ፍልስፍና

ሰውነትን ነጻ ስለማውጣት

1. መግቢያ

ባለፉት ጽሑፎች ረጅም ጉዞ የሚያስሄድ እና ውስብስብ ጉዳይ ላይ ትኩረት ተደርጓል። ይኸውም ሰው የመሆን ጉዞ፣ ሰው የአለመሆን ጉዞ፣ ሰው የመሆን እዳ የሚሉ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ይህን ውስብስብ እና በአያዎ የተሞላ የሰው ልጆች ጉዞ በምልዓት ለመተንተን ጊዜና ቦታ አይበቃንም። ረጅሙን ታሪክ በአጭር ቃል ለመግለጥ (“To make a long story short” እንዲሉ) እነሆ ይህ ጽሑፍ የባለፉት ጽሑፎች ማሳረጊያ ነው። ሰው ስለ ራሱም ስለ ሌላው ፍጡር እና ልዕለ ተፈጥሮ ጉዳዮችም ያገባኛል በሚል እሳቤ ይገባኛል የሚለውን ድርሻ ለመውሰድ ሲጥር እና በጋባኝ እሳቤ በተረዳው ልክ እየገለጠ ኖሯል። በሰው ልጆች የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የተረት እና “አማህልሎ” (Myth)፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ምጥቀቶችን ሲያስገኝ፤ የሰው ልጆች ስሑት መስመሮች ደግሞ የሰውን ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብርም ሆነ የሌላውን ተፈጥሮ ሰላማዊ መስተጋብር ሲረብሽ ተስተውሏል። ይጠቅማሉ ብለን ስንመክርባቸው እና ስንመከርባቸው የኖርነው ሕጎች፣ የሞራል መርሆዎች፣ የሃይማኖት አስተምህሮዎች፣ የሳይንስ መላምቶች እና ቀመሮች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዘምን እና በቦታ መፈራረቆች የራሳቸውን የጎንዮሽ ችግሮች እየወለዱ መልሰው የሚወጉን የሚያስወጉን ስውር መሳሪያዎች ሆነዋል። ሰው ከራሱ ከተፈጥሮው በሚመነጭ ፈተና ወይም ከውጫዊ ዓለም በሚመጣ ጉስጫ የሕይወት መስመሩ ሲላጋ የኖረ ፍጡር ለመሆኑ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተከሰቱት ጦርነቶች፣ ጅምላ ጨራሽ በሽታዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ድርቅና ረሐብ፣ ያስከተሏቸውን “መቅሰፍቶች” መመልከት በቂ ነው። እናም ሰው ከነዚህ ሁለት ዓበይት አቅጣጫዎች (ከራሱ ስልጣኔ- ስይጣኔ እና ከፈጣሪ-ተፈጥሮ ቁጣ) በሚመነጩ ጠንካራ ጡንቻዎች እየተደቆሰ የግዞት ሕይወትን እንዲገፋ ግድ ሆኗል። ከእነዚህ ውስብስብ ሰንሰለታማ ግዞቶች ሰውን ነጻ የሚያወጣው ኃይል ምንድን ነው? በውኑስ ነጻ መውጣት ይችላልን፤ ነጻ መውጣትስ አለበትን? የሚሉት ጉዳዮች የዚህ ጽሑፍ መነሻ ናቸው።

2. የወጣበትን መሰላል ሰባሪው ሰው?

የሰው ልጅ ከሌሎች ተፈጥሯዊ ነገሮች በምን ይለያል? ለምሳሌ እንስሳት እንደ ሰው ባህል፣ ታሪክ፣ ህግ እና እምነት አላቸው? ሰውን ሰው ያሰኘው ምንድን ነው? የሌሎች ማኅበረ እንስሳት ዓለም ምን እንደሚመስል የተሟላ ጥናት ወይም ሙግት የሰው ልጆች ስልጣኔ ዋና አካል ተደርጎ አልተወሰደም። የእንስሳቱ ዓለም ከስነ ሕይወታዊ ጥናት እና አልፋልፎም ለሰው ልጅ የሚያስገኙትን አበርክቶ ዓላማ ካደረገ ምርምር ውጭ ሌላው “ተፈጥሯቸው” ለራሳቸው የተተወ ይመስላል። የሰው ልጅን የትመጣነት መላምት ካስቀመጡ ሙግቶች ወስጥ “የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ መላምት” በመባል የሚታወቀው ሙግት የሰው ልጅ ከችምፓንዚ እንደመጣ ይሞግታል። ሰው እና እንስሳ ከአዳኝ ታዳኝ፣ ከጠላትነት ወዳጅነት፣ ከአጋዥ ታጋዥ ተስስር ወጣ ብሎ DNA የሚጋሩ የስጋ ዘመዳሞች መሆናቸውን እቅጩን የነገረን ዳርዊን ነው። ይህ ጉዳይ አማንያን የሚባሉትንም ሳይቀር ተገዳድሮ ነው መሰለኝ እንደነ “ሉሲ” ወይም “ድንቅነሽ” ያሉቱ የዝግመተ ለውጥ እርከን ውስጥ ታሪካቸው የሚመዘዘው ቅሪቶች ከዘመናችን “የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች ነን” ባዮች መካካል የልጅ ልጆች ማግኘት አልተቸገሩም። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ አስተማሪያችን የዚህን ሐሳብ አቀንቃኞች “ራሳቸውን የዝንጀሮ ዘር ማድረግ ከፈለጉ መብታቸው ነው” በሚል ስላቅ ፈገግ እንዳደረገን አስታውሳለሁ።

