ታዛ ወግ

ትውልድ በቡሄ መነፅር ያጣናቸው እሴቶች

ዛሬ ከስራ መልስ ወደ ቤት ስሄድ መንገድ ላይ ለሽያጭ የቀረቡትን ችቦዎች ሳይ፤ ቡሄ መሆኑ ትዝ አለኝ። እቤት ስደርስ ጎረቤት በር ላይ አራት ልጆች ቆመው በር ያንኳኳሉ። ሁለቱ ዱላ ይዘዋል ሁለቱ ምንም አልያዙም። ልክ በሩ ሲከፈት ሆያ ሆዬ መጨፈር ጀመሩ። ዱላ የያዙት ሲጨፍሩ ካልያዙት አንዱ የቤቱን አጥር ደገፍ ብሎ ቆሟል። አይጨፍርም።

ወደ ቤቴ ገባሁ። የእኔ ዘመን የቡሄ አከባበር ትውስ አለኝ። ከእሱ ጋር ተያይዞ እያጣናቸው ያሉ እሴቶቻችንንም ጭምር። የልጅነት ጨዋታዎቻችን በውስጣቸው ብዙ እሴቶችን ይዘው ነበር። እነዚህ እሴቶች ምን ፋይዳ እንደነበራቸው ስገነዘብ፣ የአሁኑን ትውልድ የምንወቅስባቸው ብዙ ነገሮች የእነዚህ ያጣናቸው እሴቶች መመናመን ነው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል። “እንዴት?” ከተባለ ቡሄን ብቻ በጥቂቱ አንስቼ በእንዲህ መልኩ ምልከታዬን ላጋራዎ።

ለቡሄ ዝግጅት የሚጀመረው ወሩ ሲገባ አንዳንዴም ከዚያ ቀደም ብሎ ነው። ለጅራፍ የሚሆን ልጥ መሰብሰብ፣ በውሃ ማራስ፣ መግመድ… ሁሉም ልጆች ማለት ይቻላል በንቃት የሚሳተፉበት ነው።

የስራ ክፍፍሉ ዝም ብሎ በዘፈቀደ የሚሰጥ አይደለም። ባለፈው ዓመት የነበረውን ተሳትፎ ያገናዘበ (የገመገመ) ነው። በዚህም ከባለፈው ዓመት ልምድ ተነስቶ ከቡድኑ ጋር ዘንድሮም የሚጨፍር፣ እንዲጨፍር የማይፈቀድለት፣ ሌላ ቡድን የነበረ ጎበዝ ልጅ ካለ ወደ እዚህ እንዲገባ በተለያየ መልኩ ጥረት የሚደረግበት ነው። ማን ነው ታማኝ? የሌሎች ሰፈር ጎረምሶች የጨፈረንበትን ገንዘብ አምጡ ብለው ሊቀሙን ቢሞክሩ፣ ዘዴ ፈጥሮ ወይም ሮጦ የሚያተርፍ ማነው? የሚለው ሁሉ ግምት ውስጥ ይገባል። ማነው ድምፁ ጎልቶ የሚሰማ? ማን ነው ጥሩ አድርጎ ክሽ ክሹን የሚሰራው? የቡድኑ አባላት ስንት ይሁኑ? የሚሉት ሃሳቦች ላይ ውይይት ተደርጎ የሚወሰን ነው። ይህ ሁኔታ ገና በለጋነት እድሜ መወያየትን፣ አንድን ስራ ከመስራታችን በፊት ከማን ጋር መስራት እንዳለብን፣ የግልና የቡድን ስራዎች ምንድናቸው፣ ማን የትኛውን ስራ ቢሰራ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፣ ማን በየትኛው መስክ የበለጠ እውቀትና ችሎታ አለው የሚለውን እና ተገቢውን ሰው ለተገቢው ስራ የመምረጥ እሴትን የጀመርንበት ነበር።

አጨፋፋራችን ዝም ብሎ በእቅድ ላይ ያልተመሰረተ አልነበረም። የት? መቼ? መጨፈር እንዳለብን የሚያስተባብር ከመካከላችን እንደ አስተባባሪም እንደ አምበልም የሚሆን ሰው አለ። ማን ቤት የተሻለ ይሰጣል፣ ሙልሙል የሚሠጠው የትኛው ቤት ነው። አባወራው በስንት ሰዓት ነው የሚገቡት …ወ.ዘ.ተ… ጥናት ይደረጋል። ማን የተሻለ የመምራትና የማስተባበር አቅም አለው፤ ስራችንን እንዴት ባለ አኳኋን ብናካሂድ ስኬታማ እንሆናለን የሚለውንም መለማመድ የጀመርነው እንግዲህ በዚያ በለጋነት ጊዜያችን ነው።

