ስነልቦና

የልጅነት አጋጣሚዎች እና ስነልቦናዊ ተጽዕኗቸው

የሱፐርማርኬት ወረፋ በመጠቅ ላይ ነኝ። ለሸመታ ያሰብኳቸውን ጓዞች ሰብስቤ ገንዘብ ለመክፈል ተራ ይዣለሁ። ረዘም ያለው ሰልፍ ላይ የመጨረሻ ተሰላፊ ነኝ። ከፊት ለፊቴ አንዲት ጠይም ረጅም ሴት ትገኛለች። በተንቀሳቃሽ ስልኳ እየተነጋገረች ነው። በአንድ እጇ ስልኳን በሌላኛው እጇ ራሷን የምትመስል ልጅ አጥብቃ ይዛለች። ሕጻኗ በግምት ከ6 ዓመት ይሆናታል። ግራ ቀኙን፣ ፊት ኋላውን፣… በማማተር ላይ ያለችው ሕጻን ትኩረቴን ስባዋለች። አንዳች የጠፋባትን የምትፈልግ ወይም የቀጠረችውን የምትጠብቅ ትመስላለች። ከጥቂት ቆይታ በኋላ በፈገግታ ተሞልታ ወደ አንድ አቅጣጫ መመልከት ጀመረች። ዐይኗን ተከትዬ የምታየውን ዐየሁ። ከበስተኋላዬ የፊተኛዋን ልጅ እድሜ እና ጾታ የምትጋራ ታዳጊ ህጻን ከወላጅ እናቷ ጋር በመምጣት ላይ ናቸው። ሕጻናቱ ሲተያዩ ፈገግታ ተለዋወጡ። በተለይ የመጀመሪያዋ ከእናቷ እጅ አምልጣ የናፈቀቻት ጓደኛዋን ለመሳም መዳዳቷን አሳበቀች። ስልክ በማነጋገር ላይ የነበረችው እናት ንግግሯን ለአፍታ ገትታ “አርፈሽ ቁሚ!!” ስትል ገሰጸቻት። አጠር ያለ ቁጣዋን ለልጇ አድርሳ ረዘም ያለ የስልክ ንግግሯን ቀጠለች።

ተግሳጽ ያልበገረው የልጆቹ ድርጊት በናፍቆት ከመተያየት ወደ አጫጭር የሹክሹታ ንግግሮች ተተካ። “ልደቴ እኮ ተከበረ” ንግግሯ የማስቀናት አልነበረም። ደስታን የማካፈልም አልነበረም። ይልቁንም ቅሬታ ያዘለ ነበር።

“ወይኔ ታድለሽ! እና ጓደኞችሽ መጡ? እነ ቢታኒያ፣ እነ ጆኒ፣… እና ፎቶ ተነሳችሁ? ኬኩ ምን ዐይነት ነበር? ትልቅ ነው?…” መልስ ሳትጠብቅ ጥያቄዋን አከታተለች። ልጆቹ በአካል ተራርቀው፣ በልብ ተቀራርበው፣ በእናቶቻቸው ጥበቃ ስር ሆነው፣ ከደስታ ቀኖቻቸው መሐከል አንዱ ስለሆነው የልደት በዓል አከባበር መረጃ እየተለዋወጡ ነው። ባለልደቷ ለልቅሶ በቀረበ ቅላፄ አንገቷን ደፍታ የእግረኛ መንገዱን ጠርዝ በእግሯ ጫፍ እየተመተመች፤ “ብቻዬን እኮ ነው ያከበርኩት” አለች። “እና ብቻሽን ኮፍያ አድርገሽ ፎቶ ተነሳሽ?! ለብቻሽ ‘ሀፒ በርዝደይ’ አልሽ?!” ግርምትም ሹፈትም በተቀላቀለበት ሁኔታ፤ “ይቺ ማሚ እኮናት፤ መጥቼ ልጠራሽ ስል ኮሮና ነው ሰው ቤት አይኬድም፣ ልጆችም ዐይመጡም ብላ ብቻዬን ያስከበረችኝ”

