ከቀንዱም ከሸሆናውም

ነገረ ውሻ

ዉሻ ይወዳሉ? ገዝተውስ ያውቃሉ? በኢትዮጵያ ነጠላ ውሻ ምን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ ይመስሎታል? ስለ ውሻስ ግንዛቤዎ ምን ድረስ ይሆን?

ሀሳብ እየተምዘገዘገ አእምሮዬ ጓዳ ላይ ይመላለሳል፡፡ ሀሳቤን በደርዝ በደርዝ ለመሰተር ቀኑ ድብርት የጠራብኝ መሠለኝ፡፡ ድብረቴን ድራሹን ለማጥፋት ቡና ደጋገምኩበት፡፡ ሆኖም ያው ነው፡፡ አጅሬ ድብርት ተጣበቀብኝ፡፡ ” እያዛጋ ቡናዬን ያመክናል እንዴ?” የሚመስል ግልምጫ አከናነበችኝ ቡና በረከቦቷ ሴት፡፡ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ በፍዘት ውስጥ ስንቀዋለል አንድ ሰው ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡ በዓይን አውቀዋለሁ፡፡ የፍንጃል ቡናውን ፉት እያለ ስልክ ተደወለለት፡፡ ጥቂት ሠላም እንደተባባልን አንድ ሌላ ሰው አብሮኝ ለተቀመጠው የታሰረ ገንዘብ አቀበሎት “የታሉ” አለው፡፡ ወዳቆመው መኪናው ሄዶ በሩን ሲከፍት ሁለት ውሾች ወጡና አስረከበው። ገንዘብ ለምን እንደተቀባበሉ ገባኝ፡፡ ድብርቱ ከላዬ ላይ ሲበን ታወቀኝ ፡፡ ለካስ ብዕሬ ውብ ታሪክ ናፍቆ ነበር፡፡

ወዳጄ ወጉን እንደሚከተለው ቀጠለ…

“እነዚህን ውሾች 70 ሺህ ብር ሸጥኳቸው” የግንባሬን መጨማደድ አይቶ “ገረመህ አይደል?” አለኝ። “ታዲያስ” አልኩት፡፡

“ህብረተሰባችን ለውሻ ብዙም በጎ አመለካከት ባይኖረውም አሁን አሁን ግን እየተቀየረና ለውጥ እያሳየ ነው፡፡ “70 ሺህ ስልህ ገርሞሀል። የሚገርምህ 1 ነጠላ ውሻ በተለይ አድጎ ከውጭ የመጣ ከሆነ እስከ 90 ሺህ ይደርሳል። በተለይ የውጭቹ እንደ ጀርመን ሼፐርድ፣ ጎበር ማን እና ፒትቡል አይነቶቹ ውድ ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥ ግን የውጪውን ያህል ተፈላጊ አይደለም፡፡ ግን እነሱም ቢሆኑ በጥሩ ዋጋ ማለትም ከ 20 እስከ 30 ሺህ ይሸጣሉ። እርግጥ ትንንሾቹ ረከስ ይላሉ፡፡ ውሻ እወዳለሁ፡፡ የሚወጣባቸው ዋጋም ያንሳቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ አንተ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰው የሚሸጥበትን ዋጋ ሲሰማ አፉን ይይዛል፡፡ ገንዘቡ ውሻ ለሰው ልጅ በሚሰጡት ፍቅር ልክ ስለማይመዝኑ አልፈርድም፡፡ አንዲት ውሻ ነበረችን፡፡ ስራዋ መብላትና መተኛት ብቻ ሲሆን ከማደሪያዋ መውጣትና እንደሎሎች ውሾች መንሸራሸርና ብትለቃትም ከግቢያችን የመውጣት ፍላጎት አልነበረንም፡፡ ትክክለኛ የቤት እንሰሳ እርሱ ነው፡፡ አንድ ቀን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወጣች፡፡

