ጥበብ በታሪክ ገፅ

ዓባይ እና የፈርኦኖች ሀተታ ተፈጥሮ

የጥንታዊት ግብጽ ፈርኦኖች ስልጣኔ ታሪክ ከዓለም ቀደምት ስልጣኔዎች መካከል የሚጠቀስ የታሪክ አካል ነው። ይህ ስልጣኔ በጽሑፍ ተመዝግበው ከሚገኙ በርከት ያሉ ታሪኮች በተጨማሪ በልዩ ልዩ ተረኮች ማለትም ሀተታ ተፈጥሮዎች (Mythologies)፣ አፈታሪኮች (Legends) እና ተረቶች (Folktales) የታደለ ነው። እነዚህ ተረኮች ደግሞ አስደናቂ የፍቅር ታሪኮችንም ይዘው ይገኛሉ። እነዚህ የፍቅር ታሪኮች በቀደምት የመቃብር ስፍራዎች እና በተለያዩ ሀውልቶች ላይ ተጽፈው ይገኛሉ። ከእነዚህ በጣም ቆየት ያሉ የፍቅር ታሪኮች መካከል የሁለቱ አማልክቶች ‘ኦሳይረስ’ እና ‘አይሲስ’ የፍቅር ታሪክ በብዙ ግብጻውያን ዘንድ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል። የእነዚህን አማልክት የፍቅር ታሪክ የሚሰማ ወይንም የሚያነብ ሰው ሌላም የሚገነዘበው ነገር አለ የዓባይ ወንዝ አፈጣጠር ጉዳይ ላይ ጥንታዊ ግብጾች ያላቸውን አመለካከት ነው።

