አድባራተ ጥበብ

አሳምነው ገ/ወልድ የመጀመርያው ሕዝባዊ ጋዜጠኛ

የጋዜጠኞች ሙያና ተግባር ለገዥው መደብ ማሞገሻና ማወደሻ ብቻ በነበረበት አገር እና ዘመን ከዚህም በላይ የሕዘዊ ጋዜጠኝነት ባህል እና ልምድ ጨርሶ ባልነበረበት ኅብረተ-ሰብ ጥቂትም ቢሆን ሕዝባዊያን ጋዜጠኞች ነበሩ ብሎ መናገር እርስ በርሱ የሚቃረን ሊመስል ይችላል። ነገር ግን አንድ የማይካድ ዓለም አቀፋዊ የሕይወት እውነታ አለ። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ስግብግቦች፣ ሌቦች እና ቀጣፊዎች መካከል ጥቂቶች እንኳንስ ሊሰርቁ እና ሊያታልሉ የራሳቸውን ጥቅምም ሕይወታቸውን ጭምር ለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡ ሐቀኞች አሉ። በፍርሃትም ሆነ በጥቅም ለአንድ አምባገነን የፖለቲካ ሥርዓት ሰጥ ለጥ ብለው ከሚገዙት መካከል ያን ሥርዓት በአደባባይ በመቃወም ለፍትሀዊ ትግል አርአያ ሆነው ራሳቸውን የሚሰዉ ጥቂቶች ቢሆኑም አሉ። ይህ ባይሆን ኖሮ ፀረ-አምባገነን እና ፀረ-ጭቆና ትግሎች ጨርሰው በየትኛውም የዓለም ክፍል ባልታዩም ነበር። ኢትዮጵያም ከዚህ ዓለም አቀፋዊ እውነት ውጭ ልትሆን ባለመቻሏ የአምባገነኖችን ጨቋኝ እና መዝባሪ ሥርዓት የታገሉ እና ለዓላማቸው መሳካት ሕይወታቸውን ሳይቀር የሰዉ ልጆች እንደነበሯት እና ዛሬም እንዳሏት አሌ ሊባል የሚችል አይሆንም። አሳምነው ገ/ወልድ ናደው ከነዚህ ዓይነት ብርቅ ሰዎች አንዱ ነበር።

በተወለደ በ37 ዓመቱ በነሐሴ ወር 1965 ዓ.ም. ሲመኘውና ሲጓጓለት የነበረውን የፊውዳሉን ሥርዓት በ1966 ዓ.ም. መደምሰሱን ሳያይ ለሞተው ሕዝባዊ ጋዜጠኛ አሳምነው ገ/ወልድ የሙት ዓመት መታሰቢያ በወጣ ጽሑፍ በአንድ ስሙ ባልተገለጸ ወዳጁ የተዘጋጀ አንድ አስተያየት እንዲህ ይላል፣ “መወያየት መልካም” በሚል ፕሮግራም የተነሳ የሞት ድግስ እንደተዘጋጀለት ያውቅ ስለነበረ ሁኔታውን ሲገልጽልኝ ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄ ባቀርብለት “ዓላማዬን ለኢትዮጵያውያን ወገኖች ካበረከትኩ በኋላ ሞት ለኔ ሕይወት መሆኑን ስለማምንበት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ቀን ያለቅስልኛል” በማለት የነገረኝን ሳስታውስ ህሊናዬ በሀዘን እየተነካ ነው። ከቃሉም እንደተረዳሁት በእውነትም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ እንደ ጎርፍ ወረደለት። ከልብ በመነጨ ሀዘን አለቀሰለት። ይህንንም በሥርዓተ-ቀብሩ በመገኘት በዐይኔ ለማየት ቻልኩ” ይላል ያ ጽሑፍ።

አሳምነው ገ/ወልድ ለዕውነት እና ለፍትሕ የቆመ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሕይወት መሻሻል፣ ለአገር ደህንነት እና ዕድገት ተቆርቋሪ ነበር። ግፍንና ጭቆናን በጽናት የሚቃወም እና በዛ የሀሳብ ነጻነት መግለጽ በማይቻልበት ‘ፊውዶ ሞናርኪ’ ሥርዓት በቻለው መንገድ ሁሉ የሚታገል ስለነበር በወቅቱ ዓላማውን በሚጋሩና በሚደግፉ ሙህራንና ተማሪዎች ከዚያም አልፎ በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅ ጋዜጠኛ እንደነበር ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ። ስለሆነም ከላይ የተጠቀሰው ስሙ ያልተገለጸው ወዳጁ የሰጠው የምስክርነት ቃል ባብዛኛው በዚያ ዘመን በነበረው ሕዝብ ዘንድ የሚጉላላ ሀሳብ ሆኖ እስከዛሬ ይገኛል። ስለ አሳምነው ይባል የነበረውን እኔ እንዲህ ተባለ እያልኩ ከምጠቃቅስ ይልቅ አስተያየት ሰጪዎቹ ራሳቸው ካሉት ጥቂቶቹን እንደወረደ ማቅረቡ ይሻላል።

