የታዛ እንግዳ

“ኮሚኒዝም ያዋረደውን እውቀትና አዋቂነት ስላከበራችሁ እጅግ አመሰግናችኋለሁ”

ኮሚኒዝም ያዋረደውን እውቀትና አዋቂነት ስላከበራችሁ እጅግ አመሰግናችኋለሁ” – ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

“ጌታቸው ኃይሌ የኢትዮጵያ ምድር በኛ ትውልድ ካፈራቻቸው ምርጥና ውድ ልጆቿ ቀዳሚው ናቸው።”

ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር።

“ጌታቸውን ከአርባ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ አውቃቸዋለሁ። በጠቅላላው የኢትዮጵያ ጥናት ረገድ እጅግ ከሚታወቁትና ከሚደነቁት ታላላቅ ምሁራን አንዱ ናቸው። ዛሬ ለደረሱበት የሙያ ከፍታ ያሳዩትን አስደናቂ እርምጃም በቅርበት ተመልክቻለሁ።”

ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡለንዶርፍ። (ትርጉም ዓለማየሁ ገ/ሕይወት)

“በዚህ ዘመን እንደ ዶ/ር ጌታቸው ያሉት ሰዎች፤ ‘ሰው ማለት ሰው ማለት፣ ሰው የሚሆን ነው፣ ሰው የጠፋ ዕለት’ የሚለውን የሃገራችን ስንኝ ያስታውሱኛል።”

ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ (ከፊል ትርጉም ዓለማየሁ)

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ዛሬ ሥራና ሕይወታቸውን የምናካፍላችሁ፣ ለጥያቄዎቻችን የሰጡንን መልሶች የምናስነብባችሁ ባለታሪክ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው። እኒህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ለማክበርና በሙያቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ለማመስገን ግንቦት 18 ቀን 1993 ዓ.ም. (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሜይ 26, 2001) በተዘጋጀ ክብረበዓል ላይ ከተነገሩት የአድናቆት ቃላት የተወሰኑትን ነው ከፍ ብለን ያቀረብንላችሁ። በዋሺንግተን ዲሲዋ የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በተካሄደው በዚሁ ሥነሥርዓት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ምሁራን ተሳትፈዋል። የአማርኛና የግእዝ ቅኔዎች ተዘርፈዋል። በጽናጽልና በሽብሸባ የታጀበ ወረብም ቀርቧል። ፕሮፌሰር ጌታቸው በፕሮግራሙ ማብቂያ ከተናገሩት፣ “ኮሚኒዝም ያዋረደውን እውቀትና አዋቂነት ስላከበራችሁ እጅግ አመሰግናችኋለሁ” የሚለው ይገኝበታል። ይህ ክብር ከተሰጣቸው አሥራ ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል። ከዚያም ወዲህ ለቁጥር የሚያታክቱ የጥናትና የምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። በ1987 (እንደ አውሮውያን አቆጣጠር) የብሪቲሽ አካዳሚ አባልነትን ሲያገኙ በኤድዋርድ ኡለንዶርፍ ስም የተሰየመ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። በ1988 (እ.አ.አ) የታዋቂው የመክ አርቱር ፋውንዴሽንን (John D. and Catherine T. MacArthur Foundation) ሽልማት አሸንፈዋል። በ1995 (እ.አ.አ) ደግሞ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ማኅበረ ግሩያን ዘረ ኢትዮጵያ (Society of Ethiopians Established in the Diaspora (SEED) ከምስጋናና አድናቆት ጋር ሸልሟቸዋል። ሌሎች በርካታ ሽልማቶችንም ተቀብለዋል።

ከልጅነታቸው ጀምሮ፣ በችግር ውስጥ ሆነው እንኳ፣ ከምግብ ይልቅ የትምህርትና የእውቀት ረሃብ የበለጠባቸው ታላቅ ምሁር፣ ዛሬም በአረጋዊነታቸው ከንባብ፣ ከጥናትና ከምርምር አልተለዩም። ዛሬም ለወገናቸው ይሆናል፣ ይጠቅማል የሚሉትን ሃሳብ ከማካፈል ወደኋላ አላሉም። ጥያቄ ሲቀርብላቸውም በፍጹም ትህትና የሚቀበሉ፣ እምቢታን የማያውቁ፣ ቀጠሮ የማያበዙ አባት ናቸው።

