ታሪክ እና ባሕል

የኮቪድ ከባድ ክርን እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው መድቀቅ

ሄኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ)

ይህ በሰው ልጅ የእንቅስቃሴ ታሪክ አንዱ ከባድ ጋሬጣ ነው። ለብዙ ኢንዱስትሪዎች ፈተና የሆነው ኮቪድ 19 ለቱሪዝም ደግሞ ከመርሁ ሳይቀር ይቃረናል። ቱሪዝም ከቤት መውጣትን የሚሻ ኢንዱስትሪ ነው። ኮቪድ 19 ከቤት አትውጡ ባይ ወረርሺኝ ነው። ሊቃውንቱ ዛሬም ቤተ ሙከራ ውስጥ አንገታቸውን ደፍተው ይኼንን ማስታረቅ አልቻሉም።

ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የዓለም አንድ መንደር መኾን ሰርጉ ነበር። እንዲህ ያለው ወረርሺኝ ደግሞ መንደሩን በቀላሉ ለመድረስ ቀላል ሆነለት። ኮቪድ 19 አውሮጳ ገባ ሲባልና ጣሊያንን ከባድ ፈተና ላይ ሲጥላት የዓለም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከዳር ዳር ድባቡ ተቀየረ።

እንደ ብዙ የቱሪዝም ገበያ ባለሙያዎች የሮምን ጎዳናዎች ጭር ያደረገ፣ የቬንስን ደጃፍ ያዘጋ፣ የፍሎረንስን አደባባዮች በሰው ድርቅ የመታው ወረርሺኝ ሌላውን ዓለም የት ሊያደርሰው እንደሚችል መተንበዩ ቀላል ነበር።

በውጪም በሀገር ውስጥም የበለጸገችው ቻይና የወረርሺኙ መነሻ የመጀመሪያ ከባድ ጥቃቱ ምዕራፍ መክፈቻ እንደመሆኗ ወረርሺኙን ለመቆጣጠር ያደረገችው ጥረት የከፈለችውን ዋጋ ከፍላ ለሚቀናበት ድል አበቃት።

ኮሮና እንደ ቱሪዝም፣ አቪዬሽንና አገልግሎት ዘርፉ በከፋ ደረጃ ክንዱን ያሳረፈበት ኢንዱስትሪ የለም። ሰው ያጨናነቃቸው የመዝናኛ አደባባዮች ዛሬ ሰው የሚናፍቁ ምድረ ባዳ ሆኑ። ዓለም አንድ መንደር መሆንን በበጎ እንዳላየችው ከዓለም መራቅ መዳን ተደርጎ ተቆጠረ። ስልጣኔ ተሸነፈ። ወረርሺኝ ሰውን አሸነፈ።

እንዲያም ሆኖ የሊቃውንቱ ጥረት ቀጥሏል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ግን ዛሬም ከሚያስፈራ ድባብ አልወጣም።

የዓለም የቱሪዝም ድርጅት በ2020 የፈረንጆቹ ዓመት ወረርሺኙ ያደርሳል ብሎ የሰጋው ከ20 እስከ 30 በመቶ ኪሳራ ከትንበያው ገዝፏል። በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ብንመለከት የውጪ ጎብኚዎችን ብቻ ሳይሆን ዜጎችን ከቦታ ቦታ አላላውስ ብሎ ከርሟል። ድምር ውጤቱ ገዝፎ ታይቷል።

ዓለም በጋራ 50 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ኪሳራን በዚህ ኢንዱስትሪ ብቻ ያስተናግዳል የሚለው ግምት የወረርሽኙ መቆሚያ የት ጋር እንደሆነ በድፍረት ለመናገር ስላላስቻለ “ከዚህ ይከፋ ይሆን?” አስብሏል።

ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው እጓዛለሁ ብሎ ካቀደው የዓለም ህዝብ ሰማኒያ በመቶ “አርፎ መቀመጡ ይበጀኛል” ብሎ ከጉዞው እንደታቀበ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ይፋ አድርጓል። በሌላ ቋንቋ ሰማኒያ በመቶ የቱሪዝም ደንበኛ እግሬን አላነሳም ብሏል።

