ታዛ ወግ

ሰማይን ለመንካት መሞከር

በየዓመቱ አንድ የሆነ በዓል ሲደርስ አንድ የሚነገር ተረት አለ። አንዳንድ ግዜ “ታሪክ ሲቆይ ተረት ይሆንብሃል” ይባላል። “ተረት” ሲባል ነገሩ እውነት ለመሆኑ ማስረጃ የሌለው ወይም በእውን ለመፈጸሙ በትክክል ለማረጋገጥ የማይችል ቢሆንም እንደተደረገ ሆኖ የሚነገር በፈጠራ የተቀነባበረ ታሪክ መኖሩንም ልብ ይሏል።

እናም ይህ በየዓመቱ የሚነገረው ተረት እንዲያው “ተረት” ተባለ እንጂ “ሊደረግ የማይችል ነው” ብሎ መገመት የሚያዳግት ነው። ነገሩም እንዲህ ነው፡-

በአንድ ገጠር ነክ ቦታ ሰዎች ዓመት በዓል ደርሶ ለቅርጫ የሚሆን ሰንጋ ለመግዛት ገበያ ይወጣሉ። ገበያውን ሲቃኙ ውለው ተስፋ የመቁረጥ ድርበብ ላይ ሲደርሱ አንድ ሸበቶ ሰው ማለፊያ ሰንጋ ይዘው ያዩና ይጠይቃሉ። እኒያ አረጋዊም መሸጣቸውን ሰዎቹ በውል ካረጋገጡ በኋላና ዋጋውም እንደ ነገሩ “ሻል ያለ” ስለነበር ገንዘቡን አውጥተው ከመክፈላቸው በፊት ስለ ከብቱ “ማለፊያነት” አጥብቀው ይጠይቋቸዋል።

መቼም ሻጭ የንብረቱን ጥራት እንጂ የዕቃውን ክፋት ተናግሮ አያውቅምና የዚያን “ቅልብ” ያሉትን ሰንጋ ታሪክ አውርተው ሲጨርሱ እንደገና ለማረጋገጥ ገዥዎቹ በድጋሜ አጠንክረው ይጠይቋቸዋል። እርሳቸውም ሳቅ ብለው “እንግዲህ ወገኖቼ እኔን ዐይታችሁ ማየት ነው” ይሉና ይመልሱላቸዋል። ከሽማግሌ አፍ ውሸት አይወጣም ይባላልና ቃላቸው ልዩ ትርጓሜ ያዘለ መሆኑን መጠርጠር አላሻም።

በዚያ ወቅት ገዥዎቹ በአረጋዊው ቃል ላይ ሙሉ እምነታቸውን ጥለው፣ ብራቸውን ከፍለው ሰንጋውን አስነድተው ይሄዳሉ። ዳሩ ግን ያ እንዲያ አዛውንቱ የበሬ ሻጭ ምለው የተገዘቱበት ሰንጋ እንደተባለው ሳይሆን ቀረና አሳዘነ። ሰንጋው ሲታረድ ብልቱ ሲወራረድና ተቀራማጮቹም በጉጉት ሆነው፣ ዙሪያውን ከበው “ጥብስ” ቢሉት ወዴት? “ቅቅል” ቢሉት ወዴት? ያ በቁመናው ያማረ ሰንጋ እንዲያው “ዛላው ደኅኔ” የተባለ ሆኖ ብቻ ዐረፈው። ሥጋው እንደ አጥንቱ የሰው ጥርስ የማይደፍረው ሆነና ገዥዎችን አሳፈረ፣ ባለ ቅርጫዎችን ለቁጣ አደፋፈረ።

በዚህም ምክንያት ለግዥ የተወከሉት “የኮሚቴ አባላት” የሻጩን ሰው ቤት እንደ ምንም ብለው ሲያፈላልጉ ሰንብተው አገኙና እንደ መርዶ ነጋሪ ማለዳ ከቤት ሳይወጡ ይደርሱባቸዋል። ሽማግሌውም እንግዶቹን ቀድመው ያዩዋቸው ቢሆንም ዘነጉና የመጡበትን ምክንያት ይጠይቋቸዋል። እነርሱም የሆነውን ነገር ሁሉ በማዘን ይተርኩላቸዋል።

ይኸንን በጽሞና ያዳመጡት ሸበቶ አዛውንትም “አዬ… የእናንተ ነገር! ታዲያ እኔ ምን አጠፋሁ? አጥብቃችሁ ስለ ከብቱ ብትጠይቁኝ ሳቅ ብዬ እኔን ዐይታችሁ ማየት ነው አላልኳችሁምን?” አሉና መልስ አሳጥተው በገቡበት እግራቸው እንዲወጡ አደረጓቸው ይባላል።

