ጣዕሞት

አርቲስት ሱራፌል ምን ሰርቶ አለፈ

ሙዚቃን በከፍተኛ ኪነት ውስጥ በታዳጊነት ዘመኑ የጀመረው አርቲስት ሱራፌል “ልጅ እያለሁ ለድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ልዩ ፍቅር ነበረኝ” ይላል። በቀበሌ ከፍተኛ ኪነት ቡድኖች በመጫወት ችሎታውን አዳብሮ በ1972 ዓ.ም. በተቀጠረበት ራስ ቲያትር ረዘም ላሉ ዓመታት በድምጻዊነት እና በተወዛዋዥነት አገልግሏል። በ1979 ዓ.ም. ከሮሃ ባንድ ጋር የሰራው “ታድለሻል” የተሰኘው አልበሙ ከቲያትር ቤት መድረክ በተጨማሪ ለህዝብ ጆሮ ያደረሰው የበኩር ሥራው ነው። በ1980 ዓ.ም. ደግሞ ከሌሎች ድምጻዊያን ጋር በጋራ ተጫውቷል። ከስራዎቹ መካከል “ሳዱላዬ፣ እንደኔ ነው ወይ፣ ይገርማል፣ የማር ወለላ” የተሰኙት ተጠቃሾች ናቸው።

አርቲስት ሱራፌል

አርቲስት ሱራፌል ከ1970 ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ፊቱን ወደ ግጥም እና ዜማ ድርሰቱ መልሷል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ደማቅ ስም ካላቸው እና ጉልህ አሻራቸውናን ካሳረፉት የዜማ እና ግጥም ደራሲዎች ማለትም አበበ መለሰ፣ አበበ ብርሃኔ፣ ሞገስ ተካ፣ ዘላለም መኩሪያ ጋር ተሰልፎ ዘመን የማይሽራቸው ስራዎቹን አበርክቷል። በብዙዎች ዘንድ እውቅና ያተረፈለት እና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በስራ ላይ የነበረው በሙዚቃ ድርሰት ሙያው ነው። ነጻነት መለሰ፣ ገረመው አሰፋ፣ ራሄል ዮሀንስ፣ ምናሉሽ ረታ፣ መሀሪ ደገፋው፣ ሻምበል በላይነህ፣ ትዕግስት ወይሶ፣ ሐመልማል አባተ፣… የግጥም እና ዜማ ድርሰቱን ከተጫወቱ ድምጻዊያን መካከል ይገኙበታል።

በሙያ አጋሮቹ አመለ ሸጋ መሆኑ የሚነገርለት አርቲስት ሱራፌል አብዛኛዎቹ የግጥም እና ዜማ ሥራዎቹ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተደማጭነት አግኝተውለታል። ከእነዚህ መካከል፡- ቴዎድሮስ ታደሰ “ጥፋተኛው ገላ”፣ ማርታ አሻጋሪ “ደማይ ደማይ”፣ ጸጋዬ እሸቱ “ተጓዥ ባይኔ ላይ”፣ ኩኩ ሰብስቤ “ዘንድሮ”፣ ሕብስት ጥሩነህ “እምዬን አደራ”፣ ዳዊት ጽጌ “የኔ የኔ” ተጠቃሾች ናቸው።

የድምጻዊ ብስራት ሱራፌል አባት የሆነው አርቲስት ሱራሴል አበበ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር አጋማሽ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የዝግጅት ክፍላችን ለአድናቂዎቹ እና ለቤተሰቦቹ መጽናናትን ይመኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top