ስርሆተ ገፅ

የህይወት ዥንጉርጉር መልኮች

የመን ያለፍኩባቸውን መንገዶችና መስዋእትነቶችን ባትመጥንም ቆንጆ ጊዜ አሳልፌያለሁ፣ ህዝቦቿ ካየኋቸው ህዝቦች በሙሉ የሚከበር ባህልና ደግነት እንዳላቸው ተረድቻለሁ። የትኛውም ስደት የራሱ በጎ የሆነም ያልሆንም ቢኖረውም የኛ ኢትዮጵያውያን ከስደት መልስ ተረክ እንከኑን እያጠፉ መዐዛውን መቆስቆስ ነው።

ህይወት ዕፁብ ድንቅ ናት ሲባል “ምኗ” የሚል ይኖር ይሆን?

ካርታ ሲጫወት በትኩረትና በንቃት ነው። ከጨዋታው መሀል አረብኛ፣ አማርኛና ትግርኛ የሚችሉ ሠዎች ተሠይመዋል። በእጁ ሲጃራ የያዘ፣ ጫት እየቃመ ካርታዋን የሚመዝ፣ ቢራ እየተጎነጨ የሚስብ ሞልቷል፣ “ኮንከር”፣ “ሴካ”፣ “ቢዝነስ” ቤቱ ውስጥ ሞልተው የፈሰሱ ቃላት ናቸው። ከሞቀው የካርታ ጨዋታ እና ተጫዋቾች መሀከል “ተጫወት” የሚለኝ እርሱ ብቻ ነው፤ ደጋግሞ ስላሸነፈ “ቢራ ጠጣ” አለኝ። አዘዝኩ።

ስደት ላይ መደበሪያዬ ነበር አለኝ። አንዴ ወደ ካርታው አንዴ ወደኔ እየተመለከተ የስደቱን አልፋና ኦሜጋ ነገረኝ። ከሞት ጋር ትንቅንቅ ነበረበት፣ እርሷ መንደር ደርሶ የተመለሰበት አያሌ ጊዜ ግብግብ የገጠማት ሞት እርሱ እንደሚለው የሸወዳት “ኤልሻዳይ፣ ኤሎሄ፣ ክርስቶስ እየሱስ” ብሎ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም በሚሰጠው አምላኩ አማካኝነት ነው፤ እፍታ ጨዋታው ስላረካኝ ከካርታ ውጪ እንዴት እንደማገኘው ወጠንኩ። ጥቂት ለወጋችን መንደርደሪያ ያወጋኝ ነገር ነበር ህይወትን ዕፁብ ድንቅ ያስባለኝ። ታጠቅ ታደሰ አፍዝ አደንዝዝ አንደበት ሲኖረው

“ብዙዎች የሰው ሀገር ስለመኖር ይናገራሉ፣ ይተርካሉ፣ ይገልፃሉ። እኔ ግን ስደትን ገልጬ አሣይሀለሁ።” አለኝ። መጽሔት ላይ እንዴት እንደሚያሳየን አስቤ ፈገግ አልኩ። በሌላ ጊዜ ቀጠርኩት። ያለ ካርታ እንደሚያገኘኝ ቃል ገባልኝ።

ቃሉን ጠብቆ እንዳለው ተገናኘን፣ ስለ ሕገ ወጥ ስደት እንደሚነግረኝ በአለባበሱ ያስታውቃል። በሰኔ ሸሚዝ ለብሷል። ‘በረሀውን ሳቋርጥ እንዲህ ለብሼ ነበር ለማለት ይሆን?’ አልኩ ለራሴ። መቅረፀ ድምፄን አስተካከልኩ። ብዕሬን ቀለም አጠቀስኩ። ረዥም ዝምታ ሰፈነ። የጠጣውን ቡና መራራ ወዝ ከአፉ ለማጥፋት በሚያስመስል ሁናቴ ውሀውን ወደ ውስጥ ተጉመጠመጠ። ከዚያም በረዥሙ ተነፈሰና “ምን መሠለህ…” ብሎ ወጉን ጀመረ

