አድባራተ ጥበብ

የአጭር ህይወት ረዥም ጉዞ

ሀጫሉ ሁንዴሳ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የመንፈስ ልጅ ነው። የስጋ ዘመድ ነው። የአገር ልጅም ነው። የታላቁ ገጣሚ የኪነት ዛር ለድምጻዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ጥቂት ጠብታ ደርሶትስ እንደሁ ማን ያውቃል? የሥጋ ዝምድናው የመንፈስ በረከት እንዳለው ማን ልብ ብሏል? በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። አንጋፋውና ታዳጊው ከያኒ የዕድሜ ዝምድና የላቸውም። ምክንያቱም ሃጫሉ የሎሬቱን ዕድሜ ግማሽ ብቻ የኖረ ሰው ነውና። ሮጦ ያልጠገበው ድምጻዊ ምድራዊውን ዓለም የተሰናበተው ገና በ36 ዓመቱ ነው። አምቦም ገና የእደግልኝ ምርቃቷን ሳትጨርስ “ነፍስ ይማር” ለማለት ተፈረደባት። አባትም ልጁን ቆሞ ቀበረ። እንግዲህ ለእንዲህ ዓይነቱ ትዕይንት ይሆናል የታላቁ ገጣሚ የስንኝ እንጉርጉሮ መከተቡ። ሎሬቱ የስጋና የመንፈስ ልጁን ተከትሎ ከለቀስተኛው ጋር እያለቀሰ፣ ከቆዘመው ጋር እየቆዘመ፣ ከሚተመው ጋር እየተመመ… በእሳት ወይ አበባ መጽሐፉ እንዳሰፈረው “ምነው አምቦ”? እያለ…

ምነው አምቦ?

ዛሬ እንደዚህ ምነው አምቦ፣

የቀትር ጥላሽ ተስቦ፣

የጡቶችሽ ወዝ ተሰልቦ፣

ውስጥ አንጀትሽ ተለብልቦ፣

የመዐዛሽ መፍለቅለቂያ መንጸባረቅሽ ተሸብቦ፣

ተረምርሞ ተተብትቦ፣

ምነው? … ምነው አምቦ?

የሙዚቃ ጉዞ

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የተወለደው በ1976 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ውስጥ ሲሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለውም እዚያው አምቦ ነው። እሱና ሙዚቃ መተዋወቅ የጀመሩትም ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ሲሆን፤ ሙያውን ይበልጥ እያሳደገና እየገፋበት የመጣው ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጀመረ በኋላ ነበር። በጊዜው በአምቦ ከተማ ይንቀሳቀስባቸው የነበሩ የተለያዩ ክበባት ለሙያ እድገቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይም በከተማው በስፋት ይንቀሳቀስ የነበረ “ትውልድህን አድን” የሚባል የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ክበብ ለድምጻዊው ሁለንተናዊ የሙዚቃ ጉዞ መሰረታዊ አስተዋጽኦ ነበረው። በዚህ ክበብ ውስጥ የሙዚቃ ችሎታውን ከማዳበሩም በላይ በርካታ ባለሙያዎችን ተዋውቆበታል። እነዚህ ሰዎችም ለዛሬው ኮከብ ልምዳቸውን እያጋሩ፣ የመድረክ ጥማቱን እያረኩ መንገድ ጠርገዋል።

ድምጻዊ ሃጫሉ ከማይረሳቸው የሙዚቃ ዳዴ ምርኩዞቹ መካከል አንዱ አማኑኤል እንዳለ የሚባል ሰዓሊ ነው። አማኑኤል የስዕል ሀሳብ ሀሰሳና፤ ለተመስጦ ከከተማ ወጣ ሲል የወጣቱን የሙዚቃ ችሎታ ከእንጉርጉሮው ተረድቶ ነበርና ክራር ገዝቶ ሰጠው። ሃጫሉም በአዲሷ ክራር ከሬድዮም ከአካባቢውም የሰማቸውን ዘፈኖች እያንጎራጎረ ወዲህ የመዝፈን አቅሙን ሲያሳድግ፤ ወዲያ የክራር ሙያን ተማረ።

