በላ ልበልሃ

ዓባይና ሐይማኖት በኢትዮጵያና ግብጽ ግንኙነት

የኢትዮ-ግብፅ ሺህ ዘመናት የዘለቀ የግንኙነት ታሪክ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ጉዳይ የውሃ ፍላጎት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ያም ሆኖ ግን ይህንን እውነት ዋነኛ ጉዳያቸው አድርገው በይፋ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የጀርባ ድብቅ ፍላጎት በማድረግ ዲፕሎማሲያዊ መስመራቸውን በሌላ መንገድ ሲያከናውኑ ረጅም ዘመናትን ኖረዋል። በዚህ መንገድ የተዘረጉ ሁሉም ዓይነት የግንኙነት መስመሮቻቸው ውስጣዊ ዓላማቸው የጀርባ ፍላጎታቸው ዐብይ ትኩረት የሆንው የውሃ ፍላጎትን ማሳካት መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።

ሁለቱ አገራት ያካበቱት የሺህ ዘመናት የግንኙነት ታሪክ መሰረት ከጣለባቸው መንገዶች መካከል ደግሞ ሀይማኖታዊው መስመር ከዋነኞቹ ተርታ ይመደባል። ከላይ ከተጠቀሰው እውነታ አንፃር ሲቃኝ ይህ የግንኙነት ታሪክም ከመንፈሳዊ ፍላጎቱ ይልቅ የጀርባ ፍላጎት ማረፊያ የሆነው የወሃ ጉዳይን ዐቢይ ትኩረቱ እንደሚያደርግ መገመት ቀላል ነው።

ይህ ጽሑፍ በኢትዮ ግብፅ ግንኙነት ውስጥ ሰፊ ድረሻ ያላቸውን ሁለቱ አንጋፋ ዕምነቶች /ክርስትናና ዕስልምና/ በዚህ የታሪክ እውነታ ውስጥ የነበራቸውን ሚና ይቃኛል። ጽሑፉ የሁለቱ ሀይማኖት ታሪክን የመዘገብ ዓላማ የለውም። ነገር ግን ሀይማኖቶቹ በሁለቱ አገራት የግንኙነት ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ አበርክቶ ያላቸው በመሆኑ ዘገባው ሀይማኖታዊ ታሪኮቹን ለተነሳበት ጭብጡ በሚጠቅም መንገድ ብቻ የሚዳስሳቸው ይሆናል።

ፅሑፉ ‹‹The Cross and The River›› የተሰኘው በሃጋይ ኤርሊች የተፃፈውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ፤ «ቅድስት አገር» በሚል ርዕስ የተሰናዳው የአማከለ ገበየሁ መጽሐፍ፤ በሀብተሥላሴ የተፃፈውን «የኢትዮጵያ ጥንታዊና መካከለኛው ዘመን ታሪክ» ዋነኛ የመረጃ ግብዐቱ አድርጎ ተጠቅሟል። በመረጃ ምንጮቹ ምክንያት የዘመን አቆጣጠሮቹ የጎርጎርሲያውያኑን ቀመር ተከትለው ተዘግበዋል።

በክርስትና ዕምነት

ግሪካዊው ፍሬምናጦስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ333 ዓመት አካባቢ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ አቅንተው ስልጣነ ጵጵስና በማግኘት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ፓትሪያርክ ለመሆን እንደበቁ ታሪክ ይናገራል። ለፍሬምናጦስ ስልጣነ ጵጵስናውን ያቀዳጁት የግብፁ ፓትርያርክ አትናሲየስ ናቸው። እኚህ ፓትርያርክ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተመለከቱትን ሀይማኖታዊ ቅንዓትና ፅናት ሲነግሯቸው በታሪኩ በእጅጉ ለመመስጥ በቅተዋል። በዚህ ምክንያት ፍሬምናጦስን የዚህች ቅድስት አገር ክርስትና ዕምነት አባት ሆነው እንዲያገለግሉ ያግባቧቸዋል። ፍሬምናጦስም በሃሳባቸው ተስማምተው ስልጣነ ጵጵስናን በመቀበል የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። በንጉሡ ችሎት ዘንድም ማዕረጋቸው ተቀባይነት አግኝቶ «አቡነ ሰላማ» ተብለው በመሰየም የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ሆነው እንደተሾሙ ታሪክ ይነግረናል።

የታሪክ መዛግብቱ ይህ ክስተት ኢትዮጵያና ግብፅ በክርስትና ዕምነት የተሳሰሩበት የመጀመሪያው መሰረትን ሊጥል እንደበቃ ያስረዳሉ። የአቡነ ሰላማ ሹመት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ መሪ ፓትሪያርክ የምትሾምበትን ዘልማዳዊ ሥርዓት መዘርጋቱም በስፋት ይነገራል። የአቡነ ሰላማ ሞትን ተከትሎ ግብፅ «አቡነ ሚናስ» የተባሉ ፓትሪያርክ ሾማ ለመላክ የበቃችውም በዚህ ዘልማዳዊ ስልጣኗ በመጠቀም መሆኑ በታሪክ ተዘግቧል።

