ታሪክ እና ባሕል

የሽምግልና ባህላችን

ኢትዮጵያ በብዝኃ-ህብረ-ብሔራዊ ኃብት የታደለችና የተዋበች ሀገር ናት። ነገር ግን በተለይም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ የብሔረሰብ ሜዳሊያ ባጠለቁ፤ በህዝብ ኪሣራ ትርፍ በሚያነፈንፉ የብሔረሰብ ‘ምሁራን’ ጽንፈኛ “የፖለቲካ ብሔረሰበኛነት”ደዌ አብቅላለች። በግጭት ውስጥ ትገኛለች። እናም “ያገሩን ሰርዶ፣ በሀገሩ በሬ” እንደሚባለው ሀገራዊ መፍትሔ ትሻለች። ዋነኛው ሀገርኛ የመፍትሔ መንገድም ባህላዊ የሆኑትን የሽምግልና ተቋሞቿን አጠንክራ መጠቀም ይኖርባታል። በእርግጥ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የሽምግልናው ባህላዊ ተቋም ከማርክሲዝም እስከ ብሔረተኛ ተለዋዋጭ ፖሊቲካዊ ርዕየተ-ዓለምና አስተሳሰብ ተጽዕኖ ሥር ወድቆ፣ እንደ ‘ጎጂ ባህል’ ተቆጥሮ፣ በመቆየቱ እየተዳከመ ቢመጣም፤ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል፣ መልካም አስተዳደርንና አዳዲስ የዲሞክራሲ እሴቶችን ለማሥረፅና ለማጠናከር ብሎም በሁሉም ገጽታዎች፣ ማለትም፡- በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በሰብአዊ የእውቀት ሀብት እድገትን ለማፋጠን መሠረት ሆኖ በማገልገል ረገድ የሚኖረው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው።

በዚህ ርዕስ ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ያነሳሳኝ፣ በአንድ በኩል ሀገራችን በተለያዩ የውስጥና የውጭ ችግሮች ዙሪያውን ተከብባ በምትኝበት አውድ ውስጥ የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ተሳካም አልተሳካ በአንዳንድ ክልሎችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለማርገብ የጀመሩት እንቅስቃሴ ነው። በሌላ በኩል፣ ይህን ተከትሎ በብዙዎቹ መንግሥታዊና ዘወትሯዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ጨምሮ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተላለፉ ዜናዎች፣ ውይይቶች፣ አስተያየቶችና ግምቶች በተለይም ደግሞ በባህላችን መሠረት እንዲህ ያሉ ክብደት በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የሚካሂያዱ የሽምግልና ሥራዎች ከሚጠይቁት ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች አኳያ የሚጋጩ ብቻ ሳይሆኑ ሸማግሌዎች ከፍሬያማ ውጤት ላይ እንዳይደርሱ አፍራሽ ሚና ሊጫዎቱ ይችላሉ የሚል ስጋት ስላለኝ የበኩሌን ሀሳብ ለአንባብያን ለማካፈል እወዳለሁ።

በመሆኑም በቅድሚያ “ሽምግልና” የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ እንመልከት። ሽምግልና በባህል የተፈጠረ፣ በረዥም ዘመናት የህብረተሰብ ታሪክ እየተሻሻለ፣ በገቢር እየተፈተነና እየዳበረ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃልና በድርጊት ያለማቋረጥ እየተላለፈ የመጣ፣ የእሴት ሥርዓትን የተከተለ፣ ዓላማና ግብ፣ መርሆ፣ የአሠራር መንገድና ደረጃ ያለውትውፊታዊ /ባህላዊ ተቋም ነው።

