አድባራተ ጥበብ

የኪን እና ከያኒያን ወቅታዊ ፈተና

መግቢያ

በቀደመው ጽሑፌ በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ ያመጣውን ፈተና ለመቋቋም ይሆን ዘንድ ለኪነጥበብ ባለሞያዎች አስቸኳይ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ አንስቼ ነበር። ሀሳቡ በዋናነት በእኛው ሀገር ያሉ እና ወረርሽኙ ያመጣውን ጉዳት መቋቋም ያልቻሉ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን የሚመለከት ይሁን እንጂ ጉዳዩን በንፅፅር በሌላው ዓለም ካለው ጋር በማስተያየትም ጭምር ነው። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዛ ያሉ የዓለማችን ቴአትር እና ሙዚቃ ማዘጋጃ ቤቶች ስራ አቁመዋል። በለንደኑ ‘ዌስት ኢንድ’ የሚገኙ ቴአትር ቤቶች እ.አ.አ. እስከ ነሀሴ መጀመርያ አይከፈቱም። በአሜሪካም በ’ብሮድዌይ’ የሚገኙ ቴአትር ቤቶች እስከ መስከረም መጀመርያ ድረስ ዝግ ሆነው ይቆያሉ። በዛ ያሉ ቴአትር ቤቶች ኪሳራ እያወጁ የሀገራቸውን መንግስት ድጋፍ እየጠየቁ ነው። ከድጋፍ ጥየቃው ባሻገርም አብዛኛዎቹ የቴአትር ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለመሙላት በማሰብ እና ለወቅቱ የሚሆን ገቢ ለማግኘት የቴአትር ሥራዎቻቸውን በ ኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት እና በዩቲዩብ (YouTube) ቻነሎች ለማቅረብ እየተጣጣሩ ነው። በዚህም ምክንያት እስከዛሬ ባልተለመደ ሁኔታ በተለይ በዩቲዩብ እጅግ የበዙ የተቀረፁ የቴአትር ስራዎችን መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል። የቴአትር ስራ በባህሪው ከታዳሚው ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በድረ ገፅም ሆነ በሌሎች መድረኮች ለመቅረብ የተመቸ ስራ አይደለም። ተመልካች እና ትዕይንት አቅራቢዎቹ በአካል መገናኘት አለባቸው። ግዴታ ነው። ነገር ግን የኮሮና ወረርሽኝ ባመጣው ችግር ምክንያት የቴአትር ጥንተ ተፈጥሮ ባልሆነው መንገድ ለመጓዝ በመላው ዓለም ያሉ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተገድደዋል። ከተዋናዮች እና አዘጋጆች እኩል ደግሞ ቴአትርን በገንዘብ በመደገፍ እና ትርፍ በማግኘት ኑሯቸውን የሚገፉ ባለሞያዎችም እንዲሁ አሳሳቢ ጉዳት ላይ ናቸው። በእንግሊዝ Corona Theater Club የተሰኘ የድረ ገፅ (ትዊተር) መገናኛ መድረክ በመፍጠር ተዋንያን በየቤታቸው ሆነው የቀረጿቸውን አጫጭር ቪዲዮዎች በትዊተር እና በዩቲዩብ በመጫን ተመልካች ለማግኘት ወዲያውም ጥቂት ገንዘብ ለመሰብሰብ እየታተሩ ነው።

በአፍሪካ ደግሞ ጉዳዩ ከዚህም የባሰ ነው። ታኩድዛ ቺሃምባክዌ በድረ ገፅ በሚወጣው “The African Theater Magazine” ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አሳሳቢ በሆነው የዚምባብዌ ቴአትር እና ክዋኔ ጥበብ እና በሰፊው የአፍሪካ ቴአትር እና ክዋኔ ጥበብ ላይ ባለሞያዎችን ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። እንደ ባለሞያዎቹ አባባል ወረርሽኙ በአፍሪካ ቴአትር እና የክዋኔ ጥበብ ስራዎች ላይ ከባድ ፈተና ደቅኗል። በተለይ አብዛኛው የኪነጥበብ ታዳሚ ኢንተርኔት በማይጠቀምበት እና የኪነጥበብ ስራዎቻችንም ሆኑ ማቅረቢያ ቤቶቻችን ለቴክኖሎጂ ብዙም ቅርብ ባልሆኑበት አህጉር ሞያው በኮሮና ምክንያት የሚደርስበት ፈተና እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህም ባለፈ በተለይ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ኪነጥበባዊ ስራዎች ህዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች እና በትናንሽ አዳራሾች የሚቀርቡ በመሆናቸው የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብሱ ስለሆኑ በቀላሉ በአጭር ጊዜ የመከፈት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። ማህበራዊ ዕርቀትን በጠበቁ መልኩ ይከፈቱ እንኳ ቢባል ወደ አዳራሹ በሚመጡ ትንሽ ቁጥር ባላቸው ተመልካቾች ሳብያ እዚህ ግባ የሚባል ገቢ አያገኙም። በዚህም ምክንያት የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች ኢኮኖሚያዊ ፈተና እጅጉን ከባድ ይሆናል።

ይህንን አስቸጋሪ ፈተና ለማለፍ በልዩ ልዩ የዓለም ሀገራት የኪነጥበቡን ኢንዱስትሪ ለመደገፍ እና ለማገዝ ከየሀገራቱ መንግስታት ልዩ ልዩ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ። በእኛም ሀገር መሰል እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን በቅርቡ ለመገንዘብ ችለናል። የኪነጥበብ ባለሞያዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምንያት የገጠማቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየተሞከሩ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ ሲሆን ጉዳዩን ግን ከዚህ በሰፋ መመልከት ያስፈልጋል።

