መጽሐፍ ዳሰሳ

ከጥቁር ሰማይ ስር

ርዕስ . . . . . . .. . ከጥቁር ሰማይ ስር

ደራሲ . . . . . . . . እንዳለጌታ ከበደ

የመጀመሪያ ሕትመት. . . 1996 ዓ.ም.

ዘውግ. . . . . . . . . አጫጭር ልቦለዶች

የገጽ ብዛት. . . . . . .139

መጽሐፉ በተለያዩ አጫጭር ከእውኑ ዓለም በተወሰዱና ልቦለዳዊ በሆኑ ታሪኮች የተቀነባበረ፤ ለአንባቢው ምስል እየፈጠሩ በሚጓዙ ድርሰቶች ያሸበረቀ ነው። አሥራ ስድስት አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተው ይህ መጽሐፍ፤ በውስጡ ያሉት ታሪኮች መጨረሻቸው ላይ እኛን አንባቢዎቹን ቀጣይ ታሪካቸው እያጓጓን ልባችንን አንጠልጥለው የሚሄዱ፤ ተጀምረው እስከሚጨረሱ ድረስ ያላቸው የገፀባህርያት አወቃቀር ሳቢነትም አብሯቸው የሚዘልቅ ነው። ለምሳሌ፡- ደራሲው በዚህ መጽሐፍ ላይ ያሰፈራቸው ታሪኮች በተለይ በማኅበረሰባችን ውስጥ ጎልተው የምናያቸውን ፍፃሜዎችና የሚተገበሩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው። በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት አሥራ ስድስት ርዕሶች በተጓዳኝ ታሪኮቹን በአጭሩ የሚያሳዩ ገለጭ የካርቱን ስዕሎች ተካተዋል። ለምሳሌ ምጣዱ

ምጣዱ

ምጣዱ በተሰኘው አጭር ልቦለድ ላይ እርቃኗን አልጋዋ ላይ እንጀራ የምትጋግር ሴት ምስል ይታያል። ይህ የሆነበትን ምክንያትም የልቦለዱን የመጀመሪያ አናቅጽት ስናነብ በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን።

“ከርቀት… አንድ ሰባኪ ድምጹን እያስጮኸ የመዝጊያ ጸሎት ሲያካሂድ ይሰማታል። ‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ…› … ‹አሜን› አለች ፈገግ ብላ። አልጋዋን አየችው፤ የዕለት እንጀራዋን የምትጋግርበት ምጣዷን።” (ገፅ 7)

ይህ ልቦለድ በጥናት እና በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዞ እንደተፃፈ ሆኖ እንደሚሰማን ያህል፤ በዚህ ምጣዱ በተሰኘው ርዕስ ስር ያለው ገፀ-ባህርይ ልክ መጽሐፉ ውስጥ እንደወረደ የተገለፀው ሰው፤ አማቹ ችግር ሆነውበት ከሚስቱ ጋር መገናኘት ስላልቻለ በምትኩ በገንዘቡ ከሴት ጋር ለማደር ፍላጎት ያደረበት ይመስለናል።

አንዳንዴ ደግሞ ሰውየው ከልጅቷ ቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ እስኪወጣ ድረስ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያጣደፈ ሲጠይቃት ይታያል። “እንዴ! ሰውየው የመጽሐፉ ደራሲ ነው እንዴ!” ለማለት እንገደዳለን። ምክንያቱም አብሯት ሳይተኛ ታሪኳን አስቃኝቶናልና ነው። አገባቡ ጥናት ለማድረግ ይመስልበታል።

የበእውቀቱ ስዮም የስዕል ስራ ወደሆነችው ገላጭ ምስል እንመለስ። ስጋዋን በመሸጥ የምትተዳደረው ወጣት ገንዘብ ከፍሏት አብሯት ያደረው ሰው “ጠባብ ቤት ከመኖር ለምን ሆቴል ገብተሸ የተሻለ ብር እየተከፈለሽ አትሰሪም” ሲላት፤ እሷም በልቧ እንዲህ ትለዋለች።

“ይህንን ቤት የምለቅቀው ይመስልሃል? አላደርገውም። የምፈልገውን ወንድ ወደምገኝበት አስመጣዋለሁ እንጂ!… አውቃለሁ ቤቴ ጠባብ ናት- ሁለት አልጋ አታስዘረጋም። ቢሆንም ለኔ ትሰፋኛለች። እናቴ የወለደችኝ ዕለት የሞተችበት ክፍል እንደሆነ ብነግርህስ ምን ይሰማህ ይሆን?” ትለዋለች።