ከ53 ዓመት በፊት አንዲት እታፈራሁ ታደሰ የተባለች ተማሪ ኅዳር 6 ቀን 1957 ዓ.ም. ለአቶ አሳምነው እንዲህ ስትል ጽፋ ነበር፣ “የተከበሩ አቶ አሳምነው እኔ አንዲት ተማሪ መሳይ ነኝ። በፕሮግራሞችዎ በጣም ስለምደሰት ይህንኑ እንዲያውቁልኝ ስለምፈልግ ይህችን ደብዳቤ ጽፌልዎታለሁ። በፕሮግራሞቹዎ የሚደሰቱ ብዙዎች እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ። እኔ ግን በተለይ “መወያየት መልካም” የሚለውን ፕሮግራም በጣም እወደዋለሁ። እደሰትበታለሁም። የሚጠይየቋቸው ጥያቄዎች በሙሉ የአዲስ አበባ ሰው ግማሹ ሊጠይቅ የሚፈልገው ነው ብዬ አምናለሁ። የፕሮግራሙ ዓላማ ደግሞ በጣም ጥሩ ነው። መቸም ፕሮግራሙ በሆነ ወይም ባልሆነ ምክንያት ቢለወጥ የሚያዝኑት ብዙዎች ናቸው።” አክባሪዎ እታፈራሁ ታደሰ

“መወያየት መልካም” የተባለው የሬድዮ ፕሮግራም እንዲቋረጥ ተደርጎ አቶ አሳምነው ከሬድዮው ሥራው ተነሳ። አሳምነው ገ/ወልድ በሕዝብ ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅ የሬድዮ ጋዜጠኛ እንደነበረ የታፈራሁ ትሁት ደብዳቤ ከብዙዎቹ ምስክርነቶች አንዱ ነው። ‘ፊውዳሎች’ እና አምባገነኖች በሚመሩት ሥርዓት በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ መሆን በሥርዓቱ የሚያስጠላ እና የሚያስጠምድ ለመሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ስለሆነም እታፈራሁ ታደሰ የፈራችው ነገር አልቀረም።

አቶ አሳምነው በጊዜው የሀረር ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ የነበሩት ሌፍትናንት ጀነራል ከበደ ገብሬ ቀደም ብለው ለጻፉለት የግል ደብዳቤ ኅዳር 1 ቀን 1959 ዓ.ም. በጻፈው መልስ፣ “…ለብሔራዊ ችግራችን መወገድ ያደረግሁት ትግል እንደ ኃጢአት ተቆጥሮ የውይይቱ ፕሮግራም እንዲቋረጥ፣ እኔም በሬድዮ እንዳልናገር በአለቆች በመወሰኑ አሁን ደግሞ አገልግሎቴን በጽሑፍ ሳልቀጥል አልቀረም” ይላል። ስለዚህ ፕሮግራሙ የተጀመረበትንና የተቋረጠበት ቀኖች እዚህ ላይ በትክክል መጥቀስ ባይቻልም ከኅዳር 1 ቀን 1959 ዓ.ም. በፊት እንዲቋረጥ መደረጉን ከራሱ ከአሳምነው ደብዳቤ እንረዳለን።

ከእታፈራሁ ደብዳቤ የምንረዳቸው አንዳንድ ቁምነገሮችና የሚያስደንቁ ነገሮች አሉ። አንደኛ “እኔ አንዲት ተማሪ መሳይ ነኝ” የሚለው አነጋገር በዘመኑ የነበረውን ሌሎችን የማክበርና ራስን ለፍጹም ትህትና የማስገዛት መልካም ባህርይ ያንጸባርቃል። ከዚያም አልፋ እታፈራሁ ራሷ “መወያየት መልካም” የተባለውን ፕሮግራም የምትወደው ከመሆኑም በላይ የሚወዱትም ሌሎች ብዙዎች እንዳሉ ጥያቄዎቹም የአብዛኛውን ሕዝብ አስተያየት የሚወክሉ እንደሆኑና ፕሮግራሙ ቢቋረጥ ግን የሚያዝኑ ብዙዎች እንደሚሆኑ በሚገባ ትመሰክራለች።

