ፍልስፍና

የሙሴ ትዕዛዛት

ፈላስፎች ጥያቄ እንደሚያበዙ ሁሉ ነቢያት ደግሞ ትዕዛዝ ያበዛሉ። ከዚህ ጥቅል እውነታ ተነስተን ለዛሬ የሙሴ ትዕዛዛት የሚባሉትን እንመለከታለን። ሙሴ በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ኃይማኖቶች በነብይነት ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀስ ታላቅ ሰው ነው። አይሁዶቹ ሞሼ፣ ክርስቲያኖቹ ሙሴ ሲሉት፤ ሙስሊሞቹ ደግሞ ሙሳ ይሉታል። በሦስቱ ኃይማኖቶች መካከል ያለው ልዩነትም የዚያኑ ያህል ነው፣ መሰረታዊ የሆነ ልዩነት የላቸውም። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ምንጩ አንድ የሆነ እምነት እየተከተሉ በኃይማኖት ሰበብ እርስ በእርስ የመናቆራቸው ነገር ነው።

የሙሴ ታሪክ በርካታ አስገራሚ ነገሮች አሉት። ወገኖቹን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት በማሰብ፤ ለቅዱስ ዓላማ የአይሁዱን እግዚሄር የፈጠረው ሙሴ ነው የሚሉ አሉ። አክሱማዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብ እንዳለው ከእርሱ በኋላ የመጡት የምር አደረጉትና እምነት ከዚያም ኃይማኖት ሆነ! ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ እንዲህ ነበር ያለው፤ “ሙሴ ፈቃዱንና ሕጉን ልነግራችሁ ከእግዚያብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ ይላል። ከእርሱ በኋላ የመጡት በግብፅና በደብረ ሲና እንዲህ ተደረገ እያሉ እውነት አስመሰሉት።”

መጀመሪያ ላይ የሙሴ እግዚሄር በቁጥር በጣም ትንሽ የሆነው የአይሁድ ህዝብ አምላክ ብቻ ነበር። የፈላስፋው ዘርአያዕቆብ አንዱ ጥያቄም ይሄ ነው፤ የሁሉም የዓለም ህዝቦች አምላክ መሆን ሲችል እንዴት የአንድ በጣም በቁጥር ትንሽ የሆነ ህዝብ አምላክ ብቻ ሊሆን ቻለ ነው። ስለዚህ የሙሴን ጠባብነት ነው የሚያሳየው እንጂ እግዚሄርማ እንዲህ ሊሆንና ሊፈቅድ አይችልም የሚል ነው የነገሩ ማጠንጠኛ! ይሄ የሙሴ አምላክ በኋላ ኢየሱስ መጥቶ የክርስቲያኖች ሁሉ አምላክ እንዲሆን ጥረት አድርጓል። ከዚያም ቀጥሎ መሀመድ መጥቶ የእስላሞች ሁሉ አምላክ እንዲሆን ጥረት አድርገዋል፤ በሃውላህ የተባለ ኢራናዊ፣ የብሃኢ እምነት መስራች ደግሞ የብሃኢዎችም፣ የህንዶችም ጭምር አምላክ እንዲሆን ለማድረግ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ እያጣቀሰ ለማሳመን የተለየ ጀግንነት የሚጠይቅ ተነሳሽነትን ወስዷል። እስከዛሬ ድረስ ግን የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ ለመሆን አልቻለም።

ለማንኛውም ወደ ተነሳንበት ጉዳይ እንመለስ፤ የሙሴ አሰርቱ ትዕዛዛት በጣም ታዋቂና መሰረታዊ ከሚባሉት ትዕዛዛት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብ ከሙሴ ትዕዛዛት ውስጥ “ሰንበትን አክብር” ከሚለው በስተቀር ሌሎቹን እንደሚቀበል ጽፏል። ዘጠኙ ተፈጥሯዊ ከሆነው ሕገ ልቦና ጋር አብረው እንደሚሄዱ ነው የገለፀው። አራዳው ዘርዓያዕቆብ ከአሰርቱ ትዕዛዛት ዘጠኙ ከሕገ ልቦናው ጋር የሚስማሙ ሆነው ስላገኛቸው ተቀብሏቸዋል ማለት ነው። እኛም የመንፈስ አባታችን ዘርዓያቆብ ነውና ትዕዛዛቱ እንዳሉ እንደበቀቀን ከመድገምና ዝም ብሎ ከመቀበል ምን ያህሉ ተገቢ ናቸው የሚለውን በመጀመርያ መመርመር ወደድን። እስኪ ትዕዛዛቱን አንድ ባንድ እንያቸው፦

