ታዛ ስፖርት

የተሸዋወዱ ቦክሰኞች

መጋቢት 1986

ደቡብ አፍሪካ

ከቀኑ 4 ሰዓት

ጆሀንስበርግ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በር ላይ ዘበኞችና ሰባት ጎረምሶች ውዝግብ ይዘዋል፡፡ “ወደ ውስጥ ዘልቀን ካልገባን ሞተን እንገኛለን!” ብለው ያስቸገሩት ሐበሾች ጥያቄያቸው አንድና አንድ ነው፡፡ “አምባሳደሩን ማነጋገር እንፈልጋለን” የሚል ነበር፡፡

ጥበቃዎቹም የዋናውን በር አልፈው የገቡትን የተወሰኑትን ገፍትረው ሊያስወጧቸው ቢፈልጉም “ና ሞክረኛ!!” ዓይነት እልህ ተጋብተዋል፡፡ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ቦክስ ቡድን ተጫዋቾች ሲሆኑ፤ ዘበኞቹ ሲጠጓቸው ቦክሰኝነታቸውን ለማሳየት ፈለጉ፡፡ ጥያቄያቸው ተፈፃሚ የሚሆንበት ማንኛውንም ነገር ሁሉ ይጠቀማሉ፡፡ ቦክሰኞቹ ስለ ደቡብ አፍሪካ የሰሙት ነገር “ከህግ በላይ ጉልበት ዋጋ አለው” የሚል በመሆኑ ዘበኞቹን ለመደብደብ ተዘጋጅተዋል፡፡

ቦክሰኛ መሆናቸውንም ነግረዋቸዋል። ቦክሰኞቹ እነዚህን ግርግር ፈጣሪ ቦክሰኞች ለመግባት ከሚታገሉበት በር ላይ አስቀቆሟቸውና “ምንድነው የምትፈልጉት?” አሏቸው፡፡

“አምባሳደሩን!”

“አምባሳደሩ የለም!”

“ውስጥ እንዳለ ተነግሮናል!”

“ቢኖርም አታገኙትም!”

“ለምን?”

“በቀጠሮ ነው… ሌላ ቀን ኑ”

“እኛ ዛሬ ነው የምንፈልገው”

“አይቻልም”

“ይቻላል”

“አሁን ከዚህ ጥፉ”

“አንሄድም”

“እና”

“አምባሳደሩ ጋር እንግባ”

በሩ ላይ ቆመው ጥሰው ለመግባት ፈለጉ፡፡ ቦክሰኞቹ በጣም ስላስቸገሩ ዘበኞቹ ለበላይ አለቆቻቸው አስታወቁ፡፡ የጥበቃው ኃላፊም ለአለቆቻቸው አስታወቁ፡፡ ጉዳዩንም ተነጋግረው ወደ ቦክሰኞቹ መጡ፡፡ የጥበቃው ኃላፊ ቦክሰኞቹን ጠራቸውና “አምባሳደሩ ሊያነጋግራችሁ ፈቃደኛ ሆኗል” አሏቸው፡፡

“በጣም ደስ ይላል… አስገቡና”

“ሁላችሁም መግባት አትችሉም”

“እና”

“ሁለት ሰው ብቻ ነው የተፈቀደለት”

“ሌሎቻችንስ?”

“እነሱ ጉዳዩን ያስጨርሱላችኋል”

ሰባቱ ቦክሰኞች ደስ አላቸው፡፡ አምስቱ ውጭ ይቆዩና ሁለቱ አምባሳደሩን ያነጋግራሉ፡፡ አነጋግረውም ጥገኝነት ይጠይቃሉ፡፡ እናም ጉዳዩን አስጨርሰው ይመጣሉ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ደግሞ ጥገኝነት ለሚጠይቁ ስፖርተኞች ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ተነግሯቸዋል፡፡

ቦክሰኞቹ ይሄን አሰቡና ተወክለው የሚሄዱትን ሁለቱን ለመምረጥ ተዘጋጁ፡፡ ማን ይግባ? በሚለው ጉዳይ ተወያዩ፡፡ ከመሃላቸው በተሰባበረ ሁኔታ እንግሊዝኛ የሚችሉትን ፈለጉ፡፡ በዚህ መንገድ ሁለት ሰው መረጡ፡፡ ተወካዮቹ መግባት እስኪፈቀድላቸው ድረስ ሁለቱ አምባሳደሩን ሲያገኙት ምን ዓይነት ጉዳይ ማንሳት እንዳለባቸው ሀሳብ መቀባበል ጀመሩ፡፡

ጥቂት ቆይቶ ግን አምስቱ በሁለቱ ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው፡፡ ሁለቱ የራሳቸውን ጉዳይ አስጨርሰው እኛን ቢዘጉንስ? ብለው ተወሰወሱ፡፡ እንደገና ሌላ ምርጫ ለማድረግ ፈለጉ፡፡ ወዲያውኑ በምርጫ መሆኑ ቀርቶ “እኔ ልግባ… እኔ ልወከል” በሚል እሽቅድድምና ውዝግብ ጀመሩ፡፡ ተወካዮቹን በድምፅ ብልጫ እንደገና መምረጥ አለብን አሉ፡፡ አምስቱ በድምፅ ከሁለቱ ይሻላሉ፡፡ ግን ሌላ ሁለት ሰው ቢወከል ቀሪዎቹ አምስቱ እንደገና እኛ መግባት አለብን በሚል ማመፃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገሩ እልባት ማግኘት አልቻለም፡፡ ጭቅጭቁም እየበረታ ሄደ፡፡ ቦክሰኞቹ እየተከራከሩ ባለበት ጊዜ የኤምባሲው ሰራተኞች ሁለቱን ተወካዮች ቶሎ እንዲያሳውቋቸው ስላሳሰቧቸው መጀመርያ የተመረጡትን ሁለቱ ልጆች እንዲገቡ ተስማሙ፡፡