ኪነጥበባችን ሰፊውን የፈጠራ ምህዋር ቀዝፎ ህብረተሰቡን ሊያነቃበት፣ ሊያስተምርበት እና ሊያውያይበት የሚችልበትን የፈጠራ ስራ ሰርቶ የተገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ማስቻል በየጊዜው የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ እና የኑሮ ተግዳሮት እንዲቋቋም ምክንያት ይሆነዋል። ኪነጥበባችን በተለይ በኢኮኖሚው ራሱን ችሎ፣ ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ እንቅፋት የሆኑት መሰናክሎች ኮሮናን የመሰሉ ባለሞያዎችን ረዘም ላለ ጊዜ ከቤት እንዳይወጣ የሚያደርጉ ፈተናዎች ሲጋረጡ ፊት ለፊት ዓይናቸውን አፍጥጠው ይመጣሉ። እነዚህ ተግዳሮቶችን ከስር መሰረታቸውን መርምሮ መፍትሄ ለመስጠት መሞከር ባንድ በኩል ፈጣን የሆነ የኪነጥበብ ዕድገት ዕውን ለማድረግ ሲረዳ በሌላ በኩል ደግሞ በነዚህ ፈተናዎች ምክንያት ልናጣ የምንችለውን የኪነጥበብ ፈጠራ እና ዕድገት እንዳያመልጠን መፍትሄ ይሆነናል። በኪነጥበቡ ላይ የተጋረጡትን ዋና ዋና ችግሮችን ለውይይት እንዲሆን ማንሳቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ጉዳዩ ሰፊ ጥናት እና ውይይት የሚያስፈልገው ቢሆንም በዛሬው ጽሑፌ ግን በወፍ በረር ዋና ዋና ያልኳቸውን ችግሮች ለውይይት መነሻ እንዲሆን ለማንሳት እወዳለሁ።

የኪነጥበብ ምልከታ

“ለሀገራችን እና ለስልጣኔአችን የወደፊት ጉዞ ሳስብ ለኪነጥበብ ባለሞያዎች ሙሉ ዕውቅና ከመስጠት ውጪ ምንም የተሻለ ነገር አይታየኘም። ኪነጥበብ ባህላችንን እንዲያለማ እና እንዲያሳድግ ከተፈለገ፣ ኅብረተሰባችን የኪነጥበብ ባለሞያውን ነፃ ለቅቆ ምናቡ ወደመራው እንዲጓዝ ሊፈቅድለት ይገባል።”

ጆን ኢፍ ኬኔዲ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት

የኪነጥበቡን ሰፊ ችግር ስንመረምር ዋነኛ ብለን ከምናነሳቸው ጉዳዮች አንዱ በሀገራችን ለኪነጥበብ ያለ ምልከታ መዛባት ነው። ለኪነ-ጥበብ ያለ ምልከታ ስል በጥቅሉ ኪነጥበብን መውደድ፣ ኪነጥበብን መተግበር፣ በኪነጥበብ መጠቀም እና ስለ ኪነጥበብ መመራመርን ሊያጠቃልል ይችላል። በሀገራችን ያለው የኪነጥበብ ምልከታ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው መልኩ ዥንጉርጉር ሆኖ እናገኘዋለን። በመንግስት በኩል ኪነጥበቡን የፖለቲካ መሳርያ ብቻ አድርጎ ከመመልከት ጀምሮ በህብረተሰቡ ዘንድ ደግሞ የኪነጥበብ ስራ የማዝናናት ዓላማ ብቻ ያለው አድርጎ መውሰድ በሀገራችን ሁለት በዋናነት የተለመዱ ጥግ የያዙ ሀሳቦች ናቸው። በነዚህ ሀሳቦች መሀል የሚያርፈው ኪነጥበባችን ዋነኛ ግቡ ምን እንደሆነ ግልፅ በሆነ ሁኔታ በልዩ ልዩ መንገዶች ለታዳሚው ሰፊው ህዝብ አልተዋወቀውም። በርግጥ ኪነጥበብ ለፖለቲካውም ሆነ ለማዝናናቱ ያላት ጠቀሜታ ከ-እስከ የሚባል አይደለም። ነገር ግን ሁሌም ፖለቲካ መስራት እና ሁሌም ማዝናናት ግን የኪነጥበብ ስራ አይደለም። የኪነጥበብ ሀሳብ ከዚህ እጅግ ይሻገራል። ኪነጥበብ ሀሳቦችን በመተንተን፣ ምናቦችን በመተግበር፣ ፍልስፍናዎችን በማብሰልሰል በሰዎች ህላዌ ላይ አንዳች ነገር ጠብ ለማድረግ ሌት ተቀን ከሚታትር አዕምሮ የምትፈልቅ የሀሳብ ድር ነች። ይህ የሀሳብ ድር ሰፊውን የሰው ልጅን ህይወት በመመርመር በልዩ ልዩ መልክ ሰብዓዊ ቀለሙ እንዲደምቅ፣ ህፀፆቹን እንዲያርም፣ ተስፋውን እንዲያለመልም እና ዕሴቱን እንዲያዳብር የሚረዳ እና የሚያግዝ ነው። ሲለውም መፍትሄ በሌላቸውን ሰፋፊ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር መፍትሄ የሚሰጥ ነው። በዓለም ላይ በየጊዜው የተነሱ ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ፍልስፍናዎችን ስንመለከት ዋነኛ ዓላማቸው በራሳቸው ጊዜ እና ቦታ ያገጠሙ ችግሮችን የመፍቻ መንገዶችን ከመፈለገ የመነጩ ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ መፍትሄ የመሻት ህልሞች ግን መፍትሄዎቹን ከፖለቲካ ሰልፎች ወይም ከማዝናናት ጋር ብቻ የተጣመሩ አይደሉም። ከዚህም በሰፋ መፍትሄዎቹ እንደነገሩ ሁኔታ ከማብሰልሰል፣ ከመተንተን፣ እና የተግባር መንገዶችን ከመተለም ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ኪነጥበብቡ እና ተግባሩን ስናስብ ከአንድ ዘርፍ እና መንገድ ጋር ብቻ ማቀናጀት እና ማያያዘ ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም።