ትዕዛዝ አንድ እና ሁለት

የመጀመሪያው ትዕዛዝ በኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ ሃያ ቁጥር ሦስት ላይ የሚገኝ ሲሆን “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አታምልክ” የሚል ነው፤ ትዕዛዝ ሁለት ደግሞ “በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማንኛውም ምሳሌ የተቀረፀውንም ምስል ላንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” የሚል ነው።

የሁለቱም ትዕዛዛት ዋነኛ መልዕክትና መሰረታዊ ሀሳብ ተመሳሳይ ነው፤ “ከእኔ ሌላ ፈፅሞ አታምልክ” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ለእነዚህ ትዕዛዛት በምክንያትነት የሚያቀርበው ደግሞ “እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ” የሚል ነው። እዚህ ላይ የአይሁዱ አምላክ አመሉን እንዲህ በግላጭ ሳይደብቅ መናገሩ የሚያስመሰግነው ነው።

የሚገርመው ነገር ውዷ ባለቤቴም “ወደ ቤት ከገባህ በኋላ ሴት ፈፅሞ መደወል የለባትም፤ የሌላ ሴት ምስል ደግሞ በሞባይልህም፣ በኪስህም፣ በቦርሳህም መያዝ የለብህም።” የሚል አቋም አላት። እንግዲህ እኔ ስገምት ውዷ ባለቤቴ የእግዚሄር ዘመድ ሳትሆን አትቀርም፤ ተመሳሳይ የሆነ ባህርይ አላቸውና። ስለዚህ ሴት የምትባል ፍጥረት በሙሉ ቅናት እና ብልሀት ከእግዚሄር፣ ክህደትና ውሸት ደግሞ ከሰይጣን ለመውረሷ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም።

እነዚህን ትዕዛዛት የጣሰ ሰው የሚሰጠው ቅጣት ከፀረ ሽብር አዋጁ የከፋ ነው! እንዲህ ነው የሚለው “በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ሀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወዱኝ ትዕዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ነኝ” ነው የሚለው።

እዚህ ላይም ሦስት ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። አንደኛ የሚጠሉኝ ያለው ነገር ነው። ሰዎች ሌላ እንዲያመልኩ የሚያደርጋቸውን እርሱን በትክክል ካለማወቅ ወይም ሌላ የተሻለ አምላክ ስላገኙ ሊሆን ይችላል እንጂ ለምን ይጠሉታል። ለምሳሌ እኔ ለምን እጠላዋለሁ? የትስ ተግናኝተን ነው? እርሱ የሚኖረው በሰማይ፣ እኔ የምኖረው በምድር! እስከዛሬም ድረስ በምንም ነገር አስቸግሮኝ አያውቅ! ለምን እጠላዋለሁ?

መንግሥትም እንደዚሁ በሰማይ የሚኖር ቢሆን እና በእኛ ጉዳይ ላይ ጥልቅ እያለ ባያስቸግረን እንዴት በወደድነው። በእርግጥ የሀይማኖት ሰዎች “የእግዚሄር ወኪሎች ነን፤ በምድር ያሰርነው በሰማይ የታሰረ ነው፤ በምድር የፈታነው በሰማይ የተፈታ ነው” ቢሉንም እንደ አያ ጅቦ ተረት ከምንም አንቆጥራቸውም፤ ምክንያቱም የእግዚሄር ወኪል ለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ ስለሌላቸው ነው። በእርግጥ አክራሪ ኃይማኖተኞች ትዕግስት ስለሌላቸው አንገትህን በሜንጫ ሊሉህ ይችላሉ። እግዚሄር ሁሉንም እየሰማ፤ እያየ ዝም ብሎ ሳለ እነርሱ ሜንጫ እንዲያነሱ የሚያደርጋቸው ምንድነው? ይሄ ተግባራቸው በራሱ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ከእግዚሄር አለመሆናቸው ነው፤ ይሄው በግልፅ የሚታየው ስራቸው ዋና ምስክር ነው።

