ጣዕሞት

“ዳኛው ማነው?” ገበያ ላይ ዋለ

በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓ ምድር ስመ ገናና ነበር፤ ደሴ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት ተምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሏል፡፡

አንደበት ርቱዕ፣ ደፋርና ላመነበት ነገር ወደኋላ ማለት የማይወድ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ መሬት ላራሹ በሚል መፈክር ሠላማዊ ሠልፍ አስተባብረሀል በሚል ከዩኒቨርሲቲ ተባሮ ወደ ኬንያ በመሄድ የBBC ሬድዮ ሞኒተር በመሆን አገልግሏል። በ1959 ዓ.ም. ወደ ሀገሩ በመመለስ ለሄራልድ ጋዜጣ በሪፖርተርነት እና በበተርጓሚነት ሠርቷል። በ1961 ዓ.ም. ባህርዳር ከ6 ጓደኞቹ ጋር B3 አውሮፕላንን ጠልፈው ወደ ሱዳን ወስደዋል፡፡ ኢህአፓን ከጥንስሱ እስከ ምስረታው በመሪነት አገልግሎአል ብርሀነ መስቀል ረዳ ወልደ ሩፋኤል። ስለዚህ የዚያ ዘመን ትንታግ ፖለቲለኛ ብዙ ተብሏል፣ ተፅፏል፣ ተነግሯል፡ ፡ ሆኖም ስለሱ ከተጻፉት የልባችን አልደረሠም ለሚሉ ወገኖች አዲስ የምስራች የመጣ መስሏል፡፡ ስለ እርሱ በባለቤቱና የሦስት ልጆቹ እናት የተፃፈ በዚህ ሣምንት የወጣ እጅግ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ጀባ ተብለናል፡፡

ልክ የዛሬ 41 ዓመት፣ የኢሕአፓ መሥራችና መሪ የነበረው ብርሃነመስቀል ረዳ፣ በደርግ ተይዞ ያለፍርድ ተገድሏል፡፡ በደርግ እጅ ተይዞ ማዕከላዊ ቢታሠርም፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ ወንጀሉ ሳይገለጥ በግፍ መገደሉን ስታወሳ፣ የተራኪያችን ስቃይና ኀዘን ጠልቆ ይሰማናል፡፡ ዳኛው ማነው? የሚለውን ጭብጥ አጉልታ ታሳየናለች፤ የትግሉ መሪ የነበረው ባለቤቷን፣ ብርሃነመስቀል ረዳን፣ ለመዘከር ዋነኛ ዓላማዋ አድርጋ፣ በዓይን ያየችውን፣ በተግባር የተሳተፈችበትን፣ መከራና ኀዘን የተቀበለችበትን ትውስታ፣ በውብ ቋንቋ ከሽና ታደለች ኃ/ሚካኤል እነሆ ብላናለች፡፡ ታሪክን መጻፍ ታሪክን ከመሥራት ጋር ሲዋሃድ ድንቅ ስለመሆኑ ምስክር የሚሆን መጽሐፍ! ዳኛው ማነው?

ስለ ኢሕአፓና ትግሉ ብዙዎች ጽፈዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን “በኢሕአፓ ውስጥ ያገነገነው ቅራኔ፣ አማራጭ የትጥቅ ትግልን እንዴት ወለደ? በዚያስ ምን ተከናወነ? ሰውዬው ማነው? ለመሆኑ ከትግል ሌላ ነገር ያውቅ ነበርን? እንደ ማንኛውም ሰው ወግ ማውጋት፣ ማፍቀር ይችል ነበርን?” የሚሉትን እስካሁን ያልታወቁ እውነታዎች ደግሞ ፍቅረኛው፣ ባለቤቱና የትግል አጋሩ በነበረችው ታደለች ኃይለ ሚካኤል ተጽፎ እነሆ ለንባብ የቀረበው መጽሐፍ በአጥጋቢ ሁኔታ ይመልስልናል፡፡

ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ በቆየችበት ወህኒ ቤት ያሳለፈችውን ሕይወት ስታስቃኘን፣ ፅናትና ተስፋን ሥጋ ለብሶ እናየዋለን፡ ፡ ለዚህ ፅናትና ተስፋ የጀርባ አጥንት የሆኗትን እናቷን ከማድነቅ አልፈን የጀግና ክብር ለማቀዳጀት ይዳዳናል፡፡ የታናሽ እህቷ አለኝታነት የእህት ፍቅር ሁነኛ ተምሳሌት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከእንባችን ጋ እየታገልን የምናነባቸው ታሪኮችና ስለአገራችን ፖለቲካ የምናብሰለስልባቸው አሳቦች ታጭቀውበታል፡ ፡ ዳኛው ማነው?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top