ስነልቦና

የሕግ ስህተት እና ስነልቡና

“ቅጣት ለሰው ልጅ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ነው። አከራክሮ ብቻ ሳያበቃ ተጨማሪ ጥያቄ ይወልዳል። “ቅጣት ራሱ ምንድነው?”፣ “እንዴት መከወንስ ይገባዋል?” መልሱ እንደ ጥያቄው አይቀልም። በየራሳቸው ጽንፍ በቆሙ የሐሳብ መንገዶች ያስጉዛል። ጽንፎቹ እንደቆሙበት ፍልስፍና ብዙ ሊያባብሉ የሚችሉ አሳማኝ ምክንያቶችን ያዘሉ አስተሳሰቦች ናቸው። ከስነልቦናዊ፣ ከማኅበራዊ፣ ከፍልስፍና፣ ከሃይማኖት፣ ከሕግ፣… ስርአተ-አስተሳሰቦች አንጻራዊ ምልከታ በልዩ ልዩ መልኮች ልዩ ልዩ ምላሾችን ይወልዳሉ።

የሰው ልጅ በምድር ላይ ላጠፋው ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቀው ሃይማኖቶች ይሰብካሉ። የፍልስፍናው መንገድ ደግሞ ጥፋት እና ትክክል የሚባለው ‹ብያኔ› ከየት መነጨ ሲል ስሩን ይፈትሻል። ማኅበራዊው አስተሳሰብ የማኅበረሰብ ደህንነትን ያስቀድማል፤ የሕግ አስተሳሰብ ሁሉንም የሚያግባባ የማይጣስ ደንብን አስፈላጊነትን አጽንኦት ይሰጣል፤… ሁሉም እንደየቁመናቸው የራሳቸውን አቋም ይሰብካሉ።

ልጅነት

እንደኛ ያለው ማህበረሰብ በአብዛኛው ሰው የቅጣትን አስፈላጊነት አምኖ ያደገ እና ባፈራው ትውልድ ላይም የሚተገብር ነው። አታድርግ የተባለውን በማድረጉ ወይም አድርግ የተባለውን ባለማድረጉ ቅጣት ያልደረሰበት የለም ማለት ይቻላል። ከቁጣ እስከ ግርፊያ፣ ከቤት ውስጥ መጫወቻ ንጥቂያ እስከ ጉዞና መዝናኛ ክልከላ፣ እንደሚገዙ ቃል የተገቡ ነገሮች ስረዛ፣ ከፋ ሲልም በርበሬ ማጠንና አስሮ መግረፍ ድረስ ቅጣት ይፈጸማል። ቅጣቱ ተመጣጣኝ ነው ወይስ አይደልም? ተመጣጣኝ ቅጣት ማለት ራሱ ምን ማለት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለጊዜው እንዝለላቸውና እንደቤተሰቡ የልጅ የአስተዳደግ የአቀጣጥ ባህልና ዘይቤ ሁላችንም ቅጣት መቀበላችንን እንደጋራ ታሪክና ትዝታችን ወስደን እንቀጥል።

ሳያጠፉ መቀጣትም አለ። ታላላቆቻችን ወይም ሌሎች ባጠፉት እኛ ተቀጥተናል። “ከተናገርክ(ሽ) ዋ!” በሚል የአጥፊ ማስፈራሪያ የማስረዳት አቅሙን አጥተን፣ ወይም በተመሳሳይ ሰበቦች የሌሎችን ቀንበር የመሸከም እጣው ወድቆብን ይሆናል።

ብዙዎች እንደሚስማሙት የቅጣት ዓላማው ሰውን ከስህተቱ ማረም (ማስተካከል) ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መቀጣጫ ማድረግ ነው። ልጅነቱ ላይ በአግባቡ የተቀጣ ህጻን ጥፋቱን ከእርምት ጋር አግባብቶ የሚቀል ስብዕና ሲያጎድለብት፣ (ማለትም፡- ተቀጪው ሕጻን ማጥፋቱን ተቀብሎ፣ ቅጣቱ ከጥላቻ ያልመነጨ መሆኑ ገብቶት፣ በቅጣቱ ከእልህና ደግሞ ማጥፋት ይልቅ ትምህርት ወስዶበት… ሲሆን) ያልተጎዳ ስብእናንና ስህተትን ተቀብሎ የማረም አስተሳሰብን ይዞ ያድጋል።

