አድባራተ ጥበብ

በኢትዮጵያ ገኖ በኢትዮጵያ የሞተው ባለሙያ

ዛሬ የማነሳላችሁ ባለሙያ ትውልዱ በኬኒያዋ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ ይሁን እንጅ ጥንተ-መሠረቱ ተገልጦ ሲፈተሸ ሥሩ ከወደ ህንድ ይመዘዛል። ወላጆቹ እ.ኤ.አ በ1927 ከሀገረ-ህንድ ጓዛቸውን ጠቅልለው ኑሮና እህል ውሃቸውን የአውሮፓ ቅኝ ግዛት አውሮፓዊ ባህልና ባህሪ ባረበበባት የምስራቅ አፍሪካዋቷ ኬንያ ለማድረግ ባህር ተሸግረው የመጡ ስደተኞች ናቸው። አባቱ ሳርዳር ሙሀመድ ይባላል። ከሞምባሳ እስከ ቪክቶሪያ ሃይቅ በሚዘረጋው የባቡር ሃዲድ ሠራተኛነት ተቀጥሮ በመሥራት የኬንያ ኑሮውን ‘ሀ’ ብሎ የጀመረ ህንዳዊ ፤ እናቱ አዝማት ቢቢ ሙሐመድ ትባላለች። የቤተሰቧን ኑሮ ለማቅናት ማጀቷን ወጥራ የምትለፋ የቤት ዕመቤት ናት።

የዛሬው ባለታካሪችንም የተገኘው ከእነዚህ ሙስሊም ህንዳውያን አብራክ ሲሆን የተወለደው ኦገስት 29 ቀን 1943 በኬንያዋ ርዕሰ ከተማ ናይሮቢ ነው። ገና “ጉልበቴ ጥና ጥና” እያለ ድክድክ በሚልበት የሰባት ዓመት ዕድሜው አባቱ ቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችውና ታንጋኒካ እየተባለች በምትጠራውና በዛሬዋ ታንዛኒያ ለተሸለ ህይወት ሲል በመረጠውና በለመደው የባቡር ሃዲድ ሥራ ላይ ለመሠማራት ከራሱ ጋር ዘጠኝ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ታንዛኒያ አመራ።

ስሙን ባስጠራባት ኢትዮጵያ ህይወቱ ያለፈው የዛሬ ባለታሪካችን ሙያዊ ስር የሚመዘዘውም በታንዛኒያ ዳሬሰላም ገና የ11 ዓመት ልጅ ሆኖ በገዛትና እጁ ላይ በገባችው Box Brownie እየተባለች በምትጠራው ጥንታዊቷ ቦክስ ካሜራ አማካኝነት ነው። የመጀመሪያው የሆነችውን ይህችን ካሜራ በመግዛት እጅና ዓይኑን አፍታትቶ ዓለም አቀፍ ዝናውን ወደቀደደለት ሙያ የተሰማራው ይህ ሰው ኋላ ላይ በብዙዎች ዘንድ ‘ሞ’ እየተባለ ተሞካሽቶ የሚጠራው ዕውቁ ኬኒያዊ ፎቶ ጆርናሊስት ሞሐመድ አሚን ነው።

ሞሐመድ አሚን

ሞሐመድ ፎቶ የማንሳት ጥበብን የተካነው ገና ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ ነበር። በትምህርት ቤቱ የፎቶግራፍ ክበብ አባል በመሆን ፎቶ ማንሳት ምን ማለት እንደሆነ ፤ ፎቶ በጨለማ ክፍል ውስጥ እንዴት እንደሚበለፅግና እንደሚታጠብ የተማረውም በዚያው ነው። ይህ የተማሪነት ዘመኑ ያስተማረውና ያለማመደው ፎቶ ማንሳትን ብቻ ሳይሆን የሚያነሳቸው ፎቶዎች እንዴት ዋጋ እንደሚያወጡና እንደሚሸጡ ጭምር ነበር። በዚህም በትምህርት ቤቱ የሚደረጉ ማኅበራዊ ክዋኔዎችን ተከታትሎ ፎቶ በማንሳት ከሚያገኘው ገቢ ከትምህርት ቤቱ ጋ እኩል ተካፋይ በመሆን የቢዝነስ ሀሁንም አብሮ ለመቅሰም ችሏል።

