ታዛ ወግ

እውነተኛ ፍቅረ-ሀገር የማንነት መገለጫ

በአንድ ወቅት- ጊዜውም ጥቂት ሰንበትበት ብሏል- አንድ ጸሐፊ “እናት እና አገር- የሁሉም ዘመን ምርጫ” በሚል ርዕስ ለገጸ-ንባብ ያበቁት ማለፊያ ጽሑፍ የአንዳንዶቻችንን ልብ የሚነካ ሆኖ መገኘቱን መንደርደሪያ ሳላደርግ ማለፉን አልፈቅደውም። “ምነው?” ቢባል በዚህን መሰል ርዕሰ ጉዳይ ብዕርና ወረቀት ተዛምዶ እምብዛም የተስተዋለበት ወቅት የቅርብ ትዝታ አይደለምና!

እንዲያውም ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለ አርበኛነት፣ ስለ ባንዲራና ስለ መሳሰለው ታሪክ ሲነሣ እጅግ አሳዛኝ ሊባል በሚበቃ መልኩ እኛ “ድንቅ” የምንለውን “አኩሪ ታሪክ” ብለንም የምንጠራውን ዘመኗ እንዳለቀባት “ድርሳነ ባልቴት” የሚቆጥሩ ዘመናዮች ዛሬ ዛሬ እየበረከቱ የታዩበት ጊዜ መሆኑን እናያለን። ይህ በእውኑም እጅግ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት ነው ብሎ መናገር አይቻልም።

ይልቁንም የዲቪ ታሪክ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ እየተወሳ፣ ሌት ተቀን እየተነሳ ተሰምቶ እንደማይጠገብ “ታላቅ ገድል” መነበብ ከጀመረ ውሎ ያደረበት ጊዜ መሆኑን ሲመለከቱት ለሰሚው ግራ ከመሆን በቀር ሌላ ስም ሊሰጠው የሚቻል አይደለም።

ቀደም ብዬ በማንደርደሪያነት የተጠቀምኩበት ጽሑፍ ውስጥ “ማነው ከጥላው መሸሽ የሚችል ጥላው አካሉን ይከተለዋል፣ ስለምን ቢባል አካሉ የጥላው መንሥኤ ነዋ! በወረቀት ላይ የእናትንም የሀገርንም ስም በሌላ በሌላ አማራጭ ስም መለወጥ ይችል ይሆናል፣ -ስያሜ ግን እውነቱን አይቀይረውም፣ -ስም ሳይሆን በተጨባጭ ያለው ሕልው የሆነው ነገር ነው ወሳኙ” ካሉ በኋላ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብርም ዥንጉርጉርነቱን… ይለውጥ ዘንድ ይቻለዋልን?” በማለት ጠይቀው “አይመስለኝም” ሲሉ ምላሹን በአስተሳሰብ አዘል ስሜታዊ ቃል ደምድመውታል።

ለነገሩ እንኳ ትሕትናን መርጠው ተገኙ እንጂ “አይቻለውም” ብለው በድፍረት ቋጭተው ቢተውትም ማንም ቅን ሰው የሚቃረናቸው ይኖራል የሚል ግምት ጨርሶ ሊኖረኝ አይበቃም።

ይሁንና አበው “አትሕቶ-ርዕስ” የሚሉት አገላለጽ ለሰው ልጅ ሁሉ ዘወትር የተገባው በመሆኑ በዚህም እኒያ ጸሐፊ ይሞገሱ እንደሆነ ነው እንጂ አይወቀሱም። ድሮ አቅራሪዎች፡- “ሰው በአገሩ ቢበላ ሣር ቢበላ መቅመቆ፡- ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ” ይሉ ነበር። የዛሬዎቹ እነ ኪኪ፣ እነ ፒፒ፣ እነ ጂጂ… ግን ይህንን የጀግንነት መቀስቀሻ ዜማ ሲያደምጡ “ሀገሬ! ሀገሬ! የፋራ ወሬ” ከማለት እና በአቅራሪው ከመሳለቅ ሌላ የሚሰጡት አንዳች ፋይዳ ያለው አስተያየት የለም ለማለት ያስደፍራል።