ሽማግሌው “ሳቅ” ብለው ሲናገሩ የሚታይ ገጽታ ነበርና!! ጥርሳቸው አልቆ በድዳቸው የሚስቁ መሆናቸውን የበሬው ገዥዎች ሳያስተውሉ ቀርተው ኖሮ ለዚህ ምንም ምላሽ አላገኙም። ያ በሬም በጉፋያነት ጥርሱ ያለቀ መሆኑን ከጠዋቱ ነግረዋቸዋል። እነሱ በወቅቱ ልብ አላሉም ነበር እንጂ!! መቼም ሥጋ የወደደ ነፍሱን እረስቶ፣ ቁም ነገርን ሁሉ ትቶ ይገኛልና በወቅቱ የተነገራቸውን ጨርሶ አላስተዋሉትም ነበር።

የዚህ “የቅርጫ ኮሚቴ” ነገር ሲነሣ ዘወትር ያን የጥንቱን የጉፋያ ታሪክ ከግዥው አደራ ጋር አባሪ ሳያደርግ የሚቀር ሰው አለመኖሩ በወቅቱ ዛሬም ሲወራ ይኖራል። ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት የቅርጫ ነገር እንዴት ነው? በታሪክ መዘክርነት ብቻ እንዳልቀረ እናውቃለን። ብዙ ጊዜ የሚደንቀው ግን ዓመታዊ በዓል በመጣ ቁጥር ሁሉ የሥጋ ዓይነት፣ ሁሉም የእርድ ከብት በዓይነት በዓይነቱ ወጡም፣ ቅቅሉም፣ ጥብሱም፣ ክትፎውም፣ ቁርጡም፣ ዝልዝሉም በአንድ ገበታ በአንድ ቀን እንዲቀርብ፣ ድህነትም በአንድ ጀምበር፣ በአንድ ብቸኛ ጥሪ ወደ ጎጆ ዘልቆ እንዲሰበሰብ የመታደሙ ጉዳይ ነው። “ሁልህም በአንድ ፀሐይ እንድታርድ፣ ብልት እንድታወራርድ” ተብሎ “ከበላይ አካል” የታዘዘ ይመስል እንዲያው ትንሹም ትልቁም ተፎካክሮ ጣሪያ ሊነካ ይደርሳል።

ይህንንም ሁልጊዜ በየወቅቱ የምናየው እንጂ እንዲያው “አልፎ አልፎ” የሚባል እንኳ አለመሆኑን በየጊዜው በምናሳልፈው በዓል በማየት በሚገባ ስለምናረጋግጥ “ማስተባበል የሚደፍር ይኖራል” የሚል ግምት አለ ብሎ ማሰብና መጮህ እሪ በከንቱን መሆን ነው።

የዘንድሮን የፋሲካ ዶሮ ዋጋ የተመለከተ ሰውማ “ዶሮ” እስከመሆኗም ይጠራጠራል። ሆኖም አንድ ቤተሰብ “አነሰ” ቢባል ዶሮ ማረዱ አይቀርምና ገዝቶ ሲሄድ ተስተውሏል። ከዚያ ባለፈ ደግሞ ኮረጆው በመጠኑ ዳጎስ ያለ ሰው በግ አርዷል። ዶሮና በጉ መታረዱ ሳይቀር ለቁርጥ ተብሎ ደግሞ ብልት ሥጋ የሚገዛ እንዳልጠፋ ሉካንዳዎቹ በምስክርነት ይቆጠራሉ። ለነገሩ ጉዳዩ በዚህ ብቻ ቢያበቃ እንኳ መቼም እንደ ነገሩ “ዕንዳላዩ ማለፍ” ይመረጥ ነበር። ግና መቼ በዚህ ብቻ ያልቅና!!

ዶሮ ታርዶ፣ በጉም ተጨምሮ፣ የቁርጥ ሥጋውም ገበያ ተደምሮ ሌላ የሚታከልበትም አለመጥፋቱ “የውድድሩን ግሩምነት” ይፋ አድርጎታል። “የቱ” ቢባል “የቅርጫው ማኅበረተኝነት” የተሰኘው ምላሽ ይሆናል። አንዳንዶቻችንን የሚገርመን የሰዉ ወሬ ነው። በአንድ በኩል የኑሮ ውድነትን እያነሡ ማማረር፣ በሌላ በኩል ልክ አለፍ ሆኖ መቀናጣት! በኋላ ደግሞ የለቅሶ ጥሩንባ መንፋት! ይኸ አሁን ምን መልክ ሊሰጠው ይችላል?