ሞሐመድ አሚን በልጅነቱ ያደረበትን የፎቶግራፍ ጥበብ በማሳደግ በ19 ዓመቱ ፎቶግራፍን የሙሉ ጊዜ ሥራውና ትጋቱ አድርጎ በመወሰድ በዳሬሰላም ዕምብርት የመጀሪያው የሆነውን CAMERAPICS ብሎ የሰየመውን ፎቶ ቤት በመክፈት ከትንሽ ወደ ትልቅ ፤ ከቀላል ወደ ውስብስቡ የሚወስደውን የሙያና የህይወት ጉዞ ‘ሀ’ ብሎ በመጀመር የቢዝነሱን ዓለም ማልዶ ተቀላቀለ።

CAMERAPICSም ከትንሽ የመንገድ ዳር ፎቶቤትነት ተነስታ ከሠሃራ በታች ባሉ 22 ሀገራት ውስጥ ሥር የሰደደውን ዓለም አቀፍ ካምፓኒ ጥንስስ ለመጣል አስቻለችው።

የሞሐመድ አሚን ስምና ዝና በአፍሪካ ሀገራትና በዓለም ላይ እንዲሰማ ያደረገው የመጀመሪያ አጋጣሚ የተፈጠረው እ.ኤ.አ. በ1965 ነበር። ይህ ወቅት በዛንዚባር ደሴቶች የሚኖሩ ዜጎች በተደጋጋሚ የሚያምፁበትና ለለውጥ የሚታገሉበት የተፋፋመ ወቅት ስለነበር ፤ ሞሃመድ አሚን በተደጋጋሚ በቀጥታም በድብቅም በትግል ወደሚናጡት ደሴቶቹ ሰርጎ በመግባት በዚያ ያለውን ሁኔታ ፎቶ በማንሳት ለዜና አውታሮች ለማቀበል ያለእረፍት ይተጋ ነበር። የሞሀመድ አሚን መሠረታዊ መርህ “አይሆንምን ማሸነፍ” የሚል ስለነበር ፤ አይሆንምና አይቻልም በሚባሉ ቦታዎች እየተገኜ የሚሠራቸው ፎቶ ዜናዎች ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጣቸው ነበሩ።

በዚያ ወቅት በዛንዚባር ባለስልጣኖች ዘንድ ኮሽ ባለ ቁጥር የመጓጓዣ መስመሮችን በተለይ የአየር ማረፊያዎችን መዝጋት የተለመደ ነበር። ይሀ ግን ሞሐመድ አሚንን ወደ ቦታው ከመሄድና ከመዘገብ የሚያቆመው አልነበረም። እየተሹለከለከ፣… በድብቅ እየገባ፣… የአደጋ ትንፋሽን በቀርበት እያዳመጠ፣… ምን እየተካሄደ እንዳለ ህዝቡን ጠጋ ብሎ እየጠየቀ ሥራውን በትጋት ያከናውናል። በዚህ ጥረቱም አንድ ወቅት ከሀገሬው ሰው ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ጠቃሚ መረጃ ይደርሰዋል። መረጃውም በዛንዚባር ደሴቶች ሶቭዬቶችና ምስራቅ ጀርመኖች በሚስጥር የሚከናወን የማሰልጠኛ ጣቢያ የከፈቱ መሆናቸውን የሚጠቁም ነበር። ይህ ፈጽሞ የማይገኝና ለማግኘትም የማይታሰብ ከፍተኛ ሚስጥራዊ መረጃ ነበር። በተለይም ወቅቱ የኩባ ሚሳይል ቀውስ የምስራቁና ምዕራቡ ዓለምን ከናጠ ገና ሦስት ዓመት እንኳን የሞላ ጊዜ ስላልሆነው ይህ መረጃ በክፉም ይሁን በደግ የ‘ሞ’ ን ታሪክ ሊቀይር የሚችል እጅግ ከፍ ያለ ወሳኝ መረጃ ነበር። ‘ሞ’ ተሳካለት። ሚስጥራዊ ፎቶግራፎቹ ድብቁን ሚስጥር ተሸክመው ሶቭየትኅብረትን ጨምሮ በመላው ዓለም ጋዜጦች የፊት ገፅ ላይ ታትመው ወጡ። የሞሐመድ አሚንም ስም ታሪክ ሊሆን በማይለቅ ቀለም አብሮ ታተመ።