ከዚህ ላይ “ባህላዊ ተቋም” ሲባል በቁሳዊ መልኩ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ገጽታው፣ ለምሳሌ፡- በእምነት፣ በርዕዮተ-ዓለም አመለካከት፣ በአስተሳሰብ፣ ወ.ዘ.ተ… ጥልቅ፣ ሥር የሰደደ ሥርፀት ያለው ኃይል እንደማለት ነው። ከዚህ ጋር አብሮ መገንዘብ የሚያስፈልገው ባህላዊ ሽምግልና ከ’ዘመናዊ’ ሽምግልና የሚለይበት ዓይነተኛ ባሕርይም፤ በአንድ ኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ በሚኖረው ‘ጥልቅ ሥርፀት’ ምክንያት መሆኑ ነው። ማንኛውም ተቋም ‘ተቋም’ ስለተባለ ሥርፀት አለው ማለት አይደለም። በአጭሩ ‘ዘመናዊ’ የሽምግልና ተቋም ባህላዊ የሽምግልና ተቋም ያለውን ሥርፀት ያህል እንደሌለው ልብ ማለት ያሻል።

ባህላዊ/ትውፊታዊ ሽምግልና ከባህል ባህል በአውድ ይለያያል። በመርሆውና በግቡ ደግሞ ከባህል ባህል ይመሳሰላል። መርሆው እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ከአድልኦ የራቀ ተሳትፎ፣ ሚዛናዊነት፣ እውነት፣ ሰብአዊነት፣ ወ.ዘ.ተ… ሲሆኑ ግቡ በተለያዩ ምክንያቶች፣ ባህርያትና ደረጃዎች የሚገለፁ የግጭት ዓይነቶችን በመፍታት ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ የማኅበረሰብን ህልውና ማስተማመን ወይም ማረጋገጥነው። ግጭት የተፈጥሮ ሕግ ነው። በመሆኑ ከግጭት ‘የነፃ’፣ ‘የፀዳ’ ኅብረተሰብ አይኖርም። ይህ ማለትም ግጭት የሌለው ኅብረተሰብ እድገት፣ ለውጥ፣ አይኖረውም ማለት ነው። ስለዚህ የሽምግልና ሥራ ከውሃ ልኩ አልፎ የፈሰሰን ግጭት ወደ ተለመደው የውሃ ልክ ደረጃ ለመመለስ የሚደረግ እንጂ ‘ግጭትን ለማስወገድ’ የሚከናወን ተግባር ሆኖ መታየት የለበትም።

ሽምግልና የሚገባባቸው ቀላልና ከባድ የግጭት ዓይነቶች አሉ። ቁጥራቸውም እጅግ በጣም ብዙ ነው። ከዓይነቶቹ መካከልም እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ከሀገር ሉዓላዊነት፣ ከህዝብ ህልውና አንስቶ፤ በተዋረድ በጎሳዎች፣ በማኅበረሰቦችና በቡድኖች መሀል ከሚጠሩት እስከ ቤተሰብና ግለሰቦች ግጭቶች፣ ወ.ዘ.ተ… የሚያካትቱ ይሆናሉ። በዚያው መጠን የእነዚህ የግጭት ዓይነቶች ምክንያቶችና የሚሰጣቸው ትኩረት፣ በመካከላቸው የሚኖረው ባሕርያትና አሳሳቢነት፣ የሚጠይቁት የሽማግሌ ማኅበራዊ ደረጃም ሆነ የአፈታት መንገዶችና ስልቶች፣ ወ.ዘ.ተ… በዚያው መጠን የተለያየ ይሆናል።

በባህሉ መሠረት የሽምግልና ሥራ አንድም በራስ አነሳሽነትና ፈቃደኛነት ኃላፊነት በመውሰድ ወይም ደግሞ በግጭቱ ባለቤቶች በኩል የሚቀርብ የእርቀ-ሰላም ጥያቄን ተከትሎ የሚከናወን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነፃ አገልግሎት ነው። እንደ ሀገራችን ባሉ በማንኛውም ትውፊታዊ ህብረተሰቦች ዘንድ እድሜ የእውቀትና የነገር አፈታት ጥበብ፣ የካበተ ልምድና ተሞክሮ፣ የሚዛናዊነት በአጠቃላይም፣ ለመልካም ውጤት የሚያበቃ የተሟላ ስብዕና ምልክት ተደርጎ ይታያል። ከዚህ እምነት የተነሳ ይመስላል በባህላችን “ሰማይ ተቀደደ ቢሉት፣ ሽማግሌ ይሰፋዋል! አለ” ይባላል። ይህ “ሽማግሌን የሚያቅተው ነገር የለም” እንደማለት ነው። በዚህም በማኅበረሰቡ አባላት ቅቡልነት፣ አክብሮትና ቅድሚያ ይሰጠዋል። “ወንዝ ያከበረው፣ ዝናብ ያፈረው” የሚባለውም ለዚህ ነው። በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ ከባድና ቀላል ግጭቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠሩ ጊዜ፤ የመፍቻው ቁልፍ በሽማግሎች እጅ መሆኑ ስለሚታመንበት፤ በጊዜው መፍትሔ የመሻቱ ኃላፊነት የእነርሱ ድርሻና ሚና ተደርጎ ዕንደሚታይ ሁሉ፤ ይህን የኅብረተሰቡን እምነት የራሳቸው እምነት አድርገው የሚጠበቅባቸውን ተግባር በግንባር-ቀደምነት ይወጣሉ።

