ጥበብ በታሪክ ገፅ

የእጅጋዬሁ ሽባባው /ጂጂ/ “የአገር ፀጋው፣ የአገር ልብሱ፣ የአገር ሸማው. . . ” – ዓባይ!!!

ኪነጥበብ ሰርክ ከሚታየውና ግልጽ ከሆነው አካባቢያዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣… ዕይታ ጋር ጉዳይ የለውም፤ የኪነጥበብ ህላዌው እውነታ ቢሆንም እንኳ። ኪነጥበብ የታየ፣ የተዳሰሰ፣ ተሟጦ ካለቀ ትርጉም ጋርም ትስስር የለውም። “ከሰማይ በታች ምን አዲስ ነገር አለ?” ለሚለው ሀሳብምም ኪነጥበብ ተገዥ አይደለም። ኪነጥበብ ሁሌም የአዲስ ዕይታ ባለቤት ነው። ኪነጥበብ ፍልስፍና ይገለጽበታል ስንል፤ የአዲስ ፍች፣ ትርጉምና አስተሳሰብ ባለቤትም ነው ማለታችን ነው። አንድ የኪነጥበብ ስራ ላይ ተክኖ መገኘት አስቸጋሪ የሚያደርገውም፤ ኪነጥበብ ፍልስፍና ተገልጾበት ተደራሹ ጋር ቀሎ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ውበት ፈንጥቆ ሀሳቡ ሁሌም ተተኳሪ ማድረግ መቻል ፈተና ስለሆነ ነው። ታዲያ ከከያኒው የሚጠበቀው የኪነጥበብ ሀሳብን አጎልብቶ ፍልስፍናዊ ልቀት የመስጠት ግብ አብዛኛውን ጊዜ ሲሰምር አይታይም፤ ከጥቂቶች በስተቀር።

በተቀራኒው አንዳንድ የተሰጡ ከያኒያን ከላይ በትንሹም ቢሆን ከጠቀስኩት የኪነጥበብ ብያኔ በላይ ሲሆኑ ይስተዋላሉ። ለዚህ አብነት እጅጋየሁ ሽባባውን (ጂጂን) ስገልጽ እጅግ በጣም በድፍረት ነው። የድፍረቴ ማጠንጠኛ ደግሞ ተሰምቶ የማይጠገበው ሙዚቃዋ፤ “ዓባይ” ነው። ውይ! ጂጂ ግን የእውነት “ክፉ” ባለቅኔ ናት!! የኔ፣ የአንተ ደግሞም አለም ሁሉ የእርሱ ቢሆንለት እጅግ አብዝቶ የሚፈልገውን ዓባይን የእሷና የእርሷ ብቻ አድርጋው እረፍ! “በምን?” አትሉኝም? በሙዚቃዋ! የአንዳንዱ ምጡቅ ከያኒ ክፋቱ የአንተን የተለመደ ሀቅ ሌላ ፍች ሰጥቶት የእራሱ አድርጎት ቁጭ ይላል። ጂጂም ያደረገችው ይሄንን ነው። ዓባይን ያክል ግዙፍ ወንዝ እድሜ ለመክሊቷ ጠቅልላ የእርሷው የራሷው ብቻ አደረገቸው። አዳሜ በአባይ ረገድ “ጠላቴ ግብጥ ናት” ይላል፤ ውሸት! ይልቅ “ከጂጂም በላይ “ጠላት” – ለአሣር!” ማለትስ ይሄኔ ነበር! ሆቸው ጉድ! የወንዙን አውራ ዓባይን ጥልቅ ትርጓሜ ሰጥታው የእሷ ብቻ አደረገቸው እኮ!! ፍርድ ቤት አቅርበን አንከሳት ነገር እኔኑ ጨምሮ አገሩን የሚወድ ሁሉ ይፋረደናል። ዋስ ጠበቃዋ ሆኖ ይቆምላታል። ስለ እናት ኢትዮጵያ፤ ስለ እናት አገር ለስሜታችን ብቻ ሳይሆን ለልበ- ልቦናችን አንጎራጉራ አንበርክካን ገዝታናለቻ! እና ታዲያ ምን ትደረግ?… መመረቅ ብቻ! የተራቀቀው መክሊትሽ፣ ያበቀለሽ አፈር ይባረክ አቦ!!

እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)

ዓባይ ላይ አይደለም በጠቅላላው ወንዝ ላይ በቅኔ፣ በአዲስ ፍችና ትርጓሜ ተራቆ፣ ተራቆ የታየ ከያኒ እስካሁን እንደ ጂጂ አላየሁም። በዘፈነችው ልክ አይደለም፤ በገባኝ መጠን ግን የጂጂን ፍጹም የሆነ ቅኔ-ዜማዊ መራቀቅ እንደሚከተለው ለመተንተን እሞክራለሁ።

የጂጂ ብዕር ረቂቅና አስደማሚ የሆነ ቅኔ-ዜማዊ ስልቱን በገዢነት ስልጣን ማንቆርቆር የሚጀምረው ገና ከግጥሙ ስንኝ ጅማሬ አንስቶ ነው። ቅኔው ገና ከዜማው መግቢያ ጋር ህብር ፈጥሮ በስልት መንቆርቆር ሲጀምር በግልም ወይም በቡድን ወይ ደግሞ እንደጽንሰ ሀሳብ የተስማማነውን ምድራዊ ጭብጥ እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

«የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና፤ የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና” ብላ ትጀምራለች። መለኮታዊ ካልሆነ በስተቀር ምድራዊ ውበትም ቁንጅናም ከዕድሜ ጋር የሚያረጁ፤ አላፊም ጠፊም ናቸው። ታዲያ በምን ምክንያት ነው ዓባይ “የማያረጅ ውበት፣ የማይደርቅ፣ የማይነጥፍ ቁንጅና” ባለቤት የሆነው ብለን እንድናስብ፣ እንድንጠይቅ፣ እንድንመረምር ትጋብዘናለች። ወረድ ትልናም መጠይቋን ሳታብራራ(ምክንያቱም የኪነጥበብ ውበቱ ለማብራሪያ ቦታ አለመስጠቱ ነውና) የመጠቀ ሀሳቧን በአመክንዮ ታስደግፈውና “የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት” ትለናለች። ይኸው ነው አመክንዮዋ – የሀቋ፤ የእውነተኛነቷ፤ የሀሳብ ፍሰቷ ምንጭ! ማገናዘቢያዋ ደግሞ ትልቁ መጽሀፍ ቅዱስ ዘፍጥረት ላይ የተገለጸው፤ ከኤደን ገነት ከሚወጡ አራት ወንዞች አንዱ የሆነውና “የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” የሚለው ሀሳብ ነው። ይህ የዓባይ ዳራ፣ ከገነት መነሻነት በእስልምና አስተምህሮ ውስጥም ተገልፆ እናገኛለን። ለምሳሌ ነብዩ ሙሐመድ ሰዐወ “አባይ የጀነት ውሃ ነው” በማለት ማወደሳቸውን ታዋቂው የሐዲስ ዘጋቢ አስፍረውታል።