በሽልማት መልክ ከሚሰጠው ገንዘብም ሆነ ሙልሙል ጭፈራው አልቆ ክፍፍል እስኪደረግ ድረስ በማንም አይነካም። ለምሳ ወደቤት የምንበታተን ከሆነ፣ እስካሁን የተሰበሰበው ገንዘብ ተቆጥሮ ነው። ለዚህ ኃላፊነት ማንም አይመረጠም፣ ከመካከላችን ሁላችንም ብቻ ሳንሆን መንደሩም በታማኝነት የሚመሰክርለት ልጅ እንጂ። ታማኝነት የሚያስከብር መሆኑን የተገነዘብነው ያኔ ነው።

የተሰበሰበው ገንዘብ ቆጠራ የሚካሄደው በጋራ ነው፣ በአንዳችን ቤት። ሲከፋፋል ፍፁም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እኩል እኩል ነው። ትርፍ እንኳን ቢኖር ገንዘቡ በእኩል ደረጃ ሊዳረሰ የሚችል ነገር ተገዝቶበት፣ አሊያም ዕጣ ተጥሎ እስከመጨረሻዋ ሰባራ ሳንቲም ሁሉም ድርሻውን እንዲያገኝና በአከፋፋሉ እንዲደሰት የሚያደርግ ነበር።

በጭፈራው ከሚገኘው ገንዘብ ይበልጥ የምንደሰተው በጭፈራው፣ በበዓሉ በራሱ ነው። ተነሳሽነታችን ከፍ ያለ መሆኑ ከዝግጅቱ ጀምሮ የሚታይ ነው። ለጭፈራ የቆምንበት በር ላይ ከመድረሳችን በፊት የሚጨፈር ዜማ አለ። መግቢያ የሚሆን – አሲዮ ቤሌሜ – በሩ ላይ ሲደረስ – መጣና በዓመቱ – በመሃል ሙገሳው – የኔማ ጌታ – ቶሎ ካልሰጡን – ኧረ በቃ በቃ … በደንብ ተጠንቶበት የሚጨፈር ሲሆን፤ ከእያንዳንዱ ቤት የሚገኘውን ስጦታ ለማግኘት ጭፈራው በሙሉ ጉልበት ተጨፍሮ ባለቤቶቹ ካሉበት ወጥተው መጥተው፣ ጭፈራውን አድምጠው ምርቃታቸውን ተቀብለው እንዲሄዱ የሚያደርግ ጉልበት ነበረው። አለመሰልቸት፣ ስራን አክብሮ መያዝ፣ አሹፎ ሳይሆን ለፍቶ፣ ጥሮ ግሮ ማግኘትን፣ የቆሙለትን ዓላማ ከግብ ማድረስን፣ የተላመድነው በዚህን ወቅት ነው።

ጭፈራው ስንት ሰዓት እንደሚጀምር፣ ስንት ሰዓት ላይ እንደሚያበቃ ቀድሞ ነገር የተወሰነ ነው። በተባለው ሰዓት መገኘት። ለጭፈራው የሚያስፈልጉ እቃዎችን ይዞ መገኘት፤ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው። የስራ ዲሲፒሊን፣ ለስራ ሲሰማሩ አስፈላጊውን ቁሳቁስ አሟልቶ መገኘት፣ ያኔ የተቀዳ ነው።

በቡድኑ ስርዓት ያልተገዛ፣ በሰዓቱ የማይገኝ፣ ድምፁን ጎላ አድርጎ የማይጨፍር፣ የሚያጭበረብር… የሚቀጣበት የራሱ የፍርድ ስርዓትም ነበረው። ዝም ብሎ ከቡድኑ ማሰናበት፣ እስከጨፈረበት ሰዓት ድረስ ያለው ተሰልቶ ድርሻውን ወስዶ እንዲሰናበት ማድረግ፣ በሚቀጥለው ዓመት ከቡድኑ ጋር እንዳይጨፈር ማድረግ የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ናቸው።

እነዚህ ከ‹‹ስነ-ዜጋ›› ትምህትር ያላገኘናቸው (በእኛ ዘመን ይህ ትምህርት እንዳልነበረ ልብ ይሏል)፣ የ‹‹ሥነ-ምግባር መርሆዎች›› ናቸው ተብለው በየመሥሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ተለጥፈው ያላየናቸው ፤አድገን በግል ህይወታችንና በሥራው ዓለም ግብዓት የሆኑን እሴቶችን የሰበሰብነው እዚሀ ውስጥ ባልጠቀስኳቸው አበባዬሆሽ፣ አሸንዳዬ… በመሳሰሉት በየባህሉ ውሰጥ ከሚገኙ የልጅነት ጨዋታዎች ጭምር ነበር።