ይህን መሸጋጋሪያ ጉዳይ እዚህ ላይ ጣል ያደረግሁት የሰው ልጅ የስልጣኔ ጉዞ ከሌሎች እንስሳት የሕይወት ዑደት ጋር ያለውን “ልዩነት” ለመመርመር ነው። የሰው ልጅ ዋና ዋና መሠረታዊ ባህርያቱ ባህል የሚገነባ፣ ሕግ የሚያረቅ፣ ማኅበራዊነቱን የሚመራበት ዘዴ የሚፈጥር፣ ትናንቱን ከዛሬው እና ከነገው ጋር ለማስታረቅ የሚታትር፣ የምድራዊውም የሰማያዊውም ዓለማት ዜጋ እንደሆነ የሚያምን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ራሱ ለራሱ ምስጢር እንደሆነ በማመን ስለራሱ የሚጨነቅ ፍጡር መሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፤ የተፈጥሮ ምስጢር አስጨንቆት የሚመራመር፣ ተፈጥሮን ለራሱ ፍላጎት ለማስገበር በግድ ወይም በውድ (በመሳሪያ በመጨቆን፣ ወይም በባህላዊ-ሃይማኖታዊ ተማጽኖ፣ ተማሕልሎ በማሳመን) ሌት ተቀን ሳይሰለች የሚሰራ ፍጡርም ነው። በተፈጥሮ ውስጥ የሚገለጠው ልዕለ ተፈጥሮ አካል ወይም ሌላው የሰው ልጅ ሊሆን ይችላል። ሰው ገዶትም ይሁን ሳይገደው ራሱን የእነዚህ ሁሉ ኃላፊነቶች መካዘን አድርጎ በመቁጠር ተፈጥሮ ከቸረችው ሰውነት በላይ ማንነትን፣ ምንነትን ሊደርብ ይባዝናል።

ይህንን ከማይጠረቃ ፍላጎቱ የሚመነጭ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እና የተለየ ነገን ለመጨበጥ ካለው ጥልቅ ተምኔት በመነጨ ሕልምና ራዕይ በስልጣኔ ላይ ሌላ ስልጣኔ ይደርባል። አንድ ችግር ለመፍታት የተጠቀመባቸውን መሳሪያዎች እና ብልሃቶች “ያረጁ ያፈጁ” በሚል አፈር ትቢያ ያለብሳቸዋል። ወደ ተራራው ለመውጣት የተጠቀመባቸውን መሰላሎች ያንኮታኩታቸዋል። ሌላ ተራራ እንደሚያጋጥመው፣ ወይም ወደ ነበረበት ቦታ መመለስ እንደሚያስፈልገው ሳይገነዘብ በችኳሎ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። ስለ አንበሳ የሚነገር አንድ ተረት አለ። አንበሳ ብልህ እንስሳ ስለሆነ በመጣበት መንገድ ዱካውን ተከትሎ አዳኝ እንዳያጠቃው በጅራቱ ዱካውን እያጠፋ ይሔዳል ይባላል። ይህ ምክር ምናልባት በስለላ “ሥራ” ላይ ለተሰማሩት ያገለግል ይሆናል እንጅ ለሰው ልጆች አጠቃላይ ጉዞ የሚበጅ ምክር አይደለም። አንበሳ የሚያንጠለጥለው ሊጥለው ሊረሳው የሚችል ጓዝ ስለሌለው ተመልሶ ለማግኘት የሔደበትን መንገድ ማስታወስ ላያስፈልገው ይችላል። የሰው ልጅ የስልጣኔ ጉዞ ግን በአሁን ማስተባቃት እና ማስተንተን አስተውሎት ላይ የተመሰረተ የወደኋሊት፣ የምልሰት ማስታወስ፣ የወደፊት ህልምና ራዕይን ያካተተ ነው። ይህንን ከመዘንጋት የመነጨ ሰው የወጣበትን መሰላል በርግጫ በጡጫ ሲፈነግለው ተራራው ላይ ተንጠልጥሎ መሃል ገደል ላይ ራሱን ሊያገኝ ይችላል። የሰውልጅ የመጀመሪያው ፈተና፣ አንዱ የሰው ልጆች እዳ፣ ጭቆናም ሰው በእንደዚህ ያለው ራሱ በፈጠረው የስልጣኔ-ስይጣኔ አጣብቂኝ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ነው። ይህ እንዴት ይከሰታል? ከሁለት ዓበይት ምክንያቶች ይመነጫል። ከባህል ውስጣዊ ሽግግር ወይም በባህሎች መካከል በሚደረግ ቅብብሎሽ። የአውሮፓውያንን የስልጣኔ ጉዞ እና የአፍሪካውያንን ህልው ሁኔታ ማየቱ ስለሁለቱ ጉዳዮች የተሻለ መረዳት ይሰጠናል።