«ልማድ ውሎ ሲያድር ግዴታ ይሆናል» የሚባለው ደርሶ የግብፅ ኮፕቲክ ቤ/ክ በዚህ አጋጣሚ የተቆናጠጠችው ስልጣን ውሎ ሲያድር ወደ አስገዳጅ ህግነት ተለውጧል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በግብፅ ኮፕቲክ ቤ/ክ ሞግዚትነት ስር የምትተዳደርበት ግዴታም እንዲወድቅባት አድርጓታል።

ይህ ግንኙነት የዕስልምና ዕምነት በመካከለኛው ምስራቅ በጥንካሬና በስፋት መስፋፋት በጀመረባቸው ዘመናት የተወሰነ መንገራገጭ ቢገጥመውም ጨርሶ ሊበጠስ አልቻለም። ይልቁንም ይበልጥ የሚጠብቅበት ዕድል እንዲፈጠር አድርጎታል። «ይህ የሆነው ዕስልምና በአጠቃላይ መካከለኛው ምስራቅ ከትስፋፋባቸው ከ630 ዓመትና ግብፅን ከተቆጣጠረበት ከ640 ዓመት ወዲህ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ጠብቆና ተጠናክሮ መገኘቱ ለሁለቱም ወገኖች ህልውና ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ ነው» ሲሉ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ዕስልምና በመካከለኛው ምስራቅ ተጠናክሮ መስፋፋቱ ኢትዮጵያ በዚህ አካባቢ የነበራትን የፖለቲካ ተፅዕኖ እንዲዳክም አድርጎታል። ከዚህም አልፎ አገሪቱ ከአካባቢው ጋር ያላትን መንፈሳዊ ግንኙነት ጨርሶ ሊበጣጥሰው በቅቷል።ኢትዮጵያ ለዘመናት ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር መስርታው የቆየችው መነፈሳዊ ግንኙነትን ለማስቀጠል ስትል እንደ ጥሩ አጋጣሚ የተጠቀመችው ከግብፅ ኮፕቲክ ቤ/ክ ጋር የነበራትን የጠበቀ ግንኙነት ነበር።በዚህ የግንኙነት መስመር የተገኘው የግብፅ ኮፕቲክ ቤ/ክ ወዳጅነትን ምርኩዝ በማድረግ ያጣችውን የመካከለኛው ምስራቅ መንፈሳዊ ግንኙነት የማስቀጠል ዘዴን በተሳካ መንገድ ለጥቅም መዋሏ ነው የሚነገረው።

በግብፅ በኩልም ይህ ግንኙነት የሚፈለግባቸው ምክንያቶች ነበሩት።የአገሪቱ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ኢትዮጵያን ዋነኛ የዕምነታቸው እሴት አድረገው ይቆጥሯታል። በአገራቸው የዕስልምና ዕምነት መስፋፋቱን ተከትሎ ኮፕቲክ ቢ/ክ ለዕምነቱ ዕውቅና በመስጠት ተቻችላ የምትኖርበትን ዕድል ለማግኘት በቅታለች።በግብፅ የተመሰረተው ዕስላማዊ መንግስት በበኩሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከኢትዮጵያ ጋር የመሰረተችው የቆየ ዝምድና እንዲቀጥል ፈቅዷል። ያም ሆኖ ፍቃዱ የሚፀናው ኢትዮጵያ የምታቀርበው የጵጵስና ሹመት ጥያቄ በመንግስቱ በኩል የሚያልፍበት አሰራር ሲዘረጋ እንደሆነ የሚያትት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

የታሪክ ድርሳናት የግብፅ እስላማዊ መንግስት የአገሩ ክርስቲያኖች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዲቀጥል የፈቀደበት ምክንያትን ሲተነትኑ ግብፅ በዚህች ምድር ያላትን የውሃ ፍላጎት ዋነኛ ሰበብ አድርገው ያስቀምጡታል። «የናይል ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን በመቆጣጠር የውሃ ተጠቃሚነታቸውን ከስጋት ነፃ የማድረግ ፍላጎት የወለደው ስልት ነው» በማለት። ለዚህ ፍላጎት ስኬት ደግሞ ከሀይማኖት የበለጠ ምቹ ዕድልና አጋጣሚ ፈፅሞ አይገኝም።