የሚገቡት ሁለቱ ኤምባሲ ውስጥ አንዳንድ ጉዳይ ለማስጨረስ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋቸው አምስቱም ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ዶላር አራግፈው ሰጡዋቸው፡፡ በደምብ ተደራድረው ጉዳያቸውን እንዲያስጨርሱ አደራ አሏቸው፡፡ በመጨረሻም እንዳይከዷቸው መኃላ እንዲፈፅሙ አደረጓቸው፡፡ ወደ ውስጥ የሚገቡት ሁለቱ ቦክሰኞች አበባው ከበደና ዮሃንስ ሽፈራው (ጆኒ) ነበሩ፡፡

ለመሆኑ እነዚህ ቦክሰኞች ኮብልለው አሜሪካ ኤምባሲ እንዴት ደረሱ? ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድን ሞሪሺየስ ላይ ለሚደረገው የአፍሪካ ቦክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ተጓዙ፡፡ በጊዜው በ1986 ዓ.ም ነው፡፡ አውሮፕላኑ ደቡብ አፍሪካ ትራንዚት ሲያደርግ ተጓዦች ከኤርፖርት ወጥተው እንደገና ተፈትሸው ይግቡ ስለተባለ ሰባቱ አጋጣሚውን ተጠቅመው እግራቸው ወዳደረሳቸው ቅርብ ከተማ በሩጫ አመለጡ፡፡

የሆነ ስፍራ ደረሱ፡፡ ከተማ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ተደሰቱ፡፡ ስፍራው ፔምቤሳ ይባላል፡፡ አላወቁም እንጂ የግድያ ጣቢያ ነበር የደረሱት፡፡ ይሄ ቦታ በጣም አደገኛና የጥቁሮች ከተማ ነው፡፡ በዝርፊያና በአፈና የሚነገርለት ነው፡፡ ከዚያ ከተማ በሰላም መውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ እዚያ ከተማ የገባ እንግዳ ልብሱ ሳይቀር ተገፎ ነው የሚወጣው፡፡ ቦክሰኞቹ በቡጢ ቢተማመኑም ጥቁሮቹ በሴንጢ መቆራረጥ ይችላሉ፡፡

ሰባቱ ልጆች ከኤርፖርት እንደሮጡ ፔምቤሳ ደረሱና ለፖሊስ እጃቸውን ሰጡ፡፡ ፖሊሶቹም ወደ እስር ቤት አስገቧቸውና ሲጫወቱባቸው አደሩ፡፡ ፖሊሶቹ እንግሊዝኛ መናገር አይችሉም፡፡ ቦክሰኞቹ ደግሞ የአካባቢውን ቋንቋ አያውቁም፡፡ በቋንቋ ስላልተግባቡ ቁጭ በሉ ሲሏቸው ይቆማሉ፡፡ ሂዱ ሲሏቸው ይመጣሉ፡፡ በዚህ የተነሳ “እኛ የምንላችሁ አትሰሙም” በሚል ሲያንገላቷቸው አደሩ፡፡ በእዚያ ላይ ይስቁባቸዋል፡፡

በነጋታው እንግሊዝኛ የሚችል አስተርጓሚ መጣና ፖሊስና ቦክሰኞቹ ውይይት ጀመሩ፡፡ ፖሊሶቹ “ከየት ነው የመጣችሁት?” አሏቸው፡፡

“ከእንግሊዝ ነው”

“ለምን መጣችሁ?”

“ጥቁር ስለሆንን”

“እና”

“እዚያ አካባቢ በጥቁርነታችን ይሰድቡናል፡፡” ቦክሰኞቹ ከእንግሊዝ ነው የመጣነው ያሉት በእዚያን ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ሲያዙ ወደ መጡበት አገር ስለሚመለሱ ከእንግሊዝ ነው የመጣነው ካሉ ወደ እንግሊዝ ይመልሷቸዋል፡፡ እነሱ መሄድ የሚፈልጉት ወደ እንግሊዝ በመሆኑ በዘዴ የእንግሊዝን ጉዞ ያሳካሉ፡፡ ፖሊሶቹ እንደገና መጠየቅ ጀመሩ፡፡ “የት ነው የተወለዳችሁት?” አሏቸው፡፡

“ለንደን”

“ለንደን የት?”

“መሀል ለንደን”

“ስም የለውም?”