በተቃራኒው በሁሉም ጥፋቶቹ የበታችነትና አላዋቂነት እንዲሰማው ተደርጎ ተመጣጣኝ ባልሆነ እና ለሁሉም ጥፋቱ በተደጋጋሚ ሲቀጣ ያደገ ህጻን ሁለት ተቃራኒ ባህሪያትን ይዞ ያድጋል። አንደኛው ቅጣቱን ከመልመዱ የተነሳ በማጥፋቱ ይገፋበታል። ማጥፋትን ከመተው (እርምት ከመውሰድ) ይልቅ ቅጣቱን መቋቋም የሚችልበትን መላ ይዘይዳል። ካልሆነም እጅግ ፈሪ፣ በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ መተማመን የጎደለው ይሆናል። ምንም ዓይነት አስተያየት መስማት የማይፈልግ፣ ልክ ያልሆነ ስራውን ዓለም ሁሉ እንዲያሞግስለት የሚጠብቅ፣… በጥቅሉ ግብዝ የመሆን እድልም አለው። ስለምንም ነገር ጥገኛ የሆነ ሰው ሊሆንም ይችላል። ቅጣት አንድ ቢሆንም የሚያሳድረው ተጽእኖ ግን እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ፣ እንደቅጣቱ አካሄድና ተደጋጋሚነት፣ እንደተቀጪው አረዳድና ትርጓሜ፣ ልዩ ልዩ ነው።

የአዋቂነት ቅጣት

የአዋቂነት ዘመን ቅጣት ከልጅነቱ ጋር የዓላማ ተመሳሳይነት ቢኖረውም ፍጹም አንድ ዓይነት አይደለም። የልጅነት ቅጣት በአመዛኙ ማረቅና ማስተካከል ላይ ሙሉ ትኩረቱን ይሰጣል። የአዋቂነት ዘመን ቅጣት ግን በአብዛኛው ተበዳዮች ፍትሕና እንዲህ አይነቱ ብህልም ሆነ አስተሳሰብ እንዲታረምም ነው። ዋናው ነገር እድሜው ሳይሆን፤ ልክ ያልሆነው ባህርይ መታረም እንዳለበት ነው። እንዲያገኙና ሌሎች ሰዎች ወደ ተመሳሳይ ቅጣት እንዳይገቡ መቀጣጫ ማድረግ ላይ ያተኩራሉ። ማስረጃዎች ተመሳክረው፣ ግራ ቀኙ ተከራክረው፣… የሚወሰነው ብይን አጥፊን ነጻ ሊያወጣ፣ ተበዳይን ላይክስ፣… የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እውነት በማስረጃ መረጋገጥ ካልቻለች በልብ መኖሯ ብቻ በቂ አይሆንም።

ቅጣት በአዋቂ ወይም ከ18 ዓመት በላይ በሆነ ሰው ላይ ሲፈጸም፤ ከላይ በልጅነት ላይ የተጠቀሰው ትርጉሙ እንዳለ ሆኖ ፀፀትን፣ ራስን መውቀስን፣ ስለወደፊት ማሰብ መቸገርን፣ ዓላማ የለሽ ስሜትን፣ ስለራስ ጥሩ አስተሳሰብ ማጣትን፣ ራስን መጥላትንና የመሳሰሉ ስሜቶችንም ይፈጥራል።

ቅጣትን መቀበል በጥፋትና ያለ ጥፋት ሲሆንም ይለያል። ያለጥፋት መቀጣት አጠቃላይ ስለህይወት ስለመኖርና አለመኖር ያለን ዕይታ ያጨልማል። ተስፋ ያሳጣል፣ ለብዙ አካላዊና አዕምሮአዊ ጤና እክሎች በከፍተኛ ሁኔታ ይዳርጋል።