ይህን ሰፋ ያለ ቃለመጠይቅ ከዓለማየሁ ገ/ ሕይወት ጋር ካደረጉ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ወደህትመት ለመምጣት የዘገየው በጠያቂው ችግር ነው። ከዚያም ወዲህ ጠያቂው በተለያዩ ጊዜያት ምክራቸውንና ሃሳባቸውን ተጋርቷል። በዚህም ምክንያት መጨመር ያለባቸውን ጉዳዮች፣ ለምሳሌ ከዚያ ወዲህ ያሳተሟቸውን ሥራዎች፣ ለማካተት ሞክሯል።

ከተከበሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር፣ ስለሥራዎቻቸውና ስለግል ሕይወታቸው ተጨዋውተዋል። በዚህም የልጅነት ትዝታቸውን፣ የትምህርት ቤት ቆይታቸውን፣ በአገር ቤትና በውጪ፣ ከዚያ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ስላሳለፉት ጊዜ፣ ስለስደታቸውና ከቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስለአከናወኗቸው ተግባራት፣ ስለ ግዕዝ ቋንቋና ሥነጽሑፍ፣ የነበራቸው ጭውውት እንዲህ ተሰናድቷል።

ጋሽ ጌታቸው፣ የት ተወለዱ? የት አደጉ? ዘመኑስ?

አቶ ዓለማየሁ በጣም አመሰግናለሁ። የተወለድኩት ሸዋ ውስጥ ሸንኮራ የሚባል አገር አለ። እዚያው ከአዲስ አበባ ብዙ ርቀት የለውም። በዚያ ጊዜ አባቴ እና አያቶቼ ናቸው ሸንኮራ የሠፈሩት። ከዚያ በፊት ከወዲያ ከአንኮበርና ከመንዝ አካባቢ እንደመጡ ነው የማውቀው ሲናገሩ። ግን እኛ የሸንኮራ ልጆች ነን ነው የምንለው። ያው ሸንኮሮች ሆነናል። አባቴ መጀመሪያ የእርሻ ሚኒስቴር ቅጥር ሆኖ ነበር የሚያገለግል። ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ማለቴ ነው። ወዲያው የኢጣሊያ ወረራ መጣ።

መቼ ነው የተወለዱት ማለት ነው?

የተወለድኩት ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓ.ም. ነው። 3ኛ ልጅ ነኝ። የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ አረፈች፣ ሳታድግ። ሁለተኛዋ እህቴ አለች በሕይወት። ከእኔ ቀጥሎ የተወለደውም ሊያድግ አልቻለም። ወዲያው የኢጣሊያ ወረራ መጣ። ሃገራችን ሸንኮራን በጠቅላላ ጣሊያኖቹና ባንዳዎቹ አገሩን አቃጠሉት፣ እኛም ሸሸን። በዚያ ላይ አባቴ እግሩን ያመው ነበር። እሪህ ይባላል ያን ጊዜ። አንድ እግሩን በጣም ስላመመው ወዲያውም ጠበል ለመጠመቅ፣ ከዚያም አገሩ ስለፈረሰ ወደ እንጦጦ ኪዳነምህረት መጣን። ከዚያ እሱ ጠበል ሲጠመቅ እኛ ያገራችንን ትምህርት እንማር ነበር። የኢጣሊያ ወረራ ነበር በዘመኑ፤ ከዚያ ችግር መጣ። የሰው ሃገር ነው። ርስት የለም፣ ገቢ የለም፣ ቤተሰብ በሞላ በምፅዋት ሊኖር አይችልም፣ ስለዚህ እናቴ ልጆቿን ይዛ እንደገና ወደ ሸንኮራ ተመለሰች። እዚያው ርስቱ ስላለና እንዲታረስ። እንግዲህ ጣሊያኖቹም አገዛዛቸውን እያጸደቁ ሲሄዱ አንዳንድ ቦታ መታረስ ጀምሮ ነበርና ርስታችን ላይ ትንሽ የሚገኝ ነገር ፍለጋ ነው። ከዚያ ትንሽ እንደቆየን የትምህርቱ ጉዳይ ስላስፈለገ ወደ አባቴ ተመለስኩ። ወደ አዲስ አበባ ስመጣ እሱ ከእንጦጦ ኪዳነምህረት ለቆ ሄዷል። ያው ችግር ላይ ነው። መሄጃ ቦታ ሲፈልግ አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ ታውቀዋለህ ቦታውን አይደለም?

