ታሪክ እና ባሕል

ባሮ

በአገራችን ከሚገኙ ልዩ የመስህብ ስፍራዎች መካከል አንዱ በባሌ ዞን የሚገኘው የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ነው። በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ የተለያዩ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች ይከወናሉ። መንፈሳዊ ሙዚቃዎቹም ባሮ፣ ሰርመዴ፣ ሹቢሳ፣ ሰላሞ፣ እንጉርጉሮ፣ አቶረራ እና ዜከራ ይባላሉ። እነዚህን መንፈሳዊ ሙዚቃዎች የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ‘‘ኡሌ’’ በሚል የማዕረግ ስም ይጠራሉ።

ስለ ኡሌ ምንነትና የማዕረጉ አሰጣጥ ሂደትን በተመለከተ ከዚህ በቀደመው የታዛ መጽሔት ቁጥር 34 ሕትመት አቅርቢያለሁ። በዚህ ጽሑፌ ስለ ባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ምንነት እና ክወና ለአንባቢዎች ለማስተዋወቅ ያህል በጥቂቱ አቀርባለው። ለጽሑፉ ግብዓት የሆኑኝ መረጃዎች በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ለጥናት በሄድኩባቸው ወቅቶች በምልከታና በቃለመጠይቅ የሰበሰብኳቸው ናቸው።

የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ ከሚከወኑ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ነው። ባሮ የሚለው ቃል፤ ‘ባሕር’ ከሚለው የተገኘ መሆኑ ይነገራል። ‘ባሕር’ ሼኽ ሁሴንን ለማወደስ የሚያገለግል ቃል ነው። የሼኽ ሁሴን ወዳጆችና ተከታዮች ሼኽ ሁሴንን ሲያወድሱ ‘ባሕረዎ’ ይሏቸዋል።

‘ባሕረዎ’ የሚለው ቃል የተፈጠረው ‘ባሕር’ የሚለውን ቃል የኦሮምኛ ቋንቋ የቃል እርባታ ስነ-ባህርይ በማላበስ፣ ኦሮምኛዊ (Oromification) በማድረግ ነው። ‘ባሕረዎ’ ማለት ‘ባሕር የሆኑ’ እንደማለት ነው። ቃሉም ሼኽ ሁሴን ባሕር መሆናቸውን ይገልጻል። ባህር የሚለው ቃል፣ ሆደ ሰፊ፣ ቻይ፣ ታጋሽና ትዕግስተኛ የሚሉትን እሳቤዎች ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ትዕምርት ነው።

የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ መቼ እንደተጀመረ በትክክል አይታወቅም። የአጀማመር ታሪኩንም በሚመለከት የሚነገረው ሼኽ ሁሴን ከዚህ ዓለም መለየታቸው እንደታወቀ፣ የእሳቸውን ታሪክና ስራዎች ለመግለጽ በሚል መጀመሩን ነው። ሼኽ ሁሴን ከዚህ ዓለም ሲለዩ የእሳቸውን ታሪክና ስራዎች በባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጹት ሼኽ ሶፍ ዑመር (ሱፊ ዑመር) እንደሆኑ ይነገራል። ሼኽ ሶፍ ዑመር የሼኽ ሁሴን የቅርብ ጓደኛ፣ የሚወዷቸው ተማሪያቸውና የሼኽ ሁሴን ጀምዓ (ተከታይ) ዋና ኢማም ነበሩ።