አራዳው ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ ያለው እንዲህ ነው፤ ዘርአያዕቆብ ከዚህም በተጨማሪ የሙሴ ትምህርት ከሕገ ተፈጥሮ ውጪ በመሆኑ እንደማይቀበለው ሲገልፅ፤ “የሙሴ መጽሐፍ ከፍጥረት ሕግና ከፈጣሪ ጥበብ ጋር አይስማማም” በማለት ነው። አዬ ዘርአያዕቆብ ቆፍጣና እኮ ነው። ፈረንጆቹ ይሄን ዐይተው አይደለ “ይሄማ ሀበሻ ሊሆን አይችልም፤ በሆነ ስህተት ወደ ሀበሾች ምድር የመጣ የፈረንጅ ፈላስፋ ይሆናል እንጂ” ያሉት። አስተሳሳቡንና ዐተያዩን ተመልክተው ከሀበሻ አስተሳሰብ ጋር አነፃፅረው አልገጥም፣ አልገናኝ፣ ሲላቸው መሆን አለበት እንዲህ ያሉት። በዚህ ሃይማኖተኛ ህዝብ መሀል ከዘመናት አንድ ጊዜም ቢሆን እንዲህ ያለ ሰው መፈጠሩና መኖሩ ለማመን ቢከብዳቸው ነው።

ምን ላይ ነበር የቆምነው፤ አዎ ስለመጥላት ነበር የምናወራው፤ ስለዚህ ሌላ አምላክ ማምለክ እርሱን ከመጥላት ሊሆን አይችልም። ይልቅ የቅጣቱ ነገር ነው የሚገርመው፤ የሚጠላኝን እስከ ሦስት አራት ትውልድ እቀጣዋለሁ የሚለው ነገር ነው፤ አባቴ ወይም አያቴ ወይም ቅድመ አያቴ ላጠፋው ጥፋት እኔ የምቀጣ ከሆነ ይሄ ፈጽሞ ፍትሃዊ አይደለም፤ ምክንያቱም ይሄን ቅጣት ለማስቀረት እኔ የማረም ወይም የመከላከል ዕድል የለኝም። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ እኔን ያስገኙ በእናቴም በአባቴም በኩል ያለው ትውልድ እግዚሄርን አስቀይሞ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ከዚህ ዐይነቱ ቅጣት ማምለጥ ብፈልግ ማምለጥ የምችለው በእድል ብቻ ሊሆን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ “እኔን የሚወዱ ሁሉ እስከ አንድ ሺህ ትውልድ ድረስ ምህረት አደርጋለሁ” ብሏል። ከዚህ የተነሳ የእኔ ትውልድ ወደኋላ አንድ ሺህ ቢቆጠር ብዙ እግዚሄርን የሚወዱና ምህረት የተደረገላቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ በቀላሉ ምህረት ሊያደርግልኝ ይችላል ማለት ነው። እዚህ ላይም ለእኔ ምህረት ማግኘት የእኔ አስተዋፅኦ የለበትም፤ እንዲሁ በእድል ነው የምኮነነው ወይም ምህረት የማገኘው ማለት ነው። ደግሞስ ለትውልድህ ሁሉ እስከ ሺህ ድረስ ምህረት አድርጊያለሁ ብሎ በእነዚያ ትውልድ ውስጥ እርሱን የሚጠላ ቢገኝ ለወላጆቹ በገባለት ቃል ምክንያት ምህረት ያድርግለታል ወይስ በራሱ ኀጢአት ይኮንነዋል? በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆቹ የእግዚሄርን መንገድ የማይከተሉ እና እርሱን የማይወዱ ቢሆኑ፤ በአንፃሩ ከእነዚህ ሰዎች የተገኘ ልጅ ግን እድሜ ልኩን የእግዚሄር መንገድ የሚከተልና እርሱን የሚወድ ቢሆን እንዴት ነው የሚፈርደው? በወላጆቹ ኃጢአት ይኮንነዋል ወይስ በራሱ በጎ ስራ ምህረት ያደርግለታል?! ደግሞስ ለልጆች አባትና እናት የሚሰጠው ራሱ እግዚሄር ከሆነ ልጁ እንዴት ነው በወላጆቹ ምክንያት የሚኮነነው? ይሄ ልጅ በመጀመሪያ ወላጆቹን የመምረጥ ምንም ዐይነት ዕድል የለውም።