አዎ አውቀዋለሁ።

እዚያ አንድ መቃብር ቤት አግኝቶ ቁጭ ብሎ አገኘሁት። ማስተማር ይወዳል። ሕፃናትን ሰብስቦ ያስተምራል። እኔም ያንን ዕድል አግኝቼ አስተማሪዬ ሆነ። ስለዚህ ያገራችንን ትምህርት የተማርኩት ካባቴ ነው። ከዚያ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አጠገብ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ሲቋቋም እዚያው ገባሁ። እንግዲህ የኢትዮጵያን የመጀመሪያውን ትምህርት ያገባደድኩትና መጨረሻ ያደረስኩት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተማሪ ቤት በነበርኩበት ጊዜ ነው። ከዚያ ትምህርታቸውን የጨረሱና ደግሞም ወደፊት የመግፋት ዕድል ያላቸው ተመርጠው ግማሾቹ ወደ አቴና ሄዱ። ግማሾቹ ወደ ቱርክ አገር ሄዱ። የእኔ ዕድል ወደ ግብፅ መሄድ ሆነ። እኛ አራት ሆነን፣ ሶሥት መነኮሳት ተጨምረው በአንድ ላይ ሰባት ሆነን ወደ ግብፅ ሄድን። ግብፅ የመንፈሳዊ ትምህርት ቤት (Coptic Theological College) አላቸው። እዚያ ገባን።

ጋሽ ጌታቸው፣ እዚህ ላይ ላቋርጥዎትና አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት። እጅግ ከተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጋር በልጅነት ዕድሜያችሁ አብራችሁ እንደተማራችሁ ሰምቻለሁ። እስኪ ስለዚያም ያጫውቱኝ? የት ነው የተማራችሁት?

እንዴት አወቅከው?

የሆነ ቦታ አንብቤያለሁ፣ ምናልባት ከሥነ ምርምር ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ ሳይሆን አይቀርም። እንጦጦ ኪዳነምህረት ነው። አፈወርቅም እዚያው ነበር። ከብዙዎቹ ተማሪዎች እሱን ነው የማስታውሰው። ሌሎችም አሉ። ምክንያቱም ተማሪዎች ሁላችንም ድክመትም ብርታትም ያለብን ስለነበረ እንተዋወቃለን። በዚህ ምክንያት እሱን አስታውሰዋለሁ። እሱ ግን አያስታውሰኝም። አንድ ጊዜ አግኝቼው ተነጋግረን ‘እንጦጦኮ አብረን ነበርን’ ብዬው እዚያ እንደነበረ ነግሮኛል፣ ግን አንድ ዓመት ነው እንደዚህ ነው ብዙ አይደለም። እሺ፣ ግብፅ መንፈሳዊ ኮሌጅ መግባትዎን ገልጸው ነበር ያቆሙት። የእኔን ሕይወት የለወጠው ምናልባት ግብፅ የነበርኩበት ጊዜ ነው በብዙ ረገድ። አንደኛ ክርስቲያኖቹ ጥቂቶች ናቸው ቁጥራቸው። አገሩ የእስላሞች ነው። ጥቂቶች በብዙዎች ሥር እንዴት እንደሚተዳደሩ፣ እንዴት እንደሚጨቆኑ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ተገነዘብኩ። እዚያ ካይሮ በነበርኩበት ጊዜ ንኡሳን ጎሳዎች ወይንም ነገዶች ወይንም ቤተሰቦች እንበል፣ ክርስቲያኖቹ በእስላሞቹ ሥር ነው ያሉት። እና ብዙዎችና ጥቂቶች ምን አይነት ስሜት እንዳላቸው፣ በሁለቱ መሐል ያለውን ልዩነትም በኢትዮጵያ ሁኔታ ማየት የጀመርኩበት ነው። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የክርስቲያን መንግሥት ነው። የቤተክህነት ተፅዕኖ አለ። እስላሞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት ስሜት ይሰማቸዋል? የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ የመጣው እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ነው። አንደኛው ይሄ ነው። ሁለተኛው መንፈሳዊ ትምህርት በምንማርበት ጊዜ ከመነኮሳቱ ውስጥ ሁለቱ የሃዲስ ኪዳን መምህራን ናቸው። አንደኛው በተለይ ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ ይባላሉ፣ የጳውሎስንና የሐዋሪያቱን መልዕክታት ትርጉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳተሙ የታወቁ ሊቅ ናቸው። ትምህርት ላይ በነበርንበት ጊዜ ማታ ማታ ከእርሳቸው የሀዲስ ትርጉም እንማር ነበር። ትንሽ እንደቆየን ትምህርቱ እየጠነከረ ሲሄድ ጓደኞቼ ከእኔ ትንሽ ወደ ኋላ ቀረት ያሉ መሰለኝ፤ አሁን እንደማስታውሰው። እኔ ዝም ብዬ ጥርሴን ነክሼ እስከመጨረሻው ድረስ ወጣሁት። ሀዲስንና ትርጉሙን በመውጣቴም በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ያ ዕድል አጋጥሞኛል።