ግብፅ ከዕስልምና መስፋፋት በኋላ ባለው ታሪኳም ይህንኑ ክርስቲያናዊ ግንኙነት አጠናክራ የማስቀጠሉ ተግሩሯን ይበልጥ አጠናክራ የገፋችበት ለዚሁ ነው። ፍላቱቷን ለማሳካት ይረዳት ዘንድ ኢትዮጵያ ከሀይማኖታዊ ጥገኝነቷ እንዳትላቀቅ ይበልጥ የከረሩ ስራዎችን ስታከናውንም ተስተውላለች። በዚህ ረገድ በተለይም በአስራሰባተኛው ክ/ዘ አጋማሽ የተከናወነው ግብፃዊ ሴራን ታሪክ ዋነኛ ዋቢ ማጣቀሻው አድርጎ ያቀርበዋል።

በዚህ ወቅት የተፈፀመው ሴራ ትኩረቱን ያደረገው ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የሚተዳደሩበትን «ፍትሐ ነገሥት» የተሰኘ የህግ ሰነድ ነው። ሰነዱ አል ሳፊ ኢብን አል አሳል በተባለ የግብፅ ኮፕቲክ ቤ/ክ ሊቅ በ1238 በዐረብኛ ቋንቋ የተሰናዳ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ህገ መንግስት በአፄ ዘርዕያ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት /ከ1434 – 1468/ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥርዓቷ መመሪያ እንዲሆን ተቀብላዋለች። ሰነዱ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ ቋንቋ እንዲተረጎም ያስቻሉት ደግሞ /ከ1667 – 1682/ አገሪቱን ያስተዳደሩት ንጉሥ አፄ ዮሐንስ ቀዳማዊ ናቸው። ግብፅ በ325 የኒቂያው ጉባኤ ያገኘችውን የእውቅና ማረጋገጫ ፅሑፍ ትርጉም በማዛባት ፍላጎቷን አስጠብቃ የምትዘልቅበትን ሴራ የተገበረችው ይህንን የ«ፍትሐ ነገሥት» ትርጉም ስራ ተጠቅማ መሆኑን ትንታኔዎቹ ያስረዳሉ።

ለትርጉም ማዛባት ሴራ የተጋለጠው የፍትሐ ነገሥቱ ሰነድ የግዕዝ ትርጓሜ አንቀፅ 42 ቀጥሎ የተጠቀሰው ቃል እንዲሰፍርበት ተደርጓል።

«ኢትዮጵያውያን ፓትሪያርካቸውን ከራሳቸው ሊቃውንት መካከል መርጠውም ይሁን በራሳቸው ፍቃድ መሾም አይችሉም።ሀይማኖታዊ ግዛታቸው ተጠሪነቱ በአካባቢውና በራሱ ግዛት የዕምነት መሪዎቹን የመሾም ስልጣን ለተሰጠው ለአሌክሳንድርያው ቤ/ክ ነው።ተጠቃሽዋ ቤ/ክ በራሷ ፍቃድ የምትሾመው ፓትሪያርክ በሌሎች ግዛቶች የተሾሙ ፓትሪያርኮች የተሰጡት ፀጋ እንዲኖረው አይፈቀድለትም።የፓትሪያርክነት ክብር ይኖረው ይሆናል እንጂ ስልጣኑን ፈፅሞ አይቀዳጅም።»

ግብፅ በኢትዮጵያ የተቀዳጀችው የክርስትና ሀይማኖት የበላይነት ስልጣን በዚህ መልኩ የህግ ትርጉም እስከ ማዛባት በደረሰ የተቀነባበር ሴራ ተከናውኗል። ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መሪ የሚሆነውን ፓትርያርክ ሾማ የምትለከው በአሌክሳንድርያው ፓትሪያርክና በአገሪቱ እስላማዊ መንግስት / ሱልጣን/ ምክክርና ፍላጎት በመመራት መሆኑ ሲታሰብ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የጥቅም ፍላጎት ስጋት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ይህ ሁሉ የተደረገበት ዋና ምክንያት ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ባላት የውሃ ፍላጎትና ስጋት ሰበብ መሆኑንም ገምቶ ድምዳሜ መስጠት ስህተት አይኖረውም።

የግብፅና ኢትዮጵያ ግንኙነት ከክርስትና ዕምነት አንፃር ተቆላልፎ የተሳሰረበት ይህንን መሰሉ መስመር በየመሃሉ ገባ ወጣ ቢያጋጥመውምና መደነቃቀፎችን ቢያስተናግድም ለ1600 ዓመታት ያህል ዘልቆ ቆይቷል። በዚህ እረጅም ዕድሜው 111 ኮፕቲክ ፓትሪያርኮች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መንበረ ፓትሪያርክ ላይ ተሰይመው የግብፅን የውሃ ፍላጎት ዓላማ ሲያስፈፅሙ ቆይተዋል። ይህ ታሪክ በግብፅ ዘመነ ናስርና በኢትዮጵያው የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት ዳግም ላይጠገን ሆኖ በ1959 ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተበጣጥሶ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያኗን ከግብፅ ጥገኝነት ነፃ አውጥታለች። ይህ ድል እንዲገኝ ሰበብ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የውሃና ወንዝ ጉዳይ ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ይነገራል። አብያተ ክርስቲያኑን ያስተሳሰራቸው የጀርባ ምክንያት ሚናውን ቀይሮ ለመለያየታቸውም አንኳር የጀርባ ሰበብ ሆኖ ተገኝቷል።