ሌላው ሰው ደግሞ ድምጻዊ በጋሻው ተፈሪ ነው። በጋሻው ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች እየተንቀሳቀሰ በተለያዩ የምሽት ክበባት ውስጥ ይዘፍናል። በዚህ ልማዱ በጋሻው ተፈሪ ወደ አምቦ ጎራ እያለ የአምቦ ከተማ ምሽቶችን ያደምቃል። በአንድ አጋጣሚ ታዲያ በጋሻው ከከተማው እውቅ ክበብ (ትውልድህን አድን የጸረ ኤችአይቪ ኤድስ ክበብ) ጋር የመገናኘት እድል ይገጥመዋል። የያኔው ብላቴና ሀጫሉ ሁንዴሳም ድንቅ የሙዚቃ ችሎታውን ወዲያው ስላሳየው በጋሻው እሱ በሚሰራበት የምሽት ክበብ ውስጥ አብረው እንዲሰሩ ሃጫሉን ይጠይቀዋል። በደስታ ተስማማ፣ የብላቴናው ህልምም እውን መሆን ጀመረ። ከዚያች ዕለት በኋላ አምቦ ከተማም ሃጫሉ ሁንዴሳን በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም አወቀችው። እንደ ተማሪ ብቻ ሳይሆን እንደ ድምጻዊም ተቀበለችው። የአብራኳን ክፋይ ውብ ድምጽ እያጣጣመች አላፊ አግዳሚ እንግዶቿን ተቀብላ ሸኘችበት።

ሀጫሉ እንደ ዳዊት መኮንን

የሀጫሉ ሁንዴሳን የልጅነት ጉዞ የሚያውቅ ሰው አንድ እውቅ ድምጻዊን አይረሳም። ይህ ሰው ከተወደዱት የአፋን ኦሮሞ ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው ዳዊት መኮንን ነው። የወለጋው ልጅ ዳዊት መኮንን በተለይም “ani dhufee jirra”(አን ዱፌ ጂራ) በምትል ዘፈኑ ብዙዎች ያስታውሱታል። ሌሎች በርካታ ዘፈኖችም አሉት። ሀጫሉ እንደ አሊ ቢራ የመሰሉቱን ጨምሮ፤ የበርካታ አንጋፋ ድምጻውያንን ዘፈኖች ቢጫወትም እንደ ዳዊት መኮንን የሚሆንለት ግን አልነበረም። ዳዊት የዘፈነውን ይዘፍናል። የተነፈሰውን ይተነፍሳል። በቃ የእሱ ተምሳሌት ነበር- ዳዊት መኮንን። የትውልድህን አድን ክበብ አባላትና የአካባቢው ሰዎችም የሀጫሉ ጊዜ ደርሶ የራሱን ዘፈኖች ይዞ ብቅ እስኪል ድረስ የሚያውቁት፤ የዳዊት መኮንንን ስራዎች አሳምሮ በመዝፈኑ ነበር። ሀጫሉም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሰጣቸው የተለያዩ ቃለ መጠይቆቹ የዳዊትን ስራዎች እያንጎራጎረ ማደጉን በደስታ ይናገር ነበር።

ሀጫሉ የሙዚቃን ዓለም በሰፊ በር ከመቀላቀሉ በፊት ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የአምስት ዓመታት የእስር ጊዜን አሳልፏል። ከእስር በኋላ አስራ ሁለት ዘፈኖችን የያዘው የመጀመርያ አልበሙ ሲለቀቅ በጊዜው ገና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ይህን አልበም ለመስራት ከአምቦ አዲስ አበባ ብዙ ተመላልሷል። ቤተሰቦቹ በተለይም አባቱ ለሙዚቃ ያላቸው ምልከታ እምብዛም ነበርና ከአምቦ አዲስ አበባ ምልልሱ የሚከናወነው በድብቅ ነበር። በዚህ መሀል ብዙ የትምህርት ጊዜውንም እየበደለ ለሙዚቃ መገበር ነበረበት። ገበረም። ሙዚቃም ውለታውን ቆጥራ በሰባት ወራት ደፋ ቀና ውስጥ ጣጣዋ ተጠናቆ ለሰፊው ጆሮ ደረሰችለት።

እንደ “sanyii motii,” “kololonii too” እና ሌሎች ተወዳጅ ዘፈኖች የተካተቱበት ይህ አልበም እውን እንዲሆን ከጎንህ ነን ያሉ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ የሚዘነጋ አይደለም። ከነዚህ መካከል በጊዜው አስራ ሁለቱንም ዘፈኖቹን ያቀናበረለት ጓደኛው ታምራት ከበደ ዋንኛው ነው። ራሱ ሀጫሉ ሁንዴሳ በአንድ ቃለ መጠይቁ ላይ እንደተናገረው፤ ታምራት ከበደ በጊዜው ከእስቱዲዮ ክፍያ ጀምሮ ብዙ ወጪውን በመሸፈን የነበረበትን የገንዘብ እጥረት የቀረፈለት ሰው ነው። በድርሰት በኩል ደግሞ ከራሱ በተጨማሪ ስሜ ቱፋ የተባለ እውቅ ደራሲ እገዛም አልተለየውም ነበር። እነዚህ ባለሙያዎች ለዛሬው ኮከብ ድምጻዊ ታሪክ የማይዘነጋው የሙዚቃ መሰረት ድንጋይ አኑረዋል።

