ማስታወቂያዎች አሉን፤ እነሱን መከታተል ነው። በቴሌቪዥን እያስተዋወቅን ነው። በሬዲዮም ማስታወቂያ እያስነገርን እንገኛለን። በተጨማሪም ስልክ ቁጥሮች አሉን። ቨርቹዋል ባዛሩ ተጀምሯል። በየዕለቱ የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ቋሚ ነው። በሰፊው የሚቀጥል ነው። ምርትና አገልግሎታቸውን በቪዲዮ ጥሩ አድርገን ቀርጸን በቴሌቪዥን እናስተዋውቅላቸዋለን። ከአ በተጨማሪም ስልክ ቁጥሮች አሉን። በእነዛ ስልክ ቁጥሮች ደውለው፤ የሚፈልጉትን መረጃዎች ማግኘት ይችላሉ። ሁሉንም አካሄድ የሚመሩ ልጆች አሉ። ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲግባቡ ያደርጓቸዋል። ሁሉንም ነገር ያቀሉላቸዋል።

የዚህ የቨርቹዋል ባዛሩ ሐሳብ ባለቤት አርትስ ቴሌቪዥን ነው። ቨርቹዋል ባዛር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ባዛሩ በሰፊው የሚቀጥል ነው። አሁን የምንሰራው ለማስተዋወቅ ነው። ወደፊት በሰፊው የምንቀጥለው ይሆናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፤ በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች የሚገበያዩበት ነው። ለእኛም እንደሚዲያ ተጨማሪ ገቢ ይሆነናል።

የህብረተሰባችን የኦንላይን ግብይት ዝቅ ያለ ነው። ዳሽን ባንክ በዚህ የብዙ ዓመት ልምድ አለው። እናንተ ቨርቹዋል ባዛሩን ስታዘጋጁ ምን የተለየ አካሄድ እና ፈጠራ አምጥታችኋል?

ወደዳሽን ባንክ የሄድንበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው። እነሱ ሰፊ ልምድ አላቸው። ዳሽን ባንክ አሞሌ የሚባል መገበያያ አላቸው። እያንዳንዱ ስልክ ያለው ሰው በቀላሉ ሊጠቀመው ይችላል። ከእጅ ንክኪ ነጻ ስለሆነ፤ ሰዎች ራሳቸውን ከወረርሽን መጠበቅ ይችላሉ። ጊዜያቸውንም ይቆጥባሉ። ህብረተሰቡ የኦንላይን ግብይይትን ቀስ በቀስ በዚህ ባዛር ይለማመደዋል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሸማቾች አሞሌን በመጠቀም ዕቃ ሲገዙ፤ ካወጡት ብር ላይ 5% ተመላሽ ይደረግላቸዋል። በዚህም ሌላ ቦታ ከሚገዙ እዚህ በእኛ የቨርቹዋል ባዛር ቢገበያዩ የበለጠ ገንዘባቸውን ይቆጥባሉ ማለት ነው። ዳሽን ባንክ ጥሩ እያገዙን ነው። በኦንላይን ግብይይትም ጋይድ እያደረጉን (እየመሩን) ያሉት እነሱ ናቸው።

በመጨረሻም፤ የአዲስ ዓመት መልእክት እና የተለያዩ ድርጅቶች ከእናንተ ጋር ቢሰሩ ምን የተለየ ነገር እንደሚጠቀሙ ንገሪን፤ ከሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተለየ አማራጭ አላችሁ?

አርትስ ቴሌቪዥን በቅርቡ ስራ የጀመረ ነው። ከማንም ጋር ውግንና የለውም። ሃገራዊ እውቀትን በማሳደግና ሃገርን በማስተዋወቅ ላይ የሚሰራ የሁሉም ኢትዮጵያውን ድምጽ ነው። ቴሌቪዥን ጣቢያችንን ከኢትዮጵያ የሚነሳ የአፍሪካ ድምጽ ነው። እንግዲህ የተለያዩ ድርጅቶች ከእኛ ጋር ቢሰሩ ታማኝነታችን፣ ሚዛናዊነታችንን፣ በተመልካቹ ዘንድ መወደዳችንን… አብረውን በመካፈል የተሻለች የምንላትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በምናደርገው ጉዞ አብረውን ይሳተፋሉ ብለን እናስባለን። ፕሮግራሞቻችን የተለያዩ ናቸው። የግጥም መድረኮች፣ መዝናኛ ፕሮግራሞች፣ ውይይቶች አሉን። አርትስ ቴቪ አፍሪካ በዓለም መልኩ በአግባቡ አትወከልም የሚል ሃሳብ ስላለው፤ ከኢትዮጵያ በመነሳት የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን ትልቅ ህልም የያዘ ነው አርትስ ቴሌቪዥን።

በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማስተላልፈው መልእክት፤ መልካም አዲስ ዓመት እመኛለሁ። ሰላም፣ መረጋጋት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መከባበር እና መደማመጥ የሰፈነባት ሃገር እንድትሆን። እኔነት የሌለባት እኛነት የሰፈነባት ትልቂቷን ኢትዮጵያ ሁላችንም በጋራ እንድንገነባ እመኛለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top