ሽምግልና የባህል ተቋም እንደመሆኑ መጠን በዘፈቀደ (በጭፍን) አይከናወንም። ዓላማና መርሆዎች እንዳሉት ሁሉ እንደ ግጭቱ ዓይነትና ባሕርይ በአውድና በሁኔታ የሚያገለግሉ፣ ለውጤት የሚያበቁ ትውፊታዊ የአወቃቀር ቅርፆችና መመሪያ ደንቦች፣ የአሠራር መንገዶችና ቅደም ተከተል ደረጃዎች፣ አሳታፊ ዘዴዎችና ስልቶች አሉት። ለምሳሌ የግጭቱ ዓይነት ሀገራዊ ጉዳይ ከሆነ በሽምግልናው የሚሳተፉ የሽማግሌዎች ደረጃና ብቃት ሌሎች ግጭቶች ከሚጠብቁት መመዘኛ መስፈርት ይለያል። ታሪክም እንደሚያስረዳው ለዚህ ሥራ የሚመለመሉት የሃይማኖት አባቶች እና በሀገር ደረጃ አክብሮትን፣ ታዋቂነትንና ተሰሚነትን የተቸሩ ሽማግሌዎች ይሆናሉ። የሽምግልናው ሥራ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ የማንኛውም ዜጋ በጉጉትና በአንክሮ ይመለከተዋል። ስለዚህ የሚኖረውን ሀገራዊ ፋይዳ እጅግ በጣም ከፍተኛ ያደርገዋል። እናም የችግሩ ባሕርይና ደረጃ የሽማግሌዎችን ብቃትና ደረጃ ብሎም የሽምግልናውን ይዘት፣ ደረጃና አወቃቀር ጭምር ይወስነዋል።

ሽምግልና የሚያልፍባቸው የአሠራር ደረጃዎች አሉ። ቀዳሚው ደረጃ ሳይጠናቀቅ ቀጣዩ ደረጃ ውጤታማ አይሆንም። በመሆኑም በባህል የተዋቀሩና የሚታወቁ በተለይም ከፍተኛ ስጋት በሚያስከትሉ የግጭት ዓይነቶች በቅደም ተከተል የሚጠበቁ ወይም የሚከናወኑ የሽምግልና ሂደት አሠራር ደረጃዎች የሚከተሉትን ይጨምራሉ፡-

የመጀመሪያው የሁኔታ ቅድመ-ምርመራና ትንበያ ነው። ይህ ማለት በግጭቱ ተዋንያን ማንነት፣ በተፈጠረው የግጭት ዓይነት ምክንያትና እንዴትነት፣ በሁነቱ ክብደትና አጣዳፊነት፣… ላይ የሁኔታ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ ቀጥሎ መከናወን ወደሚኖርበት ተግባር ለማምራት የሚያስችል እርምጃ ነው።