“ትልቁ ወንዝ አጠገብ”

በምልልሱ ወቅት አስተርጓሚያቸው ይስቃል፡፡ መሳቅ ብቻ ሳይሆን ይንከተከታል፡፡ ቦክሰኞቹ እንግሊዝኛቸው የተሰባበረ ነው፡፡ ተወልደን አደግን የሚሉት ደግሞ እንግሊዝ ነው ተወልደው ያደጉበትን አገር ቋንቋ ያለመቻላቸው አስገርሟቸዋል፡፡ ቦክሰኞቹ አስተርጓሚውን “ምን ያስቅሃል?” አሉት፡፡ ጉዳዩን ለፖሊሶች ነግሮ ፖሊሶቹም ሲስቁባቸው ቆዩ፡፡ እንግሊዝኛ አለመቻላቸው እያጭበረበሩ መሆኑ ገብቷቸዋል፡፡ “እናንተ ከለንደን ሳይሆን ወይ ከሱማሌ ወይ ከአጎራባች ከተማ ነው የመጣችሁት” አሏቸው፡፡ በመጨረሻም ፖሊሶቹ ሊለቅቋቸው ተስማሙ፡፡ ሲለቅቋቸው ግን በአስቸኳይ ከዚህ ከተማ መውጣት እንዳለባቸው አስጠነቀቋቸው፡፡ የከተማውንም አደገኛነት ነገሯቸው፡፡

በነጋታው ከጣቢያው ሲወጡ እየገላመጡ ወደ ጆሃንስበርግ ሄደው አሜሪካ ኤንባሲ ጥገኝነት ለመጠየቅ በር ላይ ከዘበኞች ጋር ግብግብ ጀመሩ፡፡ ሁለት ተወካይ መረጡና አምባሳደሩን ለማነጋገር ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ቡድን መሪውና አሰልጣኞቹ የሰባቱን ቦክሰኞች ስም ለፖሊስ ሰጥተው በዝርፊያና በአደገኛ ወንጀለኛነት እንደሚፈለጉ አሳውቀው በከተማው ውስጥ አሰሳ እየተደረገ ነው፡፡ ፎቷቸውም በየቦታው ተበትኗል፡፡

ሁለቱ ቦክሰኞች ወደ ኤምባሲው ከገቡ በኋላ ኃላፊው ጋር ቀረቡ፡፡ ቢሮው ሰባተኛው ፎቅ ላይ ነው፡፡ እንደገቡ ጥያቄ ተጀመረ፡፡ “ከየት ነው የመጣችሁት?” አሏቸው፡፡

“ከኢትዮጵያ”

“ምንድነው የምትፈልጉት?”

“ጥገኝነት እንዲሰጠን ነው” ችግር ላይ ነን ብለው ስለነገሩት ኃላፊው በነገሩ ተስማማ፡፡ ሰውዬው ትልቅ ተስፋ ሰጣቸው፡፡ ሀሳባቸውን ከተቀበለ በኋላ “ነገ ትመጣላችሁ” አላቸው፡፡ “

አልቆልናል?.. ስንት ሰዓት እንምጣ?”

“በዚህ ሰዓት መምጣት ትችላላችሁ”

ኃላፊው ወደ ውስጥ ገባና የመጣለትን ፋክስ በደንብ ተመለከተ፡፡ እርሱ ያሰበው ቦክሰኞቹ ከግቢው ከወጡ በኋላ በእዚያው ሊሸኛቸው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እዚህ ግቢ ድርሽ አይሉም፡፡ ኃላፊው ድብቁ ክፍል ውስጥ ስክሪን ላይ የመጣውን ምስል ተመለከተ፡፡ ወደ ውስጥ ገባና ስልክ አንስቶ መነጋገር ጀመረ፡፡ ለእነዚህ ሁለት ልጆች ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሰበ፡፡ ስልኩን ከጨረሰ በኋላ ተመልሶ ወደ ዋናው ክፍል ገባ፡፡ ሁለቱን ልጆች በትኩረት ማናገር ጀመረ፡፡ “ማደሪያ አላችሁ እንዴ?” አላቸው፡፡

“የለንም”

“ታዲያ ዛሬ አሜሪካ እንድትሄዱ ለምን አልጨርስላችሁም?”

“ተገኝቶ ነው”

“እዚሁ ቁጭ በሉ”

“እሺ” ሁለቱ ቦክሰኞች ባገኙት ዕድል ተደስተው እዚያ ያሉትን ሰዎች ሊሰሙ ምንም አልቀራቸውም፡፡ ኃላፊው ወጣ ገባ አለና ወደ ልጆቹ መጥቶ እንዲህ አላቸው፡፡

“የኤምባሲ ሰራተኞች ይመጡና ትኬት ቆርጠውላችሁ ማታውኑ በሚሄደው አውሮፕላን ወደ አሜሪካ ትበራላችሁ” አላቸው፡፡ ቦክሰኞቹ የሰሙትን ማመን አቃታቸው፡፡ በጣም ተደሰቱ፡፡ ፊታቸው ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆነ፡፡ “አገር ማለት አሜሪካ ነው” ብለው አሜሪካንና አምባሳደሩን ሰላሳ ጊዜ መረቁ፡፡ ውጪ ያሉት አምስቱ ቦክሰኞች ጓደኞቻቸው ይዘው የሚሄዱትን መልስ እየጠበቁ ነው፡፡ ትኬት የሚቆረጠው ለሰባቱም እንደሆነ ገምተዋል፡፡

ሁለቱ ቦክሰኞች አሜሪካ ሲደርሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መነጋገር ጀመሩ፡፡ አንደኛው “አንተ የት ነው የምትሄደው?” አለው፡፡

“አትላንታ”

“ዋሽንግተን”

“ለምን አብረን አንሆንም?”