አባታችን ይህችን አለም ሲሰናበትና ሬሳው ወደ ቤ /ክርስትያን ሲሄድ እንቅልፋሟና ከቤት ባለመውጣት የምትታወቀዋ ቡቺ ድክ ድክ እያለች የአባቴ ሬሳ እስከሄደበት እየጮኸችና እያላዘነች ሸኘችው፡፡ ሬሳውን ስሸኘው ለአብዛኛው ሠው አስለቃሽ እሷው ነበረች፡፡ በቃ ሬሳው ከተመለሰም በኋላ ከግቢ ወጥታ አታውቅም።

ፊን የሚባል ውሻ

በሀገረ እንግልጣር አምና የሆነው ነገር ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል። በእንግሊዝ ብዙ ሺዎች በሚገኙበትና እጅግ ድንቅ ተሰጥኦ በሚታይበት እንዲሁም እንግዳ ክስተቶች የሚመዘገቡበት ከምርጦቹ የአለማችን ታለንት ሾዎች በአንዱ በሆነው Britain Got Talent ጎልመስ ያለ ሠው ከውሻው ጋር ወደ መድረኩ ሲወጣ ሞቅ ያለ አቀባበል ነበር የጠበቃቸው፡፡ የውሻውን ታለንት ለማሣየት ወደ መድረኩ የወጣው ግለሰብ በቪድዮ አስደግፎ ስለውሻው እንዲህ ሲል ነበር የተናገረው ለብዙ አመታት በፖሊስነት ሳገለግል ለ7 ዓመታት ይህ ውሻ አብሮኝ ነበር። አንድ ቀን ስራ ላይ ሆነን አንድ ወንጀለኛ እኔን ለመውጋት 10 ኢንች በሚረዝም ቢላ ሰነዘረ፣ ጉልበት ለመስጠት እጁን ወደ ኋላ አሽሽቶ ወደፊት ላከው፣ ቢላው ሰውነቴ ውስጥ ሳይሰነቀር ውሻዬ ዘለለ፣ 10 ኢንች እሷ ውስጥ ገባ፡፡ ህይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ የኔን ህይወት አተረፈልኝ ፡፡ ከብዙ የህክምና እርዳታ በኋላ ህይወቱ ተርፎ ደስታችንን ይኸው አብረን እናጣጥማለን። ዩቲዩብ ላይ እየው ብሎኝ አንድ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ ላከ

“ይሄ ፍቅር ስንት ብር ይሸጣል?” መልሴን ሳይጠብቅ የቡናችንን ከፍሎ ወጣ።

ልፈዝ ነበር ፣ ብዕሬ ቀለሙ እንዳያልቅ የሠማሁት ታሪክ ከፍተኛ ንቃት አበድሮኝ ከፊልም፣ ከመፅሀፍና ከሶሻል ሚድያ የቃረምኩትን መዓዛ ውሻ እነሆ እላችኋለሁ፡፡

የመጀመሪያ አስትሮናውት ከራሽያ

የመጀመሪያዋ ወደ ስፔስ ተልካ መሬትን የዞረች እንሰሳ ነች፣ ዮሪ ጋጋሪን ትቀድመዋለች፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1957 ዓ. ም ስፑትኒክ ሁለትን ወደ ጠፈር የላከችው ራሽያ አስትሮናዉት ያደረገችው ላይካን ነበር፡፡ ከ4 ቀናት አድካሚ ጉዞ ቦሀላ መሬት ሳትረግጥ ሞት የቀደማት ላይካ በማስኮ ሀውልት ቆሞላታል፡፡ ነፍስ ይማር

ከሞት የሚያድን ውሻ (አሜሪካ)

አንድ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ መሃን ሴት በእግዜር ተዐምር ልጅና ሚስቱን በመኪና አደጋ ላጣው ጎልማሳ ልጅ ወለደችለት፡፡ በዚህ ደስ ያለው አባት በደስታ ለሚስት ባህርዳር አጠገብ የሚገኝ ቤት ገዛላት፣ እሷ ለልጇ ውሻ ገዛች፤