አውሮፓውያን በታሪክ ዘመናቸው ውስጥ በርካታ “የስልጣኔ” እርከኖችን ተራምደዋል። ከተረት የሰውን ልጅ ለማላቀቅ የግሪክ ፈላስፎች ብዙ ጥረዋል። ይህም ፍትጊያ ፈላስፎቹን ሲያስገድል፣ ሲያሠድድ ቆይቶ የባህል ምስቅልቅልን አስከትሎ ግሪክ በሮማውያን እንድትወረር ዳርጓታል። የፈላስፎቹን ትምህርት ተከትሎ መንበሩን የተረከበው የሃይማኖት መስፋፋት በርካታ እልቂቶችን አስከትሏል። በሃይማኖታዊ ዶግማዊ እሳቤዎች ባንድ በኩል፣ በሳይንስና በፍልስፍና ምክንያታዊነት በሌላ በኩል በነበረው ፍልሚያ አውሮፓውያን ምንም ስልጣኔ አላስመዘገብንበትም የሚሉት በራሳቸው አጠራር “የጨለማው ዘመን” የሚሉትን አስከተለ። ከዚህ ለመውጣት እንደገና ዘመናዊ ፍልስፍና ባንድ በኩል አብርሆትን፣ የሳይንስ አብዮት በሌላ በኩል ቴክኖሎጂን ይዞ ምክንያታዊነት ምሉዕ በኩለሄ ሆኖ ብቅ አለ። ይህም የሰውን ልጆች ፍላጎት በምልዓት ሊመልስ አልቻለም። ይህንን ጉዳይ አንዳንዶች (ለምሳሌ ኒቼ) ዘመናዊነትን “ሁሉም ከንቱ” (nihilism) ሲለው፤ ሌሎች (ለምሳሌ ማርኩሴ፣ አዶርኖ እና ሆርካይመር) ስለጣኔ፣ ምክንያት፣ ሳይንስ ወይም አብርሆት ተብየዎች ሰው ራሱን ለሌላ ጨቋኝ ኃይል አሳልፎ በመስጠት ሕይወት አንድ አቅጣጫ ብቻ ያላት እንድትመስል አድርጓታል ይላሉ። በዚህም ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ህሊናዊ እና አካላዊ ደህንነትን የሚጋፋ ሌላው አስፈሪ ኃይል ሆኖ ብቅ ብሏል። እነዚህ ነገሮች በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ አስተሳሰባዊ ዝንፈቶች እና ውድድሮች ሲታሹ የሰውን ልጅ የከፋ የመጨረሻው ባርነት ላይ ይጥላሉ። ሚሼል ፉኮ ይህንን የቢሮክራሲ እና የቁጥጥር መሰናክሎች ሰብስቦ የያዘውን ጨቋኝ ዘባተሎ ገዥነት (Governmentalization) ይለዋል። ካፒታሊዝም ወለድ እልቆ መስፈርት ፍዳዎች፣ ሁለቱም የዓለም ጦርነቶች፣ ሃንቲንግተን “clashes of civilizations” የሚላቸውን የዘመናችን የስልጣኔዎች/የባህሎች ግጭቶች፣ በሃያላኑ መካከል የሚደረጉ ፉክክሮች በውስጣችው ስንቶችን እንደሚያስገብሩ መገንዘብ አያዳግትም። የቀደሙት ባርነቶች ምናልባትም ከስጋዊ ብዝበዛቸው ባሻገር የባርያውን ኅሊና የሚያቆስሉ ነገሮች፣ ስነልቡናዊ በሽታዎች ያስከትሉ እንደሁ እንጅ በውኑ ባሪያዎች ኅሊናቸው ምን እንደሚያስብ መረዳት አያስችሉም ነበር። የዘመናችን ቴክኖሎጂ ግን ሰው ይህን ማወቅ የሚችል “Evil genius” እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ዓይነቱ የጭቆና ቀንበር የሚመጣው አንድ ባህል ራሱን በራሱ እየነቀፈ በሚያደርገው ሽግግር ውስጥ የማይጣለውን በመጣሉ እና የማይነሳውን በማንሳቱ የሚፈጠሩ ዝንፈቶች ነው።

