ስርሆተ ገፅ

ጣፋጭ ጨዋታ ከሼፍ ዩሀንስ ጋር

ፅድት ያለና ጥንቁቅ እጅ፣ ነጭ ጋዋንና ኮፍያ፣ ንጹህ መክተፊያ ላይ ስል ቢላዋ፣ የሚያብረቀርቅ መጥበሻ ላይ የሚላወስ ዘይት፣ የሚያፏጭ ሹካ እና ማንኪያ ከአብረቅራቂ ስቶቭ ጋር የሚሞዳመድ ግራ እጅ ካያችሁ እርሱ ሼፍ ዮሐንስ ነው፡፡ አራቱንም የኢትዮጲያ አቅጣጫዎች ተጉዞአቸዋል። የሀገሪቷን ኩሽናዎች ከዳር ዳር ተዋውቋቸዋል፡፡ ከእናቶች ባህላዊ ምግብ አሠራር እየተማረ ዘመናይ ሊያደርጋቸው ጥሯል፡፡ የተረሱ፣ የባከኑ፣ ወደ አደባባይ እንዳይወጡ የተፈረደባቸውን ምግቦች ትንሳኤ አውጆላቸው ጥቅማቸውን ከEBS ቴሌቪዥን ፕሮግራሙ የተረዱ ሠዎች አጣጥመውታል፡፡ ከመጋረጃ ጀርባ ተደብቀው የነበሩ አብዛኛው የሀገሪቷ ሬስቶራንት የምግብ ዝርዝር ውስጥ ያልተፃፉ የምግብ አይነቶችን ለማያውቃቸው የማህበረሰብ ክፍል ነጋሪት እየጎሰመላቸው በሽሚያ እንዲመገቡአቸው አድርጓል፡፡ ከምስኪን የኢትዮጵያ እናቶች ጋር ኩሽናቸው ውስጥ አይኑ በጭስ እየተቃጠለ፣ የሚወቀጥ ካለ እየወቀጠ፣ ሲንበረከኩ እየተንበረከከና እሳቱን ሀይል ለመስጠት ኡፍ እያለ ለወጥነት እስኪበቁ አብሮአቸው ነበር፡፡

ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ካፌ ተቃጠርን፤ ቀድሜ ደርስኩ፡፡ ወጪ ገቢውን ለማየት በማይመች ቦታ ተቀመጥኩ፡፡ ወደሚመቸኝ ቀይሬ ተቀመጥኩ፡፡ ጥቂት ደቂቃ እንደሚያረፍድ ነግሮኝ ስለነበር ጥበቃዬ ትዕግስት ተጨመረበት። ያዘዝኩትን ቡና ለማጣጣም ዕድል ስለተሰጠኝ አብሬ ማስታወሻዬ ላይ የከተብኳቸውን ስርዝ ድልዝ የሆኑ ጥያቄዎች አዋሀድኳቸው፡፡ ቀላል የአኗኗር ዘዬ ያለው ሠው እንደነበር አውቃለሁ። ሳላስበው ተገለጠ፡፡ ኮረናዊ ሠላምታ ተለዋወጥን፡፡ ደመና በተጫነው ሠማይ ውብ ጨዋታ በምግብ መፅሀፍ ፀሀፊነት በአንድ አለም አቀፍ ሸላሚ ድርጅት መገኛው አሜሪካ የሆነ ስላሸነፈው ሽልማት አወራን፡፡ ከኢትዮጵያ እናቶች ጓዳ ለተቀዳ ጥበብ የተሰጠ እውቅና አድርጎ ስለቆጠረው ፈገግ አልኩ፡፡ የመስማት አፒታይቴ ተከፈተ፡፡

ወደ ፈረንሣይ ፓሪስ ያቀናው ምግብ ላይ እንዲህ እንደዛሬው እስለጥንበታለሁ ብሎ አልነበረም፤ በSt- Etienne ከተማ ስዕልን ተማረ፡፡ ወደ ነፍሱ ጥሪ ለመቅረብ ግን ስዕልን ተመርቆ አዲስ አበባ ላይ ጥቂት ቆይቶ ወደ ፈረንሣይ ድጋሚ ሌላ ዲግሪ በምግብ ለመማር ተመለሠ፡፡ ስልጣናው ቆሞ እንዲሄድ ካሊፎርንያ የሚገኘው ባለ አምስት ኮከብና አምስት ዳይመንድ ሴንትሪጅየስ በሚባል ሆቴል ከፍተኛ ልምምድ አደረግኩ።