በዕስልምና ዕምነት

«የመጀመሪያው ስደት /ሂጅራ/» ተብሎ በዕስልምና ዕምነት የሚታወቀው የዕምነቱ ተከታዮች የስደት ታሪክ መዳረሻው ኢትዮጵያ ነበረች። በዕምነቱ ታላቅ ነቢይ መሀመድ መመሪያ ተከታዮቻቸው ያደረጉት የሽሽት ስደት።ኢትዮጵያም ነብዩ በመጠለያነት አምነው የላኳቸው ተከታዮቻቸው /ሳሃባ/ን በአክብሮት ተቀብላ፤ ለዕምነታቸውም ዕውቅና ሰጥታ በማስጠለል በገዛ አገራቸው ከተነሳባቸው የክፉዎች የጥፋት ፍላፃ ታድጋቸዋለች።

ነብዩ ክርስቲያኒቷ አገር ኢትዮጵያ ለዕምነታቸው የሰጠችው ዕውቅናና ተከታዮቻቸው የተደረገላቸው የክብር አቀባበል እንዲሁም የተሰጣቸው ቦታ ለዚህች አገር ከፍ ያለ የክብር ቦታ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። የእርሳቸው ቃል በተዘገበበት ቅዱስ መዝገብ /ሀዲስ/ ላይ ‹‹Utruku al-habasha ma tarakukum (Leave the Abyssinians alone as long as they leave you alone)›› «አቢሲኒያውያንን እስካልነኳችሁ ድረስ እንዳትነኳቸው» የሚለው ቅዱስ ቃላቸው ለዚህ አባባል ዋነኛ አስረጂ ሆኖ ይጠቀሳል። ያም ሆኖ ይሄው ቃል በተለያዩ ፅንፈኛ የዕምነቱ አክራሪዎች ዘንድ በተዛባ ሁኔታ ተተርጉሞ ኢትዮጵያ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ለመንዛት ጥቅም ላይ ሲውል የታየባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ይህም ቅዱሱ የነብዩ ቃል ትርጉም የተምታታ ግንዛቤ እንዲፈጠር እንዳስገደደው የታሪክ አጥኚዎች ያስረዳሉ።

በእርግጥ ይህ ቅዱስ ቃል በአብዛኛው የዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቀጥተኛ ትርጉሙ ተወስዶ ዕውቅና ተስጥቶታል። በዚህ አተረጓጎም መሰረት ኢትዮጵያ የዕምነቱ ተከታይ ምድር ባትሆንም እንኳን ልትነካ አንደማይገባት ግንዛቤ ተወስዶ እንደ መመሪያ እያገለገለ ይገኛል። ነብዩ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ለኢትዮጵያ ያላቸው ልዩ ፍቅርና አክብሮትን ለማሳወቅና ለውለታዋ ቦታ ለመስጠት እነደሆነም በስፋት ይነገራል።

የነብዩ መልዕክት ስለ ኢትዮጵያ የተናገረው ቃል እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘልቆ በዕምነቱ ዓለማቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ የሚያስረዱ በርካቶች ናቸው። «በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የዕስልምና ዕምነት መሪዎች ዕስልምና ዕምነት ተከታይ ባልሆኑ አገራት በነፃነት ዕምነታቸውን እያራመዱ መኖር እንደሚችሉ የሚሞግቱበት ሃሳብ ዋቢ የሚያደርገው ይህንን የነብዩ ቃልና የኢትዮጵያን ታሪክ ነው» ሲሉ የዚህ ኢትዮጵያዊ የነብዩ ቃል ተገዢ አማንያንና ተንታኞች ፋይዳውን ያስረዳሉ።

በሀዲስ መዝገብ የተገለፀው የነብዩ መልዕክት የተጠቀሰውን አይነት እስላማዊ ፋይዳ በማበርከት በኩል ያለው አስተዋፅዖ ተቆጥሮ አያልቅም። እንደ እንግሊዛውያኑና አሜሪካውያኑ ሁሉ በእስራኤል የሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች የእነርሱ አምሳያ አማንያን በማይገኙባት ምድር ዕምነታቸውን እያራመዱ የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ የተሟገቱበት ሃሳብም ምርኩዝ ያደረገው ይህንኑ አስተምህሮ መሆኑን መጥቀስም አስፈላጊ ይሆናል።

