ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል – ቁጥር 35

የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ መገደል በኪነ-ጥበቡ ሰፈር ብቻ ሳይሆን በመላ ሐገሪቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል። ድንገቴውን ክስተት ሁሉም ለየራሱ አጀንዳ እንዲሆን አድርጎ ተጠቅሞበታል። ሚድያዎችን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶች አሰቃቂውን ግድያ ከራሳቸው የፖለቲካ አመለካከት ጋር አዛምደው ነገሩን ለማጦዝ አፍራሽ ሚና ተወጥተዋል። ከወጣቱ ድምጻዊ ሕልፈት በተጨማሪ በመላው ሀገሪቱ የሌሎችም ንጹሐን ሕይወት በዚሁ በሰበብ ተቀጥፏል። የንግድ ተቋማት፣ ሆቴሎች እና ፋብሪካዎች ለዘረፋ፣ ለቃጠሎ እና ለውድመት ሰለባ ሆነዋል። ክስተቱን ታሪክ በመጥፎ ትዝታነት መዝግቦት ቢያልፍም የማያልፍ ስጋት ለማኅበረሰቡ አቀብሏል።

የአሁኑን ጨምሮ ባሳለፍናቸው ሦስት ሰኔዎች የገጠሙን ደም አፍሳሽ ክስተቶች፣ ክስተቶቹን የተከተሉት ግብረመልሶች፣ የመንግሥት አቋም እና የተቃዋሚዎች ምላሽ፣ የፍርድ ሂደቶቹ ሁናቴ፣… ይህ እና ይህንን መሰል ጥያቄዎች ከፌደራል እስከ ክልል ብሎም ዓለም አቀፍ ተቋማት ድረስ እያነጋገረ ቆይቷል። ወደፊትም ከፍ ሲል አጨቃጫቂ እና መተማመን የጎደለው፤ ዝቅ ሲል አወያይ እና መፍትሔ ፈላጊ እየሆነ ይቀጥላል።

ከትላንትናው የመገዳደል እና የመጠፋፋት ባህል ተሻግረን የቆምንበት ዛሬ እንደምን ያለ ነው? ባለፉት የታሪካችን ገጾች ላይ በርካታ ምዕራፍ ያላቸው የሴራ ጉንጉኖች አሁን ድረስ ለምን ተከተሉን? የሐገርን ሉዐላዊነት ከግል ጥቅሙ ያስቀደመ፣ የብሔሩ ማንነት ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ያልተምታታበት፣ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ስርአት መገንባት ለምን አቃተን? ፖለቲካችን እና ፖለቲከኞቻችን አሁን ካሉበት ውጥንቅጥ ወጥተው የልጆቻችንን ምድር፣ የልጅ ልጆቻችንን ሀገር፣ ተስፋ የሚታያትን ኢትዮጵያ መገንባት ስለምን ተሳነን? ሁሉም ሰው እነዚህን ጥያቄዎች ለራሱ መጠየቅ ያለበት ጊዜ ላይ ነን። ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለመሪዎቹ፣ ለመሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካ ልሂቃኑ፣ ለፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆን ለምሁራን እና መምህራኖቹ፣ ለታሪክ ተመራማሪዎች መጠየቅ አለበት።

የጥያቄው ማዕበል የመልስ ጎርፍ ያስከትላል። ከእያንዳንዳችን የሚገኘው ምላሽ ደግሞ የጋራ መግባባት የሚባል የፖለቲካ ባህል ይወልዳል። የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን፣… እና ሌሎችን የዴሞክራሲ መሰረቶችን የምናዳብርበት ይሆናል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ወጥቶ መግባትን፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እንደልብ መጓጓዝን፣ ትላንት እንደዘበት ኖረን ዛሬ እንደ ብርቅ የናፈቁንን ነገሮች ማግኘት እንችላለን።

ለሐገራችን ሰላም እና ለሕዝቦች አንድነት ሁሉም ሀላፊነቱን ይወጣ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top