ሀጫሉ ሁንዴሳ የሚለው ስም ከኦሮሚፋ ቋንቋ ተናጋሪዎች አልፎ መላ ኢትዮጵያውያንን ማነጋገር የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው። ገና በመጀመርያ ስራው አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ ሁሉም ተቀባበሉት። ድምጹ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፣ ተወደደም። ስሙ ከአንጋፋዎቹ ድምጻውያን ተርታ መሰማት ጀመረ። እሱም በግስጋሴው በመግፋት ሁለተኛ አልበሙንና የተለያዩ ነጠላ ዘፈኖችን አስከተለ። ስራዎቹም ከፍታቸውን እንደጠበቁ ከጆሮ እየተዋሀዱ ቀጠሉ። ሲሻው እንደ አፍቃሪ እየተፈላሰፈ፣ ሲፈልግ የተዘነጉ ማህበራዊ ጉዳዮችን እያስታወሰ፣ ደሞ የህዝብን ብሶትና እሮሮ እያስተጋባ በስራው የሚሊዮኖችን ልብ ተቆጣጠረ። በተለይም የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎችን እየነቀሰ በየአደባባዩ በግልጽ መዝፈን መጀመሩ የአድናቂዎቹን ፍቅር እጥፍ ድርብ እያደረገው መጣ። ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው እንዲሉ፤ ቋንቋውን የማይሰሙትም ቢሆኑ በዜማና በድምጹ ብቻ እየተማረኩ ለዘፈኑ መልዕክት ግድ ሳይሰጣቸው ስለ ሙዚቃ ብቻ እጅ የሰጡ ብዙዎች ናቸው።

ርዕሰ ጉዳዮቹ

ኢትዮጵያ ገና ብዙ በመስሪያ ጊዜያቸው እንደዋዛ ካጣቻቸው የሙዚቃ ሰዎች መካከል አንዱ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሆኗል። እንደ ሸዋሉል መንግስቱ፣ እንደ ሰይፉ ዮሐንስ፣ እንደ ኢዮብ መኮንን፣ እንደ ኤልያስ መልካ፣ እንደ ታምራት ደስታ፣ እንደ ሚካያ በሀይሉ፣ ኬኑዲ መንገሻ እና እንደ ሌሎቹ ሁሉ፤ በአፍላ ዘመናቸው ከተቀጠፉት ተርታ ሀጫሉም ተሰልፏል። ብዙዎቹን የተፈጥሮ ሞት ሲጠራቸው ቀሪዎቹን የሰው እጅ በልቷቸዋል። በዚህ ምክንያት ሀጫሉ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዘፍኗል ባንልም ቅሉ፤ ለእድሜው የማያንሱትን ርዕሰ ጉዳዮች አንስቶ ግን ተጫውቷል። ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ተስፋና መፈናቀል በየፈርጁ ከነካካቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከፍቅር ዘፈኖቹ መካከል በመጀመርያ አልበሙ የተካተተውን “sanyii mootii”(ሰኚ ሞቲ) የሚለውን ስራ ብዙዎች ይወዱታል። የንጉስ ዘር እንደ ማለት ነው። በዘፈኑ ውስጥ ያለው ገጸ ባህሪ በንጉስ ዘር ፍቅር ከንፏል። እንዲህ እያለ፡-