ለአቶ አሳምነው ይጻፉለት የነበሩት ደብዳቤዎች የተለያዩ ዕድሜን፣ ጾታን፣ ሥራንና የጉዳዮችን ትኩረት የሚያንጸባርቁ ነበሩ። የሚላኩትን በወቅቱ ይታወቅ እንደነበረው በዚያ ዘመን አጠራር ከተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ስለነበር የማናቸውንም ኢትዮጵያዊ ብሔር፣ ብሔረ-ሰብ አመለካከት የሚያንጸባርቁ ቢሆንም የጥያቄዎቹ ኢላማም ሆነ መንፈስ ግን በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አመለካከት ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ግልጽ ነው።

አንድ “አበራ ወልዴ የተባልኩ ነባር ወታደር ነኝ” የሚል የጦር ሠራዊት አባል “በራሴ እና በሥራ ባልደረቦቼ ስም ይህችን ደብዳቤ ጽፌልዎታለሁ።” ሲል በጻፈው ደብዳቤ፤ “በኦጋዴን አምበሳ ጦር ሠራዊት ዘንድ በአማርኛ ፕሮግራም አቀራረብ ወይንም አነጋገርዎ ከፍ ያለ ዝናና ሞገስን ላተረፉት አሳምነው ገ/ወልድ ይህችን ደብዳቤ የጻፍንልዎ በኦጋዴን ጠረፍ ለአገር ፍቅር እና ክብር ስንል ጠረፍን በማስከበር የምንገኝ ወገኖችዎ በራድዮ ዜናን ሲያቀርቡ በኦጋዴን ጠረፍ የተሰማራው ሠራዊት ምን ያህል በታላቅ ፍቅር እና አድናቆት እንደሚያዳምጥዎት ለመግለጽ ነው። “ዜናውን የሚያሰማችሁ አሳምነው ገ/ወልድ ሲባል በአንድ ራድዮን ለማዳመጥ የሚሰበሰበው የሰራዊቱ ቁጥር ከ60 እስከ 70 ይደርሳል።” ይላል።

ሌላው በላይ ካሳሁን የተባለው የአሳምነው አድናቂ ከአጋሮ ከፋ ጠቅላይ ግዛት (በወቅቱ አጠራር) በ13/2/1958 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ “በጣቢያው በኩል ከሚተላለፉት ሁሉ አብልጬ የምከታተለው የርስዎ ፕሮግራም ስለሆነ በተለይም እንደተዳፈነ እሳት በልቤ ውስጥ አምቄ የያዝኩዋቸውን ነገሮች በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ፍርጥርጥ ብለው በይፋ ስለሚገለጹ ደስታዬ የበዛ ነው።” ብሏል።

አንድ ተወዳጅ የሕዝብ መሪ ወይም አርቲስት በሕዝብ መካከል ሲገኝ ሊጨብጡት እና ሊነኩት የሚፈልጉ ሰዎች እጅግ ብዙ እንደሚሆኑ ሁሉ አሳምነውን በአካል አግኝቶ ለማየት፣ ለመተዋወቅ እና ለማነጋገር የሚፈልጉ ብዙ ነበሩ። እንደ ቅርብ ጓደኛው ይህንን ዕውነት ብዙ ጊዜ እኔም ታዝቤአለሁ።

በባህርዳር ከተማ የፖሊስ ሠራዊት አባል የነበረው ወታደር ካሳሁን አልማው በ11/1/1959 ዓ.ም. የጻፈው ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ይላል። “በሬድዮ ድምጽዎን ስሰማ በጣም ደስ ይለኛል። ስለዚህ መልክዎን ባለማወቄ ቅር ሲለኝ ይኖራል። አሁን የክቡርነትዎን መልካም ፈቃድ ሆኖልኝ አንድ መታሰቢያ ፎቶዎን እንዲልኩልኝ በትህትና እለምናለሁ።”

የአሳምነው አድናቂዎች አብዛኛዎቹ ስለ ፕሮግራሙ ያላቸውን ፍቅር ሲገልፁ ሌሎች ደግሞ መነሳት ያለባቸውን የሕዝብ ጥያቄዎችን እንዲያቀርብላቸው የሚማጸኑ ነበሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ ችግር ሲደርስባቸው፣ የህይወት ውጣ ውረድ እንቆቁልሽ ናላቸውን ሲያዞራቸው፣… እንዲመክራቸውና ከዚያም አልፎ እንዲረዳቸው የሚማጸኑት ነበሩ።