ታዲያ ጂጂ አባይን ከላይ በጠቀስኳቸው ዘላለማዊነትን በሚገልጹ ቃላት የምታሽሞነሙነው የዓባይ መነሻ፣ ገነትን ወስዳ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለእኔ የ”ገነት” ፍቺ የሚያርፈው ዘላለማዊነት ላይ ነው። ታዲያ የጂጂ አባይ የዘላለማዊነት አመክንዮአዊ ፍቺ አግኝቶ የቀረበበት አግባብ ትክክል ብቻ ሳይሆን ፍፁም- ልክም ነው። “የማይነጥፍ፣ የማይደርቅ” ብትለውም አግባብ አላት። ምክንያቱም መነሻው ኤደን ገነት ናውና። ይህ የዓባይ ውበትና ቁንጅና ዘላለማዊነት በሙዚቃው ውስጥ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ድረስም የሙዚቃው ጭብጥ ማጠንጠኛም ሆኖ እናገኛዋለን። የዓባይ ውሀ ዘላለማዊነትን አስራ ልታልፍ ስትፈልግም ፣ ዓባይን በዘመን የጸና ሳይሆን፤ “ለዘመን የጸና” ነው ትለዋለች። “በዘመን የጸና” ብትለው ኖሮ ለአንድ ዘመን እንዲሰራ ሆኖ ይቀርብና ከላይ ከተነሳችበት የዘላለማዊነት ፍች ጋር ይጻረር ነበር። የእኔይቱ፤ ይቅርታ የእኛይቱ ጂጂ አሪፍ አይደለች ታዲያ? “ለዘመን የጸና” አለችው። ላለፈውም፣ ላለውም.፣ ለሚቀጥለውም ይሰራ ዘነድ!

ጂጂ ከላይ መነሻ አድርጋ ያመጣቸው እና ከታላቆቹ ቅዱሳት መጸህፍት የወሰደችው ሀሳብ ሙዚቃው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በተለያየ መንገድ ሲገለጽና ሲጎለብት ይታያል። ይህ ነው የጂጂን መክሊት ረቂቅነት የሚመሰክረው። እንደአንዳንዱ ቀሽም ከያኒ ከመፅሀፍ ቅዱስ ወይም ከቅዱስ ቁርአንም ቃል ወይም ሀሰብ ወስዳ ብቻ አላለፈችም፤ የተዋሰችውን ሀሳብ በተለያዬ መንገድ ስትገልጸው፤ ስታዳብረውና ውበትና ህይወት ስትዘራበት ማየት ይቻላል። በዝርዝር ለማየት እሞክራለሁ።

“የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” የሚል ሀሳብ ላይ “ሁሉ” የሚለው ቃልን አጽንኦት በመስጠት ከአባይ ከ”የማይነጥፍ፣ የማይደርቅ፤…” ውበት ጋር በሚንሰላሰል መልኩ ጂጂ አባይን “የአገር ልብስ” ትለዋለች። ይሄ ነው ለእኔ ትልቁ የጂጂ ፍልስፍናና ትርጓሜ ውጤት። እንዳንዶቻችን በግጥም፣ በሙዚቃ ወይ በሌላ የኪነጥበብ መገለጫ “አባይን እንገድበው፣ አባይ መብራት ያመነጫል፣ ለመስኖ ይውላል፤….” ከሚሉ አይነት የአባይ፤ ምናልባትም ሦስተኛ፣ አራተኛ፣….ጥቅም ላይ አልተነሳችም። ጂጂ ከአባይ ማዕከላዊ የፍልስፍና አስኳል ላይ ነው ዕይታዋን አነጣጥራ ሀሳቧን የተኮሰቸው። የዓባይ “የአገር ሸማ”፤ “የአገር ልብስ”ነቱ ጂጂን ሲገዛት ይስተዋላል። ይሄው ነው የኪነጥበብ ፍልስፍናም። ከሚታየው፣ ከሚጨበጠው ነገር ርቆ፤ የጉዳዩን ረቂቅነት ተረድቶ፤ ነፍስ ዘርቶ፤ ህይወት ፈጥሮና አስውቦ ማቅረብ! የጂጂ “ዓባይ” የሚታይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግርና ጥያቄ ላይ መድረሻውን አላደረገም። ይልቁንም የጂጂ “ዓባይ” ከኤደን ገነት የፈሰሰ፣ ዘላለማዊ፣ የኢትጵያን ምድር ሁሉ ከቦ፣ ልብስና ሸማ ሆኖ አገር የሰራና የገመደውን ነው። የጂጂ “አባይ” ብሄር፣ ጎሳ፣ መነሻ፣ ጂኦግራፊ የለውም። ሙዚቃውና ግጥሙም ለዚህ አይተጋም። ትጋቱ ኢትዮጵያዊ ጥበብ ሸማን ፈትሎ፣ አዳውሮ፣ ሸምኖ፣…ማስቀጠል ነው። ለጂጂ ዓባይ በአካል ሄደን ወይ በቴሌቪዥን ሲፈስ እንደምናየው ወራጅ ውሀም አይደለም። የጂጂ ዓባይ ከዚህም ፍጹም የራቀ ነው። ጂጂ ዓባይን “ግርማ ሞገስ” የምትለው ዓባይ እረጅሙ፣ ሲፈስ የሚዘፍነውን፣ ሲነጉድ የሚያሸብረውን ስሜት ወስዳም አይደለም። የዓባይ ግርማ ሞገስነቱ አገር ልብስነቱ ላይ ነው። ለጂጂ፤ የአገር ሸማነቱ ነው ለጂጂ የዓባይ ግርማ ሞገስ ምንጩ። ለዚህም ነው ታዲያ በሙዚቃው ውስጥ አጽንዖት ያገኝ ዘንድ፣ በምክንያት “ግርማ ሞገስ” እያለች ስትደጋግመው፣ አባይን ስታሽሞነሙነው የሚታየው። ይሄው ነው ኪነጥበብ። ከተደጋገመ እውነታ ውስጥ ረቂቅ የሆነን ሀቅ ፈልቅቆ ማውጣት።