ከዚህ የአውሮፓውያን የስልጣኔ ጉዞ ዓለም ምን አተረፈች? አውሮፓውያን “ከእኛ ወዲያ ላሳር” ብለው ሁሉም “የሰው ልጅ አስተሳሰብ የእኛን መስመር ብቻ መከተል አለበት” የሚል የስልጣኔ እብሪት ማሳየታቸው አልቀረም። በዚህም በቀጥታ ወረራ እና በእጃዙር ቅኝ ግዛት ወደ አፍሪካ ሳይታክቱ ይመላለሳሉ። በታሪክ የታወቀውን የቅኝ ግዛት መነሻና መዳረሻ እዚህ ላይ በመደጋገም ጊዜ አናጠፋም። ይልቁን በባህል፣ በስልጣኔ፣ በፍልስፍና፣ በአገር በቀል እውቀት ረገድ ትምህርትን እና የቴክኖሎጂ ቅብብልን ተከትሎ የሚመጣውን የጭቆና ጡንቻ እንመልከት። “እውነት በሃይለኞች እጅ ናት” በሚል እሳቤ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ጉልበታቸውን ተገን አድርገው የሚመጡ የአስተዳደር፣ የአስተሳሰብ፣ የባህል እና የትምህርት ፖሊሲዎች በተቀባዩ ማኅበረሰብ ነባር የኑሮ ይትበሃል ላይ የሚያሳድሩት ጭቆና በቃላት ሊገለጥ የማይችል ነው። ነባሩ የሕይወት ዘዴ በሙሉ ጥሬው ከነብስሉ የማይረባ፣ ለዘመኑ የማይመጥን፣ ያረጀ ያፈጀ ትብሎ ይወረወራል። “ሕደግዎ ለብሉይ ልበስዎ ለሐዲስ” (አሮጌውን ጣሉት አዲሱን ልበሱ) ይባላል። በዚህ ጊዜ የሚፈጠረውን በትውልዶች መካከል የነበረን ቅብብሎሽ ክፍተት አዲሱ እና መጤው እውቀት ሊሞላው የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። እንደ ዶክተር እጓለ ማሳሰቢያ ይሕ ሁኔታ በአግባቡ ካልተያዘ በእንደዚህ ያለው ዘመን የሚመጡ ትውልዶች የፈዘዙ፣ ከት ብለው የማይስቁ፣ ስቅስቅ ብለው የማያለቅሱ ይሆናሉ። ዲ ሳንቶስ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱን የባህል ጭቆና እውቀትን፣ አእምሮን መግደል (Epistemicide) ይለዋል። ይህ አእምሮን የመግደል ሂደት አስተሳሰብን ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰቡን ባለቤቶችንም ማኅበራዊ መስተጋብር እና የጋራ ሕልውና፣ የሕይወት ትርጉም ከምድረ ገጽ የማጥፋት ሌላ ገጽታ አለው ይለናል ሳንቶስ።

ሁለቱን በአንድ አንቀጽ እንግለጣቸው ቢባል የዛሬውን ሰው የገጠመው ፈተና “አንድ ጥብቆ ለሁሉም” (One size fits to all) የሚል ከዘመን ለመሸሽ ወይም ሁሉንም ቦታና ሁኔታ ለመጠቅለል በሚደረግ ፍላጎት የሚመነጭ ስሑት እሳቤ የሚመጣ ጭፍለቃ ነው። ይህን የመጀመሪያው ባርነት በስልጣኔ ውስጥ የተሸፈነ ስይጣኔ ነው ልንለው እንችላለን። ይህም የሰው ልጅ በታሪክ ጉዞው ውስጥ ያካበታቸውን የሃይማኖት፣ የሞራሊቲ፣ የሕግ፣ የስነ ተፈጥሮ ምርምር፣ የፍልስፍና፣ የእውቀት፣ የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ያስገኟቸውን ትሩፋቶች አሽቀንጥሮ በምጣል በዘመን አመጣሹ ሙሉ ለሙሉ ለመተካት በሚደረግ ጥረት የሚፈጠሩ ማሕበረ ስነ ልቡናዊ እና አካላዊ ጉስቁልናዎች ያስከትላል። በሌላ በኩል ደግሞ አካባቢያዊ አውዶችን እና ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮችን ያላገናዘቡ አስተሳሰቦች በኃይል ሊጫኑ በሚሞከሩበት ሁኔታ፣ ዓለም በሙላዋ በአንድ ኅሊና እንድታስብ የሚደረግ ሐሳባዊ ሙከራ ነው። በዚህም ሀርበርት ማርኩሴ እንደሚለው በርካቶች ራሳቸው በራሳቸው እንዳይወስኑ በማድረግ፣ ይሆነናል ከሚለው የሕይወት መስመር ምርጫ ገሸሽ ተደርገው ሰውነት ያለ ባህርይዋ በአንድ ቦይ እንድትፈስ ይደረጋል። ይህም የጭቆናው ሌላኛው መገለጫ ነው። ሰው ራሱን በራሱ ያሰረ ይመስል፣ የሰውነትን ጉዞ ቀይዶ የያዘበት የስልጣኔ ተዛንፎ ሰውነትን ባርነት ላይ ይጥለዋል። ከዚህ የጭቆና ቀንበር ሰውን ነጻ የሚያውጣው መሲህ ምንድን ነው? ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ሁለትኛውን የጭቆና መነሻ እንመልከት።

3. የኮበለለው ልጅ፣ ሰው ከዓለም ሸሸ?