በኮሌጅ ቆይታችሁ የምትማሩት መንፈሳዊውን ብቻ ነበር?

ሌላ ያጋጠመኝን ልንገርህ። ትምህርት ቤቱ መንፈሳዊ ሆኖ ሳለ አንድ ሰው “እናንተ እዚህ ባላችሁበት ጊዜ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሌላም እኮ ትምህርት ልትማሩ ትችላላችሁ” አለን። “እንዴት? ምን ማለትህ ነው?” ብዬ ስጠይቀው “አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የማታ ትምህርት አለው- Extension፣ ከዚያ ውስጥ የመረጣችሁትን ትምህርት ፈልጋችሁ እኮ ልትማሩ ትችላላችሁ” አለን። ምን እንዳሳየው አላውቅም። ጥሩ ሰው ነው። ሃኪም ነው። እየመጣም ጤንነታችንን የሚከታተልልን ሰው ነው። በጣም ወዳጃችን የሆነ ግብፃዊ ነው። አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ሄደን ጠየቅናቸው። “እዚህ Extension ለመማር እንፈልጋለን፣ ቀን እንማራለን” ስንላቸው ጊዜ “አይ የማታውን ትምህርት የምንሰጠው የኮሌጅ ትምህርት ጨርሰው ሌላ ትምህርት ደሞ ለመማር ለሚፈልጉና የኮሌጅ ዲግሪ ላላቸው ነው እንጂ ዲግሪ የሌላቸውን አንቀበልም” አለ።

እናንተ ገና አልጨረሳችሁም?

እኛ ገና በመማር ላይ ነን። ምን አልናቸው፣ “ዲግሪውን የምትሰጡ ዕለት ያኛውን ቀደም አድርገን ብናመጣስ? መጨረሳችንና ዲግሪያችንን ማቅረባችን ብናሳያችሁስ? በዚያ ቅድመ ሁኔታ ልትቀበሉን ትችላላችሁ ወይ?” ብለን ጠየቅናቸው። የአድሚሽን ቦርዱ እንግዲህ ተሰብስቦ፣ ጉዳዩን አይቶ በመጨረሻ “በዚያ መሠረት እንቀበላችኋለን” አሉ። እኛ አራት ነን። አራታችንም ሄደን ተመዘገብን። ቀን ያንን ስንማር እንውልና ትምህርቱ ሲያልቅ ወዲያው እቃችንን ደብተራችንን ጠቅልለን ወደዚያ ወደ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ እንሄዳለን።

የት ከተማ ነበር?

