ጣዕሞት

የተሰረቀው ውድ ስዕል

የተሰረቀው የቫን ጎ ስዕል

በእውቁ የደች ሰዓሊ ቫን ጎ የተሳለ ስዕል ፤ በኮሮና ምክንያት ተዘግቶ ከነበረው በሆላንድ ከሚገኘው የሲንገር ላረን ሙዚየም ውስጥ ተሰረቀ። ስዕሉ ሊሰረቅ የቻለው ድቀድቅ ጨለማን ተገን አድርገው በኮሮና ምክንያት በተዘጋው ሙዚየም ውስጥ ሰብረው በመግባት ሲሆን እሁድ ማታ ላይ የተሰረቀው ስዕሉ ፤ መሰረቁ ሊታወቅ የቻለው ሰኞ ጠዋት ላይ ነው። ከቆይታ በኋላም ሰዎች አዘውትረው የሚመለከቱት የፊት ለፊቱ የመስታወት በር በነጭ ፓነል ተሸፍኖ ሊታይ ችሏል።

የሙዚየሙ ዳይሬክተር የሆኑት ኤቨርትቫንኦስ ፤ በዝርፊያው ምክንያት “እጅግ በጣም ተበሳጭቻለሁ ፤ ተናድጂያለሁ” ሲሉ ተሰምተዋል። “በሙዚያማችን የሚገኘው በታላቁ ሰዓሊ የተሳለው አስደናቂ ስዕል ከሙዚየማችን ተሰርቋል። ከህብረተሰባችን ተዘርፏል” ሲሉ የተደመጡት ደግሞ ጃንሩዶልፍ ደ ሎርም የተባሉ የሙዚየሙ ሌላኛው ዳይሬክተር ናቸው።

ፖሊሶች ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት ስዕሉ ሊሰረቅ የቻለው ፤ ሌቦች የመስታወት በሩን ሰብረው ገብተው እንደሆነ ነው። መስታወቱ ሲሰበር አላርም (የማስጠንቀቂያ ደወል) መጮሁን ያስታወሱት ፖሊሶቹ ፤ ምንም እንኳ ፈጥነው ወደሙዚየሙ ቢሄዱም ሌቦቹን ሊያገኙ እንዳልቻሉ ምጨምረው ገልፀዋል።

ዘግይተው በቦታው የደረሱት የፖሊስ ኃይል አባላት እና የፎረንሲክ ባለሞያዎች በሙዚየሙ የሚገኙ በድብቅ ካሜራ የተቀረፁ ቪዲዮዎች ለማየትም ሞክረዋል።

የሲንገርላረን ሙዚየም ከዚህ በፊትም በ2007 እ.አ.አ. በታላቁ ቀራፂ አውገስት ሮዲን የተሰራው “ዘ ቲንከር” የሚባለው ቅርፅ ተሰርቆ ነበር። ከዋናው “ዘ ቲንከር” ቅርፅ በተጨማሪም ፤ ከመዳብ የተሰራ በራሱ በአውገስት የተቀረፀ “ዘ ቲንከር” የተባለ ቅርፅም ጨምሮ ሊሰረቅ ችሏል። ያኔ ታዲያ የተሰረቀው ዋናው “ዘ ቲንከር” ከጥቂት ቀናት በኋላ ቢገኝም አንድ እግሩ ጠፍቶ ነበር።

ሙዚየሙ ሌቦቹን ጠቁሞ ላስያዘሰው የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ፤ የቫን ጎ ስዕልን የሰረቁ ሰዎች ግን እስካሁን ድረስ ሊገኙ አልቻሉም። ከቪዲዮ ማስረጃው እንደተረጋገጠው ሌቦቹ በምሽት ዘጠኝ ሰዓት በሞተር ሳይክል መጥተው ነው ስዕሉን የሰረቁት።

ይህ ውድ ስዕል በገበያ ዋጋ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ሲሆን ፤ በጥቁር ገበያ ግን ከዛም ባነሰ ዋጋ ሊሸጥ እንደሚችል ግምቶች አሉ። የስዕሉ መሰረቅ እንደተሰማ በዓለማችን የሚገኙ ትልልቅ ሚዲያዎች እንደ አልጀዚራ፣ ዴይሊኒውስ፣ እና ኒውዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ ዜናውን እየተቀባበሉ ዘግበውታል።

ብዙዎች በኔዘርላንድ የሚገኙ ሙዚየሞች በተደጋጋሚ ጊዜ ለመዘረፋቸው ዋነኛው ምክንያት ፤ በተሰረቀ እቃ ላይ ያለው አወዛጋቢ የሃገሪቱ ሕግ ነው ይላሉ። በኔዘርላንድ ሕግ መሠረት ፤ አንድ እቃ ከተሰረቀ ከ30 ዓመታት በኋላ የባለቤቱ ንብረት መሆኑ በሕግ ፊት ያከትማል። ስለዚህም በዚህ ሕግ መሠረት አንድ ሌባ የሰረቀውን ዕቃ ከ30 ዓመታት በኋላ አደባባይ አወጥቶ “ግዙኝ” ቢል ፤ ማንም አይናገረውም ፤ ማንም አይከሰውም። በስርቆት አግኝቶ 30 ዓመታት የሸሸገው እቃ (ቅርስም ቢሆን) የራሱ ንብረት እንዲሆን ሕግ ከለላ ይሰጠዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top