ማዕደ ስንኝ

“…በል ተነስ ፈርዖን…”

ዳዊት (የምዕራፍ አባት)

ና.. ወዲህ
ብቅ በል… ጠራሁህ ፈርዖን
ለሳቱት ልጆችህ ልቦና ብትሆን…
ለአፍታ አፍ አውጥተህ… ምሥክር ብትሆን
ጠራሁህ ፈርዖን
ዲኦዶሮስ ሲኩለስ ምን ብሎ ከተበ?
ለእኚህ ልጅ… ልጆችህ
አውጉስተስ ምን ተወ?
ካንተም ዘመን ቀድሞ ከኖሩ ዘሮችህ
ምን ዐየህ?
ምን ሠማህ?
ምን አመንክ… ምንስ ካድክ?
የቱን ዳጥክ… ምን ደለዝክ?
ምንን ፋቅክ… ምን ሠረዝክ…?
ስማ’ንጂ ፈርዖን…
በል’ንጂ ፈርዖን…
ፈንቅል ያን ፒራሚድ… ተነስ ደርምስና
የደረቀ ሬሣህ ይዘፍዘፍ ከጣና
ምላሥህ ይላወስ… ሥጋህም ነብስ ይዝራ።
እንጅላት… ምንጅላት ቀደምቶችህ ሁሉ
ሚስቶች፣ ገረዶችህ… ፈረስ አህዮችህ
ባዝራ… ወታደሮች ቅምጦችህ ሁሉ
ቀስቅስ!ቀስቅስ!ቀስቅሣቸው… ከትቢያ ይነሡ ይፈታ ጨርቃቸው!
ይዩ የሣቱትን የልጅ ልጆቻቸው…!!
በል’ማ ፈርዖን…
የፒራሚዱ ገዥ… የበረሃው ዝሆን…
የድንጋጤ ውርጭ ብርክ ላሲያዛቸው
ለእንጅላትህ ዘሮች ልቦና ብትሆን…
በል’ማ ተናገር… ዝም አትበል ፈርዖን…
ዲኦድሮስ ሲኩለስ… ምን አውቆምን ዐይቶ?
ምን ፃፈ?
አውጉስቶስ ምን ብሏል?
ምንስ እውነት ተወ?
‘ግብፅ’… ይሏት ምንድነች?
ይህች ያንተ ምድር… ጥንት ምን ነበራት?
ቀይ ባሕርን ለብሳው የተዋጠች ሣለች…
ዝም አትበል… አትፍራ ፈርዖን…
ታውቃለህ እውነቱን… ‘ሬሳም ብትሆንዓባይ ነው!!
ናይል ነው… ላስታውስህ… ጥንት እንደ ዘንድሮ
አፈር እየዛቀ ከሃገሬ ጓሮ
ባሕሩን በደለል አሽቀንጥሮ ገፍቶ…
ዝቆ…
ዝቆ…
ዝቆ…
በቸነፈር ልምጭ አጥንቴን ሠንጥቆ
የውሃ ማማይቱን… ይቺ የኔይቱን…
ቦጥቡጦ… አራቁቶ…
ፈጠራት ያ’ንተይቱን… የእኔን ሃገር ገድሎ
ከባህር ማህፀን… የዘር ማንዘሬን ዘር
አግበስብሦ ዱሎ…
ግብጽህን ፈጠራት… ደለል ላይ አፅንቶ።
እንዲያ ነው ፈርዖን…
ላስታውሥህ ተናገር…
ሁናቸው ምሥክር…
የድንጋጤ ውርጭ ግራ ላጋባቸው
ለሳቱት ዘሮችህ ልቦና ብትሆን…
ተናገር…
ይላወስ ምላሥህ…
በል ተንፍስ ፈርዖን…
በአቡኑ እንዳይሉኝ… አቡኑን ሆኛለሁ
ሲዘርፍ…
ሲቦጠቡጥ
ሲገድለኝ የኖረን… ችሎት አቁሚያለሁ
ራስ ከሣሽ… ራስ ፈራጅ…
ራስ ወጪ… ራስ ወራጅ
ሆንኩና ባተሌ… መንገሪያ ጊዜ አጣሁ…
በ’ልማ ፈርዖን…
ዓሣ የጎረጎረ… ምን ያወጣል ቢሉ
እንኳን ውሃው ቀርቶ… ግብፂቱም
ከእኔው ናት… የሣቱት ይወቁ…
በል’ማ…ተናገር…
በል ተንፍስ ፈርዖን…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top