“Universe” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል አቻ አማርኛ አላገኘሁለትም። “ምልዓተ ዓለም”፣ “ሁለንተና”፣ “አድማስ” ልንለው እንችላለን። ዋና ቁም ነገሩ ይዘቱ ላይ መስማማቱ ነው። ምድራዊ እና ሰማያዊ ዓለማት (ከዋክብቱና ፕላኔቶቹ ለማለት ነው)፤ በውስጣቸው ያለውንም ፍጥረት በሙሉ በአንድ ላይ ጠቅልለን የምንጠራበት አኳኋን ነው። ሰይፉ መታፈሪያ “ውስጠት” ይሉታል። ሲያብራሩም አዳሪንም ማሕደሩንም ጠቅልሎ በንድ ላይ መጥራት ነው። “ከላይ ከላይ ጎበብ ያለ የሚመስለው ሰማይ እንደ ጣሪያ፣ ከታች ከታች ደግሞ፣ ሁሌ ሄዶ ሄዶ አድማስ ሲደርስ በተዳፎት ወደዚያ ከንበል የሚል የሚመስለው መሬት ወለል ሆኖ ትልቅ ትልቅ አዳራሽ ይመስላል።” (1981 ገጽ 10¬ 11) ይላሉ። ይህ አዳራሽ ባዶ አይደለም። በውስጡ በርካታ ነገሮች ተካተውበታል። ሁሉም የየራሳቸው ተፈጥሯዊ ባህርይ ቢኖራቸውም እርስበርሳቸው በመካከላቸው የተለየ መስትጋብር አለ። ያ ተፈጥሯዊ ግንኙነት በስውር የተፈጥሮ ሕግ የሚዳኝ ይመስላል። ላይብኒዝ በቅድምና የተቀመጠ የውሕደት ሕግ (Pre-established harmony) የሚለው ነው። የሃይማኖት ሰዎች የዚህ ሕግ ሰራዒ እና የዓለሙ መጋቢ፣ አስተናባሪ እግዚአብሔር ነው ይላሉ።

ራሱን በዚህ ምልዓተ ዓለም መካከል ላይ ያገኘው ሰው ለራሱ እንደሚመቸው አድርጎ ተፈጥሮን ለማበጀት እና የራሱን ዓለም ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት በርካታ የተፈጥሮ ጉራንጉሮችን ይነካካል። በዚህም የተፈጥሮን ስስ ብልቶች፣ አላግባብ ሲረብሽ የሚፈጠሩ ፍጭት ግጭቶች መከሰታቸው አልቅቀረም። አጠር ባለ አገላለጥ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ቤቱ ወጥቶ፣ ራሱን በተፈጥሮ አንጻር አስቀምጦ፤ ሌላውን ተፈጥሮ ወደ ቤቱ ማስገበር ፈለገ። ዓለም ከመስክ ወደ ቤተ ሙከራ እንድትገባ ተደረገች። ሰው መጀመሪያ ሳር አጭዶ፣ እንጨት ቆርጦ፣ ቤት ሲሰራ፤ ምድሩን አርሶ፣ ፍሬውን ቆርጦ፣ እንስሳቱን አድኖ ሲመገብ፤ ቅጠል በጥሶ ስር ምሶ ሲታከም፤ አድባራቱን፣ ወንዞቹን፣ ጫካውን ሲማጠን ሲያመልክ (በሹክሹክታ ሲግባባ) ከነበረበት ዘዴ ራሱን ነጥሎ በማሽን እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ በሚረብሽ ጉልበት እና ድምጽ፣ የሚያማምሩ ቪላዎችን እና ማንኛውንም የኢንዱስትሪ ውጤቶች ለማምረት ተፈጥሮን ሕይወት ያላት፣ የራሷ ሕግ ያላት፣ እሱም የሷው አካል እንደሆነ ዘንግቶ ከተፈጥሮ ላይመለስ ኮበለለ፤ አመጸባት። ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ብቸኛው አእምሯዊ ግብዓቱ ሳይንስ መር ምርምር እና ቴክኖሎጂ ወለድ መሳሪያ ሆነ። ተፈጥሮ ታኮርፋለች፣ ፈጣሪዋ ይቆጣል፣ መናፍስቱ ይበሳጫሉ፣ የሰው እና የተፈጥሮ ወዳጅነት ይበጠሳል የሚሉ አስተምህሮዎች እንደ ዘመኑ ያለፈባቸው ተረቶች ተቆጠሩ። ሳይንስ የፈጠነውን ያክል ይጓዝ ዘንድ ከማገዝና ከመመኘት ውጭ የሞራል፣ የምግባራዊ በጎነት ሚዛን፣ ማኅበረሰባዊ ማዕቀብ፣ ሃይማኖታዊ ክልከላ፣ የሕግ ገደብ በሙሉ ተዘነጉ።