የሱፐርማርኬት ወረፋ እስኪደርሰኝ በማድመጥ ላይ የነበርኩት የሕጻናቱ ምልልስ ከፊቴ የነበረችው እንስት ተራዋ በመድረሱ ቢቋረጥም፤ በቀላሉ የማልገላገለውን ሐሳብ አቀበለኝ። ገጠመኙ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚከወኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች ለሚያስከትሏቸው የስነ-ልቦናዊ ቀውሶች አንድ ማሳያ ቢሆንም ከዚያም ዘለግ አድርጎ ማሰብ ይቻላል። በተለይም ወላጆች እና ትልልቅ ሰዎች በቀላሉ የሚመለከቷቸው ወይም እንደ ቅንጦት የሚቆጥሯቸው፣ መኖራቸው ደስታን የሚጨምር፣ አለመኖራቸው ብዙም የማያጎድል የሚመስሉ ነገሮች፣…. ሕጻናቱ እንደምን ባለ ትኩረት እንደሚመለከቷቸው እና ቀናትን ለሚዘልቅ፣ ምናልባትም እድሜአቸውን ሙሉ ለሚከተላቸው ሐዘን እንደሚዳርጋቸው ጥሩ ማሳያ ነው።

ልደት አክባሪዋ ህጻን የምትወድደው የሕይወቷ ክፍል ባልተለመደ መልክ አልፏል። ከዚህ ቀደም ከነበሩት ልደቶች ሁሉ ባልደመቀ ስነስርአት ተከብሯል። ሁኔታው አንዳች የተከለከለችው ነገር እንዳለ እንዲሰማት አድርጓል። ኩርፊያ እና ሐዘን ላይ ጥሏታል። ከዓመታት በኋላ በፎቶ አልበሟ ላይ ብቻዋን የተነሳችበት የታሪክ መዝገቧን ልትወቅስና ለሌሎቹ የልደት በዓሎቿ ብዙም ግድ እንዳይሰጣት ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚ አልፏል። ክፉውን ያርቀው እንጂ ከትልቅ በደል ልትቆጥረው የምትችለው ክስተት ሊሆንም ይችላል።

ይህን መሰል አጋጣሚዎች በተለያየ መልክ እና መንገድ፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል ባለ ግንኙነት ያጋጥማሉ። ታዲያ እነዚህን አጋጣሚዎች የተገባ ትኩረት ሳንሰጣቸው እና ልብ ሳንላቸው ያልታሰበ የባህሪ ለውጥ እና የስነ-ልቦና አደጋ በልጆቻችን ህይወት ላይ ሲፈጥሩ እናስተውላለን።

ሳይኮሎጂስቱ (የስነልቦና ሕክምና ባለሙያው) ፒያዤ አዋቂነትን የሚቀርጹትን የልጆች የአዕምሮ አስተዳደግ ደረጃዎች (child cognitive developmental stage) በማለት በአራት ደረጃዎች ከፍሎ አስቀምጧቸዋል። ከዝርዝሮቹ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃን የያዘው preoperational stage ነው። በዕድሜ ክልል ከ2 እስከ 7 ዓመት የሚገኙ ሕጻናት ላይ ይከሰታል። እንደ ባለሙያው ብያኔ እና ትንታኔ በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ የሚኖረው የሕጻናቱ ትውስታ የነገ ሕይወታቸው ተመዝግቦ የሚቀመጥበት ነው። ስለወደፊት ህይወታቸው ጭምር አዕምሯቸው ላይ የሚመዘገብበት፣ ስብዕናቸው የሚገነባበት፣ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚጀምሩበት፣ ጓደኝነትን የሚለማመዱበት ነው። ሕጻናቱ በዚህ እድሜአቸው የሚመሰርቱት ግንኙነት ለጥቂት ጊዜ ሲቋረጥ በመጀመሪያ አካባቢ ይናፍቃሉ። ከቆይታ በኋላ ግን ሊረሱት ይችላሉ። የነገሩ ተደጋጋሚነት እና ቋሚ የሚባል ወዳጅነትን፣ መኖሪያን፣ የቤተሰብ አባላትን፣… የሚያሳጣ ሲሆን ደግሞ እየተነጋገርንበት ከምንገኘው የባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ የገባን ወይም ወደፊት የሚገባን ሰው የመፍጠር ጎዞ የመሆን እድሉ ያመዝናል። ለምሳሌ መለያየታቸው ከሦስት ወይም አራት ወር በላይ ከሆነ ሊዘነጉት የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ለዚህ ነው ሲያድጉ ወዳጅ መፍጠር መሳን (lack of attachment) ችግር የሚጋለጡት።