በሃሳቧም ቢሆን ከሰጠችው መልስ ለመረዳት እንደምንችለው፤ ሙሉ ህይወቷን የእኔ የምትለው የቅርብ ሰው የሌላት ይህች ገፀባህሪ፤ ሁሌም ቢሆን ከጎኗ ሳይለይ እድሜዋን ሙሉ ያኖሯት አሁን የምትኖርበት ቤቷ ብቻ ነው። ስለዚህ ከቤቷ ጋር ልዩ የሆነ ትስስር ቢኖራት ሊገርመን አይገባም። ከሁሉም በላይ አልጋው ላይ እሷ የተወለደችበት፣ እናቷ የሞተችበት እና ልጅቷ አሁን የምትተዳደርበት የገንዘብ ምንጭ ነው። በዐይኗ ዐይታት የማታውቃት የናቷ ትልቁ የማስታወሻ ስጦታ ነው። ለዚህም ነው ከርዕሱ በላይ ባለው ስዕል ራቁቷን የወጣች ሴት አልጋዋ ላይ እንጀራ ስትጋግር የምትታየው።

መጽሐፉ ሦስት ነገሮችን በአትኩሮት እንድመለከት ያስገድደናል። የመጀመርያው የሴት ልጅን መከራ ክብደት፣ ከመከራው ለመውጣት ስትል አንዳንዴ የመጨረሻ ተስፋዋ በማድረግ የተገኘችበትን እጅግ ርካሽ ስፍራ ወይም ተግባር ነው። ህይወቷን ለማቆዬት ወይም ልጇን ለማሳደግ እና ለማስተማር በምጻደርጔ መፍጨርጨር በአከባቢዋ ካለ ኅብረተ-ሰብ ጋር ያላት ግንኙነት፤ ሰዉ ራሱ እየተስተናገደባት መልሶ እንደሰው አለመመልከቱ ለእሷ እጅግ ጥልቅ የስነ-ልቦና ችግር ይፈጥርባታል። ሰው በሰው ላይ ምን ያህል እንደሚጨክን እናያለን፤

ሁለተኛው ለራስ ጥቅም ሲባል ተንኮል በሞላበት መንገድ አንዱ በሌላው ላይ ሲጨክን እንመለከታለን። የራስህን ህይወት ለማደላደል ስትል በሰውን ህይወት ምን ድረስ ትጨክናለህ?

ይሁዳ

ይሁዳ የተሰኘውን አጭር ልቦለድ እነመልከት። ይሁዳ የአልጋ ቁራኛ የሆነ ሰው ታሪክ ነው። የገዛ ጓደኛው በመተት ተብትቦ ከአልጋ ሲጥለው ራሱን ይሁዳ ነኝ ብሎ ያመነ ገጸ ባህርይ ነው። ባልጀራው ላይ ይህንን መጥፎ ተግባር ለመፈፀም ያስገደደው ዋና ምክንያት ፍቅር ነው። የምወዳትን ልጅ በእጄ እንዳላስገባ ወንድሟ እንቅፋት ይሆነኛል ብሎ በማሰብ ነው። ምንም እንኳ ስለ እቅዱ ስኬት እና ኪሳራ ከልብወለድ ታሪኩ ለማወቅ ባንችልም፤ የድርጊቱ ፈጻሚ ሐሳብ ወንድምየውን በዘዴ በማስወገድ ያፈቀራትን እህቱን የግሉ ማድረግ ነው።