ጂጂ የዓባይን “ለዘመን የጸና”ነት ወይም ከኤደን ገነት መፍሰስን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ጠቅሳው አላለፈችም። ትደጋግመዋለች። አንዱ ማሳያ ጂጂ ዓባይን “ብነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው” ብላ ትጀምራለች። “ብነካው” የሚለውን ቃል አጽንዖት ትሰጡልኝ ዘንድ እፈልጋለሁ። እንደሰሞነኞቹ አንዳንድ “ከያኒያን” “ዓባይን ገደብነው”፤ “ውሀውን ተጠቀምንበት”፤ “ለመስኖ አዋልነው”፤ “ዓባይ አስቆጨን”፤ “ዓባይ ከሀዲ ነው”፤…አይነት ለወሬ የቀረበ “ግጥም” አላሰማችንም። “ብነካው” ነው ያለችው። ታዲያ ብትነካው ምን አንቀጠቀጣቸው ለሚለው “መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው” የሚለው ጥያቄውን የሚመልሰው ቢሆንም፤ ወርቁ ግን ሌላ ነው። የጂጂ “ዓባይ”፤ “ለዘመን የጸና” ነው። የጂጂ ዓባይ መነሻው ዘላለማዊነት ነው። ታዲያ ዘላለም የማይደርቅ፣ የማይነጥፍ ውበትና ቁንጅና ፈላጊው ብዙ ነው። ሰው ሁሉ ዘላለማዊ ቢሆን ምኞቱ ነው። በመሆኑም “ዓባይ ገና ሲነካ የሚያንቀጠቅጣቸው አሉ” ስትለን ጎረቤቶቻችንን ብቻም አይደለም። ከፍ ይልና ወደ መካከለኛው ምስራቅም እንድናማትር ያደርገናል። እንዴት? ፖለቲከኞቻችን ውስጠ ሚስጥሩን ያውቁታልና አልፈዋለሁ። የዓባይ “የአገር ልብስ” ሆኖ አገሬን ቀዳሚ መሆኖ የሚያንገበግባቸው እንዳሉም ፍንጭ ሰጣ ማለፎን ልብ ይሏል። ለዚህም ነው ጂጂ በሙዚቃዋ ውስጥ “ዓባይ ወንዛወንዙ ብዙ ነው መዘዙ” የሚለውን ሀረግ ስትደጋግመው የሚስተዋለው። ሀረጉ የዓባይን ለአገሬ የሚሰጠውን ፋይዳ ብቻ ሳይሆን፤ ያለውን ፓለቲካ እንድንፈራው ሳይሆን እንድናጤነውም ጠቁሞን ያልፋል።

