ዘባሪቆም

ሠይጣንና የ3ኛ ሀ ተማሪዎች

የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር ሲፈርድበት 10ኛ ክፍል ታሪክ አስተማሪ ተደርጎ ለተመደበዉ ወጣት የእግድና ምደባ ደበዳቤ ላከ። ከ10ኛ ክፍል መምህርነት ታግዶ 3ኛ ክፍል ስዕል እንዲያስተምር ቀን ተጠቅሶበት፣ ቁጥር ወጥቶለት የረቀቀ ደብዳቤ ደረሰው።

ደብዳቤ እንደሚደርሠዉ አልጠበቀም። አነበበዉ። ሞራሉን ለመንካት እና ባስተማራቸዉ ተማሪዎች ፊት እንዲቀል የረቀቀ ተንከሲስ ደብዳቤ ነዉ። ተማሪ ሲስቅና ሲያሸሙረዉ በአይነ ህሊናዉ ተመለከተ። ተቆጣ። ሄጄ በቡጢ ብነርተው ብሎ አሰበ። በጣም ቆዘመ። ፈገግ አለ። በአእምሮዉ ሁነኛ የበቀል መላ ተከሰተለት።

የስዕል ክ/ጊዜያቸዉ ባዶ መሆኑን የተመለከቱ ሕጻናት ይንጫጫሉ። እርስ በርስ ይጓተታሉ። ይወጋጋሉ። ዴስክ ላይ ይዘላሉ። ህግና ስርዐት እንዲያስከብር የተሾመዉም እልቅናዉን ዘንግቷል። ድንገት ከቁመቱ ዘለግና ደልደል ያለ ወጣት ወደ ሚንጫጫዉ ክፍል መሰስ ብሎ ገባ። ሰተት ብሎ ለሚገባ ጎልማሣ ድንጋጤ እድሜያቸዉ የሚያስታጥቃቸዉ ዝናር ነዉ።

እንግዳዉ ፈገግ ብሎ ተንጎራደደ። “ተማሪዎች ከዛሬ በኋላ ስዕል የማስተምራችሁ እኔ ነኝ” አላቸዉ። “ዬ” የሚል ድምፅ አስተጋባ። ወዲያውኑ ልሙጥ ደብተራቸዉን አዉጥተዉ አርጉ የሚባሉትን ለመሳል አንጋጠጡ። እንዲስሉ ያዘዛቸዉ ግን እንግዳ ነበር።

“ማርክ አለው” ብሎ ጀመረ። “ጥሩ አድርጎ የሳለ ይደፍናል። ከአስራ አምስቱ አስራ አምስት ያገኛል። ጥሩ ካልሆነ ግን ዜሮህን አስታቅፍሀለዉ” አላቸዉ። ማርክ የትኛውንም ተማሪ ነፍስ የሚያጓጓ ነገር ስለነበረው ጓጉ፡፡ “እሺ” የሚል ቃል በአንድ ላይ አስተጋባ።

“ሠይጣንን ሳሉልኝ። ሠይጣንን” መምህሩ ክፍል ወስጥ ከመጀመሪያዉ ቅፅበት በላይ ተማሪዎችን አሰደነገጣቸዉ። ይህን ስም ቤተ እምነት ያዉቁታል። ወላጆቻቸዉ ሠይጣን አሳሳተው.. ሠይጣን ለከፈው.. ሲባል ሰምተዋል። በአካል ግን ምን ይመስላል? ቀይ ነው? ጥቁር ነው? ረዥም ነው? ቀጭን ነው?

“ሰይጣን ምን አይነት ነው? የት ይገኛል?” መምህራቸውን ጠየቁ። ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለሰ። “እንዴት እስከዛሬ ሰይጣንን አታውቁትም?” ዝም አሉ ተማሪዎቹ። “አትዋሹ” ክፍል ውስጥ አምባረቀ። “ይኼ በእረፍትና ምሳ ሠዐት ፊሽካ እየነፋ.. ዱላ ይዞ የሚያባርራችሁን እንዴት አታዉቁትም? አስራ አምስት ማርክ ላለው ጥያቄ ፍንጭ ያገኙት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ለመሳል መጣደፋቸውን የተመለከተው መምህርም ተደሰተ።

ሠይጣንን የመሳል ጉዞው ተጀመረ። በትር መሆናቸውን ያልተረዱት ትንንሽ ሕጻናት በጥድፊያ የታዘዙትን ማከናወን ጀመሩ። ክፍሉን ከፍተኛ ወጀብ ናጠው። “እንዴት አይነት ነበሩ? ፀጉራቸዉ.. አፍንጫቸዉስ?” እየተባባሉ ዳይሬክተሩን አሰፈሯቸዉ። በስዕላቸው ያልረኩት ተማሪዎች ርዕሰ መምህሩን እንደ ሞዴል አቁመው መሳል፣ ካልሆነም ይሳሉትን ማስተያየት አማራቸው። በአምሮት አልቀሩም አደረጉት። ፊት ለፊታቸው ቆመው ከያዙት ወረቀት ጋር እያስተያዩ ሲሟገቱባቸው የተመለከቱት ርዕሰ መምህር ግራ ተጋቡ።

“ልጆች ስለምን ትከተሉኛላችሁ?” አሉአቸው።

“ልንስልዎት”

“ማንን?”

“ሠይጣንን.. እርሶ ኖት ተብለናል።”

መምህሩ ያዘዘውን ስዕል በማግስቱ እያረመ ነው። ቃል እንደገባው አስደፈናቸው። ስዕሉን ላቆነጁት.. “ሚካኤልና ገብርኤልን አስመሰልካቸው.. ሠይጣንን ካልኩ ሠይጣንን እንጂ መልአክን አላልኩም” እያለ ከማፋጠጥ ጋር ማርካቸውን ቀነሰ። ስዕሉን አስቀያሚ ላደረጉት ቦነስ ጨመረ።

ከጥቂት ግነት ውጪ የጻፍኩት እውነት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top