በሦስተኛ እና የመጨሻው የሰው ልጅ በሀሳቡ ራሱ በፈጠረው ህይወት ከሌለው ከማይናገረው እና ከማይሞተው ተፈጥሮ ጋር ሲሟገት ወይም ራሱ ተፈጥሮን ጠይቆ ተፈጥሮ ደግሞ የተጠየቀችውን ጥያቄ ከነማስረጃው ስትመልስለት ማየቴን ነው። ይሁን እንጂ ይህ ነገር ተገጣጥሞሽ ነው። ምክንያቱም እኛ ህይወታዊያን በሀሳባችን ነገሮችን ማዛመድ እንችልበታለን። ለምሳሌ በድርሰቱ ውስጥ ያለችው ገፀ-ባህርይ ወይም ጨረቃ በተመስጦ እያዳመጣት ያለውን ፍጡር (የሰው ልጅ) ብዙ ነገር ትነግረዋለች። ሰማይ የምድር ዕጮኛ እንደሆነ፤ እስከዛሬ ድረስ አንድ ላይ ያልሆኑበት ምክንያትም ንፋስ በመሀከላቸው እየገባ ስለሚያጣላቸው እንደሆነ ትነግረዋለች። ምድር ላይ ያሉት ሁሉም ተራሮች የምድር ጡቶች እንደሆኑም ትነግረዋለች። ሰማይና ምድር የተፈጠሩበት ጊዜ ምንም እንኳ ረጅም ቢሆንም እስከ ዛሬ ግን ፍቅረኛሞች ናቸው እንጂ አልተጋቡም ትላለች። በዚህ “የዘውትር ፍቅረኛሞች” የተሰኘው አጭር ልቦለድ የታሪኩ መጨረሻ ላይ ጨረቃ ሰውዬውን እንዲህ ትለዋለች

“ወደ ወጣሁበት ከመግባቴ በፊት አንድ ጥያቄ እስቲ ልጠይቅህ? ከሰማይ አካል ወጥቶ የምድርን ገላ የሚያረሰርሰው የዘር ፍሬ እናንተ ሰዎች ምን ብላችሁ እንደምትጠሩት ልንገርህ?”

“ንገሪኝ”

“ዝናብ ትሉታላችሁ!” ብላው ተሰወረች።

እንግዲህ በዐይናችን የምናየውን ከሰማይ የሚወርደውን ዝናብ የዘር ፍሬ መሆኑ ነው። የደራሲው ዕይታ እጅግ የሚደነቅ ነው። ቅድም እንደጠቀስኩት ለብቻችን በምንሆንበት ጊዜ ከድብርት ለማምለጥ ስንል በሀሳባችን ከተፈጥሮ ጋር ልናወራ እንችላለን። በዚህች አጭር ልቦለድ ያለው ገፀ-ባህርይ እንኳ ብናይ፤

“ከጎኔ ማንም የለም። ማታ ነው። 2፡30። ቁጭ ብዬ አንጋጥጫለሁ። ቤቴ በረንዳ ላይ ነው ያለሁት። ብቻዬን ነኝ። ብቻዬን በጨረቃ ብርሃን ደምቄ ዕታያለሁ። ይቅርታ! ብቻዬን አይደለሁም። ከጨረቃ ጋር ነኝ። ከጨረቃ ጋር ወግ ይዤአለሁ። ባልተቀጣጠርንበት ጊዜ እና ቦታ አገኘኋት እና ለምትጠይቀኝ ሁሉ እመልሳለሁ።

በፈገግታ እንድዋብ የምታደርገኝንና ውድ የምትሆንብኝን ጨረቃ በመመሰጥ ሳዳምጣት ቆይቻለሁ።

እስኪ ከተፈጥሮ ምን እንደሚሰማህ አውጋኝ’ ብላ ጠየቀችኝ። የመለስኩላት መልስ የፈጠረባት ስሜት እስከ መቼውንም አልረሳውም” ይላል። ይህ የሆነበት ምክንያትም ጨረቃ ማለት ሁሉም የሚወዳት የተጋረደውን ጨለማ ገልጣ ብርሃን ስለምትሰጠን በጣም ስለምንወዳት ነው። ነገር ግን በብቸኝነት ጊዜያችን በምናባችን ከተፈጥሮ ጋር ልክ እንደምናወራው ዓይነት ደራሲውም እያዝናና ሊያሳምነን ሞክሯል።