የሰው ልጅ አዕምሮ በጎ ሐሳቦችን ለማምረት፣ ቀና አስተሳሰቦችን ለመቀመር፣ ጥሬ እቃዎቹ የተመረጡ መሆን ይገባቸዋል። ያልተዘራበትን ሊያበቅል አይችልም። እሾህ ተዘርቶ ጣፋጭ ፍሬ እንደማይጠበቅ ሁሉ፤ የምናየው፣ የምንሰማው፣ የምንውልበት፣ የምናመሽበት፣ የምናደርጋቸው ድርጊቶች፣ ስሜታችንን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችንን ይወስናሉ።

እንደማንበብ፣ ከሌሎች ጋር ሃሳብ መለዋወጥ፣ መደናነቅ፣ በቀና መንፈስ መተቻቸት (ስህተትን መተራረም)፣ የጋራ ስራዎች ማከናወን (በሙያ ዙሪያ መመካከር) እና ሌሎችም አእምሮ ብርሃናማ ሐሳቦችን እንዲያመነጭ የሚያግዙት ግብአቶች ናቸው። እነዚህ የተጠቀሱ ክንውኖች ግን ለሁሉም ታራሚ የተፈቀዱና የሚዘወተሩ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ለሁኔታው የተመቸ ገጽታ ላይኖራቸውም ይችላል።

በዚህ አረዳድ አንድ ታራሚ ወይም እስረኛ ረዘም ያለ ጊዜውን በብቸኝነት ወይም ተስፋ በማይሰጥ ሁነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲያሳልፍ አዕምሮው መመገብ ያቆማል፤ ወይም ምግቡ ይቀየራል። ከተስፋ ይልቅ ተስፋ መቁረጥ፣ በጥሩነት ከሚገኝ ሽልማት ይልቅ በብልጣብልጥነት የሚገኝ ክብር በልጠው ህሊናውን ይሞግታሉ። አንዳንዴም በአካልና በአዕምሮ ያሉ መግባባቶች በተቃራኒያቸው ይተካሉ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታን ያሳለፈ ሰው ከሚገጥሙት ስነ-ልቦናዊና ስነ-አዕምሮዊ ህመሞች አንዱ ለከፍተኛ ድባቴ መጋለጥ ነው። ያን ጊዜ መብላት ፈልጎ እጁ አልታዘዝ ይለዋል። ማሰብ ፈልጎ አዕምሮው አልገባ ይለዋል። የማስታወስና ትኩረት የማድረግ እክል ይገጥመዋል። መተኛት ፈልጎ ወገቡ ይደርቃል። ሁሉም ነገር የሚረብሸው ይሆናል። መናገር ፈልጎ አንደበቱ ይከዳዋል። በቀላሉ ሊከውናቸው የሚችሉ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች ይሳኑታል። ከዚህ በላይ ህመም አለ? አለመግባባትና መለያየት አለ? ምላሹን ለየራሳችን እንስጥ

የዓለም ተሞክሮ

ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ካገላበጥኳቸው ጥናቶች መካከል ኤሪክ የተባለ ሰው ገጠመኝ አንዱ ነው። ኤሪክ የ17 ዓመት ወጣት እያለ የክፍል ጓደኛው የነበረችን የአምባሳደርን ልጅ ገድለሃል በሚል ይጠረጠራል። ፍርድቤትም ጥፋተኛ ብሎ 41 ዓመት እስር ይፈርድበታል። ከዓመታት እስር በኋላ ግን ንጹህ መሆኑ ይረጋገጣል።