በአንድም ወይም በሌላ መንገድ መንግስታዊ መነሾ ያለው የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ አጭር በሚመስለው ጉዞው ከሀገሪቱ መንግስታት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። አሁንም አለው። ባለፉት መቶ ዓመታት የተለዋወጡት የኢትዮጵያ መንግስታት ይህንን ጥብቅ ግንኙነቱን በመጠቀም ኪነጥበቡን ከማገዝ በላይ በሰፊው ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ማስፈፀሚያ መሳርያ አድርገው ተጠቅመውበታል። አሁንም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። መከራከርያው ያለው ‘ለምን ተጠቀሙበት?’ ላይ ሳይሆን ‘ተጠቅመውበት ምን ጠቀሙት?’ የሚለው ላይ ነው። ኪነጥበቡ የመንግስትን ፍላጎት ከሟሟላት ባሻገር በምላሹ እንዲህ ነው የሚባል ልማት እና ድጋፍ አላገኘም። ቴአትር ቤቶቻችን አሁንም በጣት ከሚቆጠሩ እና በልዩ ልዩ ምክንያት በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከተሰሩት ውጪ የተጨመረ የለም (እነሱም አሁን ሶስት ብቻ ሆነዋል። ሁለቱ በግንባታ ሰበብ ስራ አቁመዋል።)፣ የሙዚቃ እና የፊልም መሳርያዎች አሁንም መንግስት ዘንድ የ‘ቅንጦት እቃ’ ሆነ ይቆጠራሉ ፤ ይህንንም ያማከለ ቀረጥ ይቀረጣሉ፣ የስዕል ስራዎች ማሳያ ይሄ ነው የሚባል ቦታ የለም፣ ሀገር በቀል ክዋኔዎች የሚያድጉበት እና የሚስፋፉበት መንገድ አልተቀረፀም፣ የፊልም እንቅስቃሴው በከፍተኛ ተግዳሮቶች በየዕለቱ የሚፈተን ነው። በዚህ ሁሉ ፈተናው መሀል ግን አሁንም መንግስት በኪነጥበቡ መጠቀም እንጂ ኪነጥበቡ ያን ስለመጠቅም አያስብም። ትልቁ ፈተና ይሄ አመለካከት ነው። መንግስት በኪነጥበቡ ስለመጠቀም እንደሚያስበው ሁሉ ኪነጥበቡን ስለመጥቀምም ሊያስብ እና ሊጨነቅ ይገባል። ኪነጥበቡ ለመንግስት ልዩ ልዩ ሥራዎች ጠቃሚ ነው ብሎ እንደሚያስበው ሁሉ ማህበረሰቡም ይህንን ጠቃሚነቱን እንዲረዳ የኪነጥበብ ባለሞያዎችን ማገዝ እና መደገፍ ያስፈልገዋል። መንግስት ኪነጥበቡን ሊመራ የሚችል ጠንካራ ተቋም ማቋቋም ይገባዋል። ኪነጥበብ፣ ባህል እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ አሁን እየተመሩ እንዳለው ሶስቱንም ባንድነት ሳይሆን በየራሳቸው እጅግ ሰፋፊ ጉዳዮች እና ተግባራት ስለሆኑ እያንዳንዳቸው በሚገባ ከተመሩ እና ስራቸው ተግባራዊ ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ አላቸው። ኢትዮጵያ ሰፊ የሆነው የቱሪዝም ሀብቷን፣ ተዝቆ የማያልቀውን የክዋኔ ጥበብ እና መሰል ባህላዊ እንቅስቃሴዋን እንዲሁም ከዓለም የኪነጥበብ ጉዞ አንፃር በአንድ አንድ የኪነጥበብ አይነቶች የቆየ ልምድ ባላት የኪነጥበብ እንቅስቃሴዋ ጠንካራ የሆነ የአመራር እና እገዛ ስራ ብትሰራ በዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅሞች በሰፊው ትቋደስ ነበር። መንግስት ምናልባት ዘርፎቹን በተናጠል መምራት እና ማገዝ ቢችል እና በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች በጥንቃቄ ብልሀት በተሞላበት እርምጃ ለመፍታት ቢሞክር፣ ከእያንዳንዱ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ያስችለው ነበር።

በኪነጥበቡ ላይ ያሉትን የአመለካከት ችግሮች ለመቅረፍ ከመንግስት ባሻገር የኪነጥበቡ ባለሞያ ሚና ከፍተኛ ነው። የኪነጥበብ ባለሞያው ስራው በተለምዶ እንደሚባለው ከ’ማዝናናት’ ባሻገር ሰፊ የሆነ ግለሰባዊ እና ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ እንዳለው በስራው ማሳየት አለበት ፤ ማስተማር አለበት። በሚሰራቸው ቴአትሮች፣ ሙዚቃዎች፣ ፊልሞች፣ የስዕል ስራዎች፣ እና ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ስልቶች የኪነጥበብ ስራ ለሰው ልጆች ህላዌ፣ ለማህበራዊ መስተጋብር እና ለኢኮኖሚ እድገት የሚጫወተውን ሚና በሚገባ ማ ስ ተ ማ ር እና ማስረዳት ይጠበቅበታል። ከዚህም ባሻገር መንግስት ልዩ ልዩ ድጋፎችን እንዲያደርግ በተደራጀ መልክ ማሳወቅ፣ መግፋት እና ማገዝ ያስፈለግዋል።

በኪነጥበቡ ላይ ያለ አመለካከት በሚስተካከልበት ጊዜ የኪነጥበብ ባለሞያው ተገቢውን ስራ መከወን የሚችልበት ከባቢያዊ ሁኔታ ይፍጠራል። ይህ ከባቢያዊ ሁኔት በመንግስት ደጋፊ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ የድጋፍ ተግባራቶች እና የተሟላ መሰረተ ልማቶች ይታገዛል። በዚህም የኪነጥበብ ስራዎች የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ይከውናሉ፣ የሚገባቸውን ገቢ እና ክፍያ ያገኛሉ። ለስራቸው የሚገባቸውን ዋጋ ሲያገኙ የኮሮና ወረርሽኝን የመሳሰሉ ድንገተኛ ችግሮች ሲከሰቱ የመንግስትን እና የህዝብን ደጅ ለመጥናት አይቸገሩም። እንዲያውም ኪነጥበቡ መንገዱ ከተመቻቸለት ከፍተኛ የሆነ ሀብት የማመንጨት አቅም ስላለው፣ ለመንግስትም ሆነ ለህብረተሰቡ ተጨማሪ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ሊያደረግ ይችላል።

ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ እና ደንቦች

በአንድ ሀገር ለህዝቡ የሚጠቅሙ እና የመንግስቱን ስርዓት የሚያግዙ ህጎች፣ ፖሊሲዎች እና የአሰራር ደንቦች በተለያየ ጊዜ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ሲባል ይወጣሉ። እነዚህ ህጎች እንደሁኔታቸው እና አስፈላጊነታቸው ቅድሚያ እየተሰጣቸው ተግባራዊ ይሆናሉ። ተግባራዊ ሲሆኑ ግን ጉዳዩን እና ስራውን እንዲያግዙ እና እንዲደግፉ ነው። በሀገራችን ኪነጥበቡ እንዲያግዙ እና እንዲደግፉ ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ ልዩ ልዩ ህጎች ቢወጡም ያን ያህል ግን ኪነጥበቡን ሲደግፉ አይታዩም። ይባስ ብለው አንዳንዶቹ ኪነጥበቡን የሚያቀጭጩ እና የሚያደክሙ ናቸው። ለምሳሌ በቅርቡ ቢሻሻልም የኪነጥበብ ባለሞያው የሚጮህበት የቀረጥ ጉዳይ ብናነሳ ኪነጥበቡ ከመደገፍ ይልቅ መጉዳት ላይ የሚያተኩር ነበር። ይህም ከላይ ያነሳሁትን ሀሳብ ይደግፋል። ለኪነ-ጥበብ ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ እንደ “የቅንጦት እቃ” መቆጠራቸው ኪነጥበብ ዋነኛ የሀገር እድገት መሳርያ ወይም ደጋፊ ሆኖ ከመታየቱ ይልቅ የትርፍ ሰዓት ስራ እና የቅንጦት ጉዳይ አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ነው። ይሄ በሁለት መንገድ ይታያል። በአንድ መልኩ ይህን ህግ ያወጡ የታክስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ባለሞያዎች በትምህርት ሂደታቸው የኪነጥበብን አቅም እና ጠቀሜታ አልተረዱትም (ከታች እመለከተዋለሁ)፣ በሌላ መልኩ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ይህንን የኪነጥበብ ጠቀሜታ በተግባር በታገዘ መልኩ አላስረዳንም። በነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከታክስ ጋር ተያይዞ ያለው የመንግስት ህግ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪውን ከመደገፍ ይልቅ ማሸማቀቅ እና መስበር ላይ ያተኩራል። በእያንዳንዱ የኪነጥበብ ስራ ሰንሰለት ላይ ያለው የታክስ፣ የህግጋት፣ የድጋፍ ማነስ እና ልዩ ልዩ አላስፈላጊ ህጎች ምክንያት የኪነጥበብ ሥራዎች በተፈለገው መንገድ ሊጓዙ አልተቻላቸውም። በመሆኑም አብዛኞቹ ኪነጥበብን የተመለከቱ ህጎች ሙያውን ከማገዝ ይልቅ ጎታችነታቸው ይጠነክራል።

ከታክስ ህጎች ባሻገር ከ 1983 ዓ.ም. ወዲህ ኪነጥበብን ሳንሱር የማድረግ ጉዳይ በህግ የታገደ ቢሆንም በተግባር ግን ይሄ አይታይም። በተለይ የክዋኔ ጥበቡ ላይ የነበረው እና ያለው የቀጥታም ሆነ የእጅ አዙር ሳንሱር ጉዳይ አሁንም አልባት አላገኘም። መንግስት ሙሉ ለሙሉ ከኪነጥበቡ ላይ እጁን ባለማንሳቱ ምክንያት የኪነጥበብ ባለሞያው ራሱም ሆነ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ሰርቶ ለመኖር አልታደለም። ህገ መንግስታዊ አዋጁን በተጻረረ መልኩ ቴአትሮች ሳንሱር ሲደረጉ፣ የሙዚቃ ስራዎች ሲታገዱ ወይም ባለሞያው ሲዋከብ እና ሲታሰር፣ የፊልም ስራዎች ማሳያ ፍቃድ ሲከለከሉ እና መሰል ተግባራት ለኪነ ጥበብ ባለሞያው አዲስ አይደሉም፣ የተለመዱ እንጂ። ጠንካራ የሙያ ማህበር በሌለበት፣ ጠቃሚ የኪነጥበብ ፖሊሲ ባልተቀረፀበት ወይም አንድ አንድ የተቀረፁትም በአግባቡ ተግባራዊ ባልሆኑበት፣ ህገ መንግስታዊ ነፃነቱ በተገፈፈበት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የሚሰራ ኪነጥበብ “አለ” ተብሎ መክረሙ እንዲሁም ሻል ሲል በዛ ያሉ ስራ ማሳየት መቻሉ በራሱ የሚደንቅ ነው። መንግስት የኪነጥበብ እንቅስቃሴውን ሲያሻው የሚጠቀምበት፣ ሳይፈለግ ሲቀር ዞር ብሎ የማያየው፣ ድጋፍ ለመስጠትም ብዙም የማይሳሳለት አካሉ ነው። ይሄ ደግሞ በሀገሪቱ ስልጣን ላይ በቆዩ የተለያዩ መንግስታት በይፋ ታይቷል። እንዲህ በችግር እና በድጋፍ ማጣት የተተበተበው ኪነጥበብ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስራው ሁሉ ሲቆም መንግስት ለልዩ ልዩ መስኮች ከሚያደርገው ድጋፍ በጥቂቱ እንኳ እንዲደርሰው እጁን አልዘረጋለትም። ወይም መዘርጋቱን አላሳወቀም፣ አላሳየም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ተገኝተው የኮሮና ወረርሽኝ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ እንዳይጎዳ መንግስት ምን እንዳደረገ በየዘርፉ ሲያብራሩ እና ድጋፉን ሲገልጡ አንድም ቦታ ግን ለኪነጥበቡ የተደረገውን ድጋፍ አላነሱም። ይህም በመንግስት ዘንድ ስለ ኪነጥበብ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳይ ነው።