በለጋ ዕድሜ ላይ የሚፈጠር የተግባቦት እና የጓደኝነት ክህሎት መሳን፤ በአዋቂነት ላይ በሚታይ ባህሪ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ብዙ የተነገረበት እና ብዙ የተጻፈበት ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፤ በዚህ የዕድሜ ክልል ያጋጠማቸውን አያስታውሱም የሚለው ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም ሊያስታውሱም ላያስታውሱም ይችላሉና። ነገር ግን (አንኮንሺየስ ማይንድ) የተባከለው የአዕምሮ ክፍል ማናቸውንም በህይወታችን የተከወነ ድርጊት መዝግቦ ያቆያል። ምዝገባው ያስታወስናቸውን ወይም የምናስታውሳቸውን ብቻ ሳይሆን የማናስታውሳቸውን የሕይወት ገጠመኞቻችንን ያካትታል።

በኋለኛው ዕድሜያችን (ታዳጊነት፣ ጉርምስና፣ ጉልምስና፣ እርጅና) ላይ ቀስ በቀስ በኑሯችን፣ በአስተሳሰባችን፣ በስብዕናችንና በባህሪያችን እየተገለጠ ህይወትንና ጤናን መረበሹ አይቀሬ ነው። ስለዚህም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉ የተሻለ ነው ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው።

እንደ ኮሮና ዐይነት ልዩ የአኗኗር ይትባህልን የሚያስከትሉ ሁነቶች ሲከሰቱ ለልጆች የምንገልፅበት ወይም የምናስረዳበት ሁኔታ ጥንቃቄ የተመላበት እና አስተሳሰባቸውን የመጠነ መሆን ካልቻለ፤ በባህርያቸው ላይ ዘላቂ ውድመት የማስከተል እድሉ ሰፊ ነው። ልጅነቱ ላይ ጤናማ ያልሆነ ሰው በኋለኛው ሕይወቱ ላይ በርካታ የስብዕና ውጥንቅጥ (ዝብርቅርቅ)፣ ስነ-ልቦናዊ ቀውስ፣… ውስጥ መግባቱ ከተገማችነት በላይ ጥናቶች ያረጋገጡት ሐቅ ነው።

ያለተጨባጭ ወይም የሚታወቅ ምክንያት መፍራት፣ ባሏቸው ነገሮች አለመደሰት፣ ለህይወት ትርጉም ማጣት፣ ለመኖርና ለመሞት አቻ ትርጉም መሥጠት ‹ብሞትም ብኖርም ግድ የለኝም› የሚሉበት ዐይነት የስሜት መዘበራረቆች፣ ከፍተኛ የሆነ ተጠራጣሪነት፣ ምክንያት አልባ ጥላቻ፣ እንደ ባይፖላር፣ ኦሲዲ፣ የመሳሰሉ የስብዕና ቀውሶች፣… ሊያሳዩ ይችላሉ።

እዚህ ላይ ከላይ ያነሳነውን ሐሳብ ሊያጠናክርልን የሚችል ታሪክ እንመልከት። ታሪኩን የሰማሁት ከመምህሬ ነው። ፕሮፌሰሩ የሕጻንነት የኑሮ ገጠመኞች ሙሉ ሕይወትን ሊያመሰቃቅሉ ስለሚችሉበት ሁኔታ ለማስተማር ችግሩን ያሳይልኛል በሚል ያጫወቱን ገጠመኝ ነው።

