ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል – ቁጥር 36

ባሳለፍነው ወር ትልቅ የሚዲያ አጀንዳዎች ሆነው ካለፉ ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት ዜና ነው። ይህ ዜና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምስራች ሆኖ አልፏል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግድቡ ዙሪያ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ልዩነቶች ታይተዋል። ይህ ልዩነት ግን እስካሁን በተጓዘበት መንገድ ሊቀጥል አይገባም። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርጉና በአንድ ሐሳብ ዙሪያ ሊያሰባስቡ ከሚችሉ ጥቂት ነገሮች አባይ አንዱ ነውና። ሌላው በግድቡ ላይ ትንሽም ቢሆን ገንቢ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎች ተገቢውን ከበሬታ ልንሰጥ ይገባል። ግድቡን አቅዶ ካስጀመረው፤ ገንብቶ እስካጠናቀቀው ድረስ ያሉት ሁሉም ተሳታፊ አካላት ለፕሮጀክቱ ከፍፃሜ መድረስ የራሳቸውን የሆነ ገንቢ ሚና ስለተወጡ ምስጋናው ለሁሉም ቢሆን መልካም ነው።

የሚዲያዎች ገንቢ ሚና በሃገራችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም የበለጠ እየጎለበተ ሊሄድ ይገባል። ዳር እና ዳር ሆኖ ከመጯጯህ ባለፈ ሚዲያዎች ራሳቸውን በሃገራችን ለሚፈጠሩ መልካም ነገሮች እንደመነሻ እና ማነሳሻ አስበው፤ ጠንክረው ቀና የሆነ ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል። ይህ ተግባር እንደባህል ከተወሰደ ለአጠቃላይ የሃገሪቱ መፃኢ ዕድል ሰናይ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ለመጪው ትውልድም ጥላቻን፣ መናናቅን እና ስድብን ከማስተማር ይልቅ፤ የጨዋ ባህላችንን አርአያ በመከተል መልካም መልካሙን እና ለሃገርም ለራስም ጠቃሚ የሆነውን ባህል ወልማድ ማስተማሩ እና ማሳወቁ በጎ ነው። ያልተዘራ አይበቅልም እንዲሉ አበው፤ ዛሬ የተሰራው ነውና ለነገ ፍሬ አፍርቶ ውጤቱ የሚታየው፤ ከስር ከስሩ በተገቢው መንገድ ዛሬን የታነጸ ትውልድ ነው ነገ ለሃገርም ለወገንም ስም አስጠሪ እና አኩሪ የሚሆነው።

ኢትዮጵያ ከብዙ ዘመናት አንስቶ ለአካባቢ እና ለአየር ንብረት ጤናማነት በመቆርቆር የምትታወቅ ሀገር ናት። ይህ መቆርቆሯ ታዲያ በሃገር ውስጥ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፤ በመሪዎች ደረጃም የአፍሪካን አህጉር ወክላ በዓለም መድረክ ስለከባቢ አየር ጥበቃ የሰበከች የተሟገተች ነች። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ “አረንጓዴ አሻራ” የተሰኘ መርሃግብር ተቀርጾ፤ ከፍተኛ የሆነ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ በመላው ሃገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል። ይህ ተግባር በሃገራችን የከባቢ አየር ለውጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለማችን ከባቢ አየር ለውጥ ላይ ጥሩ ሚና ስለሚጫወት፤ ይበል ይቀጥል የሚያስብል ስራ ነው። አሁን የምንተክላቸው ችግኞች ለመጪው ዘመን ትውልዶቻችን ንጹህ አየርን የምናቀብልባቸው ደኖቻችን ናቸው።

እርግጥ ነው በሃገራችን ውስጥ ቁጥራቸው አያሌ የሆነ መሻሻል እና በበጎ መልኩ መለወጥ ያለባቸው ነገሮች አሉ። ይህ እንዲሆን ግን ከፍተኛ ልፋት እና ጥረት ይጠይቃል። ታዲያ ሁሉንም ነገር ለማሳካት እያንዳንዱን አጋጣሚ ለበጎ ነገር ለማዋል ፍላጎት ሊኖር የተገባ ነው። አዲስ እና ያልተጠበቀ አጋጣሚ በተከሰተ ቁጥር ተሯሩጦ የራስን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት መሞከር ሌላውን እስካልጎዳ ድረስ ክፋት የለውም። አጋጣሚዎችን በሌሎች ላይ ለማትረፍ እና ብዙ ሰዎችን ጎድቶ ራስን ለመጥቀም መሯሯጥ ግን ለትዝብት የሚዳርግና የሚያስገምት ተግባር ነው። እናም አጉል ራስ-ወዳድነትን ለማናችንም ስለማይጠቅም ወደኋላ አቆይተን፤ ስለጋራ ፍላጎታችን፣ ስለጋራ ጥቅማችን፣ አብረን ከፍ ከፍ ስለምንልበት ጉዳይ… እያሰብን እየሰራን ቀጣዩን ዘመናችንን ብሩህ እናድርገው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top