“አሁን 48 ዓመቴ ነው፣ ማግባት እፈልግ ነበር፣ ትምህርቴን ጨርሼ የራሴ ስራና ኑሮ እንዲኖረኝ እጓጓና እመኝ ነበር፣ ነገር ግን አሁን ከማቀዝቀዣ እንኳ ምግብ አውጥቶ መብላት የሚያቅተኝ፣ ሱቅ ሄጄ እቃ ገዝቼ መምጣት የሚሳነኝ፣ የመኖር ፍላጎቴ ህልም ሆኖ የቀረ እስኪመሥለኝ ከብዶኛል። ዓይኔ ብርሃን ሲያይ ያነባል፣ ፍርሃት ይሰማኛል፣ ሰፊው አልጋ ላይ ዘና ብዬ መተኛት ፈልጌ ጫፉ ላይ ተኮራምቼ ራሴን አገኘዋለሁ፣ የሚታሰበኝ መሞት የተሻለ እንደሆነ ነው። ሁለት ጊዜ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬም ነበር የተረፍኩባቸውን አጋጣሚዎች እጠላቸዋለሁ።”

የተሳሳተ ቅጣት የሚወልደው እስር፤ እስሩን ተከትሎ የሚኖር መገለል ደግሞ ሌላው ስነልቦናን የሚያሳምም ድርጊት ነው። በደረሰዉ ጉዳት ላይ ከማህበረሰቡ የሚሰነዘሩ አግላይ ቃላት እና ድርጊቶች፣ መጠሪያዎች (ቅጽል ስሞች)፣ ጥላቻዎች ናቸው።

ታስሮ የተፈታን ሰው ያለጥፋቱ ፍርዱን ጨርሶ እንደወጣና ስሙ እንደጠፋ ማን ያውቃል? የስራ እድል ልፍጠርለት ወይም ልቅጠረው ብሎ ሊያስብ የሚችልስ ስንቱ ነው?! የፍቅር ጥያቄውን ብቀበል ጥሩ ህይወት መኖር እንችላለን ብሎ የሚቀበልና ትዳር የመመሥረት ፍላጎት ያለውስ ምን ያህሉ ነው?!

ሌላኛው ገጠመኝ ከካሊፎርኒያ የተገኘ ነው። 20 ዓመታትን በእስር እንዲቆይ የተፈረደበት መምህር 13 ዓመታትን በማስተማር ልምድ አለው። ፍርድቤቱ ጥፋተኛ ያለው የሚያስጠናትን ልጅ ደፍሯል በሚል በወላጆቿ የቀረበለትን ክስ መርምሮ ነው።

ጄፍ ጥፋተኛ አለመሆኑ ከዓመታት በኋላ ቢረጋገጥም ከማኅበረሰቡ ጋር የተቀላቀለው ከነቅሬታው ነው።

“መጨረሻ ላይ ነፃ ነህ ተብዬ ስፈታ ያኔ ደፍሯል ተብዬ በየአደባባዩና ሚዲያው ፎቶዬን ሲለጥፋና ክብሬን፣ ሰሜን ሲያጠለሰሹ የነበሩት የተፈታሁ ዕለት መጥተው ስህተት ነበር ብለው አልዘገቡም፣ ይቅርታም አልጠየቁኝም፣ በዚህም የተነሳ የሚያድጉ ህፃናት አዕምሮ ውስጥ ‘ደፋሪው ሰውዬ’ ተደርጌ ሲያዩኝ እየጠቆሙ እንዲሸሹኝ ሆኗል። አንድ ጊዜ ሱፐር ማርኬት ሄጄ የምገዛውን ዕያየሁ እያለ ዞር ስል አጠገቤ የነበረች ልጅ የያዘች ሴት ልጇን በፍጥነት ካጠገቤ እያሸሸች ያ በቲቪ ያየነው ያ ደፋ*… እያለች ወጣች።

ያለጥፋቴ የታሰርኩ ቢሆንም፣ መፈታቴን ጠላሁ፣ ስራ ለመቀጠር ራሱ አልቻልኩም፣ አንዴ የወንድሜ ሬስቶራንት ውስጥ ተቀጥሬ መስራት እንደጀመርኩ ደንበኞች ፊታቸው ሲቀየርና ሌላ አስተናጋጅ ሲጠሩ ዐይቻለሁ፣ ትዳሬ በመታሰሬ ምክንያት ሲበተን ዐይቻለሁ፣ ብዙ መዘበራረቅ ውስጥ ነኝ፣ ከዚህ በኋላ ብዙ ችግር እንደሚገጥመኝና መኖር እንደሚከብደኝ ይሰማኛል” ይላል።