ሴተኛ አዳሪነት እየተስፋፋ ወጣቱን ትውልድ ሲበክለው ለጋብቻ፣ ለጤና፣ ለቤተሰብ ምስረታ፣… ጠንቅ እየሆነ ሲሄድ መንግሥት እንዴት ዝምብሎ ያያል? በፋብሪካ ፈንታ መጠጥ ቤቶች ሲስፋፉ፣ ስራፈት ሲበዛ፣… ባለሥልጣኖቻችን እንዴት “ጆሮ ዳባ ልበስ” ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ “የሚመለከታቸውን ለምን አታነጋግርልንም” ብሎ አንደኛው ሲጽፍ ሌላኛው ደግሞ የአሜሪካን ፊልድ ሰርቪስ የሚባለው ፕሮግራም ወጣቶቻችንን ባህላቸውን እና የኑሮ ዘይቤአቸውን እንዲረሱ፣ የአሜሪካን የኮካኮላንና የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኝነት ባህል እንዲላበሱ፣… እያደረገ ነው። ስለዚህ ለነኝህ ወጣቶችና በጠቅላላውም ለኅብረተ-ሰባችን ምክር ስጥልን” ሲል ይማጸናል። አንዳንዱ ደግሞ የግሉን ችግር በማስቀደም “ሕይወቴን እንዴት እንደምመራው ምከረኝ፤ ስላላገባሁ እንዴት ወደ ጋብቻ እንደምሸጋገር አስተምረኝ። መሥሪያ ቤታችን የደሞዝ ጭማሬ ለትጉኃን ሠራተኞች አያደርግምና እስቲ አስታውስልን” ሲል ሌላው ደግሞ በነፃ ትምህርት አሰጣጥ (ስኮላርሺፕ) አድልዎ እየተፈፀመ ነው። የወረዳ እና የአውራጃ ገዥዎች በአንድ ቦታ ከ20 እስከ 25 ዓመት በመቆየት ህዝቡን በጉቦ ይገፉታል። መሬቱን በየምክንያቱ ይቀሙታል። ምርጥ ምርጡን የከተማ ቦታ በምሪት ስም እየተሻሙ ዛኒጋባ በመስራት እና በማከራየት ሕዝቡን ይመዘብራሉ የሚሉ ጥቆማዎች ይልኩ ነበር።

ለአሳምነው ከሕዝብ ይላኩለት የነበሩትን የአድናቆትም ሆነ የጥቆማ ደብዳቤዎች ይዘትም ሆነ አጠቃላይ መንፈስ በዚች አነስተኛ ጽሑፍ እንዳለ ማቅረብ አይቻልም። ከላይ የተጠቃቀሱት አሳምነውን ሕዝቡ ምን ያህል ያፈቅረው፣ ያደንቀው እና ያምነው እንደነበረ በመጠኑም ቢሆን ሊፈነጥቁ ይችሉ ይሆናል በሚል እምነት ነው።

ሌላው ስለ አሳምነው ገ/ወልድ ስናነሳ የሚያስገርመው ነገር የዚያ አንደበተ-ርቱዕና ብልህ ጋዜጠኛ ተወዳጅነት በተራው ህዝብ ብቻም አልነበረም። ከዘመኑ ትልልቅ ባለ ሥልጣኖች መካከል አንዳንዶቹ ምናልባት ደብቀው ይወዱት እና ያከብሩት ነበር ማለት ይቻላል። ከሕግ እስረኞች እስከ ሥራ አጥ ተማሪዎች፣ ከኢንዱስትሪ ወዝ- አደሮች እስከ መንግሥት ሠራተኞች፣ ከጦር ኃይል አባሎች እስከ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ ከተራ ተማሪዎች እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ባለ ሥልጣኖች ለአሳምነው የአድናቆት ጽሑፎች እና የውይይት ግብዣ የሚያበረክቱ ደብዳቤዎች ይልኩለት ነበር። በተለይ አንዳንድ ሰዎች የማይገባ ፍርድ ተሰጠ፣ ግፍ ተፈጸመብን፣ አድልዎ ተደረገብን፣… በማለት እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ ድረስ አቤቱታዎች ሲጽፉ ግልባጭ ለአቶ አሳምነው ገ/ወልድ ይደረግ እንደነበር ስለዚህ ታዋቂና ተወዳጅ የሕዝብ ሰው ቤተ-ሰቦቹ ያጠናቀሩት የሰነዶች ስብስብ ያስረዳል። ለምሳሌ መጋቢት 28 ቀን 1958 ዓ.ም. 3,500 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወኽኒ ቤት እስረኞች፣ የወኽኒ ቤቱ አስተዳደር የአመክሮ አንቀጽን በሥራ ላይ አያውልም። በአመክሮ መለቀቅ ሲገባን ጉዳዩን የሚመለከቱትን የሕግ አንቀጾች በመተው በእስር ያቆዩናል፣ በአመክሮ ልንለቀቅ ሲገባን ያለ ሕግ በእስር ያቆየናል። አንድ ጊዜ እስረኞች የወኽኒ ቤቱ አስተዳደር ከተወሰነው ጊዜ በላይ በእስር ስላቆየን ኪሣራ እንዲከፍለን ብለው በመጠየቅ ለክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሉሊሉ ሀብተወልድ አራት ገጽ አቤቱታ ሲያቀርቡ ለአቶ አሳምነው ገ/ወልድ ግልባጭ አድርገው እንደነበር ከሰነዱ መረዳት ይቻላል።