“እኔ እዚያ የማውቀው ሰው አለ”

“ጓደኛህ ነው?”

“ዘመዴ ነው”

“እቅድህ ምንድነው?”

“እንደሄድኩ ትምህርት ቤት ነው የምገባው”

ሁለቱም ቦክሰኞች ሶፋው ላይ ቁጭ ብለው መወጠን ጀመሩ፡፡ አሜሪካ ከደረሱ በኋላ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ክለብ ገብተው ቦክስ እንደሚጫወቱ አሰቡ፡፡ ሰርተው ከብረው ዶላር ጭነው ከጊዜ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ፡፡ ከሰፈር ጓደኞቻቸውና ከዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ስለማያወሩት ነገር እያሰቡ ነው፡፡ አሜሪካ ሲሄዱ ማንን ማግኘት እንዳለባቸው እያሰላሰሉ ነው፡፡ ስለ ተስፋይቱ ሀገር እያሰቡ በሩ ተንኳኳ፡፡ በተከፈተው በር ሰዎች ገቡ፡፡ ኃላፊው ወደ ቦክሰኞች ዞረና “ወደ አሜሪካ የሚወስዷችሁ እነሱ ናቸው” በማለት ወደሚሄዱበት ሀገር ሲደርሱ መማርና እራሳቸውን መለወጥ እንዳለባቸው ነገሯቸው፡፡ በርትተው መስራት እንደሚገባቸው በደንብ አድርገው አስረዷቸው፡፡

ቦክሰኞችም ኃላፊውን አመስግነው በሁለት እጃቸው ጨብጠው “ውለታህን ለመክፈል ያብቃን” በማለት ሰራተኞቹን ሁሉ እጅ ነስተው “አሜሪካን ለዘላለም ትኑር!!!!” በሚል ጠለቅ ያለ ልባዊ ምስጋና አደረሱ፡፡ አቤት ዕድል!!!!!!

ከሚሸኟቸው ሰዎች ጋር ተያይዘው ወደ ኤርፖርት ለመሄድ ከግቢው ወጡ፡፡ ሰዎቹ ከግቢው ከመልቀቃቸው በፊት ሳምሶናይቱን ከፍተው “ትኬትና ዶክመንታቸው ይሄውና፡፡ ኤርፖርት እናድርሳችሁ ወይስ ትኬቱን ሰጥተናችሁ እናንተ ትሄዳላችሁ?” አሏቸው፡፡

“እናንተ ብትሸኙን አይሻልም?”

“እንደእሱ ጥሩ ነው”

“ምናልክ?”

“የአምባሳደሩ አደራ ስላለብን እኛ ኤርፖርት እናድርሳችሁ”

ሁለቱም ተያይዘው ከግቢው ወጡ፡፡ ሁለቱ ቦክሰኞች የዛሬን ዕለት አሰቧት፡፡ ዕድለኛ ቀን ናት፡፡ መቼም ቢሆን አይረሷትም፡፡ ሌሎች ሰዎች ተጉላልተው ነው ጉዳያቸውን የሚያስጨርሱት፡፡ አንዳንዴም አይሳካም፡፡ የእነሱ ግን በ30 ደቂቃ አልቆላቸው እነሆ ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ነው፡፡ አይ ዕድል!!! ደግሞም ሸኚ ተመድቦላቸዋል፡፡ ምርቃቱን ደግመው አዥጎደጎዱ፡፡ አሜሪካ ያደገችው በስደተኞች ምርቃት እንደሆነ አሰቡ፡፡ ሸኚዎቹን በስም ለመተዋወቅ ፈለጉ፡፡ እነሱም ባለውለተኞቻቸው ናቸው፡፡ አንድ ቀን ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ደቡብ አፍሪካ ትራንዚት ማድረጋቸው ስለማይቀር ከተገናኙ ሊገባበዙና ስጦታም ይዘውላቸው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ስማቸውን መያዝ አለባቸው፡፡

ከግቢው እንደወጡ መኪናው ጋር ደረሱ፡፡ ቦክሰኞቹ ለሸኚዎቹ “ስማችሁን እኮ አልነገራችሁንም” አሏቸው፡፡

“የእኛን?”

“አዎን”

“ምን ችግር አለው?”

“ንገሩና”

“ወረቀትና እስክርቢቶ ይዛችኋል?”

“የለንም… በቃላችን እንይዘዋለን”

“በቃልማ ይረሳል”

“ኧረ እኛ አንረሳውም” ወደ መኪናው ተጠጉ፡፡ ወዲያውኑ በፍጥነት ሸኚዎቹ ከቦክሰኞቹ ጀርባ ዞረው እጃቸውን ጠምዝዘው ካቴና አስገቡላቸው፡፡ ቦክሰኞቹ ተደናግጠው “ምንድነው ነገሩ?” አሉ፡፡

“ስማችንን አይደል የጠየቃችሁን?”

“ምን አልክ?”

“ፖሊስ እከሌ እንባላለን”

“ሸኚ አይደላችሁም እንዴ?”