ትዕዛዝ ሦስት

ሦስተኛው ትዕዛዝ “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነፃውምና።” የሚል ነው። ይሄ ትዕዛዝ ችግር የለውም። በከንቱም ይሁን ከንቱ ባልሆነ ነገር እኔ እርሱን አልጠራም። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት እርሱ የሚኖረው በሰማይ ቤት እኔ የምኖረው በምድር፣ ድንበር አያዋስነን፤ መንገድ አያገናኘን፤ ደግሞም እንኳን የእርሱን የውዷ ባለቤቴንም ስም በከንቱ የምጠራ ሰው አይደለሁም። ይሄ ትዕዛዝ የሚያሸልም ጥያቄ እና መልስ ሆኖ እስካልመጣ ድረስ በከንቱ የማልጠራ መሆኔ እርግጥ ነው። ስለዚህ ይሄ ሦስተኛው ትዕዛዝ እኔ በቀላሉ ልቀበለው የምችለው ዐይነት ትዕዛዝ ነው ማለት ነው።

ትዕዛዝ አራት

ወደ አራተኛው ትዕዛዝ ስንሸጋገር “ሰንበትን አክብር፥ በሰንበት ቀን አትስራ፥ በቤትህ ያለው ሰው ሁሉ ልጆችህም፣ ገረድህም፣ ሎሌህም፣ ከብትህም ጭምር በሰንበት ቀን መስራት የለባቸውም።” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ይሄ ትዕዛዝ ለማን ነው የተፃፈው? ለሀብታም ወንድ የተፃፈ ይመስላል። እንደዚያ ከሆነ አይመለከተንም። እኔ ድሀ ነኝ፤ ገረድም ሆነ ከብት የለኝም። በእርግጥ ሰንበትን ማክበር ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን ስራ የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ራሱ ምን ማለት ነው? የሚለው ነው አስቸጋሪ የሚሆነው። በሳይንስ ስራ ተሰራ የሚባለው አንድን ነገር ከሆነ ቦታ ወደሆነ ቦታ ማንቀሳቀስ ሲቻል ነው። ለምሳሌ በሰንበት ቀን በሰሀን የነበረውን ምግብ አንስተህ ወደ አፍህ አስገብተህ አኝከህ ብትውጠው ስራ ነው ወይስ ስራ አይደለም? ለምሳሌ እማማ ማዘንጊያሽ በእሁድ ቀን ከወንዝ ውሃ ቀድተው አያመጡም፤ የአርብ ውሀ ነው የሚጠጡት። ነገር ግን በእሁድ ቀን ከማሰሮው ውሀ ቀድተው ይጠጣሉ። የእኛ ነፍስ አባትም በደህና የተቀመጠውን ውሀ አንስተው ባገኙት ነገር ላይ የሚረጩት በእሑድ ቀን ነው።

ትዕዛዝ አምስት

አምስተኛይቱ ትዕዛዝ “አባትህና እናትህን አክብር”፤ የምትል ነች። ይሄ ሙሴ ባያዝህም ወላጆችህን አለማክበር አትችልም። ነገር ግን ምን ዓይነት ወላጅ ነው ክብር የሚሰጠው? የሚለው ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ነው። ለምሳሌ አንድ አመፀኛ ወታደር ወይም አመፀኛ ሽፍታ እናትህን አስገድዶ ቢደፍራትና አንተን አርግዛ ብትወልድህ ይሄን አባትህን ታከብረዋለህ ወይ? አባትህስ ተብሎ መጠራት አለበት ወይ? ወይም ደግሞ ከተረገዝክ በኋላ ፅንሱን ማስወረድ አለብሽ ብሎ ከእናትህ ጋር የተጣላና እናትህ በዚህ ምክንያት ብዙ ተንገላታ፣ ከቤት ተባራ ብትወልድህ ይሄንን አባት ታከብረዋለህ ወይ? ወልዳ የትም ጥላህ የሄደች እናትስ? ድንገት በጎ አድራጊ አግኝቶህ ካሳደገህ በኋላ ለዚህች እናት ምን ዐይነት ክብር ነው የሚኖርህ?!