ሼኽ ሁሴንና ሼኽ ሶፍ ዑመር የቅርብ ዝምድናም አላቸው። ዝምድናቸውን በሚመለከት ብራውካምፐር (2004) የተባሉ አጥኚ ሼኽ ሶፍ ዑመር፣ የሼኽ ሁሴን አጎት (የእናታቸው የሸምሲያ ወንድም) ናቸው ይላሉ። እኔ የአካባቢው ታሪክ አዋቂዎችን ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ሼኽ ሶፍ ዑመር የሼኽ ሁሴን አማችና የሰኪና (የሼኽ ሁሴን ሚስት) ወንድም መሆናቸውን ነው። ሼኽ ሶፍ ዑመር እንደመሰረቱት የሚነገረውና በተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ የሚገኘው የሶፍ ዑመር መካነ ቅርስ ተጠቃሽ ነው። መካነ ቅርሱ በባሌ ዞን፣ በዳዌ ቃቸን ወረዳ፣ በሶፍ ዑመር ቀበሌ የሚገኝ የአገራችን የተፈጥሮ፣ የባህልና የኃይማኖት መስህብ ነው።

በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ የተለያዩ ስርዓቶች የሚፈጸሙበትና ባሮ የሚከወንበት ስፍራ ዋሬ ተብሎ ይጠራል። በመካነ ቅርሱ ሁለት የዋሬ ስፍራዎች አሉ። ስፍራዎቹም ዶቆ ከራ እና ዶቆ ድንኩሬ በሚል ስያሜ ይጠራሉ። የዋሬ ስፍራዎች በደረጃ የተሰሩ መቀመጫዎች አሏቸው። የደረጃ መቀመጫዎቹም የአምፊ ትያትር ማሳያ ዐይነት ቅርጽ ያላቸው ናቸው።

የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ግጥም በአብዛኛው በኦሮምኛ ቋንቋ የሚቀርብ ነው። የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ በኦሮምኛ ሲቀርብ በግጥሞቹ ውስጥ አልፎ አልፎ የአማርኛ፣ የአረብኛ፣ የሱማሊኛ፣… ቃላትና ሀረጋት ይደባለቁበታል። በባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ፈጣሪን፣ ነብዩ መሐመድን፣ ሼኽ ሁሴንን፣ ሼኽ ሶፍ ዑመርን እና ሌሎችን ይለምናሉ፤ ያወድሳሉ።

በባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ የሼኽ ሁሴን ተዓምራት፣ ታሪክና ባህርይ ይገለጽበታል። በግጥሙም የሼኽ ሁሴንን ፈጥኖ ደራሽነት፣ አባትነት፣ ሩሕሩሕነት፣ መድኃኒትነት፣ ከችግር አውጪነት፣ የቅርብ ዘመድነትና ሁሉንም እኩል እንደሚያዩ ይገለጻል። ግለሰቦች በሕይወታቸው ከደረሱባቸው ችግሮች እሳቸው እንዴት ፈጥነው እንዳወጧቸው በግጥም ይገልጻሉ።

በባሮ አማካኝነት በስፍራው የተሰበሰበው ሕዝብ ጥሩ ስነ-ምግባር እንዲኖረው፣ ለሰው ልጅም ሆነ ለፍጡራን ሁሉ አዛኝ እንዲሆን፣ እርስበርሱ እንዲከባበር፣ መረዳዳትና መተሳሰብ እንደሚገባ፣ መካነ ቅርሱን በአግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ፣ የሌላን ሰው ንብረት ማውደምና መውሰድ እንደሚያስቀጣ፣ ልጆች ወላጆችን ማክበር፣ ወላጆች ደግሞ ልጆችን መውደድ እንዳለባቸው ይገለጻል።

ከእነዚህ መንፈሳዊና ስነ-ምግባራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ በስፍራው ተከስተዋል ተብለው የሚታመኑ ታሪኮች፣ አፈታሪኮች፣ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም ወደፊት በመካነ ቅርሱ አካባቢ ወይም በአገር ደረጃ ይፈጸማሉ ብለው የሚያምኗቸው ሁነቶችን በትንቢት መልክ በባሮ ይገልጻሉ። በባሮ አማካኝነት የሚነገሩ ትንቢቶች በስፍራው የተገኙ መንፈሳዊ ተጓዦች እውነት እንደሆኑና በትክክልም ይከሰታሉ ብለው ያምናሉ። በመሆኑም መንፈሳዊ ተጓዦቹ በባሮ አማካኝነት የሚገለጽ የወደፊት የአካባቢውና የአገር እጣ ፈንታ ለማወቅ በከፍተኛ ጉጉት ያዳምጣሉ።