የዛንዚባር ባለሥልጣኖች የዜናው ምንጭ እሱ መሆኑን ሲያውቁ አበዱ! ከነፉ!…. በንዴት ጦፉ። በገባበት ገብተው የእጁን ሊሰጡት ያለ የሌለ ቃፊራቸውን አሰማርተው አሰሱት። ፍለጋው በድብብቆሽ አላደከማቸውም። እሱም ምንም እንዳልተፈጠረ አስመስሎ እንደተለመደው ሥራውን ሠርቶ በአየር ሊሳፈር ወደ ደሴቷ የአየር ማረፊያ ሲጓዝ ያዙት። በአስቸጋሪና አስከፊነቱ ወደሚታወቀውና በደሴቷ ላይ ወደሚገኘው ኪሊማምጉ ወደተባለው እስር ቤት ወስደውም ወረወሩት። በእስር ጊዜውም የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለውን ድብደባና ዘግናኝ ምርመራ ሁሉ አካሄዱበት። ከ28 ቀናት ከባድ ቶርቸርና ስቃይ የተሞላበት ምርመራ ውስጥ ካለፈ በኋላ ዛንዚባርን ዞር ብሎ እንዳያይ ከሚያስገድድ ማስጠንቀቂያ ጋር ከእስር አውጥተው ወደ ትውልድ ሀገሩ ኬንያ ጠረዙት። ‘ሞ’ በወቅቱ ባለፈበት ሁኔታ ከመጎዳቱ የተነሳ በ28 ቀናት እስር 28 ፓዉንድ ወይም ወደ 13 ኪሎ ገደማ ያህል ቀንሶ ነበር።

ይህ ሁሉ ሲሆን ሞሃመድ አሚን ገና የ23 ዓመት ሎጋ ነበር።

ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ በዛንዚባር የደረሰበት ስቃይና መከራ ተስፋ ሳያስቆርጠው ፤ በአዲስ ጉልበትና ሃሳብ ተጠናክሮ በመነሳት ልጅነቱን የከፈለለትን የፎቶግራፍ ጥበብና የፎቶጆርናሊዝም ሙያውን ከፍ በማድረግ ከግብ ሊያደርስ ሌት ተቀን በመልፋት ሙያና ችሎታው ከሀገሩ አልፎ በመላው አፍሪካ በሚፈጠሩ አበይት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኹነቶች ላይ ቀድሞ በመገኘትና ዜናውን በፎቶና ፊልም አስደግፎ በመዘገብ ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን ለማትረፍ አስችሎታል።

‘ሞ’ በሀብትም ይሁን በቴክኒዮሎጅ የሚልቁት የአውሮፓና አሜሪካ የዜና አውታሮች የሚያሰማሯቸውን ፎቶሪፖርተሮች ቀድሞ በመገኜት በሚያነሳቸው ፎቶዎች ምስሎችና ፊልሞች ያገኜው ስኬት አላዘናጋውም። በውድድር የሚያምንና ቀድሞ ካልተገኜ በቀላሉ ከውድድር ሊወጣ እንደሚችል ቀድሞ በመረዳትና እንደ ቢቢሲ ያሉ በአቅምም በቴክኒዮሎጅም ከፍ ያሉ የዜና ተቋማት አሸንፈው ጥላ እንዳይሆኑበት በማሰብ በአንድ ጊዜ 6 ካሜራዎችን ገዝቶ ያለ እረፍት በመሥራት በተለይም በአንድ ጊዜ የፎቶ ካሜራንና ተንቀሳቃሽ ምስልን በመጠቀም በሁለቱም መንገዶች ፈጥኖ የመገኘት ብቃቱን በማሳደጉ ከተወዳዳሪዎቹ ቀድሞ እንዲገኝና ተፈላጊነቱም ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ሞ “አይሆንምን ማሸነፍ” በሚለው የሁሌውም መርሁ በመመራት ፤ ይጠቅመኛል ብሎ ካሰበ ለማንኳኳት የሚፈራው አንዳች በር አልነበረም። ጦርነትና ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ይስቡታል እንጅ አያስፈሩትም። አነፍንፎ ይሄድባቸዋል፣ አሳምሮ ይዘግባቸዋል። የማይደፈሩ የሚመስሉትንም አለዝቦ ይደፍራቸዋል።