ለመሆኑ አንድ ሰው ይኸን ያህል፣ ጥንት አበው እንደሚሉት እንዲህ “ለሥጋው መሞቱ” ለምን ይሆን? የዛሬን ብቻ በልቶ የነገውን ረስቶ መታየቱ ምን ሊባልስ ይችላል? እኔን በግል የሚያውቀኝ አሁን ከበርካታ ዓመታት ጀምሮ ሥጋ ጠል፣ ቅጠል በል ነኝና ምላሹን ለሥጋ ሰዎች እተወዋለሁ።

ለሀገራችን ሰው ነገርን አቆርፍዶ ከመመለስ እንደ ማለፊያ ወጥ በመከለሻ ቅመም አዋዝቶ ማለስለስ የኢትዮጵያዊነት ልዩ ባሕርይ መሆኑ ይታወቃልና ከጥንት ጀምሮ “የቅቤ ነጋዴ ሁሌ ድርቅ ያወራል” ሲባል ይሰማል።

እናም ለዚህ ሳይሆን የቀረ አልመሰለም የዘንድሮ ቅቤ “ሰው አይቀምሴ” ሊባል ዳር ዳር ያለው። ባለፈው አንድ ሰሞን በአንዳንድ ሥፍራዎች ሊከሰት ስለሚችል የዝናብ ወቅትን አለመጠበቅ ወይም ጥቂት እጥረት እንደተነገረ አልያም ከመጠኑ በላይ የመዝነብ ሁኔታ መከሰቱ ይታወሳልና የቅቤ ነጋዴም ይህችን “ማለፊያ ዜና” የፋሲካ ስንቅ ሳያደርጋት የቀረ አይመስልም። ወረደም ወጣ የቅቤው ዋጋ ንሮ የተስተዋለበት የፋሲካ ገበያ መሆኑን ለግዥ የወጡ ሁሉ ሲናገሩት ተሰምቷል።

እንዲያው “ድርቅና የቅቤ ነጋዴ” የተሳሰሩበትን ሐረገ ተዛምዶ ጠቀስኩ እንጂ የዶሮውም፣ የበጉም የልኳንዳ ብልት ሥጋውም ሆነ ሌላው ቀርቶ የቅርምቱ ሰንጋ የነፍስ ወከፍ ተቀራማች ሒሳብ ንረት እንዲህ በቀላሉ የሚወጋ አልመሰለም። በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ሥጋ የረከሰ ይመስል ሰው “ቆጠብ” እንዲል ሲመክሩ ተደምጠዋል። በርግጥ ሥጋ ተወደደ ወይም ረከሰ በማለት ምክራቸውን ይተው አልልም። ነገሩ ጥቂት ገርሞኝ እንጂ!

ምሁራን የምግብ ዓይነትን ሰዎች በሚመርጡበት፣ ገንቢውን ከአፍራሽ መባልዕት ለይተው በሚያውቁበት ረገድ ተገቢ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ ምክራቸውን በሚገባ ሲለግሱም ይስተዋላሉ። ምክሩን ያደመጠ ግን ስንት ይሆን? ሰዎች በአንድ ወገን የዋጋ ንረትን እያማረሩ ያወራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃራኒውን ይሠራሉ። ያው እንደተባለው ነው።

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሊቪዥን ብሮድካስት በቴሌቭዥንም ዘወትር ሳያቋርጥ በሚያስተላልፈው ግሩም ፕሮግራም በአንድ ወቅት በበዓለ ትንሣኤ ዋዜማ እንግዳ ያደረጋቸው አቶ ተመስገን ዐወቀ የተባሉ የምግብ ሳይንስና የአመጋገብ ሥርዓት ተመራማሪ ትዝ ይሉኛል። ለምሁሩ ምስጋና ይድረሳቸውን ከዚህ ጋር በተዛመደ መልክ ሰው አበላሉንም ሆነ አጠጣጡን ከጤናው አኳያ እየመዘነ፣ በጤናው ልክ እየመጠነ ማድረግ እንደሚገባው ሲመክሩ ተደምጠዋል። አትክልትና ፍራፍሬ እንዳይለየው ሲነግሩ ተሰምተዋል፣ ታይተዋልም። በርግጥ አትክልቱም ሆነ ፍራፍሬው ከሌላው ወጭ ተርፎ በሚገኝ ገንዘብ ስላለበትና ያ “ትራፊ” ሊባል የሚበቃ ገንዘብም ስለማይኖር እስከነ ግዥውም መደረጉ ያጠራጥራል። ሆኖም ያም ቢሆን ሰው ተጣድፎ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ሲገሰግስ አይስተዋልም። የምሁሩ ምክር በተለገሰ ገና አንድ ሙሉ ቀን እንኳ ሳይሆነው ወዲያው ተረስቶ፣ ሰውም ዕድሜ ልክ ሥጋ በልቶ እንደማያውቅ በየገበያው ተጋፍቶ፣ ሲለውም የበለጠ በመክፈል ከገበያተኛ ተጫርቶ፣ የኮሮና ቫይረስ ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያ ሁሉ ተረስቶ አንዱ በአንዱ ላይ ሲራኮትም፣ ሲራቆትም ታይቷል።