በዋሬ ስፍራ ላይ የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ የሚቀርበው የተለያዩ መንፈሳዊ ስርዓቶች በሚከወኑበት ወቅት መሀል ላይ ነው። በዋሬ ላይ የሚከወኑ መንፈሳዊ ስርዓቶች ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ይከወናሉ። ከእነዚህ ሰዓታት መካከል የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ የሚከወነው ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 10 ሰዓት ብቻ ነው። ከእነዚህ ሰዓታት ውጪ ባሮ አይከወንም።

ባሮ የሚሉ ኡሌዎች በዋሬ ስፍራ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ይቀመጣሉ። አንዱ ኡሌ ተነስቶ ባሮ ይላል። አንዱ ኡሌ ባሮ እያለ ሲደክመው ሌላው ኡሌ ይቀበለዋል። ኡሌዎቹ አንዱ ከሌላው እየተቀበለ ተራ በተራ ባሮ ይላሉ። ኡሌዎች እየተቀባበሉ ባሮ ማለት ከጀመሩ ስሜት ውስጥ እየገቡና ይበልጥ እየተመሰጡ ይሄዳሉ። በዚህም ሳቢያ አብዛኛውን ጊዜ በፕሮግራም አስተባባሪዎች ትዕዛዝ ክወናውን እንዲያቆሙ ሲገደዱ ይስተዋላል።

ኡሌዎች እየተቀባበሉ ለሰዓታት ያለማቋረጥ ባሮ ይላሉ። በነሐሴ፣ 2009 ዓ.ም. በመካነ ቅርሱ በተከበረው የኢድ-አል- አድሃ (አረፋ) በዓል ወቅት ሦስት ኡሌዎች እየተቀባበሉ 1 ሰዓት ከ31 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ ያለማቋረጥ ባሮ ሲሉ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህም በመስክ ቆይታዬ ወቅት ከሰበሰብኳቸው የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃዎች መካከል ረጅሙ ነው።

ባሮ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ በርካታ የግጥም ስንኞች ያሉት ነው። በመረጃ ስብሰባዬ ወቅት በአንድ ሰው ብቻ ሲከወኑ ከሰበሰብኳቸው የባሮ መንፈሳዊ ግጥሞች መካከል ረጅሙ 22 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የፈጀውና በኡሌ ሀሰን ሙሳ የቀረበው ባሮ ነው። ኡሌ ሀሰን ሙሳ የ60 ዓመት እድሜ እንዳላቸው የሚናገሩ፣ ድምጻቸው እጅግ የሚያምር የተከበሩ ኡሌ ናቸው።

ኡሌዎች የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ሲያቀርቡ በዋሬ ላይ በተሰበሰበው ሕዝብ መሃል በመቆም፣ ወይም ከፍ ያለ ቦታ ላይ በመውጣት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ነው። ባሮ ሲሉም በቀኝ እጃቸው ረጅምና ወፍራም ‘ደንቄ’ በመያዝ ነው። ‘ደንቄ’ የሼኽ ሁሴን ወዳጅ የሆኑ ሰዎች የሚይዙት በትር ሲሆን፣ አናቱ ላይ የባላ ቅርጽ (“Y”) አለው።