በተደጋጋሚ እንደታየው መንግስት ኪነጥበቡን እንደ አንድ የልማት አካል ተመልክቶ ፖሊሲ ለማውጣት እና ለማገዝ ፍላጎት የለውም። ይሄም ከላይ ካነሳሁት ከአመለካከት መዛባት፣ ጉዳዩን ካለመረዳት እና በኪነጥበቡ ባለሞያዎች በኩል ለመንግስት የኪነጥበብን አቅም እና ጉልበት ካለማስረዳት ይመነጫል። እንዲያም ሆኖ ግን ጥያቄው ከነመፍትሄው መቀጠል አለበት። መንግስት ኪነጥበቡን ሊያግዝ የሚሻ ከሆነ በአንድ ቢሮ የሚመራም ቢሆን በጠቅላላው ግን ሰፊውን የመንግስት መዋቅር ባካተተ መልኩ ከኪነጥበቡ ባለሞያዎች ጋር ተማክሮ ጥንካራ የኪነጥበብ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልገዋል። ይህ ፖሊሲ ኪነጥበቡ ለሀገር ሊያበረክት የሚችለውን አቅም የሚገነዘብ እና እውቅና የሚሰጥ፣ መንግስት እና የመንግስት መዋቅር ለኪነጥበብ እድገት የየራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል፣ እንዲሁም ኪነጥበቡ በሀገሪቱ ልማት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ የሚጋብዝ መሆን ይገባዋል። መንግስት ከኪነጥበብ ከመጠቀም አልፎ ኪነጥበቡ መደገፉ በሌላ መንገድ የራሱን የልማት እና የዕድገት መንገድ መደገፉ ነው። ምንም እንኳ የኪነጥበቡ ማህበረሰብ በቁጥር ሲሰላ ከንግዱ ወይም መሰል ከሆኑ የስራ ዘርፎች ከተሰማራው የሰው ሀይል ያነሰ ቢመስልም በሰፊው ከታሰበበት እና በትክክለኛ ፖሊሲ ከተመራ ግን ሰፊ የሆነ ድጋፍ ለሀገር ያበረክታል። በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥ በዝርዝር ጉዳዩን ባልሄድበትም በሌላ ዓለም የሚታየው ይሄው ሀቅ ነው። ስለዚህ በጥቅሉ ጠንካራ የሆነ የኪነጥበብ ፖሊሲ በመቅረፅ በዝርዝር ደግሞ ለየኪነጥበብ ዓይነቱ በተናጥል ህግጋት እና የአሰራር ደንቦችን ከኪነጥበብ ባለሞያዎች ጋር በጋራ ተማክሮ በማውጣት ማስፈፀም ያስፈልጋል። ፖሊሲዎች ጠቃሚ እንኳ ቢሆኑ በተግባር ስራ ላይ ካልዋሉ ጠቀሜታቸው ያን ያህል ነው። ስለዚህ ፖሊሲው ሲቀረፅ ተግባራዊ መሆኑ መከታተል እና ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት አካላት እና መዋቅሮች ለተግባራዊነቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ መከታተል፣ ማስተማር እና ማገዝ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ከፖሊሲው ባሻገር ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚወጡ ህግች እና የአሰራር ስርዓቶች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል። ትንሽ የሚመስሉ ነገር ግን የኪነጥበብ ስራ እንቅስቃሴን የሚያግቱ አሰራሮችን ኪነጥበቡን ከሚመለከቱ መንግስታዊ መዋቅሮች በማስወገድ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው።

የትምህርት ስርዓት እና ኪነጥበብ

“ራሴን እና አስተሳሰቤን ስፈትሸው፣ በመጨረሻ የደረስኩበት ድምዳሜ እውቀትን ከመቅሰም በላይ ለምናብ ያለኝ ተሰጠኦ ከፍ ያለ ሆኖ ማግኘቴ ነው።”

አልበርት አንስታይን

ኪነጥበቡን እንዲያድግ እና እንዲስፋፋ ብሎም ባለሞያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚያግዙ ዋነኛ ተግባራት መሀል የትምህርት እና ኪነጥበቡ መቀራረብ ነው። የኪነጥበብ ትምህርት ስል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ስልጠና ብቻ ማለቴ ሳይሆን በተለይ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ባሉ የትምህርት ዕርከኖች ሊሰጥ የሚገባውን ነው። ከመደበኛው የትምህርት አሰጣጥ አካል ሆኖ የኪነጥበብ ትምህርት ቢሰጥ እጅግ በብዙ ረገድ ለኪነጥበቡ እድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ ያበረክታል። መሰረታዊ የሆኑ ሶስት መከራከርያ ሃሳቦችን ብናቀርብ፣ አንደኛ የኪነጥበብ ተሰጥኦ እና ፍላጎት ያላቸው ልጆች ገና ከአፍላነታቸው ጀምሮ ኪነጥበቡን እየተለማመዱት ስለሚያድጉ ብዙ መስራት በሚጠበቅባቸው የወጣትነት ጊዜያቸው መሰረታዊውን ዕውቀት ለመረዳት ጊዜ እና ጥረት ሳይጠበቅባቸው ኪነጥበቡን ወደ መደገፍ ያመራሉ። ይህም በወጣት ነገር ግን በፈጠራ እና በዕውቀት የታገዘ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪ እንዲገነባ ትልቅ ድርሻ ይጫወታል። ሁለተኛ በትምህርት ሂደታቸው ለኪነጥበብ የተሰጠ ፍላጎት ባይኖራቸው እንኳ ኪነጥበብን የሚያደንቅ፣ የሚወድ እና የሚደግፍ የማህበረሰብ አካል ይሆናሉ። ዞሮ ዞሮ በሀገሪቱ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የህግ፣ የጤና እና መሰል ጉዳዮችን የሚዘውሩት እነዚሁ ወጣቶች በመሆናቸው ለኪነጥበብ የሚኖራቸው ምልከታ ከመደበኛው የትምህርት ገበታቸው ጀምሮ ከታረቀ ዛሬ የምንናገርባቸው ጉዳዮች በቀላሉ መፍትሄ ያገኙ ነበር። ኪነጥበቡን የሚረዱ፣ የሚያደንቁ እና በኪነጥበቡ የሚጠቀሙ የመንግስት እና የስራ ኃላፊዎች በየቦታዎች ሲገኙ ኪነጥበቡም ለማደግ እና ለመስፋፋት ሰፊ በር ተከፈተለት ማለት ነው። ይህም ዞሮ ሲደመር ኪነጥበቡ ለሀገር ሊያበረከት ይችል የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ድርሻን እንዲያሰፋ ምክንያት ይሆነዋል። በርግጥ ይህ መፍትሄ በአጭር ጊዜ ሊፈቱ ለሚገባቸው ችግሮች ዋነኛ እና አዋጩ ባይሆንም በረዥሙ የሀገሪቱ የእድገት ጉዞ ውስጥ ግን ኪነጥበቡ የራሱን ድርሻ እንዲጫወት በትልቁ እንደሚያግዘው ጥርጥር የለውም። ሶስተኛም የኪነጥበብ ትምህርት የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አካል ማድረግ የየቦታውን ባህል እና ቋንቋ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አለው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመሰጠቱ ዋነኛ ዓላማ የአካባቢውን ባህል እና ቋንቋ ተማሪዎቹ እንዲያሳድጉት እና ሌሎችም በተጨማሪነት እንዲማሩት ነውና የኪነጥበብ ትምህርት ይህንን ዓላማ በልዩ ልዩ መንገድ (በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በስዕል…ወዘተ) ያግዙታል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለህፃናት ትምህርትን በቀላሉ ለማስተማር ኪነጥበብ የተሻለ መንገድ ነው። ስለዚህ ሰፊውን የኪነጥበብ እንቅስቃሴ እንደግፍ ብሎ የመነሳት ቀና ፍላጎት በመንግስት ዘንድ ቢፈጠር የመጀመርያው ነገር ግን በረዥም ጊዜ ውስጥ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችለውን ሀሳብ በመያዝ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አካል በማድረግ ኪነጥበቡን በዘላቂነት ለማገዝ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል።