ኦሳይረስ እና አይሲስ ‘በግ’ እና ‘ነት’ ከተባሉ ሌሎች አማልክቶች እንደተፈጠሩ የሚነገር ሲሆን ፍቅራቸው ከጸሃይና ከጨረቃ በላይ የሚያንጸባርቅ ነው እየተባለ ይነገር እንደነበረም ይገለጻል። እነዚህ አማልክቶች ከመጋባታቸው በፊት እህትና ወንድም የነበሩ ሲሆን ‘ሴት’ የተሰኘ ወንድም እና ‘ናፓታ’ የተሰኘች እህትም ነበረቻቸው። ኦሳይረስ ‘ራ’ ከተባለው ከቀዳሚ አማልክቶች መካከል የሚመደበው አምላክ ሰማያዊውን ዓለም ለማስተዳደር ሲሄድ ምድርን ካስተዳደሯት አማልክቶች መካከል ጠቢቡ እና ተወዳጁ አምላክ እንደሆነ የግብጽ ህዝቦች እምነት እንዳላቸው ይነገራል። ከአይሲስ ጋር ከተጋቡም በኋላ ለህዝቡ ሥልጣኔን እንዳስተዋወቁ እና ሕግን እንዳቆሙ ይነገራል። ደግነታቸው እና ፍትሃዊነታቸው እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ መወደዳቸው ልቡ ከክፋት እና ጥላቻ የተሰራውን የመጥፎነት ተምሳሌት ተደርጎ የሚቆጠረው ወንድማቸው ሴትን በቅናት ያበግነው ነበር። በዚህም የተነሳ ወንድሙን ለማጥፋት እና የእርሱን ቦታ ለመውሰድ ይነሳሳል። አንድ ቀንም ውበቱ የተመለከተውን ሁሉ ልብ የሚገዛ ከተመረጠ እንጨት በልዩ ጥበብ የተሰራ ሳጥን ያስቀርጻል። ቁመቱ በሳጥኑ ልክ የሆነ አምላክ ከተገኘ በስጦታ መልክ ሊሰጥ እንደሚችልም በኩራት ይናገራል። ኦሳይረስም ሳጥኑ ውስጥ ገብቶ እነዲለካው እና በቁመቱ ልክ ከሆነ በስጦታ መልክ እንደሚሰጠው ሲነግረው ይስማማል። ከገባም በኋላ ሳጥኑን አጥብቆ ዘግቶ እንዳይከፈት ያደርጋል። አርቆም ይጥለዋል። የባሏን መሞት ያወቀችው አይሲስም ረዥም ቀናት እና ረዥም ሌሊቶች ታለቅሳለች፤ እንባዋም ከመብዛቱ የተነሳ ዓባይ ወንዝን እንደፈጠረ ይነገራል። እንባዋ እንዳቆመም ረዥሙን ጸጉሯን በአጭር ተቆርጣ የምታፈቅረውን ባሏን መፈልግ ትጀምራች። ከብዙ ጊዚያት በኋላም የፊንቄ ህዝቦች የሚኖሩበት ሸለቆ ውስጥ ትደርሳለች። የባሏ አስከሬንም በዛፎች ተሸፍኖ ታገኘዋለች። አስከሬኑን ከማግኘቷ በፊት ግን የባሏ አካል ተደብቆበት የነበረው ቦታ ላይ የሚገኙ ትንንሽ ቁጥቋጦዎች በተቀደሰው አስከሬን ምክንያት ታይተው ወደ ማይታወቁ ውብ ዛፍነት ተቀይረው ዛፎቹን በአካባቢው ነዋሪዎች ተሸምተው ለቤት መስሪያ ምሰሶነት መጠቀም ጀምረው ነበር። የቦታው ገለጥ ማለትም ሳጥኑን በቀላሉ እንድታገኘው እንደረዳት ይነገራል። እነዚህ ምሰሶዎችም የመረጋጋት እና የጽናት ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠሩ እንደነበር ይተረካል። አይሲስ አስከሬኑን ይዛ ወደ ግብጽ ትሄዳለች። የባሏን አስከሬን ፍለጋ መሄዷን የሰማው ሴትም ቀድሞ ተዘጋጅቶ ይጠብቃት ነበር እና እንደገና ጠብቆ ከወሰደ በኋላ አካሉን አርባ ሁለት ቦታ ቆራርጦ በተለያዩ የግብጽ ቦታዎች ላይ ይጥለዋል። በዚህ ያዘነችው አይሲስ አካሉን እንደገና ለረዥም ጊዜያት አፈላልጋ ከለቀመች በኋላ በወርቅ እና በሰም ታጣብቀዋለች። ከአካሉ መካከል ግን የወንድ የመራቢያ አካሉ በእንባዋ ዥረት እንደተፈጠረ የሚነገረው ዓባይ ውስጥ በጥልቀት ስለወረወረው ልታገኘው አልቻለችም። በዚህ የተነሳ የዓባይ ዉሃ የነካው የምድር ዘር ሁሉ ይራባል፣ ይባዛል እንዲሁም ይለመልማል ተብሎ ይታመናል።

አይሲስ የባሏን ቁርጥራጭ የአካል ክፍሎች በምትፈልግበት ወቅት ደግሞ የግብጽን ወንዞች የሚጠብቀው እና ለተበደሉት እንደሚቆም የሚታመነው የወንዞች አምላክ ሶቤክ እንዳገዛት ይነገራል። ከአንደኛው የዘር የአካል ክፍሉ ውጭ ያሉ ክፍሎቹን ብቻ ከገጣጠመች በኋላም በመንፈስ ከእርሱ አርግዛ ሆሬስ የተባለ ልጅ ትወልዳለች። የሆሬስ እጣ ፋንታም ክፋተኛ እና ተንኮለኛ አጎቱን መበቀል ነበር። በዚህ የተነሳ ሆሬስ አጎቱን ለማጥፋት ይወስናል።