ሳዋ

1990 ዓ.ም. ጥቅምት 2 አሰብ ነበርኩ። ከመላው ኤርትራ ወንድና ሴት ተለቅመን ሳዋ (ወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋም) ገባን፣ ለጦርነት ሰልጥኑ ስንባል “እኛ ኢትዮጲያዊያን ነን፤ ሀገራችንን ለመውጋት አንሰለጥንም” ስንላቸው ሻድሻይ ብርጌድ ከዛም ጆን ጋራንግ ወደሚባል የጦር ካምፕ ወስደው አሰሩን፤ ቦታው ስቃይ ነበረበት። ስቃጥላ የሚባል አሰልቺና ተደጋጋሚ ምግብ ከጥቂት ዳቦ ጋር እየተመገብን ኑሮን እንገፋለን። የስቃጥላው ተደጋጋሚነት ስላሰለቸኝ በርበሬ ቢለወስበት ጣፋጭ እንደሚሆን ገባኝ። በርበሬም ለኛ እሩቅ ስለሆነ ቃሪያ ብናገኝ አልኩ። አፈፃፀሙን ደጋግሜ አሰብኩ። አንድ ቀን አንዲት ቦቴ ታንከራችን ላይ ውሃ ለመገልበጥ ወደ ግቢያችን ገባች። እመር ብዬ ተነሣሁና ሾፌሩን ማገዝ ጀመርኩ። ሹፌሩ ለምን ታግዘኛለህ የሚል ጥያቄም ስላላነሳ ጎማ ፈተሽኩለት። መስታወት ወለወልኩ። ሠርቶ ሲጨርስ ጥቂት ገንዘብ “እንካ” አለኝ። “አልፈልግም!”ግራ በመጋባት “ታዲያ ምን ፈልገህ አገዝከኝ?” አለኝ።

አገልግሎቱን ነግሬው፤ ባቀበለኝ ገንዘብ ቃሪያ እንዲገዛልኝ ነገርኩት። አደረገው። ከዚያ በቃ የ5 ናቅፋ ቃሪያን በ39 ናቅፋ ቃሪያ እየሸጥኩ ትርፋማ ሆንኩ።

“ጉዕ በርበረ ዘይወአል ዘይሀደረ

ዝመፀ ካብ ደቀምሀረ”

(ቃሪያ ቃሪያ ያልዋለ ያላደረ

የመጣው ከደቀምሀረ)

እያልኩ ቀልብ-ሳቢ የቃሪያ ነጋዴ ሆንኩ።

እስር በኢትዮጵያ

ከኤርትራ ከተመለስን ቦሀላ በእኛና በኤርትራ መካከል የጦርነት ነጋሪት ተጎሰመ። ፕሮፖጋንዳው ከሁለቱም ሀገሮች የሚሰማው ስሜት ቆንጣጭ ቢሆንም የሀገሬን መወረር ስሰማና ሰልጥን ተብዬ እምቢታዬን የገለፅኩበትን ሳዋ ሳስብ እምባዬ ተናነቀኝ። የእምቢታዬን ትክክለኛነት ያረጋገጥኩት መወረራችን እንደተገለፀ ነው። ግን “ሳዋ ስለነበራችሁ ለኤርትራ የምትሰልሉበት ነገር የምታደሉበት ነገር” ተብለን በድጋሚ ሳዋ የታሰርን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከያለንበት ተለቃቅመን ታሰርን። በሁለቱ መንግሥታት አንዱ የአንዱ ነህ እየተባልን ብንታሠርም የያረጋል ገጠመኝ ግን ይለይብኛል።” አለኝ።

“ምኑ?” የኔ ጥያቄ ነበር።

ያረጋል

ያረጋል የጎጃም ሠው ሲሆን የሚወዳትን እንስት ተለይቶ ኤርትራ በውትድርና ታፍሶ ሄደ። በጦርነቱ በሻዕቢያ ተማርኮ ለ7 ዓመታት ታሰረ።