ይህ ከተከናወነ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣው ሥራ የእርቅ እሽታን ማግኘት ይሆናል። የእርቅ እሽታን ከሁለቱም ባላጋራዎች ለማግኘት አንድም በራሳቸው አነሳሽነት ወይም ችግሩ በሰላም እንዲፈታ የሚፈልግ ከባላጋራዎቹ የአንደኛው ወገን ቅርብ ዘመድ በሆነ ሰው ወትዋችነት በግራ ቀኙም ተቀባይነትና ተሰሚነት የሚኖራቸው የሀገር ሽማግሌዎች ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ በሚደርጉት ጥረት የሚከናወን ተግባር ማለት ነው። እንደነገሩ ክብደት ሥራው ጊዜና ድካምን ሊጠይቅ ይችላል። ስለዚህ እሽታን ለማግኘት ያለመታከት፣ ያለመሰልቸት፣ ጥበብንና ትዕግሥትን የሚጠይቅ ይሆናል።

በዚህ መልክ እሽታው ከተረጋገጠ በኋላ በሦስተኛ ደረጃ የሚከናወነው፤ በሁለቱ የግጭቱ ባለቤቶች ወይም ወገኖች ፍላጎትና ስምምነት አስታራቂ ሽማግሌዎችን የማንሳት (የመምረጥ) ተግባር ነው። አስታራቂ ሽማግሌዎችን የመምረጡ ሂደት በታራቂ ወገኖች ነፃ ፍላጎትና የቆየ የግንኙነት ታሪክ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ምናልባት በመጀመሪያ የግራ ቀኙን እሽታ ለማረጋገጥ የደከሙትን ሽማግሌዎች ሊጨምርም ላይጨምርም ይችላል።

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውና አራተኛው ደረጃ የሽማግሌ ዳኛ የመምረጥ፣ ድንጅ (ቃለ-መኃላ) የማስገባትና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሁለቱም ወገኖች ነገረ-ፈጅ የማቆም ደንብን ማከናወን ይጨምራል። የሽማግሌ ዳኛ የሚመረጠው በተመረጡት ሽማግሎች ሲሆን መመዘኛ ነጥቦች ተደርገው ብዙውን ጊዜ የሚወሰዱት በግራ ቀኙ ታራቂ ወገኖች በኩል የሚቀርቡ ስሞታቸውን ልብ ብሎ በማዳመጥ፣ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማጠቃለልና በተገቢ አገለላለፅ በቅደም-ተከተል መልሶ ማስደመጥና የሽምግልና ሂደቱን ሥነሥርዓት በማስጠበቅ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ የመምራት ልምድና ክህሎት ያለው መሆኑና የመሳሰሉ ናቸው። በባህሉ መሠረት ሰዎች ጉዳያቸው ወደ ሽምግልና ሲቀርብ ከሽማግሌ ዳኝነት ላይወጡ ቃልኪዳን ይገባሉ። ይህ የሚፈፀመው ባላጋራዎቹ እርቀ-ሰላም ለማውረድ ከልብ መቅረባቸውን በአደባባይ ማረጋገጣቸውን ለማፅናት ሲባል የሚፈፀም ደንብ ነው። የገቡት “ቃል ከሚሞት የወለዱት ልጅ ይሙት” ነውና በባህላችን ቃል አፍራሽነት ‘እርጉም’ ምግባር ተደርጎ ይታያል። በመሆኑም የቃልኪዳን ሥነሥርዓቱ እንደ ቅድመ-ሁኔታ የሚወሰድ ትልቅ ጉዳይ ስለሆነ፤ በሽማግሌ ፊት ሳያረጋግጡ ‘ደረሰብኝ’ የሚሉትን በደል በቀጥታ ወደማፍሰስ አይራመዱም።