ደራሲው ተፈጥሮን እያደነቀ ተፈጥሮ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ትይዩ በማዛመድ አተጫጭቷቸዋል። ደራሲው ለምን ወደ እንደዚህ ዓይነት ድርሰት ገባ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙዎች ተፈጥሮን ያደንቃሉ፤ ተፈጥሮ ሲባል ግን ስለ አንድ ተፈጥሮ ሳይሆን ስለተለያዩ ተፈጥሮዎች ነው። ለምሳሌ ጨረቃ በተፈጥሮ ውስጥ የምትካተት አካል ናት። የሰው ልጅን በብዙ ነገር ልትጠቅመው ትችላለች። በጨለማ ጊዜ እንደ ብርሃን ሆና ልታገለግለን ትችላለች። እንዲሁም ብቸኝነት በሚሰማን ጊዜ ብቸኝነታችንን ለማስወገድ ብለን ከቤት ውጭ ቁጭ ብለን ፊታችን ወደ ሰማይ አቅንተን ጨረቃን እያየን በሀሳባችን እያዋራናት እንመሰጥባታለን። የሰው ልጅ እና ጨረቃ እያወሩ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ የሰፈረውን አጭር ልቦለድ ድርሰት ስናይ እውነተኛ እና ሁሉም የሚያውቀው ታሪክ ስለሆነ አይደለም። ወይም ደግሞ ሰማይና ምድር ባልና ሚስት ስለሆኑ አይደለም። በአካላቸው ግን የተለያዩ ተፈጥሯአዊ ክስተቶች ይካሔዳሉ። እንዲሁም እኛን የሰው ልጆችን ጨምሮ የተለያዩ ህይወታውያን እና ህይወት የሌላቸው ነገሮችን አቅፈው ይኖራሉ።

ስያሜ

ከጥቁር ሰማይ ስር በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት አስራ ስድስት አጫጭር ልብወለዶች ውስጥ “ከጥቁረ ሰማይ ስር” የሚለው ልብወለዱ መጠሪያነት መመረጡ ትክክለኛ ምርጫ ነው። ምክንያቱም እነዚህ አሥራ ስድስት አጫጭር ልቦለዶች ምድር ላይ የሚፈፀሙት የተለያዩ ጉዳዮችን ስለሚያነሱ ነው። ደራሲው ክፋት፣ ርህራሄ፣ ፍቅር፣ ግጭት መነፋፈቅና ሌሎችን ጉዳዮች በውስጣችን እና በዙሪያችን እንዳሉ ውብ በሆነ የቃላት አጠቃቀም አስጊጦ ምን ዓይነት መልክ እና ባህርይ እንዳለን በሚገባ መልኩ በድርሰቱ በኩል አሳይቶናል። ነገር ግን “ከጥቁር ሰማይ ሥር” ማለት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ሁላችንም የየራሳችን ብያኔ እየሰጠን የተለያየ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን። ለምሳሌ በኔ እይታ ሲተነተን መጽሐፉን የፃፈው ደራሲ ጥቁር ነው፣ ፊደሎቹ የጥቁር ህዝቦች ወይም የኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ቋንቋውም እንዲሁ። ውስጡ ያለው ታሪክ የራሳችን እና በማህበረሰባችን ውስጥ የሚገኝ ታሪክ ነው። በአጠቃላይ ይህ ታሪክ የኢትዮጵያውያን ነው ብዬ ለመናገር የሚከለክለኝ የለም።

ሌሎች መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ “ከጥቁር ሰማይ ሥር” የሚለውን የመጽሐፏ ስያሜ በራሳቸው አገላለጽ “ከአፍሪካ ሰማይ ሥር” ለማለት ተፈልጎ ነው ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን ጥቁርነት የሁሉም አፍሪካዊያን መገለጫ እንኳን ቢሆንም፤ እኛ አፍሪካዊያን መልካችን ሊመሳሰል ይችላል። ባህርያችን፣ ተግባራችን፣ አኗኗራችን፣ አመጋገባችን፣ ቋንቋችን፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለን ተሳትፎ እና ከሌላው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት ግን ላይመሳሰል ይችላል።

ስለዚህ ከሞላ ጎደል በዚህ መጽሐፍ ሥር ያሉት ሁሉም ታሪኮች በኢትዮጵያዊያን የአኗኗር ዘዴ እና የሚካሄዱ ፍፃሜዎችን መሠረት ተደርገው የተፃፉ ድርሰቶች ናቸው የሚል ድምዳሜ ነው ያለኝ።

አቦቸር

ናትናኤል ሲሳይ

በአማርኛ በብዛት አጫጭር ልቦለዶችን በመጻፍ የሚታወቀው እንዳለጌታ ከበደ በርከት ያሉ ልቦለዶችን ለአንባቢ በማቅረብ የሚታወቅ ደራሲ ሲሆን፤ እኔ የተመለከትኩት አጭር ልቦለድ “ከጥቁር ሰማይ ሥር” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ “በሰንበት የተጸነሰው” የሚለውን ሲሆን፣ ከይዘት አኳያ እንደሚመለከተው ለማዬት ሞክሬያለሁ።

በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እጅግ ኃይማኖተኛ ወግ አጥባቂ ሀገራት ህዝቦች ዘንድ ሰንበት የተከበረ ቀን መሆኑ እሙን ነው። እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ በሰንበት ቀን እንኳንስ በሀጥያትነት የተፈረጁ ድርጊቶችን መፈጸም ይቅርና የትኛውንም ሥራ ማከናወን ያስኮንን ነበር። አሁንም ቢሆን ከዘመናዊነት ጋር ተያይዞ ነገሩ የለዘበ ይምሰል እንጂ ይህ አስተሳሰብ ጨርሶ አልጠፋም። ደራሲው ለልቦለዱ የመረጠለት ርዕስ ሊያስተላልፍ ካሰበው ጭብጥ ጋር ተመጋጋቢ ሆኖአል። በሀገራችን ፍልስፍና በሰንበት የተጸነሰ የረከሰ ነው። በዚህም ምክንያት “በሰንበት የተጸነሰ” ማለት እንደ አሸማቃቂ ስድብ ይቆጠራል። ይህንንም ስድብ የኔታ የተሰኙት ገፀ-ባህርይ በትንሹ አቦቸር ጭንቅላት ውስጥ በቀላሉ እንዳይነቀል አድርገው ደጋግመው ሲቸነክሩት እንመለከታለን። (በርግጥ አቦቸር እንዲህ አሉኝ ብሎ ለእናቱ ሲከሳቸው እንጂ እሳቸው በቀጥታ ሲሰድቡት ልቦለዱ ውስጥ አልተጠቀሰም። አቦቸርን በማመን ትንተናየን ልቀጥል።)

በመጽሐፉ ውስጥ የሚታዩት ገፀ-ባህርያት በገሀዱ ዓለም ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር እጅግ ተቀራራቢ ባህርይ ያላቸው በመሆኑ የምናነበው ታሪክ ልቦለድ መሆኑን እስክንዘነጋ ድረስ እንድንመሰጥ ያስገድደናል። የአቦቸር ጣፋጭ ኮልታፋ አንደበት የእያንዳንዳችን ልጅነት ከተኛበት የመቀስቀስ ኃይል አለው። የምንትዋብ እናታዊ እንስፍስፍነት የእናቶቻችንን ባህርይ ያስታውሰናል። የየኔታን ወሽካታነት እና ሰካራምነት ከቀረበ በአባቶቻችን እጅግ ከራቀም በጓደኞቻችንን አባቶች በኩል በደንብ እናውቀዋለን። በዚህም ምክንያት በልቦለዱ ውስጥ የተአማኒነት ጥያቄ እንዳይነሳ ያደርገዋል።

የጽሑፉ መልዕክት ስንመለከት፤ ልቦለዱ የማንነት ጥያቄዎችን በጉልህ ያንፀባርቃል። እኔ ማን ነኝ? እኔ የማን ነኝ? የሚሉ ጥያቄዎች አቦቸርን ሲያስጨንቁት ይስተዋላል። የአባቱን ስም ቢያውቅ ተማሪዎች አይስቁበትም ነበር፤ እናቱን ቢወድም በእናቱ ስም መጠራቱ ግን ዋጋ አስከፍሎታል። “የሴት ልጅ” አስብሎታል፣ በማህበረ-ሰቡ አስገልሎታል። (የሱ ማህበረ-ሰብ የቄስ ትምህርት ቤት ጓደኞቹ ናቸው።) ለአቦቸር አባት እንደ እቃ የሚገዛ እስኪመስለው ድረስ በልጅነት ልቦናው ሲያብሰለስለው ይታያል። “ለአልቤቾ ባል የለኝም ብለሽ አልቅሰሽ ካስለቀስሽው አባት አያስመጣልኝም?” እያለ እናቱን ይጠይቃል። ለአንድ ህፃን አባት የለሽ ሆኖ ማደግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ዓለማየሁ እሸቴ “ህይወቴ አባቴ ነው” በሚለው ዘፈኑ እንዲህ ይለናል።