ኡሌዎች የደንቄን በትር ወደ ፊት፣ ወደ ላይ፣ ወደ ጎን በዝግታ በማወዛወዝ፣ ትከሻቸው ላይ በማድረግ እንዲሁም የግራ እጅ አመልካች ጣታቸውን በግራ የጆሯቸው ቀዳዳ ውስጥ በመክተት፣ ከጉልበት ሸብረክ እየተባለ በጥልቅ ስሜት ውስጥ በመሆን በሚያስረቀርቅ ድምጽ የባሮን መንፈሳዊ ሙዚቃ ያቀርባሉ። በስፍራው የተሰበሰበው ሕዝብም እጅግ ጥልቅ በሆነ ስሜት ውስጥ በመግባት ክወናውን ይከታተላል። በስፍራው የተሰበሰቡ ታዳሚዎች የባሮን መንፈሳዊ ሙዚቃ በእንባ ጭምር ታጅበው በከፍተኛ ስሜት ያዳምጣሉ። ሕዝቡ የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ግጥም አዝማችን ከዋኙ ብሎ እንደጨረሰ በጋራ ይደግማሉ። አንድ ኡሌ ባሮውን በጥሩ ሁኔታ ካቀረበ፣ ሕዝቡ በጭብጨባ ድጋፍ ይሰጠዋል። የተለያዩ ሽልማቶችን በመስጠት ያበረታታዋል። የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ሲከወን በምንም ዓይነት የሙዚቃ መሳሪያም ሆነ በጭብጨባ አይታጀብም።

የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ በቅኝት መደቡ “ዶሪያን ፔንታቶኒክ ስኬል” የሚባለውን የድምፅ አደራደር የያዘ ነው።

በመካነ ቅርሱ ሲከወን በመቅረጸ ድምጽ የሰበሰብኩትን የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ አሰምቼው የሙዚቃውን ስኬል በዚህ መልክ በኖታ ምልክት የሰራልኝ የሙዚቃ ባለሙያው ወዳጄ አቶ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት ነው። በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዬን እንሆ ብያለው።

የባሮ መንፈሳዊ ሙዚቃ ሌሊት ሲከወን፣ የአካባቢውን ድቅድቅ ጨለማ ለማሸነፍ ትግል ላይ ያለችው ጨረቃ በጥልቀቷ ላይ ሙሉ ክብ ቅርጽ ይዛ፣ በመካነ ቅርሱ አቅራቢያ በሚገኙት በአበልቃሲም እና በደደላ ተራራዎች መሃል ብርትኳናማ መልኳን ስታደምቅ፣… የአካባቢውን የሌሊት ብርድ ለመቋቋም ጋቢና ፎጣ ትከሻ ላይ፤ ጥምጣም አናት ላይ አድርጎ በደረጃ በተሰራውና የአንፊ ትያትር መመልከቻ በሚመስለው ስፍራ ላይ ከተቀመጠው ሕዝብ ብዛት ጋር በአንድ ላይ የሰመረ ሕብር ይመሰርታል። በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነ ቅርስ በመገኘት ይህን ትዕይንት መመልከት ልዩ ሀሴት ይፈጥራል።

የኡሌዎቹ የሚያስረቀርቀው ኃይለኛ ድምጽ ያስደምማል። ኡሌው ባሮ ሲል፣ የባሮውን የግጥም ስንኝ አዝማቹን ሕዝቡ በጋራ አንድ ላይ… በአንድ ዐይነት ዜማ የሚያሰማው ከፍተኛ ድምጽ የአበልቃሲም እና የደደላ ተራራዎች ጋር ሲላተም… የሼኽ ሁሴን አፍቃሪዎች በባሮ አማካኝነት የውዳሴ፣ የምስጋና፣ የአትርሱን የምልጃ ጥሪ፣… ሰማየ ሰማያት ዘልቆ ከአምላክ ዘንድ ሲደርስ፣ ከሼኽ ሁሴን ዘንድ ሲደርስ፣ ከሼኽ ሶፍ ዑመርና ከሌሎች ቅዱሳን ዘንድ ሲደርስ፣… ምልጃቸው ሰምሮ የአይዟችሁ፣ የአለንላችሁ፣… ምላሽ በስፍራው ሲያረብብ በዐይነ ሕሊና ይታያል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top