ጥበብ በታሪክ ገፅ

ዘመን አሻጋሪው የትውልዶች ጀግና

“ጥቁር ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው፤ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን አለባቸው” በሚለው መርሁ የሚታወቀው ማርከስ ጋርቬይ፤ ኋላ ላይ ታላላቅ የጥቁር ህዝብ መብት ታጋይ እና የንቅናቄ መሪ ለሆኑት ለኔልሰን ማንዴላ፣ ጆሞ ኬኒያታ፣ ኩዋሜ ንኩሩማ፣ ማልኮም ኤክስ፣… ፋና ወጊ ቀዳሚ የነፃነት ታጋይ በመሆን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መቀየስ የቻለ ትጉህ ሰው ነበር።

ታዋቂው የጥቁሮች መብት ታጋይ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለማርከስ ጋርቬይ እንዲህ ብሎ ነበር “ማርከስ ጋርቬይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ማንነታቸውን እንዲያውቁና በታሪካቸውም እንዲኮሩ ያደረገ የመጀመሪያው ነፃ አውጪ መሪ ነበር።”

የማርከስ ጋርቬይ ጁንየር ህይወት

ማርከስ ጋርቬይ ጃማይካዊ የፖለቲካ አክቲቪስት፣ አሳታሚ፣ ጋዜጠኛ፣ ስራ ፈጣሪ እና ታላቅ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ አንደበተ-ርቱእ ሰው ነበር። የዩኒቨርሳል ኒግሮ ኢምፕሩቭመንት ተቋም፣ የአፍሪካ ማኅበሮች ሊግ መስራችና የመጀመሪያው ተቋሞቹን በፕሬዝደንትነት መምራት የቻለ ሰው ነው። እነዚህን ተቋማት መምራት ስለቻለም ራሱን ጊዜያዊ የአፍሪካ ፕሬዝደንት በማለት፤ ሹመቱን ይመጥናሉ ያላቸውን ስራዎች በመስራት ታላቅ አስተዋጽኦ በዓለም ላይ ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች አበርክቶ አልፏል። የማርከስ ጋርቬይ ርዕዮተ-አለማዊ አስተሳሰብ በጥቁር ብሔርተኝነት እና በፓን- አፍሪካኒዝም ፅንሰ-ሃሳቦች የተቃኘ ነበር። ከህልፈቱ በኋላ የእሱ አስተሳሰቦች እና አስተምህሮዎች ‘ጋርቬይዝም’ በመባል ይታወቃሉ።

ማርከስ ጋርቬይ

ጋርቬይ የተወለደውና ያደገው በዘመኑ ከነበረው የጃማይካ ማኅበረሰብ ጋር ሲነፃፀር ጥሩ ሃብት አለው በሚባል ቤተሰብ ውስጥ በኦገስት17፣ 1887 እ.አ.አ. ነው። የተወለደባት አካባቢ “ሴንት አን ቤይ” የምትባል የጃማይካ ግዛት ስትሆን፤ በአፍላ የታዳጊነት ዕድሜውም ከህትመት ንግድ ጋር ተዋውቋል። ምንም እንኳ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ሲነፃፀር ጥሩ የሚባል ህይወት ያላቸው የማርከስ ወላጆች፤ ከፍተኛ ትምህርት የማስተማር አቅም ባይኖራቸውም በአካባቢው በሚገኝ የቤተክርስቲያን ትምህርትቤት ልጃቸው ማርከስ ጋርቬይ እንዲማር አድርገዋል። የማርከስ ጋርቬይ ጁኒየር አባት የሆነው ማርከስ ጋርቬይ ሲኒየር፤ በሞያው የድንጋይ ቀራፂ ሲሆን ትእግስት-አልባ እና ቁጡ ሲሆን ከልጆቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት አልነበረውም።

የጋርቬይን የህይወት አቅጣጫ መሰረት ያስያዘው የወለደው አባቱ ሳይሆን፤ የክርስትና አባቱ ነው። በክርስትና አባቱ ማተሚያ ቤት ውስጥ ገና በ14 ዓመቱ በ1901 እ.አ.አ. ተቀጥሮ ስራ የጀመረው ማርከስ ጋርቬይ፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ ከአካባቢው ራቅ ብሎ በሚገኘው ‘ፖርት ማርያ’ የማተሚያ ቤቱ ቅርንጫፍ ሲከፈት፤ ከሚኖርበት ሴንት አንስ አቤይ እየተመላለሰ መስራት ጀመረ።