ሆሬስ እና አጎቱ ሴትም ከሰማኒያ ዓመታት በላይ ተዋግተዋል። ፍልሚያው በምድር ተደርጎ ማሸነፍ ባለመቻሉ በዓባይ ወንዝ ላይ በጀልባ ለረዥም ዘመናት ተደርጎ በሆሬስ አሸናፊነት ተጠናቋል። የዓባይ አምላክ የሆነው ሶቤክ ሆሬስን ድል እንዲነሳ እንዳገዘውም ይነገራል። ከዚያ ጊዜም ጀምሮ ሰላም ሰፍኗል ተብሎ ይታመናል። የግብጻውያን ሰልጣኔም ይበልጥ እያበበ እንደሄደ እና በዓባይ ሸለቆዎች ዙሪያ ልምላሜ ሊሆን የቻለው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። እናትና ልጅ አማልክትም በሰላም ለረዥም ዓመት የግብጽን ህዝብ መርተዋል። ኦሳይረስም ከሞተ በኋላ የሙታን አምላክ በመሆን ሙታን ላይ እየፈረደ በፈርኦኖች መመለኩን ቀጥሏል ተብሎ ይታመናል። ይህን የአማልክቶች ታሪክ ብዙ ህዝቦች እንደዚህ ሲተርኩት ጥቂቶቸ ደግሞ ዓባይ ኦሳይረስ እና አይሲስ ከመፈጠራቸው በፊትም እንደነበረ ነገር ግን በአይሲስ የሀዘን እንባ ዥረት ምክንያት መጠኑ እንደጨመረ እና አፈሳሰሱ እንደተስተካከለ እምነት እንደነበራቸው ይሰማል። ያም ሆነ ይህ ግን የዓባይ ወንዝ የፍቅር ተምሳሌት ተደርገው ከሚቆጠሩት ኦሳይረስ እና አይሲስ ጋር የተገናኘ ታሪክ እንዳለው ሲነገር መቆየቱ በጥንታውያን ግብጾች ማንነት እና ዓባይ ያላቸው ዝምድና ውስጥ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ለመገመት አይከብድም።

ሌላው ከዓባይ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ታሪክ ከላይ የተጠቀሰው የዓባይ ወንዝ አምላክ የሆነው ሶቤክ ታሪክ ነው። ዓባይ ወንዝ ከዚህ አምላክ ላብ የመነጨ እንደሆነ ይታመናል። የዓባይ ጠባቂ አምላክ እንደሆነ በጽኑ ይታመን ነበር። ይህ የዓባይ አምላክ በባህሪው እና በሰውነት ሁኔታው የሚከበር እና የሚፈራ አምላክ እንደነበረ ይገለጻል። አንዳንድ ጊዜ በትልቅ አዞ ጭንቅላት በአብዛኛው ደግሞ ከአንገት በላይ አዞ ከአንገት በታች ደግሞ ፈርጠም ባለ የሰው አካል ይመሰላል። ይህ አምላክ በጣም የሚከበር ቢሆንም ከጠባዩ ተለዋዋጭነት የተነሳ ስለባህሪው ለመናገር እንደማይቻል ይጠቀሳል። የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን የባህር እንስሳትም ይፈሩት እንደነበረ በተደጋጋሚ ይነሳል። ከዚህ ተፈሪነቱ እና ተከባሪነቱ የሚመነጩ ብዙ ታሪኮች የሚነገሩ ሲሆን የሆሬስን አራት ህጻናት ዓባይ ውስጥ ሰምጠው ከመቅረት እንዳዳናቸው ሲነገር በተቃራኒው ደግሞ ከእንስሳዊ የማይተነበይ ጸባዩ የተነሳ የኦሳይረስን አንድ የሠውነት ክፍል ዓባይ ወንዝ ላይ አግኝቶ ጎምዥቶ በመብላቱ ምክንያት ምላሱ እንዲቆረጥ በሌሎች አማልክት ተፈርዶበታልም ይባላል። ለዚህ ይመስላል ብዙ ግብጽ ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የአዞ ምስሎች ምላሳቸው ቆራጣ የሆነው ተብሎ ይገመታል። ይህ አምላክ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን በወንዝ ውስጥ የሚገኙ እንስሳትም ሁሉ ያፍሩታል፣ ያከብሩታል፣… ተብሎ ስለሚታመን የማይፈራው የዓባይ ጠባቂ ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ የተነሳ ቀደምት ግብጾች የእርሱን መንፈስ ለማስደሰት በማሰብ አዞ ያረቡ ነበር። ለሚያረቧቸው አዞዎች የሚሰጡት እንክብካቤ የተለዬ ሲሆን አዞዎችም ወይን ማርና ስጋ ያበሏቸው እንደነበር ይነገራል። በአዞ ተበልተው ለሞቱ ሰዎችም በሶቤክ እንደሚባረኩ ይቆጠርላቸዋል ተብሎ ይታመናል። ሞታቸውም በዓባይ ወንዝ ዳርቻ በሚደረግ ዝግጅት ይዘከራል። ከመካከለኛው ዘመን በኋላ ሶቤክ ከትልቁ አምላክ ራ ጋር ተዋሀዶ ሶቤክ ራ ሆኗል ብሎ በማመን የበለጠ ክብሩ ከፍ እንዲል በማድረግ ያመልኩት እንደነበረ ይወሳል። በተለያዩ የግብጽ ጥንታዊ ከተሞችም ምስሉ ተቀርጾ የሚመለክ ሲሆን በተለይ ሽድየት የተሰኘችው ከተማ የአዞ ከተማ በመባል ትታወቅ የነበረች ከተማ እንደሆነች ይዘከራል። በዚህች ጥንታዊ ከተማም ብዙ የዚህ አምላክ ምስሎች ናቸው ተብለው የሚታመኑ ቅርጾች የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል። እስካሁንም ሶቤክ የዓባይ አምላክ እንደነበረ የሚተርኩ ሰዎችም አሉ።