ለዘብተኛዎቹ የእስራኤል ሙስሊሞች በ1990 በአገሪቱ መንግስት ዕምነታቸው ዕውቅና እንዲያገኝና ነፃነቱ እንዲረጋገጥ ጥያቄ ሲያቀርቡ «የእስራኤል መንግስት የሳሃባን መስመር ሊከተል ይገባል» የሚል ሃሳብን ዋነኛ መሟገቻቸው አድርገው ነበር። ተሳክቶላቸውም የዕምነት ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ መቻላቸውን የቅርብ ጊዜ የታሪክ መዛግብት በሰፊው ዘግበውታል።ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ሳንወጣ በተመሳሳይ የተወሰኑ የቅርብ ታሪክ እውነታዎችን በአጭሩ ማሳየቱ ለርዕሰ ጉዳያችን መዳበር ጠቃሚ በመሆኑ ቀጣዮቹን የታሪክ እውነታዎች በወፍ በረር አቅርበናቸዋል።

አንዋር ሃዳም በአልጄሪያ ይንቀሳቀስ የነበረ እስላማዊ የነፃነት ግንባር መሪ ነው። ይህ ታዋቂ የነፃነት ታጋይ በአገሩ ከተፈጠረበት የማሳደድ ጫና ለመላቀቅ ስደትን እንደ መፍትሔ ወስዶ በ1994 ላይ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኮብልሏል። አንዋር ሃዳም ለእስልምና ኃይሎችና የነፃነት ታጋዮች ቅን አመለካከት ወደማይታይባት አገር ሲሰደድ፤ መልካም አቀባበል እንደማይጠብቀው እርግጠኛ ነበር።ያም ሆኖ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ በመንግስት በኩል ባልተለመደ ሁኔታ ፈጥኖ ተቀባይነት አግኝቷል።

ሃዳም በአሜሪካ ያገኘው ያልጠበቀው ምላሽ እጅግ አስደስቶት «ክሊንተን ልክ እንደ ኢትዮጵያው ንጉሥ ናቸው። እስልምና አደጋ በገጠመው ጊዜ ነብዩ በሰጡት መመሪያ ተከታዮቻቸው ሸሽተው መጠለያ እንዳገኙባት አገረ ኢትዮጵያ ንጉሥ አል ነጃሺ ያለ ቅን ሰው» ሲል ተናግሯል።

ሌላው ተመሳሳይ ሁኔታ የተከሰተው በፍልስጤም ነው። በ1996 ያሲር አራፋት የሚመሩት የፍልስጤም አስተዳደር መመስረቱ ይታወቃል። አራፋት በእስልምና ዕምነት ላይ የሚከተሉት አመለካከት ለዘብተኛ በመሆኑ፤ የመሰረቱትና የሚመሩት የፍልስጤም አስተዳደር ከዕስልምና የተለየ ዕምነት ለሚያራምዱ ህዝቦችም መኖሪያ መሆኗን ለማረጋገጥ ችግር አልገጠማቸውም። ነገር ግን የአራፋት ዕርምጃ ስጋት በማሳደሩ በገለልተኛ ወገን እንዲጠና አስገድዷል። የአራፋት ለዘብተኛ አመልካከትና አመራር የመሰረታት የፍልስጤም አሰተዳደርን ጉዳይ ከዕስልምና ፍላጎትና ጥቅም አንፃር ለማጥናትም የአገሪቱ ልሂቃንን ያካተተ የጥናት ቡድን ውሎ ሳያድር የተመሰረተው በዚህ ምክንያት ነው።

ይህ ቡድን የአራፋት አስተዳደርን እርምጃ ለፍልስጤማውያንና ለዕስልምና ዕምነት ካለው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ አንፃር በሰፊው ጥናት አድርጎበታል። ይህንን ተከትሎም የአራፋት ለዘብተኛ አስተዳደር ቅቡልነትን የሚያትት ባለ ሰባ ገፅ አመክንዯዊ ፅሑፍ ይፋ አድርጓል። ጥናታዊ ፅሑፉ ለዚህ ሃሳቡ ማሳያ አድርጎ በዋናነት ያቀረበው የነብዩ መሐመድንና የኢትዮጵያዊው ንጉሥ አል ነጃሺ ላይ ያተኮረውን ታሪክ እነደ ዋና አስረጂ በማሳየት ነው። ጥናቱ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ከአስራ አንድ ገፅ በላይ ሃተታ ያቀረበ ሲሆን፤ ሁሉን አካታች አገር የመመስረት አስፈላጊነት በነብዩ እና በኢትዮጵያዊው ንጉሥ ታሪክ በአግባቡ የተቀመጠ መሆኑን በማውሳት ይህንኑ ለአራፋት ውሳኔ ቅቡልነት አስረጂ አድርጎ አቅርቧል።