ሌላ አንድ ግብር ከፋይ ነኝ የሚሉ በኅዳር ወር 1958 ዓ.ም. ለገንዘብ ሚንስቴር የመሬት ገቢ ዲሬክሲዮን በጻፉት ደብዳቤ የመሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣኖች በመወያየት መልካም ፕሮግራም ላይ ስለ መሬት ግብር አከፋፈል ሥርዓት እና ተግባር የተሰጠው መልስ ትክክል አይደለም ሲሉ የጻፉ ሰው ግብርን ሊከፍል የሚገባው ባለ ርስቱ ሲሆን በባርነት የሚያርሰውን ድሀ ገበሬ ግብር ክፈል በማለት ጭቃ ሹሞች እና ዝቅተኛ የመንግሥት ሹማምንት በድሀው ገበሬ ላይ የሚያደርሱት ግፍና ጭቆና አሳዛኝ መሆኑን ለመጠቆም በጻፉት ማመልከቻ ላይ ግልባጭ ለአቶ አሳምነው እንዳደረጉለት ይታወቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሦስት በጅሮንዶች ጋር ኅዳር 10 ቀን 1958 ዓ.ም. ምሽት በተደረገ የ“መወያየት መልካም” ፕሮግራም ስለ መሬት ግብር አከፋፈል የተሰጠው መልስ ከዕውነት የራቀ ነው ሲሉ ግራዝማች አብዱላሂ ገልሞ የተባሉ ሰው ኅዳር 13 ቀን 1958 ዓ.ም. ለአቶ አሳምነው ገ/ወልድ ሲጽፉ ግልባጭ ለክቡር የሐረር ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ማድረጋቸው ተመዝግቧል።

ሌሎች ለአሳምነው ይደርሱት የነበሩት ደብዳቤዎች ደግሞ ወይ በውይይት እንዲካፈል አለዚያም ውይይቶችን በሊቀ-መንበርነት እንዲመራ እንደ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ እንደ ኃይማኖተ-አበው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር እንደ ዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት፣ እንደ ምስራቅ አዲስ አበባ መንፈሳዊ ድርጅቶች፣ እንደ ኮከበ-ጽባህ የቀ.ኃ.ሥ ትምህርት ቤት፣ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ የመምህራን ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት፣ እንደ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት፣ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ያሉት የትምህርት ተቋማት ይጽፏቸው የነበሩት ደብዳቤዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚባለው የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክረምት ወራት እረፍት ጊዜያቸው ጊዚያዊ ሥራ እንዲያገኙ ላደረገው አስተዋጽኦ የተጻፈለት የምስጋና ደብዳቤም በጋዜጠኛው የሕይወት ታሪክ ማህደር ተመዝግቦ ይገኛል።

ከግለሰቦች፣ ከቡድኖች፣ ከትምህርት ተቋሞች፣ ከኢንዱስትሪ ወዛደሮች እና ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች፣ ከጦር ኃይል እና ከፖሊስ ሠራዊት ባልደረቦች እና መኮንኖች ለአሳምነው ገ/ወልድ የፕሮግራሙን ይዘት በማድነቅ የውይይት ርዕሶችን በመጠቆም፣ በቡድንም ሆነ በተናጠል ለሚደርሱት ችግሮች እርዳታውንና ምክሩን እንዲለግስ በመጠየቅ እንዲሁም በልዩ ልዩ ውይይቶች እንዲካፈልና ውይይቶችንም በሊቀ-መንበርነት እንዲመራ የሚጠይቁት ደብዳቤዎች ሁሉ ዓላማቸው የተለያየ ይሁን እንጂ ያለ ጥርጥር የሚያረጋግጡት አንድ ዐቢይ ጉዳይ ነው። ይኸውም በተለይ ከነኝህ ልዩ ልዩ የኅብረተ-ሰቡ ወገኖች ባጠቃላይም በአሳምነው ገ/ወልድ ሀቀኛነት እና ህዝባዊነት ከፍተኛ እምነት የነበራቸው መሆኑን ነው። ስለዚህም ነው ይህ ጸሐፊ ይህችን አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ ጽሑፍ አሳምነው ገ/ወልድ “የመጀመርያው ሕዝባዊ ጋዜጠኛ” የሚል ርዕስ በድፍረት ሊሰጣት የቻለው።