“የት ነው የምትሸኙት?”

“ወደ አሜሪካ”

“እስር ቤት ትገባላችሁ”

“አንፈልግም”

“ታድያ የት ፈለጋችሁ?”

“ዋሽንግተን”

“ዘራፊ እና ወሮ በላ ዋሽንግተን አይገባም”

ቦክሰኞቹ ደነገጡ፡፡ ኃላፊውና ሰራተኞቹን አሜሪካንን ጭምር መራገም ያዙ፡፡ ኃላፊው መጀመርያ “ነገ ኑ!” ያላቸው ከግቢው ሊባርራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ስክሪኑ ላይ በፖሊስ በጥብቅ የሚፈለጉ ወንጀለኞች መሆናቸውን ምስላቸውን ሲያይ “ተፈላጊዎቹ ወንጀለኞች እኔ ጋር ናቸው” ብሎ ለፖሊስ ስልክ ደወለ፡፡

ሰዎቹ የፖሊስ ልብስ ለብሰው ከመጡ ቦክሰኞቹ ከኤምባሲው አንወጣም ብለው ያስቸግራሉ፡፡ ፖሊሶቹ የሲቪል ልብስ ለብሰው በሱፋቸው ላይ ከረባታቸውን ግጥም አድርገው መነጽራቸውን ገድግደው ሽክ ብለው ስለመጡ ሸኚ ነው የመሰሉት፡፡ ሳምሶናይትም ስለያዙ አመኗቸው፡፡

ሳምሶናይት ውስጥ የነበረውን ትኬትና ከኤምባሲ የተጻፈላቸውን ደብዳቤ ነገር ዐይተው ስለ ጉዟቸው ብቻ ነበር ያሰቡት፡፡ ፖሊስ ተረከባቸውና ይዟቸው ሄደ፡፡ በዚሁ ሰዓት ደግሞ አምስቱ ቦክሰኞች ጓደኞቻቸውን መጠበቅ ይዘዋል፡፡ እስከ ማታ ቆዩ፡፡ በሌላ በኩል መውጫ እንዳለ አረጋገጡ፡፡ ሁለቱ እንደሸወዷቸው ገመቱና በገንዘባቸው መበላትም አዝነው እየረገሟቸው አከባቢውን ለቅቀው ሄዱ፡፡ ሁለቱንም ቦክሰኞች ፖሊስ ወስዶ ካቆያቸው በኋላ ለቡድን መሪው ሰጣቸው፡፡ ቡድን መሪው ሁለቱን ይዞ ወደ ውድድር ሜዳ ሄደ፡፡ በመጨረሻ ተመልሶ ወደ ሆቴሉ መጣና “የውድድር ሰዓታችሁ አልፏል” ፍቃዱ ተጫውቶ አሸነፈ፡፡ እናንተም ብትወዳደሩ ጥሩ ውጤት ታመጡ ነበር፡፡ በመንግሥትና በህዝብ ገንዘብ እንደቀለዳችሁ አትቀሩም፤ አዲስ አበባ ስትደርሱ ዋጋችሁን ታገኛላችሁ፡፡ አሁን በዙምባብዌ አድርጋችሁ ወደ ሀገራችሁ ትመለሳላችሁ” አላቸው፡፡ ቦክሰኞቹ ግራ ተጋቡ፡፡ ከዚያ በኋላ የተፈጠረውን ነገር አበባው እንዲህ ያወጋል “ወደ አዲስ አበባ ፓስፖርትና ትኬታችን ዙምባቡዌ እንደደረስን ለደህንነቶች ይሰጣል፡፡ ሐራሬ እንደደረስን አጥር ዘለን የምናመልጥ እየመሰላቸው ይከታተሉናል፡፡

አራት ቀን ሙሉ ኤርፖርት ግቢ ውስጥ ደረቅ ወንበር ላይ እየተኛን ተንከራተትን፡፡ አንድ ቀን ሽንት ቤት ስንገባ አንድ ፖሊስ ተከትሎን መጣ፡፡ ሰክሯል፡፡ ጠራንና “በኢንተርፖል የምትፈለጉ ወንጀለኞች ናችሁ፡፡ ገንዘብ ስጡኝ እና ወደ ከተማ እንድታመልጡ አደርጋችኋለሁ” አለን፡፡ በነገሩ ብንስማማም ገንዘብ ስላልነበረን አልተሳካም፡፡ በነጋታው አውሮፕላን ስለተገኘ እንደምንሄድ ተነገረን፡፡ ማምሻውን ከጆኒ ጋር ቁጭ ብለን የማምለጫ ዕቅድ አወጣን፡፡

ከተመለስን የሚጠብቀን መጥፎ ነገር እንደሆነ ነው የገመትነው፡፡ በ1983 መጀመርያ የወጣት ቡድኑ እግር ኳስ ተጨዋቾች ካይሮ ላይ ጠፍተው በፖሊስ ተይዘው ነው የተመለሱት፡፡ ብዙዎቹ ተፈነካክተዋል፡፡ አዲስ አበባ እንደተመለሱ ኤርፖርት ብዙ ፖሊስ ተመድቦ በመኪና ታፍነው ወኽኒ ቤት ነው የገቡት፡፡ እኛም ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ ይህ ሁኔታ እንደሚጠብቀን ነው የገመትነው፡፡ የሚደርስብን ነገር ስላስደነገጠን ላለመመለስ የመጨረሻውን እርምጃ መውሰድ አለብን ብለን ተስማማን፡፡ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰን አንድ ነገር ሆነን ከሚፀፅተን እኔ ባወጣሁት ፕላን ጆኒ ተስማማ፡፡ ወደ አውሮፕላን ገባን፡፡