ከእለታት በአንድ በከይሲ ቀን እናት ውሻና ህፃን ልጇን መኝታ ቤት ትታ ወደ ገበያ ሄደች፣ ስትመለስ ልብን ቀጥ የሚያደርግ ነገር አየች፣ ውሻውን አየችው፣ መኝታ ቤት በር ላይ ቆሞ የሆነ ነገር ያመነዥካል፣ አፋ በደም ጨቅይቷል፣ ኪችን ሄደች፣ መጥረቢያ ይዛ ተመለሰች፣ ውሻውን ገደለችበት፣ ይህ ሁሉ ሲሆን ልጇን አላየችውም፣ መጥረቢያውን አስቀምጣ ወደ ልጇ መኝታ ገባች፡፡

ልጁና የሞተ እባብ ነበሩ፡፡

ውሻና ፊልም (ጃፓን)

በሚልየን የሚቆጠሩ ተጓዦች በየቀኑ በሚመላለሱበት ቶክዮ (ጃፓን) የሚገኘው ኪዩባ ባቡር ጣቢያ በኩራት የቆመ የውሻ ሀውልት አለ፡፡ ውሻው በህይወት በነበረ ጊዜ በአንድ የጃፓን ጋዜጣ ላይ ተዘግቦለታል፣ ከመላው ኣለም ተጎብኝቷል፣ ሲሞት በሺህ የሚቆጠር ህዝብ አልቅሶለታል፣ በጃፓንኛና በእንግሊዝኛ ፊልም ተሠርቶለት የፅናትና የፍቅር እንዲሁም የታማኝነት ተምሳሌት ተደርጓል፡፡ እንዴትና ምን ከውኖ ሀውልት ተቀረፀለት? የሚለውን እንደሚከተለው ታሪኩን እንይ፦

በ1924 እ.ኤ.አ ኣንድ ጃፓናዊ የእርሻ ፕሮፌሰር ጤንነቱ ያልተስተካከለ እና ከሲታ ውሻ ተማሪው የነበረ ሠው ያወጣለታል፡፡ ውሻው ስሙ ሀቺኮ ሲሆን ጤንነቱ እንደተስተካከለ ጌታውን ወደ ቶክዮ ዩኒቨርሲቲ ለመሄድ ኪዩባ ባቡር ጣቢያ እሰኪደርሱ ጧት ጧት መከተል እና ሲመለሱ ቀድሞ ጠብቆ ቤት ድረስ መሸኘት እለታዊ ተግባሩ ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩም ወደ ቤቱ እንደሚመለስ ውሻው ሀቺኮም ጌታው መምጣቱን እርግጠኛ በሆኑበት ሠዐት በሺቡያ ፕሮፌሰሩ ቀረ፡፡ እያስተማረ ድንገት ክፍል ውስጥ ተዝለፍልፎ ወድቆ ህይወቱ ያለፈው የሀቺኮ ጌታ ወደ ባቡር ጣቢያው ባይመለስም ሀቺኮ ግን ለ9 ዓመት ከ9 ወር ሲነጋና ሲመሽ ማለትም ባለቤቷ ወደ ስራ በሚሄድበትና በሚመለስበት ሠዐት ባቡር ጣቢያው ጋር መጠበቁ ነበር፡፡ ሊሞት በሚቃረብበት በመጨረሻው አመት እንኳ አይኑ ባለቤቱን ተስፋ ሳይቆርጥ በመጠበቅ ላይ አተኩሮ ነበር፡፡

ውሻና መፅሀፍ

በአጋጣሚ ሬድዬ ከፍቼ ስሰማ “ቪክቶሪያ” ከሚል መፅሀፍ የሚፈሰው ትረካ የረሰረሰ ልብ አቀበለኝ፡፡ ብሄራዊ ቴአትር ጀርባ ካለው በአንዱ ቤተ መፅሀፍ አድኜ አገኘሁት፡፡ ይህንን ጣፋጭ ውሻዊ ቸርነት አነበብኩት፡ እነሆ ታሪኩ ፦