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ከመጠን በላይ በየመደብሩ እየገባ፣ በልቶ ብቻም ሳይሆን ከተገቢው በላይ ጠጥቶ የሚናገረው ቋንቋ ጠፍቶት አንዳንዱም ከትዳር ጓደኛው ጋር አፈ ጭቃ ሆኖ ሲሳቅበት የዋለበት ሁኔታ ነበር። ይህ እጅግ የሚያሳዝን ሆኖ እያለ አንዳንድ “ሠለጠንኩ” ባይ ደግሞ ከባለቤቱ ሌላ ልጆቹንም እየጎተተ በየመጠጥ ግሮሰሪ ለስካር ምስክርነት አቁሞ ውሎ ከሚስቱ ጋር ከጠጣ በኋላ ሁለቱ እየተጓተቱ የነበረበት ሁኔታ አለ። የወለዷቸው ልጆች እነርሱ ሲያድጉ ደግሞ በተራቸው አባትና እናታቸውን እየጎተቱ ሲወጡ የመታየታቸው ሁኔታ ሲታሰብ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ትዕይንት ሊሆን የሚበቃ ይመስላል።

እናስ ይህን በማድረግ ወዴት እያመራን ነው? ይህ ሥልጣኔ ወይስ ዘመናዊ ጅልነት? በመሠረቱ “ሥልጣኔ” ብለን እንዳንጠራው ባሕር ማዶው እጅግ ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት በሚከበረው ሃይማኖታዊ በዓላት በፈረንጆቹ “Easter, X-mas New Year” ማለትም “በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ልደት፣ እንቁጣጣሽ” በተሰኙት ቀናት ለመሐላ እንኳ አንድ ሰው በጎዳናው አይታይም። ንግድ የያዙ አመዛኙ (በሙሉ ማለት ይችላል) ባለመደብሮች ለሥራ አይወጡም መደብሮቻቸውም ዝግ ናቸው። ሁሉም በቤተሰብ የሚያከብራቸው የተከበሩ ዐውደ ዓመታት ናቸውና! በኢትዮጵያም ገና እና ፋሲካ፣ እንዲሁ የተከበሩ በዓላት ናቸውና ቤተሰባዊ የባህል ሁኔታቸው የታወቀ ሆኖ ሳለ ዛሬ ዛሬ ግን እንዲሁ በየመሸታ ቤቱ ሲዘፈንባቸው መታየቱን ስንመለከት “ለመሆኑ ባህላችን ወዴት ቀረ?” ሊያሰኘን እና ሊያጠያይቀን የሚበቃ ነው።

አንዳንድ ሰዎች ግን በዚህ ረገድ የሚደረገውን ተቃራኒ ተግባር “ሥልጣኔ ነው” ብለው ሲሟገቱ ሰምቻለሁ። እኔ የዚህ የአሁኑን አንዳንድ አረማመድ ስመለከት ግን “ሥልጣኔ” ነው ብሎ በዚያ በከበረ ሥያሜ ለመጥራት ይቸግረኛል። ምክንያቱም “ሥልጣኔ” ሲባል “እድገት፣ ዘመናዊነት፣ ከፍተኛ የዕውቀት ወይም የመሻሻል ደረጃ…” ማለት ነውና!! እናስ መጠጣት፣ መስከር፣ ከዐቅም ዘለል ለመኖር መሞከር፣ መልካም ባህልን ሽሮ በአጸያፊ ባህል ለመተካት መጣር ምን ሊባል ይችላል? ዘመናዊ… ምን? እስቲ አንባቢ ነገሩን መርምሮ ምላሹን ይስጥበት። እኔ በበኩሌ አመዛኙ ነገራችን ከዐቅም በላይ ለመኖር መጣጣር እንጂ ሌላ አይመስለኝም። ይህ ደግሞ ሰማይ ለመንካት መሞከር መስሎ ይታያል። ከንቱ ድካም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top