ይኸ ነገር ምን ይዞ መጣ? ተደጋግሞ ከሚነገረን እንኳን ብንጀምር የዓለም ሙቀት መጨመር እና የተፈጥሮ አየር ጠባይ መዛባት የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ባደረጋቸው ያልተገደቡ ጣልቃ ገብነቶች የመነጩ ናቸው ተብለናል። ይህንን ተከትሎ የሚመጣ የድርቅና ጠኔ፣ የበረሃነት መስፋፋት የሚያስከትላቸው እልቂቶች እና መጎሳቆሎችን በታሪካችን አይተናል። የኦዞን ንጣፍ መነደልን ተከትሎ የሚመጣ እፍተኛ ሙቀት፤ ከኢንዱስትሪ ጭስ በሚመነጭ የአየር ብክለት ምክንያት የሚመጣ መርዛማ ዝናብ፤ የሰው ልጅ መርዛማ ኬሚካሎችን ወደ ምድር በመጣሉ የሚከሰቱ የአፈር እና የውሃ ብክለት ወለድ በሽታዎች፤ ከመሬት መራቆት የሚከተል ጎርፍና የመሬት መንሸራተት፤ እነዚህ ሁሉ ሰው ራሱን ከተፈጥሮ በመነጠሉ፣ ተፈጥሮን በመበደሉ የሚከተሉ ናቸው። በዘመናችን እየተበራከቱ የመጡት የሰው ልጅ በራሱ አደልቦ ወይም አምርቶ ከሚመገባቸው ምግቦች ጋር የተገናኙ መድኃኒት ዓልባ በሽታዎች፤ ምስጢራቸው በወል ያልታወቁ ጅምላ ጨራሽ እንደ ኢቦላ፣ ኤድስ እና የወቅቱ ኮሮና ያሉ ተስፋፊ፣ ተላላፊ በሽታዎች ከእንስሳት ጋር የተገናኙ ናቸው መባሉ፤ ወዘተ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ፣ ከዩኒቨርሱ በማፈንገጡ፣ ራሱም ካስቀመጠበት ቦታ ባህርይ የሚመነጩ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።

አንባቢ እንደዚህ ዓይነቶቹ ነገሮች እኮ ቀድሞም ነበሩ፤ የሰው ልጅ ታሪክ አካላት ናቸው፤ አሁን ምን አዲስ ነገር ተገኘ? የሚል ክርክር ማንሳቱ አይቀርም። ልክ ነው። እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ቀድሞም ነበሩ። አጭሩ መልስ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ያፈነገጠበት ዘመን ከጥንት ጀምሮ ነው። የሚል ሊሆን ይችላል። ጠለቅ ብለን ስንመረምር ግን ማብራሪያው ሌላ አቅጣጫ ይይዛል። ለምሳሌ የሰው ልጅ ከበረሃማነት ጋር ያለው ቁርኝት በግብጽ ፎርኦኖች ዘመን እስራኤላውያን በሲናይ በረሃ የደረሰባቸውን እንግልት በመጽሐፍ አንብበናል። እውነት ነው። ሕማምና ቸነፈርም ለምሳሌ እንደ ወባ ያሉ የቆላ በሽታዎች ብዙሃኑን ያሰቃዩ እንደነበር አባቶቻችን ይነግሩናል። ነገር ግን የሰው ልጅ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ፈተናዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በረሃውን ገነት ከማድረግ ይልቅ ገነቱን ወደ በረሃማነት የሚለውጥበት አግባብ ያይላል፣ የሚል ነው ሙግቱ። አዋሽን ቀይሶ በመስኖ የሚያለማው የአገሬ ሃብታም እንዳለ እሙን ነው። በዚያው ልክ ደግሞ በጋምቤላ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኝ ጫካ እንዳልነበር አውድሞ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለአፈሩ የማይበጅ፣ አካባቢውንም ወደ በረሃማነት ሊቀይር የሚችል ማዳበሪያን ተጠቅሞ ያላግባብ በተፈጥሮ ላይ ጣልቃ የገባውን ኢንቨስተር ሲታሰብ ድሮ ፈልገውን ሲመጡ የነበሩትን ችግሮች ዛሬ ፈልገን ወደ ቤታችን እየጠራን እንደሆነ ያሳያል።

ዘረመላቸው የተለወጠ ዘሮች በኢትዮጵያ ሊተገበሩ ነው መባሉን በርካቶች እየተቃወሙት ነው። ሊያስከትለው የሚችለውን የረጅም ጊዜ ተስቦ ስጋት ከባለሙያዎች ሰምተናል። ድሮ በተፈጥሮው በርካታ ፍሬ ሊሰጠን የሚችለውን መሬት ካራቆትን በኋላ ምርታማነቱን፣ ለምነቱን እንዲጨምር ከላባራቶሪ አፈር (ማዳበሪያ) ይዘንለት ሄድን፣ ለዚያውም በትክክል ባልተጠና መንገድ። ያንን የለመደ መሬት ነገ ላይ ጭራሹኑ ማፍራት አልችል ቢል አይደንቅም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ እንኳ ታላላቅ ወንዞቻችንን ቀይሰን በረሃማ ቦቻዎችን ከማልማት ይልቅ የሚቀናን የቤታችንን ቆሻሻ ወደ ወንዞቹ መወርወር ነው። ለዚህ ቀላል ማሳያ በአዋሳ ተገኝቶ ወደ ሐይቁ የሚወረወረውን ቆሻሻ ማየት ነው። ከሐይቁ የምናጠምዳቸው ዓሳዎች የኛን ቅሪት ተመግበው አንዳች የመርዛምነት ባህርይ ይዘው እኛኑ እደማይመርዙን ማረጋገጫችን ምንድን ነው? ጣና ሐይቅን እየሸፈነ ያለው እምቦጭ ከሰማይ የወረደ ወይም ከሐይቁ ጥልቅ የተወለደ ተፈጥሯዊ አረም ነው ብሎ የሚያስብ አይኖርም።