ከነዚህ ታሪኮች ብዙ መገንዘብ ይቻላል። አንዳንዴ ስነ-ልቡናዊ ህክምናም የማይመልሳቸው ችግሮች እንዳሉ፣ ካሳ የማይክሳቸው ክስተቶች እንደሆኑ የጉዳዩን ከባድነት ያስረዳል።

በሃገራችንስ

ለምሳሌ ያህል ከላይ ያሉትን አነሳን እንጂ በየጊዜው ብዙ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ክስተቶች በየሀገራቱ፣ በየጤና ተቋማት፣ በየጥናት ተቋማቱና ማረሚያ ቤቶች እንዳሉ መረጃዎች ያስረዱናል። ነገር ግን የሚከራከርላቸው ተቋምና ሰው ያላቸው ናቸው፤ ዘግይቶም ቢሆን ነፃ መሆናቸውን የሚያስመሰክርላቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ፈጣሪና፣ ግለሰቡ፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ ቢያውቅም በብዙ ምክንያቶች እስከመጨረሻው ተከራክሮ ነፃ እንደሆኑ የሚያስፈርድና ካሳ እንዲያገኙ እንኳ የሚያደርግ ሁኔታም፤ የሕግ ማዕቀፍም የለም። ይህ ጉዳቱን ማንም የማያድነው ያደርገዋል። ምን ያህል በስህተት ተፈርዶባቸው የተጎዱ ሰዎችን መጠን የሚያስረዳ እንኳ መረጃ ስለሌለ አስቸጋሪ ጠባሳ ይሆናል። ነገር ግን የስነ-ልቦና ህክምና ተቋማት ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙዎቹ የህመም ምክንያቶች በስህተት መታሰር ያመጣቸው ውስብስብ ችግሮች ናቸው። ይህም ሆኖ ለህክምና የመጡትን እንጂ በየሜዳው ታመው የሚያግዛቸውና የሚያሳክማቸው አጥተው የቀሩትን፤ የት እንዳሉ የማይታወቁትን፣ ግን አያካትትም።

ከሌላው ሀገራት የሚለየን ስህተቱን ሳንሰራ ቀርተን ሳይሆን፤ በስህተት እንኳ እንደሆነ ቢታወቅም፤ የይቅርታ ወይም ካሳ የመስጠት ሲስተም (አሰራር) አለመኖሩ ነው። (የካሳ ጉዳይ እየረቀቀ ባለው አዲሱ ሕግ ላይ እንደተካተተ ከሕግ አማካሪዬ ሰምቻለሁ) በስህተት ስለመፈረዱና ነፃ ስለመሆናቸው የሚከራከር ገለልተኛ ተቋም አለመኖሩ ነው።

ግን ግን የሆነውስ ሆነና፤ ለእንዲህ ዓይነት ስህተት ተጠቂዎች ካሳ ያክማቸዋል?! በየቀን ተቀን ህይወታቸው ውስጥ እያንዳንዱን የሚፈጠርን ጥሩም ይሁን ያልሆነ የህይወት ክስተት መተካት ይችላልን?! በራስ ጥሮ ግሮ የሚገኝን ሻይ የመጠጣትን ያህል ደስታ ይሰጣልን?! ትዳር ለማግኘት አንዱን ካንዱ የመምረጥን ሰዋዊነት ሊሠጥስ ይችላልን?!

ያለጥፋት መታሰር የሚያመጣቸው ጉዳቶች

ባላጠፉት ጥፋት የዕድሜ ቀበኛ ለሆነ እስር መጋለጥን ማን ያክማል? ለተበከሉ፣ ለባከኑ ስሜቶች እንደገና መፍጠር ይችላልን?! ሳያጠፉ መታሠር ምን ዓይነት ማህበራዊ ችግር እንደሚያመጣ 3 ነጥቦችን ላንሳ:-