እነዚህ እና መሰል ተረኮች የጥንታውያን ግብጾችን እምነቶች የሚያሳዩ እና እውነት እንደሆኑ ተቆጥረው ከትውልድ ወደ ትወልድ ሲተላለፉ የቆዩ ተረኮች ናቸው። በተለይ ከላይ የቀረበው እና በቅድሚያ ያየነው ታሪክ የፍቅር ታሪክ ቢመስልም ልክ ቀጥሎ ያየነው የእምነት ሁኔታን እንደሚያሳዬው የአምላክ ሶቤክ ታሪክ ሁሉ፤ የሰው ልጅ በቀላሉ ሊረዳ፣ ሊነካ እንዲሁም ሊዳስስ ከሚችላቸው ነገሮች ጀርባ አሉ ተብለው ስለሚታመኑ አማልክቶች እና አፈጣጠር ሁኔታዎች ላይ አተኩረው ከሚነገሩት ሀተታ ተፈጥሮዎች መካከል የሚመደብ ነው። ሀተታ ተፈጥሮዎች የማኅበረሰብ ታሪኮች በመሆናቸው የተነሳ የጋራ ማንነትን እና አስተሳሰብን ከመፍጠራቸው እንዲሁም ከመግለጻቸው በተጨማሪ ስለነገሮች ጥንተ-አመጣጥ መልስ የሚሰጡ የባህል እና የማንነት ተረኮች ናቸው። ሀተታ ተፈጥሮዎች እውነት ናቸው ተብለው ከመታሰባቸው የተነሳ ተደጋግመው ሲነገሩ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ይታያሉ። ድግግሞሻቸው የሚያሳየው በታሪኩ ባለቤት ማኅበረሰብ ዘንድ ምንያህል የእውናዊነት ስሜት እንደፈጠሩ ነው። በዚህ የተነሳ የሚነገርበት አካባቢ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ ሆነው ሲቀርቡ ይታያሉ። ምክንያቱም አንድ ማኅበረሰብ የእኔ ብሎ ያላመነበትን ታሪክ እና ድርጊት ደጋግሞ ሲተርክ ወይንም ሲከውን አይታይም። እነዚህ የማኅበረሰብ ተረኮች ተምሳሌታዊነት ስለሚታይባቸው በብዙ መልኩ ሊፈከሩ እና ሊተረጎሙ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ ተመሳሳይ ተረክ በተለየ አውድ ውስጥ ሲነገር ወይንም ይነገር እንደነበረ መስማት የተለመደ ነው።