በዚህ ክፍተት ልጃቸው የት እንደወደቀባቸው ያላወቁት የያረጋል ቤተሰቦች ልጃቸውን ሲጠብቁ “አርፋል” የሚል መርዶ ተነገራቸው። እርማቸውን አወጡ። ሚስት “ባሌ አልሞተም። ደመ ነፍሴ ነግሮኛል” አለች። እናትና አባት “ሞቷአል” ሚስት ‘አለ’ እያሉ ሲቆዩ ሚስት በዚህ ሀሳቧ ከቀጠለች ማግባት እንደማትችል ስላወቁ ሌላ አግቢ ብለው ለመኑ። ሚስት “እሺ” ለማለት ብዙ ዓመታትን ፈጅታ ነበር። የሱ ቤተሰብ የመረጡላትን ወጣት ልታገባ የተደገሰ ዕለት ታዲያ ያረጋል ተከሰተ።

ሠርጉን የራሱ አድርጎ አዲስ ኑሮ ተጀመረ። ኑሮ በዳግም ጎጆዋ የሞቀላት እንስት ታዲያ እንደኔ በሻዕቢያ ታስረው የነበሩ እየታደኑ ሲለቀሙ ባልዋ ተወሰደባት። ደዴሳ አስተዋውቆኝ ከታሰርን ወዳጆቼ አንዱ ሲሆን ጦርነቱ ሲያበቃ አብረን ተፈታን።

ሶማሌ

በሀገሬ እንደማልቀየር እርግጠኛ ስለነበርኩ ስደትን መርጬያለሁ። ከእስር በኋላ ወደ ጅቡቲ ሄድኩ። ደስ አላለኝም። ወዳ ሀገሬ ተመልሼ ጥቂት ጊዚያትን አፋር ክልል ቆየሁ። ኑሮ ጥሩ መሰለ። ጓደኞች አፈራሁ። እንደውም ስጋ ቤትም ከፍቼ ነበር። ህይወት በአፋር እንዳጀማመሩ አልነበረም። ስቆይ ተቀየረ። ቢዝነሴ ጀምበር አዘቀዘቀባት። “በቃ ጠብ የሚልልኝ ሀገር ስለቅ ነው” አልኩኝ።

የጎደለኝ ነገር የሚሞላው ከአረብ ሀገራት መሀከል ባንዱ ብቻ ነው ብዬ ከ6 ጓደኞቼ ጋር ወደ መንግስት አልባዋ ሶማሊያ ጓዛችንን ጠቅልለን።

ለመሄድ ተሰናዳን። ለመቀየር ህንድ ውቅያኖስን መሻገር ግድ ነው። እሱን ለመሻገር ደግሞ ቦሳሶ ጥቂት መቆየት። ቦሳሶ ከተማዋ ብዙ ስደተኞች ያቀፈች ሲሆን ህንዳዊያን፣ አረቦች፣ ናይጄሪያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ታንዛኒያውያንና ኢትዮጲያዊያን በጋራ የሚኖርባት ነች። ሀገሪቷ ባላት ነገር ንፉግ አልነበረችም። ባላት የስራ እድል ባህር አቋርጠን አረብ ሀገራት እስክንሄድ ቀጥራና መግባ እንዲሁም አስተናግዳ አኑራናለች።

ባህሏንም ተገንዝቤያለሁ፣ ሲኖረኝ ገዝቼ ሳጣ አሳ አጥምጄ በልቻለሁ። ብዙ ዐይነት ሠውም ዐይቻለሁ። ኢትዮጲያዊያን ችግርን የመቋቋም አቅማችንን ዐይቻለሁ። ከገጠሙኝ ሠዎች የማልረሣው ግን አለ።