  1. የተበቃይነት ስሜት እና አስተሳሰብ

ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስነልቦናቸው የተጎዳ ነው። ብዙ ጊዜ የከፋ በቀል ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። አንዳንዴም የሚበቀሉትን ሰው ላይመርጡ ወይም ያኔ ለእስር የዳረጋቸውን ላይሆን ይችላል። የበቀሉ ደረጃና ዓይነትም ከባድ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ መድፈር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል፣ መዝረፍ፣ ሌሎች ውስብስብ የበቀልና ወንጀል ዓይነቶችን እንዲፋጽሙ ያደርጋቸዋል።

2. ኢኮኖሚ

ለምሳሌ ይህ ጉዳት የደረሠበት ሰው ቤተሰብ ያስተዳድር የነበረ እና ኃላፊነት ሥራ ላይ ያነበረ ከሆነ፤ እንደ ሀገር በአንድ አራተኛ ምከንያት ይገኝ የነበረው ኢኮኖሚ ይጎድላል። እንደ ቤተሰብ ደግሞ ቤተሰብ ይበተናል።

3. አዕምሮዊና ስነልቦናዊ ህመሞች ይበራከታሉ።

ማስረጃ እና ምስክር

በስህተት የመታሰር ምክንያት ብዙ ነው፣ አንዳንዴም ውስብብስብና ረቂቅ ነው፣ ተፈፀመ እንደተባለው ወንጀል ዓይነት ቢለያይም የፎረንሲክ ሳይኮሎጂው ከሚጠቅሳቸው ነጥቦች ጥቂት ላንሳ።

  1. የግል ችግርና ስነልቦና

ለምሳሌ በከፍተኛ የራስ-ወዳድነት ችግር ውስጥ ያለ ከሆነና፤ የሚያገኘው ጥቅም የሚበልጥ ከሆነ፤ በሐሰት መመሰክር የሚያስፈራው ወይም የሚረብሸው ላይሆን ይችላል።

2. የስሜት ብስለት

ነገሩ ሲፈፀም ሲያይ መደናገጡና መረበሹ እንደሰው መፈጠሩ ባይቀረም፤ ማመጣጠን አለመቻልና በተምታታ ስሜት ውስጥ የሚቆይ ከሆነ፤ ነገሩን የማስታወስና የማስረዳት ችሎታው ስለሚቀንስ የመሰለውን ይመሰክራል።

3. የመስካሪው አመለካከት

ነገሩ ሲፈጠር ቢያይም ግፊቶች ካሉበት፣ ለህሊናውና ለእውነት ታማኝ ካልሆነ በግድየለሽነት በሐሰት ሊመሰክር ይችላል።

4. የመረጃ ተአማኒነት

አንዳንዴ ወንጀሉን የፈፀሙት ሰዎች ከሳሽ ሆነው ይገኛሉ። ስለዚህ መረጃዎችን ማጥፋት ወንጀሉን ላልፈፀመውና ተጠርጣሪ ተብሎ የተያዘውን ሰው፤ እንደፈፀመው ተደርገው መረጃዎች በረጅም እጅ ተቀናብረው ይቀርባሉ።

5. የሂደቱ ደካማነት

ውጭ ሃገር የተገኙት መረጃዎች ሁሉ ተመርምረው ካልበቋቸው፤ እንደ ፖሌግራፍ፣ ዲኤንኤ ዓይነት ምርመራዎችን ያደርጋሉ። ተጠርጣሪ የተባለውን በተለያየ አቀራረብና ዘዴ ይመረምራሉ ትክክለኛውም ይገኛል። ነገር ግን የምርመራው ሂደት ውስንነት ካለበትና የጠበቃው ክህሎት ማነስ ካለበት፤ ሂደቱ እንዲጎተትና ላልሰራው ወንጀል እንዲፈረድበት ይዳርጋል።

መደምደሚያ

እንደማህበረሰብ እና እንደግለሰብ፤ እንዲህ ዓይነት ስህተቶች እንዳይፈጠሩ፣ በሞራልና ስነምግባር መጠንከር፤ ከሙስናና የተበላሹ ሕጋዊ ሂደቶች የፀዳ የሕግ ሲስተም(አሰራር) እንዲኖረን እመኛለሁ። ጥረት እንደሚያስፈልግም እመክራለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top