በሁለተኛ የአለም ጦርነት መባቻ አሜሪካዊ ወታደሮች የሩስኪ ከተማ ላይ ይርመሰመሳሉ። ቦታው ሞስኮ ነው፣ የዛኔዋ የስታሊኗ ራሽያ ዛሬ በ90 days to wedding ታዋቂ የቲቪ ፕሮግራም ላይ እንደምናየው ኣንድ አሜሪካዊ ከራሽያዊት ጋር ጋብቻ መፈፀም የተፈቀደ አልነበረም። በደማቅ ወረቀት ከውጪ ዜጋ ማግባትና መውለድ አይቻልም ተብሎ ህግ የረቀቀባት ከተማ ላይ በደራ ፍቅር ከአንድ አሜሪካዊ ወታደርና ራሽያዊት ሴት ቪክቶሪያ የተባለች ህፃን ተወለደች፡፡

አባት የአሜሪካ መንግስት ወታደሮችን ተመለሡ ብሎ ባዘዘው መሰረት ወደ ሀገሩ ልጅና ሚስቱን ጥሎ ገባ፡፡ እናትና አባት ባጠፉት ቪክቶሪያ ከልጅነቷ ሀገሯ ቀጣቻት፡፡ ት/ቤት ውስጥ የእድሜ እኩዮቿ “ዲቃላ” ብለዋታል፣ ከልጅ እስከ አዋቂ ቪክቶሪያ ተጠልታለች.. ለምን?

አባቷ አሜሪካዊ ነው፡፡ “ከሀዲ የወለደሽ” ተብላለች፣ ስድብና ቅስም ሰበራ ሲበዛባት ከት/ቤት ቀረች፣ ቤት መቀመጥ ጀመረች፡፡ ምስኪኗ ቪክቶሪያ ብቻዋን ቀረች። ታዲያ ለታመመ ልቧ መጠገኛ ውሻ መንገድ ላይ አገኘች። እየዳበሰች ወደ ቤት ወሰደቻት፣ ግን ቤተሰቦቿ ራሽያ በገጠማት የኑሮ ውድነት ምክንያት በሌለ ምግብ ባመጣችው ውሻ አልተቀበሏትም። ምግብ የለምና ጣይው ኣሏት። ዳቦዬን አካፍለዋለው አለችና ውሻዋን አስቀረች። ፈቀዱላት። በእድሜዋ ኣቻ የሠው ወዳጅ ባይኖራትም የውሻ ጓደኛ አገኘች፡፡ ለሽርሽር ይዛት ትወጣለች ውሺት ትከተላለች። ሲርባት ወደ ዋሻ እየሄደች ትመገባለች። ፈጣሪ ለመልካም ልቧ መልካም አጫዋች ሰጣት። ቪክቶሪያና ውሻዋ ፍቅር በፍቅር ሆኑ።

ከእለታት ባንዱ ብሽቅ እለት ቪክቶሪያ እየተጫወተች ውሻዋ ደግሞ ምግብ ፍለጋ ዋሻ ገብታለች። ”የአሜሪካዊው ልጅ” እያሉ የሚያንቋሽሿት ህፃናት(ሩሲያዊያን) ቪክቶሪያ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ውርወራው የበዛባት ቪክቶሪያ ስትሸሽ ትልቅ የቆሻሻ ክምር ዉስጥ ጠለቀች። በመጥለቋ የደነገጡት ህፃናት ሸሹና ብቻዋን ቀረች። የቆሻሻ ክምሩ ጥልቅ ውስጥ እየተዘፈቀች ስትሄድ መጮኽ ጀመረች። ማንም አልደረሰላትም፣። ስም ትጣራለች፣። እሪ ትላለች ማንም አልመጣም። ታዲያ ላይደግስ የማይጣለው ፈጣሪ ውሻዋን ላከላት፣ ውሺት ቆሻሻ ክምሩ አጠገብ ቆመች። የእመቤቷን ጩኸት ሰምታ በቀስታ ወደ ቆሻሻው ገባች፣። ቆሻሻው ውስጥ በጥንቃቄ እየተርመሰመሰች የፊት እግሯን ለቪክቶሪያ ላከችላት። በተዐምር ውሺት እመቤቷን ጎትታ ከጥልቁ የቆሻሻ ሲዖል አወጣቻት፡፡ ሆኖም ሠው አላረፈም። ቪክቶሪያን ያተረፈቻት ይህቺ ውሻ ናት ብለው አሜሪካን የተበቀሉ ይመስል መርዝ አብልተው ገደሏት፡፡

ውው ው

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top