ባለታሪኳ የ5 ዓመት ሕጻን በነበረችበት ጊዜ እናቷ ከባለቤቷ ጋር ተለያየች። ከአባቷ መለየቷን ያልወደደችው ሕጻን እናቷ ካገባችው ሌላ ሰው ጋር ለመኖር ተገደደች። ነገሩን የከፋ ያደረገው ሌላ አዲስ ባሕል እና ከቀደመው የተለየ የአኗኗር ስልት (ባህል) ያለው ቤተሰብ ውስጥ መቀላቀሏ ነው። እናም በዚያ ዐዲስ ባህል መሠረት 5 ዓመት የሞላት ሴት ልጅ በቀን 4 ጊዜ ሰውነቷ ይታጠባል። የነካችው፣ ያለፈችበት፣ የተቀመጠችበት፣… ሁሉ ይታጠባል። የእጥበት ስነ-ስርአቱ በዓመቱ ይጠናቀቃል። 6ዓመት የሞላት ሴት ሕጻን በየቀኑ እንድትታጠብ አትገደድም። የገጠመኙ ባለቤት እጥበቱን 6ዓመት እስኪሞላት ለምዳዋለች። ቀስ በቀስም ወዳዋለች። ከለመደችው በኋላ መታጠቡ እንዲቀጥል ብትፈልግም ባህሉ ስላልሆነ አንደማንኛውም ሰው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ አንድትታጠብ ትገደዳለች። ይህ ሁሉ አልፎ ልጅቷም አድጋ የራሷ ሕይወት መሰረተች። ከዓመታት በፊት የነበረው፣ ትጠላው የነበረው፣ ቆይታ የወደደችው፣ መውደድ ስትጀምር ያጣችው፣… ልማድ ተከተላት። ስራ ቦታዬ በቀን አራት ጊዜ ካልተፀዳ የምትል ሆነች። ቤቷ ከ5 ጊዜ በላይ ካልተፀዳ የሚያማትና የሚጥላት ሰው ሆነች። በዚህ ሁኔታዋ ሁሌ እየተናደደ፣ በድርጊቷ ዘወትር አንጀቱ እያረረ ዋጥ የሚያደርገው ባለቤቷ ደግሞ እጅግም ባልተጋነነ እንደውም ከመደበኛው ባነሰ የጽት ስርአት ውስጥ ያደገ እና የኖረ ነው፡፡ ከእስዋ በተቃራኒ ዕቃ ሲዝረከረክ የሚወድ ነበር። ከእለታት በአንዱ የእረፍት ቀን ሦስት ጊዜ ያጸዳችውን ቤት ለአራተኛ ጊዜ እያፀዳች ሳለ ድንገት የሆነ ነገር ይደፋባትና ልብሷን ያቆሽሻል፣ “ስጨርስ አጥበዋለሁ” ብላ የጀመረችውን ቀጠለች። ባለቤቷ ተነሳና ሁሉንም ዐየ ተፀድቷል። ምራቁን መጣል የለመደበት ነበርና ያልተፀዳ ቦታ ሲፈልግ የቆሸሸው የለበሰችው ልብስ ብቻ ነበር። ጢቅ አለባት። እጅግ ተበሳጭታ ተጣላችው። ተጣሉ። የዚህን ሁሉ ምክንያት ባታስታውሰውም ግን፤ በሳይኮሎጂስቱ አማካኝነት ‘ሂፕኖቲክ’ በተባለው ህክምና እንደታወቀና እንደዳነች ነግረውናል።

የዚህች ሴት ታሪክ ብዙ የሚያስተምረን ቁምነገር በውስጡ ያዘለ ነው። አብሮን ያደገ እኛ ልብ የማንለው ችግር በሁላችንም ውስጥ ሊኖር እንደሚችልና፤ ይህንንም የስነልቦና ችግር ቀድመን መፍትሄ ልናገኝለት ካልቻልን፤ ሳይታወቀን ተጽዕኖው ስር ሰድዶ ህይወታችንን ሊያመሳቅልብን እንደሚችል ነው።

ምን እናድርግ?

ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ለእያንዳንዷ ነገር ጥንቁቅ ሊሆኑ ይገባል። ለአዋቂዎች እንደተራ ነገር የምትታይ አንዲት ትንሽ አጋጣሚ፤ በልጆች አዕምሮ ላይ ግን ግዙፍ ሆና የወደፊቱን የህይወታቸውን አቅጣጫ የምትቃኝ፤ በአዋቂነት ዕድሜያቸው ባለ ባህሪ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድር ትሆናለች።

ልጆች ማንኛውንም ነገር እንዳያደርጉ ሲከለከሉ፤ ምክንያታችን ምን እንደሆነ፣ ያንን የተከለከሉትን ነገር ቢያደርጉ ምን ዐይነት መጥፎ ነገር እንደሚከሰት፣ እነሱ ደስ እንዳይላቸው ፈልገን ሳይሆን ስለምንወዳቸው፣ እያሰብንላቸው፣.. እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ መንገርና አምነው እንዲተገብሩት ማገዝ ያስፈልጋል።

ለልጆች ስነልቦና መጨነቅ በወላጆች ላይ ብቻ የሚጣል ኃላፊነት አይደለም። እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል፣ መምህራን፣ ጎረቤት፣ ዘመድ… ልጆች ፊት ምን ማድረግ እና ምን መናገር እንዳለበት ቢጠነቀቅ መልካም ነው።

መንስኤዎቻቸውን የማናውቃቸው ስነልቦናዊ ችግሮች ሲያጋጥሙን፤ ጊዜ ሳናጠፋ የስነልቦና ባለሞያ ማማከርም መልካም ነው። እኛ ያከበድነው ቀላል፤ እኛ ያቀለልነው ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላልና ስልጡን ባለሙያን ማማከር ይልመድብን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top