የእነዚህ እና መሰል የሰው ልጅ ከተፈትሮ ጋር የሚያደርጋቸው ያልተገቡ ግንኙነቶች ድምር ውጤት የሰው ልጅ ከተፈጥሮ በሚመነጩ ቁጣዎች ስር ተጨቁኗል ያስብሉናል። በርካቶች በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙት ችግሮች ተቀርፈዋል ብለው ያምናሉ። ከስልሳ ዓመታት በፊት የጻፉት እጓለ እንኳ በዚህ በኩል የሚመጣውን የሰው ልጅ ባርነት ድል ነስተነዋል ብለው ነበር። እኔ ግን ብዙ ይቀረናል ባይ ነኝ፤ ገና ብዙ አንዳናይም ስጋቱ አለ።

4. የነጻነቱ መስኮት

የሰው ልጅ ህልው ሁኔታ ነጻነት የሚያሻው መሆኑን ማንም አይከራከርም። ልዩነቱ የሚኖረው እንዴት ነጻ ይውጣ የሚለው ላይ ነው። በርካቶች የሚስማሙበትን መስመር ተከትለን ትንሽ እንበል። ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ጭቆናዎች መፍትሄ ትምህርት ነው ይላሉ። ትምህርት ነጻ አውጭ መሳሪያ የሚሆነውም፦ አንደኛ እንደነ ፓውሎ ፍሬሬ አነጋገር ትምህርት የሰው ልጅ ያለፈባቸውን የስልጣኔ መንገዶች ተከትለው የመጡ ጨቋኝ አላባውያንን (Dehumanaizing Elements) የሚገልጥልን፣ የሚያጋልጥልን መነጽር፣ ነጻ አውጭ መሳሪያ ነው። ሁለተኛ እንደነ እጓለ ትንተና በባህሎች መካከል የሚኖርን መዋሃድ፣ መናበብ እና መነጋገር የሚዳኘው፣ እውቀቶች የተመሳሳይ ኅሊና ወጤቶች ዘመዳሞች እንጂ አንዱ ትልቅ አንዱ ትንሽ ተብለው የማይበላለጡ መሆናቸውን የሚበይን ፍትሐዊ ዳኛ ትምህርት ነው። ይህ ትምህርት እንደዚህ ዓይነቶቹን ሚናውን እንዲጫወት ከተፈለገ በጥሩ የትምህርት ፍልስፍና ሊደጎም ይገባል። እንደ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ካሉ አካባቢዎች የመጡ የቅርብ ዘመን ፈላስፎች ደግሞ “ነጻ አውጭ ፍልስፍና” (Philosophy of Liberation) የሚል የፍልስፍና ክንፍ ይዘው ብቅ ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ ፍልስፍና አዲስ ሳይሆን ከነባር የፍልስፍና ዘርፎች ተውጣጥቶ ተግባራዊ ሚና እንዲላበስ የተደረገ ሲሆን በርካታ ፋይዳዎች አሉት። አንደኛ ከውጭ ከሚመጣ ኅሊናዊ ቅኝ ግዛት (mental colonialism) ነጻ ያወጣል። ሁለተኛ ከአካባቢያዊ ህልው ሁኔታ የሚነሱ የዘረኝነት፣ የጾታ፣ የአምባገነንነት፣ እና መሰል ሁኔታዎችን ለመዋጋት ያግዛል። ይህን ዓይነት ሚና ቴዎድሮስ ኪሮስ በትችት ላይ የተመሰረተ የይሁንታ ምክር አቀባይ (“Critical/Moral Practice”) ይለዋል። ሦስተኛ በዓለም መድረክ ውስጥ አያስቡም፣ ፍልስፍና የላቸውም ተብለው አስተሳሰባቸው እና ይትበሃላቸው እየተደፈጠጠ ለሚገኙት እንደኛ ዓይነቶቹ ማኅበረሰቦች ለዘመናት ያካበቷቸውን ጥበቦች በማጋለጥ ለዓለም እይሚበጅ ነገር እንዳላቸው ማሳየት፤ በዚያው እግረ መንገዱን ምሉዕ በኩለሔ እና ለሁሉም መፍትሔ አለኝ የሚለውን አውሮፓዊው እብሪት የጎደለውን ማሳየት ነው። ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ በይነ ባህሎች ተግባቦት ላይ የተመሰረተ ፍልስፍና (Intercultural Philosophy) ሁሉም የየራሱን ትክክለኛ ማንነት የሚረዳበት የነፍስ ፍለጋ ሂደት (Soul Searching Proccess) ነው ይሉታል።