ለማነኛውም ግን አባትህንና እናትህን ማክበር ጥሩ ነው። ምክንያቱም በብዙ መንገድ አንተ እንዳትወለድ ወይም ከተወለድክም በኋላ እንዳታድግ ሊያደርጉህ ይችሉ ነበርና ነው። ለምሳሌ አንተ የተረገዝክበት ቀን አባትና እናትህ ተጣልተው ቢሆን ኖሮ፤ ወይም የእርግዝና መከላከያ ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ፤ አንተ እንዳትረገዝ ማድረግ ይችሉ ነበር። ከተረገዝክ በኋላም ቢሆን ፅንሱን ማስወረድ ይችሉ ነበር። ከተወለድክ በኋላም ቢሆን አንቀው ሲጥ ሊያደርጉህና ወደ ሽንት ቤት ሊወረውሩህ ይችሉ ነበር። በተቃራኒው በፍቅር እየተንከባከቡ፣ ሽንትህን እየጠረጉ፤ ገላህን እያጠቡ፣ የሚያስፈልግህን ምግብ ሁሉ በሰዓቱ እየሰጡ በደንብ አሳድገውሀልና ምስጋና ይገባቸዋል፤ ክብርም ይገባቸዋል። ይህን ትዕዛዝ ማክበር የሚያስገኘው ጥቅም እንዳለ እዚያው ላይ ተቀምጧል፤ እንዲህ ነው የሚለው፤ “መልካም እንዲሆንልህ፣ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድርም እድሜህ እንዲረዝም።” በአንፃሩ ይህን ትዕዛዝ አለማክበር ብሎ አባትህንና እናትህን መሳደብ በሞት የሚያስቀጣ ከፍተኛ ሃጢአት መሆኑ በኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ ሃያ አንድ ቁጥር አስራ ስድስት በሚከተሉት አንቀፆች ተገልጿል፦ “አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ በሞት ይቀጣ።” ይሄ ትዕዛዝ ተግባራዊ ቢደረግ ብዙ ሰው አይተርፍም ነበር።

ትዕዛዝ ስድስት

ይሄ ትዕዛዝ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን በደንብ ተብራርቶ መቀመጥ ነበረበት። በድፍኑ አትግደል ነው የሚለው፤ ሰው ነው መግደል የማይቻለው ወይስ ህይወት ያላቸውን በጠቅላላ ነው የሚለው ነገር ነው የሚያስቸግረው። ቅማል፣ ቁንጫ፣ ጉንዳን፣… እነዚህን መግደል ያስኮንናል ወይስ አያስኮንንም?! እዚህ ላይ የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን ገድል ማየቱ ጠቃሚ ነው። አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ በህይወት ዘመናቸው እህል የሚባል አልቀመሱም ይባላል፤ ወደ ሰማይ ቤት የሚሄዱበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ መልዓከ ሞት “ህይወትዎን ልወስድ ነው የመጣሁት” ይላቸዋል፤ “እኔ እሞት ዘንድ ተገቢ አይደለም፤ ከነስጋዬ ነው ማረግ ያለብኝ” ይላሉ፤ “እንኳን እርስዎ ክርስቶስም ሞት ቀምሷል” ሲላቸው፤ “የለም እርሱ ሠላሳ ሦስት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ሲበላና ሲጠጣ ነው የኖረው እኔ በምንተዳዬ” ይላሉ፤ በመጨረሻ የህይወት መዝገባቸው ሲፈተሽ አንዷን ዝንብ በጭሯቸው ሳያውቁ እንደገደሏት ተረጋገጠ እናም ቢያንስ የዝንብ ነፍስ አጥፍተሃልና ሞት ይገበሃል ተብለው ሞቱ። በዚህ ደረጃ ከሆነ ይህ ትዕዛዝ የሚተረጎመው አንድም የሚፀድቅ ሰው በዚች ምድር ሊኖር አይችልም።

ሌላው ይቅርና ሰው መግደል በራሱ ኃጥኢት ነው ወይ? የሚለውን ደግሞ ዕንይ፣ የሙሴ እግዚሄር አትግደል ቢልም፤ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ነፍሰ ገዳይ የሆኑ ነቢያት እናገኛለን፤ ከእነዚህ አንዱ ሙሴ ራሱ ነው። አንድ ከአይሁድ ጋር የተጣላ ግብፃዊ ገድሎ ሸሽቷል። ስለዚህ አትግደል የሚለውን ትዕዛዝ ጥሷል ማለት ነው። ንጉስ ዳዊት ጎሊያድን በወንጭፍ ገድሏል፤ ወይ በጦርነት ጊዜ ሰው መግደል ኃጢአት ካልሆነ በግልፅ ነው መቀመጥ ያለበት።