በዚህም ስሙ በሩቅ የሚያስፈራውንና ዓለም በአምባገነንነቱና ጭካኔው አሳምሮ የሚያውቀውን የኡጋንዳ የዕድሜ ልክ ፕሬዝዳንት እጅግ የተከበሩ ፊልድ ማርሻል አልሃጅ ዶክተር ኢዲአሚን ዳዳ ጋር ቃለመጠይቅ ለማድረግ ለመጀመሪያ በደወለበት ጊዜ እንኳን ቀጠሮ አልተሰጠውም። ይልቁንም በዚያው ቅፅበት ዋናውን ሰው በስልክ እንዲያገኛቸው ነበር የተደረገው። ቆይቶም ‘ሞ’ የኢዲአሚን በር እንደቤተሰብ ባሻው ጊዜ የሚከፈትለት ብቸኛው የአምባገነኑ ፎቶግራፈር እስከመሆንም አድርሶታል። በጥረት የሠራው ስሙና ድፍረቱ የብዙዎችን በር ያለችግር አስከፍቶለታል።

ሞ የካሜራፒክስን አድማስ በማስፋት ከፎቶ ሪፖርተርነት ባሻገር በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ቀዳሚ የዶኪዩመንታሪ (ዘጋቢ) ፊልም አምራች በመሆን የታወቀ ኩባንያ እንዲሆን አስችሎታል። “ከሠላማዊ ኹነቶች ይልቅ የጦርነትና የስጋት ቦታዎች ይበልጥ ይመቹታል” የሚባልለት ሞሐመድ አሚን ችግር አነፍናፊ ፎቶጋዜጠኝነቱ እና የዘጋቢ ፊልሞች አዘጋጅነቱ የጎላ ነው።

ሞሐመድ አሚን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በላይ ጎረቤቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ይበልጥ ትስበዋለች። ኮሽ ባለ ቁጥርም ሮጦ በመምጣት ጉዳቷን ብስራቷን ቀድሞ ለዓለም ያደርስላታል።

የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ ሞ በቦታው ተገኝቶ የንጉሠነገሥቱን የመጨረሻ ምስሎች ለታሪክ አስቀምጧል።

ሞሐመድ አሚንን በዓለም እጅግ ከፍ ያለ የዝና ማማ ላይ እንዲወጣ ያደረገው ኹነትም የተፈጠረለት በኢትዮጵያ ነው። ዘመኑ በእኛ 1977 በፈረንጆቹ 1984 ዓ.ም. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሶሻሊስት አይዲዮሎጅ ምክንያት ከዓለም እርቀውና ተገልለው በነበሩበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ በዘመናቷ ሁሉ ካየቻቻው ታላላቅ የረሀብ ወቅቶች የሚደረበው አስቸጋሪ ፈተና ጋር የተፋጠጠችበት ወቅት ነበር። በአንድ በኩል በኤርትራ በሚካሄድ የተራዘመ አሰልች ጦርነት ፤ በሌላ በኩል በትግራይ ውስጥ ባቆጠቆጠውና ተ.ሀ.ህ.ት ወይም (ተጋድሎ ሃርነት ህዝብ ትግራይ) እየተባለ ከሚጠራው ቡድን ጋር የሚያደረገው ዕልህ አስጨራሽ ጦርነት ፤ ኢትዮጵያ የደረሰባትን መከራ ችላ እንዳትሸከም የሚያደረግ ታላቅ ፈተና ነበር። ድርቁ ከሰሜን ኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ተንሠራፍቶ ከሀገር አቅም በላይ ሆነ።