እቅዳችን አውሮፕላን ለመጥለፍ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ኢትዮጵያ እንዳያርፍና ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ እኛን አውርደን ለማለት ነው፡፡ አውሮፕላን ጠለፋ ብዙ ዓመት ቢያሳስርም እዚህ ከመምጣት ይሻላል ብለን ስላሰብን ነው፡፡ ሐራሬ እያለን በመንግሥት የሚፈለጉ አደገኛ ወንጀለኞች ናቸው እያሉ ሲጠቋቁሙብን ስላየን እዚህ አውሮፕላን ውስጥ አንድ ነገር ለመፈፀም ተስማማን፡፡ እቅድ አወጣን፡፡ ጠለፋውን እንዴት መጀመር እንዳለብን ተወያየን፡፡ ለጆኒ “ከተቀመጥንበት ቦታ ሆነን እየተጯጯንህን ወደፊት ተንደርድረን እንሂድ እና ሆስቴሶቹን አግተን ወደ ፓይለቶቹ ክፍል እንገባለን” አልኩት፡፡ በዚህም ተስማማን፡፡ ጆኒ “ጩቤ ነገር ወይም መሳሪያ ይዘሀል?” አለኝ፡፡

“አዎ!”

“ምን?”

“አሪፍ ነገር”

“ለመጥለፍ የሚያስችል ነው?”

“በሚገባ”

“ከየት አመጣህ?”

“ኤርፖርት ከአንድ ወታደር ገዛሁ”

“እውነትህን ነው?”

“አዎ!”

“የታለ?”

ይሄውና ቦንብ ይዣለሁ ብዬ አሳየሁት፡፡ ይህን ጊዜ ጆኒ ደንግጦ ፌንት አደረገ፡፡ በትክክል ቦንብ ባትይዝም ለመጥለፍ ተመሳሳይ ነገር ያስፈልግሃል፡፡ ምክንያቱም አውሮፕላን ውስጥ ግርግር መፍጠር ነው ያለብህ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ ከአውስትራሊያ አውሮፕላን ጠልፎ ወደ ሌላ ሀገር ሄዶ ነበር፡፡ ጠለፋ ያካሄደው በህፃናት መጫወጫ ሽጉጥ ነው፡፡ እንደማይተኩስ ይታወቃል፡፡ እንደውም በውስጡ ውሃ እንዳለ ነው የሰማሁት፡፡ ነገር ግን ሽጉጥ ስለሚመስል አውሮፕላን ላይ ስላለህ ችግር ተፈጥሮ ቢከሰከስ ሁሉም ስለሚያልቅ በድንጋጤ የምትለውን ነገር ይቀበሉሃል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ነገር ባይኖርህም ተመሳሳይ ነገር ነው መያዝ ያለብህ፡፡ ምክንያቱም የሚያጣራ ሰው አይኖርም፡፡ በወቅቱ እኔም አንድ ተመሳሳይ ነገር አገኘሁ፡፡ ይሄውም የሲጋራ መተርኮሻ ክብ ነው፡፡ ብረቱ ጠቃጠቆ ነገር አለው፡፡ ጭሱ አጥቁሮት ቦንብ አስመስሎታል፡፡ የሲጋራው ማስገቢያ አፉን ገልብጬ በእጄ ያዝኩ እና አሳየሁት፡፡ እውነተኛ ቦንብ እንደሆነ ነው ያመነው፡፡ ጆኒ እንዲህ አልገመተም ነበር፡፡ ቦንብ መሳዩን ነገር ሲያይ ወንበር ላይ በቃ ፌንት አድርጎ ለጥ አለ፡፡

ሆስተስዋ መጣችና የታመመ መስሏት “ምን ሆነ?” ብላ ትጎትተዋለች፡፡ ደንግጦ “እሱ ነው” ይላታል፡፡ እኔ መተርኮሻውን ቦታው ላይ መለስኩት፡፡ ትንሽ ከቆየን በኋላ “ወደ ውስጥ ገብቼ ፓይለቱን እይዘዋለሁ አንተ ሆስቴሶቹን ተቆጣጠር” አልኩት፡፡ ጆኒ ለጠለፋ አልተዘጋጀም ብቻዬን ደግሞ የማደርገው ነገር አልነበረም፡፡ “ቦንቡን ከየት አመጣህ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ መተርኮሻ እንደሆነ ነገርኩት እና አውጥቼም አሳየሁት፡፡ አሁን ሁኔታውን ተረዳ መጀመርያ ደንግጦ ነበር፡፡ “ጆኒ ይህ ነገር የመጨረሻ ዕድላችን የምንጠቀምበት ነው፡፡ አንተ እንኳን መተርኮሻ መሆኑን አልተረዳህም፡፡ ቦንብ መስሎህ አስደንግጦህ ምን ያህል እንደተደናገጥክ ገምት፡፡ ስለዚህ ፓይለቶቹንና ሆስተሶችን በደንብ አርበትብተን አውሮፕላኑን ወደፈለግንበት እንዲያደርሰን በዕድላችን እንጠቀም” አልኩት፡፡

“አዲስ አበባ ከደረስን ከሞት ብንተርፍ እንኳን እስር ቤት ገብተን እንበሰብሳለን” ብዬ ነገርኩት፡፡ በተወሰነ መልኩ ተስማማና “አውሮፕላኑን ጠልፈን የት ነው የምናሳርፈው?” አለኝ፡፡

“አንድ ቦታ”

“አንድ ቦታ የት?”