ሌላው ቀርቶ እኛ “ምራጭ” ከማንላቸው እነሱ ግን “ምርጥ” ከሚሏቸው እና በየመንደሩ ከሚያከራዩዋቸው የቪዲዮ ፊልሞች ውስጥ እንኳ እንዲያው አከራዩ ጥቂት ተሰቶት አንዱን በቅጡ ሳያውቀው ወይም በሚገባ ሳይመለከተው ቀርቶ “የሀገር ጉዳይ” ያለበትን ወይም እንደእምነቱ “ፈሪሃ መለኮት” የታከለበትን በካሴቶቹ እና ከሲዲዎቹ እክት ውስጥ ሰንቅሮ ቢያገኙት የቱን ያህል ያን መከረኛ አከራይ እንደሚዘልፉ በጆሮ የሰማን፣ በዓይን ያየን አልጠፋንም።

እስካሁን ድረስ ፋይል ተከፍቶ በችሎት መቅረቡን ገና አልደረስኩበትም እንጂ ምናልባት ያ የፊልም አከራይ ሰው ለምን እንዲህ እንዳደረገ እና ለምን “ለበደል” እንደተነሣሣ “ክብራቸው በመነካቱ” የሞራል ካሳ ለመጠየቅ ሳይዳዳቸው የሚቀር ነው አይባልም። ምናልባትም ሳይችሉ ቀርተው ይሆናል እንጂ!! የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚህ ርዕሰ-ነገር ላይ እየተደጋገመ ቢጻፍ ለማንበብ የሚሰለች “ቅን ሰው” ወይም “ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ” ይኖራል የሚል ግምት የለውም። እኔ በግሌ ሳያሠልስ ቢጻፍና ቢነበብ እኔም ባለችኝ እውቀት ጽፌ ባስነብብ የምጠግብ አይደለሁም። ልሆንም ከቶ የሚቻለኝ አይደለምና!

በዚህ ረገድ ስለ ሀገርም ሆነ ስለ ነፃነት አንዳንድ ቀደምት እውቅ ተጠባቢ የብዕር አለቆች ያሰፈሩትን ለመጥቀስ ቢሞከር መልካም ይመስለኛል።

ፊታውራሪ ተከለ ሐዋርያት ተ/ማርያም የዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ገደማ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ ከተናገሩት ረጅም ዲስኩር የሚከተለው ይገኝበታል፡-

“በማንኛውም ዓይነት መታለል ቢሆን ለሀገሩ ሳይመከት የሚፍረከረክና የሚገነጣጠል ሕዝብ በጣም ወራዳ ተብሎ ይናቃል። ከቶም ለማንም ቢሆን… እንደዚህ ያለው ሕዝብ ለትውልድ ባርነት፣ የዘለቀ በሽታን ይተክልበታል” ብለው ስለ ፍቅረ-ሀገር ከተናገሩ በኋላ የነፃነትን ትርጓሜ ሲያብራሩም “ነፃነት በባዕድ መንግሥት ወይም በሌላ “አቅኚ ነኝ” ባይ ገዢነት ሥር አለመሆንን ራስን በራስ የማስተዳደርና የመምራት ሥልጣን መብት” መሆኑን ካስረዱ በኋላ አንዳንዶች ግን ነፃነትን በሥርዓት አልብኝነት ሲተረጉሙ እንዳይታዪ ለመምከር ሲሉ እንዲህ የሚል አረፍተ- ነገር ያክሉበታል፡- “…ስለዚህ ነፃነት ተብሎ በከፍተኛ ሐሳብ በቅንም ልቦና አስተያየት የተፈቀደውን ነፃነት አንዳንድ ሰዎች ትርጓሜው ሳይገባቸው ቀርቶ እንዲሁ በመሰለኝ አካሄድ የተፈቀደላቸው መስሏቸው እንዳይታለሉ ሁላችንም በየበኩላችን ለየወገናችን ማስጠንቀቅ የተገባ ሥራችን ነው፣ ምንም ነፃነት ቢፈቀድ የመረንነት ፈቃድ እንዳልተሰጠ ሰው እንዲያውቅ ያስፈልጋል” በማለት በነፃነት ስም ድረ-ወጥነት፣ ጋጠ-ወጥነት፣ ስድነትና ውስልትና አንዳችም ቦታ እንደማያገኙ አስረግጠው ያሰመሩበት ሐሳብ አለ።