ኢትዮጲያዊው ሽማግሌ

ብዙ ዓመት ወደብ ላይ ሰርተዋል። የመርኩበ ካፒቴን ናቸው። በስራ ላይ ብዙ ከመቆየታቸው ብዛት ብዙ ቋንቋ ይናገራሉ። አረብኛ፣ ህንድኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ የሚናገሩት እኚህ ሠው አንድ ወቅት ቦሳሶ ሁለት ህንዳዊያን የተለያየ የህንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተጣልተው የሶማሌ ፖሊስ ቋንቋ ባለማወቁ ሊዳኝ ያልቻለውን ተጠርተው የሁለቱንም ቋንቋ በማወቃቸው ሁለቱንም አናግረው አስታርቀዋቸዋል።

ባህል

ሶማሊያ መንግስት አልባ ስትሆን ይህ የሰጣት ጥንካሬ አለ። ሕገ ወጥነት ሕግ በሆነባት ሀገር ማንኛውም ነገር ይቻላል። ኑሮ ፈታኝ ስለሆነ ሠው ስለሚያደርገው ነገር የሞራል ጥያቄ የለበትም። የአንድ ነገር ጥሩነቱ የሚገለፀው በልቶ እስካሳደረ ነው። ቢሆንም ህዝብ እንደደየ አካባቢው ሁኔታ ተገዥ የሚሆንበት ሕግ አለ። ውልና ወርሀዊ ክፍያ የሚባል ነገር የለም። የሠራኸው በቀኑ ታገኛለህ፣ ጭቅጭቅ ላይ ተገኝተህ ከዳኘህ ብር ለዳኘህበት ገንዘብ ብትጠይቅ ነውር አይደለም። ሻጭ መትረየስ ይዞ ሀሺሽ ወይም ጫት ሲሸጥ አይቻለሁ። ባለመትረየሱ ደንበኞቼን አናገርክብኝ ብሎ ፖሊስ ላይ ሲተኩስ አይቻለሁ። ይህን ሁሉ ግን ከመንግስት ማጣት እጁ ከክፋት የሚመነጭ አልነበረም።

ጉዞ ከቦሳሶ ወደ ኦማርየያዝኩትን ገንዘብ በሙሉ ጨርሼያለሁ። አብረውኝ የመጡ ወዳጆቼ ለመኖር አስፈላጊ ነው ያሉትን መላ አበጅተዋል። አንዱ ሱማሌ ሴት አግብቷል። አንዱ ደግሞ ሶማሌ ውስጥ ጠጅ ቤት ተቀጥሮ ይሰራል። ሌሎቹም የተለያየ ቦታ እዛው ቦሳሶ ለእለት ጉርስ የሚሆናቸውን ይሰራሉ። በመሀል አንዲት ሀሳብ መጣችልኝ የመን ለመድረስ የሚያስፈልገውን 70 ዶላር መክፈል ስለማልችል ተደብቄ ወደ ኦማር የሚሄደው መርከብ ውስጥ ገብቼ ለመጥፋት ሁኔታውን በደንብ አጠናሁ። መቼ እንደምትመጣ፣ ኦማር ለመድረስ ምን ያህል ይፈኛል? የሚለውን አጣራሁ። ሦስት ቀን እንደሚፈጅና የኢትዮጲያ በግና ፍየል ይዞ እንደሚሄድ ተነገረኝ። “የሀገሬ እንስሳት” ከኢትዮጵያ አምላክ ጋር ደብቀውኝ ኦማር እንደምገባ ተማመንኩ። ጀልባው ላይ ቀን ሠራተኛና አጋዥ መስዬ ከበጎቹ ጋር ተቀላቅዬ ገባሁ። ሞተር ውስጥ ተደበቅሁ። ይሄዳል ብዬ ያሰብኩት መርከብ 1 ተጨማሪ ቀን አደረ። ለጉዞ ይሆነኛል ብዬ የያዝኩትን ብስኩት ጨረስኩት። መርከቧ በማግስቱ ተንቀሳቀሰች። በጎች ውስጥ ተደበቅሁ። ጊዜው ሲመሽ ረሀብና የበጎቹ ተረፈ ምርት እንደማቅለሽለሽ አደረገኝ። ያንገበገበኝን የራብ ስሜት ካለሁበት ሞተር ክፍል ቅርብ ስለነበር ሼፉ ሲወጣ ጠብቄ ለመግባት አደባሁ። ግን ሼፉ ወጥቶ ለመግባት የሚፈጅበት ሴኮንዶች ሆነና እንቅፋት ሆንብኝ። ዝም ብዬ እንዳልገባ እያዛለሁ። ዝም እንዳልል ረሀብ የሚባል የሰው ልጆች ሁሉ ተፈጥሮአዊ ነገር አለ። ማድባቴን ተያይዥው ድንገት ሲወጣና እኔ ወደ ኪችኑ ስቃረብ ተመለሰ።