እዚያው ካይሮ ነው። ከተማው ሰፊ ነው። ግን አውቶብስ አለ። በራችን ላይ ነው የሚቆመው። አንዱን አውቶብስ ብቻ ይዘን በቀጥታ እንሄዳለን። እዚያ እንደርስና ተምረን እንመለሳለን። ግን እንግዲህ ልትገምተው ትችላለህ። ሁለት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመከታተል ቀላል አይደለም። ጊዜውን መንገዱ ይበላዋል፣ በዚያ ላይ እዚህም የቤት ሥራ አለ፣ እዚያም እንዲሁ አለ። መንገድ ስንደርስ ጓደኞቼ በቃን አሉ። አይ አልቻልንም አሉ። ኧረ ግድ የላችሁም፣ እባካችሁ ብል እምቢ አሉ። እኔ እነሱ አልቻልክም ብለው ያስወጡኝ እንጂ እኔ አውቄ አልወጣም ብዬ ቀጠልኩ። አንድ ቀን ማታ እንሂድ ብላቸው እምቢ አይሆንም በቃ አሉ። እኔ ሄድኩ። አስተማሪዬ እዚያ አየኝ። አስተማሪም ዲሬክተርም ነው። ትምህርት የጀመርነው ሶሲዮሎጂ ነው። እና ግሩም አስተማሪ ነው። ሚስተር ጋርድነር ይባላል። መቼም በጣም ነበር የሚያበረታታን። ታዲያ የዕለቱን ትምህርት ጨርሰን እሱ ወደኋላ ቀረ። ወረቀቱን ሲሰበስብ እኔም እዚያው ቁጭ ብዬ ቀረሁ። ሌሎቹ ሁሉ ተበትነዋል። ከሌላ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ባለዲግሪዎች ናቸው ሁሉም። እኔ እዚያ ቁጭ አልኩ። ወዲያው በአሜሪካን አነጋገር “Hi boy! What happened to your friends?’ “ኡኡ ጓደኞችህ የት አሉ?” አለ። ነገርኩት። “እንደዚህ ሆኖ ሁለት ቦታ ስለሆነ ስለበዛባቸው አልቻሉትም፣ መቅረታቸው ነው” ስለው “ታዲያ አንተ እንዴት ትችላለህ?” አለኝ። “እኔም አልቻልኩም” አልኩት። “ታዲያ ለምን መጣህ?” ሲለኝ “አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት” አልኩት። “ትምህርቱን ተምረናል፣ የምትሰጠንን ‘ፔፐር’፣ (‘ተርም ፔፐር’ የሚፃፍ አለ አይደለም?) እሱን አልቻልነውም። በሰዓቱ ልናቀርብ አልቻልንም። ይህንን የምትጠይቀንን ተርም ፔፐር የአሜሪካን አገር አድራሻህን ስጠንና በበጋው ተማሪ ቤት ሲዘጋ እኛ ፅፈን አዘጋጅተን እንላክልህ፣ አሁን ማረን እለፈን” አልኩት። ከዛ አሰበና “Oh, I can do that” አለ። “ይኸ ከሆነ ችግራችሁ ላደርግላችሁ እችላለሁ። ውጤታችሁን ሳላስገባ እቆያለሁ። እስክትልኩልኝ ድረስ እጠብቃለሁ” አለ። በኋላ ደስ አለኝ።

ጓደኞችዎስ ምን አሉ?