የኪነጥበብ ማህበረሰብ ትብብር

ከላይ በጥቂቱ ያንሳኋቸው ሃሳቦች በዋናነት መንግስትን የሚመለክቱ ቢሆኑም ከመንግስት ባልተናነሰ ሁኔታ ግን የኪነጥበብ ባለሞያዎችም ሚና አላቸው። የኪነጥበብ ባለሞያዎች ጠንካራ እና የተደራጅ ማህበር በመመስረት ኪነጥበቡ ሊኖረው የሚገባውን እና የሚችለውን መልክ በማሳየት መንግስትን እና የኪነጥበብ ተጠቃሚ ህብረተሰቡን ማስተማር እና ማንቃት ያስፈልጋቸዋል። ጠንካራ የኪነጥበብ ማህበራት በየጊዜው በመንግስት የሚወጡ ህግ እና ፖሊሲዎችን የሚሞግቱ፣ ማህብረሰቡ የሚያስፈለገውን የኪነጥበብ ስራ በምርምር ተደግፈው የሚተልሙ፣ ኪነጥበቡን የሚያግዙ አዳዲስ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች እና ህጎች እንዲወጡ የሚያተጉ፣ ኪነ ጥበብ ከማዝናናት ባሻገር ያላትን ሚና የሚያስተምሩ እና የሚያሳዩ ሊሆን ይገባቸዋል። በሀገራችን በየዘርፉ ያሉ የኪነ ጥበብ ማህበራት ይህንን ከማድረግ አኳያ ድካም ይታይባቸዋል። የድካማቸውም ምክንያት ብዙ ቢሆንም (ጥናትም ያስፈልገዋል) በጠቅላላው ግን ኪነጥበቡ ሊኖረው የሚገባውን ሚና የማሳወቅ እና የማስተማር ድርሻ ይጫንባቸዋል። እንደኛ ባሉ የሰፋ የኪነጥበብ መነሻ ሀብት ኖሯቸው እንቅስቃሴያቸውን ግን ጀማሪ ለሆኑ ሀገራት ግለሰባዊ እርምጃዎች የትም አያደርሱም። የኪነጥበብ ዘርፉ የተጋረጠበት እና ያለበት ፈተና ብዙ በመሆኑ ምክንያት የተደራጀ እና የጠነከረ ማህበራት እና ተቋማት ያስፈልጉታል። እነዚህ ማህበራት እና ተቋማት የኪነጥበቡ ፈተናዎች በጥናት ተደግፎ በትኖ በማውጣት ደረጃ በደረጃ መልስ እንዲሰጣቸው መሞገት እና መስራት ይገባቸዋል። መንግስት መልስ ሊሰጥባቸው እና ተግባራዊ እርምጃ ሊወስድባቸው የሚገቡ እንዳሉ ሁሉ የኪነጥበብ ባለሞያዎም ሊሰሯቸው የሚገቡ ስራዎች አሉ። እነዚህ ስራዎች በተለይ ኪነጥበብ በማህበራዊ እና ሀገራዊ ልማት ላይ ያላትን እና ሊኖራት የሚችለውን ሚና አጉልተው የሚያሳዩ ተግባራዊ ምላሾች ናቸው። እነዚህ ምላሾች ህብረተሰቡን ያስተምራሉ፣ የኪነጥበብ አመለካከትን ይቀይራሉ፣ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ያግዛሉ።