በጂጂ “ዓባይ” ሙዚቃ ውስጥ የተካተቱ ቃላት እንዲያው ለስሙ ብቻ ቤት መትተውና ደፍተው እንዲያልፉም ተጠልፈው የመጡ አይደሉም። የተመረጡት ቃላትና የተሸከሙዋቸው ፍቺዎች ሰፊና ጥልቅ ናቸው። ለምሳሌ ዓባይ ለእኛ “ፀጋ” ሲሆን ለበረሀው ደግሞ “ሲሳይ” ነው። የ”ፀጋ”ን እና የ”ሲሳይ”ን ቃላት ፍቺ እንግዲህ ልብ በሉ። ካልጠፋ ቦታ ሕይወትን በበረሀ የሰጠ ውሀ ከሲሳይ ውጭ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በመሆኑም ቃሉ፤ “ሲሳይ” ተገቢ ነው። ጸጋ ሁሌም ከላይ ነው፤ መሰጠትም ነው። ለምሳሌ ሰው የመሆን ፀጋ ትልቁ የአምላክ ስጦታ ነው። ዓባይ ለአገሬ “ፀጋ ነው”፤ ትለናለች አሳቢዋ ጂጂ። እንጉርጉሮዋ ውስጥ የዓባይ የአገር ጸጋነት እጅግ ሩቅ ዘመንና ሀቅንም እንዲሸከም ተደርጎ ነው የቀረበው። የተመረጠው ቃል፣ ፀጋም ከላይ የሚሰጥ የሚለውን ሀሳብ በሚገባ እንዲወክል ሆኖ በምክንያት የገባ ነው። ጂጂ ዓባይ የኢትዮጵያ “ፀጋ” ነው ስትል፣ “ከላይ የተሠጠ ነው” የሚለውን እንዲሸከምላት መዝሙረ ዳዊትን አጣቅሳ ያስገባችውም ይመስለኛል። መዝሙረ ዳዊት ላይ “አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤” ተብሎ እንደተገለፀው ሁሉ፤ ደግሞም “ውሀን ውሀ ያነሳዋል” እንዲሉ፤ ለጥቆም ስለ አገሬ እንዲህ ይላል፡-”ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሀቸው”። መስጠት የሚለውን ቃል ከላይ እንደሆነ ስናስብ በቀጥታ “ፀጋ” ወደ ሚለው ፍሬ ቃል ይወስደናል። የኢትዮጵያ ስም የተነሳውም ስለውሀ እየተወራ ባለ ጊዜ ነውና “ምግባቸውን ሰጠሀቸው” የሚለው የወርቁ ፍች ከምግብም በላይ እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው። ለዚህም ነው ጂጂ ዓባይን “የአገር ፀጋ” ስትል የመረጠችው ቃል መርጣና አስባ እንደሆነ ለመረዳት የሚቻለው። ለዘመን የጸናው የዓባይ ምስጢር ያረፈው ደግሞ የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ፣ የአገር ሸማነቱ ላይ ነው። እንዲህ ነው ተራቆ፣ ውብ ሆኖ መገለጽ።

ጂጂዬ ሆይ፤ በታሰበው ልክ ልቆ፣ረቅቆ፣ ውብ አድርጎ ሰውን ማድነቅ ከላይ መሰጠትን ይጠይቃል፤ እንደ አንቺው የጠቢብነት ስጦታ። እኔ እንግዲህ ባወቅኩሽና ባሰብኩሽ ልክም ባይሆን በቻልኩት መጠን ይህቺን ታክል በአንዲቱ ሥራሽ ልገልፅሽ ሞክሬያለሁ። እናም ደግሞ እልሻለሁ፡- “ዓባይን ከወንዝነት በላይ የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ፣ የአገር ሸማ አድርገሽ በኪናዊ ውበት የገለጥሽበት አእምሮሽ የተባረክ ይሁን። አንቺን ውዲቱን ልጅ ያበቀለችሽ እናት አገሬ፤ ኢትዮጵያዬም ለዘለዓለም የተባረከች ትሁን! – አሜን።”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top