ስዳደግ ቁንጥጫ ያላየው

የሚባለው ስድብ አባት ከሞተ ነው

ሌባ ወሮበላ ቀማኛ ዱርዬ

ሥራፈት ወስላታ ዟሪ ነው ተብዬ

ቁጥጥር ግልምጫ ፍፁም ያልጎበኘው

የሚባልም ስድብ አባት ከሞተ ነው።

ይህ ማህበራዊ ቀውስ በአቦቸር ብቻ ሳይወሰን ምንትዋብንም የገፈቱ ቀማሽ ሲያደርጋት እንመለከታለን። ጎሮቤቶቿ “ይሄ ከየትኛው ትቦ እንደፈሰሰ የማይታወቅ ቆሻሻ” እያሉ ያላትን ብቸኛ ሀብት፤ ልጁን ይሰድቡባታል። ይህ ስድብ ለአቦቸር የተሰነዘረ ቢመስልም አቦቸር ላይ የሚያርፈው ግን ስሙ ብቻ ነው። ወርቁ ዒላማ ያደረገው ምንትዋብን ይመስላል። ጋለሞታነቷን ሊነግሯት፣ ህመሟን እንዳትረሳው ሊያስታውሷት፣ ቁስሏን በእንጨታቸው ሊነኩባት።

ፍካሬ ስነ-ልቦና (phychoanalysis) የሚባለው የጥናት ዘርፍ እንደሚነግረን፤ በልጅነት ጊዜያችን የተከሰቱ ነገሮች ከብዙ ዘመናት በኋላ በአዋቂነት ዘመናችን ለምናደርጋቸው ድርጊቶች አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። መልካም እና አስደሳች ትውስታዎቻችን ደግሞ በአሉታዊ መልኩ ከዘመናት በኋላም ቢሆን ጥላቸውን ያጠላሉ። በተለይ መጥፎ ትዝታዎች በአእምሯችን ውስጥ ጠባሳን ትተው ስለሚያልፉ ከባድ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። ይህንን ጉዳይ ሳይንስ traumatical effect በሚል እውቅና ይሰጠዋል። ምንትዋብ በልጅነቷ ያሳለፈችው አሸማቃቂ የሆነ ህይወት የኃይማኖት ሰው ነኝ በሚሉት በአባቷ አፀያፊ ድርጊቶች ምክንያት እንደሆነ አትረሳም። እሷና ቤተሰቧ የሰው መጠቋቆሚያ የሆኑት በአባቷ ሰካራምነት፤ ሴሰኝነት እና ሌብነት መሆኑን ደራሲው በትውስታ መልክ ይነግረናል። ይህን የምንትዋብን ህይወት ከፍካሬ ሥነ-ልቦና (psychoanalysis) አንፃር ብንመለከተው፤ በእርግጥም የአባቷን ተፅዕኖ በህይወቷ ውስጥ በጉሉህ እናስተውላለን። ከነዛ ሁሉ ዓመታት በኋላ አእምሮዋ ውስጥ የቀሩት አባቷ የኃይማኖት ሰዎችን በጠቅላላ እንድትጠላ አድርጓታል። የኔታ ገ/መስቀል ላይ የወሰደችው እርምጃ ለዚህ ማሳያ መሆን ይችላል። የኔታን በማዋረድ ውስጥ አባቷን ስታዋርድ፣ አባቷን የመበቀል እልኋን ስትወጣ እንመለከታለን።

የአቦቸር አባቱን የማግኘት ጉጉት ከተሳካ በኋላ የኔታን ያየ አልተገኘም። የየኔታ ገ/መስቀል መሰወር metaphor (ልዋጭ) ሊሆን ይችላል። የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮን ለማመልከት ደራሲው ሆን ብሎ ተጠቅሞት ሊሆን ይችላል። የየኔታ መጥፋት ለምንትዋብ ከአባቷ ትዝታ መላቀቅን ሊያመለክት ይችላል። ለአቦቸር ደግሞ በአዲስ ማንነት መንቀሳቀስን፤ ማለትም “ከአቦቸር ምንትዋብነት” ወደ “አቦቸር ገ/መስቀልነት” የተቀየረ ማንነትን ይዞ አዲስ የህይወት ጎዳናን መጓዝ ሊሆን ይችላል። የአቦቸር ከቄስ ትምህርት ቤት ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መግባትም ለዚህ ተጨማሪ ማሳያ ይመስላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top