በአንድ ሥራ አጋጣሚ ይህ ጸሐፊ ከአንዲት ወጣት የሬድዮ ጋዜጠኛ ጋር ተገናኘና ሲተዋወቅ ስለ አሳምነው ገ/ወልድ ምን ታውቂያለሽ ሲል ጠየቃት። መልሷ የማታዳግምና የማታጠራጥር አጭር ቃል ነበረች። “አላውቅም” አለች። “የኛ ትውልድ ስለ እንግሊዝ ሥነ-ጽሑፍ (ሊትሬቸር) ስንማር ስለ ዊልያም ሼክስፒር ወላጆች፣ ስላስተዳደጉ፣ ስለ ትምህርት ጊዜው፣ ስለ ፈጠራ ሥራዎቹ እና ስለ ግላዊ ሕይወቱ ሳይቀር ለማወቅ ያገኘነውን ጽሑፍ ሁሉ በሽሚያ እናነብ ነበር።” ቻርለስ ዲከንስ ስለተባለውም የእንግሊዝ ደራሲ ለማወቅ የነበረን ጉጉት እንደዚሁ ነበር። ስለሆነም መሐንዲሱም አርኪተክቱም፣ ኤኮኖሚስቱም ሆኑ የህክምና ባለሙያዎች በየሙያቸው ስለሚታወቁ አበይት ምሁራንና ስመጥር አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች በብዛት ያነባሉ፣ ያውቃሉ። ታዲያ ዛሬ ጋዜጠኛ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ወጣት ሌላ ቢቀር ለኢትዮጵያ ጋዜጠኛነት ታሪክ በዚህ ሙያ ውስጥ ስላለፉ እንደነ አሳምነው ገ/ወልድ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አሐዱ ሳቡሬ፣ ነጋሽ ገ/ማርያም፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ሮማንወርቅ ካሳሁን፣ ተስፋዬ ካብትህ ይመር፣ ተገኝ የተሻወርቅ፣ ያዕቆብ ወልደማርያም ወዘተ… ያሉት ስመጥር ጋዜጠኞች ታሪክ ተግባር ካላወቀ፣ ሥራዎቻቸውንም ሆነ ስለነሱ የተጻፉትን ጽሑፎች ካላነበበ፣ የጋዜጠኝነት ሙያው እንዴት የተሟላ ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ መነሳት የነበረበት ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ ነበር። በአንድ በኩል በጋዜጠኛነት ሙያ የሚሰማሩት ወጣቶች ይህን እንዲያውቁ ማድረግ የነበረባቸው አጋጣሚውንና ዕድሉን ቢያገኙ ኖሮ ሌላ ቢቀር ከሙያውም ሆነ በነበራቸው ሰፊ ልምድ የበለጸጉት አዛውንት ጋዜጠኞች የሙያው ተቋሚ አጣቃሽ ሰዎች መሆናቸውን ይገነዘቡ ነበር። አንዳንዶቹ እድሉንም አግኝተው ይህንን ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ይሆናል። ከወቀሳ አይድኑም። ሌላው ለዚህ ተጠያቂ የሀገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ምሁራን ባለሙያዎች ናቸው። የሙያው መምሕራን ስላለፉት ትላልቅ ጋዜጠኞች በሙያ መስካቸው እንዲታወሱ፣ ያደረጓቸውም አስተዋጽኦዎች እንዲታወቁ እና በሚገባ በጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርጉት ጥረት የሚያበረታታ ነው ወይ? የዚህ ጸሐፊ መልስ ከላይ እንደጠቀሰችው ወጣት ጋዜጠኛ ባጭሩ “አይደለም” የሚል ነው።

በዚህ በልዩ ልዩ የኪነት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን የህይወት ታሪክና ሥራ ለማስተዋወቅ ሙከራ ባደረገው “ኅብረ-ጥበብ” በተባለው መጽሔት የመጀመርያው እትም ስለ አሳምነው ገ/ወልድ ለመጻፍ የተሞከረው ቀደም ብሎ በተጠቀሰው ምክንያት ነው። መላው የወጣት ኅብረተ-ሰብና በተለይም በጋዜጠኝነት ሙያ የሚመረቁ በሥራው የተሰማሩ ወጣቶች ለምሳሌ ስለ አሀዱ ሳቡሬ፣ ስለ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ስለ ነጋሽ ገ/ማርያም፣ ስለ አሳምነው ገ/ወልድ ምን ያውቃሉ?