ኪነጥበባዊ ፍልስፍና እና መርሆ

ኪነጥበባዊ ፍልስፍና እና መርሆ (Artistic philosophy and Principle) ስል ለሀገራችን ኪነጥበብ እንደ ፍልስፍና እና መርህ የሚቆምለት እና የሚተነትነው ሃሳብ፣ ተግባር፣ ዓላማ ማለቴ ነው። በርግጥ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሰፊው የፍልስፍና ማዕቀፉ ምንድነው? የሚቆምለት መርህ ምን ይመስላል? ስለምን ይፅፋል? ስለ ምን ይከውናል? ስለምን ይዘፍናል? ወዘተ…ለእነዚህ ጥያቄዎች “እንደ ኪነጥበብ ባለሞያው ፍላጎት፣ አቋም፣ ፍልስፍና እና መርሆ ይመሰረታል” የሚል መልስ ከብዙ መላሽ እንደምሰማው እጠብቃለሁ። በተወሰነ ደረጃ እኔም እጋራዋለሁ። ነገር ግን በአጠቃላዩ፣ እንደ ማዕቀፍ ሆኖ በኪነጥበብ ባለሞያዎቻችን ዘንድ የተንሰራፋው ዋና ሀሳብ ምንድነው ስንል ብዙም የጠራ ምስል አናገኝም። ለምሳሌ የጊዜው የማህበረሰባችን አስጨናቂ ጣጣ የሆነው የብሄር ጉዳይ ላይ የኪነጥበቡ ሰፈር ምን ያስባል? ምን ይሰራል? ምንስ ያልማል? ብለን ብንጠይቅ አሁንም መልሱ ምናልባት አንድ አንድ የኪነጥበብ ባለሞያዎች በግላቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር እንዲህ ነው ብለን የምናወራለት ነገር አናገኝም። ለምሳሌ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፤ ጦርነቱ ባስከተለው ከፍተኛ ማህበራዊ እና ግለሰባዊ ጉዳት ሳቢያ በአውሮፓ ያሉ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተስፋ አስቆራጭ በሆነ አስተሳሰብ ተጠምደው ነበር። የህይወትን ረብ የለሽነት እና ባዶነት በማስረጃ እየተነተኑ እስከመፃፍ ደረሱ። ይሄ ተስፋ የመቁረጥ ሀሳብ ከፍ ብሎ በኪነጥበብ ስራዎቻቸው ላይ መንፀባረቅ ጀመረ። ቆይቶም ፍልስፍና ሆኖ ወለፈንዲነት (Absurdism) እና ተያያዥ ፍልስፍናዎችን ፈጠረ። ይህ ፍልስፍና በአውሮፓ ገንኖ በልዩ ልዩ የኪነጥበብ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሞያዎች ጥቅም ላይ አዋሉት። ዛሬም ድረስ በመላው ዓለም ያሉ በሀሳቡ የሚስማሙ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተግባራዊ ያደርጉታል። የአሜሪካ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ምንም እንኳን የሀሳብ ነጻነት የተረጋገጠባት ሀገር ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ ምንም እንኳ የኪነጥበብ ባለሞያዎች የግል አቋማቸውን በማራመዳቸው አንዳች ነገር ይደርስብኛል ብለው የሚያስቡበት ሁኔታ ውስጥ ባይሆኑም፣ እንደ ሀገር የአሜሪካንን ጉዳይ በሚመለከቱ ሁኔታዎች ግን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አቋምን ያንፀባርቃሉ። በኪነጥበብ ስራዎቻቸው የሀገራቸውን ሀያልነት እና የስልጣኔ ማማ ያሳያሉ። የህንድ የኪነጥበብ ባለሞያዎችም ተመሳሳይ መንገድን ይከተላሉ።

የእኛስ ሀገር የኪነጥበብ ባለሞያዎች በጠቅላላው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምን ያስባሉ? ምንስ ያሰራሉ ብለን መጠየቅ ኪነጥበቡ የሚሄድበትን ጎዳና ለመለየት ብሎም የወደፊት ጉዞውን ለመተለም ይበጀዋል። ኪነጥበባዊ ፍልስፍና እና መርህ ከሌለው ግን ሁሉም በተናጥል በሚያደርገው ሩጫ እንዲህ ነው የሚባል ቀለም ሳይኖረው ባክኖ ይቀራል። የጠራ ፍልስፍና እና መርህ ኪነጥበቡን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመተለም እና ለችግሮች የመፍትሄ ሀሳብ ለማመንጨት በር ይከፍታል። ይህን ስል ግን ሁሉም የኪነጥበብ ባለሞያዎች ተመሳሳይ ፍልስፍና እና ተመሳሳይ መርህ ይከተሉ ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ዋና ዋና በሚባሉ ሀገራዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ተመሳሳይነት ቢኖር እና ግላዊ ተግባራት ቢኖሩ የተሻለ የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ሊኖረን ይችል ነበር።

በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ የኪነጥበባችን መንደር ከሀሳብ ሰጪነት እና መሪነት ወደ ተቀባይነት እና ጊዜው እና “ተመልካቹ” የሚፈለገውን የሚያቀርብ ሆኗል። የኪነጥበባችን መንደር የሚያስጨንቀው የሚመስለው ተመልካች ምን ፈለገ? አድማጭ ምን አሰኘው? ታዳሚ ለምን ያጨበጭባል? እንጂ ተመልካችን ምን ያስፈልገዋል? ለአድማጩ መንገድ የሚያሳይ ምን ሙዚቃ ላቅርበለት ወይም ታዳሚውን እንዴት እንዲብሰለሰል ላድረገው የሚለው ብዙ አያለፋውም። እንደውም ታዳሚውን ሊገራ የሚችል፣ ሃሳብ ሊያቀብል አቅም ያለው የኪነጥበብ ስራ መስራት አልፎ አልፎ የ“አወቃለሁ” ባይነት ምልክት ተደርጎ መወሰድም ተጀምሯል። የታዳሚውን የሳቅ እና የቧልት ልብ ትርታ እያዳመጡ የኪነጥበብ ስራዎችን ማቅረብ “የብልህነት” እና “የዘመኑ ሰው” መሆን ሆኗል። ነገር ግን ኪነጥበባችን ከዚህ በጭብጨባ ልቡ ከወለቀበት አዙሪት መላቀቅ አለበት። በተመጠነ ምርምር፣ በሰላ አስተሳስብ እና አርቆ በሚመመለከት መነፅር ማህበረሰቡን፣ ሀገሩን እና ራሱን ተመልክቶ ሞያዊ አብርክቶውን ሊያሰፋ ይገባል። ከዚህ ማዕቀፍ በመንሳትም የራሱን ፍልስፍና እናም መርህ ማደራጀት ይችላል።