እንዲህ ያለው የፍልስፍና ፋይዳ በትምህርት የሚገለጠውም ጆን ዲዎይ እንደሚለው ተማሪውን የቆየ እውቀት ከመጫን ይልቅ ራሱ እንዲያስብ ስናስችለው ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ጸናይ ሰረቀ ብርሃን የአንድምታ ትርጓሜ የፍልስፍና ዘዴን (hermeneutics) ሲያብራራ ይህ ዓይነቱ ዘዴ አንድ አስተሳሰብ እንዲያብብ መደላድል (milieu) የሆነውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ዳራና ዓውድ በመረዳት የፍልስፍናውን ባህርይ እንድናውቅ ያግዘናል ይላል። ከዚህ እሳቤ ጋር ስሙ መቅርበት የሚታወቀው ጋዳመር ይህ ዓይነት ዘዴ ከዘመን እና ከቦታ እርቀት ገደብ ነጻ የሚያወጣን የሌላ ባህል ህሊናዎችን እና የሌላ ዘመን ጥበቦችን ትክክለኛ ምንነት በመረዳት የዘመናችንን ዲስኩር እንድናበለጽግ ይረዳናል ይላል። ይህም የበይነ ባህሎች (Intercultural) ንግግር እና የበይነ ትውልዶች (Intergenerational) ቅብብል ጤናማ እንዲሆን ያደርገዋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሐተታዎች በጥቂት ቃላት ሲጠቃለሉ የሰው ልጅ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወትም ሆነ ከተፈጥሮ ጋር በሚኖረው መስተጋብር ካለፈው ዘመን እና ሌሎች ባህሎች ካበቀሏቸው ነቅዓ ጥበበባት (የጥበብ ምንጮች) ቀድቶ የሞራል፣ የስነ ምግባር፣ የእውቀት፣ የሕግ፣ የተግባቦት፣ የእምነት ውርሶችን ከዘመን አመጣሹ አስተሳሰባዊ እና ቁሳዊ ስልጣኔ ጋር በማዋሃድ ለምልዓተ ዓለሙ ጤናማነት የሚበጅ የቲዎሪና የተግባር መንገድን ሊከተል ይገባል የሚል ነው። ሰውነት ነጻ የሚወጣው በእንደዚህ ዓይነቶቹ ድርብርብ ነጻ አውጭ መንገዶች ነው።

5. ማጠቃለያ

ሰው የመሆን ጉዞ ጉዳይ በመጽሔት ቀርቶ በመጻሕፍትም የሚያልቅ አይደለም። ሰውነት ውስብስብ የሆኑ ችግሮች እና ጸጋዎች ድምር ውጤት ነው። ሰው ራሱ በሚያፈልቃቸው ስልጣኔዎች የጎንዮሽ ጉዳት እና ከሌላው ውጫዊ ተፈጥሮ በሚመነጭ ስውር ኃይላት የሚንገላታ ፍጡር ነው። ራሱ በቆዳ ቀለም፣ በታሪክ ሁነት፣ በእውት፣ በፍልስፍና፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ፣ እና በመሰል ልዩነቶች አጥር ውስጥ ሸብቦ ከራሱ ወገኖች ጠላቶችን እና የእኩይ ምግባራቱ ሰለባዎችን ይፈጥራል። በዚህም በርካቶች ይጨቆናሉ። በዘመን ሂደት ውስጥ በተፈጠሩ ስህተቶች አማካኝነት ሰው ራሱን ከሌላው ተፈጥሮ ነጥሎ የተፈጥሮ ጉዳት በቀጥታ እንዳይሰማው የሚያደርግ ድንበርንም ማበጀቱ አልቀረም። በዚህም ሌላ ጠላት አፈራ። ይህ ያልተገባ የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት ፍትጊያም ሌሎች የጭቆና ዝክንትሎችን ይዞ ብቅ አለ። ሰው እንደገና ይንገላታል። በሃብትና በስልጣኔ የተሻሉ ናቸው የተባሉት በስነ ልቡና ቀውስ ሲንገላቱ፤ በድህነት ወስጥ ያሉ ጎስቋሎች ደግሞ በአካላዊ እና መንፈሳዊ በሽታ ሲሰቃዩ ማየት የዚህ ዘመን ሰው ከባርነት ነጻ እንዳልወጣ እሙን ነው።

ይህንን ብኩን ሰው ነጻ የሚያወጣው ሁለንተናዊ ሕሊናዊ በሊህነትን እና ልቡናዊ ቀናነትን የሚገነባ ትምህርት ነው። ይህም በተለያዩ ግብዓቶች የበለጸገ ነጻ አውጭ የትምህርት ፍልስፍና፣ ባንድ ወገን በዘመኖች መካከል እና በባህሎች መካከል ያለውን ቁርሾ በማስታረቅ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሰው እና በሌላው ተፈጥሮ መካከል ያለውን አዘቅት በመሙላት የተሻለ የእኩልነት እና የአብሮነት ዓለምን እንድንገነባ ያስችለናል። ስለ ትምህርት እና ነጻ አውጭ ፍልስፍና የተነሳው አጭር ዳሰሳ ጉዳዩን እንደበደለው ይሰማናል። ሌላ ጊዜ በሰፊው የምንመለስበት ይሆናል። እስከዚያው የወር ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top