በአጠቃላይ ለምንሰራቸው ማናቸውም ስራዎች እቅድ ማውጣት፣ የስራ ክፍፍል ማድረግ፣ የስራ ዲሲፒሊን መኖር፣ ታማኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ፍትሃዊነት፣ አድልዎ አለማድረግ፣ ቅንነት ዓላማን ለማሳካት ቆርጦ መነሳት፣ አለመሰልቸት .ወ.ዘ.ተ… የመሳሰሉት እሴቶች በቀድሞው የቡሄ ጨፋሪዎች ዘንድ የነበሩና የወደፊት ህይወታችን ላይ በጎ ተፅእኖ ያሳደሩ ነበሩ።

ቅድም ወደ ቤት ስገባ ያየኋቸውም ሆኑ አሁን አሁን ሲጨፍሩ የማያቸው ልጆች እነዚህ ነገሮች እንደጎደሏቸው ልብ ብዬአለሁ። በቡሄ መነፅር የእነዚህን ልጆች የወደፊት ነገር ስመለከት ትውልዱ የሚያሳስብ ነው። አንዲህ ያሉ እሴቶች ልብ ሳንላቸው በህይወታችንና በእርስ በእርስ ግንኙነታችን ላይ ብሎም በሀገር ጉዳይ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ችላ ሊባሉ ባልተገባቸው ነበር። የ‹‹ስነ-ዜጋ›› ትምህርቶቻችንም ሲቀረጹ እነዚህን እሴቶች መሰረት አድርገው የተቀዱ ቢሆን ኖሮ ይህ የትምህርት ዘርፍ ባልከሸፈም ነበር።

እነዚህን የመሳሰሉ ያጣናቸውን ሀገር በቀል እሴቶቻችንን መልሰን ለትውልድ ግንባታ ማዋል ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን እያሳሰበኩ፣ በልጅነታችን ከተከሰቱ አጋጣሚዎች ሁለቱን አነሳለሁ።

አንድ አካባቢ ጨፍረን እየተመለሰን ነው። ጉልበተኞች መንገድ ላይ ያዙንና ማን ነው ገንዘብ ያዥ ተባለ። ሁላችንም ጭጭ። አንተ ነህ አይደለሁም! አንተ ነህ አይደለሁም! ሁሉም መልሱ አይደለሁም ሆነ።

እሺ ተራ በተራ ዝለሉ ተባልን። ዘለልን። ገንዘብ ያዣችን ሲዘል በሳንቲሞች ቅጭልቅልታ ታጅቦ ስለነበር ገንዘባችን ተወሰደ። በጣም አለቀሰን። በቀጣዩ ዓመት ገንዘብ ያዣችን ሆን ብሎ ሱሪው ላይ ባዘጋጀው ጥብጣብ ውስጥ ገንዘቡን ሊያስቀምጥ ዘዴ ዘይዶ መጣ።

በዚያን ዓመት በተከበረው የቡሄ በዓል ቡድናችን ውስጥ አንድ እንደልብ መራመድ የማይችል አካል ጉዳተኛ ጓደኛችን ተካቶበት ነበር። የስራ ድርሻውም ከመጨፈር በተጨማሪ በስጦታ የሚሰጡንን ሙልሙሎች መያዝ ነበር። ቦታው አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ሃብታሞች ሰፈር ነበር። በየቤቱ ያሉት ውሾች ጅብን ያስንቃሉ። አንድ በግምብ የታጠረ ቤት እየጨፈርን ነው። በሩ ተከፈተ። ዘበኛው ሃምሳ ሳንቲም በእጁ ይዟል። ገንዘብ ያዣችን ለመቀበል የሚያበቃ አፍታ አላገኘም። ውሻው አፈትልኮ መጣ። ሁላችንም ተበታተንን። ዘበኛው ሊያስቆመው ሞከረ። አልቻለም። አካል ጉዳተኛው ወንድማችን ወደ ኋላ ቀረ። ዘበኛው ከኋላ እየተከተለ ውሻውን ተመለስ! ይላል። ጓደኛችን እሮጦ ማምለጥ ስለማይችል ውሻው ቢያንስ ፍጥነቱን እንዲቀንስ ወይም ቆም እንዲል ማድረግ ነበረበት። እጁን ወደ ከረጢቱ በመስደድ አንድ ሙልሙል ለውሻው ጣለለት፣ እሱን እስኪበላ፣ አንከስ እያለ ጥቂት ተራመደ። ዞር ብሎ ሲመለከተ ውሻው ጨርሶ እንደገና እየተከተለው ነው አንዱን ሙልሙል እውጥቶ አርቆ ወረወረለት። ውሻው ወደ እዚያው ሮጠ። ዘበኛውም ደርሶ ውሻው ወደ ቤት እንዲገባ ሆነ። ምንም እንኳን በወቅቱ ጓደኛችንን ጥለን መሮጣችን ቢፀፅተንም፣ ለውሻው ቀለብ በሆኑት ሙልሙሎቻችን ሳንቆጭ፣ የጓደኛችንን ብልጠት እያደነቅን እስካሁን አለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top