ዓለም የሚቀናበት የእንግሊዝ የስፖርት ቱሪዝም ድምቀት በአጭር ጊዜ ከል ለብሷል። ስታዲየሞች ዖና ሆነዋል። ከጨዋታ በፊትና ከጨዋታ በኋላ እንግዳ የሚያደምቃቸው የደርቢው ከተሞች በመስኮቱ ደጅ ደጁን የሚመለከት ሞት የሚሸሽ ስጉ መኖሪያ ሆነዋል።

በኢትዮጵያ እንኳን ብቻ ብንመለከተው ለወትሮው በሰው ልጅ እንቅስቃሴ ፋይዳ ያለው የማይመስለን የሀገር ውስጥ የስፖርት ቱሪዝም መቆም ብዙ ጎድቷል።

የሃምሳ ክለብ ማረፊያ ሆቴሎች በተበተኑ ተጨዋቾች ሳቢያ ገቢያቸው ቀንሷል። ከመቐለ ሶዶ ከአርባ ምንጭ ጎንደር ከባህር ዳር ጅማ ይደረጉ የነበሩ የደጋፊ ጉዞዎች ቆመዋል። ከነችግሩም ቢሆን በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ፋይዳ ያለው የኢትዮጵያ ስፖርት መቆም ጥናት የሚፈልግ ኪሳራ አምጥቷል።

ዓለም እግሩን ከስብሰባ ሰብስቧል። ጉባኤ ቱሪዝም ብሎ ጉዞ የሞት መንገድ ይመስል ተፈርቷል። እንደ ጄኒቭ ያሉ መዲናዎች እንዲህ ላለው ቱሪዝም የታደሉ ነበሩ ፤ አሁን እንግዳ ሞት ይዞ ይመጣ ይመስል ሰው ተፈራ።

አዲስ አበባ የአህጉሪቱ መዲና ናት። ስብሰባ የማያጣት መዲናችን ከቱሪዝም ተገኘ የሚባለው ገቢ ምክንያት ናት ብለው የሚሞግቱ ተመራማሪዎች የጉባኤ ቱሪዝሙን አቅም ያገዝፉታል። የአዲስ አበባ ሆቴሎች እያደገ ከመጣው የመዲናዋ የጉባኤ ቱሪዝም እድላቸው አቆራኝተው ራሳቸውን የተከሉ፣ ቅርንጫፋቸውን ያንዠረገጉ ነበሩ። ስብሰባው ሲቆም ሁሉ ነገራቸው ቆመ።

ችግሩ የዓለም ነው። እኛም ቱሪዝም ስንል የዓለምን ዓይን ዓይን እያየን ነው። በዚህ አግባብ የአውስትራሊያ ቱሪዝም እንዳልነበር ሲኾን ክንዱ ሰሜን ተራሮች ላይ ያርፋል። ወደ ሆንግ ኮንግ ከሚገባው የውጪ እንግዳ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ቁጥር ሲቀንስ ስሜቱ ባሌ ተራሮች የሚደርስ ነው።

የተሻለች የምትባለው ማሌዥያ እንኳን ከግማሽ በሚበልጥ ቁጥር የውጪ ጎብኚዋ ቀንሷል። ያቺ በንግድ ቱሪዝም ዓለም የቀናባት ሲንጋፖር የውጪ ጎብኚ ያለህ ስትል ከርማለች። 2020 ለየቱም የዓለም ሀገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የጣር ዘመን ሆኗል። የስካንዲኒቪያን የባልቲክ መርከብ መዝናኛዎች ወደ ዜሮ እንቅስቃሴ ገብተው ነበር።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቅድመ ኮሮና ብዙ ተስፋዎች ገጥመውት ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኖቤል ማግኘትና የኖቤል አዳራሻ ወሬ ስለ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት መሆን በገንዘብ የማይሰላ ኢትዮጵያን ዓለም ዘንድ የሸጠ መድረክ ሆነ። ውጤቱን ግን አላጣጣምንውም።