“ጂኒ ጁኒ” እያለ ሼፉ ጮኸ። ረሀቡ አናውዞኝ ስለነበር እምብዛም አልደነገጥኩም። ተዝለፍልፌ ከወደኩበት ያዙኝ። እንደምንም ፉድ (ምግብ) በእንግሊዝኛ ብዬ ሠጡኝ። ተንሰፍስፌ በላሁት። በልቼ እንደጨረስኩ ቀና ብዬ አይኋቸው። ህንዳዊ ካፕቴኑን ጨምሮ ብዙ ህንድና ጥቂት ፓኪታኖች ነበሩ። ለምን ወደ መርከቡ እንደገባሁ ጠየቁኝ። እንዳይከፉብኝ የተሻለ ሀሳብ ማቅረብ ነበረብኝና አንድ ነገር መጣልኝ። እኔን ሊገድሉኝ የሚፈልጉ ሶማሌዎችን ሽሽት ወደ ኦማን መምጣቴን፣ ውሸት ቢሆንም የተሻለ ነው። ሆኖም በእንግሊዝኛ ማስረዳት ችግር ሆነ። እነ ኖ፣ የስ፣ ያ እና ጉድ ሊያስረዱልኝ አልቻሉም። ለማስረዳት ወደ ሁለት ሰዓት ፈጅብኝ። ተረዱኝ ግን ወደ ኦማን አትመለስም ምክንያቱም ከተያዝክ የምንቀጣው እኛ ነን አሉኝ። ነገር ግን ፀባይ ካለህ ወደ ሶማለያ እንመልስሀለን አሉኝ። ተስማማሁ። ኦማር ሲደርሱ ወደ ባህር ገብቼ እንዳልጠፋ ነበር። እጅና እግሬን አስረው ወደ ታች 3 ደረጃ ወሰዱኝ። ድንገት እስራቴን ፈትቼ እንዳላመልጥ ደረጃዎችን በሙሉ ተመልሼ ስወጣቸው እንዲሰማቸው ሲረገጡ ድምጽ የሚያሰሙ ፕላስቲኮች አነጠፋባቸው። አጠገቤ ህፃን ጠባቂም አስቀመጡልኝ። ኦማር መግባት እንዳለብኝ ግን ለራሴ ነገርኩ። ጥቂት እያሰላሰልኩ አንድ ቆንጆ እድል ገጠመኝ። ጠባቂዬ ተኛ። ኪሴ የደበኩትን የጥፍር መቁረጫ ምላጭ አውጥቼ የእጄንና እግሬን ሰንሰለት በጠስኩ። የሚቀጥለው እርምጃ ሳይሰማኝ ደረጃውን እየረገጡ መውጣት ነው። መርከቧ እየሄደች ነው። ሠራተኞችም ስራ ላይ ናቸው። ጥቂት ደረጃዋችን እንደወጣሁ ልጁ ነቃ። ዐየኝ። አፈጠጠብኝ፣ ግን ተመልሶ ተኛ። ጥቂት እንደተራመድኩ ግን የረገጥኩት ፌስታል ተንጫጭቶ ጠባቂዬን መልሶ እንዳይተኛ አድርጎ ቀሰቀሰው። ጮኸ። ደረጃውን በሩጫ ስወጣ ተሰብስበው እንዳልወጣ ከበቡኝ። ያገኘሁትን ዱላ ይዤ የጀልባዋን ባለቤት መትቼ ላመልጥ ስል ተረባርበው ጣሉኝ። እየቀጠቀጡኝ sleeping bag የመሰለ አየር ብቻ የሚያስገባ ፕላስቲክ ውስጥ አስገብተው አሰሩኝ። እዛች ዕቃ ውስጥ ሆኜ ወንድሜን ህይወቴን እያሰብኩኝ አለቀስኩኝ። እንዲህ እያለ መርከቢቷ ኦማር ደርሳ መመለሷን ደመ ነፍሴ ነገረኝ። ምግብ ተናደውብኝ ስለነበር ስለክለውኛል። የሚገርመው ግን አንዱ ባንግላዲሽ ተደብቆ እየመጣ ይመግበኝ ነበር። ወደ ባህር ሊጥሉኝ እንደሚችሉ ደመ ነፍሴ ነገረኝ። ሀይለኛ ክርክርና ፀብ በመሀከላቸው ነበር። አንዱ ስላልተስማማ ህይወቴ ቢተርፍም ሲመለሱ እኔን መግደል ለሚፈልጉ ሶማሌዎች (እኔ በነገርኳቸው የተሳሳተ መረጃ) አሳልፈው እንደሚሰጡኝ ዝተውብኝ ይመለሱ ነበር። ቦሳሶ ስንደርስ “አንድ ወንጀል ሠርቶ ያመለጠ ሠው ይዘናል” ብለው ለሶማሊያ ፖሊሶች ሠጡኝ። ሶማሊያ ጠላት ስላልነበረኝ ፖሊሶቹ ወዲያው ፈቱኝ። ኦማር ባልገባም ህይወቴ ቀጠለች።