በዚህ ጊዜ ነበር በ1965 እንግሊዛዊው ጆናታን ዲምቢልቢ “ድብቁ ረሃብ” (The Unknown Famine) በተሰኘው ፊልም አማካኝነት እንዳደረገው ሁሉ በ1977ትም ችግር አፈንፋኙ ፎቶጆርናሊስት ሞሀመድ አሚን ረሀቡ ወደጠናባቸው የወሎ እና ትግራይ አካባቢዎች በመሄድ የቀረፃቸውን ዘግናኝ የሰው ልጆችን ረሃብና እልቂት የሚያሳዩ ምስሎች ለዓለም ገለጣቸው። በሶሻሊስትና ካፒታሊስት ርዕዮተዓለም እሰጥ- አገባ የተሸፈነው ድብቅ ረሃብ በሞሐመድ አሚን የካሜራ ሌንሶች ተገለጠ። ዓለም ባየው አሳዛኝ ምስል ዳር እስከ ዳር አነባ፣ ኢትዮጵያን የሚያውቅም የማያውቅም ልቡ ተነካ። ከየአቅጣጫው ምን እናድርግ የሚል የዓለም ህዝቦች ድምጽ ተሰማ። በዚህም እንግሊዛዊው አቀንቃኝ ቦብ ጊለዶፍ ከምድረ እንግሊዝ ቀዳሚነቱን በመያዝ በLive Aid ፕሮጀክት የዓለም ከያንያንን ሁሉ አስተባበረ። ዓለምም We are the world ብሎ በአንድነት ዘመረ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን የሚታደጉ እጆች ከየአቅጣጫው ተዘረጉ። ይህም በቀዳሚነት ዓለም The Kenyan who moved the world በሚል ቅፅል ያጀበው የደፋሩ ፎቶጋዜጠኛ የሞሐመድ አሚን ትጋት ውጤት ነበር። በዚህም ሞሐመድ አሚን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መዝገብ ውስጥ ስሙ በደማቅ ቀለም ተፃፈ። ሞ ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በርካታ ኹነቶችን ዘግቧል። እንደሁለተኛ ሀገሩም ተመላልሶባታል።

የዛሬ 29 ዓመት በግንቦት ወር ላይ ኢትዮጵያ ወደሌላ የታሪክ ምዕራፍ ስትሸጋገር ፤ ወታደራዊው መንግሥት ለ17 ዓመታት ከኖረበት መንበረ- ሥልጣኑ በአማፅያን በኃይል ተገፍቶ ከሥልጣን ሲወገድ ፤ ሞሐመድ አሚንን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባትና ወቅታዊውን ሁኔታ ለዓለም ለማሳዬት ጊዜ መጠበቅ አላስፈለገውም። አማጽያኑ ግንቦት 20ቀን 1983 ዓ.ም. ርዕሰ-መዲናዋን አዲስ አበባን በተቆጣጠሩ ልክ በሳምንታቸው ግንቦት 26 ለ27 አጥቢያ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ደቡባዊ ክፍል ሠማይና ምድር ባናወጠ ፍንዳታ ተናጠ። የፈነዳው በቅሎ ቤት ጎተራ የሚገኘው የጦር መሣሪያ ማከማቻ ዴፖ ነበርና ምድር ተጨነቀች።

አዕዋፍ ከየማደሪያቸው ወጥተው ሰማዩን በአክናፋቸው እየሰነጠቁ በሽሽት ሞሉት። የአዲስ አበባን ሰማይ በነጎድጓዳዊ መብረቅ በሚታገዝ የብርሃን ጎርፍ አጥለቀለቃት። ምድር ተናወጠች። ሰዎች መሮጫ መደበቂያ አጡ። እሪታና የጣር ድምጾች በረከቱ። የበረቱ እግራቸው እንደመራቸው ነፍሴ አውጭኝ ብለው ሸመጠጡ። በዚህ የቀውጢ ጊዜ ደግሞ በፍንዳታው አቅራቢያ ለህይወታቸው ሳይሳሱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለዓለም ለማዳረስ ሌንሳቸውን ከፍተው መቅረፀ ድምፃቸውን ደግነው በሥራ የተጠመዱ ጥቂት ባለሙያዎች ይታያሉ። እነዚያ ከአደጋው የቅርብ ርቀት በፍንዳታው ቃጠሎ ወጋገን የሚታዩት ባለሙያዎች በሞሃመድ አሚን የሚመሩ አራት የካሜራፒክስ ባልደረቦች ነበሩ። ሁሉም ራሱን ከማዳን አልፎ ዞር ብሎ ያያቸው ወይም ከአደጋው እንዲርቁ የነገራቸው ማንም አልነበረም። ከፍንዳታው ማህጸን እየተምዘገዘገ የሚወጣው የእሳት ላንቃ የደረሰበትን ሁሉ እያቃጠለ እያወደመና እየበላ ምድርን የቁም ሲኦል ባደረገበት ፍጥነተ-ሰዓት አንድ አቅጣጫው ያልታወቀ ተምዘግዛጊ የካሜራፒክስ ባልደረቦች አቅራቢያ ወደቀ። ከመቅጽበትም አካባቢው ከሌሎች የፍንዳታው ከባቢዎች ተመሣሰለ። ከሁኔታው የሚተርፍ ሰው ያለ አይመስልም። አደጋ ወዶ፣ አደጋ ደፍሮ፣ ከአደጋ ውሎ፣ ከአደጋ አድሮ፣ የሚኖረው ሞሀመድ አሚን በፍንዳታው ከነካሜራው ወደቀ። የድምጽ ቀረጻ ባለሙያው ጆን ማታይ በአደጋው ወዲያው ህይወቱ ሲያልፍ ሁለቱ ባልደረቦች ለወሬ ነጋሪ ይሆኑ ዘንድ ከአደጋው ለጥቂት አመለጡ። ሞሐመድ አሚንም ሰበብ ሆና ዓለም አቀፍ ዝና ባለበሰችው ሀገር ኢትዮጵያ በደረሰበት አደጋ ግራ አጁን ተነጠቀ።