ይህ ከተፈፀመ በኋላ፣ ባላጋራዎቹ በየተራ እየተጠሩ ከሽማግሌዎች ፊት በደላቸውን በነፃነት፣ ያለፍርሃት፣ ያለመቆጠብ፣ እንዲናገሩ ይደረጋል። በተለይም ግጭቱ ክብደት ካለው ባላጋራ ወገኖች በርቀት ለየብቻ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ሽማግሎች ከተቀመጡበት ቦታም እንደዚሁ ርቀት ጠብቀው መቀመጥ አለባቸው። ተራ በተራ እየተጠሩ የሚመጡትም ከዚህ ተራርቀው ከተቀመጡበት ሥፍራ ይሆናል። ይህ የሚደረግበት ምክንያትም አንዱ ወገን ከሽማግሌ ፊት ቀርቦ ያለመቆጠብ ስሜት በተቀላቀለበት አኳኋን ሊናገር የሚችለውን ቃል፤ ሌላው ወገን ሰምቶ ለተከላካይነት አፀፋ በመዘጋጀት ቅሬታውን በሚጠበቀው መልክ እንዳያቀርብ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ ስለሚታመንበት ነው። በመሆኑም የአንደኛውን ወገን ድምፅ ሌላው ተቃራኒ ወገን በትክክል እንዲረዳ የሚደረገው በሽማግሌዎች ብስለትና ጥንቃቄ በተሞላበት ሚዛናዊ አገላለጽ አማካይነት ነው። ከዚህ ላይ ከሂደቱ ጋር አብሮ መገለጽ የሚኖርበት አንድ ጠቃሚ ጉዳይ አለ። ይህም ለእርቅ ከቀረቡት ተቃራኒ ወገኖች የሚጠበቁ ሥነምግባራዊ ደንቦችን የሚመለከት ነው። ከእነዚህ ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች መካከልም፣ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፡-

  • የሽማግሌ ሀሳብ ማጣጣል፣ ሽማግሌን በንቀት ዐለማየት
  • አሁንም አሁንም በሌሎች ተራ ጣልቃ በመግባት አለማቋረጥ፣ ያለ ተራው አለመናገር፤
  • ከኃይለ-ቃል፣ ከአፍ እላፊ፣ ከጉንጭ አልፋ፣ ከአራጣ ንግግር መቆጠብ፤
  • ያዙኝ ልቀቁኝ አለማለት፣ በስሜት አለመወራጨት፤
  • ከስድብ፣ ከዛቻ፣ ከፉከራ መታቀብ፤
  • ሀሰተኛ መረጃ ከመናገር መራቅ፣ ስለ ነገሩ አመጣጥ እውነቱን መናገር እና የመሳሰሉት፣

ከእነዚህ ውጭ ሆኖ በሽማግሌ ፊት መታየት ከብልግና ይቆጠራል። “የቤት አመል ገበያ ይወጣል” እንዲሉ በበባህላችን ዘንድ እጅግ በጣም የተናቀ፣ ነውር፣ የአጉራ-ዘለል ድርጊት ተደርገው ይታያሉ። ስለዚህ ለእርቅ የቀረቡ ወገኖች ሃሳባቸውን ስሜታቸውን በመቆጣጠር በሰከነ፣ በተረጋጋ፣ ተአማኒነትና ጨዋነት ባለው ሁኔታ መግለጽ ይጠበቅባቸዋል። ሽምግልና ጥበብ ነው። በደል የደረሰባቸው ሰዎች የተሰማቸውን የመናገር እድል ካልተሰጣቸው የታመቀው ቁጭት አይቀንስላቸውም። ቁስላቸው አይሽርም። ስብራታቸው አይጠገንም። እርቁም እርቅ አይሆንም። ሆኖም ግን ታራቂ ወገኖች ከሚጠበቁት ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች ውጭ ከልክ አልፈው ሲገኙ ከሽማግሌዎች አንዱ ወይም ሁለቱ ለብቻ ገለል አድርገው ብሶታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያሰሙ ከወቀሳ የራቀ ስሜትን በማይነካ መልካም አነጋገር ምክር ይሰጣሉ። የሽምግልና አንዱ ትርጉም ከንዴት፣ ከቁጣ፣ ከኩርፊያና ከወቀሳ የራቀ ከልብ ስብራት የሚያሽር ትእግሥት የተሞላበት ጥበብ የሚያሰኘውም ከዚህ በመነጨነው።