“ሱማሌ”

“እዚያ ባይሳካስ?”

“እንዴት?”

“ይዘው ቢሰጡንስ?”

“እዚያ መንግሥት የለም”

“ሱማሌ ይቅር ሌላ ቦታ እንፈልግ”

አገር ማማረጥ ጀመርን፡፡ ከሱማሌ ይልቅ ኬንያ ለማሳረፍ ወሰንን፡፡ አገር መርጠን ከጨረስን በኋላ ጠለፋው ላይ መድፈር አቃተን፡፡ ምክንያቱም እዚያ ለመሄድ ነዳጅ የለንም ቢለንስ?” ጆኒ ለጠለፋው እሺ ይለኝና እንደገና ያመነታል በሙሉ ልቡ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ብቻዬን ላደርገው ወሰንኩ፡፡ ነገር ግን እኔ ወደ ፓይለቶች ክፍል ስገባ እሱ ወደ ሆስተሶቹ ጋ ሄዶ “መተርኮሻ ነው የያዘው ብሎ ቢነግራቸው መሳቂያ ነው፡፡ በመጨረሻ የሚገጥመንን ችግር ነገርኩትና ጠለፋውን ቶሎ ማካሄድ እንዳለብን አስረዳሁት፡፡ “እኔ እዚህ ያሉትን አግታለሁ” አለኝ፡፡ ግን የሚያሾፍ እንጂ ተደፋፍሮ አንድ ዓላማ ይዞ ለማድረግ የፈለገ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ወቅት አውሮፕላኑ በጣም እየሄደ ነው፡፡ በጣም እየተጨቃጨቅን ከተማ ስናይ አዲስ አበባ ደረስን እያለን እንተወዋለን፡፡ ወደሽንት ቤት በሄድኩ ቁጥር ይከተለኛል፡፡ ምክንያቱም ያንን ላደርግ ይመስለዋል፡፡ ጆኒ አንድ የተጠራጠረው ነገር አለ፡፡ እውነተኛ የጠለፋ መሳርያ ደብቄ የያዝኩ መስሎት ሰግቷል፡፡ “እዚህ አውሮፕላን ውስጥ አደጋ ከተፈጠረ እኛም እንሞታለን፡፡ እስር ቤት ከገባን ግን ልንፈታም እንችላለን” የሚለው አነጋገር ነበረው፡፡ እንዲህ እያለን ስናመነታ አዲስ አበባ ደረስን፡፡ “ጆኒ” ብዬ ጠራሁት፡፡ “በአየር ላይ የነበረው ዕድላችን አብቅቷል፡፡ አሁን ደግሞ የእስርቤት ኑሯችንን እንጀምራለን ተዘጋጅ” አልኩት፡፡

ሀራሬ እያለን የተነገረን አዲስ አበባ ስንደርስ ወታደሮች እንደሚጠብቁንና ከኤርፖርት አግተው እንደሚወስዱን አሳውቀውናል፡፡ አውሮፕላኑ እንዳረፈ መሬት ላይ ወታደሮች ጠብቀውን መኪና ውስጥ አስገብተው እየወቀጡን እንደምንሄድ ነው የገመትነው፡፡ በጣም ፍራቻ ስለነበረብን አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ እኛ ሽንት ቤት እንመላለስ ነበር፡፡ መሬት ሲያርፍ ፊታችን ከልለን ልንወርድ ብንፈልግም ያውቁናል፡፡ ሰው ሁሉ ከአውሮፕላኑ ከወረደ በኋላ እኛ ዝምብለን ቁጭ አልን፡፡ ከፈለጉ እዚ ይያዙንና ይውሰዱን አልን፡፡ ይህ ደግሞ አያስኬድም እንዲሁም እዚህ በመቆየታችን የባሰ ዱላውን ያብሰዋል፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ ሌላ ነገር አሰብን፡፡ ለምን እዚሁ ውስጥ አንደበቅም? ምናልባት እኮ ይሄ አውሮፕላን ወደ አውሮፓ ሊበር ይችላል፡፡ በዛውም ዕድላችንን እናሳካ ይሆናል፡፡ ሽንት ቤት ጣራ ላይ አለበለዚያም የሆነ ቦታ ላይ መደበቂያ አናጣም፡፡ እንዲህ እያልን ስናስብ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ዐይተውን “ውረዱ እንጂ! ከዚህ በኋላ አይቀጥልም” አሉን፡፡ ቀስ ብለን ወደ በሩ ተጠግተን ውጪውን ዐየን፡፡ እኛን የሚወስዱ ወታደሮች አይታዩም፡፡ ከአውሮፕላኑ ሥር ናቸው ያሉት፡፡ ልክ እግራችን መሬት እንደነካ አፍሰው ሊወስዱን ነው፡፡ ሆስተስዋ ጆኒ ፌንት ባደረገ ጊዜ የሆነ ነገር ልንሰራ እንደፈለግን አውቃለች፡፡ ምናልባት አውሮፕላኑ ላይ አደጋ ይፈጠራል የሚል ግምት ኖሯት ለሌሎቹ ልትነግር ትችላለች፡፡ ለጥንቃቄ ሲባል ወደ ውስጥ አይገቡም፡፡ ምክንያቱም ወታደሮቹ ገብተው እዚህ ውስጥ ግብግብ ከፈጠሩ እና አንድ ነገር ከያዝን አውሮፕላኑ ላይ አደጋ ይደርሳል ብለው ስለገመቱ እንደሆነ አሰብን፡፡ በመጨረሻም እንደምንም የመጣው ይምጣ ብለን ከአውሮፕላኑ ውስጥ ሁካታ እንዳንፈጥር ብለው አስበው በር ላይ እየጠበቁን እንደሆነ ገመትን፡፡

