ማዕደ ስንኝ

ምነው አምቦ?

ጸጋዬ ገ/መድህን (ሎሬት)

ምነው አምቦ…

የደማም አምባዎች ቁንጮ ፤ እንዳልነበርሽ የደም ገንቦ

እንዳልነበርሽ ንጥረ-ዘቦ

ዙሪያሽ በምንጭሽ ታጅቦ

በተራሮችሽ ተከብቦ

ከጠበልሽ ሢሳይ ታልቦ

ከአዝእርትሽ ፍሬ ዘንቦ

ከዓመት ዓመት ጤና አብቦ

ሕይወት ደርቶ ሰላም ቀርቦ…

የአየር ትፍስሕት እንዳልነበርሽ፤

የዘር ሆነ የእሸት የአትክልት

ከመጫ እስከ አዋሽ እምብርት

ምንጭሽ ሲያጥጥ ሲፍለቀለቅ፤

ከዳንዲ እስከ ወንጪ እትብት…

እንዳልነበርሽ የምድር አድባር ፤ የዘር ድባብ ያገር ችቦ

ዛሬ እንደዚህ ምነው አምቦ

የቀትር ጥላሽ ተስቦ

የጡቶችሽ ወዝ ተሰልቦ

ውስጥ አንጀትሽ ተለብልቦ

የመዓዛሽ መፍለቅለቂያ ፤ መንጸባርቅሽ ተሸብቦ

ተረምርሞ ተተብትቦ…ምነው?… ምነው አምቦ

1980 – አምቦ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top