አሳምነው ገ/ወልድ ጢቾ ከተማ እንደ ቀድሞው አጠራር አርሲ ክ/ሀገር የካቲት 29 ቀን 1928 ዓ.ም. ተወለደ። አባቱ በመንግሥት ሥራና በኋላም በጥብቅና ይተዳደሩ የነበሩ አቶ ገ/ወልድ ናደው የተባሉ በአከባቢያቸው የተከበሩ የቤተ- ክህነት ምሁር ሰው ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ጀማነሽ ደምሴ የሚባሉ ይህ ጽሑፍ ሲዘጋጅ ከ80 ዓመት በላይ የዕድሜ ባለፀጋ የነበሩት አዛውንት ናቸው። ከሦስት ወንዶች እና ከሁለት ሴቶች ቤተ-ሰብ ውስጥ አንዱ የሆነው አሳምነው ገ/ ወልድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አሰላ ከተማ በሚገኘው በራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በ22 ዓመቱ በ1940 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ድሮ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ይባል በነበረው ተቀጠረ። አሳምነው ለትምህርት ከፍተኛ ፍቅርና ጉጉት ቢኖረውም ከርሱ ይልቅ ትንንሽ ወንድሞቹንና እህቶቹ ከፍተኛ ዕውቀት ይበልጥ እንዲቀስሙና እንዲማሩ ይመኝ ስለነበር እና ታናናሾቹ እህቶቹንና ወንድሞቹን ከአሰላ ከፍ ባሉ ከተሞች ተቀብሎ ሊያስተምርና ሊረዳ የሚችል የቤተ-ሰብ አባል ባለመኖሩ እርሱ ሥራ ይዞ እነርሱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ ኃላፊነቱን እንደ ግዴታ አድርጎ ነበር የተቀበለው።

ሥራን ማግኘት በሚመለከት ማስታወቂያ ሚንስቴር እንዲገባ የገፋፉት አንዳንድ ምክንያቶች ነበሩ። መጀመርያ ለአጭር ጊዜ በሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት አጠገብ ይገኝ በነበረ ያገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤት ቢቀጠርም በነበረው የሥነ- ጽሑፍ ዝንባሌ ብዙ ጊዜ በልጅነቱ የተካፈለባቸው የትምህርት ቤት ቴአትሮች ባሳደሩበት ተጽዕኖ በተፈጥሮም በነበረው የአማርኛ ቋንቋ ችሎታና አንደበተ-ርቱዕነት ሳቢያ ካገር ውስጥ ገቢ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ለመሸጋገር ጊዜ አልፈጀበትም። በማስታወቂያ ሚኒስቴር ከመቀጠሩም በፊት በጋዜጦች ላይ አስተያየቶችን ይጽፍ ስለነበር የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ለሱ እሱም ለመስሪያ ቤቱ ባይተዋር አልነበሩም። ስለሆነም መጀመርያ በኢትዮጵያ ራድዮ አድማጭ ዘንድ በዜና አንባቢነት፤ ቀጥሎም “መወያየት መልካም” የተባለውን ፕሮግራም በማቀድና በማዘጋጀት በመላው አገሪቱ ሬድዮ አድማጭ ዘንድ ተወዳጅና ተናፋቂ የራድዮ ጋዜጠኛ ሆነ። በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የመንግሥት ባለሥልጣናትን በወቅታዊ ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ እየጠራ በማወያየት አከራካሪ የሆነ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን ባለሥልጣናትም ሆነ ባለሙያዎች በማቅረብ፣ በግምባር በማወያየትና በማከራከር ይፈጽመው የነበረው አገልግሎት በሀገሪቱ ምሁራን፣ ተማሪዎች እና በሰፊው ሕዝብ እየተወደደ በሄደ ቁጥር በአንጻሩ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ሂስና ጥያቄ መቅረቡ ያስደነግጣቸው የነበሩት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ፕሮግራሙን በክፉ ዐይን ይመለከቱት ገባ። ስለሆነም ብዙም ሳይቆይ ፕሮግራሙ እንዲዘጋ እርሱም ከሬድዮ ጋዜጠኝነት ወደ ህትመት ጋዜጠኝነት ማለት ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዛውሮ በምክትል አዘጋጅነት እንዲሠራ በ1959 ዓ.ም. ተወሰነ።