ያንን መልዕክት ይዤ ስሄድ ጓደኞቼ ራት ሲበሉ ደረስኩ። “እንዴት ሆነ? እንዴት ሆነ?” አሉ። “እንደዚህ ሆነ፤ ወረቀቱ ነው ችግራችን አልኩት፣ እሱን እንልካለን ብየው እሽ ብሏልና በሉ ነገ እንሂድ” አልኳቸው። ከዚያ ውስጥ አምሳሉ (ኋላ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ) ብቻ እመጣለሁ አለ። በማግስቱ ሁለታችን ብቻ ሄድን። ሁለቱ ጓደኞቻችን ይቅር አሉ። እንደምንም ብለን ያንን ወረቀታችንን በበጋ ሠርተን በሰጠኝ አድራሻ ላክንለት። እሱም ወረቀቱን አርሞ ልኮልን ትምህርቱን ለመጨረስ ቻልን። በዚህ አይነት የካይሮ ዩኒቨርሲቲውንም የመንፈሳዊውንም ትምህርት ተከታትለን ጨረስን። ኋላ ስብሰባ አድርገው የሚመረቁት፣ ዲግሪ የሚሰጣቸው ተማሪዎችና የማይሰጣቸው፣ ዝርዝሩ በሚታይበት ጊዜ እኛ ወረቀታችንን ከመንፈሳዊ ኮሌጅ አላመጣንም። አንድ ቀን ወደ እኩለ ቀን አካባቢ ነው መሰለኝ፣ በራፉ ላይ ቁጭ ብዬ ሚስተር ጋርድነር የምልህ ሰው ጂፑን እያሽከረከረ ከተፍ አለ። እዚያ ቦታ መጥቶ አያውቅም፣ አይቼው አላውቅም። “ምንድነው? What happened?” እንደዚህ ብዬ ስጠይቀው “ወረቀታችሁን አላመጣችሁም። እና ከዘንድሮው የምረቃ በዓል ልትሠረዙ ነው” አለኝ። “እንዴ ጨርሰናል እኮ እዚህ። የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የዲግሪ መስጫው ቀን እሱ ነው የቀረን” ብዬ ስለው “በል እንግዲያውስ ከዲሬክተራችሁ ‘ጨርሰዋል፣ አልፈዋል’ የሚል ወረቀት አሁኑኑ አጽፍና አምጣ” አለኝ። ከዚያ “ጌታቸውና አምሳሉ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል፣ ፈተናቸውን ሁሉ አልፈዋል። በበዓሉ ዕለት ዲፕሎማው እስኪሰጣቸው ነው የምንጠብቀው” ብሎ ዲሬክተሩ ጽፎ ሰጠው፣ ያን ይዞ ሄደ። ከዚያ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ (በ1957 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ልንጨርስ ቻልን።

ከግብፅ ቆይታዎ ሌላስ ምን የሚያስታውሱት ነገር አለ?

ግብፅ ውስጥ ሌላው ሕይወቴን የለወጠ የምለው መንፈሳዊ ትምህርት ከተማርንባቸው ቋንቋዎች ጋር ይያያዛል። ለወንጌሉ ግሪክ፣ ከምዕራቡ ዓለም ጸሐፊዎች ጋራ ለመተዋወቅ ላቲን፣ ለብሉይ ኪዳኑ እብራይስጥን ያስተምራሉ። ራሳቸው ደግሞ ‘ኮፕቶች’ ግብፃውያን ስለሆኑ ከጥንቱ የግብፅ ካይሮግሊፊክ (hieroglyphic) የመጣው፣ ከድሮ ግብፃውያን የመጣው ቋንቋ ኮፕቲክ የሚባል አለ። እሱ ደግሞ የራሳቸው የቤተክርስቲያናቸው ስለሆነ፣ እኛ ግዕዝ አለን እንደምንለው የእነሱ ኮፕቲክ ነው። እሱን ደግሞ ያስተምራሉ። ግሪክኛ፣ እብራይስጥ፣ ኮፕቲክ፣ ላቲን ይሄንን እንማራለን። የምንማረው፣ ንግግሩ ትምህርቱ ሁሉ ደግሞ በአረብኛ ነው። እንግዲህ አረብኛን ጨምር እዚያ ላይ። ከኋላችን ግዕዝ እናውቃለን፣ አማርኛ እናውቃለን። እንግዲህ ተመልከተው። ምን ልነግርህ ነው ብዙ ቋንቋ እችላለሁ ልልህ እኮ አይደለም። ይህን የምነግርህ ላንድ ነገር ላዘጋጅህ ነው። እነዚህን ሳያቸው አረብኛው፣ ግዕዙና እብራይስጡ አብረው ይሄዳሉ። ላቲኑ፣ ግሪኩና ኮፕቲኩ ደግሞ እርስ በርሳቸው አይመሳሰሉ እንጂ እራሳቸውን ችለው የሚሄዱ ናቸው። ከነዚህ ጋራ ዝምድና የላቸውም። እና ጥያቄ መጠየቅ ጀመርኩ። ምንድነው ይሄ ነገር? ቋንቋዎች ይመሳሰላሉ ነው ወይንስ አይመሳሰሉም ነው የምንለው? ምንድነው የምንናገረው? የሚል። ለማንኛውም እኔ ደስ ስላለኝ አንድ ደብተር አዘጋጀሁና ቁጭ ብዬ የግዕዙን ቃል እዚህ፣ የአማርኛውን እዚህ፣ የአረብኛውን ቃል እዚህ፣ የእብራይስጡን እዚህ፣ እያደረግኩ ዝም ብዬ እጽፋለሁ፤ ለራሴ ነው። እንዲህ ያለ ነገር መኖሩንም አላውቅም። ሰዎች አድርገውት ይሁን አይሁን አልጠየቅኩም። አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ያቺን ደብተሬን አያለሁ። እንግዲህ አስተማሪው እስኪመጣ ድረስ ደረጃው ላይ ሆነን ፀሐይ እንሞቃለን። ቁጭ ብዬ ሳለ አስተማሪዬ መጣ። ዶክተር ሙራድ ካሚል የሚባል ሰው ነው። “የፖርቱጋሎች ጀግንነት”ን አንብበኸው እንደሆነ እሱ ነው ወደ አማርኛ የተረጎመው። ኢትዮጵያም ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሆኖ ብዙ ጊዜ ሠርቷል።