ሁለቱ ተቃራኒ ወገኖች ተራ በተራ እየተጠሩ በደላቸውን በሥነሥርዓት ካፈሰሱ በኋላ ሽማግሌዎች ቀጥለው የሚያከናውኑት ሥራ ምንድን ነው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ሽማግሌዎች ቀጥሎ የሚያከናውኑት ዝግ ውይይት ይሆናል። የውይይቱ ዓላማ የታወቀ ነው። ይኸውም በግራ ቀኙ ባላጋራዎች የቀረቡት ቅሬታዎች በመካከላቸው ምን ርቀት፣ ክፍተትና ተመሳሳይነት እንዳላቸው ማነፃፀርና ማመሳከር፣ ማለትም፡- የአንዱ አቋም ከሌላው ምን ያህል እንደሚጋጭ በመመዘን ለማቀራረብና እና የተድበሰበሱ ሀሳቦችን ግልጽ ለማድረግ ጥያቄዎችን በማቅረብ፣ ወ.ዘ.ተ… ስለችግሩ ባሕርይ በቂ ግንዛቤ ማግኘት ነው። ከዚህ የተነሳም የግጭቱን ተዋናዮች እንደገና በየተራ ደጋግመው እውነተኛ ሀሳባቸውን ማዳመጥ፣ ፍሬ ነገሮችን መጨበጥና ለማመሳከርም መላልሰው መስቀለኛ ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ የሁለቱም መከራከሪያ ነጥቦች መቀራረብና መተማመን ካልቻሉ ምሥክሮችን በማዳመጥ አመኔታ ለመፍጠር በተደጋጋሚ በቀነ-ቀጠሮ በማስተላለፍ ወደሚቀጥለው ደረጃ፤ ወደ ብይን ለማምራት ይገደዳሉ። የሽማግልና ሥራ ሂደት ቁልፍ ተግባር በመጨረሻ በሽማግሌ ዳኛው አማካኝነት ተጠቃለው በሚቀርቡት መረጃዎች ላይ የሁለቱም ባላጋራ ወገኖች አመኔታ መፈጠሩን ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ ይህ ከመረጋገጡ በፊት የሽምግልናው ሂደት ወደ ብይን፣ ከዚያም፣ ወደ እርቀ-ሰላም፣ ወደ ይቅር ለእግዚአብሔር፣ ወደ ካሳና በተለያዩ ትእምርታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በሚፈፀሙ የጉምብስ ደረጃ ሊሸጋገር አይችልም።

በባህሉ መሠረት የሽምግልና ሥራ ሲካሄድ ከሽማግሌዎችና ከታራቂ ወገኖች የሚጠበቁ መልካም ምግባሮች እንዳሉ ሁሉ ከማህበረሰቡ አባላትም እንደዚሁ የሚጠበቁ ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች አሉ። “ሽማግሌ ዋሽቶ ያስታርቃል” የሚል ምፀታዊ አባባል አለ። አባባሉ የሚያመለክተው ቁምነገር በጠላትነት የሚተያዩ ወገኖችን በጥላቻ የተሞላ ስሜት ዋሽቶ በማለዘብ ወደ ይቅር ባይነትና ወደ እርቅ በመመለስ የህብረተሰብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያገለግል ስልት ወይም ጥበብ እስከሆነ ድረስ እውነት የመሆኑን ሐቅነው። ሽምግልና ሥርፀት ያለው፣ ሀገርን እንደ ሀገር ለረዥም ዘመናት ጠብቆ ያቆየ የሰላምና የደህንነት ማስጠበቂያ ትውፊታዊ ተቋም ነው። በመሆኑም በሁሉም ዘንድ አክብሮት ሲሰጠው የቆየ፣ የተቀደሰድንቅ ባህላዊ እሴት ነው። በዚህ ምክንያት በተለይም የሁሉንም ሕይወት የሚነካ እንደ ሀገር ጉዳይ ክብደት ያለውን ግጭት ለመፍታት የሚካሄድ የሽምግልና ሥራ ሲካሄድ በማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ የሚጠበቁ ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች አሉ። ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡-

  • የባላጋራ ወገኖችን በተገኘው አጋጣሚው ለእርቀ-ሰላም የመቅረባቸውን ሁኔታ ማድነቅ፣ ማመስገንና ማበረታት፣
  • በባላጋራ ወገኖች መሃል ነገር ከመሥራት፣ ከማቀባበል መታቀብ፣
  • ተቆርቋሪ መስሎ አሉባልታና አፍራሽነት ያለው ወሬ ከማቀባበል ራስን መጠበቅ፣
  • የሽማግሌዎችን ስብዕና፣ ስምና ዝና ከማጉደፍ መቆጠብና እነዚህን ከመሳሰሉ እንደ ነውር ከሚታዩ ምግባሮች መራቅ ናቸው።