ሌላኛው አዲስ እድል የኢትዮ-ኤርትራ ሠላም ነው። ሁለቱ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት የወል ታሪክ ያላቸው ፤ የአንዳቸው ታሪክ ሌላቸው ጋር የሚደርስ ሆኖ ሳለ አንዱን የረገጠ ሌላው ጋር የማይደርስባቸው ጠበኞች ሆነው ኖረዋል። ከዚያ ሲያልፍ የኤርትራው መንግሥት ምዕራባውያንን የመጠራጠር የአትድረሱብኝ ባይነት አቋም የቀጠናውን ጭምር የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መላ ቢስ ያደረገ ነበር።

በአንድ ጉዞ በርከት ያሉ ሀገራትን የመጎብኘት ፓኬጅ ምስራቅ አፍሪቃ ሲደርስ ኤርትራ ደርሶ ኢትዮጵያ መግባት የቁም ቅዠት ሲሆን ተጽእኖ በሯን በዘጋችሁ ኤርትራ ብቻ ሳይሆን በበረገደችውም ኢትዮጵያ አይቀሬ ነው።

የሁለቱ ሀገራት ሰላም ለሁለቱም ሀገራት አዲስ እድል ይዞ ይመጣል ሲባል ቀዳሚው ተስፋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሆነ። ምጽዋ የወረደው ጎብኚ በአክሱም አድርጎ ጅንካ ይደርሳል በሚል መጪው ጊዜ ተናፈቀ። ቅድመ ኮሮና በዚህ ድባብ ውስጥ ሳለ ያልለየለት የሀገራቱ ፍቅር በኮሮና ጨርሶ ድፍን አለ።

ቅድመ ኮሮና አፋፍ ላይ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በፓስፊክ እስያ ሀገራት የጉዞና ጉብኝት ጸሐፍት ጋዜጠኞች ማኅበር ምርጥ የቱሪዝም ሚኒስትር ተብለው ተመረጡ። ኢትዮጵያም በአርኪዎሎጂካል የታሪክ መዳረሻነት ተመራጯ ሀገር ተባለች። ሽልማቱ ዓለም እንዲሰማው የሚደረግበት የጀርመኑ ግዙፍ የቱሪዝም ንግድ ትርዒት /ITB/ በኮሮናው ስጋት ተሰረዘ። ቅድመ ኮሮና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ምቹ እድል ዓለም በገጠመው ፈተና- ፈተና ውስጥ ገባ።

እውነቱ የሀገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዚህ ከባድ የወረርሺኝ ክንድ መድቀቁ ነው። በተፈጥሮ መዳረሻዎች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ኑሯቸውን የመሰረቱበት ኢንዱስትሪ ነጠፈ። ራስን በሰሜን ተራሮች አናት ጓዝ በበቅሎ የሚጎትት አንድ የቱሪስት አገልጋይ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ምትክ አድርጎ ለተመለከተ ኢንዱስትሪው ላይ ያሳደረውን ጫና መገመት ይችላል።

የከተማ ቱሪዝሙ ህልውና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪው ላይ የተንጠለጠለ ነበር። ከደመወዝ ይልቅ የአገልግሎት ጉርሻ ኑሯቸውን የሚደጉማቸው የሆቴል ሠራተኞች እንደምን ያለ ጊዜ እያሳለፉ ለመሆኑ መገመት የጠለቀ ጥናት የሚፈልግ አይደለም። የአካባቢ አስጎብኚዎች መዳረሻዎቹ በሰው ድርቅ ሲመቱ የሚገጥማቸው አበሳ ከስሌት ይልቃል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙም አብሮ መውደቅ ችግሩን አክፍቶታል። መንፈሳዊ የንግስ ጉዞዎች ተሰርዘዋል። ዓመት ጠብቀው ነፍስ የሚዘሩ ከተሞች ዓመት ዘሏቸዋል። አክሱም፣ ላሊበላ፣ ግሸን፣ ቁልቢና መሰል ብዙ መቶ ሺህዎች የሚታደሙበት የንግስ በዓል ለብዙ መቶ ሺህዎች ዳቦ ነበር። በርካታ የዚያራ ጉዞዎች መሰረዛቸው፣ የግብይት ቱሪዝሙ መቀዛቀዝና የጉባኤ ቱሪዝሙ መቅረት ጥልቅ ጥናት የሚፈልጉ የተጽእኖው ምክንያቶች ናቸው።