ሀጫሉ ሁንዴሳ

Galaanni gibee guutuus

Daaktuu fi bidiruu

Nama ceesiisaa

Garaan jaalatee hin rafuu raftus jilbibbiin

Nama deemsiisaa

Ani sosoodaadhee baranaa

Qalbii kootii

Gibe gamaan jaaladhee

Sanyii mootii

ሀሳቡ በገደምዳሜው ሲተረጎም-

የጊቤ ወንዝ ቢሞላ፤

በዋና እና በታንኳ ሰው ይሻገራል፣

ያፈቀረ አይተኛም በእንብርክክ ይሄዳል፣

ዘንድሮስ ፈራሁ ለራሴ፣

ከግቤ ወንዝ ማዶ የንጉስ ዘር ወድጄ። እንደ ማለት ነው።

ከፍቅር ዘፈኖቹ ይህንን ጨምሮ ሌሎች ተወዳጅ ዘፈኖችን ተጫውቷል። እንደ “kololonii too” ያሉቱ ከተደማጭ ስራዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በፖለቲካ ረገድ በተለይም የኦሮሞን ማህበረሰብ ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቁ ዘፈኖችን ተጫውቷል። ከነዚህ ስራዎች መካከል በብዙ የምሽት የጭፈራ ክበባት ውስጥ ተዘውትሮ የሚደመጠው “laal galoo too” እና “jirra jirraa” የሚሉት ስራዎቹ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ “ላል ገሎ ቶ” የሚለው ስራ እንደ ሙዚቃነቱ ከመወደድ ባሻገር የአያሌዎች የብሶት መተንፈሻ ማዕከል እስከመሆን የደረሰም ይመስላል። ዘፈኑ በውስጡ በተካተቱበት ፖለቲካዊ ስንኞቹ ምክንያት የብዙዎችን ቀልብ ሳይስብ አልቀረም። የዚህ ዘፈን ግጥምና ዜማ ድርሰቱ የራሱ የሀጫሉ ሁንዴሳ ሲሆን ቅንብሩ ደግሞ የዳዊት ታሲሳ ነው። ይህ ስራ በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ ከመቅረቡ በተጨማሪ በዩቱብ ቻናልም ከፍተኛ ተመልካች ያለው ዘፈን መሆኑ ይታወቃል።

ሌላው ተወዳጅ ሥራ “jirra jirraa” የሚለው ዘፈን ነው። ሃጫሉን እንደ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ ተወካይ “የልባችንን ነገረልን” ካስባሉት ዘፈኖች መካከል የሚጠቀስ ነው። በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው የለውጥ ሰሞን፤ ይህ ዘፈን ተደጋግሞ ይሰማ ነበር። የመሀሙድ አህመድ “ሰላም ሰላም” የሚለው ሙዚቃ ከወደቀበት እንደ እራፊ ጨርቅ ተራግፎ፤ በተለይም የኢትዮ-ኤርትራ እርቅ ሰሞን ተደጋግሞ በየሚዲያው፣ በየአዳራሹ ሲለቀቅ፤ የሃጫሉ “ጂራ ጂራ”ም አብሮ ተሰልፎ ነበር። ኤርትራውያን ድምጻውያን ሳይቀሩ የኢትዮጵያው መሪ አብይ አህመድ(PHD) እና የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጀመርያ ጊዜ በተገናኙባት ታሪካዊ ዕለት፤ በቀጥታ የኤርትራ ቴሌቪዥን ስርጭት ብቅ ብለው “ጂራ ጂራ ጂራ” እያሉ ሲያዜሙ ተመልክተን ነበር።

Jirra, jirra, jirra

Jirra bullee barii arguuf

Garaa nu bal’ise yaa nuhii

Yaa nuhii yaa nuhii

Yaa waa irraanfachuuf yaa nuhii

ወደ አማርኛ ስናመጣው ፡-

አለን፣ አለን፣ አለን

አለን ንጋትን ልናይ ሆደ ሰፊ አድጎን፣

ወይ እኛ ወይ እኛ፣ ወይ እኛ

የሆነብንን እንድንረሳ ወይ እኛ… እያለ የሚቀጥል ነው።

በጥቅሉ ስናየው የተዳፈነ ብሶትና መከራን፤ ጭቆናና ግፍን በውስጣችን ተሸክመን፤ ላያስችል አልሰጠንምና ነገን ለማየት፤ ሁሉን ተሸክመን ይኸው አለን፤ የሚል አንድምታ ያለው ዘፈን ነው።

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለ ትዳር እና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነው። የቀብር ሥነ-ስርዓቱም ሰኔ 25/2012 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ገዳመ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መፈጸሙ ይታወሳል።

ድምጻዊ ሀጫሉ በየርዕሰ ጉዳዩ የተጫወታቸው በርካታ ናቸው። እዚህ ያልተነሱ ሌሎች በርካታ ቅኔያዊ እና ሰም ለበስ ስራዎች አሉት። ይህ ድንገተኛ ሕልፈቱን አስመልክቶ የተሰናዳ አጭር ማሳያ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለጥበብ ቤተሰቦች፣ ለአድናቂዎቹ እና ለቤተሰቦቹ ሁሉ መጽናናትን ለእርሱም ዘላለማዊ እረፍትን እመኛለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top