ልዩ ልዩ ድጋፎች

ድጋፎች መልክ አላቸው። መንግስታዊ፣ ግለሰባዊ፣ ድርጅታዊ ወይም ሌላ ዓይነት ድጋፎች ሊሆኑ ይችላሉ። ኪነጥበባችን እንዲያድግ ከላይ ካነሳኋቸው ችግር እና መፍትሄዎች ባሻገር ልዩ ልዩ (በተለይ ኢኮኖሚያዊ) ድጋፎች ያስፈልጉታል። እነዚህ ድጋፎች ኪነጥበባችን በተለያየ ጊዜ የሚጋረጡበትን ፈተናዎች ከመሻገር ባለፈ በየጊዜው ለሚኖረው እንቅስቃሴው ብርታት፣ ለስራውም ምርኩዝ ይሆኑታል። በሌሎች ዓለማት ያሉ የድጋፍ ዓይነቶች ማለትም መንግስታዊ የውድድር ድጋፎች፣ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፎች፣ ዓመታዊ ውድድሮች፣ ፌስቲቫሎች እና ሀገራዊ እና ዓለም-አቀፋዊ ሽልማቶች በልዩ ልዩ መንገድ የእኛንም ሀገር ኪነጥበቡ ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራት ናቸው። በሀገራችን ታቅዶበት እና ይሁነኝ ተብሎ ለኪነጥበቡ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚሰጡ ፤ በምላሹ ምንም የማይጠይቁ ድርጅቶች መመልከት ብዙም የተለመደ አይደለም። መንግስትም ቢሆን በየጊዜው ለኪነጥበብ ባለሞያዎች የሚያደርገው ድጋፍ ከአንድ መንግስታዊ ከሆነ ተግባር ወይም እገዛ ጋር የተቆራኘ እንጂ ራሱን ችሎ፣ ሆነ ተብሎ ኪነጥበቡን ለማገዝ በሚል የሚደረግ አይደለም። በመሆኑም በዋናነት ኪነጥበቡን ለማገዝ የሚቆሙ ተቋማት በልዩ ልዩ መልኩ እንዲበራከቱ ከመንግስት፣ ከኪነጥበቡ ባለሞያዎች እና ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት የጋራ ተግባር ያስፈልጋል። የኪነጥበብ ባለሞያዎች ለሚሰሯቸው ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ስራዎች የግለሰብ ባለሀብቶችን፣ ነጋዴ ድርጅቶችን፣ ከኪነጥበቡ ጋር ዝምድና የሌላቸውን ተቋማት ደጅ ከመጥናት ተላቅቀው የኪነጥበቡ አጋዥ ከሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ እንዲሰሩ መንገዱን መጠረግ እና መመቻቸት አለበት።

ነገር ግን የኪነጥበባችን ባለቤት ማን ነው?

ይህን ሁሉ የምናወራለት ኪነጥበባችን ግን ባለቤቱ ማነው? የመሰናበቻ ጥያቄዬ ነው። በተለያየ ጊዜ የሚመጡ መንግስታት ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ኪነጥበቡን ለፖለቲካቸው ግብዓት መጠቀሚያ መሳርያቸው እንጂ የራሳቸው ንብረት፣ የመንግስት መዋቅራቸው አንድ አካል፣ የልማት ማህበራቸው አባል አድርገው ሲቆጥሩት አይስተዋልም። ቆጥረውትም አያውቁም። በዚህም ምክንያት በየጊዜው መንግስት ለኪነጥበቡ ትኩረት ይስጥ እየተባለ የሚወተወተው በሌላ አማርኛ ሙሉ ለሙሉ፣ ባይችል እና ባይሆንለት እንኳ በከፊልም ቢሆን ባለቤት ይሁንለት ማለት ነው። በኪነጥበቡ ሰፈር ስንመለከተው ደግሞ ጠንካራ የሆነ የባለሞያዎች ማህበር ስለሌለ ኪነጥበቡን የኔ ነው፣ እንዲህ ነው ብሎ የሚሟገትለት አካል የለም። ቢኖርም በተናጥል እና የራሱን የተለየ ዘርፍ ጥቅም ለማስጠበቅ ይሯሯጣል እንጂ በሰፊው የኪነጥበቡን እንቅስቃሴ የሚረዳ አካሄድ ሲሄዱ አይታዩም። በመሆኑም ገፋ አድርገን፣ ከሁሉም አቅጣጫ ስንመለከተው ኪነጥበባችን እንዲህ ነው የሚባል ባለቤት አናገኝለትም። ባለቤት አልባ መሆኑ ደግሞ ችግሮቹ ከብዙ ማዕዘናት እንዲፈልቁ መልሱን ደግሞ እጅግ ውስብስብ እንዲሆን ያደርገዋል። ባለቤት አልባነቱ በእያንዳንዱ ዘርፍ ያሉትን ችግሮች እና የስኬት እንቅፋቶችን ስንመለክት እናገኘዋለን።

ማጠቃለያ

የኮሮና ወረርሽኝ ባንድ በኩል የኪነጥበብ ባለሞያዎችን የኑሮ ሁናቴ መፈተኑ ቢያስደነግጠንም በሌላ መልኩ ግን የኪነጥበቡን ችግር እና ፈተና ጠለቅ ብለን እንድንረዳው እና እንድንፈትሸው መንገድ የሚከፍት ይመስለኛል። ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ መመልከቱም መፍትሄውን ከአጭር ጊዜ አላቆ ዘላቂ እና ሁነኛ እንዲሆን ያስችለዋል። ኪነጥበባችን እና የኪነጥበብ ባለሞያዎቻችን ዛሬ በኮሮና ምክንያት የተጋረጠባቸው ፈተና ዘላቂ መፍትሄ ተሰጥቶት በሰፊው ካልተሰራበት ነገም ከዚሁ አዙሪት ያለመውጣት እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑ ኪነጥበባችን እንዲያድግ እና በሀገራችን የዕድገት ጎዳና የራሱን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት፣ የኪነጥበብ ባለሞያው፣ ባለድርሻ አካላት እና ታዳሚው ማህበረሰብ በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ከሆነ ኮሮና እና መሰል የኪነጥበቡን እንቅስቃሴ የሚገታ ፈተና በሚገጥምበት ጊዜ አሁን የምንሰማቸው ዓይነት ልብ ሰባሪ ዜናዎችን በቀላሉ ላናዳምጥ እንችላለን። የኪነጥበብ ባለሞያዎችም ከራሳቸው አልፈው ወገኖቻቸውን እንዲረዱ መንገዱ ይከፈትላቸዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top