በአዲስ ዘመን ጋዜጣም ቢሆን “ህይወት ተስፋዬ” በሚል የብዕር ስም በሚያዘጋጃቸው ዜናዎችና አስተያየቶች፣ በሚያቀርባቸው ጥያቄዎችና ሂሶች ተደናቂነቱ ዕየታየ በመምጣቱ እንደገና ወደ ሬድዮ ተመልሶ በዜና አንባቢነት ብቻ ተወስኖ እንዲሠራ ተመደበ። የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሳያነሳ መኖር የሚያስቸግረው አሳምነው አረሳስቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ባለሙያ ይናገር” የሚል ምሁራንና ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን የሚያወያይና የሚያከራክር ፕሮግራም ይዞ ብቅ አለ። ይህ ፕሮግራም በቴሌቪዥን ሊቀርብ የቻለው በሬድዮና በቴሌቪዥን የአማርኛ ፕሮግራም ምክትል ኃላፊ ተብሎ በመመደቡ ነበር። ከዚህም በላይ ምንም እንኳ አልፎ አልፎ በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች የተነሳ በመሥሪያ ቤቱ ላይ ቁጣ የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ቢከሰቱም ፕሮግራሙ ያልተዘጋው ከባለሥልጣኖቹ ወገን እርሱን የሚያደንቁና የሚያከብሩ ምሁራን ሹማምንት በመኖራቸው ነው።

አሳምነው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ባበረከታቸው አገልግሎቶች መወደዱና መደነቁ የሚያስገርም አይደለም። ገና በልጅነቱ በመምህራኑ እና በአከባቢ የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ “የልጅ አዋቂ” የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። አብዛኛውን የህፃንነት ጊዜውን እንደማናቸውም የዕድሜ ጓደኞቹ ኳስና ሌሎች ጨዋታዎችን በመጫወት ሳይሆን ከአስተማሪዎቹ ጋር ቁምነገር ያላቸው ንግግሮችንና ውይይቶችን ሲያካሂድ እንደነበረ አጎቱ የሆነው ሌላው እውቅ እና ሐቀኛ ጋዜጠኛ ጋረደው ደምሴ በተመስጦ እያስታወሰ ይናገራል።

“አሳምነው ከልጅነቱ ጀምሮ ቁምነገረኛ፣ አልባሌ ቦታ የማይታይ፣ ደግ፣ ለሁሉም ሰው ርህሩህ፣ ሰው እንዳይበደል የሚሟገት፣ ለፍትሕ የመቆም ጠባይ ያለው ልጅ ሲሆን፤ በመምህራኑም ዘንድ እንደ ጓደኛ የሚታይ ነበር።” ይላል ጋረደው ስለ እህቱ ልጅ ጠባይ እና አስተዳደግ ወደኋላ መለስ ብሎ ኢ-ጊዚያዊ ሞቱን በሀዘን እያሰበ።

አሳምነው ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ እንደ የ“አፍሪካ ፕሮግራም” ያሉ ዝግጅቶችንም በራድዮ በማቅረብ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነበር። አቶ ገብረህይወት የተባሉ የአፍሪካ ፕሮግራሞች ተከታታይ እና አድናቂ የነበሩ ሰው ከአስመራ ከተማ በ17/12/1958 ዓ.ም. በጻፉት 5 ገጽ ደብዳቤያቸው “ለክቡር አቶ አሳምነው ገ/ወልድ ታላቁ እና የማደንቅዎ የኢትዮጵያ ራድዮ ዜና አብሳሪ፤ ክቡር ሆይ! ክቡር ብዬ ስጽፍልዎ ማዕርጌ አይፈቅድልኝም ብለው አይንቀፉኝ። ከርስዎ በላይ ሥያሜ ያላቸው ክቡር እምክቡራን ናቸው። ለርስዎ ግን ክቡርነት ያንስዎታል ብዬ አላምንም” ካሉ በኋላ “በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞዛምቢክ እና ከኖዴዝያ አፍሪካዊያን” ህዝቦች ጎን ተሰልፈው ዘረኝነትንና ቅኝ ገዥነትን ለማስወገድ መዝመት እንዳለባቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ ሲሉ ደብዳቤያቸውን ይደመድማሉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top