የእኚሁ የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በኩር ልጅ ዕውቁ ደራሲና ዲፕሎማት ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያትም “አርአያ” በተሰኘው ዝነኛው ልብ ወለድ ድርሰታቸው “አርአያ” የተባለው ገጸ-ባሕርይ ትምህርቱን በሀገረ-ፈረንሳይ ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በተጓዘበት ወቅት ጂቡቲ ሲደርስ እዚያው ባለ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ሄዶ ታሪኩን በመተንተን ከተናገረው ውስጥ እንዲህ የሚለው ይነበባል፡-

“…ያሳደገችኝ የፈረንሳይ ሴት ስለ ግል ኑሮዬ የሚበቃ ትዳር እንዳገኝና በደኅና እንድኖር ለእኔ በማሰብ በዚያው ባደግሁበት በፈረንሳይ ሀገር እንድቀርና ትዳርም እንድይዝ ተመኝታልኝ ነበር፣ …ነገር ግን እኔ ምንም እንኳ ለራሴ ኑሮ የሚበቃ ምቾት እንደማገኝ እና በመልካምም ለመኖር መቻሌን ባውቀው ከሁሉ አስቀድሜ ሀገሬን መርዳትና ያገኘሁትን ትምህርትና ዕውቀት ሁሉ ለእርሷ አገልግሎት ማድረግ እንደሚገባኝ ተሰምቶኝ በዚሁ መሠረት ወደዚህ ለመምጣት ቆረጥኩ፣…ለሰው ልጅ ክብሩና ጸጋው ሀገሩና ነፃነቱ ስለሆኑ በሰው አገር ሆነው ቢበለጽጉ የተስተካከለ ኑሮ ቢያገኙም አይሆነውም፣… ይልቁንም የገዛ ሀገር እያለው እንደ ሌላው መሆን፣ ወገኖችን መርዳት ሲቻል እንዳላዩ ሆኖ ለራስ ብቻ መኖር እጅግ የጠበበና በኋላም የሚያሳፍር አስተያየት ነው” ብሎ በመምጣት የወሰነበትን ምክንያት ከተናገረ በኋላ፣ “…አውቃለሁ ችግርና ዕንቅፋት ሳይኖር አይቀርም፣ ነገር ግን ፈቃዴን ብርቱ አድርጌዋለሁና ምንም ሊያሸንፈኝ የሚችል አይመስለኝም… እያለ በጋለና በአዲስ መንፈስ…” መናገሩን እና የቁርጠኝነቱን አኳኋን በጽኑዕ የሀገር ፍቅር ስሜት ማስገንዘቡን አሳምረው በመግለጽ ክፍለ-ምዕራፉን ከእልባት አድርሰውታል።