ኪንግስተን (የጃማይካ ዋና ከተማ) ውስጥ ይሰራ በነበረበት ዘመንም በንግድ ማኅበራት እና በሰራተኛ ማኅበራት ውስጥ መሳተፍ ጀመረ። ከዛም ቀጥሎ ባለው ወቅት ለጥቂት ጊዜያት አልኖረም። በ1929 እ.አ.አ. በምህፃረ በኮስታሪካ፣ ፓናማ እና እንግሊዝ ሃገራት ኖረ። ወደ ጃማይካ በተመለሰ ጊዜም በ1914 እ.አ.አ. ለአጭር ጊዜ በከተማዋ ቢሮ UNIA (የዩኒቨርሳል ኒግሮ ኢምፕሩቭመንት ተቋም)ን ለመመስረት ቻለ። በ1916 እ.አ.አ. ወደ ኒውዮርክ ሃርለም አካባቢ በመጓዝ የዩ.ኤን. አይ.ኤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን መሠረተ። በአፍሪካውያን እና በአፍሪካ ዲያስፖራ መካከል አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ካስተማረ በኋላ፤ የአውሮፓውያን የአፍሪካ ቅርምት እንዲያበቃ እና ላይ ያለው ቅኝ አገዛዝ እንዲያከትም፤ አፍሪካውያንም በአንድነት የተባበረ ጠንካራ አህጉራዊ አንድ ሃገር እንዲመሰርቱ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርጓል። በአንድ ፓርቲ የሚተዳደር አፍሪካዊ አህጉር እና እሱ የሚመራው ለጥቁር ህዝቦች ነፃነትና ፍትሕ የሚሰራ መንግስት ለመመስረት ትልቅ ህልም ነበረው። ወደ አፍሪካ አህጉር አንዴም ቢሆን ጉዞ አድርጎ የማያውቀው ማርከስ ጋርቬይ “ወደ አፍሪካ መመለስ” የሚል እንቅስቃሴ በመጀመር፤ አፍሪካ አሜሪካውያን ወደቀደምት አያት ቅድመአያቶቻቸው ምድር መመለስ እንደሚገባቸው አስተምሯል። የጋርቬይ አስተምህሮዎች ተቀባይነት እያገኙ ሲሄዱ የዩኒቨርሳል ኒግሮ ኢምፕሩቭመንት ተቋም አባላት ቁጥርም እያሻቀበ ሄደ። ጋርቬይ ጥቁር ህዝቦች ከሌሎች ጫና ነፃ ሆነው ሃገር መስርተው መኖር አለባቸው (black separatist) የሚል ሐሳብ ነበረው። ለዚህም ይመስላል በአስተሳሰብ ከሚቃረኗቸው የነጭ አክራሪ ኃይል ከሆኑት በምህፃረ-ቃል ኬኬኬ ተብለው ከሚታወቁት ከ‘ኩክለክስ ክላን’ ጋር አብሮ ለመስራት እስከመስማማት የደረሰው። ኩክለክስ ክላኖች አሜሪካንን የነጮች ሃገር የማድረግ ትልቅ እቅድ ስለነበራቸው፤ የጋርቬይን ጥቁሮችን ወደ አፍሪካ የመመለስ እንቅስቃሴ በመደገፍ ለዓላማቸው ሊስማማ በሚችል መንገድ አብረውት ለመስራት ተስማሙ።

የማርከስ ጋርቬይ ከኬኬኬ ጋር አብሮ መስራት በብዙ ወገኖች አልተወደደለትም። የራሱ የጥቁር አሜሪካውያን ወገኖችን ጨምሮ፤ በተለይም በአይሁዶች ዘንድ ቂም አስቋጥሮበታል። የድርጅቶችን የአክስዮን ድርሻ አላግባብ ሸጠሃል ተብሎ በፍርድቤት ተከሶ ሁለት ዓመት ተፈርዶበት በታሰረ ጊዜም “ለዚህ ሁሉ እንግልት የሚዳርጉኝ አይሁዶች ናቸው” ብሎ ተናግሮ ነበር። ልክ እንደእሱ ሁሉ ብዙ ሰዎችም ክሱን እና እስሩን ከፖለቲካ ጨዋታ ጋር ነበር ያያያዙት።