ትዕዛዝ ሰባት

“አታመንዝር” ይሄ ትዕዛዝ መሰረታዊ ሀሳቡ ችግር የለውም። የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ግን አዲስ ነገር ፈላጊ አድርጎ ነው፤ ስለዚህ ተግባራዊነቱ ላይ ችግር ሊኖረው ይችላል። ሌላው መሰረታዊ ጥያቄ የሚያስነሳው ደግሞ ነቢያቱ ይህን ሕግ ሲጥሱት የመታየቱ ነገር ነው። አብርሃም ራሱ ከሚስቱ ሌላ ገረዱ ውሽማው ነበረች፤ ልጅም ወልዳለታለች። ንጉስ ዳዊት ከእርሱ በፊት የነበረውን የንጉስ ሳዖልን እቁባቶች ወስዷል፤ ሌላው ይቅርና የአሽከሩን የጀግናው ኦርዮን ሚስት የነበረችውን ቤርሳቤህን አባልጓል፤ ባሏንም አስገድሏል። የእርሱ ልጅ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን ጥበቡ እዚህ ላይ ይሁን በሌላ ጉዳይ ግልፅ አይደለም፤ ሰባት መቶ እቁባቶች የነበሩት ሰው ነው፤ የእኛዋ ንግስተ ሳባንም አልማራት፤ ጨው የበዛበት ምግብ አስበልቶ በዘዴ አብሯት አድሯል፤ በዚህም ምክንያት አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደች ነው የሚለው ክብረ ነገስቱ።

ትዕዛዝ ስምንት

“አትስረቅ” ተገቢና ትክክለኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። መስረቅ ሀጢያት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። ስለዚህ ከትዕዛዛቱ ሁሉ ቀጥተኛና ግልፅ ሆኖ የተቀመጠው ይሄኛው አንቀጽ ነው ማለት ይቻላል።

ትዕዛዝ ዘጠኝ

“በባልንጀራህ ላይ በሀሰት አትመስክር” የሚለው ትዕዛዝ ተገቢ ሆኖ ሳለ በባልንጀራ ላይ ብቻ መወሰን አልነበረበትም፤ ትንሽ መሻሻል አለበት። ከፍ ተብሎም ነው መገለፅ ያለበት። በማንኛውም ሰው ላይ በሀሰት አትመስክር ነው መባል ያለበት። በማታውቀው ባልንጀራህ ባልሆነ ሰው ላይም ቢሆን በሀሰት መመስከር የለብህም።

ትዕዛዝ አስር

የመጨረሻው ትዕዛዝ “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም፣ ገረዱንም፣ በሬውንም፣ አህያውኑም፣ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” የሚል ነው። ይሄ ትዕዛዝ ከኃጢአት ብቻ አይደለም የሚያተርፍ ከሰው ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ላይ በጓደኞችህ ዘንድ የሚኖርህን ታማኝነትና ከበሬታ ሁሉ የሚወስን ነው። ስለዚህ ይሄኛውን ትዕዛዝ በተገቢው ሁኔታ ማክበር ያስፈልጋል። ይሄ ትዕዛዝ ግን ለሴቷ ይስራ አይስራ የታወቀ ነገር የለም፤ ባልንጀራህ ባልሆነ ሰው ላይ ይስራ አይስራም አልታወቀም፤ ጥርት ብሎ ነው መቀመጥ ያለበት። በመሰረታዊ ሀሳቡ ግን ሸጋ የሆነ ትዕዛዝ ነው።

እንደ ማጠቃሊያ

የሙሴ ትዕዛዛትን ብታከብር ታተርፋለህ፤ ከህሊናህ ጋር የማይጋጩ፣ ለማኅበራዊ ኑሮና ተግባቦት ጠቃሚ የሆኑ ትዕዛዛትን ሁሉ አክብር። የመንግሥት ትዕዛዝ፣ የሀኪም ትዕዛዝ፣ የትራፊክ ትዕዛዝ የመሳሰሉትን ትዕዛዛትና ሕጎች የማያከብር ሰው ወይም ህዝብ የሰለጠነ አይደለም፤ ኋላቀርነቱን ነው የሚያሳየው። የስልጣኔ ዋነኛ መገለጫ ለማኅበራዊ ትዕዛዛትና ህጎች ልዩ ትኩረት የሚሰጥና የሚተገብር ማኅበረሰብ መኖር ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top