ከአርባ በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ዘንድሮ በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተማሪዎቻቸውን አያስመርቁም። ልጄን፣ ወንድሜን፣ እህቴን፣ ጓደኛዬን ላስመርቅ ብሎ ዩኒቨርሲቲዎቹ ወደአሉበት ከተማ መጓዝ የለም። በሀገር ውስጥ ቱሪዝም አዲስ የተስፋ ምዕራፍ የነበረው ይህ ዓመታዊ የምረቃ በዓል ይኽንን ዓመት አለመኖሩ በዚህ ምክንያት ገቢ አግኝተው በሚኖሩ ወገኖች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ብዙ ነው።

ከኮሮናው በኋላስ?

ዓለም አሁን ከኮቪድ 19 በኋላ ስላለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ራሱን እያዘጋጀ ነው። በኢትዮጵያ መልሶ ቱሪዝሙ የሚያገግምበት ስልት ተቀይሷል። ባለድርሻዎችን ያካተተ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል። ኢንዱስትሪው ላይ የደረሰውን ጫና ለመቀነስ በመንግሥት በኩል የተደረገው ማበረታቻም መልካም ነው። በራሱ በቱሪዝሙ ቤተሰብ በኩልም ተጋግዞ ጨለማውን ለመግፈፍ ተሞክሯል። የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ለመዳረሻ አካባቢዎች የሚሆን የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ለግሷል።

እርግጥ የሰው ልጅ ያለ ገቢ ከወጪ ሳይድን ቤት ተዘግቶበት ከርሟል። የውጪው ናፍቆት ቢኖርም ስራ ሲያደክመው አልሰነበተም። በቱሪዝም የበለጸጉት ሀገራት ደግሞ ድህረ ኮሮና እንደምን አድርገው የቆመውን ኢንዱስትሪ በአቦሸማኔ ፍጥነት እንደሚያስሮጡት እያቀዱ ነው።

ይሄ ሁሉ ተዳምሮ ድህረ ኮሮና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውድድር ከባድ እንደሚሆን መገመት አያቅትም። ፎርብስ መጽሔት ኢትዮጵያን ድህረ ኮሮና ከሚጎበኙ ሰባት ሀገራት አንዷ አድርጓታል። ፎርብስ ከሰባቱ አንዷ ብቻ አድርጓት አላቆመም ልትጎበኝ የሚገባት ብሎ ዓለም ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ ጭምር ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል። ምክንያቱንም አስቀምጧል።

የምንጎበኝበትን ምክንያት ሆነን መጠበቅ ይኖርብናል። የኮሮናው ዘመን ጨለማ ነው ብለን ብቻ በዳፍንቱ መቀመጥ የለብንም። ዳፍንቱን በማሾ አብርተን ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። እስኪነጋ የሚሰሩ ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል። አገልግሎት አሰጣጣችንን ተወዳዳሪ ለማድረግ መዘጋጀት ያስፈልገናል። ሽንት ቤቱ እንኳን በቅጡ ያልጸዳውን ብሔራዊ ሙዚየም ደረጃ አሳድገን እርጅናውን ጠግነን ዙሪያ ገባውን አስውበን መጠበቅ አለብን። ከብትና ዱር እንስሳት አንድ ላይ የሚውሉባቸውን የተፈጥሮ መዳረሻዎች ችግር ቀርፈን “የት አለህ? ጎብኚ” ማለት ይኖርብናል።

መሠረተ ልማትን የመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚነሳባቸውን የቱሪስት መዳረሻዎች ችግር ለመቅረፍ ጨለማው ምቹ ጊዜ ነው። ሰላምና መረጋጋትም እንዲሁ የግድ ይላል። ቅድመ ኮሮና አስፈሪ የነበረው የብሔር ጠብ፣ የመንገዶች ሰላም እጦት፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር ድህረ ኮሮና እንዳይቀጥል ካልተደረገ ቱሪዝሙ ብርሃን አያይም። ዓለም ጨለማው ሲገልፍለት ድቅድቁ እኛ ላይ ይብሳል። ከሰራን ግን ለዓለም የምትወጣዋ ጸሐይ አብልጣ ለሀገራችን ታበራለች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top