ያም ሆኖ ሞሐመድ አሚን ኢትዮጵያንና ሙያውን እርም ይሁኑብኝ አላለም። ደጋግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል። የተቆረጠ እጁን በሰው ሰራሽ አካል አስተክቶ የሚወደውን ሙያውን ቀጥሏል። ሞሐመድ አሚንን ጨክኖ ከሥራው ያስቀረው አጋጣሚ የተፈጠረውም በዚችው በእኛዋ ሰበበኛ ሀገር ነው። በፈረንጆቹ ቆጠራ ኖቭምበር 23ቀን 1996 ወይንም በእኛ አቆጣጠር ህዳር 14 ቀን 1989 የበረረ ቁጥሩ 961 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦንግ B767 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ በሚያደርገው ጉዞ ከተሳፈሩት 175 መንገደኞች መካከል አንዱ ሞሐመድ አሚን ነበር።

አውሮፕላኑ ሀገር ሠላም ብሎ በሚበርበት ሰዓት ዕኩይ ዓላማ ባነገቡ ጠላፊዎች እገታ ሥር በመውደቁ ያልታሰበ ነገር ሁሉ ሆነ። ሦስቱ የአውሮፕላኑ ጠላፊዎች አውሮፕላኑን አስገድደው ወደ ሌላ ሀገር ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት በአሳዛኝ ሁኔታ ከመደምደሙ በፊት ሞሐመድ አሚን በድፍረት ከመቀመጫው ተነስቶ ጠላፊዎቹ ከድርጊታቸው እዲቆጠቡ ለማድረግ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጉ ተነግሮለታል። ሆኖም ልመናውና ማግባባቱ አልያዘለትም። የአውሮፕላኑ አብራሪ የነበሩት ካፒቴን ልዑል አባተ የጠላፊዎቹን ጥያቄ ለማሟላት የሚያስችል ነዳጅ አልነበራቸውም። ምርጫቸው አውሮፕላኑን በድንገተኛ የማሳረፊያ ስልት Emergency landing ጉዳቱን በመቀነስ ለማሳረፍ መሞከር ነበርና የአውሮፕላናቸውን አፍንጫ ወደ ኮሞሮስ አይላንድ በማድረግ ቁልቁል በመውረድ አውሮፕላኑ ምድር ሳይነካ በባህር ላይ ተበታተነ። በዚህም በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ከነበሩ 175 ሰዎች ውስጥ የ125 ሰዎች ህይወት አለፈ። ከእነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ገኖ በኢትዮጵያ ሰበብ ህይወቱ ያለፈው የኢትዮጵያ ጥብቅ ወዳጅ ሞሐመድ አሚን ወይም ሞ አንዱ ነበር። ሞሐመድ አሚን በህይወት ዘመኑ በጥልቅ ፍቅር ነዶ ካበረከታቸው ሙያዊ አስተዋፅኦዎች በተጨማሪ በርካታ መጻሕፍትን ለህትመት ያበቃ ሲሆን ከእነዚህም Journey to Pakistan እና Pilgrim to Mecca የሚባሉት ይጠቀሳሉ። ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያሳትመው “ሠላምታ” የተሰኜና ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ታዋቂ መጽሔት (Inflight Magazine) አሳታሚም የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ ሞሐመድ አሚን ነበር። ነፍስ ይማር!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top