አሜሪካ ለሁለት ዓመት በማሰር ብቻ ጋርቬይን አልተወችውም። ዳግመኛ ወደአሜሪካን ሐገር እንዳይመለስ ከሚያስጠነቅቅ ዛቻ ጋር፤ በ1927 እ.አ.አ. ወደጃማይካ ተጠረዘ (Deport)፤ በእስርቤት ከፍተኛ እንግልት ይደርስበት ስለነበር፣ ባለተገባ ክስ እና በዘር መድሎ ምክንያት የጥቃት ሰለባ ስለሆነ፤ ማርከስ ጋርቬይ እጅጉን ቅሬታ ስለተሰማው ከዛን ጊዜ በኋላ የአሜሪካንን ምድር አልረገጠም።

ኪንግስተን ላይ ከትሞ ከሚስቱ ኤሚ ጃክዊስ ጋር መኖር ከጀመረ በኋላም ከፖለቲካ የራቀ ህይወት አልኖረም። በ1929 እ.አ.አ. በምህፃረ ቃል ፒፒፒ (Peoples Political Party) የሚሰኝ ፓርቲ መስርቶ ለአጭር ጊዜ በከተማዋ ቢሮ ስልጣን አግኝቶ አገልግሏል።

ጋርቬይ በሃገሩ ጃማይካ ተመልሶ መኖር ወደ ኒውዮርክ ሃርለም አካባቢ በመጓዝ የዩ.ኤን. ከጀመረ በኋላ የዩኒቨርሳል ኒግሮ ኢምፕሩቭመንት ተቋም እየተዳከመ፤ በተፅዕኖም በገንዘብ አቅምም እየተሳነፈ መጣ። ተቋሙን ለማጠናከር እና የገቢ ምንጩንም ለማሳደግ በማሰብ ሃገሩን ጃማይካን እና ዋና ከተማዋን ኪንግስተንን በመተው፤ ኑሮውን እና ስራውን በለንደን ከተማ አደረገ። በለንደን ከተማ ሲኖር ከወገኖቹ ከጥቁር አክቲቪስቶች ጋር ተግባብቶ ለመስራት ተቸግሮ ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት፤ በወቅቱ በነበሩ ጥቁር አክቲቭስቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውን የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለምን መውቀስ ማርከስ ጋርቬይ ያዘወትር ስለነበረ ነው። እስከ ዕለተ- ሞቱ 1940 እ.አ.አ. ማርከስ ጋርቬይ በለንደን ከተማ ኖሯል። በ1964 እ.አ.አ. ደግሞ አስከሬኑ ወደትውልድ ሃገሩ ጃማይካ እንዲመለስ ተደርጎ በኪንግስተን በሚገኘው የጃማይካ ብሄራዊ ጀግኖች መካነ-መቃብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

አበርክቶ

“ጥቁር አሜሪካውያን በነጮች የበላይነት በሚመራ ገበያ ውስጥ ጥቅማቸውን ሊያስከብሩ አይችሉም” የሚል እምነት የነበረው ማርከስ ጋርቬይ፤ የኒግሮ ፋብሪካዎች ኮርፖሬሽን እና ኒግሮ ወርልድ የተሰኘ ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት መስርቷል። በሰሜን አሜሪካ እና በአፍሪካ ጥቁሮች መካከል ያለን ቅርርብ በንግድም ጭምር ለማጠንከር ሲባል የተመሰረተው ብላክ ስታር ላይን (Black Star Line) የተባለ የመርከብ ማጓጓዣ ድርጅትን ከ1919 እ.አ.አ. አንስቶ በፕሬዝዳንትነት መርቷል። ከአሜሪካ ወደ ምዕራባዊ አፍሪካዊቷ ሃገር ላይቤሪያ ይደረግ ለነበረው ዘፀአታዊ ምልሰት፤ ሁኔታዎችን ያመቻቸው ይህ የመርከብ ድርጅት ነበር። ላይቤሪያ ከአሜሪካ የተመለሱ ጥቁሮች ስለነበሩባት አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ከለላ ታደርግላት ነበር። ቅኝ ገዢዎችም እንደተቀሩት የአፍሪካ ሃገራት ቅኝ ለመግዛት ሙከራ አላደረጉባትም።

አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን በሚል አስተሳሰቡ የሚታወቀው ማርከስ ጋርቬይ፤ ፍልስፍናዎቹን አስተሳሰቦቹን እና ስኬቶቹን የሚገልፅ Philosophy and Opinions of Marcus Garvey (የማርከስ ጋርቬይ ፍልስፍና እና አስተያየቶች) በሚል ርዕስ መጽሐፍ አለው። ይህ መጽሐፍ ለብዙ ከማርከስ ጋርቬይ ቀጥለው ለመጡ የጥቁር ህዝቦች መብት ታጋዮች እና መሪዎች እንደማነሳሻ አብሪ ኮከብ የሆነ ድርሳን ነበር። የጋና የመጀመሪያ ፕሬዝደንት የሆነው ክዋሜ ንክሩማ ግለታሪኩን ባሰፈረበት መጽሐፍ “ካነበብኳቸው መጽሐፎች ሁሉ ከፍተኛ ተነሳሽነት የፈጠረብኝ መጽሐፍ” ብሎለታል፡፡

ክዋሜ ንክሩማ የጋናን ብሔራዊ መርከብ “ብላክ ስታር ላይን” ሲል ጋርቬይ መስርቶት ከነበረው የመርከብ ድርጅት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማስታወሻ ስያሜ ሰጥቶታል። “ብላክ ስታር” (ጥቁር ኮኮብ) በጋና ባንዲራ መሃል ላይ እንዲኖር የተደረገ ሲሆን፤ በጋና ዋና ከተማ የሚገኝ ግዙፍ አደባባይም “ብላክ ስታር” የሚል ስያሜ እንዲያገኝ ተደርጓል።

የማርከስ ጋርቬይ ሚስት ኤሚ ጃክዊስ፤ እሱ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ነበር ጽሁፎቹን እና ንግግሮቹን አሰባስባ “የማርከስ ጋርቬይ ፍልስፍና እና አስተያየቶች” የሚለውን መጽሐፍ ልታሳትምለት የቻለችው።

ህልፈት

ማርከስ ጋርቬይ ጁንየር አኗኗሩ ብቻ ሳይሆን አሟሟቱም አስገራሚ ነበር። በጃንዋሪ 1940 እ.አ.አ. ጋርቬይ ስትሮክ አጋጥሞት ሰውነቱ ፓራላይዝ ሆነ። የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጋዜጦች ካልታወቀ ምንጭ የደረሳቸውን መረጃ ሳያረጋግጡ፤ ማርከስ ጋርቬይ እንደሞተ አድርገው ለፈፉ። ጋርቬይም የራሱን ሞት መርዶ በሚያነብባቸው ጋዜጣዎች ላይ ሲረዳ፤ በከፍተኛ ድንጋጤ ለሁለተኛ ጊዜ ስትሮክ አጋጥሞት የህይወቱ ፍፃሜ ሆነ።

በኖቬምበር 1964 እ.አ.አ. የማርከስ ጋርቬይ አስከሬን ከተቀበረበት እንግሊዝ ተነስቶ በጃማይካ የጀግኖች መካነ-መቃብር እንዲያርፍ ተደረገ።

በጁን 1965 እ.አ.አ. የጥቁሮችን መብቶች ለማስፈን ባደረገው ሰላማዊ ትግል የሚታወቀው ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር፤ ጃማይካን በጎበኘበት ወቅት የማርከስ ጋርቬይን መቃብርንም ጎብኝቷል። ባደረገው ንግግርም “እሱ ማለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቁር አሜሪካውያን ለራሳቸው ክብር እንዲኖራቸው እና ዕጣፈንታቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ ታላቅ እንቅስቃሴ የፈጠረ የመጀመሪያው ሰው ነው” ብሏል።