መቼም አዲስ አበባ ደርሰናል፡፡ ማምለጫ የለንም፡፡ የመጣው ይምጣ ብለን ወደ ውጭ ሄድን፡፡ በር ላይ ወታደሮች ተሰብስበዋል፡፡ አብዛኞቹ ፖሊሶች ናቸው፡፡ በቃ እነዚህ ናቸው የሚይዙን ብለው እስኪመጡ እንጠብቅ አልን፡፡ እዚያ አካባቢ ስልክ ስለነበር ወደቤት ደውለን ተይዘን እንደመጣንና የማናውቀው ቦታ እንደምንታሰር ግን አዲስ አበባ ውስጥ እንደምንገኝ መልዕክት ማስተላለፍ ነበረብን፡፡ ይሄንን ልናደርግ እየተዘጋጀን ፖሊሶች ሲንቀሳቀሱ ዐየናቸው፡፡ ከዛ በኋላ አዘናግተው ሊይዙን እንደፈለጉ ገመትን፡፡ እንጥፋባቸው ብለን ተነጋገርን፡፡ ትንሽ ቆየንና በሚወጣበት በላይኛው በር ቀስ ብለን እየተንሸራተትን ሄድን፡፡ በቆረጣ ግን እናያቸዋለን፡፡ ለምን ወደእኛ አልመጡም? ብለን ገመትን፡፡ ምናልባት የውጭ ዜጎች ስላሉ እዚያ አካባቢ ግርግር ላለመፍጠር ፈልገው እንደሆነ ገመትን፡፡ ከግቢ ውጭ ሊይዙን ነው የፈለጉት፡፡ ውጭ ብዙ ህዝብ ስላለ ሮጠን ከሰው ጋር ተቀላቅለን፤ ሁካታ በመፍጠር እናምልጥ ብለን ተደብቀናቸው ሄድን፡፡ ፖሊሶቹ እየገላመጡ ዞር ዞር እያሉ የሚያዩን መሰለን፡፡ እንደጠፋንባቸው አወቁ፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም እናምልጥ አልን፡፡ ተሹሎክልከን ታክሲ ውስጥ ገባን ተሎ ተሎ ንዳ አልነው ከቻልክ ቆመህ፡፡

ባለታክሲውም ፈጥኖ ሄደ፡፡ ዐይተውን በፖሊስ መኪና አባረውን እንደሚይዙን ገመትን፡፡ ይሄም ስጋት አደረብን፡፡ አምልጠን በየቤታችን ገባን፡፡ በር በተንኳኳ ቁጥር ፖሊስ መጥቶ “አገር የከዳ” በሚል አንጠልጥሎ ይወስደናል ብለን ነበር፡፡ አንድ ቀን አልፎ በሌላው ቀን ተተካ፡፡ ማንም የለም፡፡ ሳምንት ቆየን ማንም ሰው ስለእኛ የሚጠይቅ ጠፋ፡፡ ነገሩ ግራ አጋባን፡፡ በሌላ ቀን ወደ ከተማ ወጣን፡፡ ምንም የለም፡፡ ጭራሽ የሚያስታውሰንና የሚጠይቀን አጣን፡፡ በመጨረሻም እኛ እራሳችን ነገር ፍለጋ ጀመርን፡፡

ነገሩ “ለምን ዝም ተባልን?” በሚል ነው። ወደ ቦክስ ፌዴሬሽን ሄደን ሞሪሽየስ ላይ በቡድን መሪው ዛቻ እንደደረሰብን ቅሬታችንን አቀረብን። ጭቅጭቅ ስናበዛ ፌዴሬሽኑ 10 ወር ቀጣን። የቀጣን ኢንተርናሽናል ጨዋታ አታደርጉም በሚል ነው። ክርክር ባንፈጥር ኖሮ ማንም የሚያስታውሰን አይኖርም ነበር። በመጨረሻም ከጆኒ ጋር ተነጋገርን። “አውሮፕላን ጠልፈን ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር?” አልን። ይላል። ዮሃንስ አውስትራሊያ ለኦሎምፒክ ሄዶ ቀረ። አበባው ደግሞ ዛሬም ድረስ አዲስ አበባ ይኖራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top