ሌላውንም አንጋፋ ታላቅ ሰው መጥቀስ ይቻላል። “…ሀገር አለሰው ምድረ-በዳ ሆና ትኖር ይሆናል፣… ሰው ግን አለሀገር ሊኖር አይችልም… የአንድ አገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቀው እና ለአንድነታችን መጠጊያ የሆነችውን እናታችንን ኢትዮጵያን ለማገልግል ለመኖርና ለመሥራት የምንችለው በአንድ መንፈስ ስንሰለፍ እና በንጹሕ ኅሊና ጸንተን ስንተባበር ብቻ ስለሆነ፣… ወደዚህም በቅንነት መራመድ ስለሚያሻ የአንዳንዶቻችን መንፈሰ ደካማነት ወደ ጽኑዕነት መለወጥ አለበት” ያሉት ደግሞ ጀኔራል ዐቢይ አበበ ናቸው። “አውቀን እንታረም” በተሰኘው ምክር-አዘል ድርሰታቸው ነበር በጽሑፋቸው ይህንን መሰል ቃለ-መቅደም አስፍረው ያስነበቡት። በነገራችን ላይ ሁለቱም ተዋቂ ዝነኛም የሆኑ ኢትዮጵያውያን፤ ማለትም ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት እና ሌተና ጄኔራል ዐቢይ አበበ እንዲህን የመሰለ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ንጹሐን ዜጎች ቢሆኑም ሁለቱም በዘመነ-ደርግ ብርቱ ሥቃይ የደረሰባቸው ሆነው ተገኝተዋል። ጄኔራል ዐቢይ አበበማ በቀደምት የርሸና ምዕራፍ በጥይት ከተደበደቡት ከ60ዎቹ የአፄ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት ውስጥ አንዱ ሆነው የተገኙ ነበሩ። እነርሱን ታሪክና የሰማዕታት ገድል እስከ ዘለዓለም ያስታውሳቸዋልና በዚሁ እንለፈው።

ጽሑፉን ከመደምደሚያ ለማድረስ አንዳንድ ነጥብ እናንሳ። ከፍ ሲል እንዳየነው ይህን ሁሉ ስናነብ የሀገርንና የወገንን ማንነት፣ ምንነት ለማወቅ ይሳነን ይሆን? በርግጥ “እንጀራ ሆነና ዋናው ቁም ነገሩ፣ አልቀመጥ አለ የሰው ልጅ በሀገሩ” ብለው አንድ ጸሐፊ በትዕምርተ-ጥቅስ ያስቀመጡት ስንኝ “ፈጽሞ ትርጉም የለውም” ተሰኝቶ የሚወድቅ ከትቶ ሊሆን አይገባውም። ያም ቢሆን ግን “የእንጀራ ጉዳይ” የተባለው በክብር እንደተጠበቀ ቆይቶ ራሱን የቻለ ሆኖ ሊቀመጥና ለዝክር ቢበቃ የሚቃወም እጅግም ያለ አይመስለኝም። “ሀገርን የሚያስረሳ ወይም ውሎ አድሮ ጭርሱን የሚያስከዳ ነው” ለማለት ግን ፈጽሞ የሚሞከር አይደለም።

እኔ በእውኑ ቀዳሚው ትውልድ በዚህ ረገድ በብዙ መልኩ አንደሚበልጠን አምናለሁ። ከእነዚያም አባቶች ብዙ መማር እንደሚገባን ጥቂት እንኳ መጠራጠር አይቻልም። በአሁኑ ጊዜ ግን “አሳፋሪ” ሊባል በሚበቃ ሁኔታ አንዳንዶች በጊዜያዊ ጥቅም እየተታለሉ፣ በአንዳንድ ሕይወትን ሊለወጥ በማይችል የዕለት ጉርስ እየተሸነገሉ ሀገርን ያህል ታላቅ ነገር፣ መተኪያም የማይገኝላትን “እናት” ለመለወጥ ወይም ለመሸጥ ደላላ ሲያፈላልጉ የሚገኙ አልጠፉም። ለዚህም አንዳንድ በቅርቡ በስመ-“ነፃነት” እርሱን እያስታከኩ የሚናገሩት እና በተግባርም ለማሳየት ዳር ዳር ሲውተረተሩ የሚታዩበት አድራጎት ዓይነተኛ ምስክር ሆኖ ሊቆጠር ይበቃል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ ሊሆን ከቶውን የሚገባው አይደለም። እውነተኛ ፍቅረ- ሀገር የማንነት መገለጫ ነው። ይህን ዘወትር ልብ ማለት ያሻል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top