ሴንትሪጅየስ ሆቴል

እጅግ በጣም ትልቅ ሆቴል ሲሆን የሀብትና የዝና ቁመት የሚለካባቸው የአለም ታላላቅ ሠዎች የሚስተናገዱበት ሲሆን እንግዳው ከመምጣቱ በፊት እዛ የምንሰራ ለሁላችንም ደንበኛችን የሚወድና የሚጠላውን ነገር በዝርዝር ይነገረናል። ያንን መተግበር ግድ ነው፡፡ መንገድ ላይ ድንገት ከደንበኞች ጋር ከተገናኘህ ግድግዳ የመደገፍና አዎንታዊ መልእክት እንደ እንዴት ነህ? መልካም ቀን ይሁንልህ! አይነት ትላለህ፣ መልስ አትጠብቅም፡፡ እዚ ሆቴል ለእግር ኳስ ተጫዋቹ ዴቪድ ቤካምና ለፊልም ተዋናይዋ ለጄሲካ አልባህ ምግብ ሲዘጋጅ ካዘጋጁት አንዱ ነበርኩ፡፡ የካታሩ ልዑልና በሬስሊንግ ድብድብ በወቅቱ ታዋቂ የነበረው ጎልድ በርግ ደንበኞች ነበሩ፡፡ ለእኔ ግን ከሁሉም የረቀቀብኝ በቴሌቪዥን የማያቸው የምግብ ዝግጅት ነበር። ከተመሠረተች ጥቂት አመት የሆናት አሜሪካ እንዴት በምግብ ዝርዝርና ሂደት እንዴት በለጠችን? ከ3000 አመት በላይ የሆናት ሀገሬ ያን ሁሉ ባህል፣ ልማድና ብሄረሠቦች እያለን እንዴት ተበለጥን ብዬ ተቆጨሁ፡፡ ሀገሬ ስመለስ መጀመሪያ የማደርገው ቴሌቪዥን ፕሮግራም ይኖረኛል ብዬ ወጠንኩ፡፡ እንደመጣሁ በኢቢኤስ ተገበርኩት፡፡

ሳማን ወጥ አድርጎ፣ ህልበትን ማዮኒዝ እያደረገ አስደሰተን፡፡ አገር በቀልን ምግብ ባህሉን ሙሉ ለሙሉ ሳይለቅ ዘመናዊው ምግብና አሠራር በመለወስ አዲስ ቀለም መስጠት፡፡ ዝግጅቱ ተወዳጅ ሆኖ ለምን አልቀጠለም? ጥያቄዬ ነበር፡፡ “የቴቪ ፕሮግራም ያለፋል፣ ግን ለእንዲህ አይነት ዝግጅት ስፖንሰር አልነበረም፤ እርግጥ ተወዳጅ ነበር፡፡” ዝግጅቱ ላይ ሲሰራው የነበረውን ወደ መፅሀፍ ቀይሮ አለም አቀፋዊ ዝናን አተረፈለት፡፡

የጄምስ በርድ ሽልማት

ሼፍ ዮሐንስ

Ethiopia; Recipes and traditions from the Horn of Africa የሚል80 ባህላዊና 20 ራሴ በመቀላቀል የፈጠረኳቸው የምግብ አይነቶች በእንግሊዝኛ የፃፍኩሱት መፅሀሬ ለእኔም ሆነ ለሃገሬ ዝናን አተረፈልን፡፡ በዚህ አመት The guild of food writer በተባለ እንግሊዝ ሀገር በሚገኝ የሽልማት ድርጅት የመጀመሪያው አፍሪካዊ እጩ ሆኜ ቀረብኩ፣ The art of eating ላይም እጬ ሆንኩ፡፡ 3ኛው ላይ ግን አሸነፍኩኝ፡፡ ጄምስ በርድ አዋርድ በሚባለው የአሜሪካን ድርጅት አንደኛ ተባልኩ፡፡ The art of eating ምግባችን ሳይሆን በአበላላችን አስመርጦኛል፡፡ ” ብሎኝ ሁለታችንም ዝም አልን፡፡ እንግዳዬ ስለበረደው ጃኬት ሊያመጣ ወደ መኪናው ሄደ፡፡ ‘አጃኢብ ነው’ አልኩኝ፡፡

አጃኢቡ ጨዋታ ከአነቃቂ ቁም ነገር ወደ ጨዋታ ተሸጋገረ፡፡

* የአለም ውዱ ምግብ

ኮቢ ቢፍ የጃፓን ምግብ ሲሆን ዋጋው 1 ኪሎ 150ዶላር ነው፡፡

* ጥንታዊ የኢትዮጵያ ምግብ

እንፍሌ ይባላል፤ ለሰርግ የተዘለዘለ የበግ እግር ከስሩ በስልስ እንፋሎት ይጠበሳል፡፡

* የምትጠላው ባህሪ

ሠውን የሚፈርጅ ሠው

* ብቻህን ስትሆን የምታደምጠው ዘፋኝ

ጥላሁን ገሠሠ፣ መሀሙድ አህመድ፣ መስፍን አበበና ኬኔዲ መንገሻ

* በትርፍ ሠዐትህ የምታዘወትረው

ቴኒስ፣ ስዕል መሣል፣የአየር ላይ ዝላይና ሳልሳ መደነስ

* የምትወደው እና የምትጠላው ምግብ

እንደ ሙዴ

* ከእንቅልፍ ስትነሣ የምታደርገው

ስፖርት ከዛ ቁርስና ቡና

* ፈረንሣይ ስትሄድ የገረመህ

በየሄድኩባቸው ከተሞች ጥቁር እኔ ብቻ መሆኔ በጣም ያስደንቀኝ ነበር

* ፀሀይ ስትጠልቅ ማየት የምትሻው

ባህር ዳርቻ ካሊፎርንያ ሀቲንግተን ባህር ዳርቻ

ጥያቄዬ ተገባደደ፡፡ ስሰናበተው ግን ቀለል ባለ ስብዕና የሚታወቀው ዮሀንስ ገ/የሱስ በቀጣይ ጀምሮ ስላቋረጠውና የእናቶቻችንን ጓዳ ስላስተዋወቀው፣ ህመማቸውን ስላጋራውና ሀገር በቀል እውቀትን ስላስተማረን የቴቪ ዝግጅት እንዲጀምረው በመንገር ነው፡፡ ሻሎም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top