የፈነዳው ሞተር

ቦሳሶ ወደ የመን በምትሄደዋ ጀልባ ለመሳፈር የሚያስፈልገውን ገንዘብ እስክይዝ ቀን ስራ እየሰራሁ አሣለፍኩ። ቀኑ ደርሶ እርስ በርስ ተደራርበን እግራችንን ቀጥ ማድረግ በማያስችል ሁኔታ መፀዳዳት ከፈለጉ ባሉበት በሆነበት ሁኔታ ከሳፋ ከፍ በምትል ጀልባ ሁለት ናቸው። ጉዞ ጀመርን። መመሪያውን ማክበር የግድ ነው። ፈጣሪ ሲረዳኝ የጀልባዋ መሪ ዐይነ ውሃዬን ወደደው መሰለኝ ከጎኑ እንድቀመጥ አደረገ፣ እግርን ማንቀሣቀስና ወደ ፈለኩት መሆንን ነፃነት እንዳገኝ ቢረዳኝም በጉዞአችን መሀል ህንድ ውቅያኖስንና ቀይ ባህርን የሚከፍለውን መስመር ዐይተን ተገርመን ሳንጨርስ አንድ አስደንጋጭ ነገር ሆነ። ጉዳዩ አብሮን የነበረውን ጀልባ ቀድመንው ስለተጠፋፋን እርዳታ ልናገኝ በማንችልበት ሁኔታ፣ ከፊት፣ ከኋላ፣ ከግራና ከቀኝ ባህርና ሰማይ ገጥመው አለማቸውን ሲቀጩ ጀልባችን ከፍተኛ ፍንዳታ አሠማች፣ ደነገጥን፣ መሄድ እንደማትችል ተረዳን፣ ይሄኔ ነው “ይህን ያህል መስዋዕትነት መክፈሌ የሚገባኝን ህይወት ይሰጠኝ ይሆን?” ያልኩት ሁላችንም “አምላክ ሆይ ከወዴት አለህ?” ብለን አነባን። ድንገት ታዲያ ትልቅ ሀሳብ ያመነጨ ይመስል የጀልባዋ መሪ በሶማልኛ አብሮን ተሳፋሪ ለሆነው ለሶማሌው “አንድ ሀበሻ ይቀነስ” ሲል ተናገረ። ከመካከላችን አንዱ ኢትዮጵያዊ ታዲያ ነገሩን ሠምቶ ነገረን፤ በአጭሩ አንድም ሠው እንዳይነካ ከነካ ጀልባዋን ለመገልበጥ ሁላችንም እንነሣ ተባባልን፤ እሱም ተወው። የመን ለመድረስ 3 ቀን ይቀረናል። እንኳን እኛ መሪያችንም ተክዞ ባለበት ቅፅበት አብራን ተጉዛ ወደ ኋላ የቀረችው ጀልባ ከሩቅ ታየችን፣ ፌሽታ ተጀመረ፣ ቀረበችን፣ ዳሰስናት ገመድ እኛ ጀልባ ላይ አስረው 3 ቀን እየጎተቱ የመን ባህር ዳርቻ አደረሱን።