ከላይ ያየናቸው ሃሳቦች መካከልም የኦሳይረስ እና የአይሲስ ታሪክ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ዘመን የማይሽረው የፍቅር ታሪክ ሆኖ ሲቀርብ ሌሎች ስፍራዎች ላይ ደግሞ የዓባይ ወንዝ ሲነሳ ተያይዞ የሚመዘዝ ታሪክ ሆኖ ይቀርባል። የመጀመሪያው ታሪክ ላይ ዓባይ ለዚያውም የፍቅር ተምሳሌት ተደርጋ በምትቆጠር ግብጻዊት አምላክ ለፍቅር ሲባል በፈሰሰ እንባ የመነጨ ቅዱስ ወንዝ ነው። እዚህ ላይ ይህ አንድ ብቻ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ታሪክ ቢሆንም ይህንን እና መሰል ተረኮችን ሲሰማ የኖረ ማኅበረሰብ እንዴት ይህን ወንዝ እንደ ቅዱስ እና ክቡር አይቆጥረው? የአምላክ ሶቤክን ታሪክ ስናይ ደግሞ ዓባይን የሚጠብቅ ሲፈልግ ሰው ሲፈልግ አውሬ የሚሆን፤ ለጠላቱ የሚያስፈራ ለወዳጁ የሚያኮራ አምላክ እንዳለው ያሳያል። ይህ እና መሰል ተረኮች ለዚያን ጊዜው ማኅበረሰብ የኩራት ስሜት ከሚፈጥሩ እውነታዎች መካከል ሊመደብ የሚችል ነው። ምክንያቱም የበረሀ ገነታቸው ዓባይ እና መሰል ወንዞች ጠባቂ አላቸው እና። ስለዚህም የሚያስፈራ በባህሪው እና በሰውነት ሁኔታው አስገራሚው አምላክ የሶቤክ ምንነት እና ባህሪ ሙሉ በሙሉ ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው። የኦሳይረስ፣ የአይሲስን እና የሶቤክን ታሪክ አንድ የሚያደርጋቸው አንድ ቁምነገር ዓባይ ከግብጻውያን አማልክት እንባ እና ላብ የተፈጠረ የግብጻውያን ማንነት አካል ነው የሚል ትርጓሜ መስጠቱ ነው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ ተውኔት፣ ባለቅኔ እና መምህር ጸጋዬ ገብረመድህን በአንድ ወቅት የተናገረውን ሀሳብ ማንሳት ይቻላል። በእርሱ አገላለጽ “በማናቸውም የዓለም ህዝብ ባህል ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የየሀገሩ ወንዝ ጉዞ በተለይ የታላላቅ ወንዞች ጉዞ የየሃገሩ የሰፊው ህዝብ ጉዞ የየትውልዱ ተምሳሌት ሆኖ ይቀረጻል። ለምሳሌ ዓባይ አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ መረብ እና ተከዜ ሌሎችም… በኢትዮጵያ፣ በኑቢያ እና በግብጽ በተለይ ዓባይ፤ ኤፍራጠስ እና ጤግሮስ በሜሶፖታምያ፤ ቴምስ በእንግሊዝ፤ ሚሲሲፒ በአሜሪካ…” ይህ ማለት ለጥንታውያን የግብጽ ፈርኦን ትውልዶች ዓባይ ከአማልክቶቻቸው አካል በወጣ ፈሳሽ የፈጠረው ቅዱስ ወንዝ ነው። ስለ አማልእክቱ የተወራ ከነርሱ ጋር የተያያዘ ነገር ሁሉ ተቀባይነቱ ከፍተኛ ነው። ሌላው የሚገርመው ሀሳብ ቢሞቱ እንኳን ኦሳይረስ በሙታን ላይ ፈራጅ የሆነ አምላክ ነውና ይፈርድብናል ብለው ያስቡ ስለነበረ እሱን የተመለከቱ ማንኛውም ሃሳቦች ይከበሩ ነበር። በአጭሩ እነዚህ ታሪኮች በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ ታሪኮች እንደነበሩ ማስታወስም ተገቢ ነው። የነበሩ ምናልባትም አሁንም ድረስ በአማልክት የሚያምን ካለ ቅዱሳን እና የማይመረመሩ እውነተኛ ታሪኮች ናቸው። እዚህ ታሪክ ላይ የሚጠቀሱት አማልክቶችም ተወዳጅና ተፈሪ መሆናቸው ደግሞ በተናጋሪው እና በአድማጩ ላይ አዎንታዊ ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