የቬትናሙ ኮሚዩኒስታዊ አብዮተኛ ሆቺ ሚን በአንድ ወቅት ሲናገር “በአሜሪካ በነበርኩበት ጊዜ ጋረቬይ እና የኮሪያ ብሔርተኞች የፖለቲካ አመለካከቴ ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ፈጥረውብኛል” ብሏል።

በ1980ዎቹ የጋርቬይ ሁለት ልጆች የአሜሪካ መንግሥት የጋርቬይን ክሶች እንዲያነሳ ጥያቄ የሚያቀርብ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። በ2006 እ.አ.አ. የጃማይካ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት ፖርሻ ሲምፕሰን ሚለር ብዛት ያላቸው የጃማይካ ጠበቆች እንቅስቃሴውን እንዲደግፉ አዝዘው ነበር። የባራክ ኦባማ መንግሥት ግን በ2011 እ.አ.አ. የማርከስ ጋርቬይን ክስ አላነሳም ሲል መልስ ሰጥቷል። ለውሳኔው ያቀረበው ምክንያት ደግሞ፤ የሞቱ ሰዎችን ክስ የማንሳት ኃላፊነት የለብኝም የሚል ነው።

ጋርቬይ እና ኢትዮጵያ

በራስተፈሪያኒዝም እምነት ተከታዮች ጋርቬይ እንደ ነብይ የሚታይ ነው። “ከአፍሪካ አንድ ጥቁር ንጉስ ይነሳል” ያለበት ንግግሩ ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መምጣት የተነገረ ትንቢት ተደርጎ በራስተፈሪያን አማኞች ዘንድ ይታመናል። ማርከስ ጋርቬይ ጁንየር እና አፄ ኃይለሥላሴ በታሪክ አጋጣሚ በተመሳሳይ ዘመን በእንግሊዝ ኖረዋል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሁለቱ መገናኘታቸውን የሚያመላክት መረጃ አላገኘም። ነገር ግን ማርከስ ጋርቬይ የንጉሡን በእንግሊዝ በስደት መቀመጥ አልወደደውም ነበር። ንጉሡ ወደሃገራቸው ገብተው መዋጋት አለባቸው የሚል ሐሳብ ነበረው። አጼ ኃይለሥላሴም ከጋርቬይ ህልፈት አንድ ዓመት በኋላ ወደሃገራቸው ተመልሰው ተዋግተው እና አዋግተው በእንግሊዝ እርዳታ ጣሊያንን ድል አደረጉ።

ሌላው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የጋርቬይ ተዛምዶ፤ በዩ.ኤን.አይ.ኤ መዝሙር ውስጥ ያለው ነው

Ethiopia, thou land of our fathers, Thou land where the gods loved to be, As storm cloud at night suddenly gathers Our armies come rushing to thee. We must in the fight be victorious When swords are thrust outward to gleam; For us will the vict’ry be glorious When led by the red, black, and green.

— Lyrics from the UNIA anthem

ኢትዮጵያ የአባቶቻችን ሃገር

አማልክቶች ሊኖሩባት የሚወዷት የተበታተነው ደመና ሊዘንብ በምሽት እንደሚሰባሰበው የእኛም ሰራዊቶች ተሰብስበው እየገሰገሱ ይመጣሉ። ሰይፎች ወደላይ እየጠቆሙ ስለታቸው ሲያበራ ለእኛ ይሆናል ድሉ የሚያኮራ እየተመራን በቀይ በጥቀር አረንጓዴ ባንዲራ

– የዩ.ኤን.አይ.ኤ መዝሙር ግጥም

ከአንድ ዘመን ህይወት በላይ ፋይዳ ያለውን እና እሱ ራሱ ጀግና ሆኖ ለብዙ ከእሱ ቀጥለው በመጡ ትውልዶች ላይ ጀግና ለሆኑ ሰዎች አርአያ የሆነውን ማርከስ ጋርቬይ ጁንየር፤ በቂ ባይሆንም ህይወቱን በአጭሩ አስቃኝተናችኋል። ስለማርከስ ጋርቬይ ፍልስፍናዎች እና ስራዎች ለብቻቸው ትኩረት ሰጥተን በሌሎች ጽሁፎች እንመጣለን። ቸር ቆዩን!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top