የየመን ፖሊሶች ድንጋጤ

በጀልባዋ ያመጡን ደላሎች የየመን ፖሊሶች እንዳያገኟቸው በዱላ እየቀጠቀጡ አስወረዱን። በረሀብ የደከመ፣ 4 ቀን ሙሉ ታጥፎ የነበረ እግር የዛለ ሠውነት ውሃው ዳርቻ ላይ ተሳሰርን፣ ከሁላችንም ዘና ያልኩት እኔ ነበርኩ። ምክንያቱ ደግሞ ቅድም እንደነገርኩህ እግሬን ጀልባዋ ውስጥ እግሬን ወደፈለኩት እንዳደርግ መሪው አጠገቡ እንድቀመጥ ስለፈቀደልኝ ነበር። የሚገርመው ከውሃው ወጥተን ወደ ኤደንና ሰንዐ ለመሄድ ማረፊያ ቦታ ስንፈልግ ጥቂት የመኖች ወዳለንበት ሲገሰግሱ ዐየን፣ አስበው በዛ ጥማትና ረሀብ ድካም መታሰር ስለሌለብን ወደ ማናውቀው በረርን። ምንም ሳንቆይ ደረሱብን። ወደ አንድ ቦታ እየመሩ ወሰዱን። ፊታቸው የተኮሳተረና ጭፍግግ ያለ ስለሆነ እድላችንን አማረርን። ቦታው ላይ ደረስንና ገላችሁን ታጠቡ አሉን። ታጠብን። ምግብ እስክንጠግብ፣ ውሃ እስክነረካ፣ ፖሊሶች ብለን ያሰብናቸው ለካ የአከባቢው አርሶ አደሮች ናቸው፤ መርቀውን መንገድ ድረስ ሸኝተውናል። እኔም መዳረሻዬን ሰንዐ አድርጌ የስደትን ጥዑም ዜማ ከየመኒዎች ጋር አጣጥሜያለሁ።

ስንብት

የመን ያለፍኩባቸውን መንገዶችና መስዋእትነቶችን ባትመጥንም ቆንጆ ጊዜ አሳልፌያለሁ፣ ህዝቦቿ ካየኋቸው ህዝቦች በሙሉ የሚከበር ባህልና ደግነት እንዳላቸው ተረድቻለሁ። የትኛውም ስደት የራሱ በጎ የሆነም ያልሆንም ቢኖረውም የኛ ኢትዮጵያውያን ከስደት መልስ ተረክ እንከኑን እያጠፉ መዐዛውን መቆስቆስ ነው። እኔ ግን መናገር ምፈልገው የበዛውን እንከን እንቅጭ እንቅጩን ነው።” ብሎኝ ወጉን ጨረሰ።

ሲጨርስ በወጋችን መሀል የበጠበጡንን የካርታ ወዳጆቹን ስልክ አነሣ።

“ሀቢቢ መጣለሁ” ብሎ ተሠናበተኝ። “እንኳን አወቅሁህ። እንኳን ከዛ በኋላ የምት ጥሪ አመለጥክ። ለሀገርህ እንኳን አበቃህ” ብዬ ወጌን ደመደምኩ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top