(ማስታወሻ፣ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው መጽሐፍ በሚጉኤል ዲ- ካስታንሆዝ ተጽፎ በሙራድ ካሚልና በዮና ቦጋለ የተተረጎመና በአፄ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት ግራኝ መሐመድን ለመውጋት ከፖርቱጋል ስለመጡ 400 አርበኞች (ወታደሮች) የሚተርክ ነው። ዓለማየሁ)

/ር ሙራድ ምንድን ነበር የሚያስተምራችሁ?

የእብራይስጥ አስተማሪያችን ነበረ። እዚያ ቁጭ ብዬ መጣና “ምን ታደርጋለህ?” አለኝ። “ያው እስክትመጣ እንጠብቃለን” አልኩት። “ምንድነው የያዝከው?” አለና ደብተሬን ከእጄ ነጠቀኝ። “ምንድነው የምትሠራው?” ብሎ አየና “ኦው! ስለሴሚቲክ ቋንቋ ጥናት ፍላጎት አለህ እንዴ? እኔኮ እሱን ነው የተማርኩት። ፕሮፌሰር ሊትማን ቱቢንግን (Tübingen) አለ። እኔንም እሱ ነው ያስተማረኝ” አለኝ። “ይሄን ራሱን መማር ይቻላል?” አልኩት። “አዎ ይቻላል!” ከዚያ “በቃ ጥሪዬ ይሄ ነው!” አልኩ። ‘ይኼማ ለማዕረግስ፣ ሲሆን ከፍዬ የምማረው ነው። አለዚያ ደግሞ በተማሪነት የሚሆን ከሆነ እኔ እሱን ነው የምማረው፣ የሚቀጥለው እርምጃዬ እሱ ነው’ አልኩና በአእምሮዬ ወሰንኩ። በኋላ “World Council of Churches” (የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር) በየሃገሩ “Youth Camp” (የወጣቶች መሰባሰቢያ ማዕከል) አላቸው። ዓላማው ወጣቶች ከየሃገሩ መጥተው ሕብረተሰቡን እንዲረዱ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከየቦታው የሚመጡት ክርስቲያኖች እንዲተዋወቁ መርዳት ነው። ሳይ ጀርመን ሃገር አንድ ፕሮግራም አላቸው። ከዚያ ለማኅበሩ ‘እዚያ ባለው Youth Camp ውስጥ መሳተፍ እፈልጋለሁ’ ብዬ ጻፍኩላቸው። ሰጡኝ። እዚያ የኢትዮጵያ ጥናት መጻሕፍት የሚታተሙበት ዌስባደን (Wiesbaden) የሚባል ከተማ አለ- ሜይንስ ወንዙ ላይ። ሄድኩና አንድ ወር ይሁን እንደዚህ አሁን አላስታውሰውም፤ ቆየሁ። እዚያ እያለሁ ለጀማሪዎች የሚሆን የጀርመንኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ገዝቼ ነበር፣ እና ያን ይዤ ተመለስኩ።

ወዴት? ወደካይሮ?

ወደ ካይሮ መጣሁ።

ይቀጥላል

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top