የታሪኩ እውነታዊና አዎንታዊ ገፅታ ሲጠቃለል «ኢትዮጵያውያንን ተዋቸው» የሚለው የነብዩ ቅዱስ ቃል የሌላ ዕምነት አማንያን አገራትን ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት የተቀበለ መሆኑን የሚያረጋግጥ እጅግ ጠቃሚ ሃሳብ የያዘ ነው ብሎ ድምዳምሜ መያዝ ይቻላል። ከኢትዮጵያ አንፃር ደግሞ አገሪቱ ዕምነቱ በጠላቶቹ ጥቃት እንዳይጠፋ በመታደግ ረገድ ያበረከተችውን በጎ አስተዋፅዖ በማረጋገጥ በዕስልምናና በኢትዮጵያ መካከል እጅግ የደመቀ የታሪክ ቁርኝት መኖሩን እነደሚያረጋግጥ መናገርም ስህተት አይኖረውም።

ይህ የዕምነቱን በጎ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠብቅ ታሪክ በዚያው በነብዩ ዘመን መከሰቱም ኢትዮጵያና ዕስልምና በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ትስስር እንዳላቸው ያረጋግጣል። በዚህ ረገድ በዕምነቱ አስተምህሮ የነብዩን ጥሪ ፈጥኖ ለመቀበል ሦስተኛው ሰው እንደሆነ የሚነገርለት የቢላል ታሪክ ተጠቃሽ ነው። ኢትዮጵያዊው ቢላል በሰጠው ፈጣን ምላሽ የዕምነቱ የፀሎትና ስግደት ጥሪ የሚያሰማ /ሙዓዚን/ ሆኖ ለመሾም በቅቷል። ነብዩም በሀዲስ ላይ ባሰፈሩት ቃል የፀሎት ጥሪን የማሰማቱ ኃላፊነት ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ፀጋ መሆኑን አረጋግጠዋል። ከዚህ በላይ ከብዙ በጥቂቱ የተዘገቡ የታሪክ እውነታዎች ኢትዮጵያ በዕስልምና ዕምነት ውስጥ አቻ የሌለው አንፀባራቂ ታሪክ የተቀዳጀች አገር መሆኗን በግልፅ ያረጋግጣሉ። ያም ሆኖ በአክራሪና ፅንፈኛ ኃይላት በኩል ይህ ታሪኳ ተበርዞና ተከልሶ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ የጥላቻ ዘመቻ ሲካሄድባት የታዩባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው። ፋሺስቱ የሞሶሎኒ ሰራዊት በኢትዮጵያ ላይ የቅኝ ግዛት ወረራ ባካሄደ ጊዜ የተፈጠረውን ሁኔታ ማሳየት ለዚህ አባባል ጥሩ አስረጂ ይሆናል።

ሻኪብ አርሰናል የተባለው ግለሰብ ሶሪያዊ ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ ነው። ይህ ሰው በዘመነ ቅኝ ግዛት ወቅት በዐረቡ የዕስልምና ዕምነት ውስጥ አከራካሪና አወዛጋቢ የሆኑ ፅሑፎችን በማውጣት በፈጠረው ሰፊ ተፅዕኖ ከፍ ያለ ስምና ዝና ተቀዳጅቷል። ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን በወረረበት በ1935 በዐረቡ ዓለም በስፋት በሚሰራጩ የህትመት ውጤቶች ላይ ኢትዮጵያን የሚያጥላላና የሞሶሎኒ ዘመቻን የሚደግፉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፅሑፎችን ለንባብ አብቅቷል።

የዚህ ታሪክ ተመራማሪና ጋዜጠኛ ፅሑፎች ለከፈቱት ፀረ ኢትዮጵያ የጥላቻ ዘመቻ ዋነኛ መሰረታቸው ያደረጉት የዕስልምና ዕምነት ታሪክን ማዛባት ነው። ከአል ሃበሻ የነብዩ ተከታዮች ስደት ዘመን አንስቶ «ተፈፅመዋል» የሚሏቸውን ኢትዮጵያዊ የዕምነቱ በደሎች እየዘረዘረ አገሪቱን ክፉኛ ተችቷል። ይህ ፀረ ኢትዮጵያ ዕስላማዊ ታሪክ የተቀረፀበት የሀሰት ትርክቶች ወዲያውኑ በግብፅ የዕምነቱ አክራሪ ኃይሎች በኩል ከፍ ያለ ተቀባይነት አግኝተው ይበልጥ ሲራገቡ መታየቱን ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። እነኚህ ኃይሎች የፀሐፊውን ፈለግ ተከትለውም ኢትዮጵያን ከመካከለኛው ምስራቅ የዐረብ አገራትና ከዕስልምና ዕምነት ጋር ለማጋጨት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል።