ይህን ከተገነዘብን በመጨረሻ ልብ ማለት የሚያስፈልገው መንግሥታዊም ሆኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሀገራችን የሽምግልና መርሆዎችን፣ የአሠራር መንገዶችንና ደረጃዎችን አስመልክቶ የሚያስተላልፏቸው ዜናዎች፣ የሚያቀርቧቸው ውይይቶች፣ ሀሳቦችና አስተያየቶች ከዘመን ወደዘመን ትውልዶችን አቋርጦ እየዳበረና እየበለፀገ የመጣውን ባህላዊ ተቋም ድንቅ እሴቶች አክብሮት የሚቸሩ፣ የሚያበረታቱ፣ የሚያጠናክሩና ከተቻለም የሚያዘምኑ፣ ለእድገታችንም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ነው።

ከዚህ በተቃራኒ በሰሞኑ እንደተስተዋለው አራምባና ቆቦ በመርገጥ የሽማግልናን ቅዱስ ተግባርና ሁላችንም በወል የምንገለጽበትን ትውፊት አቅልሎ በመረዳት ወይም በመተርጎም ከአፍራሽ ሚና መራቅ ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። እንዲህ ያለው ሥልጡንነትን ወይም ‘ዘመናዊነትን’ ይገልፃል ከተባለም ማርሻል ቤርማን በምፀት

“ዘመናዊ መሆን ኃይልን፣ ደስታን፣ እድገትን፣ ለውጥን ያመጣልናል በሚል ተስፋ ራሳችንንና ዓለማችን የምናገኝበት ሁኔታ እና፣ በተመሳሳይ ጊዜም ያለንን ማንኛውንም ነገር፣ ማንኛውንም የምናውቀውን ሁሉ፣ ማንኛውንም እኛነታችንን የሚገልፀውን ነገር ሁሉ የሚያወድም ማለት ነው” ሲል የገለፀውን ሆኖ መገኘትን ልብ ይሏል።

በመጨረሻም ለማጠቃለል ያህል ሀገራችን በረዥም ዘመናት በታሪክ፣ በባህልና በማህበረሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ በመምጣት እነሆ የዛሬው ‘ዘመናዊ’ ትውልድ የተረከበው፣ ለተተኪው ትውልድም የራሱን ልምድ ጨምሮ፣ ከተቻለም አሻሽሎ፣ ሊያስረክበው የሚገባ ድንቅና አኩሪ ትውፊት (ውርስ-ቅርስ)ነው። ዋልተር ጄ ፊሊፕ እንደሚለው

“የሰላምና የማህበራዊ ደኅንነት ምሰሶው ትውፊትነው”‘

‘ዘመናዊነት’ ባለፉት ዘመናት በተግባር እየተፈተነና እየካበተ የመጣን የሰው ልጅ እውቀትና ተሞክሮ መሠረት ካላደረገ በስተቀር እድገትን መመኘት “ላም አለኝ በሰማይ” እንደሚባለው ይሆናል። ፍሬድሪክ ኒቼ ይህን በሚመለከት ጆሴ አንድሬስ ፑርታ እንዲህ ይላል፡-

“ያለፈው ዘመን ዘመናዊነት፣ የዛሬው ዘመን ትውፊት ይሆናል፤ የዛሬው ዘመን ዘመናዊነት ደግሞ የመጭው ዘመን ትውፊት ይሆናል”

ይህ ትውፊትን ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ማጣጣም ግድመሆኑን ያመለክታል። በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛው በባህላዊ ገጽታዎች በሚገለፁ የአፍሪካ ህብረተሰቦች (ሀገሮች) ትውፊትን በ‘ዘመናዊነት’ ለመተካት መታከት ከጥቅሙ ይልቅ ኪሣራው እጅግ በጣም ከባድ መሆኑ ከልምድ የተስተዋለ ጉዳይ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top