ብዙ በጥንታዊ ግብጻውያን ስለዓባይ የሚነገሩ ሀተታ ተፈጥሮዎች የዚህ ዐይነት የመከበር እና የመወደድ ስሜትን የመፍጠር ባህርይ ያላቸው ናቸው። ይህ ማለት ታሪኮቹ ዓባይ የአሁኑ የግብጽ ትውልድ የታሪክ እና የማንነት አካል ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈጥሩት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም የአንድ ማኅበረሰብ ማንነት የሚጀምረው ከታሪኩ ነውና። በዚህ ሰዓት ዓባይ በብዙ ግብጻውያን ህይወት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም እነዚህ እና መሰል ቀላል የሚመስሉ የማንነት ተረኮች በሰፊው የግብጽ ህዝብ ላይ የሚፈጥሩት የጋራ ስሜት ቀላል እንዳልሆነ ማስታወስም ተገቢ ነው።

ታሪኮቹ

“ጥቁር ዓባይ ከኢትዮያ መንጭቶ፤ ነጭ ዓባይ ደግሞ ከኢኳቴሪያል ተራሮች ተነስቶ፤ በአፍሪካ ረዥሙን የዓባይ ወንዝ በጋራ ፈጥረው፤ ዓባይም ከመነሻዎቹ ጀምሮ በረሀ ለበረሀ እየተሸሎከሎከ ከአስር በላይ ድንበሮችን አቋርጦ ሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ይገባል” ከሚለው ከዚህ ዘመን እውነታ የበለጠ ከላይ የተጠቀሱትን ታሪክ መሳይ በሴራ እና በአስገራሚ ገጠመኝ የተሞሉ ተረኮች በቀላሉ የአብዛኛው ሕዝብ ጭንቅላት ውስጥ ገብተው የመቀመጥ እና ሆን ተብሎ ከሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ የበለጠ ኢ-ንቁ አዕምሮን ወደ ንቃት የማምጣት አቅም አላቸው።

ግብጽም ሆነ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው። ምንም እንኳን ሁለቱም ሀገራት በጣም ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ የጽሑፍ ታሪክ ቢኖራቸውም በየሀገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች በእኩልነት የሚጋሯቸው ቃላዊ ተረኮችም አሏቸው። እንዚህ የቃል ተረኮች እውነታም ይሁኑ በማኅበረሰብ የተፈጠሩ አገልግሎታቸው አንድ ነው። የጋራ ማንነትን እና አመለካከትን መፍጠር። ግብጽ ብቻ አይደለችም ኢትዮጵያም በዚህ የታደለች ሀገር ናት። ለግብጽ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያም ዓባይ ትልቅ ትርጉም አለው። ግብጽ ብቻ አይደለችም ጥንታዊ የዓባይ በረሀ ኢትዮጵያውያንም ስለዓባይ አፈጣጠር የሚያምኑትን የሚገልጹበት ልዩልዩ ተረኮች አሏቸው። ኢትዮጵውያን የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ስለዓባይ የሚሰጡትን ሀተታ ተፈጥሮ ለሌላ ግዜ በሰፊው የምንመለስበት ሲሆን አንድ መገንዘብ ያለብን ቁምነገር ግብጻውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዓባይን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ጠንካራ ለመሆኑ ከሚጠቀሱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በተጨማሪ መሰል ታሪኮች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ለማመልከት እንወዳለን። ይህንንም ተገንዝበን የምንፈጥራቸው ማንኛውም ማኅበረሰባዊ ተረኮች ለወደፊቱ የሚኖራቸውን ፋይዳ በማሰብ ሊሆን ይገባል። ቀደምት የኢትዮጵያ አባቶች እንደሚሉት ምንም ቢሆን ምን መጥፎ የሆነን ማንኛውንም ነገር ስንሰራም ሆነ ስናወራው ደስ የማይል ስሜት ይሰማናል። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ነገሩን ቆም ብሎ ማሰብ እና ማስተካከል ይገባል። ለትውልድ የምንሰራውም ነገር እንዲሁ ነው፤ በበቀል እና በክፋት ስሜት ሆነን የምንፈጥረው ተረክ በመጥፎ ስሜት ውስጥ ሆነን የፈጠርነው ስለሚሆን ለሚመጣው ትውልድም ጥሩ ሊሆን አይችልም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top