ይህ የጥላቻ ዘመቻ ኢትዮጵያ ዕስልምናን በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ጭምር እንዳይስፋፋ ተፅዕኖ ማሳደሯን ይተርካል።ትርክቱ በነብዩ የተነገረውን «ኢትዮጵያን ተዉአት» የሚለውን ቃል ትርጉም እስከ ማዛባት ዘልቆ «ነብዩ አገሪቱ ለዕስልምና ዕምነት የማትጠቅምና ጠላት የሆነች በመሆኑ አታስፈልጋችሁም ለማለት እንደዚያ ያለ መልዕክት አስተላልፈውልናል» የሚል ፍቺ እንዲይዝ እሰከማድረግ ደርሷል።

ይህ አይነቱ ፀረ ኢትዮጵያ የጥላቻ ዘመቻ አስተሳሰብ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከሚሳተፉ አገራት መካከል ግብፅን የሚስተካከል እንደማይገኝ ተጨባጭ የፅሑፍ አስረጂዎች ያረጋግጣሉ። ከዕስልምና ወረራ ጀምሮ ባለው የታሪክ ሂደቷ የተከሰቱ ፅንፈኛ አስተሳሰብ ያላቸው ኃይላት እንዲህ አይነት የተዛባ መረጃ በመስጠት፤ ዕምነቱን ከአገሪቱ ጋር ለማጋጨት መንቀሳቀሳቸውን የሚያወሱ የታሪክ መዛግብት ስፍር ቁጥር የላቸውም። የዚህ አይነት ሀሰታዊ ትርክት ዋነኛ ሰበብም በግብፃውያን ዘንድ ዳብሮ የቆየው ውሃን የማጣት ስጋት መሆኑን ከፅሑፎቹ ይዘት በቀላሉ መረዳት እንደሚቻል ተንታኞች ያስረዳሉ።

አባባሉን በማስረጃ ለማረጋገጥ ያህል በግብፃውያን ዕድሜ ጠገብ አፈ ታሪክ ውስጥ «ኢትዮጵያ አጠቃላይ የናይል አገራትን በመውረር ታጠፋቸዋለች» የሚል ንግርት ተደጋግሞ ሲነገር መደመጡን ዋቢ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል። ይህ አፋዊ ንግርት በባግዳድ በሚገኝ አብዱላህ ኑ አይ ሚን ኢብን ሃማድ በተፃፈና ዛኪር በተባለ ግብፃዊ በተተረጎመው ‹‹al-futan›› በተባለ መፅሐፍ ውስጥ በገፅ 288 ‹‹The Etheioppians’ invasion›› በተባለው ንዑስ ክፍል በስፋት ሰፍሮ ይነበባል።

በግብፅ በ1980ዎቹ በስፋት ታትሞ የተሰራጨውና በፅንፈኛዎቹ ኃይላት በኩል ከፍ ያለ ተቀባይነት ያገኘው ‹‹Zabiyan, Al- habasha al-muslima›› የተሰኘውን መፅሐፍ መጥቀስም አስፈላጊ ነው። አንፀባራቂው ኢትዮጵያዊ የዕስልምና ታሪክን ሙሉ በሙሉ በተዛቡ ትርክቶች በርዞና ከልሶ በመላው ዐረቡ ዓለም ኢትዮጵያን እንድትጠላ ያካሄደው ዘመቻ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም።

ይህ ሁሉ የግብፅ አክራሪዎች ዘመቻ ደፋ ቀና ዓላማው አንድና አንድ ነው። በውሃ ፍላጎት ላይ ከሚመነጭ እጅግ ስስታምነት ከወለደው ስሜት የሚቀዳ። ፍላጎቱም ኢትዮጵያ በተቀረው ዓለም በተለይም በዕስልምና ዕምነት ውስጥ የተጠላች በማድረግ ድጋፍ ማሳጣት፤ ከዚህም አልፎ የአገሯ ህዝቦች በውሸት ትርክት ወደ ዕምነት ግጭት እንዲገቡ ማድረግ። በውጤቱም ኢትዮጵያ አቅሟ እንዲዳከም በማድረግ በገዛ ውሃዋ እንዳትጠቀም ማሽመድመድ። ለዚህ ፍላጎታቸው ስኬት ደግሞ ሌላው ቀርቶ የታላቁ ነቢይ ቅዱስ ቃላትን ትርጉም እስከ መከለስና መበረዝ የሚደርስ ወንጀል ከመፈፀም እንደማይመለሱ ታሪካቸው በቂ ማረጋገጫ ስጥቷል።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያና ግብፅ ብዙ ሺህ ዘመናት የዘለቀ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው አገራት መሆናቸው እውነት ነው። የዚህ ረጅም ዘመን ታሪካቸው ውስጥ የጎላ ቦታ ይዞ የሚገኘው አንኳር ጉዳይ ዕምነት ላይ የተመሰረተው ግንኙነታቸው መሆኑ አያከራክርም።ጥንታውያን የሆኑት የክርስትናና የዕስልምና ዕምነቶች ለሁለቱ አገራት የግንኙነት ታሪክ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ ይዘው መገኘታቸው በታሪክ የተረጋገጠ ሀቅ ነው።

የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ከውሃ ፍላጎት ግጭት አንፃር የፈተሹ ተመራማሪዎች የግንኙነት ታሪካቸውን በሦስት አበይት ማዕቀፍ ከፍለው ይመለከቱታል። በዚህ ማዕቀፍ ግብፃውያን ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት፤ የዕስላማዊ የግብፃውያን፣ ዘመናውያኑ ብሔርተኛ ግብፃውያን እና የዐረብ አብዮታውያን አመለካከት እንደሆኑ ይገልፃሉ።እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች የተወለዱት የእስላማዊው ፅንፈኞች በፈጠሩት ኢትዮጵያን «የተለዩት እና ሌሎቹ» ግብፃውያንን «የእኛዎቹ» ብለው በፈረጁበት የዐረባውያን ማህፀን ውስጥ እንደሆነ ተንታኞቹ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በዕስልምና ዕምነት ውስጥ ያላት አንፀባራቂ የታሪክ ድርሻ በሀይማኖቱ ወስጥ አወዛጋቢ ሆኖ እስከዚህ ዘመን እንዲዘልቅ የተገደደው በዚሁ የፅንፈኞቹ ሴራ ሳቢያ መሆኑ ይነገራል። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ሌላ ሳይሆን በሁለቱ አገራት መካከል ዋነኛ የጥቅም ፍላጎት መተሳሰሪያ የሆነው የውሃ ጉዳይ ነው።

የተቀረው ዓለም ኢትዮጵያን እንደ ባዳ ግብፃውያንን ደግሞ እንደ ወገን በመቁጠር ለወገኑ ያደላ ፍርደ ገምድል እንዲሆን ከሚመኝ ፍላጎት የመነጨ ሴራ እንደሆነ መዛግብት በስፋት አትተውበታል። ባዕዳኑን ለማውገዝና ለማግለል፤ ወገንን ደግሞ ለመደገፍና ለመጥቀም ደግሞ ሀይማኖትን ምርኩዝ አድርጎ መንቀሳቀስን ያህል አዋጭ መንገድ እንደማይገኝ ግብፃውያኑ አክራሪዎች አሳምረው መረዳታቸውን እነኚህ አስረጂዎች ይናገራሉ። ለዚህም ነው ዕምነትን ምርኩዝ አድርጎ የተፈጠረው የተዛባና ሃሰተኛ ትርክት እስከዚህ ዘመን ድረስም በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር እየታየ የሚገኘው። ለዚህ ችግር ግብፅ ብቻዋን ተወቃሽና ተከሳሽ ልትሆን እንደማይገባት ግን ሁሉም ይስማማሉ። ኢትዮጵያም ብትሆን እንዲህ ያሉ አሉታዊ የጥፋት ዘመቻዎች ሲከፈቱባት ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት ረገድ ደካማ ሆና መገኘቷም፤ ለሀሰተኛው ትርክት መጠናከር የራሱ ድርሻ ስለሚኖረው። ኢትዮጵያ በዕስልምና ዕምነት ውስጥ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የማይነፃፀር ከፍ ያለ አንፀባራቂ ታሪክ የተጎናፀፈች ምድር መሆኗ ዕሙን ነው። ያም ሆኖ ይህንን ታሪካዊ ኩራትና ክብሯን በአግባቡ ባለመጠቀሟ የሚገባትን የክብር ቦታ ሳታገኝ ቀርታለች።

«በእርግጥም ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች መካከል የፈጠረችውን መተኪያ አልባ የተቀባይነትና የተከባሪነት ቦታ፤ በመካከለኛው ምስራቅና በመላው የዕስልምና አማንያን አገራት ውስጥ ልታገኝ የምትችልበት ዕድሏ ሰፊ ነበር» የሚሉ ትንተናዎች፤ ነገር ግን አገሪቱ ለገዛ ታሪኳ ትኩረት ባለመስጠቷ በግብፃውያኑና በተቀሩት ዐረባውያኑ አክራሪዎች የሀሰት ዘመቻ ተበልጣ የመገኘቷ ሰበብ ይሄው መሆኑ በስፋት ያትታሉ።

አሁንም በዚህ ረገድ የአገሪቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ሰፊ የቤት ስራ ይጠብቀዋል። ታሪክ ኖሮት ቀርቶ ታሪክ ቀምቶ የሚያቅራራ በተበራከተባት ዓለም ታሪካዊ ሀብትን በአግባቡ ሳይጠቀሙ ሌሎችን መውቀስና መክሰስ ፋይዳ አይኖረውም። ኢትዮጵያ ይህንን ልትገነዘብና አትኩራም ልትንቀሳቀስበት ይገባል፤ ባይ ናቸው ተንታኞቹ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top